ዓላማ እንኳን ተፈጠርክልኝ ብሎ ዬሚመርቀው አቶ ኤርምያስ ለገሰ። • ለዓላማው ፍፁም ታማኝ።

 

ዓላማ እንኳን ተፈጠርክልኝ ብሎ ዬሚመርቀው አቶ ኤርምያስ ለገሰ።
• ለዓላማው ፍፁም ታማኝ።





 
ለእኔ አቶ ኤርምያስ ለገሰ ግድፈታቸው ሳይዝረከረክ ጠቅላይ ሚር አብይ እንዲመሩ የተጋበት ዓላማው ነው ብዬ አምናለሁኝ። መብቱም ነው። አያደናግር ነበር በቀደመው ጊዜ ስሞግተው የነበረው።
ኦህዴድ መራሿ ኢትዮጵያም ናፍቆቱ ናት ብዬ አምናለሁ። ይህም ሙሉ መብቱ ነው። አማራ ለሞቱ ግን ተኝተህ በለኝን ከዝኖ የያዘበት ስልቱ ያመኝ ነበር። ሰሚም ዬለም። ስንት ሰው ፈዞ፦ ደንዝዞ፣ ስንት አቅም ብን ብሎ ተፍረክርኮ ቀረ?
"ዬቤትህ ቅናት በላኝ።"
አሁን ወጀቡ ረብ ብሏል። የጎሸውም ጠርቷል። ስለዚህ ሃሳቤን በሰከነ ሁኔታ ማቅረብ ፈለግሁኝ። አቶ ኤርምያስ ለገሰን ኢሳት መስራት ከጀመረበት ወቅት ጀምሮ አዬር ላይ አውቀዋለሁ።
በደጉ ሳተናውም በሁለት ፁሁፎቼ ሞግቸዋለሁኝ። በተጨማሪም በባልደራስ እስር እና ያራምደው በነበረቀቀው ዬንደት ስልቱም በተከታታይ ፌስቡኬ ላይ ሞግቸዋለሁኝ። ሂደቱ በጥዋቱ ነበር የገባኝ እና። ከዛ በተረፈ ከህወሃት ሥልጣን ስለምን ዓላማ እንደለቀቀ፤ ሰብዕናውን ለአምስት ተከታታይ ዓመት ልክ እንደ አቶ ጃዋር መሐመድ አጥንቸዋለሁኝ።
ምክንያቴ ሁሉም በዬቀለሙ ምን አስተዋፆ ሊኖረው ይችላል በሚል አርቄ ሳይሆን አቅርቤ የእኔ ብዬ አጥንቸዋለሁኝ። የፖለቲካ ድርጅት ተከፋይ ቋሚ ሠራተኛ መሆን እና ተምሮም ፖለቲካ ሳይንስን ዕድሉ ከሌለ የሰፋ ልዩነት አለው። በዚህም የዳበረ የፋንክሸነሪ ተመክሮ አለው። ከህወሃት ጋር መሥራቱ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ከጫካ እስከ እስር ቤት ከእስር ቤት እስከ ስደት በነበረኝ ፀረ ህወሃት እና ባልተለወጠው አቋሜ ላይ ሆኜ አቶ ኤርምያስን ከህወሃት ጋር ሰራ የሚለው ወቀሳ ያመኛል፤ ለዚህ ተልዕኮም እስከ መጨረሻው ተባባሪ አልሆንም። በዘመኑ የነበረው ህወሃት ነው።
እንደ አንድ የትውልድ አባል መሳተፋ የሚያስወቅስ፤ ዬሚያስነቅስ ወንጀል ለእኔ የለበትም። በሥርዓቱ ውስጥ ሆኖ ጎዳ የሚባለው ነገር ጉዳዩ የሚመለከተው አካል በህግ በአምክንዮው ይሞግተው። አሸንፎ በህግ ፊት ተጠያቂ ሲያደርገው ባይሆን ልጠዬቅ። አሁንስ ሙሉ ኢትዮጵያ በኦነግ መራሹ ኦህዴድ አይደል የምትመራ። ስንት የድርጅት አካላት እና አባላት እንዲሁም ደጋፊወች አሉ? እነ ዶር ሲሳይ መንግሥቴ ምን እንበላቸው? በህወሃትም በአሁኑም አካል የሆኑት።
ሌላው እትብት እዬተቆጠረ የሚታመሰው አዬርም ያሳስበኛል። ወጥ ማንነት ካላቸው ውህድ ማንነት ያላቸው ወገኖቻችን ይበልጣሉ። በተጨማሪም ባለቤት የላቸውም። ወደ አደላው መሄድም ተፈጥሯዊ ነው። ቀደም ባለው ጊዜ በአባቱ ብቻ የምናውቀው ስንቱ ሰው አሁን አያቱን የሚጨምረው እኮ የይለፍ ቢዛ ነው? ስለዚህ በአቶ ኤርምያስ ለገሰ ብቻ መተኮሩ ዬተገባ ነው ብዬ አላምን። ወላጅ አባቱም ለአገራቸው አንድነት እና ደህንነት የተዋደቁ ናቸው።
ለእኔ አርበኛዬም ጀግናዬም ናቸው። የቀደመውን ዬኢትዮጵያ ሠራዊት ነፍሴ ውጥት እስኪል እወዳቸዋለሁ። ይናፍቁኛልም። ማርሹን ስሰማ ዕንባዬ ፈቃዴን አይጠይቅም። ወንድሜን ሃይልዬን፤ ዬአክስቴን ልጅ ይርግዬን አጥቸበትማለሁም። ምንም ያልነበረው ደሙን የገበረ በበቀል የጎዳና ተዳዳሪ መሆኑም እማፍርበት ታሪኬ ነው።
ዬሆነ ሆኖ ቀደም ብዬ ባነሳሁት ጉዳይ በተለምዶ ፖለቲከኛ ዬሆነውን ወገኔን ትቼ ማለት ነው። ሰብዕናው ዬተከታተልኩት ሰው ነው አቶ ኤርምያስ ለገሰ። ጥሞና ገዝቼ ተከታትዬዋለሁኝ። ፖለቲካ ሰው ነው። ሰው ደግሞ የአንድ ጀንበር ዳንቴል አይደለም። በአቶ ኤርምያስ የፖለቲካ ፍሬም ወርክ ግን ዓላማውን ማሳካቱ እንጂ የሚባክነው የትውልድ ዘመን አስተውሎት አላገኜም። አቋሙን ሲቀያይረው የኪሱ ማህረብ ያህል ክብር የለውም። የእሱ ሃሳብ የነበረም አያስመስለውም። ወዲያውን ያን የራሱን ሃሳብ እና አቋም ባዕድ አድርጎ በአዲሱ አቋሙ መጪ ነው። ያለምንም ቅድመ ሁኔታ፤ ያለምንም ተጠያቂነት እና ሃላፊነት። አስተዳደር ላይ እንደሰራ እንደ ተማረ ሰው ለትውልድ ብክነት መዳን በፍፁም አትኩሮት አላይበትም።
አቶ ኤርምያስ ለገሰ ዓይን አፋር ፖለቲከኛ አይደለም። አቋመ ጽናቱም በፍላጎቱ ስውር ምርቅነት ጫና ዬፈጠረ እጅግ በፍጥነት ተለዋዋጭ እና ድንገቴ ገብ ነው። ለዚህም ነው እስከ ስኬቱ መባቻ ሚሊዮኖችን እንዳሻው የመራው። አሁን የአራት ኪሎ ትልም እና የዲሲ የዳያስፖራ ፕሮጀክት በአንድ ላይ እርጋ ብሎ ተከሰተ።
…… ስለዚህ የትውልዱን ብክነት ከመቀነስ እና ከመጨመር አንፃር ፖለቲከኞች፤ አክቲቢስቶች፤ ጋዜጠኞች፤ የሰባዕዊ መብት ተሟጋቾች የፖለቲካ አቅማቸው፤ አቋማቸው፤ ያሉበት ተጨባጭ ሁኔታ፤ ዬዘመኑ ፖለቲካ ባህሬ ቁመና ብሄራዊ እና ዓለም አቀፍ ሁኔታወች በስክነት ሊታዩ ስለሚገባ በዚህ ዙሪያ እተጋለሁኝ። ፎቶወችን በጥልቀት ማዬት። በውስጥነት መመርመርም ይጨምራል ክትትሌ።
ይህ ብቻ ሳይሆን ለይቼ ዬምከታተላቸው ሰብዕናቸው በሚዲያ ገፃቸውን እንደ ጭብጡ ባህሪም፤ ሳቃቸውን፤ አለባበሳቸውን ሳይቀር በአትኩሮት እከታተላለሁ። የንግግር ጥበብ መምህራኖቼ ፒላር ሁለት ነው ይላሉ።
እኔ ግን ሦስት ነው ብዬ እሞግታለሁኝ። እነሱ ተናጋሪ እና አድማጭ ይላሉ። እኔ ግን #ግብረ #መልስም ፒላር ነው ባይ ነው። እነሱ ደረጃውን ዝቅ አድርገው እንደ ክፍል ነው ግብረ መልስን የሚወስዱት።
ይህን ያነሳሁት ያለምክንያት አይደለም። በንግግር ጥበብ ውስጥ የእጅ፤ የገጽ፤ ዬአለባበስ ሁኔታ ዬሚነበብ መሆን ብቻ ሳይሆን የሚደምጥም መሆን መቻል አለበት። ፍዝ ሰብዕና የፈለገ ተናጋሪ ቢሆን አይስብም። ካልሳበ የአድማጭ ተሳትፎም አትኩሮትም ይቀንሳል።
በዚህ በንግግር ጥበብ ውስጥ ጋዜጠኛ ታምራት ነገራን እምመሰጥበት፦ ላደምጠው እምፈቅድበት ሁነት፤ በተጨማሪም ልጅ ተክለሚኬኤልን አበበን አድኜ እማደምጠው የንግግር ጥበብ ክህሎቱን በውን ስለማይ ነው። በዚህ ዙሪያ አቶ ኤርምያስ ለገሰም ጥሩ ተናጋሪ መሆኑን አይቻለሁ። ስብሰባ ሲመራ፤ ውይይት ሲመራም ብቁ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። በተጨማሪም እርስ ተሰጥቶት ፕሬዘንቴሽኑንም ተከታትያለሁ። ጭብጡን ማስተር አድርጎ ከእራሱ ጋር አዋህዶ ጊዜን መጥኖ የመጠቀም ችሎታውም አንዱ ነው። እንዲያውም ብዙ ጊዜ የሚጫነው ፕሮፖጋንዲስትነት ስለሆነ ፕረዘንቴሽን ላይ ሳያውከብ አይቻለሁኝ።
ከዚህ በተጨማሪም ዓራት ዓይናማ ፕሮፖጋንዲስት ነው። ፕሮፖጋንዳ አወንታዊ እና አሉታዊ ተብሎ በሁለት ይከፈላል። በሁለቱም ዘርፍ አቶ ኤርምያስ የተሰጠው ፀጋው ነው። ከፖለቲካ ተንታኝነቱ ይልቅ ፕሮፖጋንዲስትነቱ አቀራረቡን ውጦት ብዙ ጊዜ አስተውያለሁኝ። ቃለ ምልልስ ሲያደርግ ዬመጨመቱ ልክ ደግሞ እጅግ እምወድለት ክፍል ነው። ብዙ ጊዜ አስተያዬት እጽፍለት ነበር። በዛ ላይ ብቻ እንዲሰራ።
#ስውር #ስልት እና ለዓላማ ማስኬጃው የፕሮፖጋንዳ ባጀቱ።
አቶ ኤርምያስ ለገሰ ስልቱ ተለዋዋጭ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ወቅቱን እንዲመራ አድርጎ የማቅረብ አቅሙ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ከጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ውጪ ያዬሁት ፖለቲከኛ የለም። የአቶ ኤርምያስ የሚለዬው ከግቡ ሳይደርስ የስልቱን አስኳል ለማሳዬት አለመፍቀዱ ነው።
በዚህ ብዙ አቅም በዬዘመኑ ይጎርፍለታል። እንደ እኔ ልብ ብሎ ከሚከታተለው በስተቀር። እኔ በድጋፋም በተቃውሞውም ዬለሁበትም። ሂደቱን አይቼ ይህ ለዚህ ግብ ነው ብዬ ከመፃፍ ውጪ። ስለሆነም አቶ ኤርምያስ ለገሰ #አሳቻ ስልት ተከታይ ሲሆን ውሎ መሰንበቻውን በዓላማው ውስጥ ሆኖ፤ ለዓላማው በፍፁም ታማኝነት የሚተጋ ብልህ ሰው ነው ለእኔ።
እሱ ደግፋኝ፤ እጀቡኝ ብሎ ማመልከቻ አላስገባም። ወይንም ተፍነሽነሽልኝ ብሎ ከፕላኑ ዝንፍ አላለም። ትልም አለው። ራዕይ አለው። የሚመክተውን ሃሳብ እና አመክንዮ ጠንቅቆ ያውቃል። መቋቋሚያ መስመሮችን በውል አደራጅቶ በሌሎች አቅም፤ ትክሻ ተጠልሎ የሚያስፈጽማቸውን አደራጅቶ ይመራል፤ እሱ ፊት ለፊት ወጥቶ ዬሚጋፈጠውን ደግሞ ካለ ምርኩዝ በትጋት እና በታታሪነት ይከውናል። ብዙው ነገር ያሳካለት ግን ዬአቶ እስክንድር ነጋ በፖለቲካ ድርጅት መምጣት ነው። ለዕሱ ሎተሪ ወጥቶለታል ማለት እችላለሁኝ። ለእሱ ብቻ ሳያሆን ለአቶ ገለታው ዘለቀም። ብዙ ቁምነገሮችን በመመካር በአንድ ያልተቀያዬጠ መንፈስ መስመር አስይዘዋል።
አቶ ኤርምያስ ለገሰ የሚያገኛቸው መረጃወች ሁሉ ቆሻሻ ቤት አያሞቁም። በተለይ አማራን በሚመለከት አቴናወቹ ለ24 ሰዓት በተጠንቀቅ ናቸው። ወይ ሰርጎ፤ ወይ ጠልቆ፤ ወይ ጠልፎ መዳፋ ውስጥ ያስገባ እና ጠረጴዛው ላይ አስቀምጦ ያወያያቸዋል። ለተገቢው ቦታ ለትክክለኛው ሰው ያከፋፍላል። በይፋ የህዝብ አቅጣጫ መቀዬስ ሲያሰኜውም በሰላ መንገዱ መጪ ብሎ እንዳሻው ሺወችን ይነዳል፤ የሚንበረክከውን የሃሳብ ልዕልና ውልቅልቁን አውጥቶ ትቢያ ያስግጠዋል። የፈለገ የተጠራቀመ ገድል ይሥራ፤ እንደ አንከርም ይመለክ። ያራግፈዋል ያለርህራሄ። ከዛ በኋላ ዞር ብሎ አያዬውም።
በአቋም ተለያይተናል ይላል። የተላመጠ አገዳ ያህል ቁራጭ አትኩሮት አያቀምስም መጣ ሄደ አቀባበል አሸኛኜት አጀንዳው አይሆንም። ይህ ታዲያ መብለጥ አይደልምን። ጠቅላይ ሚር አብይ የጎንደሮችን ዘዬ ላፍ አድርገው ጅል፤ ጅላጅል ጅልአንፎን ሲያስጎነጭ አቶ ኤርምያስ ለገሰ ነግሮ ሳይሆን በተግባር ዘነዘና አስቀርቶ ነው። ዘመን የሰጠ ትውልድ ዬእኔ በሚለው ምልክቱ ላይ ሲዳኝ ዬሥራዬ የልፋቴ ዋጋ ነው የሚል ይመስለኛል። ጎንደሮች ባለ ቅኔወች ናቸው "አካሄዱን አይተው ሸክሙን ይቀሙታል" ይላሉ። አንድ ጊዜ ተበለጥ በተደጋጋሚ ዳጥ መርጦ ህዝብን መረመጥ ግን መበደል ነው። ትውልድ ብዙ ተገብሯል በዚህ በዘበጠ ልሙጥ ጋብቻ እና ግርግር።
#ጥቂት ምሳሌወችን ላንሳ።
1) አዲስ አበባ 50+ ዬሚባል ማህበረሰብ የላትም አለ ከLTV ሚዲያ ጋር ባደረገው ቆይታ ኢሳት እያለ። ጋዜጠኛ ቴወድሮስ ፀጋዬ ጠቅላይ ሚሩን በአሰብ እና በአዲስ አበባ ጉዳይ ያቀረበው ሃሳብ ጥያቄው መነሳቱም #ወቅቱን #ያልጠበቀ ነው ሲል ደመደመ። ይህን ባለ ማግሥት ባልደራስ ከች ሲል በፍጥነት ተቀላቀለ። በሰብዕናው የአትኩሮት ማዕከል መሆን ይሽታል፤ ይታገልለታል የአትኩሮት ማዕከል ሆነ።
የባልደራስ መሪ ሃሳብ አደራጅ እና አማካሪ፤ ኮኦርድኔተር እና ቁልፍ ብቸኛ ተደማጭም ታማኝ ሰው ሆኖ ቀረበ። እኛን ማን ያድምጥ። ባይገርማችሁ ቅድመ ጥንቃቄወችን ዘለግ ያለ ሰነድ የማደራጃ ዬመነሻ ሃሳቤን ደጉ ዘሃበሻ ላይ ወጥቶ ከፍተኛ ሼር ነበረው። ያን ባልደራስ ከጉዳይ አልጣፈውም። አዳኝ ፈውሱ ዬአቶ ኤርምያስ ጎዳና ብቻ ሆነ። የፖለቲካ ድርጅት የገብያ ውሎ አይደለም። ሙያተኛም አለው። መርህ ድንጋጌ ደንብ ማንነት እና ዲስፕሊን አለው። መሠረቱ ያላማረ ቤት አይፀናም። ባልደራስ ከዛ እንዲድን ነበር የደከምኩት።
ግን ሁሉም ቆጫ።ሻሻ ውስጥ ወድቆ አዳኙ መሪ የአቶ ኤርምያስ ራዕይ ብቻ እንዲሆን ተደረገ። ይህን ማድነቅ ግድ ይላል። ለዚህም ጭምቱ አቶ ገለታው ዘለቀ ተመደበ። ባልደራስ ለምርጫ ብቁ መሰናዶ ቢያደርግ ኦህዴድ ስለሚያሰጋው አዲስ አበባ "ራስ ገዝ" ትሁን የሚል ሃሳብ ፈጠረ። አደናጋሪ ግርግር ነበር። አቅሙ ሁሉ ወደዚህ ሽፍት አደረገ። ተጨማሪ ቅጥልጥሎችም ነበሩ።
ጉዞ ወደ ደብረብርኃን እና የደራ አማራ መብት አስከባሪ በመሆን ባልደራስ ያን ግዙፍ #ፓን #አፍሪካኒዝም ዓላማ ስቶ በሩትን ተግባር ተተብትቦ አዲስ አበባ #ለኦህዴድወኦነግ ቅኝ ተሰጠች።
2) ለማህበረ ኦነግ የራስ ምታቱ አማራ ነው። አማራ በወጣት፤ በፖለቲካ ድርጅት ተደራጀ። ይህ መሰበር ይገባ ነበር። ስለዚህ በአቶ ገለታው ዘለቀ ሥር አብን ወደቀ። እናም አዲስ አበባን ጥሎ አብቤቶ አብን አማራ ክልል እንዲወዳደር ተደረገ። አዲስ አበባ ላይ የአማራ መንፈስ በተቋም ደረጃ ትቢያ ለበሰ። አማራ የሚል ኃይለ ቃል ሥሩዝ ሆነ።
ዬሚገርመው ጭምቱ የታሪክ ተመራማሪ ፕ/ ዶር ሃብታሙ ተገኜ በራራ የዳዊት ከተማነትን በተጨባጭ የታሪክ መሠረትነት ያቀረቡትን፤ አቤቱ አብን ሠርዞ ረግጦም አዲስ አበባን ሙሉለሙሉ ለኦነግ መንፈስ አስረከበ። በዛን ጊዜ አቶ ኤርምያስ አስፈላጊ ከሆነ ከአብን ጋር እንሠራለን ብሎ ያደረገውን አብን አላምነውም የዛሬ ትራጀዲው ነው። ይህን ሁሉ እዬታዬ ሌላም ገደል ተወጥኖ ተከወነ። ነገረ ፋኖ።
ይህ ስልት እስካሁን ድረስ ባሊህ ያልተባለ ጉዳይ ነው። ለዓላማው ፍፁም ታማኙ ጀግናው አቶ ኤርምያስ ግን ፈጽሞታል። በውጭ የሚገኙትን የአማራ ሊቃናት በባልደራስ አማካሪነት፦ በድጋፍ ሰጪነት አድርጎ መራቸው። እና አማራ በዜሮ ተወራረደ። መንፈሱ ተገብሮ ለምርጫው የኦህዴድወኦነግ ዕውቅና ሆነ። ይህን ካነሳሁ ሰሞኑን የታዘብኩትን ላንሳ። አቶ መስፍን አማን ወጣትነቱን በፖለቲካ ህይወት ያሳለፈ፤ አልፎ አልፎ ሚዲያ ላይም የሚሳተፍ በሙያም የፖለቲካ ሳይንስ ሙሁር ነው። የባልደራስ የአውሮፓ ድጋፍ ሰጪ ሰብሳቢ፤ የሙህራን አማካሪነትም ምድብተኛ ነበር ለባልደራስ።
ዘሃበሻ ሆላንድ ፕሮግራም ይሠራ ነበር። አወያዩ ጋዜጠኛ ክንፋ አሰፋ ነበር። ከእለታት አንድ ቀን በምርጫ ሰሞን እንዲህም ሆነ። ሁለቱ ፕሮግራም ሠሩ። አቶ መስፍን አማን "ብልጽግና" እንዲያሸንፍ መፈለጉን ገለፀ። ደነገጥኩ። በሁለት ምክንያት። አንደኛው ብልጽግና የሚባል ፓርቲ አልተፈጠረም ነበር። የነበረው የአብይዝም የህሊና የፋንታዚ ዳንቴል ብቻ። ደንብ፤፦ፕሮግራም፤ መሪ እቅድ፤ ጉባኤ፤ ማዕከላዊ ኮሜቴ፤ ፖሊት ቢሮ፤፦ኦዲት እና ቁጥጥር የሌለው፤ በጉራጅ የኢህአዲግ ድርጅት በውራጅ አባል ህጋዊ ዕውቅና በጠበንጃ እና በሽብር ያገኜን መና ተቋምን አንድ የፖለቲካ ሳይንስ ሊቅ እንዲያሸንፍ ሲመኝ??? ሁለተኛው አቶ መስፍን የባልደራስ የዲያስፖራው የላዕላይ አካል ሆኖ ተቀናቃኜ ያሸንፈኝ ሲል ከውስጤ አዘንኩኝ። እኔም ስለደከመኝ ተውኩት። አልሞገትኩትም።
ያው ከማደምጣቸው ውስጥ ስለሆነ ትናንትና አንከር ሚዲያ ላይ ሳዳምጠው ብልጽግና የኢህአዴግ ውራጅ ድርጅት ነው ሲል አዳመጥኩት። ሳይንሱን የተማረው በዚህ ውጥንቅጥ ውስጥ ከሆነ ያልተማራው ምን አድርግ ተብሎ መክት እንደሚባል ሆድ ይፍጀው። በዚህ ትርምስ ስንት ነፍስ አጣን??? ጥያቄው ይህ ነው።
ይህ ሁሉ ሲሆን አቶ ኤርምያስ ለገሰ ንጉሥ ነው። ትንፋሹ ጠብል የማትል እንደ ጠበል የምትጠማ። በምርጫው ሰሞን በሁለት ቀን ወደ ስድስት ሚዲያ ይቀርብ ነበር።
1) ርዕዮት ሚዲያ፤ 2) አውሎ ሚዲያ፤ 3) ሚኒሊክ ሚዲያ፤ 4) አባይ ሚዲያ፤ 5) አዲስ ታይምስ ሚዲያ፤ 5) ጽዋ ሚዲያ፤ 7) ኢትዮ 360 ሚዲያ፤ 😎 ቤተሰብ ሚዲያ። ነፍሱን አያውቀውም ነበር። 24 ሰዓት ተጋ። ኦነግ ምርጫውን ተቆጣጠረ። እሱ ኦነግ ነው እያልኩ አይደለም። ኧረ ምን በወጣኝ።
የዛ ዘመን የዓድዋ በዓል አከባበር የታሪክ ሰው ጠፍቶ በአንድ ቀን ሦስት ሚዲያ ቀርቋል። 1) ጽዋ፤ 2) ሚኒሊክ ለምርጫ ኮረጆ ያተፈጠረ ሚዲያ ነበር፤ እና 3) ኢትዮ 360።
ጽዋ ላይ በተከታታይ በሰብዕና ግንባታ ተኮር ለአምስት ጊዜ ቀርቧል። በአንድ ሳምንት ውስጥ። ያን ጊዜ ያልታሰበ የፖለቲካ ሰብዕና ከተሟላ አቅም ጋር ወጥቶ ማስደመም ሲጀምር፤ አራት ኪሎም "ከጎዳና ወደ ፓርላማ" ሲል አቶ ኤርምያስ ይለፈኝ አላለም። ዬአትኩሮት ማዕከልነቱን በጥድፊያ በትጋት እና በተከታታይነት አሳይቷል። ማን አባቱ የአትኩሮት ማዕከልነቴን ይነጥቀዋል ብሎ ተፋልሟል። ምክንያቱም የኮረጆ ትንሳኤ እንዳይደናቀፍ።
የኦነግ የምርጫ ኮረጆ ይሳካ ዘንድ በተለያዩ አደረጃጀቶች ዬነበሩ የአማራ ተቋማት ሁሉ ካፒቴኑ ኤርምያስ ለገሰ እሱ ነበር። በሰሞናቱም ከአማራ አክቲቢስቶች ጋር ተከታታይ ቃለ ምልልስ ነበረው። እኔ ይገባኝ ነበር። እናም እስቅም ነበር።የኦነግ ምርጫ አጀንዳዬ አይደለም። አልነበረምም። ወደፊትም አይሆንም።
አቶ ኤርመያስ ለገ #አራጦ ይዞ ወደ ፈለገው አቅጣጫ ሂደቱን መርቶ ለድል አብቅቷል። ኦህዴድን ከዶር ለማ መገርሳ ባላነሰ ሁኔታ ለድል አብቅቶታል። ዬአማራ ተቋም ነን የሚሉ ሠራተኞችም ተጠልፈው አብረው አሸብሽበዋል። የአማራ መንፈስ ተጣራሪውን ሃሳብ አዝሎ አጨብጭል። በምርጫው ፍፃሜ የድንጋጤ ሰዓቱ ነበረች ለአቶ ኤርምያስ ለገሰ። ዶር ደሳለኝ ጫኔ ሲመረጥ፤ ያኔ በምልሰት ሂዳችሁ ብታዩት ግብረ መልሱን ታገኛላችሁ። ረዳበራድ ነበር የሆነው። በአማራ ክልል ላይ 100% ኦነጋዊው ኦህዴድ ያሸንፋል ዬሚል ዕድምታ የነበረው ይመስላል።
ይህ ብቻ ሳይሆን የአቶ ዬሱፍ ኢብራሂም አለመመረጥ እና የማህበራዊ ሚዲያው የቁጭት ሁኔታም ግራሞት ፈጥሮበት ነበር።
የሚገርመው ከኦነግወኦህዴድ የምርጫ ኮሮጆ ድል በኋላ በማግሥቱ እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ ተቃዋሚ ሆነ ወጣ። ውግዘተ ኦሮሙማ በዓይነት ተዥጎርጉሮ አጎረፈብን። ይህንም ማንም አላስተዋለውም። ከዛ በኋላ ዬአማራ ልጅ ሆ! ብሎ ንጉሥ ሆይ! ሺህ ዓመት ንገሥልን ተባለለት።
ለምን? ከእሱ ልቆ የአማራን ዝልቅ መንፈስ ራሱን በሚያድን የውሃ ልክ መንፈሱን ሊመራ የሚችል፦ በፋክት የሚሞግት አንድስም አቅም አልተገኜምና። እና ዬዛሬ #ተከዳን ስሰማ ይገርመኛል። ይደንቀኛልም። መባል ካለበት እንፈር ነው። ቁጥቦች ግን በዝምታ ያስተውላሉ። ዘውታ አልተጋበዘም እና። ለዚህ ሂደት ኢትዮ 360 ሰፊውን ድርሻ ከመንግሥት ሚዲያ ባላነሰ ተወጥቷል። ጉዳዮን ተጠይፎ ያላስቀረበው ርዕዮት ሚዲያ ነበር። አጀንዳውም አልነበረም። ሌሎች በግለሰብ ደረጃ ጉዳያቸው ያልሆኑ ሊቃናትንም አስተውያለሁ። ዬኦነግ ምርጫ ያልናፈቃቸው ለዛውም በዘር ሐረግ ኦሮሞ ዬሆኑ። በኮረጆ ዘመን ያልተነከረበት አልነበረም።
3) አሁን ወደ ቀጣዩ አጀንዳ አንድ ድንቅ ለሁሉ ክፍት ዬሆነ ለትችትም ለገንቢ ሃሳብም ለማከልም ጠፈፍ ያለ ዬሽግግር ሰነድ #ኢዴፓ አሰናዳ። ያ ሰነድ የመፍትሄ አወቃቀሩ የዘመኑን ባህሪ ከመጪው አደጋ ጋር እንደምን እንዳናበበ የሚገርም ሰነድ ነበር።
ይህ ሁሉ መራገፍ በፖለቲካም፤ በኢኮኖሚም፤ በታሪክም ሳይኖር ሁሉንም የሚያድን መስመር ነበር። ጦርነትም "ኖ ሞር TPLF" ያ ሁሉ ድቀት እና ብክነትም አይኖርም ነበር።
ሰነዱ ተደማጭ እንዳይሆን የአትኩሮት ማዕከል ተጣሰ በሚል አዲስ የሙሁራን የሽግግር ሰነድ በጥድፊያ በባልደራስ በኩል መሰናዳቱ ተደመጠ። የመንፈሱ መሪ አቶ ኤርምያስ ለገሰ ነው። ሃሳብ በማፍለቅም የደሙ ባህሬ ይመስለኛል ይችላል። ፀሐፊም ነው። ትብትቡን እዩት። እንደምን እያደረገ በሁለገብ ሁኔታ የመፍትሄ መንገዶችን አንኩቶ እንደሚያስከረችማቸው።
ከዛ ኦፌኮም በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ታቱ አለ። ሦስቱም ዬሽግግር ሰነድ ውድቅ ተደርጎ #ኦህዴድወኦነግ በአውራ ድርጅት መሪነት ቀጥለው ተልዕኳቸውን እንዲያሳኩ መልካም አጋጣሚ ተፈጠረ። ለዚህ ሁሉ ፍርሰት፤ ለሚጠብቀው የሃፍረት ሞትም ማንም ጉዝጓዝ እንደሆነ በጥሞና ማዬት ይገባል። ቁምነገሩ መንደፋደፋ ቁሞ የተከወነው ግድፈት እንደምን ይታረም በሚል ጥልቅ ጥናት እንዲደረግ ነው።
ዬሆነ ሆኖ ውድቀትን ተንበርክኮ ለመዛቅ ፈቃጁ ለዚህ አቶ ኤርምያስ ለገሰን እኔ ተጠያቂ ላደርግ አልችልም። ማንም ያሰናዳው የመፍትሄ ጎዳናውን መርምሮ፦ አጠናክሮ ቢቀጥል ከረባት አውልቆ የተሰካበት፦ ቲሸርት ተሰናብቶ ገበርዲን ዬተለበሰበት ከሞት መልስ ትራጀዲ ዛሬ ባልታዬ ነበር። ፋክክሩ መልካም ነው። ግን እምትፎካከረው ትውልድ እና አገርን ማዳን ሲቻል ነው። ለሁሉም ኢትዮጵያ ከብደዋለች። ኢትዮጵያ እንዲህ በግልብልብ ወጀብ አልተበጀችም።
ፋክክሩ አቅምን ማወቅ ይጠይቅ ነበር። በእጅ ያለን አቅም መምራት ይቻል ነበር። ማስተዋል ከሌለው ፖለቲካ ቬርሙዳ ትርያንግል ነው። በኪሳራ ውስጥ ማሸነፍ ዬለም። በትርፍ ውስጥ ነው ማሸነፍ ያለው። ትውልዱ ዕዳውን ሳይከፍል ሁሉም ወደ አመድነት ተቀዬረ።
4) በድንገት #ኢዴፓ ዬመሥራቹ መንፈስ ከእስር ሲለቀቅ አዲስአበባ ከንቲባ ለመወዳደር አወጀ። አሳንጋላ ነበር ለአቶ ኤርምያስ ለገሰ። የራስ መርዘን ነበር። ቢዛው መታገት ብቻ ሳይሆን በሃኪም የህልውና ጥያቄ ጫና ታቅዶ ተከወነ። ለዚህ የእኛ ሊቃናት ክሱ ወደ አንድ አቅጣጫ ብቻ ያንዶለዱሉታል። የገረመኝ። ተቀናቃኙ መንፈስ ከተሻለ ሃሳብ አቅራቢው መንፈስ በእንቅፋት እዬተደነቃቀፈ ተስረክርኮ ጉዞው አብሮ መባጀቱንም አስተውያለሁ። ምንድነው ፖለቲከኝነት? ምንድነው ሊቅነት? ወዳጅ ጠላትህን ለይተህ የኃይል አሰላለፍ መስመርህን አስተካክለህ እራስህን መምራት ካልቻል እንደምን ስለ ትውልድ፤ እንዴትስ ለትውልድ አሻራ ልትሆን ትችላለህ? በመሃል ባልተገባ ግንኙነት እራስን ማጣት እንኳን አጀንዳ ሆኖ አያውቅም።
በፖለቲካ ተቀናቃኚነት ዬሚፈለግ ነው። ግን ሁለመናህን አስረክበህ፤፦ሆድ ዕቃህን አውርሰህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ድንበርም፤፦ወሰንም፤ መርህ አልቦሹ ግንኙነት እና የትውልዱ ዘመኑ መዘረፍ አጀንዳ ሊሆን አልቻለም። ጠንቃቃ ፖለቲከኛም አላዬሁም። የማዬው ተዘራፊ ፖለቲከኛ ነው።
ከኦሮሞ ውጪ አዲስ አበባ ከንቲባ ቢኮን ህመሙ፤ ተመስጥሮ የተያዘው ቅምጥ ፍላጎት በጥበብ ተመርቶ ትልሙ፤ ተስፋው ሁሉ መክኖ ዛሬ ለምታዩት መገፋት፤ መገፍተር፤ መነቀል ተደረሰ። ፖለቲካ የውሃ ሙላት አይደለም። ፖለቲካ የጎርፍ ማት አይደለም።
ፖለቲካ የምራቅ ውሎ አይደለም። ፖለቲካ ቁጭ ብሎ መስራትን ይጠይቃል። ይህን አቶ ኤርምያስ ለገሰ ሰርቶ ለድል በቅቷል። የትናት ተሸላሚ እሱ ሊሆን ይገባ ነበር። በሁሉም ዘርፍ ለድል ያበቃ ነውና።
5) "ህወሃት በአሸባሪነት ይከሰስ" የአቶ ኤርምያስ ለገሰ ሞቶ ነበር። ከዛ ጦርነቱ ሲነሳ ጦርነት ብሎ አልተነሳም። ለረጅም ጊዜ "ህግ ማስከበር" እና አስፈላጊ ብሎ ደገፈ።
እንዲያውም የኔታ አቻምዬለህ ታምሩን ቃለ ምልልስ ሲያደርግለት "ኢትዮጵያዊውን አብርኃም ሊንከን" በጦርነት እንጠብቅ ሁሉ ብሎት። ቤቴ እስኪነቃነቅ ድረስ ነበር የሳቅኩት። ለረጅም ጊዜ ኢትዮጵያኒዝም ናቸው ብሎም ሲሞግት ነበር። የሆነ ሆኖ ዬኔታ አቻምዬለህ በሰማይ ታምር ብሎታል። በዛን ወቅት ጦርነቱን የእኛ ማህበረሰቡ እንዲል ዓራት ዓይናማው ፕሮፖጋንዲስት አቶ ኤርምያስ ለገሰ ሠርቷል። አሳክቷልም። ህዝብ ግልብጥ ብሎ ኦነግ መራሹን ሥርዓት እንዲያግዝ ሆኗል።
ከዛ ተገልብጦ ደግሞ #የህወሃት ተቆርቋሪ ሆነ። ህወሃት መጠቃት ሲጀምርም ዬሰላም ሰባኪ ሆኖ መጣ። ይህ ሁሉ ሲሆን ለምን? እንዴት የሚለው የለም። አብሮ ተለልፎ አግዞ አቅምን እያስገበሮ መጪ ነው።
6) ባልደራስ ከእስር ሲፈታ ስምሪት ሰጠ። ፋኖን ለመምራት እንዲችል። ኪሳራ + ኪሳራ= ??? እና አቤቱ ባልደራስ ወደ አፋርም ወደ አማራ ክልልም አቀና። ተው ብዬ ፃፍኩኝ። ቲም ዘኔ ጥሩ ጀምሮ ስለነበር የሰኔ 15/2011 ክስተት ይደገማል ብዬ አስጠነቀቅኩ። ገና ባልደራስ ከእስር ሲወጣ ፋኖን እመራለሁ እንዳትሉ ብዬ ፃፍኩኝ።
ዘኔ "ባልደራስ መሪዬ" ሲልም ሥልጣንህን ፈጥነህ አስረክብ ወይ ይቅርታ ጠይቅ ፋኖ የፖለቲካ ድርጅት ንብረት ሊሆን አይገባም፤ ብዬ በአድራሻው ፃፍኩኝ። በባልደራስ ማኒፌስቶ ውስጥ ፋኖ የለም። ስለዚህ ምን አገባው ባልደራስ ብዬም ፊትለፊት ሞገትኩኝ። የባልደራስ መሪ አቶ ኤርምያስ አውቶማቲካሊ የፋኖም እንደሚያደርገው አውቃለሁ። ብዙ የተሻ።ጀማመሩ በጎ ጥንስሶች ነበሩ ጠረኑ ያላማራቸው አቆሙት። ለዛ ነበር ተው ያልኩት።
በተጨማሪ ባልደራስ የከተማ ድርጅት ነው ወሰን አለው። ሁለቱም አካሄድ አናርኪዝም ነበር። አናርኪዝም ድርጅትን ያፈርሳል። አዲስሎ አበባ አሳሯን እምታዬው የወለጋ ጭፍጨፋ መጠንከር መሰረቱ ይህ የተፋለሰ ጉዞ ነበር። ላም እረኛ ምን አለ ዬለም። ቀድሞ ነገር አንድ አመት ከሰባት ወር እጅግ ብዙ ነው። ጥሞና ይጠይቅ ነበር። ተማጠንኩ። ሰሚ ዬለም። ነገ ቀን አይመጣም የተባለ ይመስል ግልቢያ። ያያችሁት ሁሉ ሆነ። ሽርሽሩን ከብራናዬ ላይ አለጠፍኩም። አንድም ፎቶ አታገኙም። ሂደቱ ንግግሩ ደም ያፈላ ነበር። ብዙ የተነቃነቁ ነገሮች ነበሩበት። መሪነት እንዲህ በዝልኝ??? ከዛ በኋላም ስለ ድርጅቱ ትንፍሽ ብዬ አላውቅም። መራራ ስንብት ሆነ።
አተረፈ??? ያ ዬፋኖነት ደማቅ ብሩህ ተስፋ ከሸፈ። የባልደራስ መሃንዲስ የፋኖ ላቅ ባለም የአማራ የፀጥታ ህዝባዊ ሰራዊት ሰነድ አዘጋጅ ፦ #ስትራቴጅስት አቶ ኤርምያስ ሆነ። ከውድቀት ወደ ውድቀት። ከኪሳራ ወደ ኪሳራ። ከሞት ወደ ሞት። ከክሽፈት ወደ ክሽፈት። ከጥቃት ወደ ጥቃት። ቲሚ ዘኔ ባይረብሹት እሱም እኛ የምንለውን ቢሰማ ካለው ሁኔታ ጋር ተጣጥሞ አቅም የመሆን አቅሙ በችሎታ ነበር። ከአቶ ኤርምያስ ሆነ ከባልደራስ የአመራር ፍርፋሪ የሚያስለምንም ምንም ምክንያት አልነበረም። ያም ሆኖ ቆጥቦ መናገር በዝግታ መራመድ ለህልውና ተጋድሎ ቅዱስ ጉዞ ነበር። አልሆነም። ኤርሚ አሸነፈ።
ስንት #ሺህ ታሰረ? ስንት አቅም #ባከነ። ስንት ትውልድ #ባከነ? 12993 ተማሪወች ከፈተና ውጪ ሆኑ፤ ሰማዕት ንገረው አዲስ በባዕቱ ተቀጥቅጦ ተደብድቦ በጥይት ተገደለ። ከ2014 ጥር አስተርዬ እስከ ዛሬዋ ዕለት 2015 ድረስ የአማራ ክልል በተለይ ጎጃም ሁለመናውን ቧ አድርጎ ለአቶ ኤርምያስ የፖለቲካ የሚሊተሪ አመራር ሰጠ አሳሩን አዬ። የፋኖ መሪም ዘኔው ታሰረ።
እንኳን ዘኔ በህይወት ተረፈ። ይህ ሁሉ በውጭም በአገር ውስጥ ዬአማራ ሊቃናት እያለ አንድም ሰው ትንፍሽ ሳይል ውድቀትን፤ ሙት መሬት ላይ ሆነን እንኮመኩማለን። አስረካቢው ዬኤርሚ ስልት እና ጥበብ እኛ ደግሞ የጥቃት አይጠግቤ ጎተራ ሆነን ቀጠልን።
7) ገና ሃሳቡ ሲጠነሰስ ይሾልካል። ሚዲያ ላይ ለወሬ ማሞቂያ አርቲ ሆኖ ይቀርባል። ደራጎኑ እያደባ በሚዲያ የሚተጉት ይለቀሜበታል። ሃሳብ መሪ ብቻ ሳይሆን የሃሳብ ዘብአደር ንቁ ወታደር ጠፍቶ እንሆ ዬአማራ፤ ዬአዲስ አበባ ተስፋ ይማቅቃሉ።
እነኝህን ለናሙና አነሳኋቸው እንጂ በቃል መቅጃወቼ፤ በምስል፤ በሊንክ ያሰባሰብኳቸውን ልዘርዝር ብል አንድ መድብል ይወጣዋል ዬነገረ ኤርምያስ ከመጋቢት እስከ መጋቢት ዬድፍን አምስት ዓመታት ጉዞ።
#ምን ይደረግ?
አቶ ኤርምያስ ለተነሳበት ዓላማ ጽኑ ከግብ ሳያደርስ የማይለቅ ሰው ነው። ሰው የፈለገ ቢል ጉዳዩ አይደለም። እሱ የሚያምንበት ንፁህ ዓላማ አለው። የአማራ ሊቃናት ወጥ የሆኑ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ወሳኝ ሮል እንዳይኖራቸው ከሥር ሥር እዬተከታተሉ መንገዱን ማምከን፤ ቋንጃን መስበር፤ አይከን የሆኑ ሰብዕናወችን አራግፎ ከጥቅም ውጪ ማድረግ። አዲስ አበባ ከንቲባነት በምንም ታምር ከአማራ እጅ እንዳትገባ መትጋት። ለጠቅላይ ሚር ቦታም ዬአማራ ተስፋን ወደ መቃብር መላክ።
ዬአማራ ተቋማት ከሲቢክስ አገልግሎት ውጪ በፖለቲካ ዘርፍ ብቅ እንዳይሉ ማምከን ። ዬገዘፈ ዬ50 ዬማሌ ርዕዮት ትንፋሽ ነፍስ ዘርቶ ባለቤት አግኝቷል ለዘመኑ። የዚህ ሐዋርያ አቶ ኤርምያስ ለገሰ ነው። ተሰልፈህ በወረፋ ለድጋፍ ደጅ መጥናትህ ዬአማራ ልጅ ግን ትገርመኛለት። አሁንም እልፍኙን አልባብ ባልባብ ዬምታደርግለት አንተው ሆነህ እሱን ስታነሳ ስትጥል፤ ስታወግዝ ውለህ ታድራለህ።
ዬእሱን አመራር ተቀብለው ለእሱ ፍላጎት ያልተንበረከኩትን በመንግሥት አቅም መሰባበር። በተለይ ስሜን ጎንደርን። አቶ ኤርምያስ እና ቲሙ የጎንደርን መንፈሱ አይወደውም። ጣውንቱ አድርጎ ነው የሚዬው። ምክንያት ዘንቁልልኝ፤ ጎልጉልልኝ፤ እመሰኝ፤ አስምጠኝ፤ ብለጠኝ፤ አስከንዳኝ፤ ሙት መሪት አስተቃቅፈኝ፤ ጥበብ አንሶኛል አበድረኝ የሚል አልተገኜም ከጎንደር። በሩ ዝግ ነው። ዬተከረቸመ። እንዳሻው መሆን ያልቻለበት ወደፊትም ሊሆን የማይችልበት ባዕት ነው።
ስለዚህም "እናትዋ ጎንደር፤ እህልዋ ጎንደር፤፦ትንፋሽዋ ጎንደር" በኢትዮጵያ ህዝብ፤ በአማራ ህዝብ እንዲገለል ማድረግ ትልቁ ፕሮጀክት ነው። ፈጣሪ ለፈጠረው ባዕት አለለት እና አያስጨንቅም። በእሱም ቂም አንይዝም። ዬበቀል አምላክን ችሎትም አንጋፋም። አዲስ አበባን ሙሉ ለሙሉ ለኦነግ አስረክቦ ተከሳሹ ጎንደር ነው። ጎንደር መንግሥት እስከ ሠራዊቱ ዕድሜ ልኩን ይዘምታል። በእዮር ኃይል ይሰበራል የዬትኛውም ግለሰብ መንግሥታዊ ኃይል። ጠቡ ህወሃት ቤተ መንግሥቱን ለምን ለቀቀ፤ ቅራቅርን ሰብሮ አዲስ አበባን ስለምን አልተቆጣጠረም ይመስላል። ከህወሃት ካለው አፍቅሮት ዬተነሳ። እኛ ስኔፈጠር ህወሃትን #አክ! ብለን ነው። ድርድር የለም።
"አድርገህልኛል እና አመሰግንህአለሁ።"
1) ዬአቶ ኤርምያስ ለገሰን ሥም ከማብጠልጠል መታቀብ። በልጧል መብለጡን ዕውቅና መስጠት። መብለጡን መቀበል። አምርሮ ከመጥላት መቆጠብ። ቂምም አለመያዝ። በእጅ ባለ አቅም ላይ ግንአለመቀለድ። አማራ በእጁ ያለውን አቅም ልጠቀም ቢል የሠራዊት ጋጋታ አያስፈልገውም። "ንጉሥ በሠራዊት ብዛት አይድንም።"
ሌላው ተወቃቅሰንም፤ ተደባድበንም እልፍኛችን አንድ ናት እንገናኛለን። ከሁሉ አቶ ኤርምያስ ለገሰ ቤተሰብ አለው ልጆች አሉት። ቤተሰቦቹም ልጆቹም ዬእኛ ናቸው እና እንዳይከፋቸው በሥነ - ልቦና እንዳይጎዱ ጥንቃቄ ማድረግ ግዴታችን ነው። በቀለኝነትን መጠዬፍ ይገባል። በቀለኛ መሆን መርህ አልቦሽነት ነው።
2) ሚዲያ ፈጠረ ብለው የተበሳጩ አሉ። መብቱ ነው። እንኳንስ ሚዲያ ዬፖለቲካ ድርጅት ፈጥሮ የመምራት ሙሉ አቅም አለው።
በአምስት ዓመት ውስጥ ዬሠራው ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ እንደ መሪ፦ ኦህዲድ ኦነግ እንደድርጅት ከሰሩት እጥፍ ድል ዕጣ ነፍሱን ከውኗል። ተልዕኮውን ሲጨርስ ፈቅዶ ከኢትዮ 360 አደራጅቶ እራሱን ተሰናብቷል።
መሰናበቱን አስቀድሞ ስለወሰነ የአቋሙን ፍንጭ ብልጭታ ወይንም የወራጅ አለ ፍሬቻ አሳይቷል። ትኩንም ተክቶ ነው የወጣው። ጭምቱ አቶ ገለታው ዘለቀ።
አቶ ገለታው ዘለቀን እሱን ተሸክመህ የአቶ ኤርምያስን ፕሮጀክት እፈትናለሁ ብለህ አትሰበው። አትችለውም እና። በጣም ዲስፕሊን ናቸውና። ዝርክርክም ዝልግልም አይደሉም። አቶ ገለታው ዘለቀ በዝምታ ቀለሙ ውስጥ ያሳካው ትልቁ ፕሮጀክቱ ከአሜሪካ ኢትዮጵያ ዬገባበት ቁም ነገር አዲስ አበባን #ለኦነግ ማስረከብ ነበር። "ሙያ በልብን" ዬተረጎመ ጀግናም ነው። በተገባው ልክ ዬአቶ ኤርመያስን መሻት ለድል አብቅቷል። በቅቷልም።
እኔ አቶ ገለታውን ከ10 አመት በፊት በኢሜል አውቀዋለሁ። እማከብረው ሰው ነው። ኢትዮጵያን ይፈልጋል ።። ግን ኦሮማይዜሽን የሆነች ኢትዮጵያን። #ገዳዊት ኢትዮጵያ ህልሙ ነበረች። አሳክቷል። ታሪካዊ ግዴታውን ተወጥቷል።
ለተዋፆ ተብሎ ማስታመሙ ግን እርቃኑን ለቀረው የሃሳብ ተስፋ ራህብ ይለቅበታል። ይህ ማለት ግን እንደ አገር ልጅ አብሮነቱ በውስጣችን ይቀንስ ማለቴ አይደለም። ከአማራው ፖለቲካ ግን?? ሚናው የለዬ ጎራ ስላለው ከውድቀት መማር ብልህነት ነው።
ከሁሉ የአሳርኛው የአማራ መከራ እንዲህ የካርታ መጫወቻ ባይሆን ምርጫዬ ነው። ሚና ለይቶ በሃሳብ መታገል በአንድ መድረክ ይቻላል። ሰርገኛ ጤፍ ወይንም ዱራኛ ሆኖ መስሎ መተወን ግን እስከ ዛሬ የተጎዳነው ይበቃል። በቃ ሊባል ይገባል። ድክመትን ዓመት ድገመኝ፤ ግድፈትን ትንሳኤ ልሁንህ እብደት ነው። ወፈፌነት። በመስመሩ ሆኖ ግን መሟገት በአንድ እልፍኝ ማለፊያ መንገድ ነው። እኛ ለምናስባት ኢትዮጵያ ዬሁለቱም መንገድ አሳቻ ነው። ሃግ ሊባሉ ይገባል። እያታለሉ መዘመን ግፍም ኃጢያትም ነው። የተቀለደው ይበቃል። ለመሆኑ ምን አለን? ምንስ ቀረን???
3) ውሸታሞች ነን። ዴሞክራሲ እንላለን ከእኛ ሲደርስ አቅም የለነም። ይህ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ችግር ነው። ኢህአዴግን መደገፍ መብት ነው። የአቶ ኤርምያስ ለገሰ መንፈስ ኦህዴድ መራሽ ኢህዲግን ማዋለድ ነበር። የተጋበት ዬአምስት ዓመቱ ተጋድሎ ነው። 100% አሳክቷል።
እንደ እኔ ጥቂት ረፍት ቢወስድ መልካም ነበር። ግን ስሜን ጎንደር እንዳይነሳ አድርጎ ቅስሙን የሚሰብር ኦፕሬሽን እስኪሳካ እንቅልፍ አይኖረውም። ለዚህ ይመስላል ፋታ ያጣው መሰል።
5) እኔ ከዲስ እስከ አራት ኪሎ የተዘረጋ ሃዲድ እያልኩ ስጽፍ ተረብ ይመስል ነበር። አሁን ፍሬም ወርኩን እያያችሁት ነው። ዝንፍ ሳይል እንደ ሬድሜድ እዬተከወነ ነው። የአቅም መግቦት ለቤተ መንግሥቱም ለዲሲውም አማራ ጅሎ ነው።
ሟችም፤ ተሸናፊም፤ የሚላገጥበትም፤፦ከማናቸውም የመንፈስ ርስቱ ተነቃይም፤ ሙት መሬት ላይ ያለውም አማራ። በወሳንሳ ኦነግን ደግፎ ከብክቦ ያቆመው ደግሞ የአማራ አቅም። የሚፈቀድለት አንጋችነት እንጂ መሪነት እእ። የአቶ ኤርምያስ መነሻ እና መድረሻ የተልዕኮው ምስባክም ይህው ነው። ይህን ጥሶ የሚወጣ አቅም አላዬሁም። እምነቴ እዮር ነው። ተስፋ አያልቅምና።
ከውድቀት፤ ከመበለጥ መማርም አንድነገር ነው። በምን አይነት ስልት እና ጥበብ በዲያስፖራ አገርቤት ያለውን አቅም እንደ መስኖ ውሃ ቀይሶ በአህትዮሽ መርቶ ገዢ መሬት ላይ ዓላማውን ቁብ እንዳደረገ ማዬት ነው። የህወሃት እና ዬኦነግ ሠርግ እና መልስ በኦነግ ዬሞጋሳ ፓርክ በአዲስ አበባ፤ በቀንጣን ዬተቸነከረው ኦነግ ከህወሃት ጋር ትክሻ ለመለካካት ዬኦነግ ጆኖሳይድ እና የእውቅና ክብር ታንዛንያ ሊንኩ አዲስ ሚዲያ ከፋች አቶ ኤርምያስ ለገሰ። ቢያቅት ከሂደት መማር? አንድ ዕጣ ነፍሱን ሰጥ ለጥ አድርጎ ዲያስፖራውን፤ አዲስ አበባን፤ የአማራን ተጋድሎ ገዛ፤ ነዳም። በነገራችን ላይ አቶ ኤርምያስ ከልቡ ሲስቅ አይቼው አላውቅም። ከጥርሱ የሚቀር ነው ሳቁ።
አሁን ግን ከልቡ ሊስቅባቸው ይገባል ሲመራቸው፤ ሲረሽናቸው፤ እንዳሻው ሲነዳቸው፥ ሲቀብራቸው ለነበሩ ለዛሉ ሃሳቦች እና መንፈሶች። ተዋጊ ዋርዬር አቶ ኤርምያስ ለገሰ አትኩረተ ማዕከል ምኞቱን መርቶ በትናንት ብቃት ዛሬን ለዓላማው ድልዳል ሠርቶለታል። መሃንዲስ።
ይህ እልህን ወልዶ - ጥላቻን ገድሎ፤ ቂምን - ተጠይፎ አቅምን በቅጡ ለማስተዳደር ካስወሰነም አንድ ነገር ነው። ግን አይመስለኝም። አሁንም ከአቶ ገለታው ዘለቀ መንፈስ ማር ይዝነብልን ……… ልመና ላይ መሆናችሁን አያለሁኝ።
6) ከድኜ የምተወው የቅድስት እናታችን ኦርቶዶክስ ተዋህዶን ጉዳይ ነው። እምጋብዛችሁ ግን አለኝ። ፃድቁ አባታችን ፓትርያርከ ዘኢትዮጵያ ብፁዑወቅዱስ አቡነ መርቀርዮስ በሥጋ ሲለዩን ሰሞናቱን በምልሰት ሄዳችሁ ኤርሚን ጎብኙት።
በዚህ አጋጣሚ ከሚዲያ ሰወች ጋዜጠኛ ሃብታሙ ሃብትሽ ዬነበረህን መንፈስም ተከታትያለሁ። ፎቶውም አለኝ። የብፁወቅዱስ አባታችን በረከታቸው እንደማይለህ ተስፋ አደርጋለሁ። ልጆቻቸውም በፀሎት ያስቡህ ዘንድ በአጋጣሚ እጠይቃለሁ። ሚሊዮኖች ናቸውና።
7) ዬማይካድራ ጭፍጨፋን ኢትዮ 360 የሠራበትንም ቪዲዮ ቅኔውን መልሳችሁ ብትመረምሩት ግብዣዬ ነው።
#ክወና።
እምነታችን ፈጣሪያችን ይሁን። በኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ተጽዕኖ ፈጣሪነት ጥገኝነት ይቁም። እኛ የእኛን ብቻ እንሥራ። ዓለም ሰፊ ናት። እኛ ለዓለም የጎጆ እሳር ያህል ነን። ይህን አውቀን በገዘፈው ዓለማችን ልክ እንሰብ። አንኮርኮድ። ዓይነ ሙሉ ልበ ሰፊ እንሁን።
በእናት አገራችን ላይ ደባ ከመስራት እንቆጠብ። ብትን አፈር ለማኝነት የሁሉም ዕጣ ፈንታ እንዳይሆን ቢያንስ ቅንነትን አንንፈጋት። በእናት አገራችን ቀደምት ታሪክ አንቅና። ያ ታሪክ ዛሬን ሲሰጠን ውለታው ቀርቶ ከጠላት ጋር መተባበር ኃጢያት መሆኑን እንሰበው።
#ከዘለለው ጋር አንዛለል። #ከጎረፈው ጋር አንጉረፍ። አገር በአንድ ጀንበር አልተሠራችም። ለዛም አቅምን በጥንቃቄ ተጠቅሞ ማስቀጠል ከእያንዳንዱ በግል ከሁሉም በጋራ የሚጠበቅ ዬትውልድ አደራ ነው።
ለእኔ ነፃነት የምሳሳውን ያህል ለሌላው ነፃ መሆንም ቀናዕይ መሆን ይገባል። የዜግነት #ሲሶ፤ የዜግነት #እርቦ ዬለውም። ለዜግነት ሰጪም ነሺም ዬለም። ስለዚህ አቶ ኤርመያስ ለገሰ ሚዲያ መክፈቱ መብቱ ዬእሱ ብቻ መሆኑን እንቀበል። ዓለም ወርደ ሰፊ ናት። አንኮርኮድ።
ሁሉም እኩል መብት። ሁሉም እኩል ግዴታ አለበት። እናት ኢትዮጵያም የክትና የዘወትር ልጅ የላትም። ከሁሉ እናት አገር ኢትዮጵያን አንቅናባት፤ አንወንጅላት፤ ሴራ አንስራባት።
ክብሮቼ ኑሩልኝ። ደህናም ሰንብቱልኝ። ምዕራፍ ስምንት እዬተጠናቀቀ ነው። ዘጠንኛው አጤ አብይ አህመድ ምን ሆነው ብቅ እንደሚሉ ይጠበቃሉ። እሳቸው አያልቁም ደግ ቀናትን ጨረሱ። እኛንም።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
25/04/2023
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።