365 x 3 = 1095 x 24= 26,280

 

እንኳን ወደ ከበቡሽ ሚዲያ

   በሰላም መጡልኝ።

ዕለተ ሰኞ ዕለተ ጠባቂ

በከበቡሽ የቁራሽ እንጀራ ብራና

በቢሆነኝ የተብራራ ብራ

በሰብለ ሕይወት አዝመራ

ለራህብ የሚራራ።

„ዝም ብዬ የመከራን ቀን እጠብቃለሁ።“

(ትንቢተ ዕንባቁም ምዕራፍ 3 ቁጥር 17)



ዕለተ ሰኞ ማዕዶት ጠባቂ ሁሉም አጀንዳ የሚሰናገድበት ዕለት ነው። መንፈሴ በይ ያለኝን ሁሉ ያለገደብ የሚኮለምበት። ዛሬ የቀናው አጀንዳ እንዴት ሰነበታችሁ? ሰንበት እንዴት አለፈ? ኢትዮጵያስ እንደምን እያሆነች ነው ይላል።

·         365 x 3 = 1095 x 24= 26,280

 

የቁጥር ተማሪ አይደለሁኝም። በቁጥር ትምህርት እጅግ ደካማ ነበርኩኝ። ስለዚህ ስህትት ሊኖርበት ቢችልም እርዕሴ አይፈረድበትም። እኔ የባይወሎጂ እና የኬሚስትሪ ጎበዝ ተማሪ ነበር የነበርኩት፤ እንዲያውም 11/12ኛ በደረጃ ነበር ተሸልሜ ያለፈኩት።

የሆነ ሆኖ ወደ ዕርዕሰ ጉዳዬ ምልሰት ሳደርግ ሰውኛ ኢትዮጵያ ውስጥ በዬደቂቃው አደጋ ውስጥ ነው። ህዝብ እያለቀ ነው። ሞቱ ብቻ አይደለም በስጋት እና በሽብር ኢትዮጵያዊው ሰው ከጽንሰት ጀምሮ እዬተረሸነ ነው። ሰው አለን ለማለት አንችልም። እንዲያውም እኔ ቤት ሆኜ ሳስበው ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ያህል የሥነ - ልቦና ባለሙያ ይኖር ይሆን እላለሁኝ። መጪው ጊዜ መርግ ነው። ችግሩ አልተጀመረም ብዬ ነው እማስበው።

·       ክንያቱም …

ከአጤ ዝናቡ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጀምሮ የሥነ - ልቦና ህመም የለብኝም የሚል ሊኖር ስለመቻሉ እርግጠኛ አይደለሁም። እያንዳንዱ ደቂቃ በደም ውስጥ ያለፈ // ያለም ነው። እያንዳንዱ ደቂቃ በጭንቅ ውስጥ ነው የሚያልፈው// ያለም። „ከእኛ የሚሞተው ከሌላ አገር ጋር ሲነጻጸር ትንሽ ነው“ ባይ ሄሮድሳዊ መሪ ያላት አገር ናት - ኢትዮጵያ።

 „ግብጽ ጦርነት ትጀምር ብዙ ስራ የሌላቸው ደሃ ልጆች አሉን ለማገዶ እምናቀርባቸው“ የሚል ፈርዖናዊ ዕሳቤ ባለባት አገር፤ „ኮሮና ሆይ! ይምጣ እንኳን ደህና መጣህ ብዙ ታሳካልህ“ የተባለለት። „አንበጣ ሆይ እንኳን ደህና መጣህ መደመር ገብቶኃል“ የሚል፤ „የደረቁ ሃይቆች በችግኝ ግብረ ጻዲቅ አመነጩ“ „ሰርክ በኃይል እና መፈንቅል ተነሳብኝ በሚል በሽብር በጃት የሚተዳደር“ አታካችም // አሳቻም ፈርዖናዊ አመራር ባለበት አገር ሚሊዮኖች የሥነ - ልቦና ህመም ተጠቂ ቢሆኑ ምን ሊደንቅ?

እንዲያውም ምንም አጀንዳ ያልሆነ ጉዳይ ነው የሥነ - ልቦና ጥቃቱ መጠን አለመለካቱ ነው። ከዚህም በላይ ገና መከራ ሊኖር እንደሚችል ነው እኔ እማስበው። ጋንቤላ ላይ ያለው የተዳፈነ እሳት እና የደቡብ ሱዳን ከኗሪው መብለጥ ጋር ሲነጻጻር ዶፉ ገና አልጀመረም ባይ ነኝ። ጭካኔውም ጫፍ ጫፉ ነው። ደቡብ ሱዳን ጋንቤላ የእኔ ነው ለማለት ምን ያግዳታል? ጁቡቲ አዋሽን ይገባኛል እያለች አይደለምን? ስሜን ሱዳንስ ጎንደርን አራጣ ይዛ የለምን?

የጫካው የኦነግ ክንፍ የአገር ውስጡ በስውር ተደራጅቶ የሚጠብቀው ኃይል ኦሮሙማ ኤርትራ ሄዶ ያላሳካውን ጉዳይ ጫካ ውስጥ እንዳለ እያሰበ እንደሚሰራ የገባው አንድ ነፍስ የለም። ይገርማል ሰሞኑን አቶ አባ ዱላ ገመዳ ጠቅላይ እንደሆኑ ሁሉ እያዳመጥኩኝ ነው። እኔ የዛሬ 3 ዓመት ብሎጌ ላይ ጽፌዋለሁኝ። ለዚህም ነው ለወዳጄ ለአቶ ኦባንግ ሜቶ ነሃሴ ወር 2010 ደውዬ ትጥቁን እንዳይፈታ በትህትና ያሳሰብኩት። እሱ ልዩ አቅማችን ነበርና።

የሆነ ሆኖ ማህበረ ኦነጋውያኑ እነሱ እንዲህ ይሁኑ ይጨክኑ። „አንበላለን፤ እንሰብራለን፤ እንቀረጥፋለን፤ ትውር አይሏትም ከመዲናዋ፤ ሰብረናቸዋል፤ አይመለሱም፤ መስፋፋቱን እናሳያቸዋለን“ ወዘተ ወዘተ …  

እኛስ? ጨካኝ ስለሆኑ ጭካኔ? አራጅ ስለሆኑ እርድ? እንሰሳ ስለሆኑ እንሰሳዊነት? ነጣቂ ስለሆነ ነጣቂነት? ዋሾ ስለሆኑ ዋሾነት? አግላይ ስለሆኑ አግላይነት? ነጣይ ስለሆኑ ነጣይነት? ያተርፋልን? ይህ መስመር ኢትዮጵያዊ በሞራል የፋፋ ትውልድ ሊፈጥርልን ይችል ይሆን? እራሳችን እንሞግተው። ስሜታዊነትን እንመርምረው። ኦፕራሲዮን አድርገንም ከኩንታሮቱ እንፈውሰው። 

·       ሰው!

ሰውኛ!

ሰውነት!

ሰዋዊነት!

ተፈጥሯዊነት!

ኃይመኖታዊነት!

ፈርኃ እግዚአብሄር፤ ፈርኃ አላህነት?

ሰው መሆን ከቁስነት መውጣት እንደምን ይቻል?

·       ሙጥ ማንነት።

እኛ ቁስ ቆጠራ ላይ ነን። ሥልጣን ቁስ ነው - ለእኔ። ፈላስፎች ሳይንቲስቶች አይስማሙበትም። እኔ ግን እላለሁኝ ሥልጣን ቁስ ነው። ዝና እራሱ ቁስ ነው። መወድስ ለገኃዱ ዓለም ቁስ ነው። ቅናት ቁስ ነው። በቀል ቁስ ነው። ቂም ቁስ ነው። ቁጡነት ቁስ ነው። ብስጭት ቁስ ነው። ጥላቻ ቁስ ነው። አድመኝነት ቁስ ነው። መከፋፈል ቁስ ነው። መነጣጠል ቁስነት ነው።

መጋደል ቁስነት ነው። መካለል ቁስነት ነው። ጭካኔም ቁስነት ነው። እንሰሳት በዬቤተሰቡ ይኑራሉ። እኛ እነሱ የሚኖሩትን መኖር እንኳን መሆን አልቻልነም፤ አያስቀናነም፤ ወፍ ጎጆ ሰርታ ትኖራለች። እኛ ግን በክፉነት ጎጇችን የቀደሙት በጥበብ የሰሩትን እያፈረሰነው ነው።  

·       ውነት ቅዱስነት ነው። ኃይማኖቱ ከኖረ?

ከሰውነት ከቅዱስነት ተፈጥሮው ስንነሳ ከርህርህና - ከትህትና - ከመከባበር - ከመደማመጥ - ከመቻቻል - ከመታገስ - ከደግነት ከመልካም - ከማሰብ፤ ከአውንታዊነት ዕይታ /// ---------- //// ብጥብጥ - ግጭት - ፍጭት - የሚበልጡት ቁስነት ስለሚያል ነው።

ወንበር እኮ ቁስ ነው አይደል? ከአራት ብረት እግር ወይንም ከአራት እንጨት እግር የሚሠራ። ይህ ሁሉ የፈጣሪ ፍጡር ሲነሪቲ ያላቸው በሙሉ የተረሸኑበት፤ ገናም ይቀጥላል፤ በዬደቂቃው ንጹሃን የሚማገድበት - የሚነድበት - የሚሰቃይበት፤ ተፈጥሮ ስቅለት የሆነበት? ቅርስ ውርስ የሚነድበት፤ ይህን ሁሉ ሰቆቃ የሚያስተናግድበት ቁስነት ስለሚገዛ ነው። ይህ አስከፊ ነገር ምኑ ይናፍቃል? ይህ ነውረኛነት ምኑ ሽው ይላል?

·       ድንብልብል ማንነት።

ለቁስነት የሚያደገድጉ፤ የተነጠፉ፤ የተቀጠሩ፤ ያደሩ፤ ድንብልብል ማንነት ያላቸው ሰብዕናወች፤ ሰውነትን ድጠው ቁስነትህ ይንገሥልን - ይላቅልን - ያስብልልን የሚሉት ናቸው ብዬ አስባለሁኝ። ባትገድልም ገዳይን ከተባበርክ፤ ላራጅ አቅም ከዋጣህ ከገዳይነት ምኑ ይለይ ይሆን? 

እያንዳንዱ ደቂቃ „ተደመርኩ“ ብለህ ስትዘናከት ስትባጅ ለእያንድንዱ ሰከንድ ለሰው ልጅ ክስለት፤ ለቅርስ ውርስ አመድነት፤ ለታሪክ ዱቄትነት አንተው የሰጠኸው አቅም ነው ይህን ያደረገው። የልብ ልብ የሰጠው ለፍርሰት። ማህከነ።

ይህን መቀበል ግድ ይላል። አቅም ስትነሳው የተመለመለ ገላ ይሆናል አራዊቱ መንፈስ ወይንም ከባህር የወጣ አሳ። ግን አንተም እራስህ እንደ ፌንጣ እዬዘለሉ በሚመጡ ትራጀዲዎች „እጅ በደረት“ ስትል ለዛ ምንም ማንም ለሌለው ወገንህ ቀልሃ ማስረከብ መሆኑን አታውቀውም።

ለጨካኞች የሚሰጠው የመንፈስ አቅም በስራአት አስቀምጠው፤ ያን እዬመነዘሩ ነው በማዛል የራስህን ወገን እዬጨረሱ ያሉት። „ኢትዮጵያዊነት መለያው ነው የዶክተር አብይ“ ስትል መርዝ እያቀበልከው ነው ለቻዩ የኢትዮጵያ ህዝብ። ሰው አይጠይቅም በዬትኛውም ሁኔታ ግፍን ሲተባበር የቆዬ መንፈስ ድንገት ዘው ሲል። የሚገረመው ከዛ ጋር ደግሞ  አዲስ ዝላይም ይፈጠራል። አዲስ ዝለላ። አፍለኛ የጤፍ ጠላ ልበለው ይሆን?

ነገ ደግሞ ሌላ መሽሎኪያ ሲፈጠር ምርኮኝነቱ ይቀጥላል። እንደ ለመደነው። ለምን? ቁስነት። ሰውነት ካለ ግን ሰው የሆነ ሁሉ በሚደርስበት ሰቆቃ የቅድመ ሁኔታ ድርድር ቀጠሮ አያስፈልገውም። 

የኢንጂነር ስመኜው በቀለ ደመ ከልብነት እኮ በቂ ነበር። ቀብር ተከልክሎ ሁሉ ነበር። የአይን እማኞች ተሳደው ታስረው የት እንደደሩሱ አያታወቅም። ያ የአገር ዋርካ ደመ ከልብነት አገራዊ ንቅናቄ ፈጥሮ ይህን አራዊት መንፈስ ሊገራ፤ ሊያርቅ በወቅቱ ይገባ ነበር። አቅም በማሳጣት። በአምክንዮ በመሞጎት። 

ጭራሽ መዋጮ ነበረበት በፋይናስም ሳይቀር። „የለመደች ጦጣ“ ሆኖ አሁንም ሎቢስት ግዙልን እስከማለት የተደረሰው መቃናጣት ልባችን ታወቀ። ተለካ በእጅጉ ልፍስፍስነታችን። „በሞኝ ደጅ ሞፈር“ እንዲሉ … „በሞኝ ክንድም ጉድጓድ“ እንዲሉ …

ገና ከመባቸው …. የደቡብ ህዝብ ሲናድ በጥዋቱ የሺህዎች መፈናቀል እና የወላይታው አስከሬን መንደድስ? የቡራዩ ጭፍጫፋስ? የለጋጠፎ ለገዳዲ ዕንባስ? የሻሸመኔው ገድሎ ዘቅዝቆሰ ስቅላት እና የሚዲያ ሽፋን ድርቀት፤ የ5 አዲስ አበቤ የአደባባይ ጭፍሰጨፋስ? „እናቴ በእንቁላሌ በቀጣሽኝ“ አልነበረንም?

እራሱ የሰኔ 16/20216 „ጸጉረ ልውጥ“ ሞቶውስ? ዜጋን አገር አልባ የሚያደርግ ከባድ መርግ ዕድምታ አልነበረንም? ባሊህ ያለው የለም። ኢትዮጵያ ጸጉረ ልውጥ ዜጋ የላትም። ኑሯትም አያውቅም። ሁሉም ኢትዮጵያዊው ሰው ወዟ ነው። 

ጨካኞች፤ ዘራፊዎች፤ ገዳዮች ፋሺስቶች ትናንትም ነበሩ ዛሬም አሉ። እነሱም ቢሆኑ ጸጉረ ልውጥ አይደሉም። ዜጋ (ተወልጄ) ናቸው። ዜግነትን (ተወልጄነት) ሰጪ እና ነሺ የለም ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ዜግነት የሌለባት አገር ብትሆንም። ተወልጄ ልበለው። ይህ ያስኬዳል። የደም የሥጋ ተወልጄነት። 

·       ጡባን እና የሰውነት ክህደት። ሌሎች ይታረዱ ይዋረዱ እኔ ክብሬ ካልተነካ?!

የሰው አስተሳሰብ ለቁስ ርጥባን ልክ እንደ ከበት አሞሌ ሆነ። የሆነውን ሁሉ ስታስተውሉት ለከንቱ ውዳሴ ሲያደገድግ የሰውነት ሸቀጥነትን ማስተዋል ያሳዬናል። ዛሬ ባለው የሰማይ እና የምድር መቀላቀል በኢትዮጵያ ወዲህ እና ወዲያ የሚያወናጭፍ፤ ወዲህ እና ወዲህ የሚራገጥ፤ ወዲህና ወዲያ የሚያራውጥ፤ ወዲህ እና ወዲያ የሚያወራጭ መሆን አይገባው ነበር።

ዕንባ እንዴት አንድ አያደርግም? መከራ እንደምን ሃሳብን ወጥ ለማድረግ አቅም ያንሰዋል? የተገራ መንፈስን አፍልቆ ለማጎልበት ስለምን አቅም አጣን? ስለምን የበርሊን ግንብ በፈረሰበት ዘመን እኛ በ12 አካላታችን የበርሊኑን ግንብ ባህካሉን በውስጣችን ፈቅደን ስለምን ገነባን? ቁጣችን፤ ብስጭታችን፤ ለመቆጣጠር ስለምን ተሳነን?

ቁጣችን ብስጭታችን ስለምን ቋሚ በሆኑ አቋሞች ላይ የፍላጎታችን ላዕላይ እና ታህታይ መዋቅር እንዲሆኑ ስለምን ፈቃድ ነሳነው? ሲሞላ እና ሲጎድል ስለምን ተዥገረጎርን? ግን ፍላጎታችን እናውቀው ይሆን? የህወሃት መወገድ የውስጥ ሙሉ ሰላማችን፤ የውስጥ ቋሚ ደህንነታችን የማስጠበቅ አቅም ነበረውን? ኢትዮጵያ በዬትኛው ማንፌስቶ እና ህገ - መንግሥት ይሆን የምትዳደረው? ማን አመነጨው? ማን አስፈጻሚውን ካድሬ መልምሎ አስልጥኖ ተከለው?

የሆነ ሆኖ እኔ የቤተ- መቅደስ መጋረጃ ስለምን እንደማይቀደድ? ጸሐይ በተለመደው ሁኔታ መውጣት መግባቷ ሁሉ ይገርመኛል። የሰማያ ሰማያት ዶግማ እኮ ነው በመታበይ እዬተበረቀዘ ያለው። ርኩስት አንደበት ሁሉ እንደ ወረርሽኝ ሁሉንም እያዳረሰ ነው። ሰውነት ቋያ ላይ ነው ያለው። የአንዱ ሞት ለሌላው ድሎት ነው። የአንዱ ስቃይ ለሌላው ፌስታው ነው። ለምን? ስለምን? ሰው በመሆን ወስጥ መኖር መፈጠር ከእኛ ዘንድ ሲደርስ ስለሚያዛልጠው።

መጀመሪያ ሰው ነኝ እኔ ብሎ ሰውነትን አምኖ መቀበል ይገባል። ሰው ከተሆነ ሰውነት የራሱ ተፈጥሯዊም፤ ኃይማኖታዊም ሥራዓትና ህግጋት አሉት። በሌላ በኩል በሰውነት ውስጥ ብሄራዊ ብቻ ሳይሆን ሉላዊ ህግጋትም አለ። በዛ ጥሰት ውስጥ እኔ አለሁን ብሎ እራሰን መጠዬቅ ይገባል? ምክንያት ማቅረብ አይቻልም። ሰው ህግ ነው።

በቃል ውስጥ የተፈጠረ ለአማንያን። ህግ ጣሹ እራሱ ሰው ሲሆን ያ ሰብዕና ከሰውነት ውጪ አውሬነትን እዬተለማመደው ነው ማለት ነው። ውስጡ ጫካ አለው። ያ ጫካ ጭካኔ ነው። ጭካኔ ሰውኛ አይደለም። አራዊትነት ነው።

ቁርሾኛውን ስትጠዬፍ በአንተ ውስጥ ያለው ቁርሾነት አያታይህም። ጭካኔን ስትጸዬፍ ባንተ ውስጥ ያለው የከረፋ ጭካኔ አይታይህም። ዕድሉን ብታገኝ አንተም ቂመኛ እና ጨካኝ መሆንህ ዘመን እያነበበህ ነው። አሳምሮ አስምሮም። መራራው ገመና ይህ ነው። በዚህ ውስጥ ማን አለ? መጠያዬቅ፤ መፈታተሽ ነው። ብይኑ የራስ ነው።

ስለዚህ ከሊቅ እስከ ደቂቅ እከሌ ከእክሌ ሳይባል የቡርሽ ተቋም ያስፈልገዋል ሁሉም ላውንደሪ ቢሸምት ጥሩ ነው። ማተቡን ባናስረው ደስ ይለኛል? የለንም። ጾሙንም ባንጾመው። ዓውደ ዓመቱን ባናከብረው? የፈጣሪን ሥም ባንጠራ እንደምን መልካም በሆነ ነበር።

ያ መከረኛ ሰንደቅ ዓለማም ፍዳው ጠንቶበት። በለበሰው ውስጥ - ባቃጣለው ውስጥ - በጠቀጠቀው ውስጥ ልዩነቱ ዲስፕሊኑን የመሸከም አቅም በእጅጉ ወርዶ ነው የሚታዬው።

ሰንደቅ ስትሸከም የኢትዮጵያ ዶግማ እና ቀኖና ስለማክበረህ አስበው። በስተቀር ባልሆንክለት አለሁኝ ባትል ይመረጣል። ሰንደቁ በህግ አምላክ ይለኃል? ሰንደቁ ፈርኃ እግዚአብሄር፤ ፈርኃ አላህ ይኑርህ ይልኃል፤ ሰንደቁ ቀይ መስቀልም ነው የርህርህና ተምሳሌት። ሰንደቁ ሰውኛም ነው። በሰውኛ ውስጥ የነፃነት ቃና የረበበበት። ብታውቀው ሰንደቁ ህገ - መንግሥትህ ነው።

ኢትዮጵያንም - ሃይማኖታችንም - ሞራላችንም - ትሩፋታችን ይሁን ትውፊታችን ዘለነዋል ወይ ጠቅጠቀነዋል። ጥፋት - ስህተት በል ቀጥል በርታበት ማለት የተገባ ነውን? ሰውኛ አይደለም ቀለሙ። ሰው መዳን የሚችለው የሰውነትን ፍልስፍና በመቀበል፤ ዲስፕሊኑ የሚያዘውን በመሆን መሆን ሲቻል ብቻ ነው። እራስን መርታት። ከባድ ነው ግን ጀግንነት ማለት በፈጣሪ አምሳል የተፈጠረ፤ ቤተ - መቅደሱ የሆነ አንደበቱን፤ መዳፉን ከክፉ ነገር መቆጠብ የግድ ነው።

ጨካኝ ተጠይፈህ ሌላ ጨካኝ እምታባብል፤ ሌላ አረመኔ ሃሳብ እምታንቆለባብስ ወይንም እምታቆላምጥ ከሆነ አንተም ዕድሉን ስታገኝ የበለጥክ አረመኔ ስለመሆንህ ሌላ ማረጋገጫ የለም። ጭካኔ ትውልድ አያተርፍም። 

አይደለም የጭካኔ ድርጊቱ ሃሳቡ እራሱ የትውልድ ሊሆን አይችልም። እኔ ከዛሬው መከራ የማግስቱ ስቃይ አይሎ ይታዬኛል። መዳንን የፈቀደ የለምና። መዳን ራስን አርሞ ከመነሳት ነውና። መዳን የራስን ንሰኃ አውቆ ፈቅዶ መቀበል ነውና። ክብር ዝና ከቁጣ ከመነጬ ጤዛ ነው። ምርቃትም ያስነሳል። ይህ አስፈሪ ነው።

·       እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ መልዕክትም መክሊትም ይዞ ነው የሚወለደውና።

 … ያን ምርቃት የሚያን - የሚያበን - የሚያቃጥል - የሚያስነሳ የላይኛውን ህግ መተላለፍ ሲገጥም ነው። ለዚህ ነው ልበ አምላክ የተባለው ንጉሥ ዳዊት „ህግ ተላላፊወችን ጠላሁ“ ያለው። በእያንዳንዱ እርምጃችን የአገራችን፤ ተሰደን የምንኖርበት አገር ህግ፤ የዓለም ህግ፤ የፈጣሪ የአላህንም ዶግማ ጥሰት እንዳይኖር ጥንቃቄ ያስፈልጋል። በተለይ አክሰሱ ላላቸው ልጆቻችን እንሰብ። 

·       በጭካኔ ውስጥ ትውልድ አይበቅልም።

ጭካኔ መርዝ ነው። ማላታይን ወይንም ዲዲቲ። ትውልዱ ልክ እንደ ኢንሴክት መሞከሪያ ጣቢያ ነው እዬሆነ ያለው። ጭካኔ ጀብዱ ነው¡ ጭካኔ ክብር ነው¡ ጭካኔ ልዕልና ነው¡ ጭካኔ ልቅና ነው¡ ጭካኔ ተጽዕኖ መፍጠሪያ ነው¡ ጭካኔ አንቱ የሚያሰኝ ነው¡ ጭካኔ የሚዲያ ሰውነት የሚያስገኝ ነው¡ ጭካኔ ዘውድ ነው¡ ጭካኔ ተክሊል ነው¡ አብረን እንፈር! ጭካኔ ፎሎወር መሰብሰቢያ ነው¡

ውስጤ በጣም እዬታመመ ስለሆነ ከዚህ በላይ ባልሄድ እና ማዕዶተ ጠባቂን በዚህ ብከውነው ይሻላል። መጻፍ ሁሉ እያቃተኝ ነው። መጻፍ ለእኔ ትምክህት ሳይሆን በህይወቴ ውስጥ ቀላሉ ሥራ ነው። ቧንቧ ውሃ የመክፈት ያህል ነው። ግን አሁን ከሆነ በምሰማው፤ በማዬው አብሶ ጭካኔ ሲበረታታ - ሲነግስ - ሲዳር-  ሲኳል ሳይ አቅም እያጣሁኝ ነው።

ማን ይሁን ማን ጭካኔ በምንም መስፈርት ሊበረታታ አይገባም። ቅንጣቷ ነቁጥ እሳት ናት፤ ቅንጣቷ ትንፋሽ ሞገድ ናት። ቅንጣቷ ጠብታ ነዲድ ናት። አንዲት ክብሪት ስንት ነገር ታወድማለች? በጭካኔ ሃሳብ ውስጥ አትራፊነትም ሰማያዊ ጽድቅነትም የለም። ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር ለማለት በጣም እዬከበደኝ ነው ያለው። በምን አቅሟ ይሆን ለዘላለም እምትኖረው? እንደምን ብላ? ፈርዶባት?!

ቢቻል ሁሉም ተደብቆ ንስኃ ቢገባ፤ ጥሞና ቢወስድ፤ ዘውር ብሎ ማዕዱን ሰላም ቢሰጠው እሻለሁኝ። ሁሉም ከራሱ ጋር የሚመክርበት እራሱን የሚፈትሽበት ጊዜ ቢኖረው መልካም ነው። የውዳሴ ከንቱ አርኬቡ ለማሳደድ እንዲህ ፋታ ጠፍቶ ከምናይ። ለዬትኛውስ ዘመን ነው? አፍር እኮ ነን ትቢያ። 

እግዚአብሔር ይስጥልኝ።

ሥርጉተ©ሥላሴ

Sergute©Selassie

12.04.2021

ኢትዮጵያ ሆይ! የደግነትሽ ማዕልት ናፈቀኝ።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።