እንኳን ወደ ቀንበጥ ብሎግ በሰላም መጡልኝ።

„የሰው ልብ መንገድን ያዘጋጃል፤ እግዚአብሔር ግን አካሄዱን ያቃናለታል። ምሳሌ ምዕራፍ 16 ቁጥር 9“

#የቅዱስ የሖንስ የተስፋ አቤቱታ ለጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ፡

አዲስ አበባ።

 


#እፍታ።

 

ጤና ይስጥልኝ ዶር አብይ አህመድ እንዴት ሰነበቱ? ተለያይተን ባጀን። እርስዎ ስለፈቀዱት።

 

የፓርላማውን ዘገባዎትን ከውስጤ አዳምጬ በ9 ምዕራፍ ሞገትኩዎት ከሁለት ዓመት በኋላ። በማግስቱ አንድ ቀን ፌስቡክ አግዶኝም ዋለ። እባክዎት ማስረን ሆነ ማሳሰርን አይፍቀዱት። አይበጅም እና።

 

የሆነ ሆኖ ከውስጣቸው ካዘኑበዎት ሰዎች አንዷ እኔ ነኝ እና ከውስጤ አዳጬዎት አላውቅም ነበር። በውነቱ ያን ቀን የተሻለ መንፈስ ነበረኝ።

 

ያስታውሱ እንደ ሆን በግንቦት መግቢያ 2010 ዓ.ም እኔም ኢትዮጵያዊ ከሆንኩኝ ብዬ „አብይ ሆይ!“ የሚል ዘለግ ያለ አቤቱታ አቅርቤለዎት ነበር። ትንሽ ትንሽ ስለሚያዳምጡም የተወሰነ ነገር መከወነዎትን አይቻለሁኝ።

 

የአቶ ኦባንግ ሜቶ ሆነ በሌሉበት እስከ ሞት ፍርድ የተወሰነባቸው ወገኖቼ ክስ መሰረዝ ምን ያህል እንደ ጠቀመዎት እርስዎ ያውቁታል። ብዙ ነገር ሸፍኖሎወታል። ጋርድሎዎታልም።

 

እስቲ ከቻሉ አይደክመዎትም እና አብይ ሆይን ደግመው ቢያነቡትም ብዙ ነገር ያገኙበታል - ይጠቅመዎታልም። ስለ ወሮ/ፈትለወርቅ፤ ስለ ባህላዊ የጎንደር የትጥቅ ትውፊት የአገር ዘብነት፤ ስለ አማራ ታማኝነት ወዘተ … ብዙ ቁም - ነገሮች የከተቡኩበት ጹሑፍ ነበር።

 

የሆነ ሆኖ ያን ጊዜ ከምርጫ በፊት ምንም አቤቱታ ላለቀርብ ቃል ገብቼለዎት ነበር። እንዲህ በርቀት እንለያያለን ብዬ አላሰብኩም ነበር።

 

… የምርጫው ነገርም እንደ ጉም ሽንት ወደ ኋላ እዬሄደ ነው። ምርጫ በእርግጫም - በፍጥጫም - በልጣጭም ሆነ አልሆነ ለእኔ ብዙም ጉዳዬ አዬደለም። በድህነት ለመተንፈስ የመኖር ዋስትና ይገኝ መጀመሪያ ነገር። ዴሞክራሲ ሉክሶስ ጥያቄ ነው ዛሬ ለኢትዮጵያ ህዝብ።

 

ለእኔ ጉዳዬ ይህን አውሬ ዘመን ኢትዮጵያ እንደምን ተሻግራ ወደ ክብሯ ትመለስ፤ ድምጽ አልባዎቹ የኢትዮጵያ እናቶች፤ የደምጽ አልባዎቹ  የኢትዮጵያ ህጻናት ዕንባ መቼ ያቆማል ነው።

 

ሰው የመሆኛ ጊዜው ይናፍቀኛል። ገበርዲም፤ ሽብሽቦም፤ ከረባትም የሰውነት መለኪያ አይደለምና። ከሞድ ኢቬነት ሰውነት፤ ተፈጥራዊነት፤ እኛዊነት፤ ኢትዮጵያዊነት ከውስጥ መሆንን፤ መልካምነት ይበልጥብኛል።

 

እኔ በልጅነቴ ያለኝን ሁሉ እሰጥ ስለነበር አንዷ አክስቴ መልካም ሰው፤ ሌላዋ ደግሰው ብለው ይጠሩኝ ነበር። ለካንስ መልካም ሰውም፤ ደግ ሰውም እንዲህ የፆም ውኃ ይሆናል? ዛሬ ነው የአክስቶቼ ነብይነታቸው የሚታዬኝ። ደግነት እንዲህ በአገረ ኢትዮጵያ ሲሰደድ።

 

# የሆነ ሆኖ የሚሊዮን አብይ አህመድ አባት፣

 

ዛሬ እማልችለው፤ እማለልፈው የህይወት ፈተና ገጠመኝ እና ቃሌን አፍርሼ እነሆ አቤቱታ አቀረብኩኝ። አቤቱታው የእኔ አይደለም። የቅዱስ ዮሖንስ ጌትነት በለጠ ነው። ከውስጠዎት ያዳምጡት ዘንድ በአክብሮት እና በትህትና እጠይቃለሁኝ።

 

#ነገረ - ቅዱስ የሖንስ።

 

ነገረ ቅዱስ ዮሖንስ በጣፋጭ አንደበቱ የላክልኝ መልዕክት ከባድ ነበር። የመጀመሪያ ጊዜም ነው። በህይወቴ ልጆች እንዲህ ዓይነት መልዕክት ልከውልኝ አያውቁም እና።

 

እንደምን ላስተናግደው እንደምችል ትናንት ጥሞና ወሰድኩበት። የላከልኝ ዕለተ ማክስኞ ነበር። ያዳመጥኩት ዕለተ እሮብ ነበር። ዕለተ ሃሙስን የሰውኛ ቀን ስለነበር እሱን ሠርቼ ዕለተ - አርብን በጸጥታ፤ በዝምታ በማሰብ በጥሞና ብቻ አዋልኩት። ይገባም ነበር።

 

ህሊናዬ የፈቀደው ዛሬን እርስዎ ያስቡበት ዘንድ በተለዬ ሁኔታ መልዕክት ለመላክ ወሰንኵኝ። አንዳንድ ጊዜ እልም ብለው ሲጠፉበኝ የቀደመውን ንግግረዎትን ደግሜ አዳምጠዋለሁኝ። ግን ምን ነካዎት? ምን ሆኑ? ስለምንስ ይህን መንገድ መረጡት?

 

ሥርጉቴ!

 

„ሥርጉቴ“ ይህን ሥም የምትጠራኝ የግንቦት 7 አባል የሆነች በአገረ ጀርመን የምትኖር ጓደኛ አለችኝ። እሷ ብቻ ነው ሥርጉቴ የምትለኝ። ቅዱስ ዮሖንስ ሥርጉቴ እያለ በተደጋጋሚ ሲጠራኝ ድምጹን ስሰማው  በእሷ መጠሪያ ነው የጠራኝ እና ደነገጥኩኝ። በጣም ደነገጥኩኝ።

 

በማይጠገብ ጣፋጭ አንደበቱ ጣፋጭ ምስጋናው ከአቅሜ በላይ ሆነ። የሰጠኝ ኃላፊነትን ተሸክሜ ከዳር ስለማድረሴ እርግጠኛ አይደለሁኝም። ኮሮና ባይኖር ብዙ ነገር አቀናጅቶ መሥራት ይቻል ነበር። ጥሩ አድማጭ መንግሥታት ፕላኔታችን ስላላት ያዳምጡኝ ይችሉ ነበር።

 

አሁን ግን ኮረና ስለሆነ ብዙ መልዕክቶችን ለመላክ ብዙ ትብትብ ችግሮች አሉበት። እራሱ ለእርሰዎ ድምጹን እና ደብዳቤ ልልክለዎት አስቤ መዘግዬቱ ብቻ ሳይሆን መድረሱም አጠራጠረኝ።

 

ፖስታዎች በመንግሥተዎ እዬታፈኑ ነው ልክ እንደ ዘመነ ህወሃት። ይህንንስ ያውቁ ይሆን?

 

ለዚህ ነው ሳስብ አድሬ ዕለተ- እማማ ቀለቤን በአቶ ኦባንግ ሜቶ አህዱ ያልኩት። እሱ ጭንቀቴን ይጋራኝ ዘንድ የለምንኩት ለዚህ ነው። እኔ ምን አቅም አለኝ፤ ከጸሎት በስተቀር።

 

#ልጆች እና መንፈሳቸው።

 

ልጆች መንፈሳቸው ቅዱስ ነው። ይህ ቅዱስ መንፈስ ሊጎዳ አይገባም። ኃላፊነት እና ተጠያቂነት ያለው መንግሥት ኢትዮጵያ ቢኖራት።

 

እጅግ የገረመኝ ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ እስረኛን ከእስር የመፍታት አቅም እንዳላቸው ይህ ቅዱስ ልጅ ገብቶታል።

 

ለቅዱስ ዮሖንስ የእናቱ ጉዳይ የመኖሩ ቁልፍ አጀንዳ ነው። ለዚህ ነው እንዲህ በዬአረፍተ ነገሩ ያልተገባኝን ምስጋና ደጋግሞ የሚሰጠኝ።

 

እርግጥ ነው ቢያንስ ተስፋ ስለሆንኩት ሐሤት አግኝቸበታለሁኝ። ተስፋው ጥግ ማግኜቱ አንድ በኽረ ጉዳይ ስለሆነ። ለሚሊዮኖች ህጻናት እንዲህ ተስፋ ብሆን ብቻል የምድር ጽድቅ ነበር። ግን በዬትኛው መድረክ?

 

ክፉዎች የግንቦት 7 ሠራዊቶች አያሠሩኝም። ስንቱን መልካም ነገር አግደው ሰማያዊ መክሊትን የጋን ውስጥ መብራት አድርገውታል። ቢያንስ ስለልጆች፤ ስለወላጆች የተጻፉትም ስቶር ያሞቃሉ።   

 

የሆነ ሆኖ የእኔ ብዕር ይህችን ያህል ለአቢ ተስፋ የቀለበችው፤ አቅም ያላቸው ኢትዮጵውያን ቢሠሩበት ምን ያህል ለልጆች ህሊና ተስፋ ሊሆኑ ይችላሉ ብዬ አሰብኩኝ።

 

ለዚህም ነው አክሰሱ ያላቸው ልጆች ስለሚኖሩ እባካችሁ ጸያፍ ነገር አትጻፉ እያልኩ አዘውትሬ እማሳስበው። ስድብ ነክ ካለ፤ ህግ መተላለፍ ካለ ከእኔ ፔጅ መቆዬት አይቻልም። ፈጽሞ። ልጆች ህሊናቸው ንጹሕ ሰሌዳ ነው። ይህን ንጹህ ሰሌዳ ማቆሸሽ አይበጅም። አይገባም።

 

ለልጆች የጻፍኩት #ፊደል፤ #እንካ - ሥላንትያ፤ ለወላጆችም የጻፍኩት #የተስፋ በር፤ #ርግብ በር እንጥፍጣፊ ፖለቲካ የለበትም። ፈቅር፤ ቅንነት፤ መልካምነት፤ ኢትዮጵያዊነት የነገሠባቸው ናቸው።

 

ሌላው ቀርቶ የልጆች እና የቤተሰብን መጻህፍት ከመጻፌ በፊት ሁለት ሱባኤ ገብቼ ነበር። በጥሞና፣ ፈቃደ - እግዚአብሄርን ጠይቄ በውስጤ ያለውን የፖለቲካ ጠረን ጠርጎ እንዲያወጣልን አምላኬን ተንበርክኬ ተማጽኜ ነበር የጻፍኩት።

 

እኛ ባለፍንበት ትርምስ ልጆች ሊያልፉ አይገባም። የልጆች ህሊና ንጹህ ነው። ቀይ ቢጽፉበት ቀይ፤ ነጭ ቢጽፉበት ነጭ ይጽፋል።

 

አልገባም እንጂ አገሬ ብገባ የፖለቲካ ነገሮቼን ሁሉ ሰርዥ በህጻናት ጉዳይ ላይ ብቻ ነበር እማተኩረው። ከቤተሰቦቼ ጋር ጠቡም ይህው ነው። በልጆችን ጉዳይ ብቻ ስሪ ነው የሚሉት።

 

በሎሬት ጸጋዬ ድህረ ገጽ „#የሎሬት ተስፋ“ የልጆች ፕሮግራም ነበረኝ። በሎሬት ጸጋዬ ራዲዮ „#አገር ማለት ልጆች“ የሚል ዝግጅት ነበረኝ።

 

ልጆች ተኮር እንዳልሆን ያገደኝ ግን የድምጽ አልባዎችን የኢትዮጵያ እናቶች ለማን ሰጥቼ? ዕንባ የዘወትር ስንቃቸው የሆኑትን እናቶቼን እንደምን እረስቼ? አሁን ደግሞ የድምጽ አልባዎች ህጻናትን ጨምሬበታለሁኝ። ኢትዮጵያም አብዝታ ታሳዝነኛለች።

 

# ቅኖች ሆይ! እባካችሁ እርዱኝ።

 

ቅዱስ ዮሖንስ የሰጠኝ ኃላፊነት ከግብ ለማድረስ እኔ አቅም የለኝም። አቅም ይሆኑኛል ብዬ ያሰብኳቸው ልዕልት ደራርቱ ቱሉ ነበሩ። እሳቸውም ዘገዩ።

 

እሳቸው ፈተውት ቢሆን ኖሮ ይህን ጊዜ ሳምንቱን በሙሉ ጭንቅ ላይ አልሆንም ነበር - እኔ። የቅዱስ የሖንስ ልመና፤ ተማህጽኖ አስጨነቀኝ። ፈተነኝም። ፈተለኝም።

 

የአቢ ድምጽ ይመጣብኛል። ይደውልብኛል። ይማጽነኛል። ይለምነኛል። እርጂን ይለኛል። እና እንደምን ይህን ችዬ ልቀመጥ?

 

እርግጥ ነው ቅዳሜን ከሰዓት በፊት ለወ/ሮ ቀለቤ ሥዩም በቋሚነት ማዋሌ መልካም ነገር ነው። ጥያቄው የዮሖንስን ሳቅ፤ ሐሤት፤ ወደ መደበኛ የትምህርት አትኩሮቱ፤ ወደ መደበኛ መኖርን የመውደድ ፍላጎቱ ይመልስልኛል ወይ ነው?

 

እባከዎ?! የህጻን ሚሊዮን አብይ አባት ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ይህን ልጆዎትን ይለመኑት። እባከዎት # እሺ! // ይሁን! ይበሉት።

 

ልቦናዎት ያውቀዋል። ወ/ሮ አስቴር ስዩም ሆነች ባልደረቦቿ ቲም እስክንድር ነጋ ጥፋት እንዳላጠፉ። በቀል ትውልድ አያበቅልም። ጥላቻ ልጅ አይተካም። ለሌላው በቀል ተበቃይነትም ነውር ነው። በምድርም፤ በሰማይም የሰውነት ጠረን የለበትም። ያ እንዳለፈው ይህም ጊዜ ያልፋልና።  

 

ወ/ሮ ቀለቤ ስዩም ስትፈታ ግን የፖለቲካ አቋማዋ፤ አስተሳሰቧ ታፍኖ ሊሆን አይገባም። ይህቺ ሴት ልዩ ናት። እማማ ኢትዮጵያን በድንግልና የጸነሰች። ምንም ገደብ፤ ምንም ካቴና የማይገባት የሰላም ደግ አንባሳደር ናት ለትመሰገን ሲገባ እንደምን ትታሰር? ግፍ ፍሩ!  

 

#እርገት ይሁን።

 

ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ቤተዎ ውስጥ ሳቅ አለ። ልጆቸዎት እናታቸውን ስላገኙ። ከአባታቸው ስላልተለዩ። ለቤተ - የሖንስ ሰላምም ይሰቡለት።

 

እባክዎትን? እባክዎትን? እባክዎትን?

 

በአራስ ቤቱ በዘመነ ህወሃት ተቀጥቶ፤ በዘመነ - አብይዝም ቅጣት፤ አይበዛም? ሁሉን ቻዩ ፈጣሪ ይፈራ!

 

አሁን ወ/ሮ ቀለብ ስዩም ከእስር ብትለቀቅ ቅዱስ ዮሖንስ ጌትነት በለጠ „አብይ እናቴን ፈታልኝ“ ነው የሚለው።

 

ለጓደኞቹ ሩጦ ሄዶ፤ ለመምህራኖቹ ተጣድፎ የሚነግራቸው ይህንኑ ነው። „አብይ እናቴን ፈታልኝ።“ ይህ ደግሞ ትልቅ አቅም አለው ትውልድን በተስፋ ስለመትከል። ይሰቡበት።

 

ፍቅሩንም፤ ሳቁኑም ተስፋውን ከእነ -ተፈጥሮው ይመልሱለት። ለጋ የልጆች ህሊና እንዲህ ተቀፍድዶ ካለ አቅም ወርዳቸው ታስሮ ሉዓላዊነት ልግጫ ነው - ለእኔ። ወንጀለኛ ተቀምጦ ንጹኃንን ማሰር ወንጀለኝነት ነው ብዬ አምናለሁኝ። ፍትኃዊነት ዕውነትን መድፈር ብቻ! እግዚአብሔር ይስጥልኝ። አሜን።

 

#ምራቂ መከወኛ።

 

መልዕክትለቅዱስ የሖንስ ለአቢ።

የእኔ ጌታ እንዴት ነህ አንተስ? ትምህርት እንዴት ነው? ጨዋታ እንዴት ነው? እኔም እወድኃለሁኝ። አብዝቼ እናፍቅኃለሁኝ። ሁልጊዜ በዬሰከንዱ አስብኃለሁኝ። ቤተሰቡን አረሳም። አስታውሳችሁ አለሁኝ አብሬ እንዳለሁኝ ሁሉ ይሰማኛል።

 

አስን ልትጠይቅ ስትሄድ ሰላምታ አቅርብልኝ። ይህው ለጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ አቤቱታህን ልኬያለሁኝ። ለባለቤታቸው ለቀዳማዊ እመቤትም ማመልከቻ ልኬያለሁኝ።

 

ለአቶ ኦባንግ ሜቶም ማሳሰቢያ ጽፌለታለሁኝ። ተስፋ አለኝ እናትህ አስዬ ትፈታለች እሺ የእኔ ጌታ። አይዞህ። አንድ አዎንታዊ መልስ እንደሚሰጥ በተስፋ እጠብቃለሁኝ።

 

ሥርጉተ©ሥላሴ

Sergute©Selassie

 12.12.2020

ሰው መሆን ለሰማይ እና ምድሩ ህግ መገዛት ነው።

ልጆች አገር ናቸው።

እናቶች የመኖር ጥበብ አስትንፋስ ናቸው።

 

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።