መጸሐፍቶቼ ልጆቼም ነፃነቶቼም ናቸው!
"የሰው ልብ መንገድን ያዘጋጃል፤ እግዚአብሔር ግን አካሄዱን ያቃናለታል" መጽሐፈ ምሳሌ ፲፮ ቁጥር፱
ተስፋ ይመጣል
ተስፋም ይሄዳል
ተስፋም ያነጉዳል
ተስፋም ይክሳል ... አንድ ቀን ... ይጠበቃል!
እንኳን በደህና መጡልኝ
መጸሐፍቶቼ ልጆቼም
ነፃነቶቼም ናቸው!
ልጆችን መንከባከብ ደግሞ
የማህበረሰቡ ተግባር ነው።
ተስፋችንም በፖለቲካ ሊሂቃኑ ሳይሆን
በማህበረሰባችን ብቻ ነው!
v እፍታ።
የኔዎቹ የኔታዎቼ እንዴት ናችሁ የአገሬ ልጆች? ደህና ናችሁ ወይ? ማህበረሰባችን በዬአካባቢው በመንፈስ የታሠሩትን ልጆቹን ማስፈታት ይኖርበታል። ስደት የምንኖረው ባለመክሊት ልጆቹም በስውር ካቴና ነው የባጀነው ውጭ አገር። አብሶ አማራነት
ቀራንዮ ነው።
ማህበረሰባችንም እራሱን በሽንገላ ሳይስከበብ ነጥሮ መውጣት ይኖርበታል። ስለሆነም ለድጋሚ ዕስርም ራሱን ማሰናዳት
እንደሌለበት አበክሬ አስገነዝባለሁኝ። ታገሽነቱ በተግባር ይመሳጠር።
አሁን ያለው የአገር ውስጥም የውጭ ጭቆና ዓይነት እና ስልትና የጭካኔ ተመክሮ የጫጉላ ሽርሽር
እንዴት ሁለቱን አቀናጅቶ ጭቆናን ሉላዊ በማድረግ ንቁ፤ ትጉህ ኢትዮጵውያንን በሁሉም አቅጣጫ ማፈን እና ሰላማቸውን ማስጣት ይቻላል
ነው ምክክሩ። ይህ ስለላ እሰከ አውሮፓ ህብረትም ይዘልቃል።
ውሉም ጋብቻውም ይኼው ነው። ሞጋች ማህበረሰብ አይፈለግም። ግን ስንቱን አግልለው፤ ስንቱን ከጫዋታ ውጭ አድርገው እንደሚዘልቁት ወፊቱ ትጠዬቅ። ግሎባላይዜሽኑን በኢጎ አፍነው ማስቀረት ከቻሉ ይሞክሩት። ጥቂት ሰዎች ህይወታቸውን ሊያጡ ይችላሉ ... ግን እልፎችን ያፈራሉ ...
ስለሆነም የአፈና እጩን እንደ መነሻ ከቁምነገር ወስዶ ሰላማዊ በሆነ መልኩ አሻም ማለት ልባምነት ነው። ነፃ የወጣ ካለ፤ ከወረራ
መንፈሱ የተረፈ ካለ፤ ግን መብቱ ነው አብሮ ይገስግስ አብሮም ያንግሥ፤ አብሮ ለጥ ሰጥ ብሎ ቢያሰኘው የጸጋ፤ ቢያሻው የ አምልኮት ስግደቱን ያስነካው።
ያላዋጣው ደግሞ በተጠናከረ መልኩ ተጋድሎውን
ይቀጥላል ሥርጉተን ጨምሮ። ዕውነትን ፍለጋ ነፍሴ አትቦዝንም። እራሴው እኔው በእኔው ላይ ነው ምርምር እምሰራው። የምርምር ማዕከሏ እኔው ነኝ።
ነፃነት አለ የምለው ነፃነቱ ከእኔ ሲጀምር ብቻ ነውና። እዚህ ውጭ አገር ከባጀብኝ ከአሳሬ ጋር ለተዳበለ ነውጥ ለውጥ ነው ብዬ አላደገድግም። በይፋና በአደባባይም በባድማ ነጻነት እየተረጋገጠ መሆኑን እያስተዋልኩኝ ነው። ለመሻል እንጂ ለመባስ አልታገልኩም።
የእኛ አልበቃ ብሎ አሁንም ስደት ውጡ እያለ መንግሥት ይፋዊ ዕወጃውን መቀጠሉን እያዳመጥን ነው። የመቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ ጉዳይ በአዘቦት ጉዳይ አይታይም። በሌላ በኩል ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ደግሞ ወደ አገራችሁ ተመለሱ ይላል፤ በሰማዩ አውቶብስም አሳፍሮ አንቀባሮ አገር ያሰገባል።
እኔ ባርነትንም አድርባይነትም ልምምጥንም ፈቅዶ የኖረ ትውፊትም፤ ውርስም ቅርስም የለኝም። ሎሌነትን የፈቀደ ስብዕናም የለኝም። ልብ እንዲገጠምልኝም አልፈቅድም። ገዢዬ የነጠረ ዕሳቤ ብቻ ነው። ያደገና የበቀለ ሰውኛና ተፈጥሮኛ እውነታዊ መንፈስ ነው እኔን ሊመራኝ የሚገባው።
እኔ በመክሊቴ፤ በአቅሜ የችሎታዬን ላበረክት በምችልበት መድረክ እንዳልንቀሳቀስ
በስውር የነበረው ኢ- ተፈጥሯዊ የደቦ መከራ ቃል አይገኝለትም። ዛሬም ይኸው አገር ላይ ለተጨማሪነት ባርነት በአዲስ ገበርዲን ማዬት መቼም የነፃነት ሞት ዕወጃ ነው። ያለው የኢህዴግ አፈናም አልተቻለም እንኳንስ በደቦ አንድ ተሁኖበት።
እኔ ነፃ አልነበርኩም በነፃነት አገር ውስጥ፤ አሁንም አይደለሁም። ያሳድዱኛል። ስፈጠር
ግን ነፃነት ተሰጥቶኝ ነው። ነገር ግን ትናንትም ዛሬም እስረኛ
ነኝ። ግን የካቴናውን ግርግም ፈርቅቄ እሰከዚህ ድረስ ታግያለሁኝ።
ቀሪውን ደግሞ ተጋድሎ አብራችሁኝ ከእኔ ጋር ትጋፈጡ ዘንድ በአክብሮት የኔታ ወገኖቼን አሳስባችሁ አለሁኝ።
ይህ ማለት ምን ማለት ነው ሥር - ነቀሉ የተጋድሎ አድማስ በሁሉም ዘርፍ መሆን አለበት፤ ለዛም መትጋት። ያው ከዜሮ እንደ ጀመርን ይታወቃል። ያለንን ሁሉ ለኦነግ ድል አስረከበን።
የነፃነት ሲሶ፤ የነፃነት እርቦ የለውም። አማራ ሆኖ መፈጠር ጥቁር ግማድ ነው። ነፃነት ስለሚነገረው ሳይሆን ስለ ዘመናዊ
ባርነት ነው ተጋድሎው ሲምታታ የነበረው። ትናንትም ዛሬም ግብረ ነገሩ ይሄው ነው። እስሩ ቀላል አልነበረም - ዛሬም። አሁን ደግሞ ዘሃ እና ድር ሆነው ሚስማሩን በጋራ እያጠበቁት ነው። አሁን ሌላ አቅም ዲያስፖራው ላይ እንዳይወጣ ነው ሌላው ቁጥር ሁለት ዘመቻ ... ባንዳነት በዓይነት ...
አሁንማ ፈጣሪ ደግ ነው ፈንድቷል። በተናጠል የተጋፈጥነውን አሁን ላይ በርከት
ባለ ሁኔታ በልዩሽ ሙግቱን፤ ድፍረቱን እያዬሁኝ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብም እያዬ እዬሰማ አላዬሁም አልሰማሁም ካለ ነገ የኢትዮጵያ ህዝብም በሰጠው ድምጽ ልክ ያገኛታል። ድምጸ ተዕቅቦ ካላደረገ። ግን ሙያ በልብን መሰነቅ ይኖርበታል። ፊት ለፊት ሳይሆን አቅልን፤ ቀልብን አለመሸለም።
ሁለት ርህራሄ ያልፈጠረላቸው ጨቋኝ አፋኝ መንፈስ ተቀናጅተው ማቱን ይለቁታል … ከዚህም በባሰ ሁኔታ ቻል
ብሎ። ትብብሩ ንግግሩ ውሉ ይሄው ነው። ጠሐይ ዛሬም አልወጣችም
ትናንትም አልነበረችም።
የትናንት የዲያስፖራ አፋኞች እና የአፋኞች ተባባሪዎች፤ እንዲሁም የአፋኞች ሊጋባዎች ዛሬም
እነሱው ናቸው መድረኩን አይበቃኝ እያሉ ያሉት … እኛ ለኖርንበት ጣማራ መከራም የዲያስፐራው የመንጋ ፍርድ ታክሎ የኢትዮጵያ ህዝብ ለአዲስ እርድ እንዲሰናዳ ዘመቻውም
አና ብሏል።
የሰው ልጅ የትም ይኑር የትም ሰው በመሆኑ ብቻ ሊደገፍ፤ ሊበረታት፤ ሊታገዝ
ይገባ ነበር ቀና እሰከሆነ ድረስ። ኢትጵያዊነት ከዚህ አንጻር ነው የሚታዬው። „የሰብዕዊ መብት ተሟጋች¡“ ቅጥሉ ለእኔ ስላቅ ነው። ሥርጉትሻም ሰው ናት እና። ከሁሉ የሚገርመኝ የጎንደር
ጭብጨባ እና ወረብ የጃኖ ሽልማት እና ህውካታ ነው። ቁልቁላት?!
ሥርጉትሻም እኮ ለጎንደር ልጁ ናት። ባለ መክሊት ልጁ የደረሰባትን ግፍና በደል
በጥሞና ማድመጥ፤ መመርመር ይገባዋል ጎንደር። ምነው ጎጃም በሆነ ያሳዩ ነበር እነ አጅሬ ቅኔዎች!
እውነቱ ጎንደር ላይ አንድም ሌላ ታዋቂ ወይንም የመንፈስ ተወዳዳሪ፤ አንድም
መካች፤ አንድም ሞጋች እንዲወጣ አይፈለግም። ዕውነቱ ይሄው ነው። ጎንደር ጌጧ ልጆቿ በዬሄዱበት መታደን ነው። አዳኞቿ ደግሞ የራሷ ልጆች ናቸው።
ግን በፈጣሪዬ ስለማምን አሁንም ተስፋን እጠብቃለሁ አንድ ባለህሊና ፈጣሪ ለአላዛሯ ኢትዮጵያ እና ለድምጽ አልባዎቹ የኢትዮጵያ እናቶች እንዲሰጥ
… እለምነዋለሁኝ። አብሶ የጎንደር እናት መቼ እንደሚያልፍላት አላውቅም፤ ውዴን ነፃነቴን በውድ ቀን ካጣሁ ዘንዳ ታጥቆ መታገል ግድ ይሆናል። የቀረ ዓለም ስሌለ።
ከእንግዲህ ዓለም ለምኔ ብሎ ደግሞ ደጋግሞ ባልተቆራረጠ ተጋድሎ ትግሉ ይቀጥላል፤ የሚያስር፤ የሚጎትት ነገር ከቶውን
የለም ነፃነት የሌለው ነፍስ ቀለም የሌለው እስክርቢቶ ማለት ነው። በዚህ አጋጣሚ ጎንደር ከጭብጫው ተግ ብሎ ስለ ልጁ ስለ እኔ ከልቡ ሊያስብ ይገባል።
እሱም ችግር ላይ እንዳለ ጠፍቶኝ ግን አይደለም። ማት ታዞበት ፍዳው ታቅዶ እንደሚከውን እረዳለሁኝ። ያለበትን መከራ አውቀዋለሁኝ። ግን
ወዳጅና ጠላቱን መለዬት ይኖርበታል። ድምጡን ለማን መስጠት እንዳለበት መቁረጥ እና መወሰን ይኖርበታል - ጎንደር።
አብዩ አሜኑ የጎንደር ብቸኛው ጌጥ የተባሉትም መግደያ ሁኔታ ጠፍቶ ገድመን በመቀመጣችን ነፍሳችን መትረፉ ቆርቁሯቸው ተስፋችን አይሆኑ
እያደረጉት በአዲስ የአፈና የጫጉላ ሽርሽር ሙሽረኛ ሆነው አዬናቸው። ሚዜና ሙሽራ ለአፈና።
ጠ/ሚር አብይን ባላዝንባቸው ግን ሰብዕናቸውን መለካት ችዬበታለሁኝ። ሃዘን ናፈቂ ሰውነት አይደለም እና። እኔ ሳዝን ደስታ ማግኘት የለባቸውም። እናቴም ስታዝን፤ ስታነባ መሳቅ የለባቸውም። ስለ ኢትዮጵያ እናቶች እጬጌ ነኝ ስላሉን።
የኔታዎች የአገሬ ልጆች ተስፋ አያልቅምና ዛሬ በጉልበተኞች ታግተው ስለተቀመጡት
መጸሐፍቶቼን ላስተዋውቃችሁ። በዲያስፖራ ምስቅልቅል አፋኝ ፖለቲካ ታግተው ያሉ መጻሕፍት ...ይህን ጉዳይ በማስተዋል ለመመርመር ሰው መሆን ብቻ ይበቃል። እነሆ ቡራኬው በመጀመሪያው በተስፋ መጸሐፌ የመቅድም ትውውቅ ይጀመር … በርግብ በር ደግሞ ይጠናቀቃል። መልካም ቆይታ …
· ተስፋ (Tesfa)
ለአዋቂዎች የሥነ - ግጥም መጽሐፍ፤
ህትምት በወርኃ መስከረም በሰሞናተ -አድዮሽ በ2003 ዓ.ም፤
154 የግጥም ርዕሶችን የያዘ፤
165 ገጽ ያለው፤
ዋጋ 20.00 የሲዊዝ ፍራንክ።
v የጀርባ ገጽ የጸሐፊዋ የሥርጉተ
ሥላሴ መልዕክት።
„ምን ያልህ እንደተጓዝኩኝ
አላውቀውም?
ምን ያህል እንደሚቀረኝም አላውቀውም?
አለማወቄን ስጠይቀው?
አለማወቁን ነገረኝ።
ተስፋን እጠብቃለሁኝ።
· መክሊት (Mekelete)
ህትምት በወርኃ መስከረም በአድዮሽ በ2003 ዓ.ም፤
ለአዋቂዎች የሥነ - ግጥም መጸሐፍ፤
219 ሥነ - ግጥሞችን የያዘ፤
242 ገጽ ያለው፤
ዋጋ 20 የሲዊዝ ፍራንክ፤
v የጀርባ ገጽ የጸሐፊዋ የሥርጉተ ሥላሴ መልዕክት።
እራስን መሆን እንዳለ
ሁሉ መተላለፍም ይኖራል።
ከሁሉ የሚከፋው ግን እራስን ማንበብ ሲሳን ነው።
እኔ ለእኔ ካልሆንኩኝ እኔ „እኔን“ ማሰናበት አለበት
ይህ ደግሞ የመንፈስ የቁም ቀብር ይመስለኛል።
· ውል ውል (Wele)
· የዕትብት ውል
· የአደራ ውል
· የሕሊና ው
ህትምት ወርኃ መስከረም በአድዮሽ በ2003 ዓ.ም፤
ለአዋቂዎች የሥነ - ግጥም መጽሐፍ፤
177 ገጽ
ያለው፤
ዋጋ 20.00 የሲዊዝ ፍራንክ፤
v
የጀርባ ገጽ የጸሐፊዋ የሥርጉተ ሥላሴ መልዕክት።
እኔ „እኔ“ ነኝ የምለው
እኔ „እኔን“
ሳይዘል በውስጤ አልፎ፤
ለነፃነቴ ሲታገል ብቻ ነው።
ነፃ መውጣቴን የማረጋግጠው ደግሞ፤
ዛሬ የማላያትን የሐገሬን ጸሐይ ማዬት፤
ስችል ብቻ ይሆናል።
· እንካ - ሥላንትያ (
Eneka Selaneteya)
ባህላዊ ትውፊቱን ጠብቆ አዎንታዊ በሆነ ሞራላዊ ሁኔታ
ለልጆች በጣም ታስቦበት የተጻፈ። ልጆችም እያሰቡ፤ እዬተመራመሩ እየተማሩበትም
የሚጫወቱበት
የጥያቄና የመልስ ዓውደ ምህረት። ውጭ አገር
ለረጅም ጊዜ ለቆዩ ኢትዮጵውያን
ኢትዮጵያን ለልጆች የምክር
አገልግሎት እና የቃላት
መፍቻም ያለው።
በምልሰት የሚቃኙበት።
ህትምት
በ2014 ዓ.ም
110 ገጽ
ያለው፤
ዋጋ
18.90 የሲዊዝ ፍራንክ
v የጀርባ ገጽ የጸሐፊዋ የሥርጉተ ሥላሴ መልዕክት።
የልጅነት ጊዜ ሁልጊዜም ተናፋቂ፤ ለምንጊዜም
ተወዳጅና ፈጽሞ የማይረሳ ልዩ የህሊና ጌጥ
ነው። ሲያስታውሱት እንኳን ያልተፋቀ
ፍቅርን ይለግሳል። አዘውትሮ
ሐሤትንም ይመግባል።
· ፊደል (Fidele) ለልጆች የግጥም መጸሐፍ።
· ትውፊትና ባህል ተኮር።
ህትም 2015 ዓ.ም፤
200 ገጽ ያለው፤
174 ርዕሶች ጋር የተቃቀፈ ለልጆች የግጥም መጸሐፍ።
ዋጋ 19.90 የሲዊዝ ፍራንክ፤
ውጭ አገር ለረጅም ጊዜ ለቆዩ ኢትዮጵውያን ኢትዮጵያን
ለልጆች የምክር አገልግሎት እና የቃላት መፍቻም ያለው።
v የጀርባ ገጽ የጸሐፊዋ የሥርጉተ ሥላሴ መልዕክት።
እህ! … ሳቅ የደስታ መንፈስ ብሩኽ ህብረ ቀለም ነው።
የሳቅ ውስጠ- መንፈስ ፍጹም ቅኔ ነው።
ችግሩ በስደት ሀገር ከእውነተኛው ደስታ ጋር
መገናኘት ተራራ ከመሆኑ ላይ ነው።
ማለት የፆም ውሃ ነው።
ይህም በመሆኑ፣ የአንጀት ሳቅ እንዲህ እንደ መስቀል ወፍ
በዓመት አንድ ቀን ብቅ ሲል ጤና ነው። እባካችሁን?!
እንደ ብርቅና ድንቅ ካዬሁት ሳቅ ጋር ውስጤን ዳስሱት።
አመሰግናችኋለሁ። እወዳችኋለሁኝ። አከብራችኋለሁ!
v የተስፋ በር (Ye Tesefa Bere)
ልጅ ለወለዱ ወላጆችለወላጆች፤ ልጆችን በፈቃዳቸው ወስደው በማር ልጅነት
ለሚያሳድጉ፤ ወይንም በተለያዬ ሁኔታ ልጆችን የማሳደግ ገጠመኝ ላላቸው፤ ለት/ቤቶች፤ ለልጆች ማሳደጊያ ተቋማት የቅድመ መሰናዶ የመነሻ የምክር አገልግሎት የሚሰጥ።
የቃላት መፍቻም አለው።
እኔ አደባባይ ላይ ጃኖ ለብሰው ለማይወጡ አፋርጠኛ የቃላት ዘዬዎች ፍቅረኛ ስለሆንኩኝ እንዳይከብድ በማለት መፍቻውንም አብሬ ሰርቼዋለሁኝ። እበዛኛው ጹሑፌም በዚህ መሰል ዕሳቤ የተቃኜ ነው። ይህን ከ24 ዓመት ላለነሰ ሰርቼበታለሁኝ። ሙሽራ ቃላትን እወዳለሁኝ። ፍቅረኛም ነኝ።
ህትምት በ2005፤
ገጽ
306 ያለው፤
ወደ 298 ርዕሰ
ጉዳዮችን ያነሳል፤ የመፍትሄ አቅጣጫም ይጠቁማል።
ዋጋ 30.00 የሲዊዝ
ፍራንክ።
መሰረታዊ ሃሳቡ የልጆችን የወደፊት ራዕይ፤ ተስፋ፤
መክሊትና ፍላጎት እንዴት ሞራላዊ በሆነ ሁኔታ ኮትኩቶ ማሳደግ ይቻላል? የሚል ሲሆን፤ የዚህ መጸሐፍ የመነሻ ችግር በሰለጠኑና ባልሰለጠኑ፤ ወይንም በኢኮኖሚ ባደጉና ባላደጉ አገሮች ማህል ያለው ልዩነት ብዙም በልጆች ራዕይ
ተኮር፤ መክሊት ተኮር፤ የጋራ ሥራ (Team Work፤ በራስ መተማመን አገነባብ ወዘተ ጉዳዮች ላይ እንብዛም ልዩነት የለውም።
ምን ለማለት ነው ወላጆች የቤት ሥራቸውን በአግባቡ በመወጣት
እረገድ ተቀራራቢ ችግር አይቻለሁኝ። ስለዚህም ቢተረጎም ለውጪው ዓለም ራሱ ጠቃሚ መጸሐፍ ነው።
v
የጸሐፊዋ የሥርጉተ ሥላሴ አሰተያዬትና መልዕክት፤
ውበት እንደ አካባቢው ይተረጎማል የሚል ዕድምታ ቢኖረኝም፣ ተፈጥሯዊ የውበት ማመሳከሪያ ቤተ መዝክር አምክንዮ
አለው። እሱም እሸት ነው። እሸቱ አሽቶ ሲታይ ውበት
ነው ለእኔ። እሸት ደግሞ የጮርቃ፤ የለጋ፣ የቀንበጥ፣
የዕንቡጥ፣ መንፈስ - ጸዳሉ ፈክቶ የሚገኘው
በልጆች ላይ ብቻ ይሆናል። አዎን! ውብ
የምለው እኔ ውስጥን ነው። ውስጣቸው
ቅዱስ፤ ንጹህ፤ ቅን፤ ሳቅ፤ ፍካት፤
ሰላም፤ ኑሮ፤ ማዬት፤
ማስተዋል፤ እውነት፤ ቸር፤ የጽድቅ ጉዞ፤ ገነት፤ ተስፋም።
· ርግብ በር (Eregebe Bere)
ለቤተሰብ የፍቅር ገቨር የሆነ መጸሐፍ ነው። መጽሐፉ
ሽፋኑ በዩኒስኮ ሉላዊ የውርስና የቅርስ እውቅና አግኝቶ በተመዘገበው በንጉሦች ንጉሥ በደጉ አጤ ፋስል የቤተመንግሥት ካሉት የበራት
ቅርስ ውስጥ „ርግብ በርን“ እንደ እርዕስ አድርጌ ስወስድ
መታሰቢያነቱም ለንጉሦች ንጉሥ ለአጤ ቴወድሮስ ነው። የህትምት ወረቀቱም ለዬት ያለ በውድ ዋጋ የተሠራ ነው።
መጸሐፉ የትኩረቱ ዕንብርት ትውልዳዊ ድርሻን መሰረት
ያደረገ ስለሆነ የጸሐፊዋ ነፍስ ከትውልዱ ብክነት ላይ ስለሆነም፤ ትውልድ ከሚባክንበት አንዱ ያልተሳካ ትዳር ስለሆነ፤ የጋብቻ ፍርሻን
ቅደመ መከላከል ይቻል ዘንድ የታሰበብት ነው።
የትዳር አጋሮች፤ ወይንም ጋብቻ ሊመሰርቱ ያሰቡ ጥንዶች ፍቅርን በተፈጥሮው እንዴት አስውበው እንደምን በታማኝነት ሐሤት አግኝተው፤ እንደምንስ ቤታቸውን ገነት አድርገው ጓጉተውለት፤ ጊዜን እዬተሻሙ ውስጣቸውን ያፍነሸንሹበት ዘንድ ታስቦ የተጻፈ ሲሆን ከበድ ላሉ ቃላት መፍቻም በስተመጨረሻ
አለው።
ቤተሰብም የማህበረሰብ መሰረት ነው። ከመልካም ጋብቻ መልካም ፍሬ፤ ከመልካም ፍሬም መልካም ትውልድን ማዘመር ይቻላል።
ይህ መጽሐፍ በፍቅራዊነት ተፈጥሮ እና ህግጋት ላይም እንደተጋ መጸሐፉ ተጽዕኖ አሳድሮብኛል። ለመጀመሪያው ዩቱብ ቻናሌ መመሰረትም የበኩሉን
አሰተዋፆ አበርክቷል። ዓለም ታስፈራኛለችና።
መጸሐፉ ለህትም የበቃው በ2006 ዓ.ም
333ገጽ
ያለው ነው፤
222 ጉዳዮችን በዕርዕስነት ቤተኛ አድርጓ አፍለቅልቋል።
ዋጋው 30.00 የሲወዝ ፍራንክ ብቻ።
v የጸሐፊዋ የሥርጉተ ሥላሴ አስተያዬት ዕርዕስ አለው።
ፈጽሞ!
ነው ዕርዕሱ። ሲዊዘርላንድ ባለ መክሊት ሆኖ
መኖር ግዞት ነው። አገሯ ውብ ናት። መንግስቷም ድንግል
ነው። ምቹ አዬሯ ፈለፈል ጭምትም ነው።
ነገር ግን የዲያስፖራ ፖለቲካ፤ ካድሬውም፤ ሚዲያውም ፍዳችሁን ነው እያገለባበጥ የሚያሻችሁ። ነፃነታችሁን
በጠራራ ጠሐይ ቀምቶ በሉላዊ ልክ ከጽንፍ እስከ ጽንፍ እናንተ በማታወቁት ግን እነሱ በሚያውቁት የማፍያ ሴራ ያስገድቧችኋል። ያሳግዷችኋል፤ የአቅም ዋጩ ጭራቅ መናህሪያም ይኸው ቀዬ ይመሰለኛል። ከዚህ አንድም የሚበረከት ብሄራዊ ተቋም የለም። በሞፈር ዘመት ሌላውም አይቀርለትም። "ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል" እንዲሉ ...።
እዚህ እንደ እኔ በስውር በርብርቦሽ ያሹት፤ የሾከሾኩት፤
የፈጩት ሰው የለም። የፊትም፤ የጀርባም፤ የጎንም በግራ ቀኙ እስኪበቃኝ ተደቁሻለሁኝ የህውሃት ደጋፊዎችንም አክሎ። ማን ኑሮኝ ካለ ፈጣሪዬ በስተቀረ?
እሰኪበቃኝ ተከትክቻለሁኝ። እስኪበቃኝ ደፍጥጠው እርም
ብዬ ሁሉንም ነገር ትቼ የጓዳ አይጥ እንደሆን ታግለውኛል። ሌላም ሌላም። አብይወለማ መንፈሱ ሲመጣ የእንኳን ደህና መጣህ አቀባበል
ያደረኩለት እምጠብቀው የነፃነት ተስፋ ስላልነበረ ነው። ከሁሉም ቀድሜ
ነበር የተሟገትኩለት። እንደ እኔም የጻፈ የሞገተ
የለም።
ግን ከዛው ረግረግ ሄዶ ነው የተዘፈቀው አብይወለማ። ሚዛናዊ አድርጎ የተጎዱትን በመንከባከብ የራሱን ድርሻ ይወጣል ብዬም አስቤ ነበር። ጨፍላቂዎችንም አርቆ ዕውነትን ያጸደያል ምኞቴ ነበር።
እውሃ የበላው ቅል ሆነ እንጂ። ጋብቻውም አይሰነብትም ሲጠባበቁ አንዱ አንዱን ውጦ የሚሆነው ይሆናል። እናያለን። ያው ምርጫ ከኖረ እሱ እስኪመጣ ድረስ ነው። የምርጫ ፈቃድ ሰው በማያገባው ገብቶ ይደክማል እንጂ ወሳኙ አዲሱ ጋብቻ ነው። የእነ አርበኛ ዘመነ የእስር ትዛዝን ልብ ይበሉ ...
ብቻ አሁን ላይ እንዲህ በይፋ ጋብቻው ዕውጃው ሲከነዳ የቀራችሁ ስላለ እኔም ታክዬ በአዲስ አቅም፤ በጥምር ልከትክታችሁ የቀረ አካል ካላችሁ ነው ነገርዬው፤ እኔም ተደርቤ እወቃሻለሁኝ ነው ዕድምታው። ስለዚህ ሰውኛነት እና ተፈጥሯዊነት እንዲሁም እኛዊነት የድርቀት እስክስታ የመታበት ነው ለእኔ።
የአብይወለማ መንግሥት ከአዲሱ የዴያስፖራ ፍጹም አፋኝ፤
ፍጹም አሳዳጅ፤ ፍጹም አግላይ፤ ፍጹም በታኝ፤ ፍጹም አቅምን ፈታኝ እና የተደራጀ መንፈስን ናጂ ካደከመን፤ ከገለማን መንጦላይት
መንፈስ ጋር ዲል ባለ ሠርግ ጋብቻን ፈጽሞ፤ ትናንት ነፃነት ከነሳችሁ፤
ከከተከታችሁ፤ ከፈላጣችሁ ጋር አባሪ ተባባሪ ሆኜ እሰልቃችሁ አለሁኝ ብሎ ይሄው እንደ ወጣን ቀርተንለታል።
እንኳን ደስ አለው አብይወለማ
ቀድመን የተማገድልነት መንፈስ ይህ ውለታ ስለፈጸመ። ይህም በኢትዮጵያ እናቶች ምርቃት ካስቸረ ...
እጬጌው ሂደት ደግሞ ይህን የሳሙና አረፋ እፍ ያለ ጫጉላ ሽርሽር ላይ ያለ ፍቅር ብን
… ትን አድርጎ ደግሞ ያሳዬናል ዕድሜውን ከሰጠን። ፍቅር ያዳብር ብለናል እያቅለሸለሸንም ቢሆን።
ዕንባን የሚያዳምጥ፤ ድንግል ኢትዮጵያዊ ህሊና እስኪገኝ አቤቶ ኢትዮጵያዊው ተስፋ፤ ነገ አያልቅም እኔም እንደ እሷው እንደ
ዓለሜዋ ነይ እስኪለኝ ድረስ እታክታለሁኝ።
እኔን ነፃ ያላወጣ ጥገና በሉት ግራጫማ አብዮት ነፃነት አለው ብዬ አላስብም። አቅምም አላባክንም።
እኔ ገና ነፃ አልወጣሁም፤ ጠሐይም አልወጣችም። አሁን ማቱ ኤ ላይ ነው። ኤን ለማጥቃት ከቢ እስከ ዜድ ፍቅር በፍቅር ነው አሁን። ኤን አጥቅቶ ሲያበቃ ግራጫማው ጢሳማው አብዮት ወደ ቢ ኮተት ይላል። ከዛ ከሲ ጀምሮ ከእጬጌው ሂደት ጋር እስከ ዜድ በተራ ሲደርስ ይታያል። የሚቀር የለም የጊዜ ጉዳይ ነው። ለዛውም በዚህ በኦሮሙማ የመስፋፋት ቅርስና ውርስ ቅኝት ማን የተረፈውን ለመትረፍ ከቶ ይታሰባል?
ገና ኢትዮጵያዊዋ
ጠሐይ እንደ ተከደነች በጭጋግ በግራ በቀኝ ተዋራለች። ጠሐይ ወጥታለኝ አለች ያለ ሰብዕና ግን "መንገዱን ጨርቅ ያድርግለት" ምን አልባት ሰኔሉ የራሰ ቹቻው የተሰናዳ ወይንም አዲስ ሃሳብ ብቅል የሌለው ያለቀበት ሊሆን ይችላል ... ስለሆነም እነ አዲስ ቡቃያ ሃሳብ እርሙን ጨምሮ ሠርግና መልሱን፤ ግጥግጡን ቅልቅሉን እዬተመላለሰ ያኝክ አዬሩም ታዳሚ ነውና።
የቤተ መንግሥት ዕጣ ያልውጣለትንማ አዬን አገር አለኝ ብሎ ሲሄድ የእንኳን ደህና
መጣህን መታቀብ በቀብር ሳጥን አስተውለናል። ያም ዜጋ ነው። ያም እናት አለችው። ያም ተተኪ ዜጋ አለው። ያም እህት አለችው። ያም ጋዜጠኛ ነው።
ስለሆነም የህሊና ዓይን እንጂ የቀፈት ዓይን ለዘመኑ አያስፈልገውም። የቀፈቱማ እዛው
ከግብረ ሰላሙ ደጅ ሳይወጣ መጸዳጃ ቤት ነው የሚቀረውና።
የቤተ - መንግሥት ግብረኞች የሰሞናቱ የክቶቹ ለዘመኑ የቅልጣን ልጆች፤ የጡጦ ልጆች እነሱ ይሞሸሩ ለእኛ ግን ትናንትም
ግማድ ዛሬም ግማድ ነው … እናቴ ዛሬም ታነባለች … እሱባለው በፈቀደላት ሁኔታ።
እናቴም ነፃነቴን ሳታይ እንደናፈቃት ነው… እሷም ነፃ አልወጣችም እኔም ነፃ አልወጣሁም ሁለታችንም አልወጣነም እርር እንዳለች
… ለዚህ ነው 7ኛው መጸሐፌን የርግብ በርን የጀርባ ሽፋኑን በዕርእስ ለማውጣት የተገደድኩት። እንዲህ ይላል ... መከራውን በጥልቀት ያሳያል። ምን ያህል ወገብ ጠበቅ ማድረግ እንደሚጠይቅ ...
ፈጽሞ!
ማንነት ያለው ተስፋ
ስላለኝ የመንፈስን እስር የመፍታት አቅሙ ፈተና ላይ አይወድቅም። ይልቁንም ማንነት ያለው መፍትሄ የመፍጠር
ዕሴቱ ሆነ አቅሙ ጉልበታም ነው። ጉልበታሙ ማንነቴ ወደ ፊት የሚፈጥረው
ግፊትና የሚጨበጥ ራዕዩ ደግሞ ትጥቅና
ስንቄም
ነው። በተሟላ ስንቅና ትጥቅ የተሰናዳ
ማንነትደግሞ ጉልህና አሸናፊ ነው።
ከዚህ
በኋላ ወይንም ከእንግዲህ ወዲህ
በቃኝ ብሎ ለስንፍና
ለፍርኃት እጁን አይሰጥም እና … ፈጽሞ!።
ማስታወሻ አንድ።
በቅድሚያ ስለ
ልጆች የግጥም መጸሐፌ ስለ ፊደል።
ፊደልን ብዙ የውጭ አገር ዜጎች ይወዱታል ገዝተውኛልም።
ስለምን ለሚለው እዮር ይጠዬቅበት፤ ከዚህ በተጨማሪ ለልጆች በተጻፉት በእንካ ስላንትያ እና በፊደል መጸሐፍቴ ውስጥ የነቁጥ ያህል
በፖለቲካዊ አምክንዮ የልጆችን ውስጠት፣ መንፈስ ሰላማዊ ሁኔታ የሚያውክ አንዳችም ነገር የለበትም።
እጅግ በብርቱ ጥንቃቄ ነው የሰራሁት።
እኛ ባለፍንበት ትርምስምስ እነሱ ማለፍ ሰለሌባቸው። በተጨማሪም ልጆች እዬተዝናኑ መልዕክቱን ይከታተሉ ዘንድ ዕርዕሶቹ በሙሉ በዲዛይን
የተሠሩ ናቸው። ይህ ለልጆች ብቻ ሳይሆን ለረጅም ጊዜ አገር ውጭ ለሚኖሩም በምልሰት በእናት አገር ጠረንን ይደባብሳል።
v ማስተዋሻ ሁለት።
ለአዋቂዎች የተጻፉት ደግሞ ሁሉንም የህይወት ዘርፍ ይዳስሳል። የተስፋ በር እና
እርግብ በር በማህበራዊ ጉዳይ ላይ ያተኮሩ፤ የምክር አገልግሎት ሲሆኑ የትውልድ ተመስጦ ናቸው። እያንዳንዱ ዕርዕስ በዲዛይን የተሰራ ነው።
ተስፋ፤ መክሊት እና ውል ደግሞ የግጥም ናቸው። በፖለቲካና በማህበራዊ፤ ትውፊት ቀመስም ናቸው። በነፃነት ጥማት ዙሪያ በርካታ ጉዳዮች
ተነሳስተውበታል። በዲዛይን የተሰሩ ግጥሞች አሉበት። ፊደላችን ራሱ ለስታይሊንግ የተመቼ ነው። ስለሆነም በሥነ - ግጥም መጻፍቶቼ
ውስጥ ብዙ የቃላት ሞድ ይገኛል።
ሌላው ከዓለም ወጣ ያለ ነገር በግጥሞቼ ሠርቻለሁኝ።
የነፃነት መታፈን በራሴ ደርሶ ስላዬሁት የግጥም እርዕሶቼን ነፃነታቸውን ሳላፍን ወይንም ሳልጨፈላልቅ እንደ ዲያስፖራው ፖለቲካ፤
በራሳቸው ለዛና ውበት እንደ ተፈጥሯቸው ሥነ -ቃሎች፤ ሐረጎች፤ ዕርእሶች እንደ ፈለጉ ባሻቸው ቦታ፤ መሆን በመረጡበት ቀዬ፤ ያለ ሊዝ ህግጋት
የመኖር መብት አጎናጽፌያቸዋለሁኝ።
ስለዚህ ዕርእሶቹ ጠርዝ ላይ፤ ኮሪደር ላይ፤ ሳሎን
ቤት፤ መኝታ ቤት፤ ጓሮ፤ አትክልት ሥፍራም ካሰኛቸው እንደ ፈለጉ ተንቦላክተውበታል እልፍኙን፤ አዳራሹን፤ ደርብና ምድሩን፤ ደጀ ሰላሙን፤
ቅጽር ግቢውን … እናዳሻቸው ይዘናከቱበታል።
የግጥም እርእሶች ነፃነትን ያለ ተዕቅቦና ያለ ደንበር
እንደ አፈጠጣራቸው ካለ ጭቆና ታውጆላቸዋል። ገዳማችን ይህን ያህል ስትፈቅድ የዲያስፖራው የአውራው ፓርቲ መሪዎች፤ የአውራው ፓርቲ
ሚዲያዎች አሳላፊዎች፤ ሊጋባዎች፤ የፕሮቶኮል ሹሞች ደግሞ በነፃነት አገር ካቴና ያዛሉ።
አንድዬ መዳህኒተ ዓለም በሰጠው መክሊት፤ ችሎታ፤ ልምድና ተመክሮ ላይ አልፈው ተርፈው
ይፈርዳሉ፤ ይቀዳሉ .. ይገመድላሉ … የገዳማዊ ኑሮንን መንፈስ ያፈናቅላሉ በሞፈር ዘመት … ሳይቀር። "አፈና ትውር ብሎብን አያውቅም" አሁን ላይ ጨዋታ ሲመጣ ዝምታ የተመረጠው ወጀቡ ያለው በቂ ነው ተብሎ ነው።
v ክውና በተደሞ!
ስለ ነገ ነፃነት አገኛለሁ ብለህ የምታስብ ዜጋ ሁሉ በዚህ
ተደሞ ተደመም፤ በዚህ ዕድምታ ታደም፤ በዚህ አምክንዮ ተማርበት። መክሊትም፤ ችሎታም፤ የሰማይ ሥጦታም ነፃ እንዲወጡ ካለ ይሉኝታ ታገል፤ ከአሳሪዎችም፤ ከአፋኞች ጋር አትተባበር፤ ቀልብህን፤ መንፈስህን አቅምህን በከንቱ አታባክን። ርጋ ብቻ ከነፃነትና ከእውነት ከጋር!
„የሰው ልብ መንገድን ያዘጋጃል፤
እግዚአብሔር ግን አካሄዱን ያቃናለታል።“
የኔዎቹ ቅኔዎቹ ኑሩልኝ።
መሸቢያ ጊዜ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ