ሙሽራ ዜና ከሙሽሪት ተዋናይት ሃና የሖንስ።
እንኳን ወደ ቀንበጥ ብሎግ በሰላም መጡልኝ።
ሙሽራ ዜና ከሙሽሪት
ተዋናይት ሃና የሖንስ።
„አቤቱ በአንተ ታምኛለሁና ጠብቀኝ።“
(መዝሙር 15 ቁጥር 1)
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
17.01.2020
ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ
·
እፍታ።
ቅኔዎቹ የአገሬ ልጆች እንዴት ናችሁ? ደህና ናችሁ ወይ? አንድ ያልተለመደ ድንገቴ ብሥራት ገጠመኝ
እና ዜና ቢጤ ላቀርብ ፈልግኩኝ። ባልደራስ ለኢትዮጵያ ሙሽራም ቤተኛው ሆነለት። ታድሎ! በጥልቀቱ ሲታይ ጣና ዘገሊላ - አስተርዬ
አይታያችሁምን? ድንቅነት በህብርነት!
·
ባልደራስ ለኢትዮጵያ ሙሽራዊ ረድኤት ቀረበው።
„ጥበብ ቤቷን ሰራች፤ ሰባት ምሰሶም አቆመች።“ ሙሽርነት እንዲህ የህዝብ ወገንትኝነት ሲታከልበት
ያማራል ይሰምራል። ያበራል ያስተምራል። ቅኔያዊነት ያፈካል። እኛዊነት ያሰብላል። እንዲህ ዓይነት ህብሬነት ትውልድን ከብክነት ያተርፋል።
በዚህ ውሳኔ እናታዊነትን አይቸበታለሁኝ። እናትነት እንዲህ ነው ይራራል። እናትነት እንዲህ ነው መከራን ይደፍራል። እናትነት እንዲህ
ነው መስቀልን ይሸከማል።
እናትነት እንዲህ ነው በመሆን ያምርበታል። እናት እንዲህ ናት ለቸገራቸው ፈጥና ደራሽ። ፈውስ!
ውድ እህቴ ተዋናይት እና „የእንተዋወቃለን ወይ?“ የቴልቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ ወ/ሮ ሃና የሖንስ
ጋብቻውን የአብርኃምና የሳራ ይሆንላችሁ ዘንድ ከዚህ ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ አንዲት ባተሌ እህትሽ ተስፋዋን እንሆ ላከችልሽ። ውሳኔሽ ከአእምሮዬ በላይ ሆነ።
እንደምን አድርጌስ ልተርጉምሽ?
እንደምንስ አድርጌ ላመሳጥርሽ? የዕውነት ከበደኝ። ተስፋ ባጣንበት ወቅት አዲስ የፈካ ቀን ፈቀድሽልን። አንቺም፤ ትዳርሽም፤ ቤተሰቦችሽም
የተባረኩ ይሁኑ። አሜን። ማዕልቱን በተስፋ አለመልምሽው። ተባረኪ!
ውድነት እንዲህ አገር ሰው በምትፈልገበት ወቅት አለሁሽ ብሎ መገኜት ነው። ኢትዮጵያ በጽኑ ታማለች።
ሃኪም ፈዋሽ ልጆች ያስፈልጓታል። ወርቅ በእሳት እንደሚፈተነው ሁሉ
ውስጥን መርማሪው አምላክም ይህን መንገድ ስለመራሽ የተመሰገነ ይሁን አሜን። በውነት ከህሊናዬ በላይ ነው የሆነብኝ።
ይህ ግዙፍ የውሳኔ አቅም ውስጥሽን ጊዜ ሰጥቼ እመረምር ዘንድ ፖስተኛ ሆነ። የተግባር ሙሽርነት
በባልደራስ ለኢትዮጵያ ማዬት መቻል ንጥርነት እናይ ዘንድ ምስክር ሆነ። የአመቱ ምርጥ የተዋናይነት ሽልማትን የባልደራስ ለኢትዮጵያ
መንፈስን ገዛ። ልቅና! ለዚህ ነው እኔ ፈቀደ እግዚአብሄርም አለበት እምለው ባልደራስ ለኢትዮጵያ። አደብ ለሰጣቸው ነፍሶች የዚህ
ድርጅት መፈጠር እዮራዊ መልዕክት አለው። እርግብነት አለበት። እርግብ የብዙ ነገር ተምሳሌ ነው።
ሙሽርነት እንዲህ ከሚስጢር ጋር መሆንን ሲያበስር ታላቅ የተጋድሎ ምዕራፍ ነው። እንኳን ወደ
ሚስጢርሽ ሚስጢርነት መንገዱን ኤልሻዳይ አምላክ አቃናልሽ። የበለጠ እንደ አደንቅሽ ስለፈቀድሽልኝ እጅግ አድርጌም አመሰግኝሻሉሁኝ።
ያው ታናሽ እህቴን ባህካል አንችኑ ስለምትመስል መስጥሬ እወድሽ ነበር። ውሳኔሽ ለዘመን ተቋም ነው።
ጦር ከታወጀበት ባተሌ መንፈስ
ጋር ለመሆን መቁረጥ መታደል ነው። እህቴ ወ/ሮ ሃና ሆይ! ውስጥነትንሽን ብቻ ሳይሆን ተፈጥሯዊነትን፤ ሰዋዊነትንም ሸልምሽኝ። ተባረኪ!
ባልደራስ ለኢትዮጵያ ማዕከሉ ተፈጥሯዊነት እና ሰዋዊነት ነው።
የተግባር ተቋምነት እንዲህ በልጽጎ ማዬት የትውልዱን ተሰፍ ያፋፋዋል። በዚህ ግራጫማ ዘመን፤
በዚህ አስፈሪ ዘመን ጥበብ መፍትሄ መሆን ሲችል የሥነ - ጥበብን ታማኛነት እጬጌ ያደርገዋል። ጥበብ ቤቷ መታመን ነውና። ብርክት
ሆይ! ለእኔ የላክሸልኝ መልዕክት ጽናት ነው። እንድጸና።
ልክ ለእኔ እንደላክሽው ሁሉ ጽናት ለሳሳባቸው ቅን ወገኖችሽ ሁሉ ት/ቤት
ነው የከፈትሽላቸው። ተባረኪ። በአንቺ ውስጥ የቅኔውን ልዑል ብላቴ ሎሬት ጸጋዬን መንፈስ አዬሁበት። እሱ ለእናቱ ውስጥነት ነበርና። ሲሰጥ ሲያውቁበት ውብ ነገር ነው።
ሲሰጥ ጊዜን አለማሽሎክ መታደል ነው። ጥሪሽ ይህም ነበር
ማለት ነው። ከዛ ከማይጠገበው የተውኔት አቅምሽ በመክሊትሽ ካገኜሽው
ውድ ሽልማት በላይ ነው ዛሬ ተስፋቸው መጠጊያ ላጡ፤ መወሰን ለተሳናቸው፤ ማህል ላይ ለሚገኙት ወገኖችሽ ሁሉ ልዩ የሆነ አቅም ነው
ያበረከትሽላቸው። አብነትነት እንዲህ ነው። ዴሞክራሲን እንዲህ የሰው ልጅ በመሆን መቻል ሊለማመደው ሲፈቅድ ያስደምማል። መብት ማለት
ምን ማለት እንደ ሆነ ሐዋርያ ሆነሽ ሰብከሻል። ሐዋርያዊት ሆነሻል።
„እንኳን ደስ አለሽ“
ለቀኑ ልዩ አቅም ሰጥተሽዋል። ለቀኑ አዲስ ቀለም ሸልመሸዋል። ለቀኑ አዲስ ኪናዊ ጥበብ አብርከተሽለታል።
የእኔ ድንግል ውጽፍተ ወርቅ ትዳርሽን ጠብቃ፤ የተሳካ ህይወት ይኖርሽ ዘንድ ትርዳሽ። አሜን። ቤተሰብሸም ብሩክ ቅዱስ ይሁን። አሜን።
አንድዬ አማኑኤል ይጠብቃችሁ። አሜን።
·
በባልደራስ ለኢትዮጵያን የብዕርወብራና ብሌን ህብርነቱን አሰበለበት።
በሌላ በኩል የዘመናችን የብራና ብሌን የእመት ፋናዬ ደሳለኝ ልጅም እጬጌው ብዕረኛ ጋዜጠኛ አቶ
ተመስገን ደሳለኝም የባላደራስ ለኢትዮጵያ ልዩ ክንድ ሆኖ በቦታው ተገኝቶ እንደ ተመዘገበ ያው ክብሩ ይስፋ ለማዳህኒዓለም እንጅ
ብሩክወቅዱስ አጤ ፌስቡክ አበሰረን። ተመስገን መዳህኒዓለም አባታችን። እንዲህ ጭንቅ ላይ ቢኮንም፤ እንዲህ ድንግዝግዝ ቢልም መከራን
አብሮ ሲጋሩት መልካም ነገር ነው። ለመከራም ሰው ያስፈልገዋል የመንፈስ አቅም የሚያዋጣ። አይዟችሁ የሚል። አይዞህ// አይዞሽ ትልቅ
ነገር ነው።
የማከብርህ፤ እንደ እናትም የምሳሳልህ፤ በእጅጉ የምትናፍቀኝ ተሜ ውሳኔህ ትልቅ ነው። ጸጋህ
ዕጹብ ነው። ጸጋህ ልዩ ነው። ብቻህን መባተልህ አጥር አልባ ስለነበር በእጅጉ ያሳሰብኝ ነበር። ፌስቡኬ ላይም ጽፌዋለሁኝ። አሁን
ጥሩ ነው።
ቤተ - ባልደራስ አዲስ ጎጆ ነው። ፈጣሪ በጥበቡ የሰጠው መክሊት አለ እና አንተን የመሰለ የልጅ አዋቂ፤ ምራቁን የዋጠ፤
የትውልድ አብነት ከዚህ መንፈስ ጋር ለመሆን መቁረጥህ የባልደራስ ለኢትዮጵያ ባለ ዕድልነት ያበስራል። አቅምህን ለዚህ ለተገፋ፤
እንግልት ላይ ለሚገኝ የህዝብ ድምጽ ሥጦታ ማበርከተህ ታላቅ ተጋድሎ ነው። የእኔ ድንግል ጥላ ከለላ ትሆንህ ዘንድም እለምናታለሁኝ።
አቅሜ እሱ ነውና።
·
ክወና።
የ እነዚህ ቅን ወገኖቻችን ታማኝነት እና ውሳኔ … ውሳኔው የላቀ ነው። ውሳኔው ድንቅ ነው።
ውሳኔው ዕንቁ ነው። ውሳኔው ፍቅራዊነት ነው። ውሳኔው ሰብዕዊነት ነው። ውሳኔው ተፈጥሯዊነት ነው። ውሳኔው መሆን መቻል ነው። ውሳኔው
ዕውነት ነው።
ውሳኔው መርኃዊ ነው። ውሳኔው ብጡል ነው። ውሳኔው ትውልድ ነው። ውሳኔው ተስፋ ነው። ውሳኔው
ማግሥት ነው። ውሳኔው ወደ ሚስጢር መመለስ ነው።
ውሳኔው ስለትውልድ ነው። ውሳኔው መኖርን ካለ ሥጋት ለማኖር ሰማዕትነትም
ነው። ውሳኔው እንደራሴነትም ነው።
ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር ነው።
የኔዎቹ ቅኔዎቹ የአገሬ ልጆች ውስጤ ያለኝን አካፈልኳችሁ።
መሸቢያ ጊዜ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ