ለግራጫማው ጃዋራዊው ሰብዕና ልዋጭ የተሰጠችው አላዛሯ ኢትዮጵያ።


ግራጫማ ሰብዕና።
የደከሙት እጆች አበርቱ፤
 የላሉትን ጉልበቶች አጽኑ።
ትንቢተ ኢሳያስ ምዕራፍ ፴፭ ቁጥር 

ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
15.06.2019
ከእመ ዝምታ ሲዊዘርላንድ።



·       ጠብታ።

ወዶቹ ቅኖቹ ቅኔዎቹ የአገሬ ልጆች እንዴት ናችሁ? ደህና ናችሁ ወይ? ዛሬ ግራጫማ ሰብዕናን አስመልከቶ ጥቂት ነገር ባነሳሳ ትፈቅዳላችሁን የኔታዎቼ? … ከበታችነት ደዌ ጋርም ይህን መሰል ሰብዕና ተዳማሪ ነውና። አሉታዊው ዴሞግራፊ የነፍሱም ክር በዚህ ዘሃ የተሸመነ ነውና።

·       ሲቃ።

እንደምታውቁት አዱኛዎቼ፣ የአገሬ ልጆች የተውኔት ተፈጥሮ በሁለት ዘርፍ ይዳኛል። እኔ እህታችሁ ግን ሦስተኛም አለበት ብዬ እሞግታለሁኝ። ይህን በጸጋዬ ድህረ ገጽ በ2009 ላይ ጽፌበት ነበር። ዓለምም ጨለማና ብርሃን በሚል በሁለት ጎራ ትለያለች ከጸሐይ አፈጣጠር ተልዕኮ አንፃር። ከቀንና ሌሊት አፈጣጠር ሥነ-አመክንዮ በመነሳት።

በመኖር ሂደትም ደስታና ሃዘን ተብሎ እንዲሁ በሁለት ዘርፍ ይመደባል። እኔ ግን ሦስተኛም አለ ባይ ነኝ … ሊነጋጋ ሲል፤ ሊጨላልም ሲል ያለው ቅይጥ ግራጫማ ቀለም፤ ግራጫማ ሁነት በሦስተኛ ዘርፍ መመደብ አለበት ብዬ እሞግታለሁኝ።  

ለዕለቱ የተውኔት ሁለት አንገፋ ፒላሮች እንመልከት። ትራጀዲ እና ኮሜዲ አጫዋች አዝናኝ አሰቂኝ በአንድ ማህበር ሁለተኛው ደግሞ አሳዛኝ አስለቃሽ፤ ሆድ የሚያስብስ በሌላ ወገን በሚል ማለት ነው። የእኔ ተደሞ ተዚህ ላይ ነው። እኔ በሁለቱ ማህል ያለ ሲቃ የሚባል የትውኔት ክፍልም አለ ብዬ አስባለሁኝ። ፈንገጥ ያለ ዕሳቤ ነው አይደል?

ሲቃ ማለት ዕንባና ሳቅ የተቀላቀለበት ቅይጥ ገጸባህሬ የያዘ ማለት ነው። አንዳንድ ጊዜ ወላጆች ልጆቻቸው ሲዳሩ የሚያለቅሱት ለቅሶ ሲቃ ይባላል። ጋብቻውን በደስታ ያዩና ወላጆች፤ ልጃቸው ትዳር መስርቶ ወይንም መስርታ ከቤተሰቡ ተለይታ፤ ተለይቶ የራሱን ጎጆ አህዱ ሲል መለዬቱን፤ መነጠሉን ያስቡና ያ ያስከፋቸዋል እዬሳቁ ግን ያለቅሳሉ። ያ የሁለት ስሜት ቅይጥ ነው ሲቃ የሚባለው። ሳቅና ለቅሶ የተደባለቀበት የሁለት አህትዮሽ ስሜት ወጥ ሆኖ ሲወጣ። የሃዘንና የሰናይ።  

·         ሌላም ልከል ተለያይተው የኖሩ ቤተሰቦች ሲገናኙ ይሰቃሉም ያለቅሳሉም። ይህ እንግዲህ ሲቃ ነው። ስለዚህ ሳቅና ሃዘኑን በድብልቅ በዛችው ቅጽበት በወጥነት የሚይዝ የትውኔት ሦስተኛ ክፍል አለ ብዬ ስለማምን ያን ሲቃ ሦስተኛ የተውኔት መደብ እለዋለሁኝ። መብት ነው አይደል?
·      ሌላም ልከል አንዳንድ ሰብዕናዎች ጥርስ ብቻ የሚያሰዩበት ግን በሆዳቸው እምሽክ የሚያደርግ ሴራም ያዘሉ ነፍሶችም ይህን የተውኔት ክፍል ይቃኙበታል። ቅባዊ ተውኔት ነው። ይህን በምሳሌ ብናዬው በአንድ በኩል „ኢትዮጵያዊነት ሱሴ ነው፤ በሌላ በኩል አሉታዊ ዴሞግራፊ“
·      መልካም አሰቡ ሲባል መርግ ሲለቁ፤ መርግ ለቀቁ ሲባል የብርሃን ብልጭታ ሲልኩ፤ ያቺን የብርሃን ብልጭታ ደግሞ አፍር ድሜ ለማስጋጥ እጥፍ ድርቡን ጨለማ በድቅድቅነት ሲያፈሱት በሁለቱ ማህል ያለው ድልድይ የሲቃነት ባህሬ ይዞ አያዋለሁኝ።
·      ጨለማ ነው እንዳትሉ ጭላንጭል ያመጣሉ ብርሃን ነው እንዳትሉ ጨላማውን ይለቃሉ ራሱ አሁን ያለው የአብይወለማ ሌጋሲም ከዚህ ጋር በብዙ ይመሳሰልብኛል ለእኔ በግሌ።
·      አዲስ አባባ ላይ ጋዜጠኛ እስክንድርን ተጠያቂ መንግሥት እንዳይሆን የሚጫወተው ትዕይንት በሲቃነት ይመደባል። አልከከልኩም፤ አላገድኩም ይላል፤ ነገር ግን ህጋዊ ባልሆነ ባደራጃቸው ቡድኖች በሁሉም ዘርፍ ካቴናውን ዘርግቶ ያስራል። በአዲስ አባባ ህዝበ ሙስሊሙም ላይ የደረሰውን ግፍ በዛ መልክ ልግጫ ተወራርዷል።
·       ገራሚው ነገር ሱዳን ሄዶ ደግሞ እስረኛ አስፈትቶ ለዛውም በቤተመንግሥቱ የሰማይ አውቶብስ ይዞ ይመጣል „ቅኑ መንግሥታችን።“
·       ሌላም ልከል አማራ ክልል ላይ ስለምን የአማራ ብሄርተኝነት ብቅ አለ ብሎ እግር ከወርች ተለማጩን አስሮ ሲያስከነዳ ዓመት ሙሉ ባጅቶ ሲዳማ ደግሞ ውንብድናን በአካል ተገኝቶ ቢባ ኤጄቶ! በማለት ሲያቆላምጥ፤ ሲያበረታታ ይገኛል። ይህን እዬከወነ ደግሞ አዲስ አባባ ከተማ ላይ ቆሻሻ ሲያጸዳ፤ ችግኝ ሲተክል ቤተ መንግሥቱን ደግሞ ታያላችሁ ይህ መንፈስ የማን እንደሆነ በሚቀጥለው ንዑስ እርእስ ማዬት የሚገባ ይመስለኛል። ኢትዮጵያ የማን መንፈስ ቅኝ ተገዢ በመሆን ላይ እንዳለች … 

·       ግራጫማ ሰብዕና

ግራጫማ ሰብዕና ምንድን ነው? ምን ዓይነትስ ነው? ዘዬው ምንድን ነው? ጠረንሱ ምንድን ነው? እንዴትስ ይከሰታል?

ግራጫማ ሰብዕና ልክ እንደ ሲቃ ከሳቅም ከለቅሶም፤ ከብርሃንም ከጨለማም ማህል ላይ የተዳቀለ ሰብዕና ነው። ግራጫማ ሰብዕና መለያው ፍታዊ መሆኑ ወይንም ቅጽበታዊ መሆኑ ነው። በአንድ መንፈስ ጸንቶ ወይንም ረግቶ አይገኝም። ጽናት የሚባል ነገር ፈጽሞ አለሰራለትም። 

ይህ ቅይጥ ሰብዕና በግል ኑሮ፤ በማህበራዊ ኑሮ፤ በሃይማኖታዊ ኑሮ፤ አቋም በሚወሰድባቸው ጉዳዮች ሁሉ፤ በፖለቲካ የአቅም አቋም ግድግዳው እጅግ ፈታኝ እና አሰቸጋሪ ሰብዕና ነው። መያዣ መጨበጫ የሌለው አቅጣጫ አልበሾ ጅዋጅዊት ነው።  

ወህ! ተመስገን ብላችሁ ተስፋን ለቀቀብን፤ መተንፈሻ ቧንቧው ተከፈተ ስለትሉ ተስፋን የሚያስምጥ እና አስጎንብሶ የሚያስረግጥ ወይንም የእንፉቅቅ የሚያስኬድ በእጥፍ አባዝቶ የድቅድቅ ጫና ይከምራልኝ።

አሁንስ አለፈለት መሰል ብላችሁ ሳቀ አሳሳቀ ስትሉት ደግሞ ሌላ በረድማ ዶፍ ይለቅባችኋዋል፤ አሁንም ተዛ ድቅድ ፋታን አሰቀደመ፤ ተመለሰ ስትሉት በቅጽበት ደግሞ ቻል በለኝ አሰኝቶ የነበረበትን ዝክንትል እና ድሪቶ ጭንቀት፤ ስጋት፤ የመከራ ድባብ አምጥቶ ይጭንባችኋዋል።

ለዚህ ጥሩ መግለጫው „የሃጂ“ ጂዋር መሃመድን ሰብዕና አብዝቶ ማጥናት ይጠይቃል። እኔ ለረጅም ጊዜ ተከታትዬው ብዙም ሳልጋፋው፤ ብዙም ቲካ ቲካ ሳልለው፤ እንብዛም እርር ድብን ሳልልበት፤ ወንድሜ ቢሆን፤ ልጄስ ቢሆን በማለት ግን የቅጽበታዊ ተለዋዋጭ ሰብዕናውን በሥርዓትና በተደሞ አጠናሁት። እንደ አንድ የምርምር ማዕከል አድርጌ ማለት ነው።

ጸንቶ የሚቆምበት ባህሬ የለውም። ጸንቶ የሚናገረውም ቃል የለውም። ጸንቶ የሚቆይ ፍላጎትም የለውም። ጸንቶ የሚሰነበት ራዕይም የለውም ይመስላለችኋል „ኦሮምያ የምትባል አገር“ ዕውን ብትሆን „ኦሮምያ የሚባል አፍረካ ቀንድን“ ይሻል፤ ያም ቢሳካለት „መከካለኛው አፍሪካን የሚጠቀልል ኦሮሙማ“ ይሻል ያም ቢሳካለት „እማማ አፍሪካ የኦሮሙማ መናህሪያ“ እንድትሆን ይመኛል፤

ይህም አይበቃውም ቀጥሎ ደግሞ በኦሮሙማ የሃይማኖት ተሃድሶ ይዞ ከች ይላል፤ ይህም አይበቃም ጋብቻ ላይ ይወርዳል እንደ አቶ በቀለ ገርባ። አሁን ጫፍጫፉን ነው እያዬን ያለነው እጩን ማለቄያ በሌለው መባተት ውስጥ ያለ ህልቆ መሳፍርት ያለው ድብልቅ - ዝንቅንቅ - ቅይጥይጥ፤ ውጥንቅጥ ራዕይ ነው ያለው።

ስሜን አሜሪካንም አውሮፓንም ይመኛል … ገዳን ሉላዊ ለማድረግ። ለዚህ ነው ተጠማኝ ሆኖ ላቲንን የሙጥኝ ያለው .. ግራጫማ ሰብዕና እንዲህ ነው ማቆሚያ ወሰን፤ ተግ ብሎ የሚያስብበት ደንበር የለውም  „አባገዳ ጃዋርን መሃመድን“ ለደቂቃ እሱን ሊገልጥ የሚችል ገጸ ባህሬ ማግኘት አይቻልም ከግራጫማነት በስተቀር።

እንዲያውም አንድ ጊዜ በጠ/ሚር አብይ አህመድ ወደ ፊት መምጣት ከቢቢኤን ጋር በነበረው አሉታዊ አቅላይ ቆይታ ያን አስመልክቶ ሞግቼ ስጽፍ እግዚአብሄርን ባገኘው ስለምን እንደፈጠረው እጠይቀው ነበር ሁሉ ብየ ጽፌያለሁኝ። ደጉ ሳተናው አውጥቶት ነበር።

አሁንም ስለምን ልዑል እግዚእብሔር እሱን እንደ ፈጠረው ባገኘው እጠይቃዋለሁኝ። ስከንት ለነሳው አዬር፤ ህውከት ለሚንጠው ንፋስ፤ አደብ ለነሳው ትውልድ የተፈጠረ የገጭ ገው ግራጫ ስለሆነ። ኢትዮጵያና ልጆቿ ይቀጡበት፤ ይወቁበት ዘንድ ነው እሱ የተፈጠረው።

ሳያሸነፍ እንቅልፍ የለውም። ይህን ደግሞ ቀደም ብዬ ጽፌዋለሁኝ። ደግሞም ይሳካለታል። ኢሳት ላይ የቋጠረውን ቂም በምን ሁኔታ እንዳሳከ ራሱን አስችሎ የምርምር ተግባር ያስከውናል። ስኬቱ እስከምን እሰከመቼ? ለሚለው ግን ነብይ ስላልሆንኩኝ አሁንም እዮር ይጠዬቅ።

„ሀጂነትን“ ያስወሰነው በቅጽበት ነው ጠ/ሚር አብይ ከአረቡ ዓለም ጋር ጠንከር ያለ ግንኙነት ሲፈጽሙ „የአባቱን መስመር የካደን ለእሱ አለሁ ከምትሉ በተፈጥሮዬ ያለሁትን እኔን ላይ ትኩረት" ሲል ነበር ያን የፈጸመው፤ ጠ/ሚር አብይ አህመድ ሃጂ የመሆን ዕድላቸው አልፏል እንደማለት።

ከዛ ሲመለስ ደግሞ ሬቻ ላይ ነበር። ከአድባሯ ጋርም መጣላት አልፈለገም። እዛ ጠ/ሚር አብይ አህመድ እንደማይሄዱ ያውቃል „ሀጂነቱም ሬቻነቱም አቅዶት ወስኖት አይደለም። ቅጽበታዊ ተፈጥሮው አስገድዶት እንጂ … 

የ2011 ዓ.ም መስቀል ደግሞ መዲናዋ ላይ እንዴት በቅይጥ መጤ ዝብርቅ በወታደር ጫና ታስሮ በርዕሰ መዲናዋ በሽብርና በስጋት እንዲሁም በውጥረት እንደ ተከበረ በምልሰት መቃኘት ነው። መግደል የሚሻው አለ፤ ትንሳኤውንም ማወጅ የሚሻው ክሰተት ደግሞ አለ። ታስታውሱ ከሆነ ሬቻ በሰላም መስቀል በስጋት ነበር የተከበረው። ሲፈልጉ አበባ ይዘው አቀባበል ሲፈልጉ ደግሞ አፈሙዝ፤ ሜጫ፤ ገጀራ አስይዘው ብጥብጥ።

የሆነ ሆኖ ቀልብ አሸማመቱም ሆነ አቀናኑ ቅጽበታዊነትን የተከተለ ነው። አሁን ለብዙዎቹ ግራጫማ ስብዕናውን ሽግግር ውርርስ እያደረገ ስለመሆኑ እያዬን ነው። ሲዳሞን አካቶ ጉራጌ ላይም ምልክቶች አይደለም መሰረታዊ ክንውኖች እዬታዬ ነው … አሁን ሃይማኖትን ብዙም አይነካካም … ያ ለይድር በቀጠሮ ነው።

ሲያሰኘው ፍልውሃውን ይለቃል፤ ሲያሻው በረዶውን ይልከዋል፤ ሲያሰኘው ለብ ያለውን ያሰከነዳል፤ ሲለውም ጨለማውን ተስፋ ያጎናጽፋል ሲያሻው ብርሃናማውን ያመጣዋል፤ ሲለው እሳት ይለቃል፤ ሲለው ደግሞ „ሃጂ ገዳ ጃዋር መሃመድ“ ሆኖ ደግሞ ሽምግልና ላይ ይቀመጣል፤

ቤተመንግሥትም ምን የመሰሉ ጠባቂዎችን መደቦ በቅልጣን፤ በቁልምጫ ሲያሽሞነሙነው ዕብደትን ለመማር ለተሰበሰቡ ገላጭ አድርጎ መንበር ላይ ጎልሎታል።  

መጋቢት አንድ ቀን 20111 ዓ.ም በሚጸዬፈው የታላቁ ንጉሥ አጤ ሚኒሊክ ጠረን ላይ ተቀምጦ ለተፎካካሪ/ ለተቀናቃኝ/ ለተቃዋሚ/ ለተዳማሪ የፖለቲካ መሪዎችና ሚደያዎችም፤ ለግል ሚዲያዎችም ስለ ግራጫማ ሚዲያ ይተነትናል፤ ሲያሻው ደግሞ ሜጫን አሰለፎ ኑ ውረዱ ኑ ተሰቀሉ ይላል

ሳስበው፤ ሳስተውለው ለግራጫማ ሰብዕና ትክለኛው ባላባት „ሀጂ/ አባገዳ/ ጃዋር መሀመድ“ ሆኖ አገኘሁት። ስለሆነም በዬትኛውም እንቅስቃሴው ቀይ ጃኖ ቢያጠልቅ፤ ጥቁር ካፖርት ቢደርብ፤ ዥንጉርጉሩን ቢዥጎረጎረበት አቶ ጃዋር ግራጫ ነው ተሃሳቡ፤ ተራዩ ጋር። ጋድም ሰብዕናም ይታከልበት።

አሁን አገር ሰጥ ለጥ አድርጎ መግዛት ብቻ ሳይሆን ዴያስፖራውን አውራ ፓርቲውን የቀሰተዳመናው ድርጅትን ወራሽ ግንቦት 7 እሰከ መሪው መንፈሱን አወራ ኢሳትን ሚዲያውን ምንጣፍ አድርጓቸዋል። መቼም ይህን ዓሊ የሚል ሰው አይኖርም። እሱ እንዲህ ነው።

ዛሬ በጃዋራዊው መንፈስ የምትማራው ኢትዮጵያ ከራስ ጸጉር እስከ እግር ጥፍር ድረስ አሸርጋጁ፤ አደግዳጊው፤ የአውራው ፓርቲ የቀስተደመና ወራሹ የግንቦት 7 ሊቀመንበር የአሁኑ የኢዜማ ጠ/ሚር አክሎ እያስራደ ነው። እያርበተበተ ነው። ጫማው ውስጥ ወሽቋቸዋል።

አንዲት ቃል ትንፍሽ በእሱ ዙሪያ የለም። የት ሊገባ?!!!! የሚገርመው ሁሉንም ጥግ አልባ መለመላውን አሰቀርቶታል። ከባህር የወጣ አሳ አድርጎ … እርቃናቸውን አስቀርቷቸዋል። የቀረው አንድም ባለመወድስ፤ ያላራገፈው አንድም ባለክበር የለም። አሁን በቀደመው ክብሩ በልዕልናው ላይ ያለ የለም የአብይወለማ መወደሱን አክሎ ቁልቁል ለቆ እንደ ፎከረ ትቢያ አስለብሶታል

ገናናው ኢሳት ሳይቀር በመዳፉ በቁጥጥሩ ሥር አስገብቶታል። ኢሳትን አሳምሮ ተበቅሎታል፤ ወቅቶታልም። የተክልዬን ስለት የበላ ይመስልም ሊሂቅ ነኝ፤ አክቲበስት ነኝ፤ ጋዜጠኛ ነኝ፤ መሪ ነኝ  የተባለውን ሁሉ ዝርግፍግፉን አውጥቶ ቡን አድርጓቸዋል። አመዳማ ቀለም ለቅልቋቸዋል።

የሚከላ ካለ ደግሞ ያሰከላዋል። እስታሁን ሦስት ንጡሃን ገዳያቸው ሳይታወቅ ደመ ከልብ ሆናዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩት ደግሞ በጠራራ ጠሐይ ተረሽናዋል፤ ተጎሳቆላዋል፤ ባዕት አልቦሽ ሆነዋል። ይቀጥላልም።

ይህ ያልጋባው ነፍስ ሁሉ „ለውጡ፣ ዴሞክራሲ ምርጫ፣ ኮሚሽን፣ አዋጅ፣ ረቂቅ የዓዋጅ ጽድቀት፤ የተዋካዮች ምክር ቤት፤ የፌድሬሽን ምክር ቤት ሹመት ከሹመት መነቀል ወዘተ እያለ ይታመሳል ይተራመሳል“

 …. ሁሉም በግራጫማው አብዮት የሚተዳደሩ ለዛም የሰገዱ ናቸው። ዕውነቱ ይሔው ነው። ያን አሻም ያሉ „ያልተደመሩ፤ ለውጥ አደናቃፊዎች፤ ሰላም አዋኪዎች“ ተብለው ገና ብዙ ፍዳ ይጠብቃቸዋል … በተለይ አገር ውስጥ ያሉ። ውጭ ያሉት ደግሞ ብዙ መሰናክሎች ይጠብቃቸዋል። የምግብ ብክለት፤ የመኪና አደጋ፤ ዝርፊያ፤ የግድያ ሙከራ ወዘተ … ወዘተ …  

ጎንደር መሬት ላይ ከ90ሺህ በላይ የተፈናቀለው በስል ገብቶ በተከታዩ፤  በአድናቂው፤ በውድ የልብ ወዳጁና በአወዳሹ በምግባርም በመሰሉ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ተነጣፊነት ገብቶ የልቡን ሰርቷለኝ። ጎንደርን በጥርሱ የያዘው ነበር ይህ  እስኪበቃው ተበቅሎታል። ብአዴን ጢባ ጢቦ ተጫውቶባቸዋል። አብረክርኳቸዋል። አርዷቸዋልም። ብአዴን ሎሌነቱ አሁን ለሃጅ፤ ለአባገዳ አቶ ጃዋር መሃመድ ነው።

ያልተገለጠው የተሸፈነው ጉዳይ ደግሞ አቶ አባ ዱላ ገመዳ „ርዕሳነ ሊቃንነትም¡ ነው። እሳቸው ያደራጁት ሙሉ አካል ነው ሁለመናውን እዬተቆጣጠረው ያለው። የሳቸው ኔት ነው አሁን ሥራውን እዬሰራ የሚገኘው።

ጠ/ሚሩ ቀን ቀን ከካቢኔያቸው ጋር ይመክራሉ ለዛ አጀንዳ ተፈጻሚነት ግን ማታ ላይ „የሊቃነ¡“ አቶ አባ ዱላ ገመዳ ፊርማ ያስፍልገዋል። ሴክሬታሬያታቸው ደግሞ ያው ጃዋራዊው አቶ ንጉሡ ጥላሁን ናቸው። እሳቸው ለሁሉም ሊንክ ናቸው።

የውጭ መንግሥታት ኢትዮጵያን ሰልልኝ ቢሏቸውም ዓይናቸውን አያሹትም። ለጊዜው የቅርብ አለቃቸው ግን ጠ/ሚሩ አለመሆናቸው ሊታወቅ ይገባል። በጠ/ሚሩ ቢሮ የግራጫማ አብዮት ጉሪንጥ ጎርምጥም ናቸው … የቻይናውን፤ የኤርትራውን ጉዞ ከልብ ሆኖ በማስተዋል ሊመረመር ይገባል።  

ቁመነገሩ ግን መላ የአማራ ልጆችን ግን እንዳሻው መንዳት መቼውንም አለመቻሉን አሰረግጬ ልነገረው እሻለሁኝ ለሃጂ አባገዳ ጃዋር መሃመድ እና ለቤተኞቹ። ለቅንጣት፤ ለሰከንድ የእኛን መንፈስ ማንበረክክ፤ ማስረግድ አይችልም። ፈጽሞ! ፈጽሞ!ምን እንዳለን፤ ምን እንደምንችል አሳምረን እናውቃለን፤ ብድርና ትውስት የሚያስኬደን አንዳችም ነገረ የለምና። 

የሆነ ሆኖ አላዛሯ ኢትዮጵያን የሚመራት ግራጫማው የጃዋርውያን አብዮታዊ መንፈስ ነው። የሚናገረው እውነቱን ነው። ሹመቱን የሰጡት ደግሞ „ሊቀ ሊሂቃኑ ¡“ ምርኮኛው አቶ አባ ዱላ ገመዳ ናቸው። ጄኒራላቸው እሱ ነው። ከእሱ መንፈስ ፈቅ የምትል አንዳችም ነገር የለችም። እሱን ደፍሮ የሚናገር ቤተ መንግሥት ከቶውንም አላበደም።

ውዶቼ የአገሬ ልጆች ….

ናዚን እሰቡት፤ …. ናዚን አጥኑት፤ ናዚን ምርምር አድርጉበት … መሳውን፤ አቻውን ኢትዮጵያ መሬት ላይ አግኝቷል። ሃያላን አገራት ያልገባቸውና ያልተረዱትም ይህን ነው። ፊት ለፊት ሌላ አለ፤ ስውሩ መንግሥት ደግሞ በስተጀርባ አለ።

ግራጫማ ሰብዕና ሰብዕዊነት ክፍላቸው አይደለም፤ ተፈጥሯዊነትም ምናቸውም አይደለም። በሰው ስቃይና መከራ የሚዳንሱ … የሚፈርሹ … የሚዝናኑ … በቃኝንም የማያውቁየትርምስ ኢንፓዬር የመሰረቱ ናቸው።

አብይወለማን እንደግፍ ከሚሉን ዘመን የማያስተምራቸው ፕ/ ብርሃኑ ነጋ ለጃዋራዊ መንፈስ ተንበርከኩ ማለት ቀላሉ መንገድ ነበር። ቀድሞውንም ሻታ ሲዞሩት ነበር አስቀንቷቸው የኦሮሞ ፕሮቴስት። ካድሬዎቻቸውን ልከው ምህረት አስጠይቀው „ምን እንርዳችሁ“ አስብለው ሁሉ ነበር አቶ ጃዋር መሃመድን። እሳቸውም ይህን ተናገረው ነበር … ቀልባቸው አቅም አለበት ከተባለ ቦታ ላይ የቸከለ ነው። የኦሮሞ ፕሮቴስት የበለጠ እዬተጠናከረ ሲመጣ ደግሞ „ኦሮሞ ዳማም“ ሆነው አረፉት።

የቢሾፍቱ ልጅ ነኝስለዚህ ኦሮሞነት አለብኝ” – / ብርሃኑ ነጋ በብራሰልስ ያደረጉትን ንግግር ቪዲዮ ይዘናል"

„(-ሐበሻ) የአርበኞች ግንቦት 7 መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በቤልጀየም ብራሰልስ አውሮፓ ፓርላማ አይ ከዶ/ መረራ ጉዲና እና አትሌት ፈይሳ ለሌሳ ጋር ንግግር አድርገው ከጨረሱ በኋላ ከኢትዮጵያውያን ኦሮሞ ኮምዩኒቲ አባላት ጋር ተወያዩ:: በዚህ ውይይት ላይ ፕሮፌሰሩ ባደረጉት ንግግር ታሪክን መመለስ እንደማይቻል እና በታሪክ ላይ መስማማትም እንደማይቻል ታውቆ አሁን በአንድነት መቆም ላይ ትኩረት እንዲሰጠው ጥሪ አቀረቡ:: ፕሮፌሰሩ በንግግራቸው በቢሾፍቱ /ደብረዘይት መወለዳቸውን ጠቅሰው ኦሮሞነት እንዳለባቸው አስታውቀዋል:: ንግግራቸውን ይዘናል ይመልከቱት“ አሁንማ ህይወትም መንገድም እናንተው ናችሁ ብለውናል።

·       ክወና።

አዬሩ ቅኝቱ ጃዋራዊ ነው። ወፊቱም ግራጫማ፤ ጥገናዊ ለውጡም ግራጫን ወራሽ ነው … ብዙ ነገርን በቀጣይነት ወዮልህ እያለው ነው!

የጋዜጠኛ እስክንድር ንቅናቄ፤ የአብን ንቅናቄ እስተምን ድረስ ይዘልቃል?! በግራጫማው ሀጂ አባ ገዳ ጃዋራዊው ቀጭን ትዕዛዝ የሚታይ ይሆናል። በዚህ ውስጥ ተጥለቅለቁ ጥምቀት ይካሄድላችሁ ግን የተገባ ስላልሆነ ጎራ ለይቶ የድርሻን ማድረግ ከእያንዳንዳችን በግል ከሁላችንም በጋር ብዙ በጣም ብዙ ይጠበቃል።

27 ዓመት የታገልነውን ለግራጫማው አብዮት አሰረክበን ባዶ እጃችን አጨብጭበን እንደቀረን አምኖ ተቀብሎ „ሀ“ ብሎ መጀርን መቀደስ ይገባል እናላልን፤ እኔና ትጉህ ብዕሬ … ግን በሜጫ፣ በፍጥጫ፣ በግልምጫ፣ በእርግጫ ሳይሆን በጭምትነት፤ በጭብጥ፤ በሃሳብ ልቅና፤ በአዳዲስ ዕይታ የጎለበት፤ የጎለመሰ ሙግት በማድረግ።

ጠ/ሚሩ አብይ አህመድም እኔ ግራጫማውን አብዮት ተቀላቅያለሁና እዛች ዝንፍ ብትሉ ወዮላችሁን! የጦር ነጋሪ ቢያቆሙት ይመክራል። እሳቸው እኛን ጠፍጥፈው ወይንም አንቦልቡለው መፍጠር አቅሙም ሥልጣኑም የላቸውምና። 

እኔ አይደለሁም እዮር መጋቢት አንድ ቀን ያሳዬውን የአርምሞ ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው የሰጠውን ምልክት ከልብ ሆኖ ማድመጥ ይገባል።
ከዛ በፊትም መሬት ሲተረተር፤ ቤት ሲተረተር፤ አስደማሚ ጩኽት ከሰማይ ሲሰማ፤ ሰማይ እሳት ሲያዘንብ ልብ ያለው አልነበረም። 

ለዛም ነው መጋቢት አንድ ደግሞ ሌላ ሉላዊ መከራ ባዕታችን ያስተናገደችው። እዮር ሰሚ ጆሮ ከሌለን ይቀጥላል ቅጣቱን በተለያዬ ሁኔታ …

ከግራጫማ ውርስ እና ቅርስ ፈጣሪ ያድናችሁ! አሜን!
ትእግስት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል
ፍቅርም ሲያልቅ ትእግስት ይሰደዳል።
የኔዎቹ ቅኔቹ መልካም ሰንበት።
መሸቢያ ጊዜ።  

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።