የፓርላማ የጠቅላዩ ውል ውይቡ የኢትዮጵያ እናቶች ፍቅረኛነት። መደምደሚያ።
እንኳን ወደ ቀንበጥ ብሎግ በሰላም መጡልኝ።
„የሰው ልብ መንገድን ያጋጃል፤
እግዚእብሄር
ግን አካሄዱን ያቃናለታል።“
ምሳሌ 16 ቁጥር 9
የፓርላማ የጠቅላዩ ውል ውይቡ የኢትዮጵያ እናቶች ፍቅረኛነት። መደምደሚያ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
ምንጭ።
https://www.youtube.com/watch?v=I-43KpkmB24
አሁን ወደ ሙግቱም ተመልሻለሁኝ። ይልመድብሽ ሥርጉትሻ ብያለሁኝ። በህይወት ኑሬ በድጋሜ በመገናኜታችን ደስ ብሎኛል። ምንም እንኳን የ አገራችን ሁኔታ ብዙም የሚያስደስት ነገር ባይኖረውም። ዳንኤሏ ኢትዮጵያ በውነቱ ጸሎት በእጅጉ ያስፈልጋታል። ኢትዮጵያ አሳቻ መንገድ ላይ ናት ያለችው። እሱ አንድዬ ይሁናት እንጂ። አሜን።፡
·
እምምም።
በአማሮ፤ በደቡብ ባሉ ከተሞች፤ በጉርጂ፤ በወለጋ፤ የእናቶች ዕንባ የልጆቻቸው ደም ጎርፍ የሆነበትን ዘመን ጠቅጥቀው ያን ስላቃዊ ንግግር ለሚያዳምጥ ከጁቢተር ወይንም ከኡራኖስ መጡ ያሰኛል።
ኢትዮጵያ ከዓለም በአገር ውስጥ መፈናቀል አንደኛ የወጣችበት አመክንዮው ምን ይባል? ሲፈናቀሉም፤ ሲገደሉም፤ ሲታረዱም፤ ጽንሳቸው ሲወርድም፤ ተገድለው ኩላሊታቸው ሲባልም እያንዳንዱ ልጅ እናት አለው።
እባከዎት ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ሰው ይሁኑልን ብዬ ልለምነወት?
አንዲት ነጥብ ዕንባ እኮ አላፈሰሱም። አላዬሁም፤ አልሰማሁም ብለው ቆስቁሰው ውጭ አገር ሽርሽር ይሄዳሉ። ለሱዳን፤ ለቤይሩት፤ ለጃፓን፤ ለዬመን የሚያዝነው አንጀተወ ለኢትዮጵውያውን ግን ዳሽ ነው።
አንድ ቀን ጥቁር ለብሰው አልታዩም። እራሱ የፓርላማ ውሎ ቀይ ከረባት የሚያስስር አይደለም። ይህ ግፍ የት እንደሚያደርሰዎት እንጃ? ልጅ አለኝ፤ ሚስት አለኝ አባት ነኝ ይሉናል በእርስዎ ዘመን ትውልዱ የከፈለው ሰቆቃ አባትነተዎትን ይሰርዝዋል። ያዬሁት ጭካኔ ነው።
የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስተር ሳሉ አንዲት ሰራተኛ ልጇ ታሞ፤ ትራንስፖርት አጥታ ብትዘገይ ሊከውን ስለሚገባው ሰባዕዊነት የነገሩን፤ ያስተማሩን የት ወሰዱት?
ይህ ሁለት ዓመት ተኩል ያዬነው ሰቀቀን፤ አሁንም የቀጠለው ሰቆቃ ለእርስዎ ለምለም መንገድ ነው። ሌላው ቀርቶ አሁን ባለው ጦርነት የስንት ሰው ደጅ ተዘግቷል። አሁን በኢትዮጵያ እኮ ሰው ሙቶ እሬሳ ማንሳት የማይቻልበት ጊዜ ነው ያለነው። ሁላችንም ሱባኤ ልንገባ የሚገባበት ጊዜ።
የሆነ ሆኖ እርስዎ እና የኢትዮጵያ እናቶች ምንም መሰመር ሊያገናኛቸሁ የሚችል የለም።
የወላይታዋ፤ የጋሞዋ፤ የጉራጌዋ፤ የአገዋ፤ የዶርዜዋ፤ የአዲስ አበባዋ፤ የአማራዋ እናት እሳቸውን መሪዬ ልትል? አላበደችም በአራስ ቤቷ። ሄሮድስ፤ ፈርኦን መሪዬ ተብለው ነበር ይሆን በዘመናቸው?
ለናሙና አንዲት ለኮሮና የተሰጠች፤ ህክምና የተነፈገች እህት ላንሳ። ለምስክርነት። የሳቸው ሸረኛ እና ዘውገኛ ዘመናይ በዬወሩ ሹመት ላይ ናቸው ወሮ አዳነች አበቤ።
አሳርኛዋ የኢትዮጵያ አምሳያ ወ/ሮ ቀለብ ስዩም።
በዘመነ ህዋህት ታሰረች። በረዶ ውስጥ ተዘቅዝቃ ተሰቀለች። አንድ ቀን ብቻዋን ከተወረረወረችብት በጎርፍ ተዋጠች። ብቻዋን ጨለማ ውስጥ የተቆለፈባት ምስኪን ናት እና።
በጥይት ተኩስ ተከፍቶ በሩ ለ አንድ ቀን አዳር ወደማታውቀው ቦታ ተወስዳ አደረች። ቤቱ ምንም መሰናዶ አልነበረውም ያችን አሳዛኝ ቦታ አይዞሽ የሚልበት። ከቅጣት ወደ ቅጣት።
ህወሃት ክፉ አውሬ ነው። ሞት አይደለም ከዛ በላይም ቢፈረድበት ይገባል።
አሁን ዝም እምለውም ዝርክርኩ እና ዝልግልጉ የ አብይ አገዛዝ የ አቅም እጦት ነው ብዬ ነው እኔ እማምነው። በጊዜ መከወን ይቻል ነበር።
በሌላ በኩል እነሱም አገር ምሰረታ ላይ መሆናቸውን አሳምሬ አውቃለሁኝ። እነሱም መስፋፋት እና ወረራ ላይ መሆናቸውን በስፋት ጽፌያለሁን። የጨለመበት ባርነት ኢትዮጵያውያንን ይጠብቃል።
የሚገርመው የቀዳማዊ እመቤት ወሮ ዝናሽ ታያቸው እና የ እሷ ቤተሰቦች አንድ ወንዝ የፈለቁ ናቸው። አንዷ ለዙፋን ሌላዋ ለካቴና።
ወደ ቀደመው ምልሰት ሳደርግ ይህም ብቻ አይደለም የባለቤቷ ወንድም ወታደር ፋሲል ጌትነት ፎቶውን እለጥፋለሁኝ እሷ እንደ ታሰረች የደረሰበት ለ7 ዓት አይታውቅም።
ይህን ሁሉ መከራ ያሳለፈች አንዲት በጣም ወጣት ሊቅ ስትፈታ የኢትዮጵያ የሰላም አንባሳደር ሆነች። „እናት ኢትዮጵያ“ የሚል በጎ አድራጎት ድርጅት ፈጠረች፤ አደራጀች። መራች።
አሁን ለድጋሚ ጊዜ እስረኛ ናት። የሚገርመው ጠቅላይ ሚኒሰተር አብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስተር ከሆኑ የ የኢትዮጵያ ሴቶች ዕንባ ይደርቃል ብዬ የመሰከርኩትም ደርቆ ክው ብሎ ቀረ። አዋረዱኝ።
በዚህ ነው መንፈሳቸውን ለማስጠጋት የሚቀፈኝ። ሰርክ ክህደት። ክህደት ከቁንጮ ሲሆን ትውልዱ ያሳዝነኛል።
ወሮ ቀለብ ስዩም አሁንም እስረኛ ሁና ሳያት ኢትዮጵያን በእሷ ውስጥ አያታለሁኝ። እንደ ትናንቱ ሁሉ አሁንም ኢትዮጵያ እስረኛ ናትና። አሁን ወሮ ቀለቤን ያሰረ መሪ ስለ ኢትዮጵያ እናቶች ሲያወራ ያስታውካል። ያሳፍራልም።
· የሆነ ሆኖ …
ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድን አብዝቼ ስለተከፋሁባቸው ጭካኔ ከጀመሩበት ከ ኢንጂነር ስመኜው ህልፈት በኋላ እንዲህ በተምስጦ አዳምጫቸው አላውቅም። ለዚህም ነው ሙግቱ ተግ ብሎ የባጀው።
በትናንት የፓርላማ ውሎ ግን በቀደመው አቅሜ ልክም ባይሆንም ጦርነት እና ኢትዮጵያ ስለሆነ አዳመጥኩት። ለዛውም ደግሜ። እናም ሞገትኩት።
እርገት ይሁን።
ሰሞኑን የትኛውም ሚዲያ ያለውን አቋም ሆነ ዕይታ አላደመጥኩትም ነበር። ተጽዕኖ እንዳይፈጥርብኝ። ዛሬ ካቻልኩኝ አዳምጠዋለሁኝ። ምን እንደ ተሰማቸው።
በተለይ በአማራ ፋኖ፤ በአማራ ሚሊሻ፤ በአማራ ልዩ ኃይል፤ በአማራ ህዝብ ሙሉ ብቁ የተሳትፎ ልቅና፤ በአማራ እናቶች ክህደት ላይ የሚዲያውንም ሁሉ ስሜት ማወቅ እሻለሁኝ። ሁሉም መሰረቱ፤ ጉዝጓዙ ቅኑ አማራ ነውና።
የእኔ ቅኖች።
ከክፍል አንድ እስከ ክፍል 8 ድረስ ፌስ ቡኬ ላይ አለ ሙግቱ። እንደ ጤፍ እንጀራ ዝንጥፍጥፍ ያለ ምስጋናዬም፤ ክብሬንም በሞገስ ይድረስልኝ
ለቅኖቹ ለአገሬ ልጆች። እግዚአብሄር ይስጥልኝ። ኑሩልኝ። ቸር ወሬ ያሰማን። አሜን። መሸቢያ ጊዜ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ