"ሞት አያምም።" (ከእሸት ባለቅኔ ከገጣሚ በላይ በቀለ ዋያ።) 25.07.2022

የቁም እስረኛው ገጣሚ የጨመተ ፀጋው ህሊናዬ።
የማህበራዊ ሚዲያው ንቅናቄ ቴርሞሜትር።
መንግሥት የሸፈተባት አገር።
"ሞት አያምም"
እኖር ብዬ ብታረድም
ለመኖር ስል ብሰደድም
እኖር ብዬ ብዋረድም
ዘጠኝ ሞቴን ብሞታት
አንዴ እንደ መኖር አይከብድም።
መኖር ከሞመት አይልቅም
ሞት እንደ ሕይወት አይጨንቅም።
"ምክንያት"
"የሞተ እሞታለሁ ሲል
አያውቅም በጭራሽ ፈርቶ
ያልኖረም አያውቅም ሞቶ
መኖሬ እንጅ የሚያስፈራኝ
መኖር እንጂ *የሚያስገባኝ
መኖር እንጂየሚያስከፋኝ
መኖር እንጂ የሚበድል
ሞት አያምም *ከቆሰለ
ሞት አያምም ከገደለ።"
* ድምፁ ስለሚዋጥ ያልተሰሙኝ ናቸው። ግድፈት ካለበት ገጣሚ ባለቅኔም በላይ በቀለ ወያን ይቅርታ እጠይቃለሁኝ። የገጣሚ በላይ በቀለ ዋያ ድንቅ ቅኔ ነው ሥንኙ። መኖርን የሞገተበት። ሞነርን ችሎት ላይ እንዲህ ገትሮልኛል። ተባረክ የእኔ ጌታ።
'የቤትህ ቅናት በላኝ።"
የውስጤን ስገልፀው - እኔው።
ብዕር ታሰረ
በጭካኔ ተወረረ ተመረመረ
እንደ አልባሌ ተባራረ እዬተከረከረ
እያከራከረ ቆሽቱ እያረረ
የብራና ጠብታ
የዘመን ምጣት ቱማታ
በመታበይ ተመታ።
#የቃለ ምልልሱ ጭብጥ ከውስጤ ሳወያዬው መሰጠኝ፣ ጣመኝ ቃናውም ቁመናውም - እኔኑ።
"በሥራም በትንቢትም አምናለሁ ተስፋ አደርጋለሁኝ።
ሰው ለምን አስከፋኝ ብዬ አላውቅም። እኔ ምን አሰከፋሁት እንጂ።"
"ህገወጥ ህጋዊነቱ ያስፈራኛል"
"የግነት ሁነት በውስጤ እንዲኖር አልፈቅድም። በታፈንኩበት ክፍል የነበሩ ሰወች መልካሞች ነበሩ።"
"ወላጆቼ ባይኖሩ ነፃነቴን ስለምወድ አስቸጋሪ እሆን ነበር።"
"ስለ እኔ በጎ ምልከታ የሌላቸውን አላስባቸውም። መልካሞች ስለሚበዙ።"
"በዘራቸው ስለሚሞቱት ማዘን የሚያሳፍን ከሆነ? የእኔ እህት የእኔ እናት ከዛ ባይኖሩም የእኔ ወገኖች ናቸው። እንደሰው ሃዘኔን ብገልፅ?"
"ለቅሶዬን ጨርሻለሁኝ።"
"ከዛኛው ነውር ይኽኛው ነውር ይሻላል።"
"በማስመሰል አላዝንም።"
"ያን ጊዜ ግንቦት 7 እና ኦነግ፣ አሁን ደግሞ ህወኃት እና ሸኔ፣" የሁለት አገር ስደተኛው ገጣሚ በላይ በቀለ ዋያ ከምወዳት ፍልቋ አርቲስት ሃና የኋንስ በጎጆዬ ቆይታ። የሃንች አይነት ሴቶች ናቸው ለእኔ የውስጥ ውበት መለኪያ። ይስቡኛል እጥር ብለው ፎለቄወች።
#እኔን ሳስስበው።
ደክሞኛል። በዕውነት ደክሞኛል። ትውልዱ ግን ያሳዝነኛል። ከፈጣሪዬ በስተቀር፣ ከድንግል ሌላ በቅርቤ ማንም የለም። ብቻዬን ነኝ። ገዳሜ ሰላሙን ያገኝ ዘንድ። ግን ብዕርና ብራናዬ አሉ።
ከእነሱ ጋር ስለያይ ስሰናበት እንደምን የቀብሬ ሥርዓት ሊከወን እንደሚችል በኑዛዜዬ ገልጫለሁኝ። ያን ጊዜ በዝምታ፣ በቀስታ መራራ ስንብት። ግን በህይወት እያለሁ እንዴት ይቻለኛል? መፃፋን የሚሠራው እጄ ካልታመመ። ኦክስጅኔ ነው መፃፍ።
እና ወጣቱ ገጣሚ ለእኔ እንደ #ታገተ ነው። አልተፈታም። በሥነ ልቦና እንዲሰቃይ አድርገውታል። #ደመመኑ አለቀቀውም። አተያዩ ብዙ ውስጠቱን ያብራራል፣ ይተነትናል ይሞግታል።
በፃፈ ቁጥር ወላጆቹ ደውለው ያለቅሱበታል። እኔ ስልክ እማልደውለው፣ እማላነሳውም ለዚህ ነው። ስለዚህ መልስ ያልሰጠኋችሁ አትከፋ።
ኦክስጅኔ ከተነቀለ ህይወት የለም። ትንፋሽ ያጥረኛል። ታናሼ በልች፣ በልዩ ቅጣቱ ግዞት ነው። ታላቅ ወንድም ነበረኝ በላይ የሚባል። ሳይጽፋ መኖር ለፀሐፊ፣ ለእዮር የቅባዓ ባለፀጋ መኖር የሞተ ዕለት ይሆናል።
#ገፁ ሐዘንተኛ ነው።
"አይደገምም ያልከው ምኑን ነው" አለችው ሃንሽ። ባለ ቅኔው መለሰ። "መልሱም አይደገመም።" አላተኝ።
ለውጡን የደገፈ ወጣት፣ ለውጡን ያበረታታ ወጣት እንዲህ ስለምን በቁሙ ሊያሰቃዩት ፈለጉ? ኢትዮጵያን ማንሳት ፈርቷታል። ሚስጢረኛው ስለሆነች፣ ማንነቷ ስለገዘፈበት ሊሆን ይችላል።
ወጀብ ሲበዛ ዞር ብሎ ማሳለፍ ይገባል። እርምጃውን ወድጀዋለሁኝ። የማድመጥ ጊዜ ለጠሐፊ ዩንቨርስቲው ነው።
የሚያሳዝነው ግን እያደኑ ወስደው ከርችመው ገንዘው በግዞት የሚለቁት ፈሊጥ ነው። በጣም ብዙ ሰው በዘመቻ እንዲህ እዬተደረገ ነው። ዘረፋም አለ። መንግሥት የሸፈተባት አገር።
ማትም ምጣትም ነው። ብዙ ተቆርቋሪ የሌላቸው የእኛወች እንዲህ ኳራንቲ ህይወት እንደሚኖሩ ተረድቻለሁኝ።
ድምጽም ፀጋ ነው። መፃፍም ፀጋ ነው። ማድመጥም ፀጋ ነው። መኖርን ያደመጠ ፀጋ ስቅለት ሲታወጅበት አገር ስቅለት ላይ ስለመሆኗ አመላካች ነው።
በህይወት እና በግዞት እንዲኖሩ የተፈቀደላቸው ወጣቶች እንዲህ?
የሚያሰናብቷቸውን የሚንከባከቧቸው አይመስለኝም። የማህበራዊው ሚዲያ ሙቀት እና ቅዝቃዜ የጭካኔው ቴርሞ ሜትር ይመስለኛል።
የሆነ ሆኖ ስለ አዬሁት ደስ ብሎኛል። ብዙ እናቶች አሉት። ብዙ እህቶችም። ቤተ ጎጇችን ግቡ እና አዳምጡት።
ስለ ትውልዱ የምርምር ማዕከል ነው። የፖለቲካ ድርጅት አባልተኛ አለመሆኑን ግን ወድጀዋለሁኝ። ለምን? ይህም አይነገርም።
እግዚአብሔር ይስጥልኝ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
24/07/2022
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።