ተስፋ {የወግ ገበታ}
እንኳን ወደ ቀንበጥ
በሰላም መጡልኝ
ተስፋ።
„መዳህኒቴ እና ክብሬ በእግዚብሄር ነው።
የረድኤቴ አምለክ ተስፋዬም እግዚአብሄር ነው።“
መዝሙር ምዕራፍ ፷፪ ቁጥር ፯
ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
ከእመ ዝምታ ሲዊዘርላንድ
v
ተስፋ ጸጋ
v
ተስፋ ምህረት
v
ተስፋ መድህን ነው።
ምን ያህል እንደተጓዝኩኝ አላውቀውም? ምን ያህል እንደሚቀረኝም አላውቀውም? አለማዋቄን ስጠይቀው አለማወቁን ገለጸልኝ። ተስፋን እጠብቃለሁኝ። እ.አ.አ 2010 ተስፋ መጸሐፌ ላይ የጀርባው ሽፋን ላይ ያልኩት ነበር አሁንም እምለው ይኸው ነው ...
·
እፍታ እንደ መግቢያ …
የኢትዮጵያ
ቅኔዎች
የእኔም የኔታዎች የቀንበጥ ብሎግ ክቡር ታዳሚዎቼ እንደምን
አላችሁልኝ?
ዕለቱን ከተሰፋ ፈላጊና ተስፋ ፈጻሚ ጋር ያለው ድልድይ አስመልክቶ አንድ ወግ ቢጤ ለማቅረብ
ተሰናዳሁኝ እንሆ …
የተስፋ ጥገት ለአላዛሯ ኢትዮጵያ በእጅጉ ያስፈልጋታል። ይህ ማለት የተሰፋ ጥገት ያለው ያው
የፈረንጅ ላሞች ዝርያ ስለሆነ በገፍ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ እዮር ቢፈቅድላት ለእምዬዋ እንደማለት። የፈረንጅ ላሞች ወተተታም ናቸውና። ምኞት ...
ግን እኛ ለማይነጥፍ ጥገት ግሬራውን ወይንም ቆሬውን በገፍ ማሰናዳት ይጠበቅብናል። ታዲያ ምርቃታችን
ሳንረጋግጥ ጥንቃቄ ከኖረን ነው።
በስተቀር ምርቃትን የፈጠረም የሰጠም ኤልሻዳይ አምላክ ከከፋው ያነሳዋል … ምርቃቱን። አምላካችን ሲከፋው ምርቃቱን ማንሳቱ ባልከፋ፤ ቁጣው ካዬለ በዛው ልክ ደግሞ የርግማን ናዳ … ሊኖርም ይችላል … ማህከነ!
በድምጽ
ተስፋ {የወግ ገበታ}
·
የአላዛሯ ኢትዮጵያ ነገር …
ተሰፋ ቀረበ ስንለው ሲርቅ፤ ተስፋ ተጠጋ ስንለው በአሻጋሪ ሆኖ በቆልማማ አፍንጫው እያሸተተ
ሲታዘበን፤ ተስፋ አቀፈን ስንል ባለ ዓይናማው ጆሮውን ዘንበል አድርጎ ሲያስተውለን፤ እኛም እሱን ስንጠብቅ አሱም ብቅ እንደማለት
ቃጥቶት ሰብሰብ ብሎ ቅጡ ወደ ሰማይ ደጅ ሲሆን …
... ግን ሰው ነን እና፤ የተስፋም ተጠማኞች ነን እና ሳንታክት በመጠበቅ ተገትረን
አለን ይኸው እንዳለን …
የተስፋም ጥማተኞች ነን። የተስፋ ጥምት ትናጋችን አድርቆታል። የተስፋ ጠብታ ሳይሆን የተስፋ
ሙላት ነው እምንሻው፤ ቢያንስ አይዟችሁን ከቶ ማንን ገደለ?ማጽናናትስ?!
·
ግን? ቀጣዩ
…
… ተስፋ ማድረግ ባይኖር ከቶ እቴዋ ድንቡልቡሊት ፕላኔታችን እቴጌ መሬት ከቶ ምን ትመሰል ይሆን
ብዬ አሰብኩኝ?
ጠፍጣፋ? ልሙጥ? ሞላላ እንዲያው ነገር መዳመጫ ወይንስ ጨፍግግ ያለች ኮረኮንች ወይንስ ላጥ
ያለች ዳጥ?
ወይንስ ቡላማ አመዳም ወይንስ ጥውልግ ያለች ፋዳሳም? እኮ ምን ትሆን ነበር? ለራሷ ለእቴጌ
መሬት ተስፋ በእጅጉ ያስፈልጋታል። ተስፋ አልቦሽ መሬት ምድረ በዳነቱን
እንኳን አይፈቀድላትም ነበር።
ያው የምደረበዳውም ውስጥ የተፈጥሮ አካላት አሉና። እሷን በምደረበዳ ውስጥ አለች፤ ትኖራለች የሚያሰኛትም
ምድረ በዳ ውስጥም የተፈጥሮ ትርታ ስላለ ነው።
ስለዚህ የአፍ መሻሪያ ባለበት ቀርቶ በምድረበዳም ከእቴጌ መሬት ተምረን ተስፋን መጠበቅ ያስፈልጋል
እንደ ማለት።
·
ተስፋ ጠበቂውና ፈቃጁ በሰውኛ
ዘይቤ።
ለተሰፋ ቃል ጠበቂ መሆን በራሱ መኖርን
ይለግሳል፤ ጤናን ይሰጣል። ንቁ ያደርጋል። ሃይል ይለግሳል። አቅም
ያጠጣል። አቅም ገርገጭ በተደረገ ቁጥር ደግሞ ከትንፋሽ ማጠር ይዳናል።
ተስፋ ማድረግ ማሳያዥ ነው
ለመንፈስም ለህሊናም፤ ተስፋ ማድረግ ጤነኝነት የመሆኑን ያህል፤ ተስፋ በማይገኝበት ሁኔታ ደግሞ ተስፋን መጠበቅ ተስፋ ሳይመጣ ሲቀር
ቁስለት ይሆናል።
ስለዚህ የሰው ልጅ ተስፋ የሚያደርገው ነገር ሊገኝና ሊሆን በሚችል መልኩ ለክቶ ወይንም መዝኖ
መሆን ይኖርበታል ብዬ አምናለሁ።
ቢያንስ የተስፋን ተፈጥሮ ከሚያውቅ፤ ከሚያከብር፤ ታማኝ ከሆነ ሰብዕና ወይንም ተቋም
ሊሆን ይገባል ተስፋ መጠበቅ ያለበት። በተስፋ ውስጥ ያለው ሁለት ነገር አንደኛው ተስፋ አድራጊው ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ተስፋ ሰጪው ይሆናል።
ስለዚህ በተስፋ አድራጊውና በተስፋ ሰጪው መካከል ውል አለ ማለት ነው። መሪዎች አልፈረምንላችሁም
ሲሉ ይገርመኙል። አንደበቱ የተዘጋ መሪ መሆን አለበት ውል የለብኝ፤
ኪዳንም አልገባሁም ማለት የሚችለው፤ እንጂ በእያንዳንዱ እንደ መሪ ከአንደበት በሚወጣው ቃል ውስጥ ተስፋ አለ፤ በተስፋው ውስጥ ደግሞ ውል አለ።
ውሉ ግን መንፈሳዊ ወይንም ቁሳዊ፤ ገሃዳዊ ወይንም ረቂቃዊ ሊሆን ይችላል። በውል አድራጊዎች መሃል ያለው ዳኛ አንድዬ ልዑል እግዚእብሄር ብቻ ይሆናል ለአማንያን።
ስለዚህ ድርድሩ ባወቅነውም ወይንም ባላወቅነውም ሁኔታ ቢሆን በመሃል አደራዳሪ አንድ ሃይል ለአማንያን
እንዳለ እሙን ነው።
ስለዚህ ተስፋ አድራጊው በልኩ መጥኖ፤ አቅዶ፤ ተሰፋ ሰጪውም በልኩ ሊሰጥ የገባውን ውል ቢጥስ
እርግማን፤
ቢሰጥ ደግሞ ምርቃት ከፈጣሪው ያገኛል ማለት ነው። ውለታ ከፋዩ አንድዬ ልዑል እግዚእበሄር ነው የተስፋ
አምላክ።
ይህም ቢሆን በሚታይ በሚጨበጥ በሚዳሰስ መልኩ ላይሆን ይቻላል። ብቻ ምርቃት ሲበረታ እና ሲገዝፍ
ሙሉ ጤንነትን፤ ግርማና ሞገስን፤ ክብርና ማዕረግ ሲገኝ ምርቃት ሲሸሽ ደግሞ መባተት እና በተጨማሪም ደንጋጠነትና ብስጭት መገለጫ ሊሆን ይችላል።
ስለዚህ በመታመን ውስጥ ለሚጸድቅ፤ ለሚበቅል፤ ለሚያሰብል ምርቃት መትጋት የባለቤቱ የተስፋ ተዳራጊው
ጉዳይ ነው።
ተስፋ ተስፋህ ነኝ ካለ አንድ ተቋም ወይንም ሰብዕና ተስፋውን ለማዝለቅ እራሱን ሆኖ መዝለቅ
ግድ ይለዋል። ቋሚ ባህሬ ሊኖረው ይገባል። ውሽልሽል ያልሆነ ተቀዶ ያልተጠገነ፤ ጋራጅ የማያስፈልግው። በመዝለቅና በመክሸፍ ማህል
ሰፊ ልዩነት አለና።
·
እውነት እና ተስፋ።
እውነት እና ተስፋ የህሊናዊነት ጉዳይ ናቸው። መደወሪያው በተስፋ ውስጥ ያለው እውነት መብቀል
መቻል፤ ዕብለት መክሰም ወይንም እብለት መብቀል እውነት መከስም ይሆናል።
ይህም ማለት እውነት የተስፋ ገበሬ ሲሆን ዕብለት ደግሞ ለተስፋ ሙጃ ነው ማለት ነው።ይህ በሰውነት ተፈጥሮ ውስጥ የሰውነት የሞራልን ልኬታ ይሰፍራል። መሰፈር በወቄት ሳይሆን በህሊና ዳኝነት ነው። ይህ ደግሞ ከባዱ ፈተና ነው።
የሰው ልጅ ጎረቤቱ ባይስማማው ቤቱን ይለቃል፤ ትዳርም አልሆን ካለ ይለዬዋል፤ ሥራም አልገጥም
ካለ ይቀዬራል፤ ህሊና አሻም ካለ ግን ከዬት ይሸሻል?
ወደ መጨረሻው ጤናን አጥቶ ውስጥን እያባተቱ እያሰቃዩ ከመኖር በስተቀር ማንም እኔ ነኝ ያለ
ጀግና ህሊናውን ሸሽቶ በተረጋጋ መንፈስ ውስጥ መኖር አይችልም።
ስለዚህ ተስፋ
ሲደረግ አንድ ተቋም፤ ወይንም ሰብዕና ለተስፋ አድራጊው ተስፋ ሆኖ በውነት ውስጥ መዝለቅ ግድ ይለዋል። ተስፋ የሚያደረግው ነፍስ መኖሩ ራሱ ለተስፋ ፈጻሚው ልዩ ሽልማት ነው ላወቀበት።
ሲታደሉት ብቻ ነው ሰው በስው ልጅ ወይንም የሰው ልጅ በሚመራው ተቋም ተስፋ ማድረግ የሚችለው።
·
ተስፋ ለሴራ አልተፈጠረም። እንደ መከወኛ
ሴራ ለተስፋ የተፈጠረ አይደለም። ለሴራም ተስፋ አልተፈጠረም። ተስፋ ድንግል ነው። ተስፋ ንጹህ ነው። ተሰፋ ንጥር ነው። ተስፋ ለምለም
እሸት ነው።
ተስፋ በቅንነት ውስጥ
እንጂ በሴራ ውስጥ ተስፋ የለም። ተስፋ ለሴራ ሩቅ ነው፤ ሴራ
ስኬትም የለውም። ሴራ ከስኬት ይልቅ ውድቀትን በውድቅት እያባዘ መበራከት ዕለታዊ እንጂ ዝልቅ እና ጸደይ የመሆን ዕድል የለውም
ዲያቢሎሳዊው ነውና።
ሴራ የእውነት እንጥፍጣፊ የለበትም። ኑሮውም አመድ ነው። ትንፋሹም አመድ ነው። ቀብሩም አመድ
ነው። የተጋጋጠ፤ ፍቅፍቅ።
ተስፋ ንጹሁ ደግሞ ከሴራ ጋር ፈጽሞ ንክኪ የለበትም።
ተስፋ ከርህርህና፤ ከደግነት፤ ከአዛኝነት፤ ከፈጥኖ ደራሽነት፤ ከጥግነት ጋር ነው
የተፈጠረው።
የሚኖረውም ከእነዚህ መልካም ተፈጥሯዊ ምርቃቶች ጋር ብቻ ነው።
ራሱ ተስፋ የተመረቀ፤ ጠፈፍ
አድርጎ አንድዬ የሠራው መድህናዊ ሜሮን ነው።
ተስፋ እዬራዊ
የሐሤትም ፏፏቴ ነው። ተስፋ ዝልቅ የውልም ማህደር ነው። ተስፋ የድርጊትም የኪዳን ሥህነ - ማዕረግ ነው።
ተስፋን የፈጠረልን አምላካችን ተስፋችን ያቃርብልን!
አሜን!
የኔዎቹ ደጎቹ ኑሩልኝ።
መሸቢያ ጊዜ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ