“የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሄርን መፍራት ነው” {ከጸሐፊ እና ከተርጓሚ አቶ መስፍን ማሞ}
“እንኳን ወደ ቀንበጥ
ብሎ በሰላም መጡልኝ።”
“የጥበብ መጀመሪያ
እግዚአብሄርን
መፍራት ነው”
ከጸሐፊ እና ከተርጓሚ
አቶ መስፍን ማሞ ተሰማ
ሠላም ለናንተ ይሁን!
ኢትዮጵያ በዘመናት ታሪኳ እስከ 1966 ዓ/ም መጨረሻ ድረስ የመሯትና የህዝቧም እረኛ ሆነው ፥ እንደ ቀስተ ደመና ቀለማት ህብር ውበት ሁሉ፣ የተለያየ ባህል ባለቤትና ቋንቋ ተናጋሪ ህዝቧን በአንድ መሶብ አሰባስበው፣ መተሳሰብ መዋለድ ህብረትና ሀገራዊ ማንነት ተዋህደውና አምረው እንዲሰርፅና እንዲኖር ያስቻሉት እኒያ መሪዎቿ ፈሪሃ እግዚአብሄር ያደረባቸው ነበሩ። የክርስትና እና የእስልምና ሀይማኖት አባቶችም ለእምነቱ ህግጋት ተገዢ ፈጣሪያቸውንና አማንያንን አገልጋይ ነበሩ። ፈጣሪም ከእነርሱ ጋር ነበረ።
የቀደሙት የኢትዮጵያ መሪዎች በፈሪሃ እግዚአብሄር እየተመሩ የህዝባቸው መልካም እረኛ ሆነውና በሀይማኖቶችም አከባብረውና አስማምተው ህዝባቸውን አኖሩ። ኢትዮጵያን እንደ ሀገር አቆሙ። ከጠላት ጠበቁ።
የኢትዮጵያ ህዝብም ልበ ቅን፣ በራሱ ላይ ሊያደርጉበት የማይፈልገውን በጎረቤቱና በሌሎች ወገኖቹ ላይ የማያደርግ፣ ፈሪሃ እግዚአብሄር ያደረበት ሆኖ ተባብሮና ተሰባስቦ ኖረ። ለዘመናት የተገነባው ይህ ሀገራዊ/ኢትዮጵያዊ እሴት በዘመነ ደርግ ፈተና ገጠመው። ፈተናው ፖለቲካዊና መንፈሳዊ ነበር እንጂ ዘርን ተገን አድርጎ ሀገራዊና ኢትዮጵያዊ ማንነትን የዳጠ፣ የጨፈለቀ፣ ያዋረደና ኢትዮጵያዊነትን ከሰውነት ተራ ያወረደ አልነበረም። ለዚህ ብቸኛ ተጠያቂውና ሀላፊው የዘር ድርጅቶቹ ግንባር የኢህአዴግ መንግሥት ነው።
ኢህአዴግ ቤተ መንግሥት ከገባበት ቀን ጀምሮ እንደ መንግሥት የዘር ኮሌራ በመላው ኢትዮጵያ አራባ፣ ኮተኮተ፣ አሳደገ። እነሆ ፍሬው ሶስት ሚሊዮን ህዝብ ለመፈናቀል፣ አእላፍን ለህልፈትና ለመከራ ዳርጓል። ኢህአዴግ መሰረቱ፣ ዕድገቱና ቀጣይ ህልውናው የዘር ኮሌራ መዋቅሩ ነው!
እነሆ ቀደምት ነገሥታቱን በማያሰልስ ፀሎታቸውና በቅንነታቸው ከቤተ መንግሥት ቅጥር ሆኖ ይረዳቸው የነበረው ፈጣሪ አምላክ እግዚአብሄር በ1967 ዓ/ም መስከረም ሁለት 'ፈጣሪን የካዱ' ቤተ መንግሥቱን ሲቆጣጠሩ፣ የእግዚአብሄር መንፈስ ከቤተ መንግሥት ወጣ። አዎ! እግዚአብሄር ከቤተ መንግሥት ራቀ።
እነሆ ደግሞ በዚያው ዘመን የኦርቶዶክስ መንፈሳዊ አባቶች እግዚአብሄርን አሳዘኑ። በእጃቸው የሾሟቸውን ቅዱስ ጳጳስ አቡነ ቴዎፍሎስን አሳልፈው ሰጡ። ለምድራዊው ጉልበተኛ ተገዙ። እነሆ ደግሞ ይህንን በዘመነ ኢህአዴግ ደገሙ። ፈጣሪም አመረረ። በምድሪቱ ላይ ሀጢያት በረታ፣ በረከተ።
እነሆ በዘር አርማታ ላይ የቆመው ኢህአዴግ ለሰማይም ለምድርም የከበደ ነውር በምድሪቱና በልጆቿ ላይ ፈፀመ። ኢትዮጵያ የኢህአዴግን ሀጢያት መሸከም አቃታት።
ለመሆኑ በነውራቸው ተፀፅተው መንበረ ሥልጣናቸውን የለቀቁ፣ ይቅርታ ጠይቀው አንገታቸውን የደፉ ኢህአዴጎች ስንቶች ናቸው?
ቤተ ዕምነቶችን ሲያመሳቅሉና ሲያናጉ የኖሩት የት ነው ዛሬ ያሉት? የሀገርን ሀብት ንብረት መቀመቅ የከተቱ የት ናቸው? የኢትዮጵያን ስም መጥራት ተጠያፊዎቹ 'ሀገሪቷ' ባዮቹ ኢህአዴጎች የት ናቸው? የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሄርን መፍራት ሳይሆን "ክብርና ሞገስ ለታላቁ መሪ" ባዮቹ የት ናቸው? በሥልጣናቸው ሲታበዩ የኖሩ ዛሬም 'ለድሀ አደሩ የማይፈርዱ ለመበለቲቱ እንባ፣ ለህፃናቱም ዋይታ የሚራራ ልብ የሚሰማ ጆሮ የሌላቸው በምድሪቱ የሞሉ የኢህአዴግ ገዢዎች ስንትና ስንት ናቸው?
እነሆ በኢትዮጵያ ምድር የሆነውና እየሆነ ያለው ሁሉ ሰለዚህ ነው። እግዚአብሄር ለኢትዮጵያና ለየዋሁ ህዝቧ ፊቱን ይመልስ፣ ሀዘኗንም በቃሽ ይበላት!
ሰኔ 2011 ዓ/ም
(ጁን 2019)
ሲድኒ አውስትራሊያ
mmtessema@gmail.com
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ