እንኩሮ (የወግ ገበታ)


እንኳን ደህና መጡልኝ
እንኩሮ።
„እኔም ተመለስሁ ከፀሐይ በታች የሚደረገውን ግፍ ሁሉ አዬሁ
 እነሆም የተገፉት ሰዎች እንባ ነበር የሚያጽናናቸውም አልነበረም፤
በሚገፏቸው እጅ ሃይል ነበር፣ እነርሱን ግን የሚያጽናናቸው አልነበረም።“
መጽሐፈ መክብብ ፬ ቁጥር ፩
ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
21.05.2019
ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ።

·       ፍታ።

እንዴት ናችሁ ቅኖቹ የአገሬ ልጆች? ሰሞኑን ወጀቡ፣ ብርዱ፣ መከፋቱ ሁሉም ተዳምረው ቪንቲን ጨገግ አድርጓታል። አላዛሯ ኢትዮጵያስ?

የዕለቱ እርሴ እንኩሮ ይላል። እርስ ሰጥቼ መጻፍ አይሆንልኝም። እንደ እርእስ መስጠት አድካሚ ሥራ የለብኝም። ጹሑፍ ከጨርስኩኝ በኋዋላ ነበር እርእስ የምሰጠው። ዛሬ ግን አደላድዬ ለ እሱ ዘውድ ከደፋሁ በኋዋላ ነው አህዱ ያልኩት፤ ይሳካልኝ ይሆን? አይታወቅም እንፈታተን … አንላቀቅም ዛሬ …

አልኳችሁ ድሮ ድሮ ታላቅ እህቴ ነበር የምትሰጥልኝ አገር ቤት እያለሁኝ። አሁን ግን ብቻ መጋፈጥ ነው። ፈተና!

እኛ አነኮነው ወይንስ እሱ አነኮን ወይንም እኛ እና እሱ ተዳብለን ተነኳኰርን? ወይንም እንደ ዘመኑ ቋንቋ እንደ ጠ/ሚር አብይ አህመድ ሥናዊ አገላለጽ „ተደምረን አነኮርነው“ ወይንስ እንደ ቀደመው እንደ አቶ ልደቱ አያሌው ስሪት በሦስተኛ መንገድ ተነኳኰርን ይሆን? አይታወቅም። ብቻ መንገዳችን ጠፍቶብን ያለው በአነኳኰራችን ላይ በደረሰው የምህንድስና የሰልት አፈጣጠም አደጋ ይመስለኛል።

ሽሚያ ላይ መሆናችን ደግሞ ነው የሚገርመው። ስለምን ወደ ቅንጅት ተመለስን ይባላል? ያን ድል እንደግመዋለን የሚሉ ነፍሶች እስካሉ ድረስ ግድ ያላል ምልሰት ማድረግ … ደግሞ ታሪክ ነው የትውልድ ቅንጅት።

አሁን አንዲያውም እዬበሰለ ነው ከግርድፍነት ወጥቶ እዬተ እና በማጣሪያ እዬተንዘረዘረ ነው … ምን በመሰለ ሰፌድ እዬተንዘረዘረ ነው። ጎንደሮች „ሲጠሉም ሲወዱም“ እስከ ንፍጥ ልጋጉ ይላሉ እንደዛ ነው ነገሩ … ደግ ዘመን ነው አሁን ይህ ክህሎታዊ ዕድምታ በምልስት መቃኘት። መፈተሽ አለበት። የታመቀ ግን የተመሰጠረ ጉዳይ እብድ የዘራው አዝመራ ስለሆነ። እጬጌው ሂደት ብዙ ስላስተማረ ከፈረሰኛ ውሃ ሙላት ጋር የሚጋልብ ነፍስ እንብዛም ነው … ዛሬ ላይ።

በድምጽ።

እንኩሮ (የወግ ገበታ)


·       ንደቱ በጦፈ ንዴት።

የተናደደው ኢትዮጵያዊ አዬር ነው። የተናደደብን ደግሞ በእኛው ፍልስልስ ነው። ያለተናኮረ፤ ያልተናደ፤ ያልደፈረሰ፤ ያልጎሼ ነገር የለም። መናኰር ነው አዬሩም ተአዬሩም ጋር፤ ጠሐዩም ከጠሐዩ ጋር፤ ጨለማውም ከጨለማው ጋር፤ ወጀቡም ከወጀቡም ጋር፤ አውሎም ከአውሎ ጋር መናኮር።  ድብርታሙም ከድብርታሙ ጋር። የቅኔው ልዑል የብላቴው ጸጋዬ ገ/መድህን ነገር ተዚህ ላይ ይመጣል … ፈራን ፍቅር ፈራን …

ሳንዋደድ መዋደድ፤ ሳንቀራረብ መቀራረብ፤ ሳንዋዋጥ መዋዋጥ፤ ሳንፋቀር መፋቀር ብቻ ባልሆንበት፤ በሌለንብት የሰውኛ ተፈጥሮ አለን ብለን ስንመዘገብ አለመኖራችን የሚነግረን ስክነት ያጣው አየሩ ነው። አዬሩ ቦጅቦጃውን ሰብዕና የመሸከም አቅም አነሰው። ክልፍልፉን ነፍስ የማድመጥ አቅም አጣ።

ሚዲያ ላይ የሚታዬው ትዕይንት … ቁጥባ የለም መልቀቅ ነው፤ ትዝብት የለም መልቀቅ ነው። ይሉኝታ የለም መልቀቅ ነው። መልቀቁ ደግሞ መለቅለቅ አመጣ እና ከላይ አስከታች፤ ከታች እስከ ላይ ማላከክ - መካሰስ - መፎጋገር - መናቆር በቃ ይኸው ሆነ አዳራችን። ስናሳዝን …

ክረምት እዬመጣ ነው። ወገን ሜዳ ላይ ፈሷል። ካላፈው ዘመን የተሻለ ተስፋን ሰነቀን አምና እና ዘንድሮ ካለፉት ዘመናት ይሻላል ሲባል፤ በከፋ ሁኔታ ሰው መሆናችን ፈታኝ የሆኑ ቁልል ሞጋች አምክንዮዊ ጉዳዮች አሉ። ከሰው ሰው ስንለይ እኛ የሰው ዘርን መሆናችን ሳትነው። ከሞትም፤ ክህመም፤ ከጉዳትም፤ ከመፈናቀለም ሰውን ከሰው እንለያለን …

·       ርቃትና ቁጣው።

ሳይታክቱ፤ ሳይደክሙ፤ ሳይለፉ ከሰማይ መና የወረደ ያህል ፍቅር በምድሪቱ ሰፈነ። እልፍ አላፍ ሁሉ ለፍቅር እልልታ አወረዱ ተቀባይ ጠፋ። አስተዳዳሪ ታጣ። መሪ ታጣ። ሙሴም ታጣ …  

ባለፈው ዓመት እና በዚህ ዓመት ያልተዘመረለት፤ ያልተመሰከረለት፤ ላይ ያልወጣ፤ ያልተሸበሸበለት የፖለቲካ ሊሂቃን እምብዛም ነበር። ጋዜጠኛውም፤ አክቲቢስቱም፤ የፖለቲካ ሊሂቁም የእናመሰግናለን ማህሌት አቋቋም ተደርጎላቸዋል።

ግን አቅም የለም። ያጣኽው ዕለት ነው የምታውቀው ያገኘኸውን ጸጋ እና በረከት። አሁን ከሶሞኑ ጠ/ሚር አብይ አህመድ አዲስ አባባ ላይ ሲያጸዱ ተመልከቻለሁኝ። እኔን ብያላሁኝ ፍግም ሊሉ ሲኳትኑ። ባለፈው ሰሞንም መከላከያ ሚ/ሩ አቶ ለማ መገርሳ እና ካቢኔያቸው አብረው ተሰልፈው አይተናል … ወር ሞላው ይሆን?
ፎቶ ከሳተናው ድህረ ገጽ የተወሰደ።


አዘኔታዬ ግን የሰው ሳይሆን የሰማይ ስጦታ ተረግጦ ያን ሰብላማ መክሊት እንደ አልባሌ ነገር አሶ፤ ያን በረከት የትም ወርውሮ፤ ያን እዬራዊ ምርቃት እራቀኝ ብሎ ፈርዶ እንደገና ደግሞ ሌላ ድካም፤ እንደገና ደግሞ ሌላ መታከት፤ እንደገና ደግሞ ሌላ የዝና ማጠራቀሚያ ቋት ፍለጋ ልፋት መኳተን አያስፈልግም ነበር።

በምድር እንደ እሳቸው እና እንደ ጓዳቸው አቶ ለማ መገርሳ መታደልን ያፈስ አልነበረም። የት ነበራችሁ ታሪካችሁ ይመርምር? ተፈተሹ - ተበርብሩ ያለ አልነበረም። እንደወረደ ተቀበልን፤ እንደወረደ አነገስን፤ እንደ ወረደ እጬጌ አደረግን ዘውድ ደፋን ተክሊልንም አከልን፤ ግን ውሃ የበላው ቅል ሆነ ድካማችን … ካልቾ ሆነ ሥጦታችን … እዬተመረጠ የዞግ ሊሂቅ ሙገሳና ድልቅቁንም ይሁን ብለን ተቀበልንም አልሆነም …

በንጽጽርም አቶ በቀለ ገርባ እና ፕ/ መራራ ጉዲናም፤ እንዲሁም ቲም ጃዋር፤ በተጨማሪም ፕ/ ብርሃኑ ነጋ እና አቶ ዳውድ ኢብሳ ተዘመራላቸው የቀኑበትን መወደስ ተሸራቸው፤ በተሰጠው ልክ መመለስ ቀርቶ በተሰጠው ልክ ማሰብ አልተቻለም።

ለአንተ ሲል አደባባይ የተረሸነልህ ምንም ነው የዶሮ ደም … አይዋ ኦነግም ደም አማራው፤ ደም ጠማው የሰው ደም ፍሰት እና የሀብት ዘረፋ፤ እንዲሁም ህውከትን አወጀ …  ለራሱ ወገኖች ቆምኩለት ላላቸውም አዘኔታ እንኳ አልሰራለት አለ … የወ/ሮ ታደሉ ዕንባ ዛሬም አልደረቀም … እንደ አዋሽ ወንዝ ይፈሳል … ይፈሳል … ይፈሳል …

ምስጋና፤ አክብሮት ትህትና ፍቅር የተቸራቸው ሁሉ ደፉት። የሰው ልጅ ስለ ሰው ልጅ ስቃይ እንዴት ግድ አይለውም? እንደምንስ ስለ ትውልዱ ብክነት ግድ አይሰጥም?

·       ንፋሽ ለማግኘት የወረፋ ትመት።  

የአብይወለማ መደመርና ኢትዮጵያዊነት ሱሴ ነው በውጭ አገር ያን ያህል ሙሉ ቀን በተርታ ወገን ተሰልፎ ትንፋሽን ለማግኘት የወጣውን ህዝብ ሳስበው የሰው ህሊና ለሰው ያልተሰራ መሆኑን ግብረ ምላሹ አሳይቶኛል። ግን እኛ ምኖች ነን? እነሱስ ሊሂቃኑ?  
አገር ውስጥም ህዝብ በራሱ ወጪ፤ በራሱ ጊዜ፤ በራሱ አቅም አብሶ አማራ ክልል፤ አዲስ አበባ፤ ደቡብም እንዲሁ የነበረው የድጋፍ መንፈስ፤ የነበረው የብሩህ ተስፋ አቀባባል ወደርየለሽ ነበር። እውነትም አይመስልም። ሆሊውድ ኪኖ …

ያ የመንፈስ ጥሪት በውል፣ በአግባቡ፣ በመርህ ደረጃ ቅቡልነት አግኝቶ በታቀደ እና በታሰበበት ሁኔታ ኢትዮጵያዊ የሆነ ፖሊሲ ተነድፎለት አዲስ መንገድ ሊጀመር ሲገባ እንኩሮ ሆኖ አረፈው።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል አፍስሶ መልቀም፤ ለቅሞ ማፈሰስ፤ ቀዶ መስፋት፤ ሰፍቶ መቅደድ … ባህሉ ይሄው ነው። አድማጮቼ ይህን የተናገርኩት እኔ ዛሬ አይደለም … በቀደመው ጊዜ ነው … የዚህ ሁሉ መሰረታዊ ጉዳይ ግን ፍላጎታችን ጋር ተዋውቀን አለመተወቃችን ነው። በውነቱ ፍላጎታችን አናውቀውም። ለእውነት ደግሞ ፈሪዎች ነን።

የሚገርመውና የሚደንቀው ይህን የሚሞግቱ ነፍሶች ደግሞ አሁንም ወጀቡ በእነሱ ላይ እንደተለመደው ማዬሉ ነው። „ለውጥ አደናቃፊ“ ይሏቸዋል። ያን የመሰለው  የኢትዮጵውያን የነፃነት ተጋድሎ ኢትዮጵያን ኦሮማይዝድ ለማድረግ አልነበረም።

እያንዳንዳችን በአቅማችን ልክ አይደለም ከአቅማችን በላይ ህወሃት መራሹን ግንባር ኢህዴግን ሞግተናል፤ ተፋልመናል። ጤናችን ገብረን፤ ኑሯችን ገብረን፤ ወጣትነታችን ገበርንበታል። ተጋድሎው ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ አድርጎ ለማበልጸግ ነበር። ቢያንስ ጥበብ ሰው እንዴት ይህን ማዬት ይሳነዋል?

ሳይከፈለው፤ ሳይቀለብ የደገፈ፤ የረዳ ያከበረ ትህትናን የቀለበን ወገን እያሳደድክ፤ ሚሊዮንን እያፈናቀልክ፤ መንፈሱን በስጋት ሰንገህ የተወለደበትን ቀን እያስቆርክ ለውጥ ለውጥ ማለት መቼም ለእኔ እብደት ነው።

ስህተት ላይ ያለው ኦዴፓ በእያንዳንዱ እርምጃው፤ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴው እርማት ማድረግ እንዳይችል ትክክል ነኝ ብሎ እንዲሄድ ነው መከራ እዬታዬ ያለው። ይህ ደግሞ ለዞግ ማሰብ ካልሆነ በስተቀር አገርን የሚያድን አይደለም።

የተማረውም፤ ያልተማረውም፤ ሊቁም ተርታውም፤ የሥነ ጥበብ ሰውም መለዬት አልተቻለም። ቢያንስ ሰው መሆን እንዴት አያቻልም? እስር ቤቶች በፖለቲካ አተያይ ምክንያት መታሰርን ተግ በሎላቸዋል የሚሊዮኖች መፈናቀል፤ እርዳታ እንዳያገኙ ማድረግ? ለሚዲያ ችግራቸው እንዳይገለጥ ማድረግ፤ አንድ ውህድ የነበረን ህዝብ ለመነጣጠል የሚደረገው ህጋዊ ጉዞ በምን ቀመር ይሆን ትክክል ነው ብለህ እምትሟገትለት?

እዬሆነ ያለው በአካልም በመንፈስም፤ ፍራቻ፤ ስጋት፤ ግለት ንጹህ ዲስክርሚኔሽን የት ይውደቅ? መቼም አንድ  የጥበብ ሰው „ ለዛውም አገር ማለት ልጄ“ላለ … ታላቅ የአገር አንጡራ መንፈስ ስለ ዴሞግራፊ ፍልስፍና ድንብስ ሲሆን ከማዬት በላይ አሳፋሪ ነገር የለም።

ለመሆኑ የት ላይ ነን? ጉዞው ወደዬት ነው? መጨረሻውስ ምንድን ነው? ምን እና ምን አገጣጥመን ነው፤ ምን እና ምን አጣብቀን ነው ትውልድ ልንገነባ ያሰብነው …ይሆን?  
ተስፋ ሰጪ ነገር ተስፋ ቢደረግ ባልከፋ ግን ተስፋ ሰጪው ነገር ራሱ በመርዝ የተቀመመ ነው። ያ መርዝ ደግሞ አገርን እንደ እሰተ ጎመራ የሚያፈነዳ ነው። አላዛሯ ኢትዮጵያ ልትፈነዳ ተቃርባለች። ስለዚህ መተችት ሲያንሰው ነው የአብይወለማ ሌጋሲ …

ትችቱ እነሱንም ሊያድን፤ እነሱንም ከገቡበት ረግረግ የሚታደግ ነው። አዝለውት ሳይሆን ጸንሰውት ከሚዞሩት ስውር ፍላጎት ጋር መፋተት ግድ ይላቸዋል። መቼም አንድ ሰው ሁለት እግር አለኝ ብሎ በአንድ ጊዜ ከሁለት ዛፍ መውጣት አይቻለውምና። እነሱ ስለስውሩ ፍላጎታቸው ስኬት ጥድፊያ ላይ ናቸው፤ ነፍስ ደግሞ በዬደቂቃው እዬረገፈ ነው። መርገፍ በ አካል ብቻ ሳይሆን በመንፈስም ነው።

ተፎካካሪ/ ተቃናቃኝ/ ተቃዋሚ የሚባለው ስለምናውቀው፤ ያልተገባ ግምት እና ግዝፈት ሰጥተን ስለምንታመስበት ነው እንጂ ዕድሉን ቢያገኝ ኢትዮጵያን የምታክል አገር ለመሸከም መጀመሪያ ሰው ሆኖ የመገኘትን ፈተና ማለፍን ይጠይቃል። ስደት ላይ ያለው ኢትዮጵያዊ ሰው ነውና። እኔም ሰው ነኝ። እኔም ዜጋ ነኝና። አንድ ተብሎ ዜጋ የሚቆጠረው እኔንም አክሎ ነውና።

·       ው መሆን ካልተቻለስ?

ሰው መሆን ካልታችለ የሰው መሪ መሆን አይቻልም። መሪ መሆን የሚቻለው የግኡዙ ወንበር ብቻ ይሆናል። ፈርተህ መሪነት የለም። መሪነት አክተርነት አይደለም። መሪነት ሻማነት ነው።

ሻማ ለመሆን የፈቀዱ ደግሞ በህይወት የሉም። የሰው ሞት፤ የሰው ስቃይ፤ የሰው መጎሳቆል፤ የሰው ፍትህ ማጣት፤ የሰው መገለል ካልጎረበጠህ መሪነትህ የወንበር እንጂ የሰው ሊሆን አይችልም። ስለዚህ የግዑዝ መሪ ለመሆን ከሆነ ድርድሩ፤ ስምምነቱ እና ጫጉላው ያው ድምጸ ጉዑዝ ድምጽ ይሁን።

የሆነ ሆኖ ዛሬ ዓለም በመሰከረው ልክ ለጥገናዊ ለውጡ ዕውቅናው ቀጥሏል ወይ? ነገስ ይቀጥላል ወይ …? አይመስለኝም።

ስለ ሰው ልጅ የሚጨንቃቸው፤ የሚጠባቸው ያልተወለዱን፤ ያልተዘመዱን ግን የመርህ ሉላዊ ዜጎች ኢትዮጵያን አይረሷትም። አንድዬም እንዲሁ። በዚህ እንጽናናለን።
የእኛ ነገር እማ እንኩሮ ነው … አሁን የሚያሳዝነው የአፍሪካን ዕጣ ፈንታም አብረን ዳፍንት ማድረጋችን ነው … ለፓን አፍሪካም ታላቅ ውድቀት ነው የአብይወለማ ሌጋሲ እንዲህ እንኩሮ ሲሆን …

·       እርገት ይሁን …

„እኔም ተመለስሁ ከፀሐይ በታች የሚደረገውን ግፍ ሁሉ አዬሁ
 እነሆም የተገፉት ሰዎች እንባ ነበር፤ የሚያጽናናቸውም አልነበረም፤
በሚገፏቸው እጅ ሃይል ነበር፣ እነርሱን ግን የሚያጽናናቸው አልነበረም።“

ከቶ አይዟችሁ ማንን ይገድላል?! „አብይን በምርጫ እናሸንፋዋለን“ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ የሚሻው ህይወቱን የሚኖርለት መሪ ነው። መከራውን የሚጋራ፤ ጭንቁን የእኔ የሚል፤ ፍዳው የሚቆረቁረው እና የሚጎረብጠው … ሰው የሆነ ለመቅለጥ የተሰናዳ እንጂ ለዝና የሚያሸበሽብን ልሙጥ መንፈስ አይደለም። 

ማሸነፍ ማለት ለእኔ ያነ ነው … ለመቅለጥ መወሰን፤ መቁረጥ እና መማገድ … ፊት ለፊት ለካሜራ እንደምትሰናዳው በቃጠሎ ውስጥ መቀቀልንም መፍቀድ ግድ ይላል፤ ምቹ እና ደልዳለ ቦታ እዬፈለጉ ከመለመጥ ….  ውዶቼ ይብቃኝ …

ትእግስት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል፤
ፍቅርም ሲያልቅ ትእግስት ይሰደዳል።

„ልብ ያለው ሸብ“ እንደ ጎንደሮች።
ኑሩልኝ ቅኖቹ
መሸቢያ ጊዜ።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።