ለአላዛሯ ኢትዮጵያ መከራ መፍትሄው ግልጽነት ነው።


ለአላዛሯ ኢትዮጵያ መከራ
መፍትሄው ግልጽነት ነው።

„የሰው ልብ መንገድን ያዘጋጃል
እግዚአብሄር ግን አካሄዱን ያቃናለታል።“
ምሳሌ ፲፮ ቁጥር ፱

ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
16.05.2019
ከእመ ዝምታ ሲወዘርላንድ



·       እፍታ።

የትህትና ሙሉ ወርድ እና የአክብሮት ጃኖን የተጎናጸፈ ሰላምታዬ ይድራሳችሁ ቅኖቹ የአገሬ የኢትዮጵያ ልጆች? ደህና ናችሁ ወይ? እኔ አምላኬ ክብሩ ይስፋ ደህና ነኝ። ዛሬ ስለ ግልጽነት የሚሰማኝን መግለጽ ፈለግሁኝ። ስለ ግልጽነት ፍልስፍና አይደለም። ስለ ግልጽነት የምህንድስና ዝበት እና ክስረቱን ነው።

ግድ ነው ዛሬ ስለ ግልጽነት ማንሳት። ምክንያቱም መከራው፤ ፍዳው የድምጽ አልባዎቹ የኢትዮጵያ እናቶች ዕንባን ቀጣይነት አሁንም እዬታወጀ ስለሆነ። እራሱ አሁንም መንፈሳችን ብክነት ላይ ነው። ሊሰከን አልተቻለውም። አንዱን አለፍነው ስንል ሌላው እዬተተካ … ይደቁሰናል።

በድምጽ


ለአላዛሯ ኢትዮጵያ ችግር መፍትሄው ግልጽነት ነው። ( የወግ ገበታ 17.05.2019)



·       ውስጤ።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ በእኔ ዕድሜ ያለውን ማለትም የፖለቲካ ተሳትፎ ማድረግ ከጀመርኩበት ጊዜ እስካሁን ያለውን ውስጡን ስጎረጎረው ችግሩ የግልጽነት ጉዳይ ነው ብዬ አመንኩኝ። ሴራም፤ ሸርም፤ ተንኮልም የግልጽ አለመሆን ጥገኞች ናቸው። ግንዱ ግን ፖለቲካው የሚማገርበት ስውር ፍላጎት ነው።

ዋናው የትውልዱ ብክነት መሰረታዊ ችግር የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሊሂቃን የአካሄድ ግልጽነት ከሚባለው ተፈጥሮ ጋር የተላለፉ ስለሆኑ ነው። ዕውነቱን የሚነግሩን በወቅቱ ሳይሆን ነፍስ በድርቅ ከተመታ በኋዋላ ነው።

ፖለቲካ በመንግሥት አሰተዳደር መሳተፍ ነው በቀላል አገላለጹ። የመንግሥት አሰተዳደር እና አመራር መሳተፍ ደግሞ ከድንጋይ፤ ከሳር፤ ከተራራ፤ ከወንዝ ጋር አይደለም። በቀጥታ ከሰው ጋር ነው። የሰው ማህበር ደግሞ ማህበረሰብ ነው። ማህበረሰብ የምንለው ደግሞ ህዝብን ነው።

ግልጽነቱ በተደቦለቦለ፤ በተጠፈጠፈ፤ በተንጨባረቀ ቁጥር በቀጥታ የህዝብን መኖር ያድቦለቡለዋል፤ ይጠፈጠፈዋል፤ ያንጨቧርቀዋል። መኖር የሌለው ህዝብ ደግሞ ተስፋውን ያጣ ህዝብ ነው። ተስፋ ያጣ ህዝብ ደግሞ አፍ ባለው መቃብር የሚኖር ምንዱብ ህዝብ ነው።

·       ቁም ነገር።

የፖለቲካ ሊሂቃን በዬዘመኑ ዕድል ሰጥቷቸው ስልጣን ላይ ሲወጡ ጫፉን ነው የሚያሳዩት። ስልጣን ላይ ባይወጡም ጫፉን ነው የሚነግሩን። ጫፉ ቀለማም፤ ሳቢ እና አጓጊ ነው። ቀለሙ ብሩሕ ውቅያኖስ ነው።

ለምሳሌ ቀለሙ አረንጓዴ ሊሆን ይችላል። እዬቆዬ ሲሄድ ግን ወደ ግራጫ፤ ወደ መበለዝ፤ ወደ ዝገት ይቀዬራል። ከስንት ኑሮ ድቀት በኋዋላ። ስለምን? በሂደት ውስጥ ያሉ ድፍን ድንብልብሎች ጊዜ ስለሚገልጣቸው። የፈለገ ቢከረቸም አንድ ቀን የሃቅ አምላክ ውልብልቢቱን ያወጣዋል።

የሆነ ሆኖ ባልታወቀው የድንብልብል ዘመን እውነት መስሎት አጋርነቱን፤ ተባባሪነቱን፤ ደጋፊነቱን ያሳዬ ትውልድ ይታጨዳል፤ ትውልድ ይመከናል፤ ትውልድ ይባክናል። ጥሬ ዕቃ አቅራቢዎች ደግሞ ድምጽ አልባዎቹ የኢትዮጵያ እናቶች ናቸው።

ያረግዛሉ፤ ከዛ ረግረጋማ የኢትዮጵያ የፈታና ኑሮ ጋር ታግለው ልጆቻቸውን ያሳድጋሉ፤ ለፖለቲካ ሊሂቃን ቀንበጦቻቸውን፤ ሸባለዎችን ይሽለማሉ። እነሱ አጨብጭበው ባዶ እጃቸውን ይቀራሉ። ሳይድሩ፤ ሳይኩሉ፤ የልጅ ልጅ ሳያዩ …

ቀንበጦች እና ሸበላዎች ደግሞ ግልጽ ባልሆነው የፖለቲካ ፍልስፍና ሲማገዱ፤ ነፍሳቸው ቢተርፍ እንኳን መጨረሻው ስንበቱ በኮሶ ተለውሶ ይሆናል። እውነት ለመናገር የኢትዮጵያ ፖለቲካ እፉኝት ነው።

እፉኝት ሲረገዝ አባቱን ሲወለድ እናቱን እዬበላ እና እያበላ ተረኛውን ለመቀርጠፍ የሚገሰግስ። ይህ መቼ ነው የሚቆመው ነው የእኔ ጹሑፍ ዓላማ? ጉዳዬ ስለ ድምጽ አልባዎቹ የኢትዮጵያ እናቶች ነው።

አንድ የፖለቲካ ሊሂቅ ግልጽነት መንፈሱ ማድረግ ሲችል ብቻ ነው ፍትህ ነው ሊባል የሚችለው። በስተቀር ለእኔ ስብናው እራሱ ፍጥረተ ነገሩ ወንጀል ነው።

መንፈሳችን፤ መኖራችን፤ ዕድሚያችን ሁሉ ሲያባካንኑ ባጅተው እነሱ ከነከብራቸው መንበር ላይ ሲሆኑ፤ የተማገዱት ደግሞ ትቢያ ላይ ወድቀው ከቤተ ክርስትያን እንደ ገባ ውሻ ሲንከለከሉ ውስጥን ያደማል።

ሰው ስንት ጊዜ ህሊናውን ለሰው ይሸልማል? የማዬው የምስማው የህሊና ንብረትነት ውርስ የማድረግ ነገር ነው። ሰው በህይወት እያለ እንዴት ህሊናውን ያውረሳል? ህሊና እኮ ሱቅ ተሂዶ የሚገዛ ሸቀጥ አይደለም። ወይንም በሚትር እና በቦንዳ የሚቸበበቸብ ጨርቅ አይደለም። 

አሁን የማያቸው በአውራው ድርጅቶች በኦዴፓም፤ በግንቦት 7ም እማዬው መከራ ይኸው ነው። ሁለቱም ግልጽ አልነበሩም። ኦዴፓ „ኢትዮጵያዊነት ሱሴ ነው“ አለ፤ መታመንን ቅርጥም አድርጎ ከባላ በኋዋላ የዴሞግራፊ ፍልስፍና ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን በብቸኛ ባለቤትነት የመቆጣጠር ሌላውን ቅኝ የማድረግ ነገር ተፈጠረ … ይህ መቼም አሊ አይባልም። 

በግንቦት 7 እና በሚዲያው በኢሳት የተፈጠረውም ይኸው ነው። ዴያስፖራ ላይ በቅሎ ብቻውን እንዲታይ ምንም ነገር አይፈለገም ነበር።

ኢሳት ከአመሰራረቱ ግልጽ ቢሆን ይህ ሁሉ ጣጣ አይመጣም ነበር። ፍቺውም ኮሶ ሆነ፤ ፍቺውም ከእውነት ጋር ያለው መስተጋብር መታመንን አያፈልቅም። ላፍልቅ ቢባልም ከአፈጣጠሩ ነውና ግድፈቱ ይከብዳል። ግለሰብን ዋሸው፤ ህዝብን ግን ከባድ ነው።

ሲመሰረት ኢሳት የመጣ ይምጣ ብሎ እውነቱን ማሳወቅ ለህዝብ ይገባው ነበር „እውነት ተናግሮ ከመሸበት ማደር“። ግንቦት 7 ከማዳጋስካር የመጣ አይደለም። አገር በቀል ድርጅት ነው። አገር በቀል ድርጅት ደግሞ ባዕድ ተደርጎ ሊታይ አይገባም። ወገን ነው። ቢያኮራ እንጂ፤ ቢያስመካ እንጂ ህሊና ላለው ወገን እሚያሳፍር አልነበረም ከመቅድሙ የግንቦት መሆኑ ተገልፆ ቢሆን ኖሮ ኢሳት።

ስለዚህ ግንቦት 7 ሚዲያውን ሲያዋቅር ግልጽ አድርጎት ቢሆን ኖሮ ይህ አሁን ያለው የጦፈ አውሎ አይከሰትም ነበር።

ተጋድሎ ተግባር ስኬት የራስን አቅም ካለ ኮፒ ራይት በወቅቱ ማሳወቅ ቀዳሚ ጉዳይ መሆን ይገባዋል። ልፋት፤ ድካም አለበትና። ልፋት እና ድካም ብቻ ሳይሆን በረድም፤ አውሎም አለበት። ስለዚህ የራስን አንጡራ መንፈስ ሲፈጥር አንድ ተቋም፤ አንድ ድርጅት ኮፒ ራይቱን ተጠዋሪ ማድረግ በፍጹም አይገባም ነበር። ግን እውሩ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ግልጽነት እርሙ ነው።

እኔ ለመጀመሪያ ጊዜ ደውለው ሲነግሩኝ የግንቦት 7 ነው ነበር ያልኳቸው። ስለዚህም በማንኛወም ተሳትፎ አልጀምረውም አልኩኝ። ቅንነት ሰማይ ደጅ ነውና  ለኢትዮጵያ ፖለቲካ። የግንቦት 7 ስለሆነ አልሰራም ለማለት አይደለም። የተሳካን የግንቦት 7 ህዝባዊ ስብሰባን መንገድ የጠረገችው ሥርጉተ ሥላሴ ናት። አልሞቱ አልታመሙም አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ይመሰክሩታል።

·       ምን ሆነ መሰላችሁ።

እኔ የአትዮጵያ ከረነት አፊርስ ቤተኛ ነበርኩኝ። የኢትዮጵያ ከረንት አፊርስ ራዲዮ ፕሮግራም ነበር። „አደራ“ የሚባል። እዛ ትሰራለች መባልን ሲሰማ ወደ ግንቦት 7 ራዲዮ እንደሰራ ከዚህ ሲዊዘርላንድ ያለው የግንቦት 7 ወኪላቸው ሪኮመንድ አደረገኝ። ከረነት እንዳይቀድም ተብሎ ነው። ይህን ጉዳይ ከረንቶች አያውቁም፤ ለከረንቶች ደግሞ ሌላ ተነግሯቸዋል። እሱን እዮር ይወቀው።

ይህን ነገር በቅርብ የሚያውቁት አልሞቱም አልታመሙም አቶ አበባ ቦጋለ በቀጥታ ደወሉልኝ። እርጅን አለኝ። የጸጋዬ ድህረ ገጽን  የቦርድ አባላትን አማክሬ እሺ አልኩኝ። ከዛ ከተወሰነ ግንኙነት በኋዋላ የከረንት ሪኮመንዴሽን ሲደምን፤ ያ ተረጋገጠ መሰል ይኽኛው ደግሞ በፖለቲካ ውሳኔ ተዳፍኖ ቀረ።

አደራም ብዙም ሳይቀጠል ቀረ። በሁለቱም አልተሳተፍኩም፤ አቅሙ ስለነበረኝ ግን ሁለቱንም አጣምሬ መሥራት እችል ነበር፤ የእኔም የጸጋዬ ራዲዮ፤ የጸጋዬ ድህረ ገጽ ነበረ። ግን ሁሉንም አስተካክዬ መስራት እችል ነበር። ማገልገል በቅንነት መልካም ነው። በግንቦት 7 አባል መሆንን ባልፈቅደውም ግን ተስፋ በበዛ ሁኔታ ነበረኝ። ስለሆነም ላግዘው ልረዳው እፈልግ ነበር።

ከዛ በኋላ ኢሳት ተመሰረተ። ስለዚህ ኢሳት ሲመሰረት ስጠዬቅ ሁለተኛ መጨማለቅ አልፈለግሁም። ያው በሴራ ፖለቲካ ምን እንደሚሆን ተመክሮ ስላገኘሁኝ። ለተራ የፓልቶክ አድሚንነት እንኳን ስንት ፍዳ አለበት።

ከሁሉ የሚከፋው በዚህ መንፈስ ውስጥ ደግፎ መስራት መጨረሻው ኮሶ ነው። ድካሙም ልፋቱም በቅንጣት ጥፋትም፤ በፈጠራ ክስም እንዳልነበረ ሆኖ ምድማዱ፤ ድምጥማጡ እንደሚጠፋ ደርሶብኝ ስላዬሁት አልተለካለኩም።

ለዚህም በሸር የሰለጠኑ አቅምን ለነፃነት ትግሉ በትክክል እንዳይውል እንቅፋቶች የተሰማሩ ነፍሶች ስላሉ ሳልነካካ መቀመጡን መረጥኩት፤ እንጂ አሁን ግንባር ቀደሟ ተማጋጅ ሥርጉትሻ ትሆን ነበር።

እኔን የረዳኝ አስቀድሜ ንብረትነቱ የማን እንደሆን ማወቄ ነበር። ነገር ግን በዚህ ግልጽነት በጎደለው አካሄድ እንዲህ እውነቱ ሊገለጥ ብዙ የመንፈስ አቅም ባክኗል፤ የጋዜጠኝነት ኤቲከሱም ቢሆን ድንገተኛ ውስጥ ነበር

አሁን በስንት ፍዳ እና መከራ፤ በስንት ፈተና እና ኮረኮንች፤ በስንት ጠመዝማዛ ጉዞ ያለፈ ትልቅ ብሄራዊ የሚያኮራ ተቋም፤ ለዛ ስንት የከፈሉ፤ ስንት የቀለጡ ስንት ህይወታቸውን ያመሰቃቀሉ ነፍሶች ዋጋቸው አይሆኑ እዬሆነ እዬተመለከትኩኝ ነው። አብረው ነው ድቅቅ የሚደረጉት። 

በአንጻሩም ኢሳትን እንደ የጥብብ ቤተኝነቱ የተቸ፤ የተናገረ፤ የወቀሰ ነፍስ ደግሞ በቀጥታ ከድርጅቱ ከግንቦት 7 ጋር ስለሚያያዝ አቅም ብዙ በጣም ብዙ አይሆኑ ሆኖ መክኗል። ሰላማችን ታውኳል።

ስደት ላይ ሌላ ስደትን ዜጎች እንዲያስተናግዱ ሆነዋል። ግንቦት 7 በቀጥታ የሚተቹ ነፍሶችም ቢሆኑ ነፍሳቸው በፈጣሪ ሃይል ሰንብታለች ማለት ይቻላል። ወጀቡ፤ ዘመቻው ልክም መጠንም የለውም። ግንቦት 7 ሰዎች ናቸው የሚመሩት፤ ኢሳትንም ነፍስ የዘሩበት ሰዎች ናቸው፤ ሰዎች ደግሞ መላዕኮች አይደሉም። ግድፈት ተፈርቶ ለዛውም በዝግ ፍላጎት የሚሆን አይደለም።

ሚዲያ ትችትን ኤዲቲንግ ፈርቶ አይሆንም። በአንድ ጉዳይ እጬጌ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ዘበኝነትን ያለ የነበረ ጉዳይ ነው። በሌላ ጊዜ ደግሞ ተመልሶ መንበር ላይ መሆንም አለ። ደግሞም ሚዲያን የሚያሳድገው ወቀሳ ነው።

የሰው ልጅ ካለቀርብከው፤ የእኔ ካላልከው አታዬውም፤ አታቀረበውም። እንዳታጣው የምትሻውን ነፍስ ብቻ ነው ስለምትጠነቀቅለት፤ ስለምትሳሳለት ግድፈቱን እምትነገረው። ይህ ግን በዝጉ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችሎት ዜግነትን የሚያሳጣ፤ ባለፈም ነፍስ የሚገበርበት ነው።

·       ግጥግጥ።

አሁን ግጥግጡ ከኢግልጽነት ጋር ቀጥሏል። አቶ ነአምን ዘለቀ ሰሞኑን የጻፉትን አነብብኩት። እርእሱ እና መቅድሙን ብቻ እንይ  
„ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ – (ነዓምን ዘለቀ)“

„ስለ እውነት እላችኋለሁ ይህ በአገራችን በኢትዮጵያ የመጣው ለውጥ ትልቅ ነን ብለው ራሳቸውን የሰቀሉ ሰዎችን ጨምሮ የራስን ድርሻና የታሪክ አሻራ አግዝፎ ማሳየት፣ ለሌላው እውቅና አለመስጠት፣ በርካታ ሃቆችንም በመደፍጠጥ እውነትም እውቀትም እኔ ጋር ብቻ ናት

የትግሉም አልፋና ኦሜጋ እኛ ነን የሚል ከሃቁ የራቀ ሚዛናዊም ያልሆነ፣ ግብዝነት የተጠናወተው ለእኔነት፣ (ego ) ለራስ ስብዕና መገንቢያ በሚመች መልክ አጣሞ የማቅረብ፣ ከዚያም አልፎም የሌላውን ድርሻ፣ ድካምና፣ መስዋዕትነት ለማራከስ የመሞከር በጣም የሚያሳዝን ርካሽ ባሕልን እያሰፈነ መጥቷል።“

·         የተከበራችሁ የጹሁፌ ታዳሚዎች

አሁን እኔ ጭብጡን በሙሉ ላቀርበው አይደለም በዚህ ድንብልብል የዘመናት ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ መከራ ድክም ያለው ወገን ከሥር የጻፉትን ላቀርብም ፈቀድኩኝ። ከዛ በፊት ግን  ርካሽ ባህል መስፈኑ የማከብራቸው አቶ ነአምን ዘለቀ አሁን የታያቸው፤ በራሳቸው ደርሶ ስላዩት እንደ አይዲኦሎጂ መሆኑን ግን አላዩትም ወይንም አልታያቸውም። በፖለቲካ በአነሰም በዛም ሲሳተፍ የነበረው ወገን ምን ያህል ሶቆቃ ላይ ነበር? በሲሶ ዜግነት፤ በእርቦ ዜግነት?

ወደ አስተያቱ እንዝለቅ … በቅድሚያ ጹሑፉን ከደጉ ሳተናው ድህረ ገጽ ነው የወሰድኩት።  
  1. አቶ Getachew Argaw May 15, 2019 at 1:44 am
አስተያየቱ ጥሩ ሆኖ ማንን እንደሚመለከት ግልጽ አይደለም። አሁን ነገሮችን አፍርጠን መነጋገር ይገባናል። ብዙ ተስፋ አስቆራጭ ነነሮች እንደተከሰቱ ይገባኛል። እነዚህንም ለህዝብ በግልጽ ሕዝቡ ሊረዳው ይገባል። ያኔ መፍትሔ ይገኛል። አለበለዚያ ከመቼውም ተስቀልሽ ከመቼው ተለቀሰልሽ እንዳለው የአገሬ ሰው እንዳይሆን ያሰጋኛል። ከታላቅ አክብሮት ጋር።
  1. አቶ Yakob May 15, 2019 at 12:21 pm
አስተያየቱ ጥሩ ሆኖ ዙረያ መሸከርከር ለምን አስፈለገ? አላስፈላጊ ጥላቻና ጥርጣሬ በሰዎች ላይ የሚፈጥር ስለሆነ እንደዚህ የወረደ ጽኁፍ ባታቀርቡ፡፡እንደሚዲያ ለህዝብ በግልጽ የተሙአላና balanced የሆነ መረጃ ብታቀርቡ፡፡
  1. አቶ አለም May 15, 2019 at 2:41 pm
ኲርፊያ መሆኑ ነው?
የኢሳይያስ አፈወርቂ አፈ ቀላጤ እንዳልነበርክ፣ ኤርትራን እንደ ዲሞክራሲ ስታሞግስ እንዳልነበር፣ ይመልከቱ። አሁን ደግሞ ኲርፊያህ በማን ላይ እንደ ሆነ መደበቅህ ያስገርማል?
በውነቱ ሰልችቶናል። በጣም ሰልችቶናል።
·         ድንብልብል

የአቶ ነአምን ጹሑፉን ውስጡን ለማግኘት ወደ 6 ጊዜ አነበብኩት። ድፍን ነው። በሩም የተከረቸመ ነው። ግልጽ ባለመሆኑም ጨለማም ነው። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን አያድናትም። ከጨለማ ምህረት የለምና።

ባለፈው ጊዜ የሳቸውን ከሃላፊነት በፈቃዳቸው መልቀቅ አስመልክቶ እሳቸው ቀድመው እለቃለሁ ስላሉ ነው እንጂ ፈጽሞ በቀጣዬ ድርጅት በሰሞነኛው ኤዜማ ቦታ አልነበራቸውም። እሳቸው ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆነው እንዲወጡ አልተፈለገም።

ሚዲያ ላይ እኮ አልታዩም ነበር አገር ቤት። ለመከራው ቀን ብቻ እጃቸውን አጣምረው እንዲገኙ ተደርገው አይቻለሁኝ መስከረም ላይ። ለምን ለሚለው መልሱ ይኸው ነው የሚፈለጉበት ምዕራፍ ስለተጠናቀቀ ነው። ይህ እንግዲህ የፕ/ ብርሃኑ ነጋ የተለዬ ቋሚ መርህ ነው። አንድ ሙሽራ 7 ጊዜ ሲዳር 7 ጊዜም ተመሳሳይ ሚዚ ማሰናዳት ግድ የለበትምና።

ሌላው አስተያዬት ሰጪ አቶ አለም „ኩርፊያ“ መሆኑ ነው ብለዋል። ቢያኮርፉም ይገባቸዋል።  በዕብለቱም፤ በዝናውም፤ በመስዋዕትነቱም፤ በድካሙም በሁሉም ዱላውንም ክብሩንም ያሰተናገዱ ሰው ናቸው። አቅም ደግሞ አላቸው። አሁን ኢዜማ መሪ ከሆኑት የሚያንሳቸው አንዳችም ነገር የለም።

·       ኤዜማ ግልጽነትን አሁንስ በጥዋቱ ደፈረውን?

በሌላ በኩል አሁን ቀስተደማና  ያደራጀው ፓርቲ እኮ የጠ/ሚር አብይ መንግሥትን የሚገዳደር መንግሥት እና ፓርቲና መንግሥትን አጣምሮ የያዘ ድርጅት ሆነ ነው የተፈጠረው። ግልጽነትን ደፍሮ አይደለም የተደራጀው።

ቀውስ አሰኝቶት ከባላንጣው፤ አብዝቶ የሚጠዬው፤ የሚጎፈንነው መንፈስ ካደራጀው ኢዴፓ ጋርም ጋብቻ ፈጽሟል (ከ አቶ ልደቱ አያሌው ነፍስ መንፈስ ከፈጠረው ፓርቲ ጋር)? ግን ለምን? ምን ያህል ነፍሳችን በዚህ መከራ ስትባዝን እንደባጀት እረሳውን የፕ/ ብርሃኑ ነጋ መንገድ ወይንም ሌጋሲ? ብዙ ነገር ደቋል። መልሶም ለመገንባት አይቻልም። ስንጥቅ አይደለም። አመድ እንደገና ተመልሶ ማገዶ አይሆንምና? በማን ህሊና ነው ይህ ሁሉ እንድርቺ እንድርቺ

ወደ ቀደመው ምልሰት ሳደርግ፤ ኢዜማ ማሳው ሳይኖረው እንደ መንግሥት እና አንድ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚመራ ፓርቲ ሆኖ ነው የተደራጀው። የሽግግር መንግሥት የሚመራ ፓርቲ ዓይነት።

ጣምራ የሆነ ተልዕኮ ይዞ ነው የተደራጀው። „ቃለ ማህላ“ አድርጓል። በፓርቲ መስራች ጉባኤም እንደ ምርጫ አሸንፎ አዲስ ካቢኔ እንዳዋቀረ መንግሥትም ቃጥቶታል „ይህ ደግሞ እንዲህ በቀውስ ለተወጠረው የአብይወለማ ካቢኔ ለምዕራባዊን ቀልብ ሳቢ እና እንደ አማራጭ እንዲዩት የሚያደርግ ነው። ማነው ባለሳምንትን አሟልቶ ነው ብቅ ያለው።

ለሌሎቹ ድርጅት አለን ለሚሉትም እኔ ብጡል እጬጌ ነኝ በማለት የዲሞሽንም ግብዣም ልኮላቸዋል። ለራሱ ለግንባሩ ለኢህአዴግም። ይልቅ የአፍሪካ ህብረት እና የአውሮፓ ህብረት ተወካዮች አለመገኘተቸውም ገርሞኛል። ከአብይወለማ ሌጋሲ ቀንዶችም የድጋፍ መልዕክት ውርርስም ተደርጓል።

አሁን ተገዳዳሪው፤ ግንቦት 7 ሳያስበው፤ ሳያልመው ፈጽሞ ባልተጠበቀ ሁለገብ ብቃት፤ እና የእንኳን ደህና መጣህልን ድንቅ አቀባበል ተደርጎለት የነበረው በትረ ሥልጣኑን የያዘው አብይወለማ ሌጋሲ በዴሞግራፊ ፍልስፍና „ኢትዮጵያዊነት ሱሴ ነው“ ቃሉን አጥፎና በቃጠሎ አንድዶ ሲገኝ፤ ታች ላይ ዘጭ ሲል ወፍ ያወጣው የቀስተደማነው ባላባት ግንቦት 7 ነው።

ስለዚህ ተሰናድቶ ለመጠበቅ የፈጀውን ጊዜ ፈጅቶ ባገኘው መቆናጠጫ መሬት ሙሉ አቅሙን የሚያሳይበት ሁኔታ ተፈጥሮለታል። ለዚህ የኤርታራ መንግሥት ታላቅ ውለታ ፈጽሞለታል።

·       የአትዮ ኤርትራ እርቀ ሰላም ትሩፋት።

ግንቦት 7 አባላቱ በተሰላቹበት ጊዜ እና ከአማራ ተጋድሎ ወዲህ በገጠመው ፈተና ሁለት ዓመት ቆይቶ ቢሆን ኖሮ ድብዛው አይገኝም ነበር። ነገር ግን የኢትዮ ኤርትራ  እርቀሰላም ትሩፋት ነፍሱን አዳነው። ኦክስጅን ሸለመው።

የኢትዮ ኤርትራ እርቀ ሰላም የሚታዬው ከዚህ አንጻር ነው፤ የኢትዮጵያን መከላከያ መቅኖ በማዳከም እረገድ እና አገር ውስጥ ቀውስ በማደራጀት ኦነግን፤ ፖለቲካዊ አቅምን ኮትኩቶች ገዢ መሬት በማስፈለጉ ትዕይንት ደግሞ ግንቦት 7 ለድል አብቅቷል የኢትዮ ኤርትራ እርቀ ሰላም። ልክ የኢትዮጵያ አርበኞች ግንባርን አሳልፎ እንዳስረከበው ሁሉ የኤርትራ መንግሥት።

የኦሮማራ ድል በቀጥታ ተጠቃሚው የጳጉሜና የመስከረም የኦነግ እና የግንቦት 7 የአቀባበል ግዝፈትን ማዬት ነው። እሱን እንደ ማውጫ መውሰድ ይገባል። የፕ/ብርሃኑ እና የዶር አብይ ፍቅር ለእኔ ለሥርጉተ ሥላሴ የሳሙና አረፋ ነው።

ሐሤት ላይ ያለው መንፈስ የፕ/ ብርሃኑ ነጋ ነው። የአብይወለማ ሌጋሲ በኦነግ ፍልስፍና ዳሽቋል። ዕውቅ የተባሉትን፤ አራት ዓይናም የተባሉትን በግንባሩ ውስጥም፤ በተፎካካሪም ያሉትን ነፍሶች በተለይ ደመ አማራ ሊሂቃንን ሁሉንም ለሽ አድርጎ ቀንበጥ ሆኖ ወጥቷል የቀስተዳመናው ፓርቲ ባላባት ግንቦት 7። ይህን የመሰለ ዕድል በዘመነ ቅንጅት እንኳን አላገኘም ነበር።  ያን ጊዜ ሌላም ፊት ላይ የነበሩ ወገኖች ነበሩ። የዝንቁ መከራ መፈጠሪያም ይኸው አመክንዮ ነው።

ሰማያዊ ከሁለት ከፍሎ፤ ኢዴፓን እንጥፍጣፊውን እውቅና ሰጥቶ፤ የአንድነትን ቅኖች አክሎ፤ የራሱን አመራር አራግፎ፤ የሰማያዊ እና የኢዴፓ መስራቾችን የሁለቱን መስራቾች የማይክ ቤተኛ በማድረግ አንገዋሎና ከፖለቲካ ምድረበዳ ላይ አስቀምጦ፤ እግዚብሄር ረድቷታል። ወድቃ ያልቀረችው ክብርት ወ/ት ብርቱካን ሜዴቅሳ ብቻ ናት። እሷንም የረዳት የፖለቲካ ነጋዴ አለመሆኗ አይደለም። የኦዴፓን ዘመነኛ መስፈርት ስለምታሟላ ነው።

ይህም ለአዲሱ ፓርቲ ለኢዜማ መስራች ግንቦት 7 ታላቅ ድርሳን ነው የአብይ ካቢኔ የዋለለት። የነፍስ ውለታ። እሷ እወዳደራለሁ ብትል „አሞራው በረረ ቅሉ ተሰበረ“ እንደሚሆን እከሌ ተከሌ ሳይባል ሁሉም ያውቃታል። ማለት መሳጭ የሆነ ቅብዕ አላት። የእኔ መንፈስ ሁልጊዜ እሷን እሷን ያሰኘዋል። 
 
በዚህ ደልዳላ ማሳ ላይ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ግልጽነቱን ስናዬው ምንም ነው። አሁን ማንም አይታዬውም። በጫፉ ስንጨፋጨፍ የገዘፈ ህልም ይዘው ተቀናቃኛቸውን፤ ብቁና እሳት የላሱ አቅሞችን አመድ እያስገቡ ዛሬ ሁሉም ልኩን ይዞ ተለሽልሿል። ከአብን እና ከባልደራስ ንቅናቄ በስተቀረ። እነሱም ጊዜ እዬተጠበቀላቸው ነው። ውዶቼ የጹሑፌ ታዳሚዎች … ሰማችሁት የሰሞኑን የደብረታቦር የብአዴን ስብሰባ ጦሩን በአብን ላይ መዟል። ስንት ሳተና ዲያስፖራ ላይ እንዳለ ዘንግቶታል።
  
·       የቃሊቲው መንግሥት የጋዜጠና ሲሳይ አጌና ትንቢት ዋዜማ ላይ ነው።

የቃሊቲው መንግሥት የጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ትንቢት እንሆ ዋዜማ ላይ ነው። ድሉ በመንፈስ ነው መታዬት ያለበት። ያ የሚሊዮኖችን ነፍስ በፍቅር የገዛው የአብይ ነፍስ ዛሬ በውሳጣችን ትናት ሲያሰኘው ለዲያስፖራው አውራ ድርጅት ግንቦት 7 ደግሞ ታላቅ የምስራች የድል ወራቱ ነው። አብሶ ለህልመኛው መንፈስ።

ግን በትረ ሥልጣኑን እስኪይዝ ግልጥነት ጋር ተዋውቆ የማያውቀው የቀስተዳመና ፓርቲ መንፈስ አሁንም በድንብልብል ድፍን ጉዞ ከገዢው ድርጅት ከኦዴፓ ጋር ጫጉላ ላይ ነው። 80 የሚቀደደው እውነቱ የወጣ ዕለት ነው።

ይህ ያልገባቸው ነፍሶች በደጋፊ እና በተቃዋሚ ጎን ቆመው አሁንም ይፋለማሉ። ጠብ፤ ገጭ ገው አያስፈልግም። ሁሉንም በልክ መያዝ። የሚቀድመው በእውነት ውስጥ ከስሜት በጸዳ ሁኔታ እናት አገርን ከውስጥ ማስቀመጥ ነው። መድህኗ የት ላይ እንዳለ በማስተዋል ሆኖ አቅምን ማኔጅ ማድረግ ይገባል። 

·       ሲደጋገም ይሰለቻል።
 
በዛ ሰሞን አቶ ወንድም ጋዜጠኛ አበበ ገላው የአቶ ነአምን ዘለቀን ከሃላፊነት በፈቃዳቸው መልቅ አስመልክቶ አንድ ጹሑፍ አስነብቦን ነበር። ያው ድንብልብል ነው። ግልጽነት የጎደለው።

 „በተለይ ድርጅቱ እራሱን አፍርሶ ከሌሎች ጋር በጣምራ ለስልጣን የሚወዳደር የፖለቲካ ፓርቲ ከመሆኑ በፊት በግልጽ እራሱን ገምግሞ የተሻለ አሰላለፍ ማድረግ ይጠበቅበታል። በተለይም የዜጋ ፖለቲካ እየሰበኩ የሴራ ፖለቲካ የሚያራምዱ አንዳንድ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር አባላት ጥፋት እያደረሱና ድርጅቱ እምነት እያጣ እንዲሄድ እያደረጉት መሆኑን የምናውቅ እናውቃለን። በስብከትና ተግባር መሃል ክፍተት መኖሩ ጊዜ ጠብቆ ትልቅ ችግር መፍጠሩ አይቀሬ ነው።“ ግንቦት 7ትን መሆኑ ነው።

ጋዜጠኛ አበበ ገላው በነአምን ዘለቀ መልቀቂያ ላይ (አበበ ገላው)
March 19, 2019

„በተለይም የዜጋ ፖለቲካ እየሰበኩ የሴራ ፖለቲካ የሚያራምዱ አንዳንድ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር አባላት ጥፋት እያደረሱና ድርጅቱ እምነት እያጣ እንዲሄድ እያደረጉት መሆኑን የምናውቅ እናውቃለን።“

እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው? ስንት ዘመን ድምጽ አልባዎቹ የኢትዮጵያ እናቶች የልጅ ልኳንዳ ቤት ይከፈትባቸው? ይህን መታደግ እኮ ከፋና ወጊው ደፋሩ ጋዜጠኛ ይፈለጋል። እናቶችን ማዳን እኮ ነው ጉዳዩ …

አቤዋ ከሰሞናቱ ደግሞ ከናሆ ቴሌቪዥን ጋር „ችግር“ አለ በሚል አሁንም ግልጽነት በጎደለው ሁኔታ ጠቅልሎ ገልፆታል።

„ችግርን“ ፈጣሪው ግዑዝ አይደለም። መቼም ትሪ፤ ወይንም ጥራር ወይንም ሞሰብወርቅ ችግር አይፈጥርም? ሰው ነው ችግር የሚፈጥረው። ስለዚህ ያ ችግር ፈጣሪ መንፈስ ማን ነው? ማን ይባላል ሥሙ? ሥም የለውም?

የእሱ መሰመር በጥልቀት ወደ ጉዳይ መጠጋት ኢንቤስትጌትድ ከሆነ፤ ራሱን አሳልፎ የሰጠውም ለዛች መከረኛ እናቱ ስለሆነ፤ ያን በዬትም ሁኔታ፤ በምንም መልኩ ቢሆን ጸጋውን ሳይተላለፍ መግለጽ ግድ ይለዋል። በስተቀር ዝም ማለት፤ አለመነካካት። ስንት ዘመን ይከዘን የመከራችን እንጉዳይ? 

መከራን ለመቼ ነው በቅድመ ሁኔታ ተቀማጭ የሚሆነው? ለማን ሲባል? ኢትዮጵያ ወይንስ እነሱ ያልገለጡልን ሰዎች ሥም፤ ኢጎ የትኛው ይበልጣል? መቼም አገሬን እወዳለሁ ለሚል ዜጋ ከአገር በላይ ማንም እና ምንም የለም።

ጉድ አንድ ሰሞን ነው። የፖለቲካ ሊሂቁ አቶ ነአምን ዘለቀ ሆኑ ጋዜጠኛ አበበ ገላው ያለውን ሁሉ ይዘርግፉት ከዛ የሚሆነው ይሆናል። አሁን በጠ/ሚር አብይ አህመድ እና በመከላከያ ሚ/ሩ አቶ ለማ መገርሳ ብዙ ነገር ሆኗል። መታመን እና ቃል ቀብር ተልከዋል።

ይህም ሆኖ እነሱን የሚያምኑ፤ እነሱን ተስፋ የሚያደርጉ ደግሞ አሁንም አሉ። እነሱንም እንደ መላዕክ የሚያዩም አሉ።

በሌላ በኩል እነሱ ከሥልጣን ቢለቁ ደግሞ ሊመጣ የሚችለው ነገር ያሰጋን ሰወችም ብንሆን ስህተቱን በድፍረት መግለጽን ደግሞ አላቆምነም። ግን ያልሆነ አቅጣጫ ደግሞ መጥቶ የባሰ ረግረግ እንዳይገባ ግን ጠንቃቃ መሆንም ያስፈልጋል።

ወቀሳው ግን ስውሩ ማንፌስቶ ኢትዮጵያዊ መንፈስ እዬጠነዘለ ስለሆነ። አድሎ፤ ግለት፤ ግልጽ ዲስከርሚኔሽን ስለምናይ። በተለይ ጸረ አማራ መንፈስ በተደራጀ፤ በተቀነባበረ፤ በሰለጠነ ሁኔታ ስለመካሄዱ አጥርተን፤ አንቀርቅብን ስለምናውቅ። ቢያንስ መንገዱ ትክክል አለመሆኑን ከማስገንዘብ አልተቆጠብነም። እነሱንም ባናጣቸው፤ እነሱም ከስግብግብ ፖለቲካ እና ከክህደት መስመር እንዲታደጋቸው አምላካችን ከመለመንም አልታቀብንም።

·       ኦሮማራ ድሉ ለማን?  

ኦሮማራ ህወሃትን ወደ ምሽጉ ላከ፤ አሁን ደግሞ ግንቦት 7 እና ኦህዴድ በተመሰጠረ ሁኔታ አብን እና ባልደራስ ላይ አነጣጥረዋል። ቀጣይ እንደ ጠላት የታዬው ድርጅት አብን ነው። እሱን አከርካሪ ለመስበር ጊዜያዊ ወዳጅ ደግሞ ብአዴን ሆኗል። አንድ ነፍስ፤ አንድ ተቋም አብን የሚደግፍ መሬት ላይ የለም ከፌድራል መንግሥቱ ጀምሮ፤ማይክ የታደለው ሁሉ የ አፍ መፍቻ ቋንቋው አብን ነው።

ይህ ደግሞ ውስጣችን የበለጠ ቢያፋፋው ቢያበለጽገው እንጂ ለአማራ ልጅ መንፈሱን አያሸማቅቀውም። ምን አልባትም ሁሉም ጠቅልሎ እንደ ጽዮናዊነት ተጋድሎ ከጀመረ ሁሉም ነገር የከፋ ይሆናል። በችሎት እና በታጋሽነት ነው ዝም የምንለው። 

ኦዴፓ አንድ አፍታን ሚዲያን ያደራጀው ኦቢኤንን እንዲተካለት ነው። በዛ እናዳይወቀስ ይህን አደራጀ። ወደ ቀደመው ጉዳዬ ምልሰት ሳደርግ … እንደ አመሉ ግርባው ብአዴን ራሱን እዬናደ ራሱን በሚያጠፋው መስመር ካለ ብልህነት እዬነጎደ ነው። የኦነግ መንፈስ እንዳሻው ይፈነጭ ዘንድ አብን ለመጫን አዲስ ፖሊሲ እያራመደ ነው።

… ግልጽነቱ ለውጥ ስለሚባለው የማን እና የማን ጋብቻ ሆነ? ይህን ጋብቻ ማን አስፈጸመው ቢባል የፕ/ ኢሳያስ አፈወርቂ የእጅ ሥራ ነው ይሄ እኔ እንደሚገባኝ።
የዚህን ናሙና በገቢዎች እና በጉምሩክ የሥራ ድልድል የተገለጡ ፍንጭ ሰጪ አመክንዮቹ አሉ። ሬሾውን ያን በማስተዋል መመርምር ነው። ወደ ሥራ እዬተሸጋገሩ ያሉ እውነቶች አሉ።

የሰሞኑ ኢዜማን የማብቃት እና የላቀ ዕውቅና የመስጠት ሁኔታም ልጠቱ ደረጃውን አሳይቶናል። አንዱ ተገፊ፤ ተሳዳጅ፤ ተወጋዥ፤ ተገላይ አንዱ ደግሞ ታቃፊ? ሁለቱም ግን የኢትዮጵያ እናቶች የወለዷቸው ኢትዮጵያዊ ዜጎች ናቸው። 

ሌላው የቀውሱ መፋፋም፤ የቀውሱ ማፋፋት ይፈለጋል። የኢትዮጵያን ታላቅነት ለማይመኙት ሁሉ። ለዚህም ኦነግን በተሟላ ሎጅስቲክስ አቅሙን አጎልብቶ እንዲወጣ እዬተደረገ ነው። በሌላ በኩል ግልጽነት የጎደለው ወዳጅነት፤ ስምምነት አሁንም እዬበደላት ነው አገርን። ይህም ቀጣይ መሆኑ ነው አሳዛኙ ትራጄዲ …

የኦነግ አገር እምሳ፤ የውጤቱ መዳረሻ መንፈሳዊ ጎታ ኢዜማ ሁለቱም የፕ/ አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ የእጅ ሥራዎች ናቸው። ድካማቸው ባክኖ መቅኖ አጥቶ እንዲቀር የማይሹ ናቸውና። ኢሳያስ ሰራሽ ኢትዮጵያን ማዬት ህልማቸው ነውና።

ፕ/ ኢሳያስ አፈወርቂ ህወሃትን አዝለው እንዳስገቡት ማሽቀንጠሩ ባይሳካላቸውም ዕድሜ ለኦሮሞ ንቅናቄ እና ለአማራ የህልውና ተጋድሎ በስል ገብተው ግን በሰላም ሥም የልባቸውን አሳምረው፤ አደላድለው እዬፈጸሙ ባለርስተኛ ሆነዋል። ግንቦት 7 ላይ የሚፈልጉት አንድ ነፍስ ነበር። እሱም አሁን ከአንከሊሱም፤ ከወተቴውም ተርፎ ተክሊል ደፍቶላቸዋል። ፍቅሩም እስከ መቃብር ይቀጥላል … መገናኛው መስመር ዝግነት ነው።

·         ገመና በድፍንቅል ለሞት። 

አሁንም ማንም ምንም ይሁን እናት አገር ኢትዮጵያ መከራ ላይ ነው ያለችው፤ ገመና ካለ ይገለጥ። ገማና ካለ ይውጣ፤ ገመና ካለ ይዘርገፍ፤ ከዛ ፍርድ ህዝብ ይሰጣል። ለማን ሲባል? ለአላዛሯ ኢትዮጵያ ሲባል። ስንት ቀንስ ኢትዮጵያ ትዋሽ? ስንት ዓመት ሙሉስ ለአንድ ነፍስ ተብሎ ዕውነት ትንጠልጠል?

ያን ነፍስም ማዳን የሚቻለው እኮ ስህተቱ፤ ግድፈቱ ሲነገረው እንጂ ሲሸፈንለት አይደለም። ነፍሱ ከህዝብ በላይ ሆኖ እራሱን እንዲይ የሚያደርገውም ይኸው ነው። እኔ እውነት ብናገር በ2016 ያን ርጉ፤ ቅን፤ ትሁት መንፈስ ያወቅኩት ዛሬ የለም … ጠ/ሚር አብይ አህመድ መክሊታቸውን ፈርተው ሸሽተው አዲስ ሰብዕና ላይ ይገኛሉ። ዶር አብይ አህመድ ተጠለፉ ወይንስ ጠለፉ? እሱን የቡናው የሀምሌ ዝምታ ይመልሰው።

ገመናን ሞሽሮ ስለ ኢትዮጵያ ፍትህ፤ ቀጣይ ሰላም፤ ዴሞክራሲን እርሱት መኖር አይታሰብም። ንግግሮች፤ ፍላጎቶች፤ ስሜቶች፤ ለግል ኑሮ ቁጥብነት ሊጠቅም ቢችል ግን ዘመንን ዘመን በለወጠ ቁጥር ግን በአዲስ ድራማ ለግለሰቦች ኢጎ ሲባል አገር ትጎዳ ማለት ፍጹም ጭካኔ ነው። አረመኔነትም ነው። ህወሃትንም ሸኝተን፤ ኦዴፓን ሸኝተን፤ ሌላ ገሃነም ደግሞ መናፈቅ እንዳይሆን ለህዝብ የምታውቁትን የማሳወቅ ግዴታ አለባችሁ ታዋቂ፤ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች፤ የሰብዕዊ መብት ተሟጋች የምትባሉት ሁሉ። 

በአገር ውስጥ ተፋናቃይ እኮ ከሶርያም በላይ ኢትዮጵያ ሆናለች። ይህ አንገት አያስደፋም ወይ? የዚህ ዓመት በሺህ የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ተስተጓጉለዋል። በግልጥነት ድርቅ በተመታመበት ፖለቲካ።

የሰው ልጅ የተፈጠረው ለእውነት እንጂ ለእብለት አይደለም። የሰው ልጅ የተፈጠረው ለግልጽነት እንጂ ሽንገላን ለማባበል እና ለማቆላመጥ አይደለም። ይህ ደግሞ በግለሰብ ሰብዕና ቢሆን ምንም አይደለም የ100 ሚሊዮን ህዝብ ነፍስን የሚወሰን ነው።

የቅንጅት፤ ይሁን የግንቦት 7 ችግሩ ተሻጋሪ መሆን የለበትም። ያን ጊዜ በችግር ላይ ጊዜ አናጥፋ ብለን አለፍነው፤ ግን ችግሩን ሳናውቀው ነው እንዲቀጥልና እንዲፋፋ አባሪ የሆነው። ስለዚህ ከቅንጅት መራራ ስንብት ማግስት እስተዛሬም ይኸው ችግር ይንሸራሸራል፤ እኛንም ይሸረሽራል። ነገም ይቀጥላል ተሸብልሎ።

·         ዕውነት ሆይ! የት ነው ያለሽው?

የችግሩ ቁስል መግሉ ፍርጥርጥ ብሎ ሊወጣ እና ሊለይለት ይገባል። ግን ከግብታዊነትም፤ ከስሜታዊነትም፤ ከግላዊ ጥቅም፤ አብሶ ከዞግና ከቂም በቀልም ውጪ በሆነ መልኩ እንደ አንድ ንጹህ ዜጋ ትውልዱን ከብክነት ማዳን  የእያንዳንዳችን ድርሻ በግል፤ የሁላችንም ድርሻ በጋራ ሊሆን ይገባል።

የየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ቀዳሚ ቤተኞች ልትነግሩን የምትፈልጉትን ነገር ጫፉን ሳይሆን ሙሉ ሆድ እቃውንም ጭምር ነው። እናንተ ስትናገሩት ሃሜት መሆኑ ቀርቶ ዕውነት ይሆናል። የሰው ልጅ ፍጥረቱ ለእውነት ብቻ ነው።

እውነት ከተነገረ በዬጊዜው እያመረቀዘ መገል ከሚያፈስም ቁስሉ እንዲሸር ይሆናል። ያን ጊዜ ግንቦት 7 ሲመሰረት ጉባኤ ላይ ጥያቄ ሲቀርብ ፍርጥርጥ ብሎ መልስ ተስጥቶ ቢሆን እንዲህ አዲስ ምዕራፍ በተሆነ ቁጥር አያገረሽም ነበር።
 
ነቀርሳ መዳህኒቱን በወቅቱ ካለገኜ ይገድላል። የአገርን የእምዬን ሞት በፆም በጸሎት ካልጠበቅን በስተቀር ችግርን ሳይውሉ ሳያሳድሩ መናገር ይገባል። ቀድሞ ነገር የችግር ጥሪት ምን ይፈይዳል። ይልቅ በስብሶ የፈነዳ ዕለት ብዙ ነገር ያበላሻል። ልብስህን ልትቀይረው ትችላለህ፤ ህሊናህን ክፉ አሳቢ ከሆነ ከወደድክ ትቀይረዋለህ፤ ሸርህንም ከፈቀድክ ልትተወው ትችላለህ፤ በዬዘመኑ የከሰመውን ትውልድ ግን አትተካውም፤ አሁን አርበኛ ሳሙኤል አውቀን መተካት ይቻላልን? አርበኝት ሺህብሬ ደሳለኝንስ?

ቀደም ባለው ጊዜ የነጻነት ትግሉን ይጎዳል ነው፤ አሁን ደግሞ ለውጡን ይጎዳል ህወሃትን ይጠቅማል ነው። ግን የተጎዳው ህዝባችን እና ትውልዱ ነው። በትውልድ የሚነግድ የፖለቲካ ባህል ያላት ኢትዮጵያ … በዬዘመኑ እንዲህ መታመስ የለባትም። መንገዱ ካልተሰተካከለ፤ ቀጣዩ ዕጣዋ ፍርሰት ነው። ለዚህ መተባባር ደግሞ እንደ ሰው ለመተያዬት ይቸግራል። ሰው እንሁን!

·       እናንተ ከፖለቲካ ሊሂቃን ጋር አብራችሁ የነበራችሁ ወገኖቼ ሆይ!
አሁን አዲስ ምዕራፍ ላይ ነን። ስለዚህም ጠቀመም፤ አልጠቀመም ማስፈራሪያ ከምታደርጉት ገማናን ሸፍናችሁ ንገሩን- ይዋጣለት ከትውልዱ ብክነት ጋር። ቦክስ ይጋጠም በዬዘመኑ ከፈሰሰው ደም ጋር፤ ወይንም ይቅርታ ይለምን ለወግ ለማዕረግ ሳይበቃ ከስሎ ከቀረው ትውልድ ጋር። ለነገ የትውልዱ ብክነት ፈውስ እና መዳህኒት ግልጽነት ነውና።

መዳህኒትን ሸሽቶ ማዳን ከቶም አይታሰብም። አሁን አሁን አብይ አትንኩትም የሚባለው ነገር አብሶ በቀስተ ዳመና እርስተኞች እኔ አላምነውም። ግርዶሽ ነው። ብልጠት ነው ሁልጊዜ። ቀውሱም ይፈለጋል ግን ተመስጥሮ ነው። ጫናው ይፈለጋል ግን ተመስጥሮ ነው። ምክንያቱም  የአብይወለማ መንገድ በነቀዘ ቁጥር ህሊና ሌላ ለም ማሳ ይፈልጋልና። ገብያ!

በዚህ ሰዓት ለገብያተኞች የአብይወለማ መንፈስ በእጅጉ ያስፈልጋል። ግሉኮስ ነው። አብን ለማስተንፈስ የተያዘው ዘመቻም ከዚህ ጋር የሚታይ ነው፤ ቀጣዩ ደግሞ ብአዴን ይሆናል።
የመጨረሻው የፍልሚያ ሜዳያ ወይንም የጋብቻ አዳራሽ ቀስተዳመና እና ኦዴፓ ይሆናል። እንደ ሃይል ሚዛኑ …  ሌላው ማጓጓዣ ነው …

እርግጥ አቶ ሙስጡፋ ኡመር እጅግ ለሁለቱም ድርጅቶች ለኦዴፓም ለቀስተደማነው ውራሽም ለግንቦት 7 አስፈላጊ ናቸው እንደ ጠቃሚ ሊንክ … ስለምን በዐለም አቅፍ ደረጃ ይታወቃሉ፤ ንጽህናም ይጨርስላቸውና አይባቸዋለሁኝ። ከሴራ ጋር ንክኪ ያለባቸው አይመስለኝም። ይህ ደግሞ በጦም በጠሎት የማይገኝ ነገር ነው። ለሳቸው የረዳቸው ግን አማራ አለመሆናቸው ነው። አማራነት ግማድ ተሸክሞ መኖር ነው።
·         ፖለቲካ እና የፍቅር ተፈጥሮ።  

የፖለቲካ ፍቅር ሽኝት አመሉ ነው። ፖለቲካ እና የፍቅር ተፈጥሮ ሆነ ህግጋት አይተዋወቁም፤ መተዋወቁንም አይፈቅዱትም። በአንድ ወቅት ፕ/ ብርሃኑ ነጋን አታውቋቸውም፤ ልወቃቸው ብላችሁ ብታስቡ ልታውቋቸውም አትችሉም ብዬ ነበር። አሁን ኢትዮጵያ ሄደው ስንት እኔ ነኝ ያለ የፖለቲካ ሊሂቅ፤ የሚበልጧቸውን ሁሉ መሬት ላይ እንዳስነጠፉት ማዬት ነው … አሁን ከአውሮፓ ህብረት ጋር ምን እዬሠሩ እንደሆን አይታወቅም። ራሱ ከ ኤርትራ መንግሥት ጋርም። በተገኘቸው ሰከንድ የምትባክን ጊዜ የለችም። አብሶ በነጮች አብዝተው ያምናሉ።

አንድ አምክንዮ ላንሳ እስኪ እሰቡት የኤርትራ የነጻነት ቀን አንድም ቀን ኤርትራ አሳልፈው አያውቁም፤ ያን ሰሞናቱን ታኮ የአውሮፓ ህብረት ስብሰባ እንዲያዘጋጅላቸው ይደረጋል። ስለዚህ ካለምንም መቃቃር በታቀበ ስልት ለእኔ ጥበብም ነው በፍቅር ተለያዩ። ኪዳን ለማስከበር ደግሞ ቀጣዩ ተልዕኮ ይሆናል።
ወር ባለሞላ ጊዜ ውስጥ ያለ የኢ- ግልጽነት ድራማ።

ሌላው የሽግግር መንግሥትነትን የሰላ ረቀቅ ሰልጠን ያለ ፓርቲን በዚህ ሲያዋቅሩ በሌላ በኩል ደግሞ ቀበሌ ላይ ተገኝተው ምርጫ ላይ ተሳትፈዋል። ድርጅታቸው እዬፈረስ፤ ድርጅታቸው እዬከሰመ እሳቸው ደግሞ ቀበሌ ላይ ተገኝተው ደግሞ ምርጫ ላይ ሲሳተፉ አይተናል? ይህ ነፍስ ከምን ተፈጠረ? ከዬትኛው ፕላኔት ይህን መሰል ተመክሮ ሰለጠነበት? ከዚህ መሰል ወጣገብ ፍላጎት አፈጻጻም እንደ ሮል ሞዴል ትውልዱ ምን ይማር?
የተሸወዱት በህይወታቸው OBN ላይ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ነበር። በዛ ውስጣችው የብልጭታ ታክል ለማዬት አጋጣሚሰጥ ነበር። በዚህ ውስጥ የአገር መሪነት እና ቀውጤ ቀን ላይ ያለ ጽናትን መመርመር ነው … 

ከሁሉ በላይ ግን ቻይ ናቸው። የልባቸውን ስለሚያደርጉ። ቻይነታቸው ደግሞ ለህልማቸው ስኬት መቅኗቸው ፏፏቴማ እንዲሆን አድርጎታል። ከባድ ሰብዕና በረቀቀ ስልት ንጥረ ነገርን ሳያባክኑ፣ ቆጥቦ ለጊዜ ማዳረሻ እንደ አዬፈጣጠሩ የሰው ሃይልን፤ የሰው መንፈስን መጠቀም፤ ሳይጠቅም ሲቀር ደግሞ ሰው ጊዜው አልፎ የሚገኘው በሳቸው ሌጋሲ ነውና፤ በሚገፋው ነፍስም ለሚፊጠረው ቀውስ ደንታ ቢስነት ይህን ያቻቸለ፤ መውደቁን እንደ ትልቅ አጋጣሚ አይቶ አገግሞ ነፍስ የሚዘራ፤ በዛለ ክንዱ፤ ጠንካራ ተስፋን ሰንቆ በድፍን የተመሰጠረ ምህንድስና የብሥራት ዋዜማ ላይ ለመድረስ የሚኳትን ስልጣኔ ...የሚገርመኝ ግንቦት ለጎንደሮች መልካም ያልሆነ ወር ነው፤ ለሳቸው ደግሞ ቅብዕ ቅዱስ … 

·       ክወና።

ሀምሌ 18 ለሀምሌ 19 እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2018 አንድ ህልም አዬሁኝ። ጠ/ሚር አብይ አህመድ ጉዞ ላይ ነበሩ ወደ ስሜን አሜሪካ። ህልሙን እንዳዬሁት ደንግጬ ወንበሩ ባዶ ሆኖ አዬሁት ብዬ ጽፌያለሁኝ ብሎጌ ላይ።

በዛ ወንበር ፊት ለፊት ከራስ ጸጉሩ እስከ እግር ጥፍሩ የተሰነጠቀ ግምሽ ገጽ ብቻ አዬሁኝ፤ ያ ገጽ ደግሞ የፕ/ ብርሃኑ ነጋ እንደነበር ነግሬያችሁ አለሁኝ። „ልብ ያለው ሸብ እንደ ጎንደሮች።“ እህቴ ህልሜን ስነገራት ህልሙን በስመ አብ ብላ ነበር ያማተበቸው። በትክክል ህልሙን እኔ አይቸዋለሁኝ። አሁን ያለው ሁኔታ እንዲህ ነው የሆነው … የጥምረት መንፈስ ባልተቋጨው ድብርት ላይ በሚገኘው በኢህዴግ እልፍኝ …

እውነት ብቻ የኢትዮጵያን መከራ ይታደጋል!
ግልጽ ያልሆነ ነፍስ የኃጢያትን ጉዞ ያበረታታል!

የማከብራችሁ የጹሑፌ ታዳሚዎች … ዘለግ ያለ ጹሑፍ ነው … ጽሞናችሁ፤ እርጋታችሁ፤ ስክነታችሁ መሰጠኝ፤ ስለዚህም እናንተን ያኑርልኝ ዘንድ ፈጣሬዬን ለመንኩት።
ኑሩልኝ።
መሸቢያ ጊዜ።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።