ስንት እኛወች አለን?
እንኳን ወደ ከበቡሽ ብሎግ በሰላም መጡልኝ።
ስንት እኛወች አለን?
ግራ ይገባል።
ግራ ያጋባል።
ፈቃደ እግዚአብሄር ይረሳል።
"ንጉሡም ኢትዮጵያዊውን አቤሜሌክን፦
ከአንተ ጋር 30 ሰወች ከዚህ ውሰድ ነብዩም
ኤርምያስ ሳይሞት ከጉድጓድ አውጣው ብሎ አዘዘው።"
(ትንቢተ ኤርምያስ ምዕራፍ ፴፰ ቁጥር ፲)
· #ጠብታ።
በዚህ ውስጥ ሲሪላንካ፣ እንግሊዝ፣ ሊባኖስ፣ የመን፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ጋና፣ ኬኒያ፣ ኡጋንዳ፣ አሜሪካ፣ አረብ ኢምሬት፣ ሳውዲ እንዳሉ ትነጉሩኛላችሁ። ግራ ቀኛችሁ ምኞታችሁ ሲጓዝ ስለማይ የፋንታዚ ዋናተኞች።
የፀደዩን አብዮት ተመኜን አሁን ደግሞ የክረምቱን?በመዳፋችን #ምን እና #መቼ ተገናኝተው ያውቁስ ይሆን?
1) ሰሞኑን የሲሪላንካ ህዝባዊ አብዮት፣ የእንግሊዞች የጠቅላይ ሚር አለመበርከትን አስመልክቶ ዕድሉ ለኢትዮጵያ ቢሆን ሲሉ ያስተዋልኳቸው ሁኔታወች ነበሩ።
· በዚህ ዙሪያ ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ ከለቀቁ እልቂት ይሆናል የሚሉ አፍቅሮተ - ኦነግን አዳምጫለሁኝ። አሁንስ? ሠርግ ላይ ነን ያለነውን? አይናችን ዳሽን ተራራ ያከለም አለን?
· በሌላ በኩል ይህ መንገድ ለእኛም ጠቃሚ ነው። በህዝብ ማዕበል ማስወገድ ይቻላል የሚሉም አሉ። ተወግዶስ? ምን ያህል ሊለምኑ ያፈሩ ወገኖች አሉን? የታወቀውን ድህነት ትተን?
ለግማሽ ቀን የሚሆን የሌላቸው ሚሊዮኖች እኛወች አሉን። ደሃ ነን። ድህነታችን የኢኩኖሚ ብቻ ሳይሆን የምኞትም። የፋንታዚ መሳፍንታት ወዘተረፈነት ይጨንቃል።
· ስንት እኛወች አለን?
· ስንት እኛወች ይኖሩናል?
· ስንትስ እኛወች ነን?
· እኛ እና እኛስ ተዋውቀን እናውቃለን ወይ?
#ስንተኛ ጊዜስ ነን?
መቼ ነው አዛውንት ተሁኖ ከኮበሌ ፖለቲካ የሚወጣው?
መልሱ #ከባጥ፣ #ከጣሪያ ወይንም #ከቆጥ መፈለግ የሚሻል ይሆናል። ወይ ከግድግዳ ወይንም ከሰንበሌጥ። ምክንያቱም በእኛ ውስጥ እያንዳንዱ በነፍስ ወከፍ መኖሩን ማረጋገጥ ያለበት እራሱ ስለሆነ።
ትናንት የተጠዬፍነውም፣ ዛሬም ሌሎች ሲያደርጉት እምንጠያፈውን እኛ ስናደርገው ቅድስና ነው? አናርኪዝም ግን የትውልድ አረም ነው። ቀውስም - ጦሮ።
· #ትንፋሽ።
መሪነት የአቅም፣ የብቃት፣ የተመክሮ፣ የልምድ፣ የመቻል አቅል፣ አደብ፣ የማድመጥ ልቅና፣ የህዝብ ፈቃድ ከሁሉ በላይ #ፈቃደ እግዚአብሔር መሆኑ ቀርቶ #ወረፋ ሆነ። እናም አንዘላለጠው።
መደባደብ? ለእኛ? በውጭ አገር? ከዬት የመጣ ገመና ይሆን? አበስኩ።
የማናውቀው ነገር የኢትዮጵያ ትንፋሽ በውስጣችን መኖሩን መሳታችን ነው። ችሎት መሄድ አያስፈልግም። ለጓማችን ኢትዮጵያዊነት ውስጥ ያለው ትንፋሽ ሊሆን ይገባል።
ሰንደቁን ስትይዝ ፈርተህ፣ ተንቀጥቅጠቅህ አክብረህ፣ አንተ በዛ ውስጥ #በጨዋነት ስለመኖርህ አረጋግጥ።
በዛ ሰንደቅ ውስጥ ያለው ሎጎ እኛነት በተደሟዊነት ነው። ከሊቅ እስከ ደቂቅ የኢትዮጵያዊነት አመክንዮን ስትፈፅም ህግ አክብረህ ይሁን። ህግ ተላላፊወች ምንግዜም የውድቀት ምልክቶች ናቸው። ጡንቻ ለቦክሰኛ፣ የበሰለ፣ ያፈራ ሃሳብ ለፖለቲከኛ።
· #ኢትዮጵያ ህግ ናት።
እኔ ብቻዬን ኢትዮጵያ በተፃፈ ህግ እንደሚተዳደሩት በተፃፈ ህግ ትተዳደራለች። ባልተፃፈ ህግ እንደሚተዳደሩት ባልተፃፈ ህግ ትተዳደራለች። ይህ የበለጠ ገዢ ነው። ግሎባልም ነው። አገራችን ትተን ተሰደንም እያንዳንዱን ሰከንድ ይመራዋል። ይህን ከጣስክ አንተ በአንተ ውስጥ፣ አንተ በእኛነት ውስጥ የለህም። #አልቦሽ ነህና!
ሃሳብ ካለህ ሃሳብህን ይዘህ ሞግት። የዬትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ሚዲያ፣ ሰብዕና ደጋፊ ይሁን። አቅም ካለህ ድርጅትህን በኢትዮጵያ አቅም ልክ ቅረፀው። የሚፋለመው ፋክት እንዲሆንልህ።
ኢትዮጵያ ተፈጥሯዋ የጠብ ግድግዳ አይደለችም። ኢትዮጵያ በተፈጥሮዋ እርቀ ሰላም ናት። ፀረ ሰው እና ፀረ ተፈጥሮ የሆኑ፣ ግለሰቦች፣ ድርጅቶች ኢትዮጵያዊነትን የሚፈሩት ለዚህ ነው።
"እስከ ሲኦል ድረስ እንሄዳለን "ሲሉ በውስጣቸው የበከተ ጥላቻ ስላለ ነው። ሥልጣኔ ከተነካ በቀን 100ሺህ አርዳለሁም ሲልህ በጥላቻ የበከተ ጎማ ልብ ስላለው ነው ሃሳቡ። "አማራን ገድለን አጥንታቸውን እናቃጥላለን ሲሉም የበሰበሰ ፀረ ፈጣሪ፣ ፀረ አላህ ሃሳብ ስላላቸው ነው።"
አንተም ስደት ላይ ሆነህ በሃሳብ የተለዬህን ስታሳድድ፣ ከበከተው፣ ከበሰበሰው የጥላቻ ክምር ቤተኛ መሆንህን እሰበው።
ለዚህ ነው እኔ #ኢትዮጵያ #የከበደችን ለሁላችንም ነው እምለው። አልከበደችኝም የሚል ደፋር ካለ ይምጣ እና ይሞግተኝ። አለሁለት።
· #ሲሪላንካ እና እንግሊዝ።
መጀመሪያ #ጉርምስናዊ ፖለቲካ አመራራችሁን አስታግሱ። ቦክሱ ይቁም። ኢትዮጵያ አዛውንት ናት። ኢትዮጵያ የበቃች ናት። ኢትዮጵያ ልኳ በሳል ሃሳብ ነው። የረጋ የሰከነ ጥሞና በተደሞ ነው።
ሁለቱም አገሮችም ኢትዮጵያን አይመሳሰሉም። ፈፅሞ። የመመጣጠን ጉድይ አይደለም። ተፈጥሯቸው ይለያያል። በሌላ በኩል ፖለቲካዊ ንቅናቄ #ሬድሜድ አይደለም። ሊሆንም አይችልም።
የዬአገሩ ተጨባጭ ሁኔታ፣ ማህበራዊ የንቃተ ህሊና ደረጃ፣ ባህላዊ ተስጥዖ፣ ታሪካዊ ጥሪት፣ ከሁሉ በላይ ፈቃደ እግዚአብሔር ይወስነዋል። ትውልዱ ስኩን ሃሳብ እንዲመራው ያስፈልጋል። የሚበልጥ የላቀ።
· #ምኞት በሥራ ልክ።
መመኜት ወሰን የለውም። ይቻላል።
መመኜት ደንበር የለውም። ይቻላል።
መመኜት የማንንም ይሁንታ አያስፈልገውም። መብት ነው።
መመኜት መብት ነው። የግዴታ ጣሪያና ግድግዳ የሚጠይቁ ሁነቶችም አሉበት። ሁሉም ከህግ በታች ነው። ፈጣሪ ከሰራው ህግ ማለቴ ነው።
· #ስለዚህም።
የምትመኜው ነገር በአቅምህ ልክ ካልሆነ ተስፋ ቆራጭነትን፣ ሥርዓት አልበኝነትን ያዋልዳል። ሁለቱም ህሙማን ያደርጋሉ። ጥስትን ያመጣሉ። ያ ደግሞ ያዬነው ነው። አቅምህ ነው ምኞትህን ማሳካት የሚችለው።
#የአማራ የበቃ ንቅናቄ።
"ከጎዳና ወደ ፓርላማ" የጠቅላይ ሚሩን ሆድ ያንበጫበጨ ገድል ነበር። ነገር ግን ሥውር ደጋፊወች አለቃቸው በወጉ በምርጫ ሂደት እንዲያልፋ ጠንክረው፣ ተግተው ሰሩ። ሌላውም አጃቢ ሆኖ ሆ! አለ። እና እፎይ አሉ። አሳክተው።
ዛሬ ከአንተ ጋር ሆነው ተቃዋሚ ሆነው ሺወች በአጀብ እንደ ታቦት ይከበክቧቸዋል። ከመወድስ ጋር። እኔ ከጭምቷ ጎጆዬ ሁኜ ውሽክ እላለሁኝ። ተሰላፊው እና አሳላፊው ሲ ……… ሳይ።
የአማራ ህዝብ እራሱን መርቶ የበቃ ንቅናቄ ሲያደርግ ሁሉም ተግ ብሎ ሊያደምጠው ይገባ ነበር። ህወኃት ጠበንጃውን አውልቆ ከጥፋት የሚያድነውን ንቅናቄ ማወኩን ማቆም ይገባው ነበር። ሁሉም አመዱን አፈሰ። ማድመጥ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች እና መሪወች ምጣቸው ነውና።
የአማራ ህዝብ ጥንግ ድርብ አብዮት አካሂዷል። ከሐምሌ 5ቱ አብዮት በኋላ። የሚመራው ተቋም አላገኜም። ስለዚህ ድካሙ ለገዳዮቹ ተሰጠ።
በጥገናዊ ለውጡ አሻምን ያሞገሰ የአማራ ህዝብ ነበር። ያጓጓል። ግን ድርጅትህ አማራዊ ቃና ሊኖረው ግድ ይላል።
የሆነ ሆኖ አሁን የምትሉት የሲሪላንካ አብዮት ሆነ የለንደኑ ነገር ቢሳካ ፖለቲከኞች ከእጃችሁ #የደረጀ ሃሳብ አላችሁን? ወይንስ እንደ አለፈው ጊዜ ኦነግ ይወገድ ከዚያ በኋላ ጨርቃ ጨርቅ ፋፍሪካ ሄደን #ዩኒፎርም እናሰፋለን ትሉን ይሆን?
ማን አለ? ምን አለ? እኛነትስ ለመሆኑ አለን? ወይንስ ወደ ሰማይ አረገ? አገር ቤት የመንገድ ላይ ባዕል ጦርነት፣ ውጪ አገርም ተናፋቂ ቀን ቦክስ፣ ፍጥጫ። ለትውልዱ ማሰብ ልሙጥ።
· #ያመለጡ ዕድሎች።
1) ትውልድ የማይተካቸው የጄኒራል ፋንታ በላይ ንቅናቄ። አሁን ሳስበው አማራ መሆናቸው ይሆን ተላልፈው የተሰጡት እላለሁኝ።
2) አቶ ልደቱ አያሌው ያዘጋጁት ሰነድ ነበር። አገር የሆነ ጭብጡ፣ አደረጃጀቱ መንፈሱ ለኢትዮጵያ ልኳ የነበረ ዘመኑን ያደመጠ በሳል ጎዳና ነበር።
ከሳቸው ቅን መንፈስ በኋላ #ሃሳቡ #እንዲታወክ ጥድፊያ ነበር። ለማወክ። ለማፎካከር። እና ውድቅ እንዲሆን። ተሳካ። የሚገርመኝ ያን ያደራጁ ፋክክሩን የመሩ ማለቴ ነው፣ በኋላ ተገልብጠው ደግሞ አቀንቃኝ ሆነው አዬሁኝ።
የአቶ ልደቱ ረቂቅ ሃሳብ እኛነት በይተን ኑሮ የሚገርም፣ ወቅቱን ያደመጠ፣ መቻቻልን ያፈለቀ መንፈስ እንደ ተራ ነገር በጥድፊያ በተነሱ ኃሳቦች ተደፋ። እና ኢትዮጵያ ተጠቀመች? በጦርነት ተጠመቀች። አብረን እንፈር እምለው ለዚህ ነው። ኢትዮጵያ ለሁላችን ከብዳናለች እምለውም ለዚህ ነው።
ሃሳብ ብቃቱ ነው ሊለካ ሊመዘን ዬሚገባው። ማንም ይሁን ማንም ሃሳቡ ለትውልድ ይጠቅማል ወይ? ከውርዴት ያድነናል? ወይ ብሎ ማሰብን ይጠይቃል። በወይፈን ፖለቲካ ትናትም ኢትዮጵያ ታመሰችበት ዛሬም። ???? ቆባነት ግጥሜ አይደለም።
· #ፈቃደ እግዚአብሔር ፊት መንሳት።
ዬእግዚአብሔር ፈቃድ ከአጀንዳ ውጭ ነው ለኢትዮጵያ ፖለቲከኛ። "በዘፈን፣ በፁሁፍ ጋጋታ ሥልጣን አለቅም" የሚል አገዛዝ አለ።
በሌላ በኩል ሌሎች አገር የተፈጠሩ ክስተቶች እንደ ሸቀጣ ሸቀጥ ኢንፖርት እና ኤክስፖርት ላድርግም አለ። ሁለቱም ፋርሽ ናቸው።
እግዚአብሔር የወደደው አቅም፣ እግዚአብሔር የፈቀደው ጊዜ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ የታተመበት ጤናማ ዘመን እንዲኖረን ተንበርክኮ አምላክን፣ አላህን መጠዬቅ ግድ ይላል። ግን እኛነት ስለእኛ ኃላፊነት እና ተጠያቂነቱን መውሰድ ከቻለ።
· #ከዛስ?
ከዛ በኋላስ?
የሚለው ጉዳይ ጥሞና ይጠይቃል። ሃሳባችን፣ መንፈሳችን ብኩን ስለሆነ የግል የብስጭት፣ የቁጣ፣ የአግላይነት፣ የማንአለብኝነት መንፈስን የገራ ያስተዋለ ፖለቲካ እና ፖለቲከኛ መቼ እንደሚወለድ ይናፍቀኛል።
· #ፍላት።
ፍላቱም ፍላሎቱም የአማራ የዘር ፍጅት፣ የአማራ መንፈስ ውድመት ሲከሰት ብቻ ነው። ሞቅ ደመቅ የሚለው መድረኩ ሁሉ። አልባብ ባልባብ የሚሸተውም።
የሚገርመው ኢትዮጵያ ዜናው ሁሉ መንፈሱ ሁሉ ምግቡ ሳይቀር አንድ ቦታ ላይ ብቻ ነው ሆሆምሻምሾም።
አገር ዘርፈ ብዙ አውታሮች ጠንክረው ሲደጋገፋ ነው ልትቆም የምትችለው። ለዛ ደግሞ ጥሞና ያለው፣ ምራቁን የዋጠ ሃሳብ እና ሃሳቡን የሚመራ ጭምት፣ ቻይ፣ እራሱ ደክሞ በፈጠረው የተደራጀ አቅም መነሳት የሚሻ ብቁ ልቅና ያለው ሰብዕናን ይጠይቃል። አላችሁን? ትህትናዊ ጥያቄ ነው።
ምን ይደረግ?
የምንፈልገው ይታወቅ። መቼ? እንዴት? እነማን ይምሩት? መሪነት ከባድ ሰብዕናን ይጠይቃል። ችሎት ነውና።
ሥር ነቀል ለውጥ። የሥርዓት ለውጥ። ዘመናይ አስተዳደር። ተፈጥሯዊነት። ሰዋዊነት። ኢትዮጵያን የሚያክል ሰብዕና???? ?????? ??????
እግዚአብሔር ይስጥልኝ።
ማለፊያ ቀን ይሁንልን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
12/07/2022
ጭምተኛ ፖለቲከኛ ይርበኛል።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ