በእልኸኝነት የኢትዮጵያ ፖለቲካ አገር አጥተን እንደ ኩርድሾቹ … ? እናት ዓለም ገናናው ሥምሽ በክብርሽ፤ በሞገስሽ ልክ ይቀጥል ይሆን?

 

 

እንኳን ወደ ከበበቡሽ ብሎግ በሰላም መጡልኝ።

 


በእልኸኝነት የኢትዮጵያ ፖለቲካ አገር አጥተን እንደ ኩርድሾቹ … ?

·      እናት ዓለም ገናናው ሥምሽ በክብርሽ፤ በሞገስሽ ልክ ይቀጥል ይሆን?

ዕለተ አርብ ማዕዶተ - ኢትዮጵያ

በከበቡሽ የቁራሽ እንጀራ ብራና

በቢሆነኝ የተብራራ ብራ

በሰብለ ህይወት አዝመራ

ለራህብ የሚመራራ።

„ዝም ብዬ የመከራን ቀን እጠብቃለሁ።“

(ትንቢተ ዕንባቆም ምዕራፍ 3 ቁጥር 17)

 

·      ብታ!

እንዴት አደራችሁ ቅን ቤተሰቦቼ?

ልዕልት ኢትዮጵያስ እንዴት አለሽልኝ ናፍቆት ዓለሜ?

·      ፍታ ለአንድ አፍታ።

 

እልኸኝነት አቅም ሲኖርህ ቢያምርም ቢከፋም ሞክረው። አቅም በሌለህ ሁኔታ በባዶ እጅ እልኽኝነት ሽንፈትን ቢደርብ እንጂ አትራፊ አይሆንም። ለነገሩ እልህ አይደለም ለብሄራዊ ጉዳይ ለሦስት ጉልቻም አይሆንም።

እልህ ከሦስት ጉልቻ ዝቅ ላለው የግል ማህበራዊ ግንኙነትም አይረዳም። ወጣት ሳይሆኑ የወጣት ባህሪን፤ ጎረምሳ ሳይሆኑ የጎረምሳን ባህሬ፤ ኮረዳ ሳይሆኑ የኮረዳን ባህሪ ሁነኝ ማለት የዕድሜ ጸጋ እና በረከትን ካለማገናዘብ የሚመነጭ ይመስለኛል። ይመስለኛል እኔ በጹሑፎቼ አዘውትራለሁኝ። ይሕ የሆነበት ምክንያት ጥናታዊ ተግባር ያልፈጸምኩበት ስለመሆኑ ለማጠዬቅ ነው።

የሆነ ሆኖ የ60/የ70/የ80 ዓመቱ ፖለቲከኛም እልኸኛ ነው። ጎረምሳም ኮረዳም ልሁን ባይ ነው። ከልጆቹ፤ ከልጅ ልጆቹ እኩል። የሚገርመው እልኸኝነቱ ያበቀለ ቢኖረው መልካም በሆነ ነበር። የተካው እሳት የላሰ ወጣት ቢኖርም ይሁን እንበለው። ግን የለም። አንዳቸውም የላቸውም።  ምክንያቱም ተተኪ ማፍራት ፕሮጀክታቸው አይደለም። የሚፈሩትም ይኽነኑ ነው።

ፕ/መራራ ጉዲና፤ ፕ/ በዬነ ጴጥሮስ፣ ዶር አረጋይ በርሄ፤ ፕ/ ብርሃኑ ነጋ፤ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፤ አቶ መርሻ ዮውሴፍ፤ አቶ እያሱ አለማዬሁ፤ አቶ ፋሲካ፤ አቶ ሌንጮ ለታ፤ ዶር ዲማ ነጉ አንድም የሚተካ ሰው አለፈሩም። ተጠሪውም፤ ወካዩም ተዋናዩም እራሳቸው ናቸው። ዘመን ከዘመን።

በሌላ ሁኔታ ብቅ ሲሉ ወጣቶች አደናውም ይኽው መተካት ሃራማቸው ስለሆነ ነው። የኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ገኖ መውጣት ከቅንጅት ፍርሰት በኋላ ለሽ ያለውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሙቀት የሰጠ በወጣቶች ያበቀለ ሰብላማ ነበር።

ግንቦታውያን አገር ከመግባታቸው በፊት አድነው ተረተሩት። አገር ሲገቡ መንፈሱን ወርሰው አከሰሙት። ኢንጂነሩ የፈጠሩት አዲስ ኢኃንም ድርጅትም በገዳ ምርጫ ቦርድ ልዕልት በወት/ ብርቲካን ሚዲቅሳ ተሰረዘ። የወጣት ሊቃናት ቀደምትነት እንደ መቅሰፈታቸው አድርገው ነው የሚያዩት።

ማህበረ ሌንጮ፤ ማህበረ ቀስተዳመና፤ ማህበረ የደቡብ ህዝቦች፤ ማህበረ ኦፌኮን፤ ማህበረ ኢህአፓ፤ ማህበረ መኢሶን የመሩት እራሳቸው ከሦስትም /// ከአራትም ///  ከስድስትም /// ከስምንትም ተሸንሽነው ትናንትም ያሉት፤ ዛሬም ያሉት እነሱው ናቸው። ያው ሰብሳቢ፤ ፕሬዚዳንት፤ ሊቀመንበር ተብለው። በ ኢህዴግ ጎራም ያው ነው። ብህወሃትም እንዲሁ።

60 ዓመት ሙሉ ኢትዮጵያን ሊረከብ የሚችል አንድም አቅም ያለው ብቁ የፖለቲካ ድርጅት የለም። ዛሬም። አፍሶ መልቀም፤ ለቅሞ ማፈሰስ፤  አዲስ  እነሱ ፈንገጥ ያለም አይፈቀድለትም።

እነሱው ሥም አያልቅም በአዲስ ሥም አሸብርቀው ብቅ ይላሉ የሳሙና አረፋ ሆኖ ኩፈፍ ብሎ ረብ ሲል እራሱ ያከሰመዋል። ዬዘመኑ ገዢወች ተጻረው ከሚንዱት በላይ ለዚህ የተፈጠሩ ፍጥረተ እፉኝቶችም አሉ። የፋፋ፤ ያደገ፤ የተመሰገነ፤ ለትውልድ የሚሆን ነገር በሽታቸው ነው። ተረባርበው ያነዱታል። አመዱን ይቀብሩታል።

ዛሬ ላለው በሁሉም ዘርፍ የዝቅታ መስመር ሳይቆረቁር፤ ሳይጸጸት፤ ይቅርታ ሳይጠዬቅበት፤ ለጠፋ ነፍስ ሁሉ ተጠያቂ ሳይሆኑ፤ አንድ ወጣት ኮትኩተው አሳድገው፤ አብቀልለው ሳያሰብሉ አረጁ። አፈጁ። 

ምን አለ እነሱ አክተሮች ናቸው አይሞቱ አይታመሙ ድምጽ አልባዋ  የኢትዮጵያ እናት ልጅ ትወልዳለች፤ ታሳድጋለች ወግ ማዕረግ በምታይበት ጊዜ ሰልበው ይወስዱታል መጨረሻው ሰኔል እና ቹቻ ሆኖ ተስፋም ትውልድም ይምክናል። ይህ ነው ፕሮጀክታቸው።

በአዲስ ሃሳብ፤ በአዲስ ቅኝት ኢትጵያ እፎይ እንድትል ፈጽሞ አይሹም። ሲበዛ ቀናተኞች፤ ሲበዛም አድመኞች ናቸው። የሰለጠኑት አገሮች ስልጣኔ መሰረቱን እያዩ በሰለጠነው አገር ተቀምጠው ለኢትዮጵያ ይህ ዕድል እንዳይሆን መሰናክሉ እነሱው ናቸው። ዘመቻቸው የሃሳብ ዲታን መጥለፍ፤ ጠልፎ ማጫጫት ወይ አሳዶ ማምከን።

ካለምንም የትርፍ ጉዞ በባዶ እጅ በወጣቶች ዘመን ደግሞ እልህን ሰንቆ በተለመደው ሽክርክሪት ዬኢትዮጵያ ወጣቶች በዕድሚያቸው የፖለቲካ ተሳትፎ ሊያድርጉበት የሚችሉትን መስመር ከርችሞ ዛሬም እንደ ትናንቱ ያዙኝ ልቀቁኝ ዕለት ተለት የምናዬው ትውና ነው።

ለኢትዮጵያም የምጽዓት ቀኗ ናቸው። ሱሰኞቹ የቀደሙት ፖለቲከኞች ኢትዮጵያ ጠላታቸው ትሁን ጣውንታቸው፤ ጣውንታቸው ትሁን ጎባናቸው አይታወቅም። መፍትሄው የእነሱ ከመድረኩ መገለል ሆኖ ሳለ በመጥፋቷ እዬተሳለቁ ሌላ አጥፊ አገር ጨምረው እንሆ በበቀል፤ በበታችኝነት ስሜት አራሷት፤ አመሷት፤ ቆሏት፤ አንገረገቧት። አቆሰሏትም። ጠፍታ ብን ብትልላቸው ምን ሊጠቀሙ እንደሚችሉ አይታወቅም።

·       ወጣቶቹ ዘመናቸው ነው። ዘመናቸው ሊዘረፍ አይገባም!

ወጣቶች በዘመናቸው የራሳቸውን ዕድል እራሳቸው እንዲወስኑ ለወጣቶች መልቀቅ ያሰፈልጋል። ከፊት ለፊት አንድ ወጣት ብቅ ይደረግ እና በኋላ በስተጀርባ አዛውንታት ያማስሉታል። እንዲህ ፖለቲካውን በእልህ፤ በማን አለብኝነት፤ በማናኽሎኝነት ሲያነኩሩት ማዬት አገር ምን እሾህ ስታበቅይ ብቻ ትባጂ ይሆን ያሰኛል።

ወጣትነት እንኳንስ በዕወቀት ፋፍቶ ቀርቶ ባይሆንም የአቅም አርኬቡ ነው። ወጣትነት ጤናም ነው። ፈለጠኝ ቆረጠኝ የማይባልበት፤ ደከመኝ ሰለቸኝ የማይባልበት የኃይል ፏፏቴ ነው።

ኢትዮጵያ በጸጋዋ እንዳትጠቀም ንጹሕ ዲስክርምኔሽን ተፈጽሞባታል ብዬ አስባለሁኝ። ትናንት በእነ አቦይ ስብኃት፤ በእነ አቶ በረከት ስምኦን፤ ዛሬ በእነ አቶ አባ ዱላ ገመዳ። ለሳቸው አልጋ በሚያነጥፈው ግንቦት 7 እና በማህበረ ሌንጮ። 

አዛውንት ፖለቲከኞች ዘመናቸውን በመልካም ነገር ሰርተውት፤ አበጅተውት ቢሆን ኖሮ ዛሬ ከዛው በክፋት፤ በምቀኝነት፤ በደም ከተጨማለቀ የኢህአዴግ ጉራጅ ሥር ወድቀው ፍርፋሪ ሥልጣን፤ ብጥቅጣቂ ተቀባይነት ሲለቅሙ ውለው ባለደሩ ነበር።

አዲስ አበባን አንረከብም ብለው 15 ዓመት ከነደደ፤ ስንት ወጣት ከተገበረ በኋላም ባዶ እጃቸውን እዬተንከወከዉ ገብተው አሁን ልመና ላይ ናቸው። የሚገርመው በህይወታቸው አንድም የሚተካ ሰው ለማፍረት አለመቻላቸው ነው። ምድረ በዳ። የነጠፉ!

ባዶነትን ሰንቀው እነሱ አክተርነት ሲዘባበኑኑ፤ መድረክ ለመድረክ፤ ማይክ ለማይክ፤ አዳራሽ ለአዳራሽ ሲያሽቃብጡ ባጅተው ዛሬም እነሱው ደግሞ ምረጡን ብለው ከቸች ብለዋል። ከጉራጁ ኢህዴግ የሥልጣን ተጠማኝም ሆነዋል።

በሌላ በኩል ኦህዴድ መራሹ ጉራጁ ኢህዴግም በቅቶታል። ኤክስፓዬርድ አድርጓል። የተቃጠለ ካርቦን ነው። ዕድገቱን የጨረሰ መንጋጋ አያድግም፤ አይጎረምስም፤ ልደግ፤ ልጎርምስ ቢልም የገረዘዘ ስለሆነ አይቻለውም።

 ተፈጥሮን መመለስ ስለማይችል አርጧል። 1983 ተመልሶ አይመጣም። ኢህዴግን መሥራቾችም ያው የ60ወቹ ናቸው። ዛሬም ያሉት እነሱው ናቸው።

ከዛ ትውልድ የተረፈው ኢትዮጵያን በቀደመው መክሊቷ ልክ ሊፈወስ የሚችል አንዳችም ነገር የለም። ዴሞክራሲ መርኃችን ነው ይላሉ።

 አይደለም ለህዝብ በራሳቸው ውስጥ ዴሞክራሲ ስለሌለ ነው ሲፈርሱ - ሲሰሩ፤ ሲፈረካከሱ - ሲሰነጣጠቁ፤ ሲንገዳገዱ፤ ሲወነጃጀሉ፤ ሲደለዙ ሲለጣጠፉ ዘመንም ወቅትም እንዲህ ጥሏቸው ሲነጎድ ግራጫም ሳይሆን አልፎ ተርፎ ልክ እንደ ወጣቶች በእልህ ተወጥረው ሲያምሱት፤ ሲያተራምሱት እምናዬው ፖለቲካውን።

ኢትዮጵያ ዕዳዋ እንሱው ናቸው። በግለሰብ ደረጃ መልካምነትን የሰነቁ ሊኖሩ ቢችሉም የበቀለ ሃሳብ፤ የፋፋ ሃሳብ እንደ አቶ ልደቱ አያሌው ማብቀል ካልተቻለ ተያይዞዞ ሞክ ነው።

የሚገርመው አዲስ ሃሳብ ለዬዘመኑ ይዘው የሚቀርቡት አቶ ልደቱ አያሌው መፍትሄውንም፤ የችግሩንም መውጫ በር ሰርተው አበጅተው ነው የሚቀርቡት። እሳቸውን እንኳን ኢትዮጵያ ጠቀም ለማድረግ የምናዬው ነው።

ወጣትነታቸውን ገብረው የመሰረቱትን ድርጅት እሱም አስቀንቷቸው ሲነሪቲ ያለው ኢዴፓ እሱንም አፍልሰው ሞታቸው ታጭቶ በፈቀደ እግዚብሔር አሻምነት ነፍሳቸው አለች።

እንደ ሥርጉተ ሥላሴ ዕይታ ልደቱን መማር፤ ልደቱን ማጥናት፤ በልደቱ ላይ ምርምር መሥራት ትውልድን ዘመን ከዘመን ሊተክል የሚችል ክህሎተ ጎዳና ይመስለኛል። ፍጽምና ከሰው አይጠበቅም። ነገር ግን ለምክክር የሚያቀርቡት ዘመን የመጠነ ሃሳብ በኢትዮጵያ ፖለቲካ እጬጌ ያሰኛቸዋል በእኔ ዕይታ እና ግምገማ።

እኔም በጋሜ እና በቁንጮዬ ስለሆነ ፖለቲካን አህዱ ያልኩት፤ የኖርኩበትም። ሃሳብ አፍላቂነት ብቻ ሳይሆን ያፈለቁት ሃሳብ በሳልነት እና ዘመን ተርጓሚነት የዘመን አናባቢ ቫወልም ልላቸው እደፈራለሁ።

ሳንረዳቸው የተቃጠለው ዘመንም ያሳዝነኛል። ይቆጨኛልም። ደግፈናቸው፤ ረድተናቸው ቢሆን ኖሮ ዛሬ የማህበረ - ኦነግ መጨፈሪያ ኢትዮጵያ ባልሆነች ነበር። አሁንም ብቅ የሚሉ መልካም የሆኑ ያልባለቁ ወጣቶች ሲመጡ አቅም ልንመግባቸው፤ ልንከባከባቸው ይገባል። 

ህወሃት እራሱ ሳይጠዘጥዘው አይቀርም ብዬም አስባለሁኝ በነገረ ልደቱ፤ እና በነገረ አቶ ይልቃል። ካፈርኩ አይመልሰኝ መሆኑን ብረዳም።

ከውድቀቱ ለመማር የማይችል መሆኑን ባውቅም። መታብይ እና እልኽ እንዲህ እንኩትኩት አድርጎት በስተርጅና ካብ ለካብ እዬዳህ ዲታ አገሮችን ተማምኖ መፎግላቱን ሳይ አለመታደሉን የበለጠ አያለሁኝ።

ለመማር ዝግነቱንም አስተውላለሁ። አዛውንት ፖለቲከኞች አብዛኞቹ ትናንትም የነጠፈባቸው ናቸው - ዛሬም። ተው የሚል የለም። በአልኽ መንጎድ ብቻ።

ጥሞና አይውቅም ድርጀቱ ሁሉ። ያበዱም አያለሁኝ የሌላ አገር ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማ አቃጥሉ የሚሉ፤ አሜሪካ ትጠፋለች የሚሉ። ይልቅ የ ኦዳ ቤተ መንግሥት ማህበረ ዕብዳውያንን የሚፈውስበት ጠበል ቢጤ ቢያበጅ መልካም ነው የፓርክ ትርኢት ከሚያሳዬን።

የሆነ ሆኖ የአቶ ልደቱ አያሌው በህይወት መኖር አጀንዳው ከሆኑት ሰብዕናወች አንዷ ስለሆንኩኝ በድንግል እርዳታ ህልውናቸው መቀጠሉ አስድሰቶኛል። አቶ ልደቱ አያሌውን አይደለም ግለሰብ ኢትዮጵያ እራሷ ይቅርታ ልትጠይቃቸው የሚገባ ልጅ ቢኖሯት አቶ ልደቱ አያሌው ናቸው። በጣም ተገፍተዋል። በጣም ተገለዋልም።

… ግን ጆሮ የለውም የኢትዮጵያ ፖለቲካ። መጸጸትም ሃራሙ ነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ። ምህረት መጠዬቅም እንደ ውርዴት ያዬዋል የኢትዮጵያ ፖለቲካ።

ይቅርታ መጠዬቅም ነውሩ ነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ። በሳቸው ሦስተኛ አማራጭ ነፍሱ የሰነበተችው፤ ከውርዴት የዳነው ሁሉ ሃሳቡን ዘርፎ እዬኖረበት የሃሳቡ ፈላስፋ ደግሞ እስከ ታሪኩ እንዲጠፋ፤ አንዲፈልስ ይፈለጋል። የልደቱ ትውልድ ገና ይመጣል። ጠብቁት። 

ቀድሞ ነገር ኢትዮጵያ በውስጥ ብትጸነስ ችግሯ ይመንን ነበር። ግን የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ኢትዮጵያ ሳትሆን ጣወታቸው እራሳቸው ናቸው። በተከታዮቻቸውም ዘንድ ገነቡት የሚባል መልካም በጎ ነገር አለ ከተባለ „እኛን ጣዖት አድርጉን ነው።“ አምልኩን፤ የጸጋ ስግደት ስገዱልን ነው። ወላልቀው፤ ዘነዘናቸውን ቀርተውም ያው ምኞታቸው ጓጉሎ አገር ያተራምሳል። ፍሪንቲቶች!

ለተከታዮቻቸው ጣዖታቸው ባለስድት ክንፍ ስለሆኑ አይሳሳቱም። አይፎርሹም። ብላሽነቱ እዚህ ላይ ነው። ዛሬ በማስተውለው ልክ ብዙ ጭምት ወጣት ፖለቲከኞችን አያለሁኝ።

ወጣትነታቸውን ገፍትረው ነጥረው የወጡ ዕብደት የማይነካካቸው፤ ስካር ሽው የማይላቸው፤ ቅብጠት የማይዳዳቸው ፋክትን የሙጥኝ ያሉ፤ የሰከኑ ወጣት አንቱወችን አያለሁኝ። እምሰጥባቸው።

ኢትዮጵያ ለእነኝህ ምቹ ናት። ትመቻቸዋለች። እነሱም ይመቿታል። ሃሳባቸው፤ ትጋታቸው ዕውነት ፈላጊነታቸው እሸት ነው።

ዘመኑም የእነሱ ነው። ዘመኑም ወቅቱም የእነሱ ከሆነ አዛውንታት ፖለቲከኞች ከነስብርባሪያቸው፤ በአረም ከተዋጠው ከማርክሲስት ሌኒኒስት የኢንትሪግ ቡተቶ ፍልስፍናቸው ጋር ከኢትዮጵያ እራስ ቢወርዱ እና ለወጣቶቹ ሁሉን ነገር ቢያስረክቡ ኢትዮጵያ ትፈወስ ነበር።

መዳኛ መንገዷ ያ ብቻ ነው። ቀደምት ፖለቲከኞች ለአማካሪነት እንኳን አይበቁም።

ሁለንታዊው ፓለቲካውን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ውጭ ጉዳዩን አቶ ሌንጮ ባቲ የኦዳገዳን ቤተ - መንግሥት አማከሩ ይኸው ታዬ ትጠጣ ቀን ከሌት ኢትዮጵያ ደም እና ውርዴት ሆነ ነገር አለሙ ሁሉ። ጨርሰዋል። አልቀዋል።

አለኝ የሚሉት ምንም ነገር የለም። መክነዋል። አርጠዋል። ወጣትነትን፤ ጎረምሳነትን የሙጥኝ ቢሉትም ካለልኩ የተሰፋ እጀ ጠባብ ሆኖ ተንቦራቅቆ አገር አከሰለ።

ለአዛውንታት ፖለቲከኞች „ዴሞክራሲ“ ማሳቲካቸው ነው። ጡጧቸው ነው። ህይወቱን ኑረውበት ግን አያውቁትም። አቅም አለ ከተባለ፤ ተደማጭ ሆነ ከተባለ፤ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆነ ከተባለ ይወረሳል፤ ይዋጣል፤ ይወረራል።

ይህም ባልከፋ ጭነት መጫን ፍልስፍናቸው መሆኑ ነው የሚገርመው። በአድማ ማሳደድ። ባድማ ማሸማቀቅ። በአድማ ሰላም መንሳት። አቅል አደብ ብሎ ነገር አልፈጠረላቸውም። ጆሯቸው የተሠራው ለምስል ብቻ ነው። አልኖሩበትም ጆሯማ ሆነው። 

አሁን ያለው ጭምት ወጣት ደግሞ ይህን የሚቀበል አይደለም። በሸኘነው ወራት ያዬነው የአማራ ህዝብ የበቃኝ አብዮት ያሳዬው ይኸው ነው።

በቃኝ ያለው አትራፊ ያልሆነው አገዛዝ፤ ድቀታሙን ሥርዓት፤ የሴራ ቸረቸራን ፖለቲከኞች እና ዥንጉርጉሩን አክተርነታቸውንም ጭምር ነው።

ከበቃኝ በላይ የሚታከል፤ የሚጨመር ወይንም የሚቀነስ ምንም የለም። ውኃ ከሞላ ብርጭቆ ላይ እስኪ ውኃ ወይንም ጠላ እሞላለሁ ብላችሁ ሞክሩት። ይፈሳል። አሁን ያለውን የምርጫ ዳንኪራ እማዬው እንዲህ ነው።

·       ምረጡም አትምረጡም ልል አልችልም። በዚህ ላይም የመሥራት ፍላጎቱ የለኝም። ግን ዕውነት አለ።

ህልውና ሳይኖር ምርጫ ቅልጣንም ዘመናይነትም ነው።

·       ለመጠለያ ድንኳን ያጣ ማህበረሰብ ምርጫ?

·       ጫካ ለምትወልድ እናት ምርጫ?

·       ጽንስዋ ወጥቶ ታቀፊ ልምትባል እናት ምርጫ?

·       ለአፍ መሻሪያ እህል ውሃ ያለበቃ ነፍስ ምርጫ?

·       አንዲት ትንሽ ብረት ምጣድ ቆሎ ለመቶወች ጭብጡ ሽሚያ እያለ ምርጫ?

ለማን ሲባል? መነሻውም መድረሻውም ለማይታወቀው ለአሳቸው የአብይዝምን ቅቡሉነት ጨርሻነት፤ ደምሳሽነት ሲባል።

·       ለሞት ውድድር ምርጫ?

·       ለስጋት ውድድር ምርጫ?

·       ለሽብር ሽሚያ ምርጫ?

·       ለመጥፋት መለፍለስ ምርጫ?

„ቤተ - ክርስትያንም መስጊዲም ገና ይፍርሳሉ፤ ሞቱም ይቀጥላል“ ለሚል አውሬ መንፈስ ሲባል … ቅቡልነት ሲባል ምርጫ? ምርጫ በለው ዴሞክራሲ መኖርን ማኖር ሲቻል ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ መኖርም የመኖር አኗኗሪ ተፈጥሮም ተዘርፏል። ተሰፋም መክኗል። ግራጫማው ዘመን መርኽ አለው ከተባለ ሞት እና ሰኔል እና ቹቻ በገፍ በጅምላ እና በችርቻሮ መሸለም ነው።

ቀን የወጣላቸው ናቸው ሰኔል እና ቹቻንም የሚያገኙት። በግሪደር ታርሶ የሰው ልጅ የሚቀበርባት አገር እዬመራሁልህ ነውና ምረጡኝ ጲላጦስነት፤ ፈርዖንነት፤ ሄሮድስነት ነው። ጭካኔውም አረመኔነቱም ሚዛናዊ ልክ የለውም። ዕውነት አለ ያልኩት ይህን ነው።

ስለዚህም ነው ነው እኔ በምርጫ ጉዳይ እጅግ በበዛ ሁኔታ ቁጥብ የሆንኩት። ነፍስ ከአለ የመኖር ዋስትና አውላላ ሜዳ ኤሉሄ እያለች፤ ስውር የተደራጀ ገዳይ ቡድን በመንግሥት ተደራጅቶ እዬጠበቀ፤ ገጀራ በገፍ እዬተሸመተ ኮሮጆ ጋር ግብግብ ሰው መሆኔን ይፈትነዋል። ስለዚህም የለሁበትም። ይመረጠም አይመረጥም ከሚሉት ወገን አይደለሁም።

ጥሞናዊ ሰብዕናዬ ለሁለቱም ሂደት አይሆንም እና።

·       ኢትዮጵያ እንዴት መሽቶ ነጋላት ነው አጀንዳዬ።

·       በሰው እጅ ያሉ እስረኞች እንደምን አደሩ ይሆን ነው ህሊናዊ ጉዳዬ።

·        ከተሞች እንዴት ይሆኑ ይሆን ነው ሩሄ እምትባትልበት፤

·       ብጹዓን አቨው እና ምህበረ ምዕመናን እንደምን መሽቶ ነጋላቸው ነው የእኔ ጭንቀት እና ጥበት?

·       እናት አጥቶ  አባት ያለው፤ አባት አጥቶ እናት ካለው ይልቅ ምንም አባትም እናትም የሌላቸው ልጆቼ ይበልጡብኛል።

·       እናትም፤ አባትም አጥተው ዘመድ ካላቸው ደግሞ ምንም እናትም አባትም፤ ዘመድም የሌላቸው ልጆቼ ይበልጡብኛል።

·       እናትም አባትም ዘመድም የሌላቸው ግን መጠለያ ካላቸው ይልቅ እናትም፤ አባትም፤ ዘመድም አጥተው መጠለያ ያለገኙት ዱር ገደል ብቻቸውም የሚከላተሙት ልጆቼ ይበልጡብኛል። ለጅብ የተሰጡት።

መከራው እንዲህ በአግባቡ ሊታይም ሊያዝም ይገባዋል። በዚህ ውስጥ ትውልድ እዬረራ፤ እንዲህም እዬመከነ ስለምርጫ ገሃነም ይመስለኛል ሃሳቡ እራሱ።

ሌላው ሴራው እና ሸፍጡ ደግሞ ፍንትው ብሎ ስለሚታዬኝ ከፈጣሪ ጋር በጥሞና መነጋገሩ እሸታዊ ጎዳና ይመስለኛል። አሁን ያለው ዘመን የልጆች ግብር የሚከፈልበት፤ ፆታው ያልታወቅ ሰይጣኒዝም ነው።

ፏፏቴ የዲስኩር አቅም እና ኃይል ለአሳችው ጠቅላይ ሚነስተር አብይ አህመድ አሊ ቸርቻሪው ይኸው ክፉ መንፈስ ነው። ቅርቤ  ለእኔ ይህን ክፉ መንፈስ ፈጣሪ በረቂቅ ስልጣኑ እንዲያስወግድ መለመን ነው።

የተሰወረባቸው ተገልጦላቸው አቅም ማዋጣተቸውን ተግ እንዲያደርጉት ፈጣሪ ማስተዋሉን እንዲሰጣቸው መማጠን ነው።

ዘመኑም አሁን ያልንበት ወቅትም የገባው የለም። ትልልፍ ነው እማዬው። ነገ ከዛሬው እጅግ የከፋ እና የከረፋ ሆኖ ይታዬኛል እና። በኢትዮጵያ ቅርፊት እንጂ ዕውነተኛ ሃይማኖት ለወደፊት ይኖራል ብዬ አላምንም ከ20/30 ዓመት በኋላ። ይህ የጨለማው የፒኮክ ንጉሥ ግራጫማ ዘመንን በኃይለ ሥልጣኑ በእዮር ካልተወገደ በስተቀር።

የዶር አብይ አህመድ ደረታቸው ላይ ያጎጠጎጠው ጉድ ሁሉ ያስፈራኛል። ዕይታቸው ከተባዕት ጋር የሚያደርጉት መሳለቅ እና ማሽካካት ሁሉ በዝምታ እማልፈው ጉዳይ አይደለም።

ፎቷቸውን በዝግታ በጥሞና ነው ውስጡ እማነበው። ኢትዮጵያ ምን መንፈስ እዬመጣበት ይሆን?! ይህ እንጂ የኮረጆ ቁጥር ለአሳቻዋ የገዳ ልዕልት ለወ/ት ብርቱካን ሚዲቅሳ ዝክር ይሁንላቸው።

ምኞታቸውን በልካቸው አግኝተዋል በበቀል ኩትኩት በሰመመን ፍቅር ይፍነሽነሹ። ጠያፍ ነገሮች በእርኩሰት እዬዘነበ ነው በምድሪቱ ላይ። ጎግማንጉዝ ዘመን።     

·       ዕውነት ለመናገር ኢትዮጵያም የአርምሞ ጊዜዋ ስለሆነ በቃኝ ብላለች። ምልክት ይታያል!

ዛሬ የተፉትን ከመላስ፤ የወደቀውን አጥንት መልሶ ከመጋጋጥ ውጪ ምንም ተስፋ ሰጪ ነገር አልታዬም። ሲፎክር፤ ሲፎገላ፤ ሲፈላ እና ሲበርድ የሰነባባተው ግንቦት 7 መራሹ ኦህዴድ አሁን አዲስ ሉዑክ ወደ አገረ አሜሪካ እንደሚልክ እዬተደመጠ ነው።

በአንባሳደር ተቀዳ አለሙ። ይህን ኢትዮ ፎረምም ድንኳን ጥሎ ስለ መሪው ጭንቀት ላይ ባለውም ተተራ ሚዲያ ኔት ጭምጭማታ ሲል ጠቅሶታል።

·       መጥኖ በልክ መኖር።

·        መጥኖ በልክ አቅምን ማስተዳደር ብቻ ሳይሆን፤

·        መጥኖ ገርጭራጫማነቱን ሆነ ቱማታበቱማታ ባህሪያት ሁሉ በቅጥ ማስተዳደር ይጠይቃል።

·       አገር ማስተዳደር የሆሆ ምሻምሾ ሁነት አይደለም።

·       አገር የዕለታዊ ዳንኪራ አይደለችም።

·       አገር ዳንቴል አይደለችም። 

ስክነት ቀርቶ እብደቱም ልክ በኖረው። ያለው መፎግላት፤ እልኸኝነት ብቻ።

 „በህዝባዊ ትዕይንት አሜሪካ አታስፈልገነንም፤ ሩስያ፤ ቻይና ቱሪክ ኑሉን!“ በአደባባይ ያለ የድንፋታ እልኃዊ የሳሙና አረፋ አሁን ደግሞ አሜሪካ ሆይ! ባጠፋሁ ማሪኝ ዓይነት ይመስላል ጉዞውን ወደ ዛው ሊያቃና ይባላል።

ይማጠን እስኪ … ሰንደቁ እኮ በመኪና ሲጎተት ሁሉ ታይቷል። ማህበረ ኦነግ አገር የመምራት አቅሙ ብቻ ሳይሆን ቅባውም የለውም። አድሮ ጥጃ ነውና። አገር ለመምራት በራስ የመተማመን አቅምህ በልኩ ሊሆን ይገባል። ከእኔ ወጥተህ የእኛ ላይ መስከን ይጠይቃል። አቅም የለውም የኦሮሞ ፖለቲካ።

·       ውስ ጠማኙ ሽብር ተጠማኙ ኦህዲዳዊው አስተዳደር።

ቀድሞ ነገር 100% ተመረጥኩ ባለው የኢህአዴግ ጉባኤ ላይ ነበር ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ የተመረጡት። በመጀሪያው በምክር ቤቱ በግርባው ብአዴን ሙሉ ድመጽ ተመረጡ።

በኋላም በአዋሳ ጉባኤ ጸደቀለት። ይህን ገልብጦ፤ አፈራርሶ፤ መሬት ደብድቦ ጦርነት ለምኖ እና ተበድሮ ሃይልና ግድያ፤ እልህ እና ትዕቢት በኢትዮጵያ ፖለቲካ አልበቃ ብሎ አልፎ ተርፎ „ጎርምሳ አገር፤ የአሜሪካን ብሄራዊ ሰንደቁን አቃጥሉ፤ ልጆቻችን እናስታጥቃለን፤ የነቀዘ ስንዴ አንሻም፤ ባንዳ እና ባዳ“ ይህ ሁሉ ኳኳቴ ለኢትዮጵያዊው ሰው ተፈጥሮ የተገባ አልነበረም።

ግን ኢትዮጵያን ለማያውቃት ዛሬኛ ከምን ያመጠዋል?

·       ኢትዮጵያ ልክ አላት።

·       ኢትዮጵያ የተፈጠረችበትም፤ የኖረችበትም በልክ ነው።

·       ኢትዮጵያ እልኽኛ አይደለችም።

·       ኢትዮጵያ በታሪኳ ስትደፈር ከመከላከል ውጭ የትኛውንም አገር ደንበራ ጥሳ ተዳፍራ አታውቅም።

·       ኢትዮጵያ ቁጥብ ናት።

·       ጭምትም!

·       ኢትዮጵያ የምትታበይም አይደለችም።

·       ኢትዮጵያ ጋብቻዋ ፈት አይደለም። ኢትዮጵያ ጋብቻዋ ከፈርኃ እግዚአብሔር እና ፈርኃ አላህ ቃል ጋር ነው። ኢትዮጵያ ተራጋጭም ገረጭራጫም አገር አይደለችም።

·       ኢትዮጵያ ብስጩም አኩራፊም አገር አይደለችም።

·        ኢትዮጵያዊነት ስክነት ነበር በቀደመው ዘመን።

·       ኢትዮጵያ ከኦሪት በፊትም በህገ - ልቦና አምላኳን አውቃ ያደረች አገር ናት። ለዛ ነው የጥበብ ምድር የሆነችው። ለዛ ነው የአውሮፓ ሥልጣኔ እንብርት የሆነችው። ይህን ታሪክን ማንበብ ነው። የካህን አገርነቷ ከእሷ አልፎ አውሮፓን አንቱ አሳኝቷል። እነሱም አይክዱትም።

የጥበብ ምድርነቷን የሚያፈሱት፤ የናቁት፤ የረገጡት፤ የጠቀጠቁት የነፈሰባቸው ውራጅ አምላኪ ካህዲ ልጆቿ እንጂ እሷ የፍቅራዊነት ልዕልት ናት።

·       ለሁሉም እኩል የሆነች።

·       ሁሉንም አጥግባ ማደር የምትችል። ግን መሪ ሙሴ አላገኜችም። ይህ ቆጥቁጦት ጥቃቷን ለማውጣት ቀና ልቦና ንጹሕ ልብ ያለው አልተፈጠረም ማለት ባልችልም ግን ዕድሉና ቀኑ አልተገናኝም ብል የሚሻል ይመስለኛል።

ኢትዮጵያ የራሷ የእኔ የምትለው ዘመን - ጠገብ ትውፊት፤ ዘመን - ጠገብ ትሩፋት፤ ዘመን ጠገብ የተባ ታሪክ፤ ዘመን ጠገብ መክሊት፤ ዘመን ጠገብ ፈርኃ እግዚአብሔራዊነት አላኃዊነት፤ ዘመን ጠገብ ሥልጣኔ፤ ዘመን ጠገብ የዴፕሎማሲ አያያዝ እና አመራር አላት።

ልትዋስ እምትሻው ዘመኑ የፈቀዱ ነገሮች ቢኖርም የአገረ ምሥርታ ታሪኳ እና ሁነቱ አንቱ ነው። ዓራት ዓይናማ ነው። የምንከብርበት እንጂ አንገት የምንደፋበት አልነበረም። አሁንም መዳኛው ይኸው ነው። መስመሩን የሳተ ባቡር አወዳደቃችን እንዲህ አንኮተው።

·       ሚገርመው።

ያን አንድዶ በአንድ ያበደ የህሊና የእማጅኔሽን ዳንቴል ስካር እና እልህ እና መታበይ ከበፊቱም በከፋ ሁኔታ፤ በባሰ ሁኔታ፤ በጠነዘለ ሁኔታ፤ በወዬበ ሁኔታ እንሆ ድብልቅልቅም፤ ዝንቅንቅም፤ ዝርክርክም፤ ዝልግልግም፤ዝብርቅርቅም ተሆነ።

መካሪ አልባ መወደቅ ብቻ ሳይሆን አወዳደቁ የከፋ ሆነ። ስለምን? እልኽ መራሹ የየቤተ - መንግሥት መራራ አስተዳደር እና አማካሪው ልኩን ያለወቀ፤ ያበጠ፤ የተለጠጠ ግን ጥፍጥፍ ስለሆነ።

ባዕዳዊነት ይማርከዋል ከራስ ነገርነት። የብርቅርቅ ሰው ሰራሽ ብልጭ ድርግም አርቲፊሻላዊ ሃይቅ ኩነት በፍቅር ጥሎታል።

ኢትዮጵያን የማያውቃት፤ ሊያውቃትም የማይሻ፤ ቢውቃትም የሚቀናባት መሪ ሲገጥማት ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ባይሆንም ይህ የአሁኑ ዘመን ግን ጠረኑ ባዕዳዊ መንፈሱ ግራጫማ ነው። አሳቻ ነው። እራሱን የቻለ የምርምር ማዕከል ያስፈልገዋል። በጉዞው ሁሉ ኢትዮጵያዊ ጠረን፤ እዬራዊ ፈቃድ የለበትም። መከራው ዝልቅ ማቱም ጥልቅ ነው።  

በሌላ በኩል ቀደም ባለው ጊዜ የገዙ፤ የነዱ የረገጡት ነባሩ የአድዋ ሥርዕወ መንግሥት ሹመኞች ደግሞ ዴሞክራሲ በሚሉት ቋንቋ ቁጭ ብለው ድምጽ ሰጥተው የመረጡትን የራሳቸውን የእንግዲህ ልጅ ኦነጋዊውን ኦህዴድ በዛ ሥር ሆናችሁ ተዳደሩ ሲባሉ ደግሞ ወገቤን ሆነ። በራሳቸው ማንፌሰቶ መንፈስ በጸደቀው ህገ - መንግስታቸው መተዳደር ተሳናቸው።

እልኽ፤ መታበይ፤ ዘወትር መስቃ፤ ዘወትር የሰራዊት ትርኢት፤ ዘወትር ፉክክር፤ ዘወትር እራስን ከፍክፍ ማድረግ ሆነ። ከፍ ብላችሁ ግዙ … ንዱ … ሲባሉ ያን ያህል ጥጋብ እና የከበሮ ድልቂያ ታዬ፤ በቃኝ  እንያችሁ ተባሉ። ተጠግነን እንቀጥልም ሲሉም እሺ ከተማራችሁ ተባሉ። አልቻሉም። ዝቅ ብሎ ለመኖር አልተቻላቸውም። እናም አልገዛም አሉ።

አዲሱ የገዳኦዳ ሥርዕወ መንግሥት ደግሞ ገዢ ነኝ እገዛሃለሁ ትገብራለህ፤ የሞጋሳ ልጅነትህን ተቀበል አለ። በዚህ ማህል አገር ታመሰች።

አስታራቂ አዛውንት ብቻ ሳይሆን አድማጭም ፖለቲከኛ ጠፋ። ሴራው፤ አድማው፤ ሸፍጡ ሁሉም ታደሙ። እንሆ ሁለቱም የአዳማው ሥርዕወ መንግሥትም የአድዋው ሥርዕወ መንግሥትም ከትቢታቸው ተራራ ላይ ሆነው ኢትዮጵያን አነደዷት። ህዝቡም ተሰቃዬ። ፍዳውን አዬ።

ከሁሉም የሚከፋው ዕውነት የት ላይ እንደሆን ለማወቅ እራሱን የቻለ ዘመን ማስፈለጉ ነው።

ዝም እንዳይባል መረጃ ነው ይሠራበታል። ቆይቶ ደግሞ ይስተባበላል። ይህ ሁሉ ቀልድ፤ ይህ ሁሉ ዳንኪራ፤ ይህ ሁሉ መከራ ተበጅታ በቆዬች፤ በነበረች አገር ነው። ሱዳንም፤ ሱማሌም፤ ጣሊያንም፤ እግሊዝም፤ ፖርቹጋሎችም፤ ቱርኮችም በዬዘመኑ ተሳክቶላቸው ገዝተው ቢሆን ኖሮ ይህ ሁሉ ዘመናይነት ባልታዬ ነበር።

እነሱ የ60ወቹ ከመፈጠራቸው በፊት ነበር ኢትዮጵያ የተሠራቸው። እንኳንስ እነሱ ቅደመ አያታቸው እንኳን አልተፈጠሩም ኢትዮጵያ ስትፈጠር። የዛሬዋ ገናና አገር አሜሪካም አልተፈጠረችም ኢትዮጵያ ገናና መንግሥት በነበራት ወቅት። በ60 ዓመት ውስጥ ግን የነበራትን ሁሉ ጨርሰው፤ አራግፈው አዲስ የወደቀች፤ የተሰለቀች፤ አንገቷን የደፋች ኢትዮጵያን እንኳን ለዘመኑ ወጣቶች ለማስረከብ ፈቃደኞች አይደሉም። የሚያሳዝነው ይኸው ነው።

ሁሎችም ከአንድ ወንዝ የተቀዱ ናቸው። ሁሎችም እናታቸውም አባታቸውም አንድ ነው። ማርክሲስት ሌኒኒስት ቲወሪ።

ወደ ኢትዮጵያ ሲተረጎም የበቀለ የሚነቅል፤ አዲስ ሃሳብ የማያስተናግድ፤ አቅም የለሽ፤ በዘረፋ፤ በማሳደድ፤ በአድመኝነት፤ ሰላም በመንሳት የተመረቀ፤ በቅናት የሰከረ፤ አሁን ያለው ግሎባላይዜሽን የተሻለ ዘመን ላይ ስለመሆኑ የማያምን የኩሬ ውሃ። አድሮ ጥጃ። ዘመንም የማያስተምረው። 

ዓለምን የሚመራት የላቀ፤ የበለጠ፤ የበረታ፤ የዳበረ ሃስብ ነው። ይህ ያቅረዋል የ60ው ፖለቲከኛ /// ፖለቲካም። ኢትዮጵያ የራሷ አላት። የእኔ የምትለው የራስ ነገር አላት። አገር መምራት የሚስችል የቀደመ የጥበብ ዘር አላት። የምትፈወሰብት በተፈጠረችብት ልክ የሆነ ዊዝደም አላት ግን ተጣሰ።

ዕውቅና ለመስጠትም ፈቃዱ የለም። እንዲያውም ይጣጣላል። ይደሰቃል። ይናቃል። ይረጋገጣል። የሚገርመው ንቀቱም የራስ ነገር ቢኖር መልካም በሆነ ነበር።

ከአውሮፓ ከእስያ በተቀዳ ርዕዮት ነው ንቀቱም መንጠራራቱም። አሁን እማ አመድ ሆኖ ይቃጠላል ይነዳልም። ላቲንን ቋንቋን ተውሶ መታበይ ከምን ግባ ከዬት ነህ ሳይባል?

„ባዕድ እና ባዳ“ ሲሉ ጠቅላዩ አለማፋራቸው ይገረመኛል። ሃፍረት ብሎ ነገር አልሰራላቸውም። ለአማጽያን መረጃ ሲያቀብል የነበረ ነፍስ ደፍሮ ባንዳ ሲል የምላስ ቁርጥማት ከዬት ነህ ያሰኛል። ክህደት ከሳቸው ወዲያ። አንበሳን ረግጦ ፒኮክ፤ የተፈጥሮን ኩሬ ትቶ አርቲፊሻል ኩሬ ለባዕድ አምልኮ_?

የሚነደው በዬዘመኑ ኢትዮጵያን ያበጃት፤ ያደረጃት፤ በዘመኑ ገናና ከነበሩ የዓለም መንግሥታት ተርታ ደረጃ ጋር በልቅና ካሳወቃት  የዕውቀት፤ የፍልስፍና፤ የሃይማኖት፤ የምርምር፤ የቅርስ፤ የውርስ አንጡራ ጥሪት ነው።

ለወደፊት በዚህ አያያዝ ዓለም አቀፍ ውርስ እና ቅርስ፤ የትውፊት መሰረትነት አዲስ ከሚመሰረቱት አገሮችም በታች የወረደ ዕጣ ፈንታ ኢትዮጵያ ይገጥማታል። ለዛውም ከኖረች።

ቱሪዝም እኮ መሰረቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ተቀንቶበት በአርቲፊሻል ኩሬ እና በአረብ አገር የአንፖል ብሊንግ ብሊንግ እዬተንደፋደፈ ነው።

አብይዝም መንፈሱ እራሱ የደም መንፈስ ነው። አብይዝም መንፈሱ ራሱ ባዕዳዊ መንፈስ ነው። አሳቻ ያልታወቀ መንፈስ ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው።

ጤነኛውን ሰው ሁሉ መስጦ በሽተኛ አድርጓል። ለምን? ስለምን? ብሎ የሚጠይቅ የለም። ሁልጊዜ ከእኛ ጋር የነበረ ቤተሰብ ይለዬናል። እናጣዋለን። ወይ በሞት ወይ ደግሞ በምርኮኝነት። አቅማችን ይዘረፋል ከነመንፈሱ። ሙቀቱ ተስፋው አሸተ ስንለው ያጨበጨበው ቡቃያ ሲጫጫ ይታያል። ክፉው መንፈስ ይጫነዋለ።

ትኩረቱ በዕለታዊ የሞገድ ዜና ሱናሜ ብቻ ነው። በጸጸት ውስጥ መዳን አለ። አድማጭ ካገኜ። የሚጸጸት ፖለቲከኛ ቀርቶ ዛሬ የተናገረውን የሚደግም አይገኝም። መጋለብ ብቻ። እከሌ እንዲህ እከሌ እንዲህ አለ ላይ ነው ትንተናው አቅም የሚፈስለት።

·       ኢትዮጵያ አንዴት ተበጀች?

·       ኢትዮጵያ እንዴት ቆዬች?

·       ኢትዮጵያ እንደምን ባጀች?

·       ኢትዮጵያ እንደምን ከዚህ ዘመን ደረሰች?

·       ኢትዮጵያን የትኛው አቅሟ አሰነበታት?

·       ለመሰንበቷ የአቅሟ ጥሪት ምን ነበር?

·       ኢትዮጵያ እንዴት አደረች?

·       ኢትዮጵያ እንዴት ትዋል?

·       ኢትዮጵያ እንደምን ዋለች?

·       እትዮጵያ እንዴት ትደር??

·       ኢትዮጵያም እንደምን ትሰንብት?

·       የኢትዮጵያ ህመም፤ ድካም ምንጩ ምንድን ነው? መፍትሄውስ?

·       ከእኔ ምን ይጠበቃል?

·       ይህ አይደለም አጀንዳው የኢትዮጵያ ፖለቲካ። አቶ እከሌ እንዲህ አለ፤ አቶ እከሌ እንዲህ ያለው እንዲህ ለማለቱ ነው። በቃ በዚህ መሽቶ ይነጋል - ነግቶ ይመሻል። አገር ገደል አፋፍ ላይ ተቀምጣ። ቅደም ተከተል የለም።

ከመቼውም ጊዜ በላይ ኢትዮጵያ ልትጠና፤ ልትታወቅ፤ ምርምር ሊካሄድባት የሚገባ ጊዜ አሁን ነበር። ጦርነቱ አጨናገፋቸው እንጂ ኮ / ብንያም ተወልደ የቀድሞው የኢንሳ ምክትል ዳሪክተር ቁልፉን አግኝተውት ነበር ብዬ አስባለሁኝ። ከአውሎ ሚዲያ ጋር ያደረጉት 6 ክፍል ውይይታቸውን በጥሞና ስከታታል የተቃጠለው ጊዜ ቆርቆሯቸው ነበር።

በተለይ መታሰራቸው ወደ ቀልባቸው መልሷቸው ነበር ብዬ አስባለሁኝ። እሳቸው በሰጡት ገለጻ ሰው አልተሠራበትም ብለውናል። ሰው አልተበጀበትም ብለውናል።

ኢንሳን ስንሰራ የሌላ አካባቢ ሰወችን ብንቀይጥበትም በትግራይ መንፈስ ነበር አሉን። ኢትዮጵያ በዚህ ውስጥ ደረጃዋ ተስቷል። ህብራዊነት መንፈስ ነው ኢትዮጵያን ሊፈውስ የሚችለው የነበረው። ይህን የመጫን ምክንያታዊ ሁኔታ ትውልዱን ማብቀል አልቻለም። አምሳያውን ጉልበታም አራዊት ፈጠረ እንጂ።  

ያ ግን ትክክል እንዳልሆነ ነበር የገለጹት ኮነሬል ብንያም ተወልደ፤ አሁን ምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ አላወቅም። በህይወት ካሉ በቀደመው የጸጸት ጎዳና ይሄዱ ወይንም እልኽ ሰንቀው በህወሃት ውስጠት ይስመጡ አላውቅም። ብቻ ላዬው የፈቀድኩት ትልም ነበራቸው። ሰው አድርጎ ትውልድን መፍጠር።

·       ኢትዮጵያ በፉክክር አልተበጀችም።

·       ኢትዮጵያ በፈንግጪው አልተሰራችም።

·       አጤ ዮሖንስ አንገታቸውን መተማ ላይ ሲሰጡ ለፉክክር አልነበርም።

·       አጤ ቴወድሮስ መቅደላ ላይ እራሳቸውን ሲያጠፉ ለፉክክር አልነበረም። ያ ቢሆን ኖሮ ህይወታቸውን ማቆዬት ይቀድም ነበር። ግን አልነበረም።

·       ከእነሱ በላይ የሚያስቧት አገር ነበረች። አገር ስላለን ብቻ አናውቀውም። ከኩርዲሾች ጋር የሠራ፤ የኖረ አገር ማለት ምን ማለት እንደሆን ያውቀዋል።

·       አገር ነፍስ ነው። ነፍስህ የሚሰክነው አገር አለኝ ስትል ብቻ ነው። ከአገር ውጭ ቀፎነት ነው የሚኖረው። በተሠራች አገር መሸቀጡ፤ መመቀጡ ሱቅ በደረቴ መክፈቱ አይበጅም።

ያልነበረ አልነበረም። የነበረም መኖሩን በነበረውም ቢሆን በመክሊቱ በጥበቡ በጸጋ እና በረከቱ ልክ መሆን ይገባል።

ትዕቢቱም፤ እልኹም መፍረስ እና መዋራድ ብቻ ነው ያተረፈው። ኢትዮጵያን የሰራት ማስተዋል ብቻ ነው። ያስተዋሉት የሰሯትን አገር ማንድድ ከወንጀልም በላይ ኃጢያት ነው። ግፉን እዮር ይዳኛው።

·       ክወና።

እናስተዋል!

ማስተዋል ጎድሎብናል። ፈጣሪያችን እንማጸን።

ማስተዋልንም አጓጉለናዋል። ወደ ቀልባችን እንመለስ።

ማስተዋልንም አጉል አድርገነዋል። ወደ ተፈጥሯችን እንመለስ።

ማስተዋልን ጭራሮ  አድርገን አጎፍረነዋል። በልኩ እንከርክመው።

ማስተዋልን ጎርፋማ አድርግነዋል። ወደ ጸጋው የጠራ እዬራዊ መክሊቱ እንመልሰው ዘንድ እንፍቀድ። 

 


መሸቢያ ጊዜ።

ኑሩልን ለእኔም ለቅኒትም ኢትዮጵያም።

ሥርጉተ©ሥላሴ

Sergute©Selassie

13.06.2021

 

ኢትዮጵያ ሥምሽ ከእነ ግርማ ሞገስሽ ይቀጥል ይሆን?

ልዕልት ኢትዮጵያ ጥቃት የሚያወጣስ ሙሴ እዮር ይስጥሽ ይሆን?

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።