የቃልቋንጣ (የወግ ገበታ)


እንኳን ደህና መጡልኝ

የቃልቋንጣ
„የሞቱ ዝንቦች የተቀመመውን የዘይት ሽቱ ያገሙታል፤
እንዲሁም ትንሽ ስንፍና ጥበብን ክብርን ያጠፋል።“
መጽሐፈ መክብብ ምዕራፍ ፲ ቁጥር ፩
ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
10.05.2019
ከእመ ዝምታ ሲዊዘርላንድ።
የወግ ገባታ።
ከሥርጉተ© ሥላሴ
(Sergute© Selassie)


የአላዛሯ ኢትዮጵያ ራህቧ እውነት ብቻ ነው።




  • ·         ቅድም


·         ድምጽ።
·          
የቃልቋንጣ (10 05 2019)


·         ፍታ።

እንደምን ናችሁ የኔዎቹ ቅኔዎቹ? ደህና ናችሁ ወይ? የንጉሦች ንጉሥ አጤ ቴወድሮስ የሚታወቁበት ሥነ - ቃል „ቃል የዕምነት ዕዳ ነው“ የሚለው ዘመን ተሻጋሪ ፍልስፍናቸው ነው።

ለነገሩ ጠ/ሚር አብይ አህመድም በአብዛኛው ሰው ልብ ሊመሰጠሩ የቻሉበት „ቃል ይተክላል፤ ቃል ይነቅላል፤ ኢትዮጵያም የተተከለችውም፤ የተነቀለችውም በቃል ነው“ ያሉት ሁላችንም ልባችን የሸለምንበት አምደ ጉዳይ ነበር። ምን ያህል በቃላቸው ውስጥ እንዳሉ ህዝብ መስታውቱ ስላለው የህዝብ ህሊና ይዳኘው።

መይሳው ካሳ አጤ ቴወድሮስ ግን በቃላቸው ውስጥ ሰክነው፤ ቃላቸውን ቋንጣ ሳያደርጉ፤ ቃላቸውን ሳያጠንዝሉ፤ ቃላቸውን ፍርሃትን ሳይቀልቡ ለውጭ አገር ጠላት እጄን አሳልፌ አልሰጥም፤ ትውልዱንም ዕድሜ ልኩን በቅኝ መንፈስ አንገት አላስደፋም ሲሉ ጀግናውን ገብርዬን ተከትለው የድል ጽዋውን እንደ ቃላቸው አጬጌውታል።


·         ሪና ቃሉ።

መሪ ማለት ቃሉ እንደ ቃለ ህይወት የሆነ ማለት ነው። የመሪ ቃል ህልው የሆነ ማለት ነው። የመሪ ቃል ለማውጫነት በዘመን ሁሉ የጸደቀ ልሳነ - ህዝብ፤ አንደበተ ህሊና ማለት ነው።

ቃሉ ራሱ መሪ ለመሆን የተቻለው ማለትም ነው፤ የመሪ ቃሉ የተስፋ ፖሊሲ መሆን ይገባዋል። ቃል ከመውጣቱ በፊት በጥንቃቄ፤ በአትኩሮት ከህሊና ጋር ሊመከርበት ይገባል። በመደዴ የመሪ ቃል አይለቀቀም። ልጓም ይሻል።

ቃል የህሊና የተደሞ ውጤት የመሆኑን ያህል ቃሉ ተደሞን አክብሮ፤ እርጋትን አንግሦሶ ባይነትን ተጠይፎ መውጣት አለበት።


የመሪ ቃል በዬፌርማታው መንጠባጠብ አይኖርበትም። የመሪ ቃል እብድ የዘራው እዝመራም መሆን የለበትም።


የመሪ ቃል በዬፌርማታው የኦርኬሰተር ማድመቂያ፤ የጭብጫ ማውጫ መሆን የለበትም። የመሪ ቃል የሀተታ ማዛጊያ ሊሆን አይገባም።


የመሪ ቃል የአውጫጭኝ ማህበርተኛ አይደለም። ቃሉ ሲወጣ መን ከዘመን ቢቀያዬር፤ ዘመን ከዘመን ቢፈራረቅ፤ ዘመን ከዘመን ቢወራረስ ቃሉ እራሱን የመጠበቅ፤ እራሱን የመከላከል አቅም ሊኖረው ይገባል። ቃሉ በዬዘመኑ ሙት መሬት ላይ ሳይሆን ገዢ መሬት እርስቱ ሊሆን ይገባል።


የአንድ ምራቁን የዋጠ፤ ደልዳላና ስኩን ጨዋ መሪ ቃሉ ድልድይ ነው፤ ዘመን ከዘመን የሚያገናኝ ሊንክ ነው። የመሪ ቃል የኔት ልሳኑ ዕውነት እና ዝልቅት፤ ዝልቀት እና ጽናት፤ ጽናት እና ውህደት መሆን ይገባዋል።

የመሪ ቃል ወፍ ዘራሽ መሆን አይገባውም። የመሪ ቃል ሙጃ መሆንም አይገባውም። የመሪ ቃል ጉርፍም ሊሆን አይገባም። የመሪ ቃል የወጀብ ግብር ገባሪ ሊሆንም አይገባም። የመሪ ቃል በራሱ ውስጥ የፈለቀ፤ ራሱን በእውነት ያጸደቀ፤ የበቃ የጽናት አንጓ ወይንም ዕዕማደ ሚስጢር ሊሆን ይገባዋል።

መሪ ከሌላው ከተርታው ሰው ልዩ ሆኖ ስለመፈጠሩ ገላጩ መሪው ውስጥ የሚፈልቁት ቃሎች ሁልጊዜም ቃናቸው፤ ለዛቸውወዛቸውላሂያቸው እሸት ሁኖ የሚዘልቅ፤ የሚያዘልቅ መሆን ይኖርበታል። ካለ እድሜያቸው የማያንቀላፉ፤ ካለ ዕድሜያቸው የማይገረጅፉ፤ ካለ ዕድሜያቸው የማይዝሉ፤ የማይሞቱም።

መሪ ቦታ ሲቀይር፤ መሪ ዕድሜው ሲሸሸው፤ መሪ ዕድሉ ሲበራ፤ ወይንም መሪው ዕድሉ ሲጠፋ ቃሉ አብሮ ብልጭ ድርግም የማይል፤ ቋሚ አምክንዮን የሙጥኝ የሚል፤ ጠበቃ የማያስፈልገው፤ አቃቢ ህግ የማያሰኘው ችሎት፤ ሰበር ችሎት የማያርደው ወይንም የማያሸማቀው ደፋር ሊሆን ይገባል። 

የመሪ ቃል ሙት መሬትን የሙጥኝ የማይል ቀናት፤ ሰዓታት፤ ወራት ወቅታት ቢፈራረቁም ምች የማይመታው፤ ለገርፍታ የማይጋለጥ፤ ለቁርጠት፤ ልፍልጠት እጁን የማይሰጥ፤ ትውልድን ከብክነት የመታደግ የኪዳን ብሩሕ ቀለበት ሊሆን ይገባዋል።

የመሪ ቃል እንደ አዬሩ ጠባይ ዘመንበል ቀና የማይል፤ ፈረሰኛ ውሃ ሙላት የማያንገራጅጀው፤ ጦሮ የማይንጠው፤ የመሬት መራድ የማይተረትረው፤ ዶፍ የማያስበረግገው የእውነት ፍሬዘር መሆን ይገባዋል የመሪ ቃል።
የመሪ ቃል ጭብጨባ፤ አጀብ፤ ሞቅታ፤ ለብታ፤ ቀታ ወይንም ጉማም የአዬር ጠባይ የማያውከው በተነሳበት ልክ የሙቀቱን ልኩን፤ ሚዛኑን ጠብቆ እንደ ንጹህ አዬር የህልውና መተንፈሻ ቧንቧ ሊሆን ይገባል።

የመሪ ቃል በስንጥቅ፤ በትርትር፤ በብልት፤ በውብዬት፤ በዝገት ተከዝኖ አዲስ ሁኔታን ባዬ ቁጥር ያን ሳሳ፤ ለዛም እዬጎመጀ የሚሳሳ፤ የሚያባዘት፤ የሚዳምጥ ሊሆን አይገባም።

አድሮ የማይገኝ ቃል ለመሪ መሪነቱ በሰብዕናው አለመፈጠሩን የሚገልጥ ማህተሙ ነው። ስለዚህም ከትውልድ ብክነት በፊት እራሱን በአቅሙ ልክ ለክቶ ከብዙ ወጣ ገብ፤ ከበርካታ ዝብርቅርቅ፤ ከእልቀተ ቢስ ኩፈሳ ራሱን ማግለልም አንድ የመሪነት ሥጦታ ነው።

መሪነት ቅብዕው በአዎንታዊ ከሆነ፤ ቅባዕው ቁርኝቱ እውነት ብቻ ነው። ሃቅን አይፈራም እሱም ሃቅ ነውና። ፋክትን አይፈራም እሱም ፋክት ነው፤ እውነት አይርደውም እሱም የእውነት ደፋር ጀግና ነው።

ለእውነት ደፋርነት የመሪነት መለያ ባህሪ ሲሆን መሪ እውነትን ፈርቶ እውነትን በደለዘ፤ እውነትን በቀደደ፤ እውነት በፈለጠ፤ እውነትን በሾከሾከ፤ እውነት በለነቀጠ፤ እውነትን በሰቀለ ቁጡር የቃልቋንጣ አምራች ፋፍሪካ ይሆናል። ቃል በእውነት ውስጥ እንጂ በእብለት የመብቀል፤ የመጽደቅ፤ የመስበል ተፈጥሮ ስሌለው።

አላዛሯ ኢትዮጵያ የራባት ይኸው ነው … ራህብተኛ ናት እናቴ፤እምቤቴ፤ ልዕልቴ ኢትዮጵያ … ራህቡ አንጀቷን ቦርቡሯታል፤ ራህቡ ሁለመናዋን ጎርጉታል፤ ራህቧ መዳረሻው የትውልድ ብክነት ስለመሆኑ ትረዳለች። እናት ሊኳንዳ ቤት የተከፈተባት በሰው ነው። ልጅ ታመርታለች በማይጸና ቃል ይታጨዳል፤ በወለም ዘለም ዝንፈት ትውልድ ዘመን ከዘመን ይባክናል፤ በራሱ ውስጥ መስከን በተሰናው ዝልብ ሰብዕና ትውልድ ያለመባራት ይከስላል፤

የቃል እራህብተኛዋ እምዬ ያሰኛት፤ ሽው እንዲያው ሽው፤ ትዝ እንዲያው ትዝ ያላት የቃልቋንጣ ሳይሆን የቃል ኪዳን የቀራንዮ ጽናት እና ውል ብቻ ነው። ቋሚ ውል ለእናት አገር መስጠት እንደ አዬሩ ጠባይ መሆን አይገባውም። አክተሩ ይኖራል አምሮበት ነግሦ ተዋናዩ አመድ ይሆናል።

አክተሩ እንደ ሁኔታው አክሮባት በሰራ ቁጥር እናት ደግሞ ለአዲስ የሰው ብርንዶ፤ ለአዲስ የሰው እርድ አሳድጋ ለዝንኞች ታሰረክባለች።

አክተሩ ሁልጊዜ ቃሉን እያሰገረ በሰከረ ቁጥር ቦታ ይቀያይራል። ልክ እንደ ቄብ ዶሮ … ሰው በአንድ ቀን አይመረትም። የሰው ልጅ የሂደት ውጤት ነው። የራሱ ቤተሰብ የ አክተሩ ማለቴ ነው አንዳችም ሰቆቃ አይደርስበትም፤ የመሞከሪያ ጣቢያው የአንጋቹ ዕዳ ብቻ ነው።
·         ዬት።

ጋዜጠኛ፤ የሥነ ጥበብ ቤተኛ፤ የሰብዕዊ መብት ተሟጓች፤ የሃይማኖት መሪ እና ማህበረ ምዕምኑ እውነት የዕለት ዕለት የህልውናቸው ፖሊሲያቸው ሊሆን ይገባል። አድሮ በማይገኝ ጥቅል ዕብለት ማህበርተኝነት ጊዜ ባዝረከረከው ቁጥር ከመንበር አውርዶ ይፈጠፍጣል። ቆጥ እንኳን አይፈቅድም የእውነት ተፈጥሮ ለአባዩ ነፍስ።

ጋዜጠኛ ይሁን የሥነ - ጥበብ ሰው፤ የሥነ - ጥበብ ሰው ይሁን አማኝ ነኝ፤ ሃይማኖት አለኝ የሚል ሰብዕና ከግለሰብ ዝና፤ ከግለሰብ የኢጎ ቁልል ይልቅ ዋቢ፤ ጠበቃ፤ ሁነኛ መስመሩ ሊሆን የሚገባው የእውነት ተፈጥሮ ሊሆን ይገባል። እውነትን የፈጠረው የሰማይ እና የምድር ንጉስ እዬሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው።

የሰው ልጅ ለራሴ ታማኝ ነኝ ካለ መጀመሪያ የተፈጠረብትን ሚሰጢር ማወቅ ይገባዋል። የሰው ልጅ የመፈጠሩ እዮራዊ ሚስጢር የባለዝናዎችን ኢጎ ሊከምር ሳይሆን ፈጣሪ ቀድሶ እና አንጽንቶ ለፈጠረው እውነት ብቻ ጥብቅና እንዲቆም ነው። የእውነት አራት ዓይናማ ወታደር እንዲሆን።

እውነትን በወገኑ ቁጥር ፈተናውምማዕበሉምመገለሉምጫናውም፤ ጭቆናውም  ሊያል ሊበረታ ይቻላል። ግን እውነትን የተጠጋ ነፍስ ሲፈጠር ነው አሸናፊ የሚሆነውና አሸናፊነት ፈቅዶ መኖር ራሱ አሸናፊነት ነው። እውነትን የሸሸ ደግሞ ሲፈጠር ነው ሰውነቱ የሚሸሸው፤

ሸሽትን የፈቀደ ደግሞ በራሱ ውስጥም ተሰዶ ነው የሚኖረው።  ልድገመው ሸሽትን የፈቀደ ደግሞ በራሱ ውስጥም ተሰዶ ነው የሚኖረው። ምን ያህል ዘመን ስለ ግለሰቦች የኢጎ ቁልል ሲባል ጋዜጠኞች፤ የሥነ -ጥበብ ሰዎች፤ የሃማኖት አማኝያን በራሳቸው ውስጥ ተሰደው እንደኖሩ ዘመኑን መቁጠር ነው።

እንደ እኛ ስደት ላይ የሚኖሩ ከሆኑ ደግሞ ሁለተኛውን ስደት ፈቅዶ በመኖር ህሊናን በስጦታ ለሌላ ሰው በገጸ በረክትነት ማበርከት ይሆናል። ህሊና አልቦሽ ሰብዕና ሥምየለሽ እንትን ምንተሶ ነው።

·         ውነት እኮ የተፈጥሮ ነፍስ መርህ ነው።

እውነት ሲፈጠር ኑሮን ለመምራት ነው። ተፈጥሮ መርህ አለው። የተፈጥሮ መርህ ደግሞ ዕውነት ነው። የሰው ልጅ የተፈጥሮ አካል ነው። ስለዚህም የሰው ልጅ ተፈጥሮው የሚገለጸው የኑሮውን ህልውና በመርህ ሲመራ ነው። መርሁ ደግሞ ዝንቅም፤ ጠቃጠቆም ያልሆነ እውነት ነው።

እውነትን የፈራ የሰው ህልውና በተፈጥሮ መርህ ውስጥ ስለማይሆን ነፍሱ በሥርዓት አልበኝነት የተሸመነ ይሆናል። ሥርዓት አልበኝነት ደግሞ መጀመሪያውም ፍጻሚውም አቅላይ እና አባካኝ ብክል መከራ ነው።

እውነት የተፈጥሮ ብርሃንነቱ የሚገለጠው መርህን ተከታይ በመሆኑም ነው። ብርሃን ተከታይነት መንገድ መሪነት ማለትም ነው። ስለዚህ እውነት የብርሃን መንገድ ጠራጊም፤ መሃንዲስም ወይንም ንድፈኛም ነው ማለት ነው።

በብርሃን እና በጨለማ መካከል ያለው ልዩነት ሲሰላ በእውነት እና በዕብለት መካከል ያለውን ልዩነት ማዬት ማስተዋል ይቻላል። አብሶ ለእውነት ያለደረ ብዕረኛ፤ ጋዜጠኛ ጨለማን የፈቀደ መርህዊ መንገዱን የሳተ ነው ማለት ነው።

መርህ መሳት እና ጨለማን መፍቀድ ደግሞ ካሰቡት ለመድረስ እንቅፋት ይሆናል ማለት ነው። በዚህ ውስጥ እምነት የጣለ ህዝብ እና ትውልድ ምን ያህል የህሊና ትነት እንደሚገጥመው ሲሰላ ሚዛኑን መለካት አይቻልም። ጋዜጠኛ የፖለቲከኞችን እግር እዬተከተለ ፕሮፖጋንዲስት ከሆነ እነሱ ያን ፌክ ባሾለኩት መጠን ደረጃው ቁልቁል ያሰኘዋል።

ጋዜጠኛ ዕብለታዊ መሪን በደገፈ፤ ባንቆለባበሰ ቁጥር የመረጃ ፍስቱ ድልዝ ይሆናል። የመረጃ ፍልሰት ድልዝነት ደግሞ የጋዜጠኛ ኤቲከስን አመድ ነው የሚያደርገው። በዚህ በተሳሳተ መረጃ የሚባክነው ትውልድን ለጨካኞች አሳልፎ መስጠት በመሆኑ ህሊና እረፍት አልበሾ ይሆናል።

ፖለቲከኞች የሚቀድምባቸው ራሳቸው እና ሥማቸው ብቻ ነው። ለዚህም ነው አንድም መሪ በ60ዎቹ ዓመታት ውስጥ ተጋድሎ ላይ ነፍሱ ትግል ላይ እያለ አለፈች ተብሎ ሰምተን እማናውቀው። ምሽጉ እብለት ነውና።

ከማያሰነብተው የሰው ዕብለት ጭነት ይልቅ የሰው ልጅ ፈጣሪ የፈጠርለትን የተፈጥሮ መርህ እና ብርሃን የሆነውን እውነት መከተል፤ አድንቃቂው መሆን፤ መንከባከብ እና አብሮ ለመኖር መቁረጥ እና በዛም መዝለቅ ይገባል።

ለነገሩ አንድ ጊዜ ዕብለት ከተገኜ ማህበረሰቡ ማንዘርዘሪያ ስላለው ሚዛንን ጠብቆ ለመዝለቅም ሌላው ፍዳ ነው … „ቃል የዕምነት ዕዳ“ የሚሆነውም በዚኸው አግባብ ነው። ተቀባይነት በመታመን ውስጥ እንጂ በዕብለት ውስጥ አይገኝም፤ ቢገኝም ኮሸሽሌ ወይንም የዶሮ ቅማል ነው። 
·         ውና፡

እውነት ካኖሩት የሚገኝ፤ የማይረሳ፤ የማይደለዝ፤ ቢደግሙት፤ ቢሰልስቱ በዛው በልኩ፤ በመጠኑ ሳይጓደል፤ ደርበብ ሳይሆን የሚገኝ ሲሆን ዕብለት ግን ጤዛ ነው፤ ጎርፍ። የሳሙና አረፋ።

እውነት ራሱን በገለጠ ቁጥር በእሱ ላይ ያደሙ የዕብለት ግብረኞችን እያራገፈ እዬነጠረ ይሄዳል። ወርቅ ወርቅ ነው ዘመን ቢገለባበጥ እንዳማረበት ፈልቆ የሚኖር። እውነት ወርቅ ነው።

እውነት ጻድቅ ነው የሚጸድቅ፤ እውነት ቅዱስ ነው የሚያስቀድስ፤ እውነት ብሩክ ነው የሚያስባርክ፤ ዕውነት የተመረቅ ነው የሚያስመርቅ፤ እውነት በረከት ነው የሚያበረክት። 


  እውነት ለደፋሮች ብቻ የተፈጠረ ክስተት ነው!


እብለት ደግሞ ለፈሪዎች የተሰጠ ዝልብ ስጦታ ነው!



የኔዎቹ ኑሩልኝ።
መሸቢያ ጊዜ።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።