ቴዎድሮስ፤ ብቻውን የቆመ የለውጥ ሐዋርያ መስፍን ማሞ ተሰማ


ቴዎድሮስ፤ ብቻውን የቆመ የለውጥ ሐዋርያ
መስፍን ማሞ ተሰማ
አፄ ቴዎድሮስ (1847 / - 1860 /)



በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ቴዎድሮስ አንጀት የሚበላ በክብር የወደቀ ታላቅ ሰው እንደ ነበር ፈፅሞ የሚያጠያይቅ አይደለም። ታዲያ ሰብዕናውን አሳዛኝና ተከባሪ የሚያደርገው ህይወቱን ያጠፋበት አስደናቂ ሁኔታ ሳይሆን፤ ከሁሉ በላይ ታላቁ ብቸንነቱና የኖረበት ዘመን ባጠቃላይ ዓላማውን ሊረዳለት ሳይችል መቅረቱ ነው።

ቴዎድሮስ ማንኛውንም የመገንጠል እንቅስቃሴ ሁሉ በቆራጥነት ይታገል የነበረውና አጋር ፍለጋ እንደዚያ ሲባዝን የኖረው ከዚህ / ታላቋን ኢትዮጵያን የመገንባት ዓላማ/ የተነሳ ነው።

ዳግማዊ ቴዎድሮስ ከወሰዳቸው ዋና ዋና እርምጃዎች ውስጥ አንዱ የባሪያ ንግድ ማስቆሙ ነው። ከዚህም ጋር የሀገሪቱ ነዋሪ ሁሉ ሥራ እንዲኖረው የሚል ደንብ በማውጣት፤ ተስፋፍቶ የነበረው የዝርፊያ ወንጀል እንዲገታ አድርጓል። ይህን የሚመለከተው አዋጅ እንዲህ ይነበባል፤ገበሬ ይረስ፤ ነጋዴ ይነግድ፤ እያንዳንዱ ሰው በየሥራው ይሰማራ።

በኢትዮጵያ ንግድና የህዝብ ግንኙነት እንዳይስፋፋ እንቅፋት ሁኖ የኖረውን የሽፍታ መቅሰፍት ከሞላ ጎደል ለማስታገስ በመቻሉ ቴዎድሮስን ሊያስመሰግነው የሚገባ ነው።

የኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት /ደግማዊ ቴዎድሮስ/ የሀገር ውስጥ አቋሙን ካጠናከረ በሁዋላ በውጪ ፖሊሲ ረገድ ታላላቅ ዕቅዶችን ነደፈ።ከሁሉም በላይ ቅድሚያ የሰጠው ኢትዮጵያን የባህር በር በለቤት የማድረጉን ተግባር ነው። ይህም ሀሳቡ ሰሜን ኢትዮጵያ በሀገሪቱ የውጪ ፖሊሲ ውስጥ እጅግ የጎላ ስፍራ ያለው ጉዳይ መሆኑን ከተገነዘቡ ታላላቅ ተደናቂ የኢትዮጵያ መሪዎች አንዱ ያደርገዋል።

የዳግማዊ ቴዎድሮስ አስተዳደራዊ ለውጦች ባጭር ጊዜ ውስጥ ሊተገበሩ የሚችሉ አልነበሩም። ግን ለዚህ ዋናው ምክንያት የሃገሪቱን መከፋፈል ለማስቆም የሚፈልግ አንድም ማህበራዊ ሃይል አለመኖሩ ነው። ውስጣዊ የጋራ ገበያ ትስስር የለም። ለንጉሠ ነገሥቱ የኢኮኖሚያዊ ምርኩዝ የሚሆነው የነጋዴ መደበ አልነበረም። እንደ እውነቱ ከሆነ ቴዎድሮስ ታላቁን አላማውን አንግቦ ብቻውን ቁሞ ነው የምናየው። {1}

ፕሮፌሰር ዶናልድ ክራሚ የቴዎድሮስን ህይወትና ገፀ ባህሪ ሲገመግም  ማብራራቱና መተንተኑ ቢጎድለውም የዘመናዊ ሥልጣኔ ሀሳብ የገባው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ንጉሥ ነበርበማለት ፅፏል። ይህ ማለት ከቴዎድሮስ በፊት የነበሩት ነገሥታትና መሳፍንት አንዳንድ የዘመናዊ አሰራር ሃሳቦች ሳይገለፅላቸው ቀርቶ ነው ማለት አይደለም። እንደ ቴዎድሮስ ግን በሰፋትና ያለመታከት ሀሳቡን ግብ ለማድረስ የጣረ ንጉሥ አልነበረም። 

ይሁን  እንጂ ቴዎድሮስ ሀገሪቷን በዘመናዊ መንገድ ለመምራት የሚያስችለውን ንድፍ በደንብ ካለመቅረፁም ሌላ በሚወስዳቸው ተቃራኒ እርምጃዎች ምክንያት ከዓላማው ሊደናቀፍ በቃ። የሚያደርጋቸውም የለውጥ ሙከራዎች በዳበሳ እንጂ ሁለገብ የሆነ የለውጥ ፕሮግራም ተከትሎ አልነበረም። ከዘመነ መሳፍንት የወረሰው ማህበራዊና ፖለቲካዊ መዋቅር ብዙም ሊያራምደው አልቻለም። ስለሆነም የጀመራቸው ወታደራዊና አስተዳደራዊ ለውጦች የኢኮኖሚና የቴክኖዮሎጂ መሰረት ስላልነበራቸው አየር ላይ ተንጠልጥለው ቀሩ። የአውሮፓውያንን የቴክኒክ እርዳታ ለማግኘት አጥብቆ ቢማፀንም የሚሰማው አላገኘም። በመጨረሻም ቴዎድሮስ ብቸኛና ግራ የተጋባ የለውጥ ሃዋርያ ሆኖ ቀረ። {2}
ዋቢ፤ የኢትዮጵያ ታሪክ - መፃህፍት

1 አንድርዜይ ባርትኒስኪ እና ዮዓን ማንቴል ኒየችኮ (ትርጉም ዓለማየሁ አበበ 2003)
2 ባህሩ ዘውዴ (1989 ዓ/ም)
mmtessema@gmail.com

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።