ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ጁቪተር ላይ ይሆን የሚኖሩት? (ጠና ያለ ሙገት)
እንኳን ወደ ቀንበጥ ብሎግ በሰላም መጡልኝ።
የተመላላሹ ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ
እልፍኝ - ጁቢተር ይሆን? የመሪነት ኃላፊነቱስ
አዳራሽ አዳሽነት ይሆን - ይሆን?!
(ሙግት)
„አንተ ምን ጥቅም አለህ ---- ?
ኃጢያት ሠርቼ ከማገኘው ይልቅ፤
ኃጢያት
ባልሠራ ኑሮ ምን እጠቀማለሁ?
ብለህ ጠይቃኃልን።“
(መጽሐፈ እዮብ ምዕራፍ 35 ቁጥር 3)
ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ።
28.01.2020
· ጠብታ።
እንዴት ናችሁ ቅኔዎቹ የአገሬ ሃብቶች። አልኳችሁ ቀኑ ውሽክ ብሏል። ምን ይደረግ እንዲህ ዘመን
ሰጥ ቀለጤ እና ቀበጤ ጠሚር ሲኖረን። በረከት ይባል መርገምት አይታወቅም። ይህ ጹሑፍ ታግቶ ቆዬ። ሁለት ሞጋች አመክንዮች ስለገጠሙኝ።
አንደኛው „እኛን ውሰዱ እና እህቶቻችን መልሱልን“ የሚል የወጣት ወንዶች ርህርህና እስከ አጥንቴ ስለተሰማኝ ያን አስቀደምኩኝ።
ሁለተኛው ደግሞ „ሳናውቅህ ስናውቅህ“ የሚል የመጸሐፍ ያህል ህሊናዬን ሞገተኝ በ28.01.2020 ከ30 በላይ በተለያዩ ከተሞች በአማራ ክልል ከተካሄዱ ሰላማዊ ሰልፎች የገዘፈ መልዕክት ሆኖ ስላገኘሁት
እሱን አስከተልኩኝ።
በእነኝህ ሁለት ጹሑፎች ምክንያት ይህኛው ጹሑፍ ማዕቀብ ተጥሎበት ቆዬ። እኔ የሲዊዝን ቀደም
ባለው ጊዜ አውሮፓ ሰልፎች ሲካሄዱ ነበር እምዘግበው እንጂ የአገር ቤት ሰላማዊ ሰልፎችን አልዘግብም ነበር። ለዚህ የተሰማሩ መደበኛ
አምደኛ ጦማርያን ነበሩ በቀደመው ጊዜ። አሁን ወደ አያቶቻችን ቀዬ ሳይሉ የቀሩም አይመስለኛም ብራና ላይ ብዙም አላያቸውም። ምንን
እና ማንን ስንታገል እንደ ነበረ ሁሉ እዬጠፋብኝ ነው። „ፍትህ“ ከሁሉም ሰፈር ተሰወረች።
ከታጋዩም ከአታጋዩም።
· እንንነሳ።
እንነሳ ስል ከሃሳቤ ጋር ማለቴ ነው። „የኢትዮጵያ የብልጽግና ጊዜ ነው። የኢትዮጵያ የብልጽግና ጊዜ ነው።
የብልጽግና ጊዜን ማቆም የሚችል ኃይል የለም። ይህ አዳራሽ 35/36 ዓመቱ ነው። ከ35/36
ዓመቱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አሁን የምታዩትን ግርማ ሞገስ ያገኘው በብልጽግና ዘመን ነው። ይህ ምልክት ነው። ምልክት ነው።
መጀመሪያ ቢሮ፤ ቀጥለን አዳራሽ፤ ቀጥለን ግቢ፤ ቀጥለን አዲስ አበባን፤ ቀጥለን ኢትዮጵያን እንቀይራለን። አንዴ ሥራ ጀምረናልን።
አንዴ ለውጥ ጀምረናል። አንዴ
የሚያምር ውስጥ ገብተናል። አንመለስም“ በለው! ዕብናዊነት። (ከዶር አብይ አህመድ ንግግር የተወሰደ።
ውዶቼ ይህን ንግግር ደጋግሜ ነው እማነሳው)
አዳራሽ አዳሽነት እኮ ነው ኢትዮጵያን የሚመራው ብሄራዊ ፕሮግራም፤ ብሄራዊ ፖሊሲ
የሚነደፍበት፣ አገር የሚመራበት የኖራ ዕሳቤ ሆኖ አረፈው። አጀብ
ነው። ኖራ የኢትዮጵያን ምስቅልቅል ችግር ሲያስተዳደር፣ ሰላም ሲፈጥር፤ ተስፋ ሲያሳካ፤ ማግስትን አደራጅቶ ቀድሞ መሰረት ሲያስጥል።
„ከልጅ መሪ እና ከህዳር ዝናብ ጠብቀን“ ይሉ ነበር ባለቅኔዎች ጎንደሮች። ሲያክሉም „የልጅ ነገር አንዱ ብስል አንዱ ጥሬ“ ይላሉ።
ልጅ ሲሉ ሰሙ ዕድሜን ወርቁ ግን የአስተሳሰብ ጮርቃነት ይመስለኛል።
„በባለ ግራማው አዳራሽ“ እሳቸው
ናቸው ባለግርማ የሚሉት በቄንጥ ልፋታቸውን ሲያጎርሩት። ንግግር ሲያደርጉ
ድምፃቸው ነው የሚገርመኝ። በዚህ ቀዳዳ በሌለው በገዘፈው ብሄራዊ የሃዘን ሰሞናት ጭንቅ ወቅት ውስጥ ሆኜ፤ እንቅልፍም ተሰዶ ጠቅላይ
ሚኒስተር አብይ አህመድ የሲቃ ሳቅ ሲሸልሙት ቀኑን አስተዋልኩኝ። መነሻዬ እሱ ነው። ግን ኑሯቸው ከወደ ጁቢተር ሆነን? አድራሻ
አልቦሽ መሪነት የለቀቀ ቀለም። አሁን ይልቅ ኤርትራ ላይ ሰርግ ላይ ናቸው የዶር አብይ ዘመናይነታቸው ወሰንም ልክም አጣ። ወለም
ዘለምም አበዛ። ተቀናጣ። ሃግም* የሚላቸው ጠፋ።
እነዛ ልንጽፈው በማንችለው መከራ ውስጥ ያሉ የአማራ ልጆቻችን ከቶ ኢትዮጵያዊ ትውልድነታቸው
ተፍቆ ይሆን?! መሰል። ለነገሩ ከመሼ መጥተው አማራ ብቻ አይደለም። የእኛው ልጆች አብረው ተጠቅተዋል ብለው ደግሞ የብሄረሰብ ስብጥር
ሰንጠረዥ ይተረትሩት ይሆናል። ያንት ያለህ ነው ነገረ አብይዝም።
„አንዴ የሚያምር ውስጥ ገብተናል። አንመለስም“ የዶር አብይ አህመድ ቅልጣናዊ ንግግር ልቅ እንዲህ ሆነ። ፈሰስ ቅልጥልጥም
አሉም። ሰው የሚባል ነገር ለሳቸው የዶሮ ያህል እንኳን ክብር የለውም። የሰው ስቃይ መዝናኛቸው ነው የሆነው። አያዩትም የሚመሩትን ኢትዮጵያዊውን ሰውን። አያደምጡትንም እሳቸውን ተስፋ ያደረገውን
ኢትዮጵያዊውን ሰውን። አያስተውሉትም የኢትዮጵያዊ ሰውን ፍጠረተ - ነገሩን። ለሳቸው ሰው በሳቸው ዙሪያ ያለው ብቻ ይመስላል። ፍግፍግ
የሆነ ገጠመኝ!
„ካለ ሰው በቀትር ቀንም ያስፈራል“ ብለውን ነበር በደጉ ዘመን ታች ሳሉ፤ እንዲህ እራስ ሳይሆኑ
በከተሞች ቀን ጎንደር በነበራቸው የተናጋሪነት ውክልና። ዕድል እንዲህ በላይ በላይ ሳይነባበር ማለት ነው። አሁንማ „እኔ የሰፈር ሚሊሻ አይደለሁም“ እያሉ ይፎግራሉ። የሠራዊት አባልነታቸው ዲሲፕሊኒን የተቃጠለ ካርቦን ሆኗል በዚህ
አቃላይ የንግግራቸው ዕድምታ። እግዚኦ! ነው ነገረ አብይዝም። እንዲህ ደፍርስ ያደርጉታል ፈልቶ እንዳላበቃ አፍለኛ የጠለለ ዝልል።
ልክ ለገዳዲ ለጋጣፎ መከራን „አልሰማሁም“ ብለው እንዳላገጡት። ወይንም ኦህዴድ „ አዲስ አበባ
የኦሮምያ ናት“ „ሰምቼ አቶ ለማ መገርሳን ስጠይቅው በድምጽ እንደ ተሸነፈ ነገረኝ“ እንደ አሉት ተረት ተረት ይቃጣዋል ምጻአታዊ
ንግግሩ “እኔ የሠፈር ሚሊሺያ አይደለሁም“ ? ? ? የህዝብ እረኛ ማለት የህዝብ ጠበቂ መሆኑን ከሚስጢሩ ጋር ተላልፈዋል።
ለሰሞኑን ሰቆቃ ነው እንዲህ የመዝናኛ ክበብ የከፈቱለት። ለእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነትም ተጠያቂነትም አለባቸው። ለእያንዳንዱ ዜጋ
እረኛ፤ ዘበኛ የመሆን ግዴታ አለባቸው። የመጀመሪያው ዕለት ያሉትን ቤተ - መንግሥታቸው ውስጥ ሆነው የተናገሩትን እረሱትን?! ልበ
ኮረኮንችነት።
ምንድን ማለት ይሆን ለሳቸው ጠቅላይ ሚኒስተርነት ማለት?! በቃ! ከረባት እና ገበርዲን ካሜራ
ሲያድን መዋል ይሆን? ሳስበው ሰው ጥልቅ ወንዝ ውስጥ ገብቶ ሲሰጥም ትንፋሽ ያጣረዋል። እና አመራራቸው ትንፋሽ ስለሚያጥረው ማስታገሻ ንግግር ማድረግ
ወይን ሽርሽር ወደ ውቢቷ አስመራ መጪ ማለት ሆነ።
እረኛ መሆን ካልቻሉ እኮ ስለምን ከክልላቸው ውጪ ልጆች በዩንቨርስቲው ይመደባሉ? ማንንስ አምኖ
ህዝብ ይቀመጥ? ለማንስ ነው የታሪክ አደራው? ማንን ተስፋ ያደርግ ይህ መከረኛ ህዝብ? ሲያሰኛቸው ደግሞ ቀበሌ ወርደው የግለሰብ
ቤት አዳሽ ሆነው ሽሮዋ ላይ ተሰልፍው ይገኛሉ። ሲያስፈልጋቸው ልጆች ማሳደጊያ ሄደው ሲተቃቀፉ ይገኛሉ፤ ታዲያ እሳቸው የልጆች ማሳደጊያ የእንክብካቤ ሠራተኛ ሆነው ይሆን ከዛ የሚገኙትን? ወይንስ የሰፈር ቡና አጣጭ?
ጎደሎ ቁጥር።
· ትርታ።
ወደ ቀደመው ምልሰት ሳደርግ የመኖር ትርታ ጠቅላይ ሚኒስተሩን ይጠይቃል። ምን ብሎ? እንዲህም
ብሎ። የት ላይ ይሆን ጠሚር አብይ አህመድ የሚኖሩት ብሎ? ተሰውረው ይሆን የሚኖሩት እንደ ደቂቃን? ወይንስ በጋህዱ ዓለም ውስጥ እንደ ረቂቃን
ሆነው ይሆን እዬመሯት ያሉት አላዛሯን ኢትዮጵያ? ወይንስ ወደ ዕልፍኘ ጁቢተር ለሽርሽር ክራሞታቸውን ወደ ሰማይ ቤት አረጉን?
ግን
ለመሆኑ አድራሻቸው የት ይሆን? ሰማይ ቤት ነው ወይንስ መንኮራኩር ውስጥ ይሆን ወይንስ ቤተ - ምኽዋር ውስጥ ልዩ እልፍኝ ተዘጋጅቶላቸው?
የልብ ልብ የሚሰጣቸው ጤነኛ ያልሆነ መንፈስ ደግሞ እንዳለባቸውም አስታውላለሁኝ። እልህ ይባል ቁጭት ሥሩን አላገኘሁትም። ብቻ ሁሉን
የማድረግ ሥልጣን የተሰጣቸው ያህል ነው በልበ ደንደናነት የሚናገሩት። በጣም እርግጠኛ ሆነው።
መቼም ከቅዱስ መንፈስ ጭካኔያዊ ሰብዕና
አይጠበቅም? ከግራጫው ዓለም ካልሆነ በስቀር እንዲህ አፍ ሞልቶ የሚያናግር። ዕንባ የተዘራበት ዘመን ነው ዘመናቸው። መራራ። ኮምዳዳ።
ወንድ ልጅ ዕንባ አውጥቶ የሚያለቅስበት። አይዟችሁ የደረቀበት። ርህርህና የመከነበት።
„የኢትዮጵያ
የብልጽግና ጊዜ ነው። የኢትዮጵያ የብልጽግና ጊዜ ነው። የብልጽግና ጊዜን ማቆም የሚችል
ኃይል የለም።“
ይህ ልበ ደንዳናነት የሚፈርሸው ከዬትኛው የመንፈስ አቅም ይሆን የሚቀዳው? ነገረ ሥራቸው እኛኑ
ይበረብራል። እያንዳንዱ ውሏቸው ከሀረሩ „ለባዕድ አዳልቼ ከሆነ“ ምህላ ጋር የተገጣጠመ ነው።
በሚመሩት
አገር ባዕድ ህዝብ፤ ድርጅት፤ ተቋም አለ አማራ ማህበረሰብን መነሻው ያደረገ፤ ወገን የሚባል የከበረ ህሊናቸውን የሚገዛ መንፈስ
ደግሞ አለ የኦሮሞ ድርጅታቸው፤ በዚህ ማህበረሰብ የተጠሩ ተቋማት በሙሉ። ሙሉ ድጋፍ፣ እገዛ፣ የተጠናከረ የምክር አገልግሎት በጠሚር
ቢሮ የሚሰጣቸው። በዬትኛውም ብሄራዊ አህጉራዊው ዓለም አቀፋዊ ቁልፍ ቦታ የሚመደብ። የክት።
ሌሎችስ ኢትዮጵያውያን ዜጎችስ አድራሻቸው የት ይሆን? ዋንኛው የግንባር ተጠቂ አማራነት፣ አማርኛ
ቋንቋ፤ ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማ ዘምተውበታል። ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶም አልቀረላትም፤ በተጨማሪም ወላይታን፤ ጋሞን፤ ጌዴኦን፤
አፋርን፤ አማሮን፤ አዲስ አበቤን፤ ድሬንም አይተናል ምን ያህል መንፈሳቸው እሩቅ እንደ ሆነ ለእነዚህ ነፍሶች?
ግን ምንድን ናቸው? ሰው እንዳትሉኝ።
ሰው መሆናቸውን አውቃለሁኝ በአምሳሉ የተፈጠሩ። የጥሪያቸው
አይነት ነው ቡራቡሬ
የሆነብኝ። የሰብዕና ጥሪያቸው ምንድን ነው? ቅድመ እና ድህረ እንበለው ይሆን የዶክተሩን ሰብዕና? በማጅራት የሰውነት አምሳል
አይታያችሁም? ማጅራት ላይ ግራ ቀኝ ዓይን፤ ሁለት መተንፈሻ ያለው አፍንጫ፤ ከናፍርወጥርስ እስኪ አስቡት። በማጅራት የሚመራ መንፈስ
ነው የሚመስለው ነገረ አለሙ ሁሉ።
ሽክ ብለው ጉብ ይሉና መድረክ ላይ የማይኳን ቴራፒ ያስነኩታል። የሚገርመኝ የድምጽ ምቱ ነው።
ከውስጥ ገብተው ጉዝጉዝ እንዲሉ የሚያደርጉት የድምጽ መግራት ኪናው ትወና። የቀረባቸው የሬዲዮ ሠራተኝነት ነው። የውነት። ምርኮኛው
ሁሉ የተሰለፈው እኮ በዚህም የድምጽ ቅላፄ የልብ ምቱ ከፍ ስላለ ነው። „እሳቸው ጥፋት አልሰሩም ከሰማ ሰማያት ወርደው ከመደመር
ተወልደው ካሜራ ላይ ስለ እኛ ሲሉ የተደገኑ፤ ለገበርዲን፤ ለከራባት እና ለማይክ ሲሉ ዳገት ቁልቁለቱን ደፍረው የተቸነከሩ“
ይሉናል እነ መደመር የኦዳ ሥርዕዎ መንግሥታ ማህበረ ካድሬ ።
· የደቡብ እርክክብ በኦሮሙማ ቅኝ ተገዢነት።
እንሆ … ይህ አጀንዳ እኔ ተረኛ ልሁን ብሎ አፈጠጠኝ፤ ይሁንልህ ብዬ እኔም ፈቀድኩለት። ያው
ከመነሻ ነጥቤ ጋር ውርርስም ስላለው። እንዲህ ነው። … ሰሞኑን ደቡብን ሙሉ ለሙሉ ለኦሮምያ እርክክብ ለማድረግም፤ ቅደመ ሁኔታ
ለማበጀትም የቤተ - መንግስቱ አውሌያ ወይንም ቆሌ ነፍሱ ጠፍታ ነው የሰነባበተችው።
አምላካችሁ አለ ብትል ብሎ። ስለሆነም ለደቡብ
ወገኖቻችን፤ ለአገር ሽማግሌዎች እና ለሃይማኖት አባቶች „በባለ ግርማ ሞገሱ በቀለም ባበደው አዳራሽ መከሩ ተመከሩ ስለመወራረሱ“ የአፍዝዝ አደንዝዝ ክኒን በረድፍ አሰልፈው ሲያድሉ ሰንበተዋል ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ።
እዚህ አገርም፣ ጀርመንም የግርዶሽ ተውኔት የሚባል አለ። ተዋናዮቹ አይታዩም፤ በመጋረጃው ጀርባ
ሆነው ነው ተውኔቱን የሚሠሩት። በዚያ የሰለጠኑ ነው የሚመስሉት ዶር አብይ አህመድ።
የኦነግን መንፈስ እያንሠራፉ፤ እያለመለሙ፤
አቅሙን አጎልብተው ድልበድል እያነባባሩ „የኢትዮጵያ ብልጽግና“ ይላሉ በላመ ድቀት ውስጥ አላዛሯን ኢትዮጵያ በሁለመና ማግደው እና
ተጭነው። ትውልዱን በሁለገብ የሥነ-ልቦና ብትነት ወጥረው እያዋከቡ። እኔ ያዬህ ተቀጣ ነው ያለው ነገር።
ከዚህ ላይ የማይረሳው የሲዳማ ክልልነትን ጥያቄ ከመመለስ ጋር ለመጠቅለል የተሰላው፣ ተቆርጦ
የቀረው የጌዴኦ ህዝብ
ነው። አሁን እራሱ ዕለታዊ ኑሮውን ለማን አቤት እንደሚል
አይታወቅም። አስተዳደራዊ ሰንሰለቱ ተጎርዷል። ሲያሹት ይባጁ እና አማራጭ ሲያጣ ውሳኔውን ይቀበላል። ምንም ይሁን ምንም።
ስለዚህም
በዚህ መስመር ገብቶ ኦሮምያ ጠቅለል ያደርገዋል በኦሮሙማ ማንፌስቶ። መንገዱ እዬተጠረገ ነው። አለስልሴ ላይ ነው የለምቾ የዴሞግራፊያዊ
ስሪት ደቡብን ለመጠቅለል። አንዱን በመንፈስ ሌላውን በሥጋ ወመንፈስ። ስክን ብሎ 16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በ21ኛው ክፍለ ዘመን
አምጥቶ ደንጉሮታል አቤቱ ለምቾ። ወራራ በመስፋፋት ቀመር።
ወደ ቀደመው ስመለስ ያው ከእልፍኘ ጁቢተር ወደ መሬት ጎራ ሲሉ ወግዬን በልስሉስ
ቅላጼ ሲያሰከነዱ የተገባ ፍተሻ ያስፈልገዋል በማለት ነው ጎራ ያልነው - ዛሬ። ይበርበር ዘመናይነቱም ሆነ ቅልጣኑም እንደ ማለት።
ምን ሰለቸሽ ብትሉ የአማራ ሊሂቃን ፕሮፖጋንዲስነት ለአብይዝም ሆነ ቃሬዛ ላይ ለሚገኘው ለግርባው ብአዴን፤ እንዲሁም የቤተ - መንግሥት
ቅልጣን እና የተለጠጠ ዘመናይነት ሳዳምጥ መሰልቸት ብቻ ሳይሆን ያቅለሸልሸኛልም። ያጥወለውለኛልም። እንደዚህ ዓይነት የገጠመኝ ኩርንችት፤
የጎረና እና የሂደት ከንቱነት ማንበብም ማድመጥም እራሱ ቅጣት ነው። ጥሎብን!
· ከቀለጤው
ንጉሥ ልሳን በፊት ለማዋዣ።
„አቶ አባ ዱላ ጠፍተው ከርመው ያልታሰበ / የልተጠበቀ / ሹመት ተሰጣቸው“ ሲሉ የዩቱብ ሚዲያዎች
አዳምጫለሁኝ። ለመሆኑ አቶ አባ ዱላ ገመዳ የት ሂደው ነበር? የስውሩ መንግሥት አራጊ ፈጣሪ አማካሪ የነበሩ ቁልፍ ሰው ናቸው።
ጠሚር አብይ አህመድ ከስሜን አሜሪካ ከተመለሱ ጊዜ ጀምሮ አዲሱ ወላዊ አደረጃጀት ተፈጥሮ ከ4ኪሎ ወንበር ዘዋሪዎች ውስጥ እሳቸውም
አንዱ ነበሩ፤ አባ ገዳዎችስ ተመስጥረው ሳይኖሩ ይቀራሉን? ተአብ እኮ ነው የእነሱ ነገር።
ዋናውን ዙፋን እኮ ይዘው የነበሩ ናቸው አቶ አባ ዱላ ገመዳ ናቸው። ወደ ፊትለፊት እንዳያመጧቸው
ተደማሪዎቻቸውን በጊዜያዊነት ፈሩ። ስለዚህም ሸጉጠው በኪሳቸው ይዘዋቸው ጓሮ ለጓሮ ሲሉ ባጁ። አሁን የጨረሱትን ተልዕኮ ስላለ ለቀጣዩ
የደቡብ የብትናው ትወና ብቅ አደረጓቸው። ኦሮሙማ እንዲህ ነው እያዋዛ ለሽ ያደርግህና የልቡን ይሠራል።
· ተዝች ላይ።
ተዝች ላይ ደቡብ ግን ዕድለኛ ነው። ሊሂቃኑ እንደ አማራ ሊሂቃን ሁሉ ይሙት በቃ አልተፈረደበትም።
ሰኔል እና ቹቻ አልታዘዘበትም። ለነገረ ቤተ - መንግሥት አያሰጋም ይመስላል ብልሃቱ። በዚህ ሰሞን ንግግር „ለሥልጣን ብዬ ሰው አልገደልኩም“ አዳምጠናል። ዶሮ ሲያርዱ ይሆን የባጁት?
አዲስ አበቤ ሆይ! ባህርዳር ሆይ! መስክሩ ያሰኛል።„ጦርነት እንገባለን“ ዓዋጁስ ምን ተብሎ ይተርጎም? ባለ መሳሪያው እሳቸው ናቸው።
በሌላ በኩል ግን አብይዝም ሆነ ሲደመርም ግንቦቲዝም የደቡብ ፖለቲካን መገንባትም ስለሆነ ውሉ
ብዙም የጠና ችግር ደቡብን አልገጠመውም። ለወደፊትም አይገጥመውም። ያው ፍሪጅ የሰጡትን ጠበቆ ቀን ያወጣል። በጣም ሲበዛም ተፈጥሮውን ይቀይራል። ብቻ ሁለቱም ሙሽራና የእግር ሚዜ የሚነጫነጩት
ሊሂቅ ከስሜን ብቅ ሲል ነው። አማራማ እንደ ጦር ነው የሚፈራው። አንደ ቀንጣ ነፍስ አቶ እስክንድር ነጋን ማስተናገድ አቅቶት ቤተ
- መንግሥት እስከ ተደማሪ አማካሪዎቹ ታመሰ። ዓይነ - ጠባቦች።
አማራ ላይ አደብም የለም ቀሰስተኛ ሆነው የማያቸውን አቶ ለማ መገርሳን ጨምሮ ሁሉም የኦሮሞ ሊሂቅ መሰል አቋም ነው ያላቸው። ብዙው የፖለቲካ ሊሂቅ መርዘኑ ይነሳል
የአማራ ሊሂቅ በልቅና ብቅ ሲል። ዶር አንባቸው ሞኮነን እርእሰ መሰተዳድርነት ሁሉም ውስጡን አሹቆት* ነበር። የልቡ ደርሷል መስጥሮ የያዘው ሁሉ።
የነብዬ
ብርጋዴር ጄኒራል አሳምነው ጽጌም የጸጥታ ኃላፊ ለክልሉ መሆንም ሌላው የአንጎል ቁርጠት ነበር። በዛ ላይ ሁለቱም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማንያን ናቸው። ይህም የህሊና ቁርጥማት ነው።
ሁለቱም ተደምስሰዋል። የጥቃቱ ልክ በጥልቀት እሰቡት። የሆነ ሆኖ መኖሩ እንኳን የማይታወቀው ኦህዴድን እንዲህ ያቀናጣው ስልቡ ብአዴን
ነው። የምድር እንቧይ።
እንደ ድርጅት መኖሩን ማን አውቆት ነበር ኦህዴድን? በስል ሰተት አድርጎ አስገብቶ የአማራን
ህዝብ ልብ የስልበት ሥንኛትን እራሱ አሰናድቶ በድርጅታዊ ሥራ ሰጥቶ፣ የቲም መሪነቱንም አጎናጽፎ፤ ድምጹም ሙሉውን ከአለ ቅደመ
ሁኔታ ሸልሞ ይኸው አፈር ስንቁ አደረገው የአማራ ሊሂቃኑን፤
የአማራ ጸጥታ ተቋማትን፤ እና የአማራን ህዝብ።
„ለሥልጣን አይደለም ትግላችን“ ይልኃል የፖለቲካ ድርጅት ሆኖ ተደራጅቶ ግርባው
ብአዴን በቀድሞው መሪው በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው አንደበት። ቀፎ የፖለቲካ። እንሆ አሁን ህዝብን ለበላህሰብ አስረክቦ ተንበርክኮ
ከጌቶቹ ምህረትን ይለምናል። ግዑዝ።
የአማራን ህዝብ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያም ሚዛኗ እንዳይጠበቅ አድርጎታል ዝልቦው ብአዴን። ለዚህ
ነው እሱን የሚያቆላምጡ ጹሑፎችም ሆኑ ነፍሶችም እኔን የሚያቅሩኝ። ከዚህም አልፎ ዛሬ መላ የአማራን ህዝብ ለሌላ መንፈስ ለማስረከብ
ደግሞ እዬፏከተ ይገኛል ግርባው ብአዴን።
ለተደራቢ አማራ የለም ለሚል ባለአንጣ። በሽንጥ ተገብቶ ሥልጣን ላይ የሚኮፍሳቸው ለዬትኛው
ድርጅት ውለታ ስለመሆኑ ጠንቅቀን እናውቃለን። የሰው ልጅ የመንፈስ መሸቀጫ መለንቀጫም መስሎታል። ይኸው ዛሬ አማራ ገናና መንፈሱን
አሳይቷል በ28.01.2020 {19.05.2012 ዓ.ም } በ34 ከተሞች ባደረገው ጨዋ፣ ብቁ፣ የልቅና መለያ ህዝባዊ ሰልፍ። ቅኑ
የአማራ ህዝብ ጥሩ ሲሰራ ሲያክበር ሲከፋው ደግሞ ውስጡን ምራቁን በወጠ ጥሞና አስጎብኝቷል።
ወደ ቀደመው ምልሰት ሳደርግ አቶ አባ ዱላ ገመዳ የአዬር መንገድም የቦርዱ ሰብሳቢ ናቸው። በተጨማሪም
ጠቅላይ አቃቢ ህጉ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬም የአዬር መንገዱ የቦርድ አባል ናቸው። አዬር መንገድ ኢትዮጵያ ነው። ቦርድ የሚባለው ሁሉ
ከአንድ ሁለት በስተቀር ሰብሳቢያቸው የኦህዴድ ቅምጥሎች ናቸው።
ዘመነ ኦሮሙማ እንዲህ እያሰላ ከማዕከላዊው ኢትዮጵያዊ ተቋም ጉብ ይላል። ምህንድስናውን ልባሙ
አቶ ለማ መገርሳ ይከሽኑታል፤ ድምጣቸውን አጥፍተው በእርጋታ እና በስክነት። ሹመቱን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስተሩ ተደላድለው ይፈጽማሉ።
ግርባው ብአዴን ታጣፊ አልጋውን ዘርግቶ እንጉልቻውን ሲለሸልሽ ኦሮማይዜሽን በሾርኔ ኢትዮጵያን በአጭር ጊዜ መዳፉ ውስጥ አስገብቷል
አይዋ ኦነግ። ዕውነቱ ይሄ ነው።
ስለዚህ ነባሩ ልቅልቅ ባለወንበር አቶ አባ ዱላ ገመዳ የሌሊቱ ስብሰባ አውራ ታዳሚ እሳቸው ነበሩ።
ብዙ ጊዜም እኔ ብሎጌ ላይ ጽፌበታለሁኝ። ፊት ለፊት አብይወለማ ይውጡ እንጂ ቱባ ሥልጣን ነበራቸው።
ለችግኝ ተከላ፤ ለአትክልት
እውሃ ለማጠጣት፤ ለአጨዳ፤ ለአገር ውስጥ እና ለውጭ ሽርሽር፤ ለወግ ገበታ፤ ለአይዋ ጽዳት ለአስኮባ ሞድ፤ ለኤርትራ ፕሬዚዳንት
ሹፌርነት፤ ለአዳራሽ እድሳት፤ ለቀለም ዴኮሬሽን ምርጫ እና የሥልጣን ሹመት ለማጸደቅ በጠቅላላ ለመድረክ ኢንተርተይመንት ዶር ሥሙ
አሉ።
ይህ ገሃድ እንዳይታይ፤ እንዳይፈተሽ ደግሞ ለዚህ ዝለት ትልቁን አስተዋፆ ያበረከተው ግን የሊቀ ሊቃውንቱ የፕ/ አለማርያም
„አክ ወሬ“ የደቦ ቅንነት ማህበርተኞች ናቸው። አሁን እራሱ በዚህ ሁሉ የህዝብ ሰቆቃ ድምጽ የለም። እነዝም።
ብቻ አሁን የሆነው በስልት አስቀድመው ያኃቲ መንፈሱን የናዱትን ደቡብን ለኑዛዜ ለማብቃትና በኦሮሙማ
ቅኝተ - ተገዥነት ለገበሮነት የምዝገባ ሂደቱን ለማሟላት የሥልጣን ክፍፍል ነው የተደረገው።
የደቡብ የንስኃ አባት አቶ አባ ዱላ
ገመዳ። ጥምቀተ - ሞጋሳ በነቂስ በመደበኛ ይደረጋል። ኦሮሙማ ሳያስጠጣ የልቡን ያደርሳል። ዬጊዜውን አጋዥ ሰፌድ ከአግልግሎት በኋላ
መሸኜት ነው በተመቼው አስኮባ። የደቡብ አንድነት መራራ ሰንብቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል። ለቀለሃ ከተመደበው ከአማራ ሊሂቃን ይልቅ ለአሰኮባ
የተመደበው ደቡብ የተሻለ የመኖር ዕጣ ፈንታ አለው። የአማራ ሊሂቅ ግን ሦስተኛው ኦፕሬሽንን ይጠበቅ። ከመሠረቱ ነው የሚነቀለው።
አሁን ብትንትን ብሎ የባጀውን መንፈስ በክፊል ግዛት ለአቶ አባ ዱላ ገመዳ ሰጥተው ሰሞኑን በሰሩት
ሸፍጥ የአማራ ተማሪዎች እገታ እና የአኖሌ የልበወለድ አፍቅሮት የበቀል ማወራራጃ አስመልክቶ አማራ ቢቆጣ ለመልቀም ደግሞ ፊታቸውን
በሙሉ አቅም ወደዛ ለማዞር ምቹ ሁኔታ ፈጥረዋል።
እሳቸው ስል ጠሚሩን ማለቴ ነው። ቀልባቸው፤ ጦራቸው፤ ውቃቢያቸው አማራ ላይ የተቸከለ ስለሆነ
ያን ለማሳካት ለደቡብ ልብጣል የሚደረግበት የሰው መረጣ መከወኑ የተደመጠው በሸኘነው ሳምንት መጨረሻ ነው። በነገረ አቡዱላ ዙሪያ
ደቡብ የውጠት ስክንት ሁን ተብሏል። አማራ ላይ ግን አለ ነገር።
አማራ፤ አዲስ አበባ እና የውጭ ጉዳይ ተግባር ነው የሳቸው ወሳኝ
ቀጠና። ታስታውሳላችሁ ከአንድ ዓመት በላይ የውጭ ግንኙነትን ከኦህዴድ ውጪ ትውር ያለበት አንድም ነፍስ አልነበረም። ዝግ ነበር።
አብሶ የኤርትራ ጉዞ አንድም ቀን የአማራ ሊሂቅ ታድሞ አያውቅም።
ሌላው ቀርቶ ኤርትራ የነበሩትን የአማራ ታጣቂዎች ጋር ለመደራደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፤ ዶር
አንባቸው መኮነን ነፍሳቸውን ይማረውና ተቀምጠው ኤርትራ ታምነው የተላኩት ጃዋራዊው አቶ ንጉሡ ጥላሁን ነበሩ። አያችሁ ጨዋታውን።
ለኦነግ ደግሞ ዶር ወርቅነህ ገበዬሁ እና አቶ ለማ መገርሳ ነበሩ። አሁን ደግሞ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ተብለው
ተቀምጠው አቶ ለማ መገርሳ ነው አብረው ነው የሚሄዱት ወይም የገንዘብ ሚኒስተሩ አቶ አህመድ ሸዴ። አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ውጭ ጉዳይ
ከሆኑ በኋላ ስንት ጊዜ ኤርትራ ሄዱ ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ? የተከደነው ሚስጢር ምንድን ነው? የሚዶለተው በማን ላይ ነው?!
ልባም ኢትዮጵያዊ ነፍስ ይፈልጋል አመክንዮው። ፍርሰትን የተጠዬፈ።
የሆኖ ሆኖ ያው ቁንጥንጡ የኦሮሞ ፖለቲካ የድንገቴ ትውናው ለእኛ አንጅ ባወጡት ቅደም ተከተል
መሰረት በአቶ ለማ የዴሞግራፊ አሉታዊ ምህንድስና ቀጥ ብሎ ሁለመናው እዬተከወነ ይገኛል። ዝንፍ የለም። ደረጃ በደረጃ በገዳ ሥርዓተ
- ወግ እዬተከወነ ነው።
አዲስ አበባ ላይ እንዴት እንዲህ፤ እንዴት እንዲያ ተደረገ ይደመጣል። አዲስ አበባ እምትተዳደረው በኦሮምያ መንግሥት ነው። በኦሮምያ መንግሥት ስል ኢትዮጵያም የምትተዳደረው በአዳማ ሥርዕዎ መንግሥት መሆኑ
ይታወቃል።
ነገር ግን አዲስ አበባ ባለቤትነቷ የኦሮሞ
ነው የሚለውን ነው ያስከበሩት ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ናቸው። ይህ „ቁርጥ ያጠግባል ነው“ እወቁት። ፍሬ ዘሩ ይኽው
ነው። ለዚህ ነው አዲስ አበባ ላይ የሚታቀዱ መንፈሶች ሁሉ መከነው እንዲቀሩ የሚደረጉት። ለቅዱስ ሲኖዶስ ቁጣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ የታመሱበት
ይህ ገመና እንዳይጋለጥ ሸፍነው ለማቆዬት ነበር። ቀኑ ሲደርስ ታዩታላችሁ።
„አንዴ ለውጥ ጀምረናል። አንዴ የሚያምር ውስጥ ገብተናል።
አንመለስም“
{ዶር አብይ አህመድ}
ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ፈቃድ አዳማ ሂደሽ አውጪ ትባላለች - ነገ። ከምርጫ በኋላ አደማ
ወደ አዲስ አበባ ከመጣም እዛ ደጅ ጥናቱ ይከወናል። እነሱ ሥራቸውን በትጋት እዬሠሩ ነው። ሌሎችም ሃይማኖቶችም የ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ
እጣ ፈንታ ይደርሳቸዋል። ጠብቁት። ይህን መርዶ የኢትዮጵያ ህዝብ አላወቀውም። ተደምረናል የሚሉት ድርጅቶች ሆነ ተናጠል ነፍሶችም
ሳይቀር ሸፍጡን አልተረዱትም።
ለዚህም ነው የአማራ ሊሂቃን በረድፍ የተረሸኑት እነ አቶ ምግባሩ ከበደ። ወጣት ትንታግ ጉልበታም
ሞጋች ነበሩ ነፍሳቸውን ይማረውና። አሁን እንጉልች ነው ያለው። ልብ የተገጠመለት።
ምን አልባት „ጭምትነት“ ማዕረጉ ለሽ ብሎ ስለመተኛቱ
ካልሆነ „ጭምትነት“ በፖለቲካ አስተሳብ ፍዝነት ድንጋይነት ነው። የፖለቲካ ትጋት አክቲብ እንጅ ፓሲብ አይደለም። ለዛውም ኦነግን
ያህል ተፈጥሮን ያህል ዕንቁ ጸጋ በጭካኔ የሚያርስ የአገር መከራን ተሸክሞ። ዝንገትን ማወጅ ቅልነት ነው።
አብሶ በጥልቀት ሴራውን የተረዱት ነብዬ ብርጋዴር አሳምነው ጽጌ ስለነበሩ፤ ያ ሁሉ ዓለም አቀፍ
ዘመቻ ከዚህ ሚስጢር መጎልጎል ጋር የተያያዘ ነው። የእነ አቶ ኽርማን ኩኽን እርዱን የተባሉበት ፍሬዘር ይህ ነው። እኔ ፌስቡኬ
ላይ ምስላቸው የነብዬ ብጄ አሳምነው ጽጌ የጸጋ ስግደት የሚደረግበት ዘመን ይመጣል ስል ነበር።
ኢትዮጵያ የምትድንበት ሚስጢር ተገልጦላቸው
ነበር። ግን እነ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አሳልፈው ሰጧቸው። እራሳቸው ናቸው አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ዝርዝሩን ለጠቅላይ ሚኒስተር ሰጠሁት
ያሉት። አስመነጠሩት የኢትዮጵያን የመዳን ማህደረ - ተስፋነት። ግን አላዛሯ ኢትዮጵያ ምን በደለቻቸው?! እንዲህ በዬዘመኑ የመከራ
ድውለት የሚያደርጓት?! ምን አለ በቃሽ ቢሏት?!
· የኢትጵያ የብልጽግና
ጊዜ ተልፍኘ ጁቢተር?
ጠ/ሚ ዶ/ር ዐብይ አህመድ ከደ/ብ/ብ/ህ ክልል ከተውጣጡ ተወካዮች ጋር ያደረጉት ውይይት (ክፍል 1)
ጠ/ሚ ዶ/ር ዐብይ አህመድ ከደ/ብ/ብ/ህ ክልል ከተውጣጡ ተወካዮች ጋር ያደረጉት ውይይት (ክፍል 2)
መቼም ብግን እንደሚሉብኝ ነው ጠቅላይ ሚኒስተሩ። ምኔ ሞኝ ኢትዮጵያን ከፊት ለፊት ገጩ አደረግኳት።
እሳቸውም ተስቷቸው ነው መሰል አስቀድመው በ“ኢ“ን ጀምረውታል።
ያው በውስጣቸው የለችም ይህንም እራሳቸው ናቸው አማረብኝ ብለው የነገሩን። በህዝብ ሃብት እና ንብረት በመሃያ እዬኖሩ ለአማጽያን
መረጃ እሰጥ ነበር ብለው። ህም! አገርን የከዳ የአገር መሪ? የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስተርንት? እም።
ወደ ቀደመው ምልሰት ሲሆን እናላችሁ የዶር አብይ አህመድ ንግግር እንዲህ ይለናል … ለተስፋ
ያመለጠ ልበለው፤ በገበጣ የተመለጠ ጉድጓድ ይባል ወይንስ ማጅካዊ ካፒቴንነት ልበለው ወይንስ የልጣጭ ገረፍታ። ኦ! አውሎ ያሳድራል የሳቸው ልግጫ ሆነ አልጫ ምኞት። ግን የት ሄዱ?
„የኢትዮጵያ የብልጽግና ጊዜ ነው። የኢትዮጵያ የብልጽግና
ጊዜ ነው። የብልጽግና ጊዜን ማቆም የሚችል ኃይል የለም። ይህ
አዳራሽ 35/36 ዓመቱ ነው። ከ35/36 ዓመቱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አሁን የምታዩትን ግርማ ሞገስ ያገኜው በብልጽግና ዘመን ነው።“ „ቿቿቿቿቿቿቿቿቿቿቿቿቿቿቿቿ ጭብጨባው ቀለጠ።
በተገኘው ቦታ ሁሉ ብሄራዊው፤ አህጉራዊው፤
ሉላዊ ቦታ ሁሉ የዞጋቸውን ልጆች እዬመደቡ እኮ ነው ይህን „ብልጽግና“ የሚሉት። ጥምንምን የሆነ ነገር። እንደ እሳቸው በብዙኃን
መንፈስ የተጫወተ ብልጥ የለም። ሰርክ ማጭበርበር። „ገድሎ እግዚአብሄር ይማርህ“
· የመወድስ ምርቃን።
ሌላው የመወድስ ምርቃን …. እኔ ምን እንደ ተመኘሁ ታወቃላችሁ? ይህን ጭብጨባ ቀርፆ በመንገዱ
ሁሉ ጠሚር አብይ አህመድ በሚያልፉበት ማሰማት ማይክራፎን ተክሎ። ጎንደር በአዳባባዩ ድምጽ ማጉያ ነበር። እንደዛ ቢያሰሩስ አልኩኝ።
የጭብጨባ ናፍቆት ስለአለባቸው። አልጠገቡትም ጭብጨባውን። ይችን ቀብ አድርገው በራሳቸው ፈጠራ የተከወነ አድርገው ደግሞ ድምጽ ማጉያ
አዲስ አበባ ላይ ተክለው ምርጫ ቅስቀስቀሳውን እንዳይሰነኩት። ለማደንቆር።
ብቻ ሳስተውላቸው ያልጠገቡት ነገር አለ። የ22 ወራት ሙሉ የጭብጨባ ጠኔያቸው አልታገሰም። አልጠገቡም።
የጆሮ ጉብራው እስከ ጥጉ አልተዳረሰም። ስንቅ ትጥቃቸው ጭብጨባ፤ መወደስ ብቻ ነው። የዳውሮ አባት አሽረዋቸዋል። ወዳሴውንም አሹሙሩንም።
· የኦሮሙማ
ዴሞግራፊ ልባሙ ጉዞ ወደ ደቡብ።
እንዳይገለጥ የሚፈለግ ሚስጢር ግን አለ። መሰናዶው ጥምቀተ - ሞጋሳ ነው። ለዛ ግርዶሹ ደግሞ
ይህ የህሊና ስልበት ተሰናዳ። ይህን መሰል ቅብ ጉዞ fake ነው „ብልጽግና“ እያሉ ልባችን የሚያፈሱት። አሁን ደቡብ ከነ ፍርስራሹ
በተበተነ መንፈስ ይተረሳል በገዳ ስርዓት። ጉዳዩ የመንፈስ ነቀላ እና ተከላ ስለሆነ ረቂቅ ነው። በአጭር ጊዜ አይታይም። የባቢሎን
ግንብ ነው የሚሠሩላቸው። አንድ ቢሆኑ የተፈሪነት አቅም ይኖራቸው ነበር። አሁን ግን ነጣጥለው አቅማቸውን መቅኖ ያሳጡ እና ቀስ
እያሉ ያንበረክኳቸዋል። በዚህ ውስጥ ኢትዮጵያዊነት ጥቁር ዕጣ ይሸለማል።
አሁንም በድርጅታዊ ሥራ ወጣቶችን አዘጋጅተው ስለ ብሄራዊ
ሰንደቅ ዓላማ ምሬት እንዲያሰሙ እዬተደረገ ነው። ይህን የሴራ ጥልቀት እንኳን መነሻውን ከልብ ሆኖ ማድመጥ አልተቻለም። እስቲ ይቀጠል ንግግሩ።
ሲቀጠል ንግግሩ … „ ይህ ምልክ ነው። ምልክት ነው።
ይህ ምልክት ነው። መጀመሪያ ቢሮ፤ ቀጥለን አዳራሽ፤ ቀጥለን ግቢ፤ ቀጥለን አዲስ አበባን፤ ቀጥለን ኢትዮጵያን
እንቀይራለን“ በለው! ቿቿቿቿቿቿቿቿቿቿቿቿቿቿቿቿ ሰናይ ተናኘ በተመላላሹ መሪ ልቦናም ሙሉነት ተከተበ ሿሿቴው። የተወለዱባትንም
ቀን አበክረው አስመረቁ።
ጭብጨባው እኮ ፋታ አልነበረውም። ከዴሞግራፊ ጀመርን ቢሉ ምን አለበት።
ቀጠለ ንግግሩ „ አንዴ ሥራ ጀምረናልን። አንዴ ለውጥ ጀምርናል። አንዴ የሚያምር ውስጥ ገብተናል።
አንመለስም“። ያደክማል። ይጨንቃልም። የአዳራሽ አዳሽነት ማዕረግ ሆኖ ነው
የሚነገረው ለአንድ የአገር መሪ። ለአንድ የኢጋድ መሪ።
አንደኛ ነገር እሳቸው ለማህበራዊ ኑሮ ኮኦርድኔተር አልተሾሙም። ለቤት
አዳሽነት፤ ለግቢ ዲኮሬሽን፤ ለአዳራሽ ውበት አስከባሪነት፤ ለአትክልት ውሃ አጠጭነት አይደለም ጠቅላይ ሚኒስተር ሆነው የተሾሙት።
የትኛው ዓለም ውስጥ እንደሚኖሩ ያሳፍራል። በጣም ያስፈራልም። አሁን በምን ዓይነት ሰብዕና ውስጥ እናንብባቸው ይሆን? በማዋዕለ
ህፃናት የመዝናኛ ሥፍራ ቅንብር ውስጥ?! የኃላፊነት እና የተጠያቂነት ግዙፍ ተልዕኳቸው አናባቢ አጣ። አናባቢ ከታጣ የፊደል ድርድር
ብቻ ነው የሚሆነው። „አ“ የለም።
ለአንድ ጠቅላይ ሚኒስተር ቀለም መቀባት
በኽረ አጀንዳው ነው። የሚራው ህዝብ እንደ ቅጠል እዬረገፈ። በስጋት ህዝብ ጠወልጎ፤ በፍርሃት ተሸማቆ። ሚሊዮን በራህብ ውስጥ
ሆኖ። ሚሊዮን የመኖር ዋስትና አጥቶ። ሚሊዮን በተስፋ እጦት እዬማቀቀ።
ሰው ወጥቶ መግባት ተስኖት። ህፃናት ታግተው እዬተረሸኑ፤
ሴቶች ታግተው እዬተሰቃዩ በአሰቃቂ ሁኔታ እዬተደፈሩ፤ በአካላቸው ላይ ጭካኔ እዬተፈጸመባቸው። የአማራ ልጅ ብትን መቆሚያ አፍር አጥቶ እዬተሳደደ ለሳቸው ቁም ነገር
„ብልጽግና „ማለት አዳራሽ አዳሽ መሆን ነው። ስንት እብድ ቀን አለ?! ስንት ዓይነትስ ዕብደት አለ? ይከረፋል ከውስጥ
ሆናችሁ እንደ ዜጋ ዕንባውን እና የሳቸው መቀናጣት በዬሉምነት ስትመዝኑት።
ይህ ለሳቸው „አንዴ ሥራ ጀምረናልን። አንዴ ለውጥ ጀምርናል። አንዴ የሚያምር ውስጥ ገብተናል።
አንመለስም“
ለሰቆቃ እርክክብ፤ ለስቃይ እርክክብ፤ ለመታረድ እርክክብ፤ ለመንድ እርክክብ፤ ለመታጨድ እርክክብ፤ ለመታገት እርክክብ፤
እንደሰው ላለመታዬት እርክክብ ለሳቸው „ሥራም፤ ለውጥም፤ የሚያምር ነገርም።“ ነው። እግዚአ!
አንድ የዲኮሬሽን ባለሙያ የሚከውነው ተግባር እንደ አንድ ትልቅ ብሄራዊ፤ አገራዊ፤ አንጎላዊ
ስኬት ቆጥረውት ይህን ያህል እርቀት ሲጓጓዙ አዘንኩኝ። ሃዘኔ ለሳቸው ብቻ ሳይሆን ለዘመን አርቲፊሻል የሃሳብ ትከት እና ድቀት አጓጉዝ ለሚባለው የተስፋ ባቡርም። እንደዚህ ዓይነት
ነገር ሳዳምጥ ይጠፉብኛል ከምል ይስዋሩብኛል ብል ይሻለኛል። ከውስጤ ነው እምነግራችሁ። ክስመት ነው እማዬው።
የሚያሳዝነው ይህን በአምክንዮ የሚመክት የተፎካካሪ/ የተቀናቃኝ/ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት
ልቅና አንብዛም አለመኖሩ ነው። የምርኮኝነት እድፍነት ይሁን? የመካች የፖለቲካ አምክንዮዊ አቅመ አጣን። ተዋጠን። ምርኮኝነት ዘፈነብን።
እራሳችን በራሳችን በብልጭልጭ ነገር አዋረድን። ተዋረድን። እራሳችን ለማዬት እራሱ እራሳችን ያስፈራንም ያሳፍረንም ጀማምሮናል።
ይህ አልበቃ ብሎ ይህን እንደ ቁምነገር ቆጥረው ወጥተው ነፍስና ሥጋቸውን ለአብይዝም የገበሩ ወገኖች ሲከራከሩላቸው ሲደመጥ የህሊና
ተፈጥሮ እና ተልዕኮውን መተርጎም ይሳናል። የተመኩበት መንፈስ እያሰፈራቸው፤ እያሸማቀቃቸው፤ እያኮማተራቸው እኮ ነው ውርዴትን ክብሬ
ማዕረጌ የሚሉት። ነገን ያዬ …
ስንት ጊዜ ይታፈር?! ስንት ጊዜስ አንገት ይደፋ? ተልፈሰፈስን። የተነሳንበት የነፃነት ፍለጋ
ጉዞ ዓላማ ጭብጥም ሙሴም አልነበረውም ማለት ነው። እንዲህ የምንፍረከረክበት አመክንዮ ምክንያት ያነ ነው።
ፍላጎታችን ልቅና በልዕልና፤ ጥበብ በጥሞና የነበረው መሪ ፈጽሞ አልነበረው። ማህንዲስም አልነበረውም።
ወናነት ወረሰን። ባዶነትም ፈተነን።
በፊት በፊት „ህወሃት ይውረድ ብቻ ¡“ ነበር፤ አሁን ደግሞ „ምረጡን ብቻ ከተመረጥን በኋላ
ታዩናላችሁ¡“ ነው፤ የቀጠሮ ፓርቲ ተስፈኞች ሞቶ። ሌላው አቅም እንዳይወጣ ቅብረት ነው፤ ስብረት ነው፤ ሚዲያውን በሙሉ በሞኖፖል
መቆጣጠር ነው፤ እነሱ ደግሞ ቅባውም፤ የፖለቲካ ቁመናውን አልተሰጣቸውም። ልውስውስ።
ይህው ፍላጎታችን መኖ መካች አቅም ጠፍቶ ለኦነግ
ተረከበ። ስንት ነገር የተገበረበት፣ ስንት ትውልድ እና አቅም የባከነበት የነፃነት ተጋድሎ እንዲህ ሆኖ ምንትሶ ሆኖ ቀረ። ብል የበላው ጨርቅ ሆኖ ባክኖ ተብተክትኮ ቀረ
ድካማችን ሁሉ። በዚህ መከራ ውስጥ እንኳን አብረን መቆም አልተቻለም። „ የአማራ ተማሪዎች“ ለማለትም ድፍረት የለም። በሸፍጥ አጋ ተለይቶ መንፈስ አሁንም እንደ ቀደመው ይዋጋል።
ግን የት ነን? እነማንስ ነን? ምንስ ነን? ማንስ ነን? ስለማንስ ነን?
· የአበደው ዕለት።
የአንድ የአገር ብቻ አይደለም ኃላፊነታቸው ዛሬ ዶር አብይ አህመድ - ቢያውቁት። የዓለሙ የሰላም
አባት ሆነው የኖቤል
ተሸላሚ ናቸው። ከሰማይ በታች ክብራቸው ሉላዊ ሆኖ ላይ
ተንጠልጥሏል። የተሸለሙበት ቀን ታህሳስ 10 ቀን 2019 እ.አ.አ ነው።
ይህ ቀን ልዩ ሉላዊ ታሪካዊ የሰብዕዊነት ቀን ነው። የሚናፈቅ
ቀን ነው። የ1948ቱ እ.አ.አ ሁለንትናዊ የሰባአዊ መብት አስከባሪው ዓለም አቀፍ መንፈስ የ30 አንቀፃት ድንጋጌዎችን መኖርን
ለማኗኗር የመኖር ነፃነት በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወጀበት። ትልቅ አስፈፃሚ አካልም የተቋቋመበት። ዓላማው ጥልቅ፤ ግቡ ውቅያኖስ
- ህንፃው እራሱ ግዝፈቱ፤ የሚሠራውም የሠራተኛ መበራከቱ የአንዲት ትንሽ አገር ሙሉ መንግሥታዊ መዋቅር ያክላል።
ቀኑን ብቻ አስባችሁ ከዶር አብይ የሹመት ዕለት ጀምሮ የሰብዕዊ መብት እረገጣን በኢትዮጵያ ስታስቡት
ዓለም እራሱ አማኑኤል ሆስፒታል የገባች ይመስላችኋል። አንድ ሽልማት ከተነሳበት ዓላማ መነሳት አለበት ቀጣይ ጉዞው።
ዛሬ ከእሳቸው ሉላዊው እውቅና ዓለምም የተባ ተመክሮ
እንዲያወጡ ይሻል። አቅም ማዋጣት ይኖርባቸዋል ለዓለሙ ሁለንትናዊ ሰላም ሆነ ሰብዕዊ መብት መከበር። እሳቸው ግን አንድ የኮንስትራክሽን
መደበኛ ሠራተኛ ከሚስራው ተልዕኮ ተቀርቅረው ከዛ ይትበሰበሳሉ። ይንጨባረቃሉ። ቀለም መቀባት ለሳቸው ምህዋር መምጠቅ ብቻ ሳይሆን
አገር የሚመራበት ፖሊሲም ነው። የሚፈነድቁበት። ዎህ!
„መጀመሪያ ቢሮ፤ ቀጥለን አዳራሽ፤ ቀጥለን ግቢ፤ ቀጥለን አዲስ አበባን፤ ቀጥለን ኢትዮጵያን
እንቀይራለን። አንዴ ሥራ ጀምረናልን። አንዴ ለውጥ ጀምረናል። አንዴ
የሚያምር ውስጥ ገብተናል።
አንመለስም“
ቅኖቹ የአገሬ ልጆች … እኔ በጋ ሲመጣ ትንሽዬዋን ቤቴን ሁልጊዜ አድሳለሁኝ። እራሴ ነኝ በዲዛያን
ቀለም እምቀባው። በልምድ የሚገኝ ተግባር ነው ቀለም መቀባት። ይህ የአንዲት አገር ወሳኝ „የብልጽግና“ የፖሊሲ መስመር ሆኖ ስትሰሙት
ይታክታችኋል።
የሚገርመው ኢትዮጵያ የምትመራበት ህላዊነትም ህሊናዊነትም ቀለም
መለቅለቅ እንደ አገር መርኽ የፓርቲ ፕሮግራም መታዬቱ ነው። ያማል። በውነት ያማል። ኢትዮጵያን እንደ አንድ የሚኒስተር መስሪያ
ቤት የሙከራ ጣቢያ ነው ያደረጓት። አገርነቷን ጨርሶ ዕውቅና ሊሰጡት አልቻሉም። በቃ ተራ ኃላፊነት አደረጉት ጠቅላይ ሚኒስተርነትን።
የጣውላ ድርድር አድርገውት አረፉ ኃላፊነታቸውን። ማህከነ!
ለማዘን እራሱ እጅግ እግሩ የጠፋበት ጉድ ነው። የትኛው ይቅደም ትውልድ
ይቅደም የሰብዕና ግንባታ ይቅደም? ውልየለሹን ጉዞ እንደ ለመደብን ተያይዘነዋል። አዳራሽ አዳሽነት የልቅና ልዕልና?!
ልጆች እራሱ ከሳያችኋቸው ይሠሩታል። ከዚህ አገር ልጆች በህፃናት ማቆያ የሚማሩት የመጀመሪያው
ነገር ቀለም መለዬት እና መቀባት ነው። ምን አልባትም „አንዴ ጀምረነዋል“ ሲሉን ከዚህ ጋር በሚስጢር የሚገባባ ይመስላል። ሥራም
የጀመሩት „ብጽግናቸው“ ከታወጀ ዕለት ጀምሮ ዕለታዊ ስለመሆኑ ነው የሚነግሩን። እስከ ዛሬ አልነበሩም ማለት ነው። የት ነበሩ?
ጁቪተር? አብሰንት ነበሩ ማለት ይሆን? ግን የት ነበሩ?
አቅሙ ከነበራቸው የሚያስቆም ኃይል ከሌለ፤ ስጋት ከሌለባቸው ስለምን ኢህዴግን በብሄራዊ የአባላት
ጠቅላላ በጉባኤ አያከስሙትም፤ „ብልጽግናቸውንም“ በብሄራዊ ጉባኤ ሥርዓት ስለምን አያበለጽጉትም? „ብልጽግናቸው“ እራሱ የመሥራች ብሄራዊ ጉባኤ ታሪክ
የለውም። ፈት፣ የነተበ ሆነ።
ለዚህ ነው እኔ የጨረቃ
ቤት፤ የዓዋጅ ድርጅት፤ የዱቤ ድርጅት፤ ሙሽራው ኢህዴግ እምለው። መሪ ዕቅድ ያልነበረው፤ ፕሮግራሙ የማይታወቅ መናነትን እንዲህ
በፕሮፖጋዳን ሰማይ ጠቀስ ከሚያደርጉት ዝግ ብለው ቢያደምጡት ይገባ ነበር። እዬሄዱበት ያለውን ቅዬሳ መርኽ መር አይደለም።
ጹሑፉ
ውስጥ ቃሉን ለመጠቀም „ብልጽግና“ በሌለ ነገር ስለገዘፈ ይቀፋል። እራሱ „መደመር“ የሚለውን እኔ ለመጠቀም ፍላጎቱ የለኝም በሃሳቤ
ውስጥ። ኢትዮጵያን የመሸጥ ያህል ይሰማኛል።
እሚገርመው እኮ ደርግ በሠራው አዳራሽ እኮ ነው ይህን ያህል መስቃ የሚወርደው „ለመጀመሪያ ጊዜ“?
አቤት መቀናጣት?! „ይህ አዳራሽ 35/36 ዓመቱ ነው።
ከ35/36 ዓመቱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አሁን
የምታዩትን ግርማ ሞገስ
ያገኜው በብልጽግና ዘመን ነው።“
እሳቸውን ለጣለለት
አዳራሽም ነው አጨብጭብልኝ ነው የሚሉት። ሌላው ባነጸው፣ ሌላው
አቅዶ በከወነው ልዑቅ ተግባር ገብተህ ኖራ ረጭተህ በቃ ትኮፈሳለህ።
ወቄቱ ጠፋብኝ የጠቅላይ ሚኒስተርነት የውኃ ልክ።
የዶር አብይ አህመድ መደበኛ ሥራቸው ለመሆኑ ምንድን ይሆን? አናፂነት ወይንስ ቀልም ቀቢነት
ወይንስ የዲኮሬሽን ባለሙያነት ወይንስ ጭብጨባ አነፍናፊነት? የት ነው አድራሻቸው? ለመሆኑ ኦሮምያን እሳቸው ተመርጠው የመጡበትን
መምራት ይችላሉን? ሙሉ ትግራይን ሙሉ ኦሮምያ እሳቸው የመምራት አቅም እኮ የላቸውም።
ደቡብ የሚሰበሰበው አዲስ አበባ ላይ ነው። ኦሮምያ እኮ እራሷን ችሏል። እንደ አንድ ሉዑላዊ አገር ነው ያለው የመንፈስ እርግጫ እና ፍጥጫ። በኢትጵያ ሙሉ መዋለ መንፈስ፤ መዋለ ንዋይ አቅም ኤርትራ እንደ ተገነጠለችው ተመሳሳይ
ተግባር ነው እዬተከወነ ያለው። እርክክቡን በመንፈስም በአካልም ጥሞናን ከሰነቅን፤ በማስተዋል ሂደቱን እያዬን ያለነው ይህን
ዕውነት ነው። እዛ ኤርትራ ነጋ ጠባ የሚሄዱትም ይህን ተመክሮ ለመቅሰም ይመስላል።
ቀጣዩ … በኢትዮጵያ አቅም ኦሮማይዜሽን እርዕሰ መዲናውና አዲስ አበባን ብቻ ሳይሆን የዲፕሎማት
ማህረሰቡን ጨምሮ በወረራ መጠቅለል። ኢትዮጵያ ቀፎ ሆኗ በኦሮማይዜሽን ቀለም መስከን። ቀፎው መጠሪያው ኢትዮጵያ ይሆናል። ቀለሙ
በአገረ ኦሮምያ ሥር ይሆናል። በጥልቀት ይታሰብ። የባጀው የጉዞው አቅጣጫ ይህ ነው። መሠረታቸውን ነው ሲያደላድሉ የከረሙትም።
እኔ እንደሚረዳኝ ኢትዮጵያ የምትዳደረው በሳቸው ሥም ሌላ ኃይል እዬመራት እንዳለ ነው። ሠራዊቱን
የሚያዘውም ያ ኃይል ነው። አዬር ኃይሉን የሚያዘው ያ ኃይል ነው። ደህንነቱን የሚያዘው ያ ኃይል ነው።
ያ ኃይል ደግሞ ኢትዮጵያ
ፈርስት ሳይሆን ኦሮሞ ፈርስትን ለማሳካት፤ ኢትዮጵያን እንዳትነሳ አድርጎ ለማድቀቅ የተሰለፈ ነው ብዬ ነው እማስበው። ፍንጮች ቢታዩኝም
ጊዜ ሰጥቶ ማጥናቱ ስለበጀ እንዲህ ሸብልዬ ላስቀምጠው።
ከእውነት በላይ የጥሞና እውነቱ ግን
ይህ ነው። ይህ ኃይል ትቢያ ለብሶ የኖረውን አፍራሽ ፍላጎቱን እና የበቀል ቁጭቱን በህጋዊ መንገድ ተልዕኮውን
እያሳካ ነው። ለዚህ ተደማሪ አጋፋሪዎች ሙሉ አቅም በማዋጣት ዘመኑን አብሮው እያርመጠመጡት እያከሰሉትም ነው። የውጭ እጅም ይታሰብበት።
እዬፈረሱ ሃኒ ሙን የለም እና።
· ጠቅላይ
ሚኒስተር አብይ አህመድ ተቸግረው ነው ስለሚሉት ቀለጤ ቅኖች፤
የቀላጤ ቅኖች ካድሬዎቻቸው ድካም ስላለ ይህን ሃሳብ ትንሽ እንሂድበት። ለምን ብለን እንጠይቅ?
ይህን ብሄራዊ ችግር ሊቋቋም፤ አቅም ሊሰጥ፤ ሚዛን ሊያስጠብቅ የሚችል ኃይል ሲነሳ እሳቸው እራሳቸው አራስ ነብር ሆነው ስብርብር፤
እንኩትኩት ያደርጉታል። አማራ
ክልል የሚሰሩ ሸፍጦች ሁሉ የዘመን መስታውቶች ናቸው። አዲስ አበባ ላይ ያለው አመክንዮም ይኸው ነው።
1.
አቅም ያላቸውን
የፖለቲካ ሊሂቃንን ሆነ ሰብዕናዎችን አያስቀርቡም።
ለምን? ፊት
የሚነሷቸው ብቃቶች ኢትዮጵያ ተቋማትን በፈቀዳቸው
ሲነኩቱ ያን የሚመክት አቅም ብቅ እንዳይል ያፍኑታል፤ ያግቱታል፤
ማዕቀብ ያስጠሉበታል።
2.
ህግ ጣሾች
አገርን መጉዳታቸውን ያውቁታል። ህግ እንዲያቸው፤ ህግ
እንዲፈትሻቸው፤ ህግ እንዲጠይቃቸው፤ ህግ እንዲመረምራቸው
አይሹም፤ ለምን?
3.
በአንጻሩ
እሳቸው በፈበረኩት የፖለቲካ ሴራ ሊጠቅሙ የሚችሉ
የአገር ሃብታትን ሲያሻቸው በቀለሃ፤ ሲያሰኛቸው የካቴና ስንቅ
ያደርጋሉ፤ ለምን?
4.
ዓለም አንድ ማህበረሰብን ነጥሎ ወንጀለኛ አድርጎ እንዲያይ የሄዱበት
የሴራ ልክ ሲስተዋል አማራ ከኢትዮጵያዊነት ጋር ያለውን ፍቅር
ለማምከን በቀጣይ በአማራ ህዝብ ላይ ለሚሠሩ የታቀዱ ወንጀሎች
ተጠያቂነት እንዳይኖርባቸው የህሊና መሰናዶ ለማድረግ ሪፖርት ሲሰጡ
በምን ሁኔታ ነው? ለምን? በቅጽበት ለጎረቤት አገሮች ሁሉ ነገረው
እርዳታ ይጠይቃሉ? ዓለምንም ሚስሊድ ያደርጋሉ? ለምን?
5.
የውጭ ግንኙነቱ ስምምነት ዝግ ነው። ለምን?
6.
ደፍረው በሚወስዷቸው እርምጃዎች የአንድዮሽ ውሳኔ ያጠቃው ነው፤
ለምሳሌ የአጤ ሚኒሊክ ቤተ መንግሥት፤ ነገረ አባይ እና የኢንጂነር
ስመኘው ህልፈት
ጉዳይ የውሃ ሽታ ሆኖ መቅረት። ለምን?
7.
የኢታ ማጆሩ ህልፈት እና ዕድምታው ምንድን ይሆን? ግቡስ?
8.
የአማራ ክልል ሊሂቃን ህልፈት እና ውስጡ የያዘው እምቅ አጀንዳ
ምንድን ነው? የክልሉ ወናነት ስለምን ተፈለገ?
9.
የደቡብ ብተናስ ምን ይነግረናል?
10.
አዲስ አበባ ላይ የመስከረም 2011 ዓም የ አደባባይ እርሸና?
ከብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማው ጋር ያለው የቂም በቀል ዕድምታ እና ዛሬ
ያለው ይፋዊ አደባባይ ላይ የታወጀበት ጦርነት ወደዬትኛው አቅጣጫ
እዬወሰደን ነው?
11.
ስለምን ይሆን ሮል ሞዴል የሆኑ ነፍሶች በአንድም በሌላም ክብራቸው
እንዲርቃቸው በትጋት የሚሰራው?
12.
ስለምን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ብቻ የጠና
ስውር ዕቀባ አስፈለገ?
13.
ስለምንስ ትውልድ በሚያፈሩ ትምህርት ነክ ነገሮች ላይ ፍልስልስ ያሉ
ብትን ጉዳዮች እንዲነግሡ ተፈቀደ?
14.
አንድም ቀን ስለ ኢትዮጵያዊነት ከአማራ ክልል እና አዲስ አበባ
ከአዳራሽ ወግ በስተቀር በዬትኛውም ቦታ አቅም ያለው፤ ብቁ ተግባር
አልተከወነም፤ ለምን? በማን ትክሻ ነው ቅምጡ ፍላጎት ልዕለ ኃያል ሆኖ
እንዲወጣ እዬተሠራበት ያለው?
በቀጣይም በአብን፤ በባልደራስ ላይ፤ „አብሮነት“ የሚል ስብስብም፤ „ሳተናው“ የሚልም ከሰሞናቱ
አዳምጫለሁኝ በዛ ላይ በተከታታይ ተጠናክሮ የሚኖረው አፈናውንም ግድያውንም የሚታይ ይሆናል። ስለምን? ኢትዮጵያ በውስጡ ያለ ዕውነተኛ
መንፈስ ሁሉ ይመታል።
ከላይ ያነሳኋቸው እነዚህ አቅሞች ግን ውስጣቸው በጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ኢትዮጵያ ጽላታቸው
ብትሆን ኖሮ ክንድ፣ መከታቸውና አጥራቸው ነበሩ። አጠንከሬ የምገልጸው ኢታማጆሩ ሆኑ የቀደመው የአማራ ክልል ሰማዕት ሊሂቃንም የኢትዮጵያ
በትረ ሙሴ ነበሩ። ነገር ግን ከመሰረቱ ነው የተነቀለው።
አሁን የሚታይ አለ የሚባል ነፍስ የለም። ግንጥል የሆነ ነገር ነው የሚታዬው።
ይህ ይሆን ኢትዮጵያን አክብሮ መነሳት?!ቅኖቸ የአገሬ ልጆች ይህን ስትፈትሹት ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ችግር ውስጥ ሆነው ከሆነ
ስለምን ኢትዮጵያዊ መንፈስ ያለውን ተጻረው ይቆማሉ?!
ስለምንስ እግር እግሩን እዬተከተሉ ያሳድዱታል ይህን ጠንካራ ብሄራዊ መንፈስ
ለማጥቃት ስለምን ተነሱ?! ይህን ፈትሾም ሆነ በልቶ አቋም አለመያዝ ፍዝነትም - ፍርሰትም ነው።
በተጨማሪም ምደባውን፤ ሹመቱን፤ የሚያቀርቧቸውን ሊሂቃን ስታስተውሉ የተደራጀ ተግባር ለሳቸው
የተልዕኮ ስኬት ነው በማደረጃት ላይ ስለመሆነቸው ቁልጭ ብሎ ታዩታላችሁ። እናስተውል።
በሌላ በኩል ህወሃት እንዲዳከም እንጂ ጨርሶ እንዲፈልስ ፈጽሞ አይሹም። ለምን? አማራን ይቅጣልኝ
ብለው ስለሚፈልጉት። በዛውም የስሜን ፖለቲካ አመድ ይሆንላቸዋል። የሁለቱ ክልል ህዝብም ይጎሳቆላል።
ሁለቱ ክልሎች ቀና ለማለት ለማገገም በሚያስፈልጋቸው ረዘም ያለ የመፍጨርጨር ጊዜ ኦሮሙማ የድሉን
እርካብ ለዝልቀት ያማክላል። ደቡብ ነው ጉሮሮው በአቶ አባ ዱላ ገመዳ ታንቋል። ከእንግዲህ መፈናፈኛ የለውም። „የብልጽግና“ በረከተ
ሥጦታ የተስፋ የመቃብር ሥፍራ ዘመን ይሉኃል ይሄ ነው። በቀውስ ውስጥ የሚዋዥቅ የትንፋሽ ሽርሽር።
ዶር አብይ አህመድ የሁለቱ ክልል ጦርነት በፆም በጸሎት የሚሹት ጉዳይ ነው። ያተርፉበታል። በዚህ
ውስጥ „ ይህ ምልክት ነው። ምልክት ነው። መጀመሪያ ቢሮ፤ ቀጥለን አዳራሽ፤ ቀጥለን ግቢ፤ ቀጥለን አዲስ አበባን፤ ቀጥለን ኢትዮጵያን
እንቀይራለን“ ይህን የሙሽርነት ተስፋ መርምሩት።
ሸንሽነው ከወገብ በላይ እና በታች ከፍለው ይሆን ኢትዮጵያ እምትቀዬረውን? ምን
አለን በመዳፋችን?! በኢትዮጵያዊ ተቋማት ላይ ያለው የፍርሰት ዓዋጅስ
„ብልጽግናው“ በዱቤ
የያዘው ትልም እንበለውን? ተቋም እዬነቀሉ ብልጽግና አለን?
አውራ ኢትዮጵያዊ ተቋማት እኮ እዬከሰሉ ነው ያሉት። ውስጣችውም እዬተናደ ነው። እርምጃቸው በለዘዘ
ቁጥር ታማኝነታቸው ሆነ ተቀባይነታቸው ስለሚቀንስ ከባህር የወጣ አሳ ይሆናሉ። ተስፋ ሲያጣ ህዝብ ተስፋህ ነኝ ወደ አለው ይተማል።
የሹመቱን ፍሰት ስከታተለው አንድ ሌላ የኃይማኖት ኢንፓዬርም ለለመስረት ታቅዶ እዬተሰራበት ነው። ይህን የባህርዳር ከተማ ሹመትን
ለናሙና ማቅረብ የሚቻል ይመስለኛል። ይህ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶን የማዳከም እርምጃ ስውር ሴራ የምናዬው አመክንዮ ነው።
ከላይ በተራ ቁጥር 14 እንዳነሳሁት አንድም ቀን የትኛውም ክልል ከአማራ እና ከአዲስ አበባ
በስተቀር ስለ ኢትዮጵያዊነት የተሠራ ሥራ የለም። ኢትዮጵያዊነት ባለቤት የለውም። ኢትዮጵያዊነትን ለዶር አብይ ፕሮፓጋንዳ ማጣፈጫ
አዲስ አበቤ በአዳራሽ ወግ፤ አማራ ደግሞ በተለጣፊ የሩብ የዜግነት ፖለቲካ ቀንበር እንዲሸከም የሚፈለገው ዓለም ኢትዮጵያ አለች
ብሎ እርዳታም፤ ብድርም እንዲሰጥ ብቻ ነው።
· ንቅሳት።
„ይህ አዳራሽ 35/36 ዓመቱ ነው። ከ35/36 ዓመቱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አሁን የምታዩትን
ግርማ ሞገስ ያገኜው በብልጽግና ዘመን ነው።“ „ ግራማ ሞገስ አዳራሹ
ያገኘው በብልጽግና ዘመን ነው“
ሁለት ወር ሞላውን በዓዋጅ የተቋቋመው „ብልጽግናው“ ድርጅታቸው? „ዘመን“ ማለት እራሱ ትርጉሙን አያውቁትንም? ዘመን እኔ እስከሚገባኝ
ክረምት፤ ጸደይ፤ በጋ፤ በልግ ሲደመሩ ነው። እሩብ ዓመት እንኳን የለውም የሳቸው የአብይዝም በውሽልሸል እና በጥገና ጠፈጠፍ ተፈጠረ የተባለው „ብልጽግና።“
ብቻ … ነገረ ሥራቸው ያታክታል። ያልረጋ ወተት እሳት ላይ ስትጥዱት ይበጣጠሳል። መያያዣ በሳል
አመክንዮ ማግኘት አይቻልም በንግግራቸው ውስጥ። መያዣ መገረዣ የሌለው ነገር ነው አገር ላይ ያለው ነገር ልባም ኢትዮጵያን ጽላቱ
ያደረገ ሁነኛ ፖለቲከኛ ቢያገኝ። እንደ አለም አቀፉ የህግ ሊቀ - ሊቃውንት ዶር ደረጀ ዘለቀ ያለ። ካለ አጠፏቸው። ሰሞኑን ይልቅ
ድምጻቸው ጠፍቷል። በሳቸው ውስጥ እማያት ኢትዮጵያ ትናፍቀኛለች።
„ግርማ ሞገሱን“ ? ዎህ! ወይ
ተአብ አለ ተጋሩ። ግርማ ሞገስ እኮ ቁንጽሉ ቅብ አይደለም። ግርማ ሞገስ ለሙሉ አካል ነው የሚሰጠው። ግርማ ሞገስ የቁመና መለኪያ
ነው። መሉ የአዳራሹ የግንባታው ሂደት ነው ግርማ ሞገስ እንጂ የዕድሳት አቅሉ* አይደለም። ግርማ ሞገስ አቀማመጡ፤ አካለ - ቁመናው
ነው። ይህን ደግሞ ደርግ የሠራውን አዳራሽ እንጂ እሳቸው ቅንጣት አቅም ያፈሰሱበት አይደለም። ያው ነገረ የታሪክ ወረራ ስለሆነ
ካልሆነ።
ለነገሩ ዴሞግራፊ የመንፈስ ነቀላ እና ተከላ ብቻ ሳይሆን የታሪክ፤ የትውፊት፤ የወግ፤ የባህል፤
የትሩፋት ስለሆነ ነው የንጉሦች ንጉሥ የአጤ ሚኒሊክ ቤተ - መንግሥት ማንም ሳይመክርበት፤ ሳይወሰንበት፤ አቋም ሳይያዝበት ብቻቸውን
እድሳውም የታለመው። የአስፈፃሚ ድርጅቱ ኃላፊ አንዲት ጥያቄ ጠይቆ በቀላጤ ነው ከሥራ ያሰናበቷቸው አቶ ዮናስ ደስታን።
ለብጠው
እዬተጓዙበት ያለው መንገድ የሚጋለጥ ከመሰላቸው ሰይፉ በአንድም በሌላም ይመዘዛል። ቅኖችን አፍዞ ለማሰከተል። ዕውነተኛው ነገር
ግን ቅምጥ ውሽማ ፍላጎት አላቸው። እሱን እያሳኩ ነው።
የሆነ ሆኖ ግርማ ሞገስ ለማግኘት ያ አዳራሽ 35/36 ዓመት አምጦ፤ ሱባኤ ገብቶ ነበር በሳቸው
ትንተና። እንዴት ዓይነት ርካሽነት ነው። ጥያቄው የአንድ መሪ የንግግር
ጥበብ እና የጭብጥ ፍሰት በምን ይለካ ነው? ሚዛኑ የት ላይ ይቀመጥ የመሪነት ቅብዐው?! ተርቲም ሆነ የአንድ አገር ጠቅላይ ሚኒስተርነት?
በውነቱ የአንድ አገር የመሪነትን የኃላፈነቱን ቅቡልነት ዕሴቱን ተቀናቀኑት። የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስተር በነበሩበት አቅም
እንኳን ለማግኜት ይኸው እኔ እመስናለሁ ግን ታሪክ ሆኖ አልፏል „ከእርምጃ ወደ ሩጫ“ ሞቶ። ኢትዮጵያዊነት እንኳንስ ሙሉው በደርበቡ
እንኳን የለም እኔ እንደማስተውለው።
· ከቶ የኢጋድ አባል አገሮች ቀለም ቀቢ እና አዳራሽ አዳሽ
መሪ ይፈልጉ ይሆን?
የዶር አብይ አህመድ የኢጋድም ሊቀመንበር ናቸው። ኢጋድ
ጥሩ አዳራሽ አዳሽ አግኝቷል። እንግዲህ የዚህ ችግር ያለባቸው አገሮች በወረፋ የአዳራሽ ዴኮሬሽን ዲዛይነር ሊቀመንበር ስላላቸው
ጎራ ይበሉ። በሌላ በኩል ከኢጋድም ወጥተን በአፍሪካዊነታቸውም የኖቤል
ተሸላሚ ስለሆኑ ብዙ የመንፈስ መኖ አህጉራችን እማማ አፍሪካም ትጠብቃለች ከእሳቸው።
እሳቸው ደግሞ ቀለም ተራ ላይ ናቸው። በአዳራሽ ቀለም ቅብ ቅብጥ እና ቅልጥ ይላሉ። የኖራ ሰርግና
መልስ ላይ። ይህ ግዙፍ አገራዊ አጀንዳ ሆኖ ፍንክንክ ፍልቅልቅ ያደርጋቸዋል። ደረታቸውንም ነፍተው ይኮራሩበታል።
ኃላፊነትን አያውቁትም እንዳልል ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ላይ የሠሩት ድንቅ ተግባር መሰረት አለው።
ችግሩ እኔ እንደሚመስለኝ ጠቅላይ ሚኒስተር ማለት የገባቸው አያመስለኝም፤ ወይንም ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ በቅምጥ ፍላጎት ፈቅደው
ታግተዋል። ፈጽሞ ከቦታው ጋር አልተመጣጡኑም። አሁን አሁን የቦታው የሰብዕና የማንነት ደረጃውም አደጋ ላይ ያለ ይመስለኛል። ንግግርም
እኮ ፕሮቶኮል አለው። አዎና! ንግግራቸው ደረጃውን ሊጠበቅ አልተቻለውም።
የጠቅላይ ሚኒስተርነት ቦታ የሚፈልገው የዲስፕሊን፤ የፕሮቶኮል፣ የተጠያቂነት እና የኃላፊነት
ቦታ እና እና የእሳቸው ህልም አልተገናኙም። ተላልፈዋል። መስመር ውስጥ ሊገቡ አልቻሉም። በአፈነገጠ መንገድ ላይ ነው ያሉት። በጥሩ አገላለጽ በአሳቻ መንገድ ላይ ነው ያሉት።
ከባዱ ነገር ይህን አምናችሁ ተቀበሉ መባሉ ነው ግጭት የፈጠረው። ይህን ደግሞ እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ተደማሪዎቻቸው እስከ ካድሬዎቻቸው
እያመሱን ያሉበት አመክንዮ ይኽው ነው። በመሃል ግን የሾለከ አገራዊ መንነት ቁልፍ ነገር አለ።
የጠቅላይ ሚኒስተርነት ኃላፊነቱ ነፍሱ ኢትዮጵያዊነት ማንነት ልክ በዕውን አለ ወይ ወንበሩ?! ነው። ቅምጥ ፍላጎታቸውን
ከገኃዱ ዓለም ጋር አዋደው ለማስተጋበር አቅም እያመለጣቸው ይመስለኛል።
ኢትዮጵያ በኦነግ በሽምቅ ተዋጊ ኃይል እዬተመራች ስለመሆኗ ተክድኖ ውስጧ ተሟጦ እስኪያልቅ እዬተጠበቀ ይሆን? ለነገሩ
ምን የቀረ ነገር አለና?
ሁሉንም ተደማሪ መንፈሶችን ሳስተውል ቅብ በሆኑ ሽር ጉዶች አገር ቀጥ ብላ የምትመራ መስሏቸዋል።
የሚገርመው „የብልጽግና
ጊዜ ማቆም የሚችል ኃይል የለም“ ብለው ይፎክራሉ ዶር
አብይ አህመድ።
ይህ አገላለጽ ለሌላ አማራጭ ሃሳብ መፈናፈኛ እስከ ወዲያው አይሰጥም ያው ልክ እንደ 50በ60
ያረጠ ፖለቲካቸው። ይህ ከሆነ ስለምን ምርጫ ማድረግ ተፈለገ? ለ2012 ብቻ ሳይሆን ለዘላለም አለሁኝ እኔ እስከ ህልፈቴ ድረስ
„ብልጽግናዬን“ አስቀጥላለሁኝ ካሉን። „የብልጽግናን ጊዜ የሚያሰቆም ኃይል የለም“ ሲሉ አክናፋት ታደላቸውን ያሰኛል።
መውቲ አለመሆናቸውን ነው አበክረው የሚገልጹት። ሰው መሆናቸውን፤ የእግዚአብሄር ፍጥረት መሆናቸውን
እራሱ የተቀበሉት አይመስልም። ይህን ሳስብ በዘመነ ደርግ „ተፈጥሮን በቁጥጥር ሥር እናደርጋለን“ የሚለው ሞቶ ትዝ አለኝ። እሳቸው
ቃሉን ብቻ ነው የሚቀይሩት።
የሆነ ሆኖ እሩብ አገር በሰላም ለአንድ ቀን መምራት ሳይቻል ፉከራው ገደለን። ኦሮምያ እኮ አገር
ሁናለች ከዳር ድንብሬ ድርሽ የሚል የለም የእኔን የግዛት ሉዕላዊነት ካልተቀበለ ባይ ናት።
ለመሆኑ ኦሮምያ ላይ እሳቸው የሚሰጡት ትዕዛዝ ይፈጸማልን? እርስ መዲናውና ይዞ ሌላውን አስገብሮ
ኦፊሻል ዕወጃ ነው የቀረው። ለዚህም መንገድ ተጠርጓል። „ትምክህተኞችን በሰበሩን ቦታ ሰብረን የአገሪቱን ዋና ከተማ ይዘናል፤ በደም
የተገኜ ድል ነው፤ ከእንግዲህ አንታገስም“ ወዘተ መንገዱ ተዬት ወደዬት ብሎ መጠዬቅ ማስተዋል ያለው ወገን ግዴታው ነው።
ይህ ድምጸት የሁሉም የኦሮሙማ ሊሂቃን ከዶር አብይ አህመድ ጀምሮ የኪዳን መሰረት ነው። የህሊናቸው
ወጥ ሃውልት ነው። ይህን የሚመከት አቅም አደራጅቶ መታገል እንዳይቻል ካታሊስት መንፈሶች ኢትዮጵያን የቅርጫ ሥጋነቷን ፈቅደው ያፈዛሉ፤
ያደንዝላሉ። የጉሮሮ አጥንቶች።
· „አንዴ
የሚያምር ውስጥ ገብተናል። አንመለስም“
„አንዴ የሚያምር ውስጥ ገብተናል። አንመለስም“ {ከዶር አብይ አህመድ የተወሰደ} የሰው ልጅ እንደ
በሬ፤ እንደ ፍዬል፤ እንደ በግ ተቆራርጦ ለመቅበር እንኳን ፈቃድ በተከለከለበት አገር ነው ይህ „የሚያምር ውስጥ ገብተናል“ ዲስኩር?
ይህ እንግዲህ በኢትዮጵያ ያለው ይህ ሁሉ ምስቅልቅል ፈጽሞ የናቁት ስለመሆኑ ይገልጣል። ዕንባው በሳቸው „የሚያምር“
መንፈስ ውስጥ ታቅዶ ሐሤት ሆኗል ማለት ይሆን?
የሻሸመኔ፤ የቡራዩ፤ የአዲስ አበባ፤ የለጋጣፎ ለገዳዲ፤ የአርሲ የዶዶላ፤ የሀርር፤ የድሬ፤ የባሌ
ሮቤ፤ የአርማጭሆ፤ የአማሮ፤ የራያ እና የወልቃይት ጠገዴ፤ የመተከል፤ የወለጋ፤ የደንቢ ደሎ፤ የመቱ፤ የባህርዳር፤ የገንድውሃ፤
የአፋር፤ የደቡብ መከራ ብራናም ብዕርም የማይችለው የሰው ልጅ ሰቆቃ ለእሳቸው የመዝናኛ ክበብ ነው። እኔ እንደማስበው የወንጀል
ፊልም ማዬት የሚወዱ ይመስለኛል።
አሁን እኮ በእውን የሚታዬው የወንጀል ዕውነተኛ ታሪክ ነው። ፊልም አይደለም። ለኢትዮጵያዊው
ሰው ያን የስቃይ ህይወት ዕለታዊ መደበኛ ኑሮው ሆኗል። ሞቱን ለምደነዋል። የሚሰቀጥጠውን የአሟሟቱን አሰቃቂነትም ለምደነዋል። አላማዱን
ሞጋሳነትን። ነውር፤ ውግዝ መሆኑ ቀረ አረመኔያዊ እርምጃዎች ሁሉ።
እሳቸው አሁን እሚያምር ድሪም ላይ ናቸው ያሉት። አለቀውም እያሉንም ነው። ይህን እያዬ፤ ይህን
እዬሰማ ደግሞ „አብይ ያሻግረኛል፤ ብልጽግና ነው ምርጫዬ“ እኛ ብንሆን የምንሠራውን አገራዊ ተግባር እዬከወነ እንዴት ድጋፍ እንንሳው
የሚል ሊሂቅ፤ ተጽዕኖ ፈጣሪ ስታዳምጥ ስንቱ ሰው ነው ጓዙን ጠቅልሎ ወደ ጁቢተር አብሮ የመጠቀው ያሰኛል።
ያነ ተከፋፍሎም ቢሆን፤ በጉልበትም አገዛዝም ቢሆን በኢህዴግ በህወሃት አውራነት ትመራ የነበረችው
ኢትዮጵያ እንኳን አሁን እንኳንስ በአካል በመንፈስም የለችም ዛሬ ላይ።
ሲሶ አገር ለዛውም በቀውስ የተናጠ ይዘህ ይህን ያህል ፉከራ፤
ይህን ያህል ቀረርቶ።
የዓለም የዓመቱ የ2019 ዘገባ ከዝቀተኛው ደረጃ ከሁሉም አልቀረብንም። በአገር ውስጥ መፈናቀል
አንደኛ፤ ቀውስ ለ2020 ከሚያጠቃቸው አገራት 3ኛ፤ ኢንተርኔት ማዕቀብ
12ኛ፤ በራህብ ከተመደቡት አገሮች ቤተኛ፤ በዋጋ ንረት ዕድምተኛ፤ በሙስና ቁንጮ፤ በብድር ዕዳ ፋና ይህን ሁሉ ተሸከምህ „አንዴ
የሚያምር ውስጥ ገብተናል። አንመለስም“ ግሽበት።
· ግሽበት።
የጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ፖለቲካዊ አመራራቸው እራሱ ግሽበት ላይ ነው። ፍላጎቱ እና
አቅርቦቱ መመጣጠን ፈጽሞ አልቻለም። ግሸበት ገጥሞታል። ለዚህ ነው ውሎው ኮሜቴ ማዋቀር ብቻ የሆነው። ሰላሙስ የትኛው አካባቢ ይሆን
„ለብልጽግና“ ምቹ የሆነው ሰላማዊ የሆነ የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚ፤ የማህበራዊ፤ የባህላዊ ሥርዓት የሚፈጸምበት? አንድ ሱማሌ ክልል
ብቻ ነው ስክነት የሚታይበት ክልል። ትልቅ ቁመነገር ሰሩ እማለው እዛ ክልል ነው።
ኃላፊነት እና ተጠያቂነትንም ሲወጣ የሚስተዋለው እዛ ነው። ይጨርስለት እንጂ ተቀንቶበት ደግሞ
ቀውስ በኦሮሞ ፖለቲካ ተደራጅቶ ካልታወከ። ፉክክሩ ለቀውስ ሽሚያነትም ነውና። ኦሮምያ ላይ አንድ ነገር ሲከሰት መሰሉ አማራ ላይ
ይከሰታል። ቀውሱ በአንድ
ማብሪያና ማጥፊያ ነው የሚከወነው።
በሌላ በኩል የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የሚሰጡት ወቅታዊ ትንተና እራሱ ለማደማጥ አቅም ታጣላችሁ።
ያስደነግጣል። በዛ ላይ በዬቀኑ ድግስ ነው፤ ፌስታ ነው፤ የቤተ መንግሥት ግብር ነው፤ በውጭ ምንዛሬ ትልቅ ቲም ውጭ አገር መጓጓዝ
ነው፤ ተተኪ ለማፍራት ሚዛኑን ያልጠበቅ ሥልጠና ነው አንዱ ቦታ ትምህርት አለ ሌላው ቦታ ዝግ ነው። በሁሉም ቦታ የአማራ ተማሪዎች
ብቻ ከትምህርት ገበታ ይታገዳሉ፤ የሳደዳሉ፤ ይገደላሉ።
36 ሺህ የተስፋ ልጆች በዚህ ዓመት ከዩንቨርስቲ ተፈናቅለዋል፤ 24 ዩንቨርስቲዎችሥራ ገበታቸው
ላይ አይደሉም እዬተባለ ነው፤ ይህ በሰባዕዊ መብት አያያዝ ብቻ ሳይሆን
በአገር የወደፊት ትልም ሚዛናዊነት የሰለጠና ማህበረሰብ ከመፍጠር አንጻርም ሊያስከትል የሚችለው ተጽዕኖ አይታይም። ጌጥ ነው ለዶር
አብይ አህመድም ይህ ተዛነፍ ገዳዳ ጉዞ። „አንዴ ከሚያምር ውስጥ ገብተናል“ ይላሉ።
ሰብአዊ መብት የሚባለው ጽንሰ ሃሳቡ እነኝህን ሁሉ ማካተት ይኖርበታል። መማር ሰባእዊ መብት
ነው። በዚህ ዙሪያ ኢትዮጵያዊው የሰባዕዊ መብት ኮሚሽኑስ ሚና ምን
ይሆን? መደበኛ ትምርት ቤት ላይ ያሉ የ አማራ ተተኪ ወጣቶች ምን አይተው፤ ምንስ ተስፋ አድርገው ይምሩ? ወላጆችስ በዬትኛው ተስፋቸው
ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ይላኩ?!
ከላይ አበክሬ እንዳነሳሁትም ይህ ሌት ተቀን እሳት የሚለቀቅበት የተቋማት ውድመት፤ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍሪያ ሙሉ
ለሙሉ መከርቸም፤ ተተኪ ትውልድ ለማፍራት ሳይቻል ሺዎች ተሰፋ ቢስ መሆን? አሰቃቂው የአሟሟት ዓይነት በተጠቂ ቤተሰቦች በሥነ
- ልቦና ሊያመጣ የሚችለው ወላዊ በሽታ ሲታሰብ እና ተደማሪዎቻቸውን ጨምሮ „የሚያማር ነገር ውስጥ“ አብረው መታደም፤ ያማል።
„አንዴ የሚያምር ውስጥ ገብተናል። አንመለስም“ ማጅካዊ ካልሆነ በስቀር ቅዠት ነው። ምን እሚያስመካ ነገር አለና? መንፈስ እንዲህ
ሊፈነዳ ውጥርጥር ብሎ። ለዚህ ነው እኔ የጠቅላይ ሚኒስተሩ ኑሮ ጁቪተር ሆነን የምላው?
· ዶር
አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ህልውና በሚመለከት ከተፈጥሮኛ ወደ ቁሰኛነት ተሸጋግረዋል።
„ከዚህ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ ህልውና በሚመለከት ስጋት አይግባችሁ። ኢትዮጵያ ለድርድር የምትቀርብ
አገር አይደለችም“ „ቿቿቿቿቿቿቿቿቿቿቿቿቿቿቿቿ። በኮማንድ ፖስት እምትመራ አገር? እትጌ ትግራይ የጦርነት መሰናዶ ላይ እንዳለችም
ይታወቃል።
የሳቸው ኦነገም ጦርነት ላይ ነው። አጤ ቄሮም ቀውስ ስንቁ ነው። ማህል አዲስ አበባ የቄሮ ታጣቂዎች
ፍተሻ ላይ ተሰማርተው ኗሪውን ቁሙ ተቀመጡ ይላሉ፤ ቦታ ሸንሸነው ሲያከፋፍሉም አልቀረባቸውም ምህንድስናው፤ የኢንባሲ ጠባቂዎችም
የሞት ዜና ይደመጣል፤ በአደበባይ በማህል አዲስ አበባ እያደባ እያዘናጋ ልምምድ ላይ ያለው የንጹኃን እርሻናስ እነ ወ/ት እጸገነት
አንተነህ? ይህ ይሆን የአገር ህልውና ስጋት አይግባችሁ የሚቸረቸርበት። ሺህ ነው ታጣቂው።
ይህ ሁሉ እያለ ሥርዓት አልበኛ ቡድን
እንዳሻው ያሻውን በፈለገው ቦታ ታጥቆ ይከውናል። ከልካይ የለበትም? ስንት አዬን እቴ አገር መሪነት? ኡኡቴ!
ባህርዳር ላይ የነበረው ጦር የአማራ ሊሂቃን ተረሽነውበታል፤ በተመላሽ የቀን ሰረተኛ አመራር
ነው ክልሉ አሁን የሚመራው የሚባልም ነገር አዳምጣለሁኝ፤ ወለጋ እስከ መተከል ያለው ጸጥታም ይታወቃል።
አዲስ አበባ ወጥቶ መግባት
አይቻልም። ጋዜጠኛ፤ አክቲቢስት፤ ተደማሪ ፖለቲከኞች በጥበቃ የሚሄዱባት አገር ናት ኢትዮጵያ ይህ ይሆን „ሥጋት እንዳይገባን“ የሚያደርገን?
ግን ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ እንደ መንፈስ የሚሰወሩበት ጊዜ
ደግሞ ይኖር ይሆን? ይህን ቅይጥ፤ ድብልቅልቅ ጭንቅ ሁኔታ የማያዩበት ወይንስ ወደ ጁቢተር ምሪት አቅንተዋልን?
ይገርማል። ቀደም ብዬ እንዳሳሁት እያሰረገ በማህል አዲስ አበባ ሰው የሚረሸንባት አገር፤
21 ባንክ የተዘረፈባት አገር፤ ቤተክርስትያን እና መስኪዶች በሰርክ የሚቃጠሉባት አገር? ኢትዮጵያዊ ተቋማት በግፍ የሚነዱባት አገር?
ቅርሶች ፓርኮች ሹግ በሆኑባት አገር?
ብሄራዊ ሃይማኖታዊ ባዕላት በአደባባይ በነፃነት በማይከበሩባት አገር? ሁሉም የራሱን መስፍንነት
ለማግኘት የክልል ጥያቄ በገፍ የሚጠይቀበት አገር? ትንሹ ኢትዮጵያ ደቡብ የፈረሰበት ዘመን?
የአማራን መዋቅራዊ ጥንካሬ እራሳቸው
ፈቅደው የናዱበትና ያፈለሱብት አመክንዮ እሹሩሩ እያሉ፤ አዲስ አበባንም በስጋት የወጠሩበት ሁኔታ ላይ ተቀምጦ „ስጋት አይጋባችሁ“
ይላሉ? የፌዝ ፈንጠዝያ መሪ።
ከመስከረም 5 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ እኮ የአዲስ አባባ ህዝብ ከጽንስ ጀምሮ በኪራይ ዜግነት ነው የምትኖረው ሲባል መኖርን በቋሚነት የሚያቅድ ይመስላቸዋልን? የተመላላሹ ሠራተኛ
ጠቅላይ ሚኒስትረነት ነገር አውሎ ያሳድራል። ተመላላሽ ሠራተኛ ማለት ቀን መጥቶ የተሰጠውን ተግባር ከውኖ አዳሩ ሌላ ቦታ የሆነ
ማለት ነው። ኢትዮጵያም ባህርዳርም የዚህ መከራ ሰለባ ናቸው።
· አገር ማለት አዳራሽ እደሳ ይሆን?
ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ አገር ማለት ሰው መሆኑን የሚያምኑበት አይደለምን? አገር ማለት
አዳራሽ ወይንም የግድግዳ ውበት መጠበቅ ይሆን? ወይንም አገር ማለት የአዳራሽ ምቹ ወንበር ማሰናዳት እሱ ይሆን አገር ማለት ለጠቅላይ
ሚኒስተር አብይ አህመድ አገር ትርጉሙ? ተፈጥሯኛ መሆን እዬተሳናቸው ቁሰኛ ሆኑ።
በሰመጠ መርከብ ላይ መቀመጣቸው ፈጽሞ በቁሙ እንኳን ሊያነቡት አይፈቅዱም። እንኳንስ ሊተረጉሙት፤
እንኳንስ ሊያመሳጥሩት ቀርቶ። የዩንቨርስቲዎች መዘጋት ማለት ትውልድ ማስቀጠል መስሏቸው ይሆን? ባፈለው ዓመት ስንት ሚሊዮን ተማሪዎች
ከመደበኛ ትምህርታቸው ተስተጓጎሉ።
እሳቸው ቤተ መንግሥታቸው፤ አድናቂዎቻቸው፤ ተደማሪዎቻቸው ሁሉሙ ሠፈረ ጁቢተር ነው ያሉት። ለመሆኑ
ለሳቸው ለራሳቸው ዋስትና አላቸውን? አንድ ቀን ቤተ - መንግሥቱን ጥሶ ቢገባ ሽምቃቸው ምን ይበጃቸው ይሆን? በዬደቂቃው ምን ሊፈጠር
እንደሚችል ያውቁታልን?
የአንድ የአገር ኢታ ማጀሩ ሹም እኮ የውሻ ያህል ክብር አጥቶ ነው ተረሸነ የተደመጠው በኢትዮ አፍሪካ ዋና ከተማ? አገራዊ የደህንነት ተቋም ያለበት አገር ላይ።
እስራኤል እኮ ወደ ኢትዮጵያ ሊደርግ የነበረውን ዕቅዷን እኮ ሙሉ ለሙሉ በ2020 በረራ ማቋረጧን አልሰሙ ይሆን? ደካማ ደህንነት ነው ያለው ብላም
አለች። ሞሳድ አበክሮ ሰርቶ መንግሥታዊ አቋም አስወስዷል። እንግዲህ እስራኤል ትንሽ አገር ግን ከኃያላኖች ጋር የሚተካከል ጥበብ
ያላት ተፈሪ አገር ናትም። የአህጉር ያክል የምትከበር።
ዶር አብይ አህመድ ጩሌለ ይበሉኝ፤ የፌስ ቡክ አርበኛ ይበሉኝ፤ ጭልፊት ይበሉኝ ከፈለጉት ይመደቡኝ።
እኔ እምላቸው ግን ዕውነት ይሁኑ ነው። የጠቅላይ ሚኒስተርነትን ህይወቱን ይኑሩት። የቆሙበት መሬትን ካለ ጠበቂ፣ ካለ ዘበኛ ለመቆም
ይሞክሩት። ኢትዮጵያ ህልውና አስጊ ስላልሆነ ይሆን ይህ ሁሉ ጥበቃ ለግለሰቦች የሚሰማራውን ያስቁሙ ስጋት ካልኖረባቸው። እስኪ እሳቸው
ካለ ጠበቂ ወጣ ይበሉ ወደ ቸርቸር ጎዳና፤ ይችላሉ? ከአንቦ እኮ ሲሾሙ በመኪና ሲፈሩ በኢሊኮፈተር ነበር ጉዞው? እርሰዎም እኔ
እንደማስበው ተመላላሽ ጠቅላይ ሚኒስተር እንደሆኑ ነው እማስበው። ያሉ የሉም። የለሉ ያሉ።
የኖቤል ሽልማተዎት አቀባበል አዲስ አበባ ላይ እንዴት ነበር? ይሰቡት? በዛ ሁሉ ሠራዊት እቅፍ
ውስጥ ሆነው ሽልማተዎት በአደባባይ ሲከበር? የወጣው ሰውስ? እሬሳ የሚያጅብ ይመስል ነበር እኮ። የበረደው።
የሹመተዎት የምስጋና
ቀንስ? አካሉን አጥቶ እኔን ተውኙ „አብይን ጠብቁልኝ“ የሚል ህዝብ እንዲህ ይቀጣ ነበርን? ያ መንፈስ አሁን አለን? ይጸልዩልኛል፤
ያለቅሱልኛል የሚሏቸው የኢትዮጵያ እናቶች መንፈስ ከእርስዎ ጋርስ ነውን? እኔ የሚታዬኝ አዬር የተሞላ ባሎን ነው። የሚናድ ነገር
ይታዬኛል።
„ከ6 ወር በኋላ መንግሥት እንሆናለን“ የሚሉ የኦነግ ሸሪካ ጉዶቸዎትን ተሸክመው „ስጋት አይግባችሁ“ ላንቲካ አይሆንበዎትንም?
ያሰለቻል። „በ24 ሰዓት ብንፈልግ ቤተ - መንግሥት እንገባለንስ“ „ቤተ - መንግሥት ላይ የጄኒራል ታደሰ ብሩን ሃውልት እንተክላለንስ“
ወዘተ ትንበያው እኮ የራስዎት ወገኖች ቃለ ምህዳን ነው። ወገኔ የሚሏቸው የሚናገሩን ሃቅ ነው።
አያዳምጡትም ይሆን ይህንስ? በዚህች ዙሪያ ትንፍሽ የለም። ቅቤ ናት ንጥር ተስማምታ የምትሰለቀጥ።
አይመርም። አንድ አማራ „ሙያ በልብ“ ሲል ግን ባሩድ ይታዘዛል፤ ፋቲክ ይኮፈሳል፤ የጦር መለከት ይነፋል።
ከላይ አብክሬ እንዳነሳሁት በጠላት የተያዘች ያክል ኢትዮጵያ ብሄራዊ ሰንደቋ በርዕሰ መዲናዋ
ማውለብለብ አይቻልም ዛሬ። ብሄራዊ ባዕላትን ቅድስት ኦርቶዶክስ ካለጫና
ማክበር አይቻልም። ለሰላማዊ ሰልፏ የገሰሰገሰ ካናዳ የሚኖር ዜጋዎ በ አደባባይ ገዳዮቹ ሳይታወቁ ተረሽኗል።
በነገራችን ላይ ጥምቀት ጎንደርን ሊበጠብጡ የነበሩት ግለሰቦችን እስኪ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ
ያደርጉልን። አሸባሪነት በመንግሥት ደረጃ ውንብድና ሳይሆን ቀርቶ ይሆን? ይህ ይሆን „ስጋት አይግባችሁን“ አንጠራርቶ የሚያናገር?
በፈለጉት ጊዜ እንደ መብራት ባልቦላ ቀውሱን ማስቆም እንደሚችሉም እዬነገሩን ይመስላል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማ በመሬቱ፤ በባዕቱ ነፃነቱ ተገፎ በሳት መንደዱ ወይንስ መረገጡ
ወይንስ የትሜና እንደ ማበሻ ጨርቅ መወርወሩ ይሆን „ኢትዮጵያ ለድርድር የማትቀርብበት“ አመክንዮ? ወይንስ እርስዎ ታመነው የኢትዮጵያ ህዝብ ስለ ሉዕላዊነት ለሽ ብሎ ሃሳብ ሳይገባው
እንዲተኛ ይሆን የሚፈልጉት?
የአፋር ህዝብ እኮ ደንበር ጥሰው በገቡ የውጭ ኃይሎች ነው ያን ያህል ሰቆቃ የተቀበለው። ይህ
እኮ የትናንት ጉዳይ ነው። 13 የቢዲዮ ክሊፖችን ሰርቻለሁኝ እኔ ለዛውም ከታህሳስ በፊት የነበረውን ብሄራዊ ሰቆቃ። ከታህሳስ በኋላ
ያለው ደግሞ ሲደምር ቁጥሩ ይጨምራል ይህን ብለጥፈው ምን ሊሉ ነው? ለዚህ ነው እኔ የእርስዎን ዘመን የመቃብር ሥፍራ ነው የምለው።
እርስዎ ደግሞ „አንዴ ሥራ ጀምረናልን። አንዴ ለውጥ ጀምረናል። አንዴ የሚያምር ውስጥ ገብተናል። አንመለስም“ ይላሉ። መጽናናቱ ለአሳቻ መንገዶ ይሆን ወይንስ መሪዬ ለሚለዎት ሚሊዮን
ነፍስ?
የኢትዮጵያ ህዝብ በዘመነ የመቃብር ሥፍራ እዬተቀበለ ያለውን መከራ እኮ ልቦናዎት ያውቀዋል።
በተለይ አማራ። የባህርዳር ደም እና የኤርትራ ሹፌርነት ለጫጉላ ሽርሽር ይበቃል። የአሁኑ ሴት ልጆች ታግደው፤ ቀንበጥ ወጣቶች ታግተው ኤርትራ ነዎት እርስዎ?
ግን በአማራ ላይ ሰቆቃ አጥንተው ኤርትራ ስለምን ለሽርሽር ይሄዳሉ? ምንድን ይሆን የኪዳን ውሉ?
በውነቱ ይህ መሪነት አይደለም። አላወቁበትም። እኔ እንደማስበው ሸፍጡ መጠንከሩ ምርቃተዎት ስለተነሳ
ኃላፊነቱ እና አርስዎ ተላልፋችኋል። የቀደመው አቅመዎት እንኳን ዬለም እንኳንሰ የጥቁር ህዝቦች መመኪያ አገር የመሪነቱ ወንበር
የሚሰጠው ግርማ ሞገስ፤ ብቃት ወዘተ ሊታከልበት። ለዛውም የዓለሙ ሎሬተ ታክሎበት። የተቀባይነቱ ሚዛን ተኗል። እንደ አንድ ተርታ
ዜጋ ለማዬት እንኳን አይቻልም ዛሬ ላይ። የጠባቂ ብዛት፤ የወግ ገበታ መበራከት፤ የካድሬ መግተልተል ቅቡልነት አያስገኝም። መንፈስን
የሚገዛ፤ የሚገራ ሰዋዊነት ርህርህና ነው የህሊና ጌታ።
ድርቀቱ ስለምን ተናኜ ቢባል በራስዎት ግድፈት እና ሹልከት። የእርስዎ ተልዕኮ ኦነግን
አቅም ሰጥቶ አገር እንዲረከብ ሁሉመናውን ማመቻቸት እና ማብቃት ነው።
ከቶ ሚስጢር አወጣሁ ይሆን? ለዚህም ነው እኔ የፖለቲካ ሙግቱ እድገት ያነሰዋል እጭ ነው እምለው። ለእኔ „ፈረቃም፤
ተረኝነትም አይደለም፤ ኢህዴግን ማስቀጠል አይደለም“ ኢትዮጵያን የመወረስ፤
አፍሪካን የመወረስ ታላቅ ተጋድሎ ላይ ነው ያላችሁት።
ክብር ግርማ መስለዎት አገርን አሳልፎ መስጠት ሚስጢር ለኦነግ አሳልፌ እስጥ ነበር እኔም ኦነግ
ነኝ እመኑኝ ከማለት በላይ ከእርስዎ ሉዕላዊነት እንዴት ሊጠበቅ ይችላል?
እንዴት ነው ስጋት የማይገባን? አሁንም በጉጉት የሚጠብቁት ነገር አለ። የአማራ እና የትግራይ ህዝብ ጦርነት። ቀውጢ እንዲሆን ይሻሉ
ስሜን ኢትዮጵያ። ይህ ህልመዎት ነው። እግዚአብሄር አምላክ ብን ያድርገው ህልመዎትን። አሜን! ይሄ ነው „አትስጉ“ የሚያሰኜው ይሆን?
መሬት እዬደበደቡ ማዕት አውርድ።
ቱርኪ ቀላል አገር እንዳትመስለዎት። ዓላማ ያላት አገር ናት። ግብጽስ? ሱዳንስ? ጁቡቲስ? ሱማሌ
ላንድስ? ኤርትራስ? የአረቡ ዓለምስ? እንዲዚህ ባለ ዝክንትል የአዳራሽ ጭብጨባ እና ሽብሸባ አይደለም „ብልጽግና“ በድህነት ህዝቡን
መረተው ለማኖር እንኳን አልታደሉም። ሁሉንም ጨርሰው፤ ተጽዕኖ ፈጠሪዎችንም የእስክርቢቶ ቀፎ አድርገው ክብራቸውን አራግፈው እርስዎ
ብቻ እንዲወጡ ጉዞ ጀምረዋል። ምኞታዎት ስለመሳካቱ ግን የሚያውቀው አንድዬ ብቻ ነው።
ሌላው ቀርቶ አሁን ኢትዮጵያ ሃዘን ላይ መሆኗን አይቀበሉም። እርስዎም ከህዝበዎት ጋር አብረው
ለማዘን አይፈቅዱም። አብረው አያዝኑም። ሙሽራ መስለው ሞድ ሲያሳዩ ውለው ያድራሉ። ቢያንስ የሚያዝኑትን እባከዎት አይወኩ? የእርስዎ
„ብልጽግና“ በሰው ስቃይ መዳናስ ነው። በኢትዮጵያ ፍርሰት የፌስትባል ትዕይንት ማሳዬት ነው። ኢትዮጵያ ግን ክብሯ ይህ ይሆን?
የትውፊት የመንፈስ ወረራ።
· የስለት ልጅነት።
ዶር አብይ አህመድ ሊታዝንላቸው፤ ሊታሰብላቸው፤ ሊጸለይላቸው፤ ምንድን ይሆን የሚያስፈልገው?
የሉም እንዳይባል አሉ። አሉ እንዳይባልም የሉም። አሉም ለማለት በመኖራቸው ውስጥ ያላቸው ኃላፊነት እና ተጠያቂነት የለም። የሉም
እንዳይባሉ ደግሞ የቴሌቪዥን ዋና አዘጋጅ ናቸው።
የፎቶ ሞዴል ዋና አክተር ናቸው። የወግ ገበታ መሪ ተዋናይ ናቸው። እንዴት አይነት
ዘልዛላ ሁኔታ ላይ እንዳለን ግራ ይገባል። እራሱ ቀኑም ሆነ ሌሊቱም መልስ የላቸውም እሳቸውን ለመተርጎም። ሳምንታቱም ወራቱም መልስ
የላቸውም እሳቸውን ለማንበብ። ወቅታትም መልስ የላቸውም መደባቸው ይህ ነው ለማለት።
የሚገርመው አብረዋቸው ያሉት ሰዎችም ያላቸውን ተፈጥሯዊ የአቅም መቅኖ ሂደቱ አሟሽሾታል። ሁለመናው
ግርማው ተገፏል። ለዚህ ይሆናል የ አዳራሽ የነራ ቅብ ግርማ ሞገሱ በ35/36 አመት ተገኜ ብለው ያወጁት። ለሰው ሰው መዳህኒቱ
የሚሆነው መንፈሱ ድንግል የሆነ አይዞህ ባይ ቅን መሪ ሲኖረው ብቻ እንጂ አዳራሽ አዳሽነት አይደለም።
ባለ የቤተ መንግሥት ቅልጥም ተጋሪዎች ሊገሯቸው ሲገባ፤ ሊመክሯቸው ሲገባ አብረው እያጨበጨቡ፣
ወርቅ እዬሸለሙ፤ ኬክ እዬቆረሱ ከዛም አልፎ ሆዴ ተንቦጨቦጨልህ ብለው ባቄላ ባቄላ የሚያክለውን እንባ ዠርከክ ሲያደርጉላቸው ይታያል።
እንዲህ ቅብጥ እና ቅልጥ ሲያደርጓቸው፤ የስልት ልጅ አድርገው ሲከበክቧቸው፤ እንደ ታቦት ሲያጅቧቸው
በእሺታ ሲንቆጠቁጧቸው፤ እሳቸው በንግሥናው ሠረጋላ ወደ አልታወቀ
አሳቻ
አቅጣጫ ግስግሴ ላይ ናቸው። „የብልጽግና ጉዟችን የሚያቆም ኃይል የለም“ ምጽዕታዊ ንግግር የዚህው ልብ ድፍንነት ነው። በድንብልብል
ውሰጥ ያለ ሸጎሬ ምናዕብ።
· „ … ይህ ምልክት ነው። ይህ ምልክት ነው።“
„የኢትዮጵያ የብልጽግና ጊዜ ነው። የኢትዮጵያ የብልጽግና
ጊዜ ነው። የብልጽግና ጊዜን ማቆም የሚችል ኃይል የለም። ይህ
አዳራሽ 35/36 ዓመቱ ነው። ከ35/36 ዓመቱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አሁን የምታዩትን ግርማ ሞገስ ያገኘው በብልጽግና ዘመን ነው። ይህ ምልክት
ነው። ምልክት ነው።„ ሥንኛቱን ደግመው ነው የተናገሯቸው። ስለምን ስትሉ መሰረት የሌለው ዲስኩር ስለሆነ። ነፍስ የማያተርፍ።
ስለ „ብልጽግናቸው“ ሲናገሩ የቢሮ፤ የአዳራሽ፤ የግቢ እድሳትን ሲያቆላምጡ የተጠቀሙበት ነው
አገላለጹ። የኢትዮጵያዊነት ምልክት እማ ጭሶ እዬነደደ ነው በዘመነ አብይዝም የመቃብር ሥፍራ። ቅርሷ፤ ቤተ አምልኳዋ። አሁን ደግሞ
አዬር መንገዷንም ለመሸጥ እዬተስማማችሁ ነው።
ዓርማው ነው የእናንተ የግብ ዋልታ። ታቦቷ እኮ ምልክቷ ነው። መጽሐፍ ቅዱሷ፤ መስቀሏ ምልክቷ
ነው። ቁራኗንም ምልክቷ ነው። ቤተ መቅደሷ ምልክቷ ነው። መስጊዷ ምልክቷ ነው። ፓርኳ ምልክቷ ነው። አብሮነቷ ምልክቷ ነው። የተፈጥሮ
አቀማመጧ ምልክቷ ነው። ሥያሜዋ ምልክቷ ነው። የጋብቻ ሥርዓቷ ምልክቷ ነው። የሃይማኗት ሥርአቷ ምልክቷ ነው። የባህል ትውፊቷ ምልክቷ
ነው። የቋንቋ ልዕልናዋ ምልክቷ ነው። የፊደል ባለቤትነቷ ምልክቷ ነው። ወጓ ልምዷ ምልክቷ ነው።
የገብያ ሥርኣቷ ምልክቷ ነው። የጉርብትና ትውፊቷ ምልክቷ ነው። የሞራል አቅሟ ምልክቷ ነው።
የሞራል ልዕልናዋ ምልክቷ ነው። የድል ውሎዋ ምልክቷ፡ነው። „በህግ አምላክ“ ምልክቷ ነው። ሰዋዊነቷ ምልክታነው።
ፈርኃ እግዚአብሄር
ፈርኃ አላህ ምልክቷ ነው። ይሉኝታ መልክቷ ነው፤ መደማማጥ ምልክቷ ነው። ይህ አለ? አለ ወይ? ጭካኔ፤ መገለል፤ ማስለቀቅ፤ ማጣጣል፤
ማቃለል፤ ጩኽት፤ ቀውስ፤ ጥሰት፤ አረመኔነት፤ ክህደት፤ የዘር ጭፍጨፋ፤ አባሩ - ንቀሉ - ዝረፉ፤ አፍልሱ ዕውጃ፤ በአገር ውስጥ ስደት፤ ጥቁር ፊት። ባይታውርነት፤
ውሸት፤ ቃጠሎ፤ ወረራ፤ መስፋፋት ምን የቀረ ነገር አለና? ሁሉም ስቃይ ላይ ነው በመቃብር ሥፍራው በዘመነ አብይዝም። ለእኔ ቀለመዎት
ለቋል።
[ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ እውነቱን ተናገሩ] የሐረር ፖሊስ ቤት ክርስቲያን እና ታቦት ላይ ሲተኩስ ነበር” ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ Jan 23,
2020
ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማ እዬተወረወረ፤ እዬተቃጠለ፤ እዬነደደ፤ እዬተጠቀጠቀ ነው ያለው። አማርኛ
ቋንቋም እዬተጠቀጠ እዬተነቃቀለ ነው። የባቢሎን ግንብ እዬተገነባ። ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶም ህልውናዋ እዬነደደደ ነው። ታቦት
ላይ እዬተተኮሰበት ነው። የትኛው ባዕድ አገር ነው ኢትዮጵያን እዬመራት ያለው? በዬትኛው ባዕድ መንፈስ ሥር ነው ኢትዮጵያ እዬተገዛች
ያለችው? ይህ ብልህ ጥያቄ ነው።
ይህን አትመርምሩ ነው የተደማሪው ሠራዊት ሚዲያ፤ ብዕር እና ብራና ፍዳ እያስከፈለ የሚገኘው?
የጸጸቱ ቋያ ከተቻለ። በዚህ ውስጥ ብልህ የሆኑ እህት ይሁን ወንድም የሚባሉ ክልል መሪዎች ሁኔታውን በጥሞና ቢያጠኑት መልካም ይመስለኛል።
አብረው ከመስመጣቸው በፊት። የኖቤል ሽልማት እኮ በኢትዮጵያ ሥም ነበር እንጂ በኦሮምያ ወይንም በኦነግ ሥም የተሰጠ አይደለም።
ኢትዮጵያን አቃሎ፤ ኢትዮጵያን ንቆ፤ ኢትዮጵያን አዋርዶ የበረከተ ነፍስም ተቋምም የለም።
· መፍቻ።
ሃግ … ተው የሚል፤ የሚገስጽ፤ የሚመክር፤ የሚያርቅ፤
የሚያስተካክል ልባዊ የሆነ አዎንታዊ የሆነ አራሚ ሰብዕና ያለው።
መለንቀጥ … ከመደቆስ በላይ የሆነ ማለት ነው። እንደ
ክሬም የላመ የሆነ ማለት ነው።
ገረፍታ … ምች።
አቅል … አደብ፤ ትዕግሥት፤ መቻል፤ ማስተዋል፤ ማሳለፍ፤
ማሾቅ … ተቆልቶ መቀቀል። የባቄላ አሹቅ ይባላል።
ከመቆላቱም ከመቀቀሉም አያምልጥም። ሁለቱንም ያስተናግዳል።
ትዕግስት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል።
ፍቅርም ሲያልቅ ትዕግሥት ይሰደዳል።
የኔዎቹ ኑሩልኝ።
መሸቢያ ጊዜ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ