ድምጽ አልባዋ።


እንኳን ደህና መጡልኝ
ድምጽ አልባዋ የኢትዮጵያ እናት
ለፖለቲካ አክተሮች የሊኳንዳ ቤት
 ማዘጋጀት አይታክታትም … ዛሬም።

„ብልህ ሰው መጽሐፍን መስማት ይወዳል።
የሚጠራጠር በመጽሐፉ የማያምን ሰው ግን
 በጥልቅ ነፋስ መካከል እንደምትጉላላ
 መርከብ ይሆናል።“
መጽሐፈ ሲራክ ምእራፍ ፴፮ ቁጥር ፪


የኢትዮጵያ አዬሩ ስትራፓ ያዘው። ጓጐለ። ውዶቼ እንዴት ሰነበታችሁልኝ? ደህና ናችሁ ወይ? እስቲ ድብርታሙን ዛሬን እንዲህ አብረን እንቃኛው …

ስክነት የት ይሆን የሚሸመተው? ውስጥሰ ከእርቃንነት መቼ ይሆን ለእራፊ የሚበቃው? ከቶ በቃን ህውሃት መባልን ትናንት በአኽትዮሽ መንፈስ በወል ማዕዶት የታለፈው ማዕደኝነትንም ጎበኘውን?

የትውልዱ የሃሳብ ብክነትስ ማቆሚያ ለመቼ ተቀጠረ? መቼም አዘኔታ የለም ትውልዱን በዬዘመኑ ለቋያ ለመማገድ። ሥልጣኔ የለለን መሆኑን ሳስበው አይሆኑ ሆኖ ነገ ጠቆረብኝ።

እንደዚህ ሰሞናት ባዶነት ተሰምቶኝ አያውቅም። እንዳሻኝ እምቀምረው ስፈለግ ግጥሙን፤ ስፈልግ ሀተታውን፤ ስፈልግ ልዩ ሪፖርቱን ስፈልግ ወጉን እንዳሻኝ በብራና ወክ እንዲህ ያላልኩበትን ያህል ሰሞናቱን ግን አልቻልኩም። ድብርት ቤቴ፤ ድብርት በብራናዬ ላይ ተዛናከተባቸው እንዳሻቸው …

ክብረቶቼ የቀንበጥ ሚዲያ ታዳሚዎቼ እኔ መጻፍ ሥራ ሆኖብኝ አያውቅም። በህይወቴ ቀላሉ ሥራ መጻፍ ነው። ሰሞናቱን ግን በዬአቅጣጫው ያለውን እብለቱን፤ ፌኩን፤ ንደቱን፤ ቦክሱን፤ ውስጥን ከፍቶ እንዳሻህ መባሉን፤ ቁጥበንት መሸጥ መለወጡን፤ መታቀብ መቀበሩን ሳስተውለው ግን ያ ሁሉ ድካም ለምን ስለምን አስፈለገን ይሆን?

ብዕሬም ብራናዬም ሱባኤ ላይ ነበሩ … ዛሬ የሙት ሙቴን ተሟግቼ ነው ይችን ልል የፈቀድኩት። እሰከመቼም ፊታውራሪ ድብርት አቅም ኖሩት ከእኔው ጎጆ እንደሚሰነብት አላውቀውም።

በጣም ረቂቅ በሆነ ሁኔታ አንድ ሰው የነፃነት ተጋድሎን ሲቀላቀል የሚያጣው ነገር አለ። ቢያንስ ጊዜውን፤ ቢያንስ የውስጥ ሰላሙን ትልቁን የመኖርን ግዴታ ትተን፤ ትልቁን ዕድሜ እያመለጠ መሄዱን ትተን፤ ትልቁን የሚወዱትን ዓይተው የማያምኑትን እናትን ያህል ነገር ሳያዩ ሳያገኙ ለመቅረት መወሰኑን ትተን ማለት ነው … እናት አለም ናት።

እናት አገርም ናት። እናት ድምጽም ናት እሷንም አስክዶ ፖለቲካ ለዛውም ለእፉኝቱ ፖለቲካ በቃ የማይችሉትን ሁሉ መሸከም …

ለማን ሲባል? በቁማር ለተዥጎረጎረው እፉኝቱ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሲባል … አሁን አሁን እማ እንደማስፈራሪያም እዬታዬ ነው። ለዛም የማስፈራሪያውም ስለቱም በውስጥ መስመር በስልት ተደራጅቶም ነው …

ብቻ ያ ሁሉ ድካም፤ ያ ሁሉ መታከት በጀንበር ጨዋታው ፈረሰ ዳቦው ተቆረሰ ሆነ። እኔ 10 ዓመት ዕድሜ ላይ እያለሁኝ እቃ እቃ ጨዋታ ላይ መሸት ሲል „መሼ ቤት ግቡ„ስንባል ቤት ብለን ያበጀነውን ፍርስርስ አድርገን ወደዬቤታችን እንደምንሄደው ማለት ነው፤ ሌላው ቀርቶ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የአንድ የፖለቲካ ሊሂቅ ሰብዕና ስንት ጊዜ ይገልበጥ? መላ አጣን። የውነት መላ አጣን።

የፈለገ ብንከታከት፤ የፈለገ ብንሟገት ትናንት ባለፍነበት በዛ አሜኬላ ሸጎሬ መንገድ ዛሬም ምርጫችን ማድረጋችን ነው እኔን ባዶነት እንዲሰማኝ አድርጎታል። በቀጣይ ቀናት፤ ወራት፤ ዓመታት ደግሞ ይኸው መናቆር ድገሙን ሰልሱን ማለቱ አይቀሬ መሆኑን ሳስበው ነገ ጥላሸት ሆነብኝ።

ያን ጊዜ ተብሎ ደግሞ ሌላ ዜማ ይመጣል ዕድሜን ከሰጠን … አንድ ሰው እኮ በአንድ ቀን ተፈጥሮ በአንድ ቀን አይጎለምስም። ሰው የብዙ ሂደት ውጤት ነው … ጨዋታ በሰው አፈጣጠር እና ሥነ - ህይወት።

የሚገርመው አለመተማመንን አምናችሁ ተቀበሉም ደግሞ ሌላው ጋዳ ነገር ነው። ነገም ያው ስለሚሆን እኔ ለወገኖቼ እምመክረው ጎራ ለይቶ መፋተጉን፤ አቅምን ማራገፉን ለእጬጌው ሂደት መሸለሙ የተገባ ይመስለኛል። አቅለ ቀላል ሆን።

ደርባባነታችን ተነነ። ውቃቤ እራቀን፤ ክብደታችን ቀነሰ፤ ልቃችን ተጎለጎለ፤ ዓውዳችን ተዝረከረከ …. ግርማችን የተላመጠ አገዳ ሆነ … በዚህ ማህል ስንቱ ተቀቅሎ አምኖ ሁለመናውን አባከን አፈር ውስጥም ኖረ?

ነገስ? ነገም በዚኸው ባልተገለጠ መንገድ ደግሞ የፈረደበት ትውልድ ይማገዳል፤ ይቆሰቆሳል፤ ይታጨዳል፤ ሰላሙን ያጣል።

ዬዬዘመኑ የሰው ልኳንዳ ቤት አሰናጇ ድምጽ አልባዋ የአላዛሯ ኢትዮጵያ እናትም ትገብር ወገቧን ታጥቃ --- ለዋና ካረክተር አክተሮች ዝና፣ መወድስ፣ ዝማሬ እና እልልታ።

ትወልዳለች ዘመን እሰከ ዘመን አሳድጋ ታስረክባለች … አስረከባም እናመሰገናለን ቀርቶ ተመልሶ ልጇ ደግሞ እንደ ገና የቀወስ ማዕድ አሰተናባሪ ይሆናል … ሲያሻም ያ ግማዱ ተረስቶ ከቤተክርስትያን እንደ ገባ ውሻ ሲንከለከል ደግሞ ታያለች፤ በህይወት ያለችው። በአካል በህይወት የሌለችውም በአጸደ ነፍስ።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት እፉኝት ነው። ወልዶ የማያሳድግ። አሳድጎ ለወግ ለማዕረግ የማያበቃ፤ ሲረገዝ አባቱን ሲወለድ እናቱን ገድሎ በአዲስ ሽል ፑፓ ሆኖ ብቅ ይላል … ያው ለንደት

… ለዛ ደግሞ አይታክቴ ታመርታለች … መቼ ደርሶ፤ ደርሳ ተድረው ተኩለው ስትል ለእፉኝቱ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ትገብርና ዕድሜዋን ሙሉ እንዳለቀሰች ታልፋለች … ህቅታዋ መከራን እንዳዘለ ይሆናል።

ውጭ አገር ተኖረ አልተኖረ፤ ተማረ አልተማረ፤ የፖለቲካ ሥልጡኑነት ደረጃው ያው ተዛው ነው። በሰው ግብር ብክነት የተደወረ። የሰው ልጅን የሰውን ቤት አቅዶ ነው የሚደራጀው።

ዛሬም እንደ ትናንቱ የትውልዱ ብክነት ያንገበግበኛል። እኔም የዛ ሰለባ ነኝና። ዛሬም ስጋት ነው፤ ዛሬም ሽብር ነው፤ ዛሬም ግለት ነው፤ ዛሬም ልዩነት ነው፤ ዛሬም አንዱ የክት ሌላው የእንጀራ ልጅ ነው። ዛሬም አገር አልባነት …

ይህም ሆኖ መከራዋ ላለቀ አላዛሯ ኢትዮጵያ በቀደመ የተቀቀለ፤ የቆሰለ፤ የተከነው ቢያንስ መለያየዬትም ቢኖር ስለምን ተከባብሮ አይሆንም? ህም!
ሌላው ትናንት ተለዬሁ ብለህ ህዝብ ታሰለፍና ዛሬ ደግሞ በአዲስ ሽወዳ አዲስ ማርቀመስ ትናጋ ይዘህ ደግሞ ብቅ ትላልህ። ይህስ ከዬት ይመደብ ይሆን? ስንት ጊዜ የሰው ልጅ እንደ ሽንብራ ቂጣ ይገለባበጥ?

እኔ ሳስበው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሊሂቃን በህይወታችሁ ምን ያስደስታችኋዋል ተብለው ቢጠዬቁ በዬዘመኑ በትውልዱ ህሊና ላይ ጢባ ጢቦሽ መጫዋት ሳይሉ አይቀሩም።

ወር ሳይሞላ በአንድ ጉዳይ ሁለት ጊዜ ትገላበጣለህ? ካልተለዬህ አልተለዬሁም፤ ከተለዬህ ደግሞ ጠፈፍ ብለህ፤ ክውን ብለህ ሳትነካካ መቀመጥ።

ሳትለይ ተለዬሁ ስትል በዛ ስር ስንት ነፍስ ነደደ፤ የሚገርመው ደግሞ ተለዬሁ ላልከው ነገር ሆነህ ሳትገኝ መለዬቴን ተቀበሉ ግን ቀዩ የመሰላችሁ አረንጓዴ ነው ማለት በተደሞ ሲሰላ ግን ለስንቱ ዘመን ያሰኛል … ስለምን ይሆን እናት አገር እንደ ጥንቸል የመሞከሪያ ጣቢያ የምትደረገውስ …

አንድ ጊዜ ዋሽ፤ ሁለትም ይሁን፤ ሦስትም ይሁን ዘወትር? የሰው ልጅ እኮ ከቅጠፍትም፤ ከዕብለትም፤ ከሃሰትም፤ ከማስመሰለም ጋር አልተፈጠረም። የሰው ልጅ ሲፈጠር በድንግልና ጽዳት ነው። አፈጣጠራችን እራሱ አቆሸሽነው። ድኖ በማይድነው በእፉኝቱ የኢትዮጵያ ፖለቲካ …

ትእግስት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል
ፍቅርም ሲያልቅ ትእግስት ይሰደዳል።

ናፍቆቶቼ ኑሩልኝ።
መሸቢያ ጊዜ።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።