ጎንደር እና አሳሩ በርብርብ።

ጎንደር እና አሳሩ በርብርብ።

 
እቴጌ ጎንደር ከምጥ እምትገላገልበት ቀን ቢናፍቀኝም እዬራቀ መሄዱን ሳስተውል እንደ ፈቃድህ ይደረግላት ማለቴ አይቀርም። የማዝነው አንድም ተቆርቋሪ ነፍስ ማጣቷ ነው።
ለምን ሲባል አብዛኞቹ ይታገላሉ ግን ለፖለቲካ ድርጅት ማልያ ነው የሚታገሉት። የጎንደር ህዝብ ደግሞ ለመላው ኢትዮጵያ ነው የሚታገለው። መፈክሮቹ፣ ሞቶዎቻ ከብሄራዊም አልፍ ሉላዊም ነው።
ጎንደር ላይ በነፍስ ወከፍ ይሁን በወል የሚከወኑ ነገሮች የተደራጁ፣ የተቀናጁ ናቸው። ይህ ግን አይወደድለትም። 27 ዓመት ሙሉ ስውር የሁሉም ነገር ምንጠራ ተከናውኗል።
ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ከሰሞኑ በሰጠው ቃለ ምልልስ ከዬኔታ ዩቱብ ጋር የጎንደር እስረኞች ተለይተው ይሰለባሉ ብሎ ምስክርነቱን ሰጥቷል።
በሁለመናው 27 አመት የደቀቀ ቀዬ ነው ጎንደር። ቀደም ባለው ጊዜ ተቆርቋሪ ሆነው የታዩት ጠሚር አብይ አህመድ የመጀመሪያ ዒላማ ያደረጉት ጎንደርን ነው። የኢንጂነር ስመኜው በቀለ ህልፈት ግንዱን ነበር ከመሠረቱ የነቀሉት። በዋዜማው ባለቤታቸው ጎንደር ልከው ነበር።
ቀጥሎ የሆነው ገዳ ንጉሡ ጥላሁን እና ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ወደ ዲሲ ተላኩ፣ ሲመለሱ የሰኔው ግርግር እና የአማራ ሊሂቃን ከጎንደር ሦስት፣ ከወሎ አንድ ተጨፈጨፋ። መቼም ለጎንደር የጦር ቀጠና ስለሆነ አንድ ዶር ማውጣት ምን ያህል ህልም እንደሆን ያለፍንበት ስለሆን እናውቀዋለን። ለሦስት ወር ስልጣን ቹቻ እና ሰኔል ተሸለመ።
ጥምቀት ምን ያህል ሎድ እንደነበረ እሰቡት ጎንደር። አደጋም ደርሷል። ያ እንዳለ የግንቦቱ ኢዜማ ጎንደር ተላከ። በዛው ፋታ በማይሰጠው ሰሞናት። ጠብ ለመጫር ነው። ያዬነው ባዶ ወንበር ነበር። ግን ስብሰባው ተስተጓጎለ ተብሎ አገር ይያዝልን ሆነ። የበጠበጡ ካሉ ሊቀጡ ይገባል። ሲጠሩ አለመሄድ ሲችሉ መበጥበጥን ምን አመጣው?
ያን ጊዜ ፃፍኩ እኔ። ወዬልህ ጎንደር ብዬ። ባህርዳርም የሆነው ያ ስለሆነ። አሁን ሰሞኑን ፕሮፌሰር ብርኃኑ ነጋ ዲሲ ነበሩ። ተልዕኳቸውን እሳቸው ያውቃሉ። ኢሳት ላይ ክሳቸው በማን ላይ እንደነበር አዳምጠናል። የሰሞኑ የጎንደር ወከባም እኔ እማዬው ከሳቸው ተልዕኮ አንፃር። አማራ ላይ ለሚደርሰው ሰቆቃ በግንባር ቀደምትነት የግንቦት ሰባት እጅ ስለመሆኑ ቅንጣት አልጠራጠርም።
ምክሩ የስሜንን ፖለቲካ ለመስበር ግንቦት ሰባትን በአማራ ክልል አስመርጦ ማምጣት የኦሮሙማ ትልም ነው። ይህ በሁለት ዘርፍ ጥቅም አለው።
1 ) የአማራ ሊሂቃን እንዳይወጡ የፖለቲካ ተሳትፎ ማዕቀብ መጣል።
2 ) ለምዕራብውያኑ እና ለአውሮፓው ህብረት ኦሮሙማ ተፎካካሪን አሳተፈ እንዲባል የምስል ግርዶሽ ለመስራት ነው።
ወሳኙ ጉዳይ።
1) የአማራ ብሄርተኝነት ለመግደል።
2) የአማራ የለም ፖለቲካን መሠረት ለማስያዝ።
3) የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማ የመበወዝ ትልም።
ይህን ተልዕኮ የሚያስፈፅመው ግንቦት ሰባት ነው። ግንቦት ሰባት እንዲያስፈፅም በማህበረ ኦነግ ሰፊ ድርሻ ተስጦታል። በዲያስፖራው ግዴላችሁም ቢሉም አልተሳካላቸውም። ወልቀው ቀርተዋል እርሾ አልቦሽ ሆነው። ይህ እንዳይመጣ አስቀድመን ነግረን። ትዕቢቱ ተራራ ነበር እንጂ አሁን አይታያችሁም ካለቃችሁ በኋላ ይታያችኋል ብዬ ተደጋጋሚ ፁሁፎችን ፅፌያለሁኝ። አሁን ዲያስፖራ ላይ በሃይልም አልቻሉም።
አሁን በኦነግ መንግሥት ኃይል አማራን ለማንበርከክ ጎንደርን አከርካሪ መስበር ታቅዶ እዬተሠራ ያለበት ጉዳይ ነው። የፕሮፌሰሩ የዲሲ ምልልስ በአማራ ብሄርተኝነት ላይ የዲፕሎማሲያዊ ምስክርነት ለመስጠት እና አስቸጋሪ ክልል መሆኑን ለማሳጣት ነው። ለኦነግ የወረራ እና የመስፋፋት ተልዕኮ ዕውቅና ለማሰጠት።
በዚህ ውስጥ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለው ዜጋ ምን ያህል ኢትዮጵያ ለኦነግ ኦሮማይዜሽን በቁሟ ስምምነት፣ ድርድር እዬተደረገ ስለመሆኑ ሊያስተውለው ይገባል።
ሌላው አማራው አማራነቱ ተሰቅዞ እንዲያዝ የሚፈለገው አገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ውጪም ጠንካራ ፀረ አማራ ተልዕኮ ያነገቡ ግለሰቦች እና ድርጅቶች እዩፈተኑት እንዳለ በማስተዋል ሆኖ ሊከታተለው ይገባል።
እነ አክቲቢስት ቴወድሮስ ትርፌ ወዝፈው የተውት የስኬት ቁልፍ ቢከልሱት የሚገባ ይመስለኛል። እኔ የፕሮፌሰር ብርኃኑ ነጋ የዲሲ ጉዞና ጦሱን በለብለብ አልመለከተውም።
የአማራ ህዝብ ሌላው የአማራ አክቲቢስት፣ ጋዜጠኛ፣ የፖለቲካ ሰው ማምለኩን ትቶ ለህልውናው እራሱን ዘብ ይቁም። የእስራኤሎች ያህል ፈተና ነው አማራ የገጠመው። የቻለ ምፅዕተ እስራኤልን ያንብብ። ፅናት ከዛ ይቀዳል። አቅሙን አያባክን አማራ። አቅሙን ቆጥቦ ያስተዳድር። አቋሙም ተዛነፍ አይሁን። ውሳኔውን ቋሚ እና ዘላቂ ያድርገው።
በመጨረሻ እምለው አማራ ለብልፅግና የጨረቃ ቤት ማህበርተኝነት የግንቦት ሰባት ሞግዚት አያስፈልገውም።
እራሱ የኦነጉን ብልፅግና መርጦ በጓሮ በር ሳይሆን በቀጥተኛው በር መርጦ በቀጥታ ማግኜት ይችላል የኦነጉን ብልፅግና በአማላጅ የግንቦት ሰባቱን ኢዜማ አማልደን ከሚል። ምን አለውና የግንቦት ሰባቱ ኢዜማ? እሱም እኮ ማጣፊያው አጥሮት ዬኦነግ ተቀላች ነው።
እውነት ለመናገር በፕሮፌሰር ብርኃኑ ነጋ ምንም ማለት አልሻም ነበር። ምክንያት ዘመን ስለሚያራግፋቸው ብቻ ሳይሆን የተጠጉት ፍራሹ ሴራቸው እራሱ ቀብሩን ስለሚያውጅ።
ዛሬ ያነሳሁት ያምናው ጉዞ ዲሲ እነ ዶር አንባቸውን ሲያሳጣን፣ ሊሂቃኑን ሲያስነቅል ለሚወሰደው እርምጃ ምዕራባውያን የቅድመ የህሊና መሰናዶ ሲደረግ፣ የአሁኑ የዲሲ ጉዞ ደግሞ ህዝብ ተኮር ጭፍጨፋ ማስከተሉን ለማጠዬቅ እንጂ ባለቀ ወይንም በሾለከ ታሪክ አቅም ማባከን አይስፈልግም ነበር። ፕሮፌሰሩ እዮራዊ ቅባዕውም የላቸውም አይደለም ሰውኛ የመተንበይ የማግስትን አቅም። በሙያቸው ቢተጉ አገርም ነፍሳቸውም ትሰክንላቸው ነበር።
የሆነ ሆኖ የአማራ ልጅ ፋከራም፣ ቀረርቶም አያስፈልገውም እንደ ጎንደሮች ሙያ በልብን ይተርጉም። ጎንደርን ማበሳጨት ለዬትኛውም አካል ዋጋ ያስከፍላል።
እንኳንስ ውሽልሽሉ፣ ዝርክርኩ፣ ዝብርቅርቁ የኦነግ አቅም ጎንደር በቃ ሲል የድርጅት አቅም የነበረው ህወኃት አንድ አመት መቆዬት አልተቻለውም። ውጪም ቢሆን የመንፈስ አቅም ያላቸው ልጆች አሏት ጎንደር። ገበሮዎችን አይጨምርም ሃሳቤ።
አብይዝም የባንዳ ማህበር እንዳቋቋመ አሳምሬ ስለማውቅ። እኔንም ለማጥመድ ለዛውም አጥቅቶና ተበቅሎ ተሞክሮ የዶግ አመድ ነው ያደረግኩት። ምክንያቱም ዕውነትም፣ መርኽም ለሌለበት ኦሮማይዜሽን ለባንዳነት ቅልውጥ የሚያስኬድ ምንም አመክንዮ ስሌለ።
እኔ ስለዶር አብይ ስፅፍ፣ ስሞግት ለመሆኑ ማን ነበር? አንድ የጎንደር ልጅ ይምጣ? ባለቀ ሰዓት ሲነጠፍ ሲጎዘጎዝለት የነበረው ላልነበረው ነበር። ትናንትም በአዎንታዊነት ስፅፍ በቃላቸው ውስጥ፣ ዛሬም እምታገላቸው በቃላቸው ውስጥ አለመኖራቸው እና ውሸታቸው ስለገለማኝ ነው።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
ትዕግሥት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል።

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።