ኢትዮጵያዊነት ምንጩና አገነባቡ ከሃሳብ በላይ ነው።
እንኳን ወደ ከበቡሽ ብሎግ በሰላም መጡልኝ።
ዕለተ አርብ ማዕዶተ - ኢትዮጵያ
በከበቡሽ የቁራሽ እንጀራ ብራና
በቢሆነኝ የተብራራ ብራ
በሰብለ ሕይወት አዝመራ
ለራህብ የሚራራ።
ኢትዮጵያዊነት ምንጩና አገነባቡ ከሃሳብ በላይ ነው።
ጥፈተኛው ማን ነው?
„ከቀና ህግ ወጥተን ሳትን“
(መጽሐፈ ጥበብ ምዕራፍ ፭ ቁጥር
፮)
· እፍታ።
·
ማዕዶተ ኢትዮጵያዊ።
ኢትዮጵያዊነት ዘለግ ያለ ፍልስፍና ነውና አንዲት ነቁጥ አንስቼ ሃሳቤ ረዘሟል። እምጽፈው ለቅኖች፤ ለገራገሮች ስለሆነ ብዙም
ጭንቅ የለብኝም ዘለግ ያለ ስለመሆኑ። እኔን ሽተው ለሚመጡ ደጎቼ ውስጤን ገልጬ ስጽፍም ሰቀቀን የለብኝም እንደ ማለት። ግልጽ
እና ቀጥተኛ ሴትም ነኝ። ሰው ጫካ አይደለም እና።
· መንፈስ!
እንዴት ናችሁ የኔዎቹ? ደህና ናችሁ ወይ? ኢትዮጵያ ሻሸመኔ፤ ኢትዮጵያ ቡራዩ፤ ኢትዮጵያ ለገጣፎ ለገዳዲ፤ ኢትዮጵያ ወለጋ፤ ኢትዮጵያ ሙሉ ኦሮምያ፤ ኢትዮጵያ ቤንሻንጉል ጉምዝ፤ ኢትዮጵያ ደቡብ፤ ኢትዮጵያ ከሚሴ - አጣዬ - ማጀቴ - ደራ፤ ኢትዮጵያ ማህል ጎንደር፤ ኢትዮጵያ ትግራይም፤ ኢትዮጵያ አፋር እና ሱማሌም ፍጥጫ ላይ ነው የባጁት፤ ያሉት፤ የሰው እልቂት ምድሪቱን ከቧታል። ደሙም አጉርፏል።
ገና ውጥን ላይ እያለ ጭካኔው ቁጣ አልነበረም ቀጠለ። የቆዬ ስለመሆኑ አይደለም ጉዳዩ ዛሬም የኦሮሙማ ባጀቱ ሰው መግደል ነው፤ ሬሳ መቁጠር፤ ሰኔል እና ቹቻ በቦንዳ ማከፋፈል፤ ለዕንባ ፊስቶ ማሰናዳት ነው። ጉዟችን ወደዬት ነው? አሁን ከዛም አልፎ ተርፎ የሰው አካልን ሰው ከሚበላበት ተደርሷል። የሰው ልጅ መፈጠሪያ አገር በዚህ አሰነዋሪ የጭራቅነት ተምሳሌት ስትነሳ መስማት መኖርን ማፋጠጥ ብቻ ሳይሆን ከእኛ ቀድመው ይህን ሳያዩ ያለፉት ያስቀናሉ።
· ውጊያ?
በዘመነ ጭካኔ፤ በዘመነ ፍዳ፤
በዘመነ ጽልመት ይህ የመንፈስ የነፍስ ውጊያ መንስኤው ምንድን ነው? ምን ተማርንበት? ምን አቀድንበት? ምን አጨንበት? ምን
አሰብንበት? ምን አስታረቅንበት? ምንስ ልንታረቅ አሰብንበት ይህ ነው ጉዳዬ። ኢትዮጵያ ምን እዬሆነች ነው፤ ምንስ እዬተደረገች
ነው?እነሱስ አረመኔዎች፤ ጽልመቶች ይሹለኩ እኛ አብረን መሹለክ አለብን?
· ምን አሰብንበት ስለ ውድቀታችን። አብረን እንፈር።
ወድቀናል። ወድቀናል ሁላችንም። ስለምን? ትውልዳዊ
ድርሻችን ለመወጣት አቅም ስሌለን - የመንፈስ ብርታት መቅኗችን ፈሰሰ። በ2008 እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር የጸጋዬ ድህረ
ገጽን እና የጸጋዬ ራዲዮ ስጀምር ዋናው ሞቶዬ „ትውልዳዊ ድርሻችን በህብረት እና በአንድነት እንወጣ“ ይል ነበር። ሁለተኛው አጋዥ ሞቶዬ እንደ ቅመም „እልፍ ነን እና እልፍነታችን እልፍ እንድርገው“ ይል
ነበር።
ለዚህም ለመጀመሪያ ጊዜ በድህረ
ገጽ ደረጃ አንድ የልጆች ፕሮግራም አዘጋጀሁኝ „የሎሬት ተስፋ“ ይል
ነበር። አትኩሮቱም እርእሰ ጉዳዩም „አገር ማለት ምን ማለት ነው?“ የሚል ነበር። የተሰናዳው ለልጆች ነበር። ዝግጅቱም
በልጆች የሚቀርብ ነበር።
ያው የሚያሠራ ጠፋና እና ቀረ።
ስለምን? አገር ቃሉን እንጂ ግዴታውን ወይንም ህብር ዶግማውን ስለማናውቀው፤ አቅም ባይኖረን አቅም ያላቸውን ሰዎች
እምናደናቅፈው እንቅፋቱ እራሳችን ስለምንሆን። ስለመጠዬቅ ከሆነ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ተጠያቂ ነን - ሁላችንም።
አለመስራቱ መብት ነው። የሚሰራን ማደናቀፍ ግን ተልዕኮው የጸላዬ
ሰናይ ነው። ሁላችንም አገር ማለት ምን ማለት ነው ከሚለው አውራ የነፍስ ጉዳይ ሳንነሳ ነው ድርጅት
የፖለቲካ፤ መዋቅር የማስፈጸሚያ አካል መዘርጋት ይገባን የነበረው። ሳንሳናዳ ነው የነፃነት ተጋድሎ የምንጀምረው። ዘውም ብለን
እምንቀላቀለው። እራስን እዬታገሉ መቼም ትውልዳዊ ድርሻ አይታሰብ እና።
አሁን የምናፍሰው የዘራነውን እሾኽ ነው የዘራነው ያመረትነውም። እየሰበሰብን
ማፍሰስ፤ እያፈሰስን መልቀም ሰልጥነንበት የለምን?
ቢመርም - ቢጎመዝዝም መቀበል ግድ ይላል።
· የነቀላ ወበራ።
አብሶ እንደ እኛ ያለ ባለብዙ ህብርነት ያለው ዜጋ አገር የቆመችበትን ምሰሶ፤ አውታሮቿን፤ ዘሃዎቿን፤ አንጓዎቿን፤ ሴሎቿን
ጠንቅቆ ማውቅ በእጅጉ ያስፈልጋል። 27 ዓመት አንድ ትውልድ ጠፍቷል። 3 ዓመቱ ደግሞ መታጨድ ነው። በጠፋው ትውልድ ውስጥ እኛም አብረን ጭልጥ ብለን ጠፍተናል።
በመንፈስ። ጭካኔውን ስንደፍረው አይሰቀጥጠንም። መለያዬቱን ስናቆመስው ይሉኝታ የለም።
የትውልዱ ጥፋት ትልም መሰረቱ
ኢትዮጵያዊነትን ነቀል ተኮር ስለ ነበር ነው።
በምንወስዳቸው እርምጃዎች
ኢትዮጵያዊነት ሥረ - መሠረቱ ስለመነቀሉ አናስበውም። አንዱን አቅርበን ሌላውን ስናርቅ፤ አንዱን አቅፈን ሌላውን ስናሸሽ፤ አጋ
ለይተን በዬዘመኑ በዛ ሰርክል ስንተበተብ፤ ኢትዮጵያዊነት መንፈሱ ከእኛ ውስጥ እየሸሸ ስለመሆኑ አናውቀውም።
ቋንቋ አብሶ የሌላ አገር
መስፈርታችን ነው። ዕውቀት ዲግሪ መስፈርታችን ነው። ዕድሜ መስፈርታችን ነው። ተጽዕኖ ፈጣሪ መሰብሰብ መስፈርታችን ነው። ገንዘብ ያለው መሻት መሥፈርታችን ነው። ከዚህ ውጭ ያሉ ነፍሶች ኢትዮጵያ በሚለው
ማዕቀፍ ውስጥ ስለመኖራቸው ትዝ አይለንም።
ትዝ እንዲሉንም አንፈቅድም። ስለዚህ መውደቅ ሲባዛ
በመውደቅ ደለቀብን።
ያልታማሩ፤ ከአንድ ቋንቋ ውጭ
ሌላ ተጨማሪ የውጭ አገር ቋንቋ የማይችሉ፤
የመማር ዕድሉን ያላገኙ፤ ዕድሉን ቢያገኙም በተለያዬ ሁኔታ በዕድሉ መጠቀም ያልቻሉ፤ በተለያዬ ሁኔታ የጤናም ችግር ያላቸው
በመሆናቸው ወይንም በኤኮኖሚ አቅማቸው ኮሰስ ያሉ ዜጎች በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ውስጥ የሉም። አይታቀፉም። ነውር ነው።
በዚህ ሁኔታ ዜግነት የሚለውን
ታላቅ የመኖር ፍልስፍና ለማስረጽ - ለማብቀል - ለማጽደቅ - ለማስበል ችግር ነው።
ቀስ በቀስ ማንፌስቷችን፤ ፕሮግራማችን በራሱ ኢትዮጵያዊነትን ተገዳዳሪ እዬቆዬ
ሲሄድም የውስጥ ሸርሻሪ መሆኑን አናስተውለውም። በጭራሽ? ከቶ ድል የሚባለው ሜሪኩሪ ላይ ነበርን የታሰበው ወይንስ „ሰው“ „ዜጋ“ በሚባለው ህሊና? ወልደ
ግራነት።
· ፍላጎት።
በፍላጎት ደረጃ እንምጣ አንዱ
ስለደንብሬ /ሉዕላዊነት ተኮር/ ሊል ይችላል፤ ሌላው ስለ ጥበቤ ሊል
ይችላል፤ ሌላው ደግሞ ስለፈጣሪዬ ሊል
ይችላል፤ ሌላው ደግሞ ስለ ሃሳብ ነፃነት መግለጽ
ሊል ይችላል፤ ሌላው ደግሞ ስለመናገር ነፃነት ሊተጋ ይችላል፤ ሌላው ደግሞ ስለተፈጥሮ ሃብት ተኮር ሊሆን ይችላል፤ ሌላው ደግሞ ስለ ሃይማኖቱ
መላ ጊዜውን መስጠት የሚፈልግ ይሆናል፤ ሌላው ዲጅታል ዓለም ያሰኘዋል፤ ሌላው ስለተመጣጠነ ኢኮኖሚ አጀንዳው ይሆናል፤
ሌላው ደግሞ ተፈጥሮ አምላኪ ሊሆን ይችላል፤ ሌላው ለቤተሰቡ ብቻ መሆንን የሚሻ ይኖራል፤ ሌላው ለራሱ ብቻ
መኖርን የሚያስቀድም ሊሆን ይችላል፤ ሌላው
ደግሞ ዞግ ተኮር በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሊታታር
ይችላል፤ ሌላው ታሪክ ቀመስ ነገሮች ላይ ሊያተኩር ይችላል፤ ሌላው ላርባን እሳተ
ጎመራን ነፍሱ ጥፍት እስኪል ተከታይ ሊሆን ይችላል፤
… ሌላው ፍልስፍና ነክ ጉዳዮች
ላይ ሊያተኩር ይችላል፤ ሌላው እንሰሳት ተበድለዋል
ሊል ይችላል፤ ሌላው በአካባቢ ጥበቃ ላይ ብቻ ማተኮር ማዘወትር
ህልሙ ይሆናል፤ ሌላው በቅርስ ጉዳይ ሊሆን ይችላል ትጋቱ፤
ሌላው ባህል ነክ ጉዳዮች ላይ ሊሆን ይችላል፤ ሌላው
ምርምር ተኮር ሊሆን ይችላል፤ ሌላው በጾታ ነክ ጉዳይ ሊባትል
ይችላል፤ ሌላው በሰብዕዊነት ላይ ሊመሰጥ ይችላል፤
ሌላው እናቶች ተኮር ላይ ብቻ ሙሉ
ጊዜውን ሊሰጥ ይችላል፤ ሌላው ትችት ፈቃጅ
ይሆናል፤ ሌላው ቋንቋ ዘይቤ ላይ ሊያተኩር
ይችላል፤ የሌላው ተደሞ ደግሞ ሞድ ላይ ላይ ሊሆን ይችላል፤ የሌላው ደግሞ እስፖርት ቀመስ ሁነቶች ቀልቡን
ሊስቡት ይችላሉ፤
ሌላው መጻፍ ላይ ሊመሰጥ
ይቻላል፤ ሌላው ሙዚቃ እስፖርት ላይ ሊፈነድቅ ይችላል፤ ሌላው ማንበብን የሙጥኝ ሊል ይችላል። ሌላው በፖለቲካዊ
ሁኔታዎች ላይ ሊጠመድ ይችላል፤ ብቻ መኖር ባፈራቸው አኗኗሪ የስሜት ተፈጥሯዊ ስፖንሰሮች በሚሰጣቸው ጥበባዊ ኩነቶች፤
ተፈጥሮ ጸጋውን በሸለማቸው ወዘተረፈ ጉዳዮች ሁሉም የሰው ልጅ በምርጫው እና በፍላጎቱ ሊታደም መቻሉ ብሄራዊ ነፃነቱ ነው፤ ሉላዊም።
ተፈጥሯዊ ነፃነቱ። ከማንም እና ከምንም
ተንበርክኮ ሆነ ተኮድኩዶ፤ ተጨብጦ ሆነ ተኮርኩሞ የማይለምነው። እንግዲህ ይህ ወደ ባህሪያት ጉዳይ ጫፉን ሳንነካ ፍላጎት
ተኮርን በጨረፍታ ነው … ማዕቀፉ ኢትዮጵያዊነት ሲሆን ግን በዛ ውስጥ ያለው መበትን ሲሰላ ሁሉም አሳቻ መንገድ ላይ ማዬትን
ያጠይቃል።
እና … ይህን ሁሉ በእኔ ወረቀት
ማንፌሰቶ ሥር ካልተዳደርክ ዜጋዬ አይደለህም ከተባለ ኢትዮጵያዊነት አቅሙን ይፈታተነዋል፤ ትርጉሙንም ያዛባዋል፤ ኢትዮጵያዊነት ነፃነትም
ነውና።
ኢትዮጵያዊነት ገናና ማንነት
ነው። ይህ ገናና ማንነት በዝንጣፊ ዜማ የተገነባ
አይደለም። በፈተናዎች ውስጥ ነጥሮ የወጣ ማንነት ነው ኢትዮጵያዊነት። ለዚህ ነው ከ20 ዓመት በላይ በሑሁፎቼ መጨረሻ ከመፈጠሩ
በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር ኢትዮጵያዊነት የምለው።
· አገርና ህዝብ።
አገር ሲባል ሁሉንም አይነት
የማህበረሰብ ፍላጎቶች፤ አስተሳሰቦች፤ ምልከታዎች፤ ራዕዮች፤ ባህሬዎች፤ ህልሞች፤ ግንኙነቶች፤ ስሜቶች፤ ሃይማኖቶች፤ ዕምነቶች
ሁሉ አካቶ ነው። አገር ማለት ምን ማለት ነው ለሚለው „አገር"
በቃላት ክምችት ብቻ የሚተረጎም አይደለም። አገር
በመኖር ውስጥ ነው የሚገለጠው። መቸም መኖር ተተርጉሞ የማያልቅ ተፈጥሮ ነውና። አገር የሚለው ቃሉ እራሱ ዕውቅና ያለው መንፈስ ነው።
በቀላል እንግለጸው ብንል …
አገር ዓለም ዓቀፍ ዕውቅና ባለው የተወሰነ መሬት ወይንም መልክዕምድራዊ አቀማመጥ ነው። ህዝብስ? በዚህ ዓለም አቀፍ ዕውቅና
ባለው መልካምድራዊ አቀማመጥ ወይንም መሬት ውስጥ የሚኖር የሰዎች ማህበር ነው፤ ማህበረሰብ። የሰዎች ማህበር ደግሞ ህዝብ ነው።
ህዝብ ደግሞ ከለይ ከዘርዘርኳች
በላይ በመኖር ውስጥ ያሉ የሚገኙ ወዘተረፈ ፍላጎቶቹ
- ራዕዮቹ - ስሜቶች - የተፈጥሮ ጸጋዎቹ - ሥነ - ባህሬዎች፤ ሃይማኖቶች፤ ዕምነቶች ከጽንሰት እስከ ህልፈት ብቻ ሳይሆን
ካለፈም በኋዋላ የሚኖር ሥም ያለውን ሰዋዊ፤ ተፈጥሮዊ ነገሮች
ያቀፈ መጠነ ሰፊ የመኖር
ርስታዊ ትርጓሜ ነው። ግዑዛን ሳይቀሩ በአገር ውስጥ ይካተታሉ። እነሱም አገር አላቸው። አፈር ጉዑዝ ነው፤ ድንጋይ
ጉዑዝ ነው፤ ተራራ ጉዑዝ ነው፤ ሸንተረረ፤ ወንዝ ሁሉም ግዑዞች ናቸው ግን አገርነትን የሚሰጡ ያገኙም ናቸው።
አንዱን ነጥለን ወይንም ጨልፈን
አገር መሆን አይቻልም። አገርን ለመተርጎም ሆደ ሰፊነትን
ይጠይቃል። ጥሞናዊ ህሊናን ይሻል። በማቻቻል፤ በማስማማት፤ በማዋደድ፤ በማስተጋብር እናት ዥንጉርጉር ልጆቿን በምትይዘው
ጥበብ ያህል እንደ ባህሪዎች ብዛት፤ እና እንደ አፈጣጠሩ መቀበልን ይጠይቃል።
አሁን እናቴ ክብዬ ሴትም ወንድም
ልጅ አላት። አንዳችንም ሌልኛችን አንመሰልም
በባህሪም በፍላጎትም። የሚገረመው በመልክም አንመሳሰልም እንኳንስ በመኖር ውስጥ ባሉ ፍላጎቶች እና ባህሪዎች የአኗኗር ጥብቦችም
እንዲሁ የተለያዬን ነን። ግን ክብዬ ሁላችንም እኩል ታስተናግዳናለች።
ሁላችንም አንጎረብጣትም። ፍጹም
ሆነን አይደለም። ስታሳድግን እጣታችሁን ተመልከቱት አንዱ ከአንዱ ያንሳል፤ አንዱ ካንዱ ይበልጣል፤ አንዱ ካንዱ
ይወፍራል ግን አብረው ተባብረው መዳፍ ይሆናሉ። እኛንም ያኑሩናል በአንዱ መወፈር አንዱ የካሳው
አይቀናም፤ በአንዱ መርዘም አጭሩ አውራ ጣት አይቀናም አትቅኑ በሰው እያለች ነው ክብዬ ሰርክ ታስተምረን የነበረው።
የባለቤቷን ወገኖችም ወዳጅ
ስለሆነች ልጆቼ አንዱን ብቻ ከወደዳችሁ ግንጥል ጌጥ ነው
የሚሆነው እኔ ጸጉሬን ግማሹን ተሰርቼ ግማሹን ትቼ ገብያ ብወጣ ያምርብኛልን? ጆሮ ጉትቻዋን ሁሉ አውልቃ ታሳዬኝ ነበር፤
የጎንደር ሰውስ አንዱን ብቻ አድርጌ ብሄድ አይስቅብኝም? ትለን ነበር። በዚህ ውስጥ የአብሮነትን ጥበብ አጠጥታ
አሳድጋናለች። ድንቂት ኢትዮጵያዊነትን ቀልባናለች።
የባሎቻችሁን ወገኖች ውደዱ
እያለች በልጅነት ትንገርን ነበር። ሳቅን እራሱ አትቆጥቡት ሁሉ
ትለናለች፤ እሷም የወጣላት ሳቂተኛ ናት። እንደዚህ ሆነን አድገን እንኳን ከክፉ ነገር ጋር ባንተባበርም
መንገዳችን ግን የተለያዬ ነው … ራዕያችን ፍላጎታችን የተለያዬ መስመርን ነው የተከተልነው …
አገር ብሎ የሚነሳ ነፍስ እንደዚህ መሆን አለበት።
እንደ እናት። መሪ ይሁን ተማላ ሰብዕና። ተከታዮቹን መርዝ ቀልቦ ሳይሆን ፈውስ ቀልቦ መቅረጽ አለበት። ከሊቅ እሰከ ደቀቂ ቃሉን አገርን መዘከር ሳይሆን በመሆን ውስጥ
መሆን መቻል አለበት።
አንዱን ሳያንኳስሱ፤ አንዱን
ከሌላው ሳያቀላቅሉ ወይንም የአንዱን ተፈጥሯዊ ጸጋ ሳይሰነጥቁ፤ ወይንም የአንዱም መክሊት ሳይሰነጥሩ ወይንም ሳያገሉ፤
ወይንም በደቦ ሳያስገልሉ፤ ወይንም ሳይጫኑ ወይንም
ሳይስጭኑ ወይንም ሳይነጣጥሉ መቀበል።
ዜግነትን ማዕከል ለማድረግ
ይህን ፈተና ማለፍ ይጠይቃል። በወረቀት
ላይ የሚቀረጸው እና በአንደበት የሚነገረው አገራዊ
ብሄራዊ ማንነት መሬት ላይ ካለው ዕውነት ጋር መገናኘት ካልቻለ ሃሳቡ ይዳጣል ወይንም ይፈናጠራል በዚህ
ሂደት አውራ ሃዲዱ ይታወካል የኢትዮጵያዊነት መንፈሱ። ትውልድስ?
· ዜግነት ከአክብሮት ይመነጫል።
ዜግነትን ክብር ለመስጠት አንድ
የፖለቲካ ሊሂቅ፤ አንድ በማናቸውም ሁኔታ ያለ ዕውቅና ያለው ድርጅት ይሁን ሚዲያ ሰው ነህ፤ ሰው ከሆንክ መከበር አለብህ ብሎ
መነሳት አለበት። ዜግነትን ሰጪም ነሽም የለምና። ዛሬም እንደ ትናንቱ ውጭ አገር በክልል ነው የሚኖረው። በተለመደው መስመር …
መዳን አልተቻለም።
የሆነ ሆኖ ወደ ቀደመው እርዕሰ ጉዳዬ ስገባ ሰብዕናውን በክፉ ተግባር የተነከረ ከሆነ ክፋቱን ልንጸዬፈው ብንችል እንኳን „እርስዎ“ ብሎ መጀመር ግድ ይላል። ሰው ነውና። ወንድ ከሆነ „አቶ‘ ሴት ከሆነች ካገባች ወ/ሮ ካለገባች ወ/ት“ ቅጥያም ዕውቅና የቀለም ይሁን የሃይማኖት ካለ ማከል ማንን ይጎዳል? ይህ አክብሮት ትውፊት ነው። ካላስፈለገውም ካላስፈለጋትም በፍላጎቷ ወይንም በፍላጎቱ ውስጥ መሆን አይገደድም። ግን በትውፊት በትሩፋታችን ውስጥ እኛ ስለመኖራችን ሁልጊዜ ማረጋገጥ ይገባል። እኛ የጣስነውን እኛነት ማን ሊያሰከብርልን እንሻለን?
አገርን የገነባ ዘመናትን
እንዳይለያዩ አድርጎ ያያዘ እትብት ነው ለኢትዮጵያዊነት ሰውን አክብሮ መነሳት ነው
ፍጠረተ ነገሩ። እራስን አክብሮ መነሳት ምስክሩም ለሌላው ክብር ለመስጠት በመፍቀድ ውስጥ ይገለጻል።
ወይ መውደቅ ወይ ደግሞ ማለፍ።
እኔ ሳድግ ጎንደር ከተማ ተወልጄ
ነው ያደግኩት። ወላጆቼም። ትልቅ ሰውን ኢትዮጵውያን በአክብሮት ነው የምንጠራው ወላጅ ይሁን አክስት - አጎቶቻችን፤ መምህራኖቻችን፤ ጎረቤቶቻችን፤ ታላላቆቻችን፤ የቁልምጫ፤ የአክብሮት
ሥም አለን። ስለ ጉርብትና ያለው ጥበብ ልዩ ነው። ጉርብትና የመቻቻል እጬጌ ተቋምም ነው። የአብሮነትም ጌጥ።
እትዬ፤ ጋሼ፤ ጥላዬ፤ ወተተይ፤
አሽኰይ፤ አንባዬ፤ ጋሻዬ፤ እቴ አንጀቴ፤ እያያ፤ እታታ፤ እማማ፤ እማዬ፤ ናኒቴ፤ አባዬ፤ አባባ፤ እቴ ሆዴ፤ አህት አገኘሁ፤ ወንድም ዓለም፤ እታባ፤ እታለም፤
እቴዋ፤ እሜትዬ፤ አያ መኩሬዬ፤ አያ ጥላዬ፤ እቴሜቴ፤
ጋሽዬ፤ ጋሼ፤ ወዘተ … ዛሬ አገር ቤት ይኑር አይኑር አላውቅም። እኔ ሳድግ ግን እንዲህ ነው የነበረው። በዚህ ሁሉ
ኢትዮጵያዊነት ይገለጻል። ኢትዮጵያም ከነሞገሷ አለች። በሌሎች ቋንቋዎችም መሰሉ እንደሚኖር አስባለሁኝ። ምክንያቱም ኢትዮጵያዊነት ምንጩና አገነባቡ ከሃሳብ በላይ ነውና።
ትልቅ ሰው ሲመጣ ብድግ ማለት፤
አለቃ ሲመጣ ብድግ ማለት፤ ከውጭ ቆይቶ ሰው ሲገባ ብድግ ማለት፤ ኖር! ማለት፤ መንገድ ላይ በዕድሜ የሚበልጠውን
የማስቀደም፤ ሬሳ - ሙሽራ - ታቦት ከሆነ አለማቋረጥ - ቁሞ በክብር ማሳለፍ፤ ከባድ ነገሮችን የተሸከሙ ሰዎችን ማገዝ፤
ቢያንስ ቀደመው እንዲሄዱ መፍቀድ ይህ ነው ኢትዮጵያዊነት እኔ እማውቀው።
ዛሬ ትልቅ ዓለም ዓቀፍ ሚዲያ ላይ ተቀምጠህ ሃሳቡ የአንተ ስላልሆነ፤ ስለጠላኸው ብቻ አንጠልጥለህ ስትጠራው
ኢትዮጵያዊነት የቆመበትን ምስሶ እራስህ እዬነቃቀልከው ስለመሆኑ አይታይህም። እናስተውል። ባህላችን፤ ወጋችን፤ ልማዳችን፤
ትውፊታችን አክብረን እምናጣው የለም። እንዲያውም በክፉነት፤ በጭካኔ የበከተውን ሰብዕና ጸጸት እንዲገርፈው በዬደቂቃው ብቁ
ምግባራችን ቦንብ ይልክለታል።
አንጠልጥለን፤ አቃለን ስንጠራ፤
ለዛውም ሊሞግት የሚችል ጉልበታም አምክንዮ እያለን የፈጣሪን ፍጡር አቃላን፤ አሳንሰን ስንጠራ ምን ብክል ዘር እዬተተከለ
ስለመሆኑ ማስተዋሉን ተነፍጎል።
መምህር ተሁኖ የአንድ አገር
መሪን „አንተ“ እያተባለ በጥላቻ ስሜት ሲጠራ የሙያ
ልጆች፤ ተከታዮችን ምን እያሰተማርን ስለመሆኑ አይታሰብም። ማሰሮ እንኳን ጆሮ አለው እንኳንስ የሰው ልጅ። እርግጥ ነው የኪነ
- ጥበብ ሰው ከሆነ አንተ አንቺ ይፈቀዳል። ቤተሰባዊ ትስስሩ መክሊታዊ ስለሆነ።
ታላላቆች የጥበብ ታቦቶች ይህን
ቅኖና ነውም ያሰረከቡን። አሁን ተፈጥሮው አገር የሆነውን
የቅኔው ልዑል ብላቴ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን አንተ ብለን እንጠራዋለን፤ ጋሼ ደረጄ፤ አቤ እንላለን። የሚገርመው እዚህ ሲዊዝም
አንተ/ አንቺ ነው የጥበብ ሰው የሚጠራራው ሚዲያ ላይም፤ የጥበብ ኮርስ ላይ ሁሉ …
ሌላው ቀርቶ የዮጋ ቤተሰብ
እንዲሁ አንተ/ አንቺ ነው የሚባባሉት። የዮጋን ካነሳሁ ዘንዳ የቤተስቡ ትህትናው እና ርህርህናው ራሱ ተቋም ነው። ፍቅሩም፤
ትብብሩም ፍጽምና አለው። ያ ለጋስ እና ቸር ስጦታ መንፈስ ሲሰንቀው
ጤና ነው። ልዩ የሰናይ ስጦታ። እያንዳንዱ የጥበብ ዓይነት የራሱ ዲስፕሊን አለው። በዲስፕሊኑ ውስጥ ዲስፕሊኑን ለመሸከም
ርህርህናን ይጠይቃል። አብሮነትን ይጠይቃል። ሰዋዊነትን ይጠይቃል። ተፈጥሯዊነትን ያነግሳል።
· በጥቃት ውስጥ ያሉትን መንፈሶች
በማዳን ነው ማሸነፍ የሚገኘው፤
ወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌሰቶ
እና መሰሎቹ ማህበረ ኦነጋውያን ጨምሮ ጸረ ኢትዮጵያ መንፈሶችን ጨምሮ እነዚህን ኢትዮጵያዊነት የቆመባቸውን ምሰሶዎች ነጥሎ
እንዲጠቁ ማድረግ የተፈጠሩበት ነው።
ኦሮሙማ በገላጣ በተሰናዳለት ሜዳ
ነው እዬተንፈራሰሰ የሚገኘው። ዛሬ „በመደመር“ ሥም የሚፈጽው ሁሉ የህወሃት ራዕይን ነው። ሌሎችም በኢትዮጵያ ሥም የተደራጁትም
ተሳክቶላቸዋል። ድል ባይቀናቸውም ግን ፍላጎታቸውን አስፈጻሚ ፈርኦን አግኝተዋል። ለዚህ ነው እንክብካቤውም ድልቂያውም።
የሆነ ሆኖ እኛ መሻላችን
የሚታዬው እንሱን አንጠልጥልጥሎ በመጥራት አይደለም። እእ።
እነሱ የተዋቀሩበትን ከይሲ
መንፈስ መንቀል የሚቻለው ኢትዮጵያዊነት ተጻሮ የሚነሳውን ንቀትን በአክብሮት ተክቶ በማሳዬት ትውልዱን በመሆን ውስጥ ሆኖ
ማሰተማር ሲቻል ብቻ ይሆናል። ማፍረስ የሰውን ጭንቅላት ሳይሆን፤ መበተን የሰውን ጭንቅላት ሳይሆን የተነሳበትን ክፉ ጨለማዊ አረሞማዊ ሥረ ሃሳቡን ነው።
ክፉ ሃሳብ አራማጆችን እራሱ አክብሮ መነሳት ትወልድ ይማርበታል። መሰሉ
በመፈጸም ነው እኛ የምንታወቀው በመናቅ አንጠልጥሎ በመጥራት። በዚህ ውስጥ ማሸነፍ አይመጣም። ይልቁንም ተሸናፊዎች ነን።
የእኛ ሽንፈት ተከታዩ
ለትውፊታችን ነቀርሳ ተጨማሪ ቁስለት በመፍጠር ይሆናል። ኢትዮጵያዊነትን የሚያፋፋው በተዘመተብት አምክንዮ የማያዳግም የመሆን
ገበር ሲበጅለት ብቻ ነው። እኔ ያነሳሁት „አክብሮትን“ ብቻ
ለዛውም አንዲት ዘለላ ጉዳይ ነው። ይህም ከአንድ ጎጆ ቤት አንድ እሳር የመምዘዝ ያህል ነው።
መሬት ላይ ከገበሬው ጋር
በመንግሥት መዋቅር ሲሠራ እጅግ ብዙ ጉዳዮች ነው ያሉት። ራሱ "ማክበር" የፍቅራዊነት ት/ቤት ቢኖረን አንድ የትምህርት ክፍለ-
ዘመን ሊሆን የሚችል ነው። የሚመረቁብት የሙያ ዓይነትም ነው እንደ ሥርጉትሻ ፍልስፍና። እንዲጠፋ የተበዬነበት የአማራ
ማህበረሰብ እኮ ተፈጥሮዊ ጸጋውን፤ መክሊቱን፤ ሰብዕናዊን ማክበረን ስለተነፈገው። የነፈገውን አውሬያዊ ልቅ ዝልግልግ መንፈስ
ማሸነፍ የምንችለው እኛ ኢትዮጵያውውን ማክበረን ስንስከብር ይሆናል።፡
የእጅ እና የራስ አሻራችን
የተለያዬበት፤ የሰው ልጅ ኮፒ የሌለውም ለዚኸው ነው ዘርፈ ብዙ የመኖር ጥበቦች ናቸው ያሉት። እስከዚህ ድረስ በጥልቀት የሰውን
ተፈጥሮ ማንሰላሰል ይገባል። እንደ ሸሚዝ፤ ሱሪ፤ ቀሚስ የሚከዘን ምንም ነገር እንደሌለ መሬት ላይ እውነቱ ይነግረናል። ዕድሉ
ተገኝቶ መሥራት ከተጀመረ …
ሊሂቆቹ አባቶቻችን ምን ያህል
ከእኛ ቀድመው ዛሬን እንደሰጡን ረቂቅ መሆናቸውን መታየት ያለበት ከዚህ አንጻር
ነው። ለዚህ
ነው ወላጆች „ወልደሽ ወልደህ እዬው“ የሚሉት
…
አንዱን „ማክበር“ መፈጸም በተሳነን ቁጥር ቀስ በቀስ እኛው ጸረ ኢትዮጵያ
ምልከታ ችግኝ አምራቾች ሆነን ቁጭ እንላለን። እነሱ ከሚፈልጉት መስመርም ቀጥ ብሎ መግባት ነው። ትውፊታችንም ሙት
መሬት ላይ የሙጥኝ ይላል። ስለዚህ በትውልዱ ሹልከት ውስጥ ሁላችንም አለን ወይንም ራሳችን ሸርሽረናል። በዛ ላይ ቤት ውስጥ ልጆች ካሉን ደግሞ ዕዳ
ከሜዳ ማፈስ ይሆናል።
… ታዲያ ምን
ይፈረዳል? የዛሬ ልጅ አቨውን ቢደበድቡ - በደቦ ሻሸመኔ ላይ አይተናል የሃይማኖት አቨው ሲደበደቡ፤ የዕድሜ እኩዮቹን ገድሎ
ዘቅዝቆ ቢያንጠለጥሉ - በወበራ፤ ነፍሰጡሮችን ገድሎ በጽንሱ ቢጫወት? ወይንም ገድሎ በመኪና ላይ ቢኬድበት፤ ወይንም ገድለው
ቢያቅጥሉት ሌላም ሌላም … ሎቱ ስብሃት ስለቃሉ።
ወይንም በመዶሻ ቀጥቅጦ - በደቦ
አምሳያ ፍጡርን ቢገድል …?! እኛም እኮ ትውፊታችን ሳናውቅ እየቀጠቀጥነው አይደለምን? ሰው መከበር አለበት ብለን ስንነሳ
በውስጥ የምናስቀምጠው ኃይለ ቃል አለ። "አንተ
እና አንቺ" እያልን ስናብጠለጥለው። የተፈጥሮ ጥሰት ምንጩን ማጥናት፤ መፍትሄ መሻት ካሰኜኝ እኔ
ከሚለው መጀመር ይገባል። እኔያዊነትን ማረም። ክክፉ ሥራ ጋር አለመተባበር ማለት እና ሰውን አንጠልጥሎ መጥራት ምን
ያገናኛቸዋል?
እርግጥ ነው ለጭካኔ፤
ለዲስክርምኔሽን፤ ለአስምሌሽን እውቅና መስጠት ሊመስል ይችላል። ነገር ግን መጠጊያ ያጣ ትውልድ እንዳለን እንሰበው። ስሜት
በሞቀ እና በቀዘቀዘ ቁጥር መነጠልን፤ መገለልን፤ ክፉነት፤ ጥርጣሬን የሚነዛ ማዕት ደግሞ አለን ሳናውቀው። ትውልዱን ፍዳውን
እያስከፈልነው ነው - እራሳችንም።
„መብት አለኝ ግዴታ የለብኝም“ ይላል ጋዜጠኛ- አክቲቢስት - ጸሐፊ፤
ካለ መብት የተፈጠረ ግዴታ፤ ካለ ግዴታ የተፈጠረ መብት ያለ ይመስል። በዬትም ዓለም እንዲህ የለም። መብትን ለመጠዬቅ ግዴታን ማሟላት ግድ ይላል። ግዴታን አሟልቶ ነው መብት የሚጠዬቀው። የሰው ልጅ ከእንሰሳም
የሚለዬው ይህን መስተጋብር በህይወቱ ውስጥ ስለሚተረጎምም ነው። ልቅ ዓለም የለምና … ህግ አልባም አገር የለም። ምን አልባት ልቅ ነፍስ ሊኖር ይችላል እንደ ተፈጠረ … ዝርግ።
በፖሊሲ ደረጃ አቅም ያለው አካል
ኢትዮጵያዊነት ነፍሱን እንደማያቆዬው፤ ሩሁን እንደማያስቀጥለው የ100 ዓመት ህልሙን እንደሚያራቁተው ስለሚያውቅ አዋጅ አውጥቶ
እዬታገለው እኛ ደግሞ ለዛ ስንቅ አቀባይ ስንሆን ያሳዝናል። ተቀናቃኝ፤ ሞጋች፤ ተቃዋሚ ሃሳብ አራማጆችን የማክበር አቅሙ
የለምና። ይህ ዕውነት ነው።
እሱ አካል አደራጅቶ፤ መዋቅር
ዘርግቶ ኢትዮጰያዊነትን ዘርፈ ብዙ መክሊቶቹን እዬታገለው እኛ ደግሞ አንዷን ዘለላ „ማክበር“ አቅቶን „አንተ አንቺ“ እያልን
ስትዘነጣጥለው፤ ቋንቋ ሁለተኛ ሦስተኛ ካልቻልክ አንተ አይመለከትህም በማኒፌስቶዬ ሲባል፤ አንቺ አይመከትሽም ምንትሱ ሲሆን፤
የተማረ ያልታመረ ሲባል ለእሱ ማዳበሪያ፤ የዛ
የጥፋት ተልዕኮ አስፈጻሚ ተቋም ህሊና ስለመሆን አይታሰብም። ላፒስ ለሁሉም ያስፈልገዋል። ላፒስ ነው ያልኩት ኡሁ አይደለም።
ኡሁ ድልዝ ነው የሚሆነው። ልባችን ላውንደሪ ያስፈልገዋል። ትውልዱ ካሳዘነን።
· ህግ ተላላፊነት እንደ ጀብዱ።
„ህግ ተላላፊዎችን ጠላሁኝ“ ይላል አካል የሌለው
የእግዚአብሄር ቅን አገልጋይ ቃለ ወንጌል።
ሌላም ምሳሌ ላንሳ … ምንም
ይሁን ምንም ህግ አለ ኢትዮጵያ፤ በዛ ህግ ልትገዛ - ልትተዳደር - ልትኖር ከፈቀድክ በፈለገው መልክ ጥፋት ሳይኖር ክስ
መበደል አለ። እሱ ለደነገገው ህግ መገዛት አልቻለም ተብሎ
ግን እርስዎ መከራ የተቀበሉለትን የህግ የበላይነት ህልም በመታበይ መዳፈር
ምን ሊባል ይችላል?
ህግ አክብረው ነው ህግ
ተላላፊዎችን መሞገት የሚገባ እንጂ በህግ
ጥሶሽ አይደለም። ከህግ በላይ ማንም የለም። ኑሮም አያውቅም። … የሃይማኖቱም ህግ እኮ አለ። የሃይማኖትም ቀኖና እና ዶግማ
አለ። ማህበረሰቡ የደነገጋቸው ያልተጻፉም ህግጋት ድንጋጌዎችም አሉ - በህሊና ሰሌዳ የተጻፉ። ለዚህ ነው እኔ ኢትዮጵያ በተፃፈም
ባልተፃፍም ህግ ትተዳደራለችም የምለው። እንዲያውም ተፈጻሚው የማህበረሰቡ ያልተፃፈው ህግ ድንጋጌም ነው ከተፃፈው ይልቅ
…
ምንም ሙያውም ብቃቱም ሰብዕናው
አይኑራቸው ግን በኢትዮጵያ ሥም ያሉ ዳኞች አሉ። ከሥሙ ፊት ለፊት ኢትዮጵያ የሚል ኃያል ተፈሪ ቃል በመንፈስ አለ። ኢትዮጵያም
እራሷ ህግ ናት። እነሱን ሳይሆን ፍ/ቤቱ
ሲጠራ የፊቱ ሥያሜ ኢትዮጵያ የሚል መሆኑን መተላለፍ በራሱ ወፍራም ግድፈት ነው።
ስለዚህ ኢትዮጵያዊነት ከገባን
ለዛ ክብር ከመቀመጫህ ዳኛ ተብሎ የተሰዬመው ሲጋባ መነሳት ምን ይገድል? ምንስ ይቀራል? አይከፈለበትም። አክብሮቱ እኮ ለቦታው
ነው። አክብሮቱ ለዕውቀቱ ኤትክስ ነው። ከሁሉ ባላይ አክሰሱ
ያላቸው ተተኪዎች ያን ይመለከታሉ። እራሳችን ለልጆቻችን አረም እንዳናበቀል መጠንቀቅ ይገባል። ይህ ኢሚንት ሊመስል ይችል ይሆናል።
ግን የገዘፈ፤ የተደለዘ የትውልድ ድንብልብል አሻራ ይሆናል።
መታብይ ትውድልን ቢያጠፋ እንጂ አይገነባም። ሁሉም የዘራውን ነው አሁን
እያፈሰ ያለው። ለነገሩ የትውልድ በመንፈስም በአካልም ብክነት አጀንዳ አይደለም። አጀንዳው ዘመን ይዞ ተዘመን አንዱን አሳጥቶ ወይንም ኮንኖ ራስን ጽድቅ መንበር ላይ መኮፈስ ብቻ
ነው። ለዚህም ነው ተፈጥሯዊነት፤ ሰዋዊነት ጠቀራዊ ጠፈጠፍ የበዛበት። ውርዘት አና ያለበት። ብልዘት የሚዳክርበት። ውይበት
ምልክቱ የሆነ። ማዲያትም።
· መከሰስ ሁሉንም ይመለከታል።
ሳስተናል። መሳሳታችን መሰረታዊ አምክንዮው እኛ እምንታገለውን
አለማወቃችን ነው። በትውፊታችን ጣር ከሳሽ
እና ተከሳሽ፤ በዳይ እና ተባዳይ ባንሆን ነው ቁም ነገሩ የእኔ ጹሑፍ። እኛው እራሳችን ፈቅድን ስንንደው የኖረውን ገመናም አለብን። ኢትዮጵያን ለመንቀል ከተጋው ክፉ መንፈስ ጋር
ለመታገል እሱ በሄደበት መስመር ተሂዶ አይደለም። አልነበረም። ይህ ወደዬትም ወደፊትም አያደርሰንም። እኛም አሳቻ መንገድ ላይ
እንዳለን እንፈትሸው።
አንድ ትልቅ ማህበረሰብ
አልነበረም፤ አልተፈጠረም ሲባል ኢትዮጵያዊነት አንደሚታመመ አይታወቅም። አክብሮትም ተጥሷል። አገር የሚለው ጽንሰ
ሃሳቡ ቢገባን፤ ትርጉሙ ብንረዳው ሚስጢሩ አይደለም በህይወት ያለውን በህይወት ለሌሉትም ክብር ይገባ ነበር። አገር ስለመቆዬቷ
የእነሱ ሙሉ ተሳትፎ እና ቀናነት ተደምሮ ነው እና።
ቁንጽላዊ በሆነ ግብግብ የተፈጠሩ
ዕሳቤዎች እና እኛ ስንጓዝባቸው የነበሩ መንገዶች ወልጋዶች ናቸው። በዚህ ውስጥ ተሆኖ ነው ትውልዱ የሾለከው። ለኢትዮጵያዊነት አለዘንለትም እኛው እራሳችን።
ለመሆኑ ትውልድን የሚያንጽ ምን
የሚዲያ ተግባር አለን? ራሱን የቻለ ድህረ ገጽ፤ ብሎግ፤ የአዬር ጊዜ ሰጥተነው እናውቃለን? ለመሆኑ ትውልድን የሚያንጽ
የትምህርት ተቋማትስ አለን? በሞራል ማለቴ ነው። ት/ሚር ረስቼ አይደለም። መማር ፕሮፌሰር ደረጃ ቢደረስም
ራስን ማሸነፍ ካልቻለ፤ እውነትን የሚሸሽ መማር
ከሆነ ትርጉሙ መማር የሚለው ለእኔ ያንሰብኛል። መማር በራሱ የትውልድ ትውፊት፤ የመንፈስ ጽንሰት ተጽናት ስለሆነ።
የሆነ ሆኖ አንድ ኢትዮጵያ ውስጥ
በእነዚህ ሥያሜዎች የሚጠራ መከባበር፤ መቻቻል፤ መቀበል፤ መታገዝ፤ መደማመጥ፤ ትህትና፤ ደግነት፤ ርህርህና፤ ኪዳን፤ ታማኝነት፤ አብሮነት፤ መሆን፤ ሥራ፤ ወዘተ የአንደኛ ደረጃ ት/ቤት ይሁን ኮሌጅ ይሁን ዩንቨርስቲ አለን?
በዚህ ሥም የሚጠራ ተቋምስ?
መቼም እነኝህ ቅዱስ ቃላት ዞግም የላቸው፤ የትምህርት ደረጃም የላቸው፤ ቋንቋም የላቸውም፤ የልደት ሰርፍኬት አይጠይቅባቸውም፤
የሃብት ደረጃ አይጠይቅባቸውም። የአንድ ዞግ አንጡራ ኃብታት አይደሉም ግን አንደፍራቸውም ስለምን? በውስጡ ስለሌለን።
በመምሰል ውስጥ ያለው መኖር ሙጃ ነው። ሙጃው
ደግሞ ለእነሳሳት መኖ እንኳን
የማይውል። እያንዳንዳችን ስንፈጽም የኖርነው 50 ዓመት ሙሉ ኢትዮጵያ የቆመችበትን ምሰሶ የሚያጠናክር ሳይሆን የሚንድ ነው
የነበረው። ስለዚህ ተጠያቂነቱ የሁሉም
ነው። ይህን ለአንድ ድርጅት ጠቅልለን የምናሸከመው አይደለም። ኢትዮጵያዊነት መሪ እንዲሆን ቢፊቀድለት ሁሉም ችግር
መልክ ሊይዝ ይችላል። ነገር ግን ከራስ መጀመር ዳጥ ነው።
አብረህ ቁጭ ተብሎ ማዕድ መቀመጥ
የማይቻል? አሁን አቶ ልደቱ አያሌው ሞት ይፈረድባቸው፤ ውገረው ውገረውን ስታዳምጡ ኢትዮጵያዊነት ደረጃው ምን ያህል ቁልቁለት
ስለመሆኑ ታስተውላላችሁ። አቶ እስክንድር ነጋ ያህል የብሄራዊነት አይከን „አብድ“ ሲባል ስታዳምጡ ውርዴነትን ታስተውላላችሁ።
ሰው በመፍቅድ ውስጥ ያለው
ልዩነት? ለመጨረሻ ጊዜ የማታዳምጠው፤ የማታዬው፤ የማይሞግትህ ሰው ሲያልፍ እንኳን ሃዘኑ እኩል አይሰማም። ወድቀናል።
እራሳችንንም ድጠናል።
እሱንም ነፃ ለማውጣት ከነበረ የነፃነቱ ተጋድሎ - ሃዘኑ ሊሰማን፤ ድንጋጤው ሊገባን ይገባል። እኔ ጠቅላይ ሚኒስተር
አብይ እና ሥም የለሹ ካቢናቸው ከእብደታቸው ቢነጹ እሻለሁኝ።
ስለምን? እምታገለው እነሱንም ከክፉነት፤ ካውሬያዊነት፤ ከደደነደነው ፈርዖናዊነት ነፃ ይሆኑ ዘንድ ነውና።
የትግሉ ማዕከሉ ዜግነት ከነበረ ፍልስፍናው ሰው ላይ መነሳት ነው ቁምነገሩ። ባልነበርንበት ውስጥ
ነበርን ዛሬ ላይ ያለውን ሁነት ስትመለከቱ ፉርሽነቱን ማስተዋል ይችላል። ሃዘን የማይሰማው ኢትዮጵያዊነት አልተፈጠረም ወደፊትም አይኖርም። ርህርህና አልባ ኢትዮጵያ አልነበረችም ወደፊትም
አትቀጥልም። ስለ ወገንህ መኖር በህይወት ከማሰብ ሞቱን ከሆነ፤ በመኖር ውስጥ አለመፈጠር ነው
ለእኔ። እራስንም መጠዬቅ እኔ የዬትኛው ቤተኛ ነኝ ብሎ መፍቀድን ይጠይቃል?
ሰው መኖር አለበት ፈጣሪ
እስኪጠራው ድረስ።
መኖር የሌለበት ክፉ ሃሳቡን ነው። ክፉ ሃሳቡን ደግሞ እሱን ስለገደለከው ወይንም ሰለ አስገደልከው አይሞትም። ወይ አጥር
አትድረሱ ስላልከው አይሆንም። አትጋባ፤ አትዋለድ ስላልከውም አይሆንም።
መሰሎቹ የክፉ ሃሳቦች
ማህበርተኞች አሉና ምድር ላይ። እሱ በነበረበት ውስጥ አንተ ስለመኖርህ ክፉ ሃሳብህ ራሱ ምስክር ነው። ሰውን ማዕከል
አለማድረግህ። ስለዚህ ተሸንፈሃል። ውሸትህም ነው አገር በሚለው ማዕቀፍ ውስጥ ስለመኖርህ። ሰንደቁም ጠንቶበት።
በሌላ በኩል በተዘዋዋሪም ቂም
ለትውልዱ የምክነት የምጥ ት/ቤት መክፈት መሆኑንም ተረስቷል። ታዘቢ ልጆች አሉና። በዚህ ክፉ ሃሳብ የያዘው ሰው ህልፈት ጮቤ
አስረግጦም ከሆነ፤ በሌላ በኩል ቂም አርጋዥ ያልተገላገሉት የአገር ዕዳ መሆንም አለበት። ክፉ ሃሳብን በደግ - ሃሳብ፤ ቂምን -
በይቅርታ፤ ጭካኔን -በርህርህና፤ መታበይን - በመከባባር፤ አደምኝነት - በአብሮነት፤ ግለትን - በማቅረብ ነው ማሸነፍ
የሚቻለው። ትውልድ እሚገነባውም እንዲህ ነው።
ያ የተገፋ፤ ይሙት በቃ በቁሙ
የተፈረደበት ሰው የወለዳቸው ልጆችም ይኖሩታል። ልጆች ባይኖሩት ቤተዘመዶች። በእነሱ ህሊና ውስጥ የባይታወርነት መንፈስ እንዲወል፤ እንዲያድር እና
እንዲያሰብል መፍቀድ በራሱ ለትውልድ ጥፋት ሌላ የከንቱነት ተቋም
ነው። ስለ አመለጠን ትውልድ ስንብሰከሰክ በመጪዎቹ ላይ ደግሞ ሌላ የእርድ ድንኳን ዘርግተን ነው።
በዚህ ውስጥ ኢትዮጵያዊነት አብሮ
ቁስል፤ ንድድ፤ ጨጓራው ቅጥል ማለቱ አይታዬነም። ኢትዮጵያ ምን ታመመሽ ብታባል ጨጓራዬ ተቃጥሎ ወጥቶ ተጥሏል ትለን
በነበረ። አቃጠልናት። አጨስናት። አንደድናት። ቢያንስ በእጃችን ባለው መልካምነት ስለምን መጽናኛዋ አንሆናትም። እዬቻልን። በማንስ
ትጽናና? እንዘንላት እንጂ? እናት እኮ ናት?
ሁለት ትውልድ ሾልኮ ከትውፊቱ
አሁን እንኳን ከ18 ዓመት በታች ያሉት በአንድም በሌላም የከፍትንላቸው መንገድ ጠናና ነው። ከቂም ራስን ማጽዳት ትልቁ ፈተና ነው። የትውልድ ብክነት ሲባል ሞቱ ብቻ ሳይሆን
በመንፈስ ያጣናቸው፤ አሁንም እያጣናቸው ያሉ ልጆቻችን በሚመለከት ብሄራዊ ብቻ ሳይሆን ሉላዊም ነው። ዛሬ ሉላዊ
ዜግነትም አለና።
በስደት ተወልደው የሚያድጉ፤ ብናኝ ፍቅር ሰጥተናቸው የማናውቅ፤ አድገው ትምህርት ላይ ያሉ፤ የጨረሱ፤ ጋብቻ ለመፈጸም የተሰናዱ ልጆች አሉን። ለእነሱ
ሁሉ መታሰብ አለበት።
ይህ ትወልድ ደግሞ ጮሌም ነው። ልጋልብህ ቢባል በጅ የሚል አይመስለኝም።
ትዝቡትም መጠነ ሰፊ ነው። ዳኝነቱም እንዲሁ። የፈሰሰ ውሃ አይታፈስም። የመንፈስ ሃብት ከማራቆት በላይ ኪሳራ የለም። ለዚህ አዲስ ትውልድ ሉላዊ ዓለም የሰጠው፤ የሸለመው፤ የፈቀደለት ሥልጣኔም አለ። ስለዚህ ቢያንስ
በእኛ ጥንቃቄ ጉድለት የሚፈጠሩ ግድፈቶችን ለማረም እኔም ጥፋተኛ
ነኝ ብሎ መቀበል ይቅደም።
እኔም ለጥፋቱ ተጠያቂ ነኝ ተብሎ ይታሰብ። ነገ የማይገኝ ነገር
ሚዲያ ላይ ወጥተህ ስትናገር ቃሉ ከስሎ፤ በኖ፤ ተኖ የጉም ሽንት ሆኖ ሊቀር አይችልም። ትውልዱ እኔም ልሞክረው ማለቱ አይቀሬ
ነው። ተስፋ እና ተስፈኛውን የምንመራበት ዘይቤ ዕለታዊ ነውና። ነገ ማግሥት የሚል ነገር አጀንዳችን ሆኖ
አይውቅም። መቼም ይህ ሃሳብ ሞጋች ስለሆነ ሙግት ያሰኘው ይምጣ እና ይሞግተኝ። ቀኖች ሳይሆኑ መሆኖች ቢመሩን ነው ፍሬ ነገሩ።
ከሁሉም የተሻለ ሳይሆን
ለሁላችንም በአውንታዊነት ዱብ ዕዳ የሆነ የትውልዱን ብክነት በመንፈስም፤ በአካልም ሊመክት የሚችል በመሆን ውስጥ ያለ
አዲስ አስተሳሰብ፤ አዲስ ፍልስፍና፤ አዲስ ቀመር እንደምን ይወለድ ነው የትናንትም የዛሬም ምጣችን። ውራጅ ያለሆነ። ቅምጥ ፍላጎት አሽኮኮ
ያላደረግ።
ለምህረት ቀን ቀጠሮ
አያስፍልገውም። እስኪ በቅድሚያ ለራስ ምህረት ይሰጥ። ቅድመ ሁኔታ አያስፍልገውም። ራስን ይቀር ለማለት። ስለ ብሄራዊ እርቅ እና ሰላም ከመታሰቡ በፊት ራስን
ይቅር ማለትም ይጠይቃል። ራስን ይቅር ማለት የተከዘነው ቂም እና በቀለ ተጸይፎ መርዙን ከራስ ማውጣት ማለት ነው። ዛሬ
እንኳን አለመቻሉን አሰተውያለሁኝና።
ዝም ብሎ በሌለ ነገር ላይ
መንፈስን ከማንጠልጠል፤ ባለ ነገር ላይ
ተነስቶ እራስን በዛ ማደረጀት ይጠይቃል። መደራጀት በመንፈስ ይሁን። የመንፈስን
ቤት አጽድቶ። ቆሻሻን ከልቶ - ተጸይፎም። ቂምም፤ በቀልም፤ ጥላቻም፤ አድመኝነትም፤ ቅናትም ቆሻሻዎች ናቸው።
ዘመኑ ከፈቀደው አዲስ መስመር
ጋር ለመጓዝ በጥንካሬ ላይ ጊዜ ከማቃጠል በድክመቶቻችን ላይ አትኩሮት፤ አዲሱን መስመር ለመከተል ራስን ማረምን ማስቀድም
ይጠይቃል። ማንም ብፁዕን ስላልነበር ዛሬም ሊሆንም ስለማይችል። ኢትዮጵያዊነት ሲቆጠር ከአንድ
ሰው እንደሚጀመር አምኖ መቀበል። ከዚህ ጋር እርቀ ሰላም ሳያወርዱ ዜግነት ላይ መነሳት አይቻልም። ቢሞከርም
ትልሙ እንደለመደበት ይፈረካከሳል።
አንድ ነገር ጸንቶ እንዲቀጥል ካስፈለገው ራስን አሸንፎ መነሳት ይኖርበታል። ለዚህ ነገረ ልደቱ አያሌው ታላቅ የመማሪያ
ተቋም ናቸው። በሳቸው ያለፈው መካራ፤ አሁንም ይልተቋቸው መከራ። ሞትን በዬሰከንዱ እንዲጠብቁ የተደረገበት የደቦ ውሳኔ ኢትዮጵያዊነትን
አያሰነብትም።
· 13ወራቶቹ ሥማቸው ሰኔ ነው። ለምን?
መታበይ ካለብን ከዛ መለያዬት፤
ማንአህሎኝነት ካለብን ከዛ መጽዳት፤ ውሸት ካለብን ከዛ ራስን ማጠብ፤ ኢጎ አሉታዊ ከኖረብን ከዛም መፋታት፤ ቂም ካለብን ከዛም
መለያዬት ዜግነት ላይ ለመነሳት እነዚህ ሁሉ ፈተናዎች ማለፍን በጥቂቱ
ይጠይቃል። ለሁሉም ሁሉም ቀን ሰኔ ነው ለዘመኑ። 12 x 30= 360 ቀናት ሁሉ ፈተና ላይ
ለመቀመጥ ሰኔ ነው ለደፋሮች።
አገር የሚገነባው፤ ትውልድ
የሚታነጸው ራስን ባሸነፈ ደፋር፤ ቆራጥ ቅን ንጹህ ልቦና አቅም እና ክህሎት የመሪነት ጥበብ ነውና። ልቅና የሚመዘነው ከዚህ አንጻር ነው። ላመኑበት አዲስ መስመር ደፋር ሰብዕና ያስፈልገናል። የማይደፈረውን መስመር
እና አምክንዮ የሚደፍር። ግን ጥላቻ በምንም አቀራረብ ቢሆን መጸዬፍ ግድ ነው። በጥላቻ አገር አልተመሰረተም፤
አልጸናምም። ጥላቻ አቀንቃዮችን ዕውቅና ከመስጠት መታቀበም አንዱ ብልህ መስመር ነው። ሊቀጡ ይገባል። ሊጸጸቱ ይገባል።
· ደፋር ቢገኝ!
ህወሃት ሙቷል ሲሉ ይገርመኛል።
አስተሳሰቡ እኮ አገር ምድሩን እየገዛ ነው ያለው። አሁን ሁሉ ሰው ልብ አላለውም። ሥር ነቅል ለውጥ ሲል እንኳን ይህ የፖለቲካ
ፍልስፍና የሚባል ሳይንስ ተንሳፎ ይታያል። የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ ሙሉ ለሙሉ በህይወት አለ። ያለው ትግራይ ላይ ብቻ
ላይ አይደለም አገር ውስጥም ውጭም ነው። ስለምን? ሁለት
ቁምነገሮች ናቸው ህወሃትን የሚገልጡት ፒላሮቹ።
1. አንዱ አማራን በሁሉም
መስክ መቅኖ ማሳጣት - በመንቀል፤
2. ሁለተኛው ቅድስት ኦርቶዶክ
ተዋህዶ ሃይማኖት ማባከን - በመዳፈር፤
እነዚህ የወያኔ ሃርነት ትግሬ
ማንፌስቶ መሥራቾች የተነሱበት አውራ አንኳር ዶግማ ነው። ምርኩዞችንም ሲፈጥሩም፤ ባላዎቹ ሆኑ ማገራቸው የአወቃቀር ሂደታቸው
ይኸው ነው። ስለምን ሲባል? ሁለቱም የኢትዮጵያዊነት ጽኑ፤ የማይናወጹ ትንፋሾች ናቸው ተብለው ይታመኑ ስለነበረ በጠላትነት
እንዲጠፉ የታወጀባቸው ናቸው። በመንፈስ እራሱ እንዲፋቁ ነው ፖሊሲ ተንድፎ የተሰራበት።
ሁለቱም አሁንም እጅግ በሚሰቀጥጥ
ሁኔታ ህላዊነታቸው አደጋ
ውስጥ ነው። ለዛውም ከቀደመው በባሰ ሀኔታ በእጥፍ ድርብ። እራሱ የፌድራሉ እና የትግራይ ጦርነቱ ስለምን ለሚለው መልስ አይሰጥም?
ያው ህወሃታዊ ማንፌስቶ እንዳለ ኦሮሙማዊ ለማድረግ እኛ የበላይ እናንተ የበታች ሁኑ ነበር የትዕቢት ግብግቡ። አለፍ
አድርገን ስናስሰው ደግሞ ጸረ ኢትዮጵያዊነት የሰሜን ፖለቲካ ቅርስ ውርስ ሲነሪቲን ማድቀቅ እና ማውደም። በሁለቱ ህዝቦች
መሃከል ዘመን የማይሽረው አዲስ የበቀል ፋፍሪካ በጽናት መክፈት። እናም ተሳክቷል።
ህወሃት እንኳን በ17 ዓመት ያላሳካውን ነው ኦህዴድ የህወሃትን ማንፌስቶ በፍጥነት እና በስኬት በሦስት ዓመት ለድል
ያበቃው። የጣሊያንም ፍላጎት ከ100% በላይ አሳክቶታል ባንዳው ኦህዴድ እና አንጣፊዎቹ።
ኦነጋዊ ኦህዴኢድ ኢትዮጵያን ሰቅዞ ይዟታል። ኢትዮጵያን በውንብድን ለመምራት ህገ ወጥ ወታደራዊ ኃይል አደራጅቷል።
ጫካ ውስጥ ኦህዴድ አለ። ቤተ - መንግሥትም አለ። እንዲያውም ቤተ - መንግሥቱ የጎለበት ጫካው ነው።
ህጋዊ የሚባለውም የጸጥታ ተቋማት የዚህ ከይሲ መንፈስ አስፈጻሚ ነው። ሉዓላዊነቷ ኢትዮጵያ መደፈር ብቻ ሳይሆን
ደቋል። ኦሮሙማ የሄሮድስ መለስ ዜናዊ ዳግሚያ ተንሳኤ ቢባል የሚሻል ይሆናል።
ኢትዮጵያዊነት ይህን መሰል አደጋ ውስጥ ሆኖ ቢያንስ እኛ ከትውፊታችን አፈንግጠን ስንገኝ ማንን እያበረታታን እንደሆነ
ልብ ብንለውስ? ቅንጣቱ ይንዳል፤ ቅንጣቱ ይገነባል። ቅንጣቱ በአረም ያስውጣል፤ ቅንጣቱ ለሰብል ያበቃል። ንቅናቄያችን አሳቻ
ከሆነ ኪሳራ ይሆናል። ኪሳራችን ለድል ይበቃል።
የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌሰቶ
ትግራይ ላይ ተንጠልጥሎ አይደለም የቀረው። አንድ አይነት ናቸው ኦህዴድድም ህወሃትም። እንዲያውም ኦህዴድ ሰውር፤ የታመቀ ገመና
አለበት። አፍሪካን እጠቀልላለሁ ማለት ብቻ ሳይሆን መሰረታዊ ተግባርም እዬከወነ ይገኛል። በፍጥነት በታታሪነትም። የራሱን መከላከያ
አደራጅቷል። የክት እና የዘወትር የሽምቅ እና የከተማ ተዋጊ አደራጅቷል። ሌላው OBN እንደ ናሙና መውሰድ ይቻላል። የውጭ
ግንኙነቱ ዝግ መሆኑም ሌላ ትንታኔ ነክቶት የማያወቀው ገመና ነው።
የሆነ ሆኖ ኢትዮጵያዊነት ሲከበርም፤ ሲኮነንም ከተሳሳተው አስተምኽሮ
ወጥቶ ራስን፤ ውስጥን ማጽዳት ያስፈልጋል። ራስን፤ ውስጥን ካጸዱ እግዜሩም ይቅር ብሎ ጎዳናውን ይጠርጋል … በስተቀር ግን ያው ዳጥ ነው። በዳጥ ውስጥ መከራም አለ።
ባሉት አለመገኘትን የመሰለ የገዘፈ ሬሳ ሃሳብ የለም እና …
· መከወኛ። ሳናልክክ ውርዴታችን ዋጥ እንድርገው!
በምናዬው አሰቃቂ ሰቅጣጭ ሁኔታ
ውርዴቱ የሁሉም ነው። ክስረቱም የሁሉም ነው። አልሠራነም። ስብሰባ ትጠራለህ፤ የሚገኘው አብዛኛው ወጣቱ ነው፤ "ኢትዮጵያ ገና ያለተሰራች አገር ናት" ሰባኪን አድምጡ ትላለህ
በአደባባይ።
የተባጀው እንዲህ ነው ቁስል
እያልን፤ እርር ኩምትር እያልን። ለዚህ ድውይ መንፈስ አንጣፊዊ አሸርጋጁ ደግሞ የጉድ ነው። ስለሆነም ለጥፋቱም ሁሉም ነፍስ ተጠያቂ ነው። በተጠያቂነት ውስጥ መንግሥት፤
የፖለቲካ ድርጅቶች የሚባሉት፤ ሚዲያዎች፤ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች፤ የማንፌስቶ ቤተኞች ብቻ ሳይሆኑ ት/ቤቶች፤ ዩንቨርስቲዎች፤
ኮሌጆች በትልቁ ወላጆችም ናቸው። በወል ሲታይ
ደግሞ ማህበረሰቡ በሙሉ።
እኛ ጎረቤቶቻችን ሳይቀር
ገርፈው፤ ቀጥተው ነው ያሳደጉን። ጎረቤቶቻችን የወላጆቻችን ያህል እንፈራ ነበር ግድፈት ስንፈጽም እንዳያዩን። ልጆች
የወላጆቻቸው ብቻ ሳይሆኑ የማህበረሰቡም ልጆች ናቸው።
ትውልዱ ካለበት ያልጠራ መንፈስ ለማዳን በእኛነት ውስጥ
እኛው ስለመኖራችን መጀመሪያ እናረጋግጥ። ኢትዮጵያዊነት ምንጩና አገነባቡ ከሃሳብ በላይ ነውና። አንድ የምርምር ተቋምም ነው። ውበቱ፤ ጸዳሉ፤ አስተምህሮው ልዩ ፍጹም ልዩ ነው። ግን ሙሴ
አጣ። እንጸልይ። ድዋ እንድርግ። ቢቀናን ቢለመነን አንድዬ ….
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
09.04.2021
ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት
ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር ነው!
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ