ስትዘነጣጠሉ ባጃችሁ አሁን ደግሞ ትቅቅፍ። የፖለቲካ ግሽፈት ( Inflation.)

ስትዘነጣጠሉ ባጃችሁ አሁን ደግሞ ትቅቅፍ። የፖለቲካ ግሽፈት ( Inflation.)
 
"ህግ ተላላፊወችን ጠላሁ።"

 
 
#ምራቃቸውን ለዋጡ የአድማጭነት ፀጋቸው ኢትዮጵያን ቁም ነገር ዬማድረግ ዓላማ ላላቸው የዕንባ ሁነኛወች።
ህግ መተላለፍ ቅጣቱ የምድር ይመስል ይሆናል። ወይንም ዳንቴል የእጅ ሥራ፤ ወይንም የፋንታዚ ግንብ አይደለም። ህግ መተላለፍ መንፈሳዊ ቅጣት ያመጣል። ከአቅም በላይ ቅጣት ያስመጣል። 
 
"ወግዱ፤ ጥርግ በሉ፤ እናሳያችኋላን፤ የቀን ጅብ፤፦ መጤ፤ ፀጉረ ልውጥ፤ ሰፋሪ፤ ወዘተ …"
 
ኢትዮጵያ እንዲህ ያሉ ዝልኝ ዕሳቤወችን የፈጠረች አገር አይደለችም። በዚህ ልቅ ሁነት አይደለም የጥቁር አብነቷ፤ የአፍሪካ አንከሯ ኢትዮጵያ የሦስት ጉልቻ ኩነትም አይፈጠርም። ህግ፤ ሥርዓት በባርኔጣ፤ በገበርዲን፤ በከረባት ወይንም በፋሽን እና በፎቶ ሸው አይተረጎምም። 
 
ይህንን "መሬት ነህና ወደ መሬት ትመለሳለህን" የመሰጠሩ ብቻ ይኖሩታል - ህይወቱን። ምክንያቱም መሬትን ስትራመዱባት ተጠንቅቃችሁ ተብለው በዚህ ዝልቅ የመንፈስ ልዕልና በአርምሞ ልቅና ያደጉ ብቻ ያውቁታል።
 
እኔ ሚዲያ ዬሚባለው #ኦሜኮ ምን አንደበት ኑሮት፤ ምን ልሳን ኑሮት የህወኃት እና የብአዴንን ትቅቅፍ እንደሚዘግብ፤ አብኖች ለዚህ ድልቂያ እንደምን እናሸብሽብ እንደሚሉ፤ ህወሃትን ብን አድርግልን ብለው አብይዝምን የከበከቡ መንፈሶች ሁሉ በዚህ ውስጥ መንፈሳቸው ተረጋግቶ ዕለታዊ መኖራቸውን እንደምን በተስፋ ማጣት እንደሚያሳቅሉት አስበዋለሁ።
 
ለዚህ ነበር ጦርነት አያስፈልግም፤ በጦርነት አሸናፊ የለም፤ ፊታውራሪ ጦርነት አሸነፍኩ ካለም #በቀል እና #አመድ ያፍሳል በማለት የሞገትኩት። አሁን የጥንቱ ወዳጄ አቶ ሻንቆ እና "ህወሃት ከጠፋ ቀሪው ገብስ ነው" እያሉ እጅ በደረት ያስከነዱትን ያዬ ሰው።
 
ወደ ጦርነትም ሲኬድ #ድልቂያ፤ ወደ ዕብለታዊ የሽንገላ ኳኳቴም ሲመጣ #ድልቂያ። መቀሌ ተለቀቀ #ርችት፤ መቀሌ በህወሃት ሆነችም #ድልቂያ። አድራሻ ቢስ ቅዝፈት እና ንቅዘት። የፖለቲካ ግሽፈት Inflation.
 
የኢኮኖሚ ግሽፈትን ሙህራኑ ይሆኑበት። እኔ ደግሞ የፖለቲካም፤ የባህልም፤ የትውፊትም፤ የትሩፋትም፤ የወግም፦ የልማድም ግሽፈት፤ የራስ እራስነት ወይንም እንደራሴነትም በኢትዮጵያ ገጥሟል ብዬ አስባለሁኝ።
 
ትናንት በመታበይ በተከፈተ ጦርነት ትቢያ እና ማቅ ተላብሶ አልተጠናቀቀም። "ሌባ፤ ሞላጫ፤ ኢ - ታማኝ፤ ካህዲ ……" ይህ ሁሉ ኢትዮጵያዊ ነኝ ለሚለው ሁሉ የዓለም ሚዲያ ዬሚቀባበለው ማለያችን መሆኑ እራስን ለማዬት በረዳ ነበር። ብዙ ነገር ማዳን ሲቻል በጦርነት ውቂ ደብልቂ #ተሰመጠ። ክብረ ልዕልናችንም #በአሉታዊ #ተላመጠ
 
በዛ የወረራ ሰሞናት የተራረፋት የባህርዳር፤ የፍኖተሰላም፤ የዳንግላ፤ የማርቆስ፤ የደብረታቦር፤ የወረታ፤ ዬአዲስ ዘመን፤ የጎንደር ከተማ፤ የዳባት ከተማ፤ የደባርቅ ከተማወችም ትንንሽ ከተሞችን ግን ታሪካዊወችንእንደ ማንኩሳን፤ እነ እንፍራዝን ስቻቸው አይደለም። አሁንም እንደ ኮንቦልቻ፤ እንደ አጣዬ፤ እንደ ሽዋ ሮቢት ካልነደዱልን የሚል #ጦሮም አለ። የኦነግ ፖለቲካ በባህሪው መናድ አንዱ ገፁ ነው። እና እሱ ወደየሚፈልገው አቅጣጫ እሽቅድድሙ የፖለቲካ ግሽፈት ነው።
 
እንሆ ……… እኔ ከአገር ስወጣ የነበሩ ከተሞች በሽምግልና ውስጥም ሆነው እራሳቸውን እንዲያሰነብቱ ስክነትን ቁመው ይለምናሉ። ሰሚ ከተገኜ።
 
ጥሞና አዳኝ ነው።
ጥሞና ርትህ ነው።
ጥሞና ችሎትን መተርጎም ነው።
ጥሞና ትኔፋሽ ነው።
ጥሞና ለሌላውም ማዘን ነው።
ጥሞና ማግሥት ነው።
ጥሞና መሪነት ነው።
ጥሞና ጥበብ ነው።
ጥሞና የዊዝደም ሰማዬ ሰማዬት ነው። ሚስጢረ ሄኖክ። 
 
"ዝምታ ወርቅ ነው።" ብዙ ጦሮችን ቅስም ይሰብራል። መናገር፤ ጊዜ - ሁኔታ እና ቦታ ይጠይቃል። መሰዋትም ጊዜ - ሁኔታ እና ቦታ ይጠይቃል። እሳት እዬነደደ፤ ግን እሳት #የሌለበት #መሻገሪያ እያለ በእሳቱ ካልተረማመድኩ የጤና አይመስለኝም። ተናግረንም መክረንም፤ አቅም አፍሰንም አድማጭ ማግኘት አልተቻለም። ስለዚህ ዝምታን መምረጥ ግድ ይላል። እሺን ለፈራ እንብኝን እናስታጥቀዋለን እኔ እና ሊቀ ትጉኋ ብዕሬረብራናዬ። ቤተሰቦቼ የሚፈሩት ዝምታዬን ነው።
 
የእኔ እሽታ፤ የእኔ ሳቅም፤ አብሬ እንደ ቤተሰብ ለወግ መታደምም ቤተሰቦቼ በፆም በፀሎት የሚያገኙት ነው። ዝም ለእኔ ምኔ ልብላችሁ? ሥሜ ነው። ግሴ ነው። ስዋሰዌ ነው። አናባቢዬ - ተነባቢዬም ነው። እና ደክሜለት ለማያዳምጠኝ መራራ ስንብት ይሆናል። 
 
አውሮፓወች ያጥበብን ልቅና በአመት አንድ ጊዜ ይታደማሉ። በአብሮነት ገበታ። ኢሮ ቢዥን ሶንግ ኮንቴስት ይሉታል። ጥበብ እና ዘመን የሚታረቁበት ዓለም አቀፍ ትዕይንት ነው። አወስትራልያ ይታደማል። ቻይና ሙሉ መሰናዶውን በሚዲያው ያቀርበዋል። እና በራሽያ እና በዩክሬን ጦርነት ምክንያት የራሽያ የጥበብ እጩወች ለሁለት ዓመት ታገቱ። እና ሥርጉትሻ ጠዬቀች።
 
ጥበብ ማዕቀብ፤ ጥበብ እገታ ሊደአግበት አይገባም። ትውልድን የሚያገናኙ ድልድዮች ጠንክረው መቀጠል ሲገባቸው በንግግር ሊፈቱ የሚችሉ ዕድሎች የመብት ጥሰት ለምን ይፈፀምባቸዋል??? አዬደለም የእትብቴን ጉዳይ። ግን ልደመጥ ግድ ይላል። ተው፤ እረፋ። ያለፈውን ግድፈት ላፒስ ግዙለት። ቢያንስ ለእናት ለሚስት ለልጅ ይታሰብ። #አደብ ሁኑ፥ ጥሞናን ሁኑበት ሲባል አሻም ላለ፤ አቤቶ እንብኝ በዝምታ ከዝምታ ቤት በርጋታ #ርጋ ይላል። ሚስጢርነት - ይከበከባል። የእስር ፍቺን የምስራች ያልዘገቡ፤ #ግጭቱ ሠርግ እና መልሳቸው ሆኗል። የዌብ መዝናኛ ቅባዓ እንዲሆን ስለምን ይፈቀዳል? ባለ ጉዳዩ። ፍሰት። #መከደንስ ለምን ይፈራል???
"እግዚአብሔር በአንድም በሌላም ይናገራል፤ ሰው ግን አያስተውለውም።" 
 
የህዝብ #ወህታ ሁሉም ይቀናበታል። ህወሃት ኤርትራ ላይ በተከዘነው ዕምቅ የአመጽ ቡድን ነበርን የተወገደው? እእ። አልነበረም። በጣም እርግጠኛ ሁኘ ነው እምናገረው። ህወሃት እራሱም ሲሰናበት ለእሱም #ድንገቴ ነበር። ለህወሃት ባላ እና ወጋግራ ሆነው የጥገና ጋራጅ የነበሩ በተፎካካሪ ሥም ሆነ፤ በግል የሃሳብ ዕምቅ ክህሎታቸውን ለመገቡም ቢሆን ደራሽ ጉዳይ ነበር።
 
 አሁንም ሊለምዱት አልተቻላቸውም። የማይታሰብ፤ የማይታለም ታምር ነበር እና። አሁን የድል አጥቢያ አርበኛው ዶር ዓለሙ ስሜ ሲዘባነኑ፤ በመስቃ ሲራጋጡ አስተውላለሁኝ። እናም ይገርመኛል። ለዚህም የተበቃው፤ የተንጠራራው ግልምጫቸውም ህግ ሥርዓት ያስይዘወል። 
 
የሆነ ሆኖ የህወሃት ዩ100 ዓመት ህልም ክስመት የጥንስሱ መሪ፤ አደራጅ እና ፈፃሚ እግዚአብሄር ነበር። ግን #አልተመሰገነም። ስለ ተገኘው ትንፋሽም ከሊቅ እስከ ደቂቅ ሱባኤ ወስዶ #ጥሞና የወሰደ አልነበረም። ሌላው ቀርቶ በዝግታ እንዲያዳምጡ እንደ አቶ ኦባንግ ሜቶ ያሉ ሊቀ - ሊቃውንት የሰባዕዊ መብት ሞጋች እና ተንታኝ እንኳን #ሊያዳምጡኝ አልቻሉም።
 
#ስሜት በግርድፍድፋ ጥበብ አይደለም። ስሜት ጥበብ የሚሆነው ስሜትን ለማድመጥ ጥሞና ሲጎርስ ብቻ ይሆናል። ጥሞና ለኢትዮጵያ ፖለቲከኞች እና አጋር ሚዲያወች ትናንት አልነበረም። ዛሬም የለም። ነገም ፈጣሪ ይወቀው። እኔ ተማላ ባተሌ ሴት እንጂ ነብይ አይደለሁም። እንደ እህት አርቲስት አስቴር በዳኔ። 
 
የፖለቲካ ግሽፈቱ ትናንትም ነበር። ዛሬም አለ። ወደፊትም በዚህ አያያዝ ቀጣይ ነው። ግሽፈት በኢኮኖሚስቶች ትርጓሜ የህዝብ ፍላጎት እና የገንዘብ የመግዛት አቅም አለመመጣጠን ነው ይሉታል። በኢትዮጵያ ፖለቲካም ኢትዮጵያ ያላት ያልተነገረ፤ ተጽፎም ያልተጠና አቅም እና #የመሪነትህልመኞቿ የሚፍተለተሉበት ጉዞ አልተመጣጠነም። ችግሩ ባልተመጣጠነ ጉዞው የሚደቀው የሃብት ልክ እና የትውልድ ብክነትም፦ የሞራል ተስፋ ማጣት ከልኩ ያለፈ መሆኑ ነው። ገበሬ ማዳበሪያ ተከልክሎ ሰላማዊ ሰልፍ የሚወጣባት አገር???
 
የፖለቲካ ግሽፈቱ በሁሉም ዘርፍ ነው። አንዱ ይወጣ እና እከሌ "የእኛ መሪ ነው፤ እከሌ የእኛ መሪ ናት" ይላል። ሌላው ይወጣ እና "እከሌ ማለት መላው አማራ ማለት ነው። " "ወይንም እከሌ ማለት መላው ኢትዮጵያዊ ማለት ነው" ይልሃል። በሌላ በኩል የጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ሥርዓት ዲስክርምኔሽን ፈፀመ ብሎ ይሞግታል። አራባ እና ቆቦ የሆነ ጉድ።
 
ኢትዮጵያዊ ስትል፤ አማራ ስትል፤ ሴት ስትል፤ ኦርቶዶክስ ተዋህዶንም ስታክል፤ ስታካትት እኔ ሥርጉተ ሥላሴ፤ ሰብለ ህይወት አለሁበት። ስለሆነም እኔ እኔ እንጅ ውራጅ ማንነትህን፤ የለጠፍከውን እንደማልቀበልልህ ልታውቅ ይገባል። በሌላ በኩል እኔ በአንደበቴ ነው እራሴ ወስኜ መሪዬ ማለት እምችለው እንጂ አንተ ማይክ ተመቸኝ ብለህ፤ አጃቢ እረበበልኝ ብለህ ለእኔ ልትጭንብኝ ቅንጣት አትችልም። ፈፅሞ። እኔንም በሃሳብ የመምራት አቅም የለህምና።
 
ድርጅት ከኖረህ አባል የሆኑልህን ለይተህ እነሱን አቅርብ። #ዲስክርምኔሽን አትፈጽም። እራስህን - ግራ። በሌላ በኩል መላ አማራ እከሌወእከሌም አትበል። እያንዳንዱ ዛሬ ሚዲያ አለው። ስለ እራሱ ወስኖ እኔ አቶ ወይንም ወይዘሮ ወይንም ወይዘሪት እከሌ ነኝ ይበል። ያለ ውክልና ገብቶ በእያንዳንዳችን የፖለቲካ አቅም እና አቋም እና አቋም መወሰን #ዲስክርምኔሽን ነው። #ሊቆም ይገባል።
 
አብሶ ሚዲያወች እርእሳችሁ የእናንተን ምሾ በሉት ሆሆምሻምሾ በእኛ ላይ የሚጭን ሊሆን አይገባም። ጦርነትን በአካልም በመንፈስም፤ ጫካውንም በአካልም በመንፈስም፤ እስር ቤቱን በአካል በመንፈስም፤ ስደቱንም በአካልም በመንፈስም፤ የፖለቲካ መሪነቱንም በአካልም በመንፈስም አንጥረን፤ አበጥረን፤ አንተርትረን፤ ኑረንበታል።
 
ስለሆነም ማንም ሰው በእኔ የፖለቲካ አቋም እና ውሳኔ፤ የመሪነት ምርጫ የመበያን ቅንጣት አቅም ያለው ዬለም። እኔ #ባለቤቱ አለሁለት። ስፈልግ እራሴ እለዋለሁ። አቦካቶ አያስፈልገኝም። ተናገሩልኝ የምል ሴት አይደለሁም ወይንም ምላሴ አልተጠቆረም።
 
24 ሰዓት ነው እምሰራው። ቁሮ -- ልጥፍ -- ወይንም -- ውራጅ ወይንም - ማሟያ ወይንም መጣያ ለመሆን አልፈቅድም። እንደ እኔ የሚያስቡ ሚሊዮኖች ናቸው ብዬም አስባለሁ። "እኔ አቶ እከሌ ነኝ ማለት ይቻላል።" የሚዲያ ሥሙንም፤ ፕሮፋይል ፎቶውንም ባመኑበት፤ ተስፋ ባደረጉበት ሰብዕና ማድረግ ይቻላል። ያ እኔን አይጎረብጠኝም። ግን የእኔ ያልከውን ለእኔ መጫን የፖለቲካ ግሽፈትን እንደጨለጥክ ያስተረጉማል።
 
#እራስህን ቻል! አንተ በምታነኩረው ፍሬ ያለው ይሁን የለለው አልቦሽ ጉዞ እራስህን ስጠው። እኔን ሊሆን አይገባም። ልክ እንደ እኔም በዝምታ ያሉ የጨመቱ ሰወች አሉ። አትዳፈር! ዛሬ ተሰብስባችሁ ነገ ለምትበትኑት፤ ዛሬ በሴሪሞኒ ቅብጥ ቅልጥ የምትሉበት ነገ በአንጃ በምትቧከሱበት ውቂ ደብልቂ እና የደራ ገብያ እዛው እናንተ ተዶሉበት፤ ተንዶልዶሉበት።
 
እኔ መድረክ ላይም፤ ሚዲያ ላይም፤ ሥልጣን ላይም ያለ መሪ የለኝም። መሪ ይሆናሉ ብዬ እማቀርባቸው ወገኖች ይኖሩኛል። ግን መሪዬ መሆን መቻላቸው ዕድሉን አግኝተው የአይኳዟሁ እጬጌ ሲሆኑ፦ በህይወት ከኖርኩ በድርጊት አይቼ የእኔ መሪ ልል እችላለሁ። አሁን ግን አትሰቡት። እኔ መሪ የለኝም። የራሴ መሪ እኔው እራሴ ነኝ። አራት ነጥብ። 
 
ለኢትዮጵያም እምመኝላት ይህንኑ ነው። መሪዬ በምትለው መሪ እንዲሰጣት። እራሷ መርጣ እራሷ ፈቅዳ። ዲስክርምኔሽን እንዳይፈፀምባት እፈልጋለሁ ለልዕልቴ። ኢትዮጵያ አጽናኝ መሪ በተፈጥሯዋ ልክ ትሻለች። ፍልስፍናው፤ ሳይንሱ ኢትዮጵያኒዝም የሆነ። መሪነት ሚስጢሩ ከሚስጢር ጋር በህይወት መኖር ነው። 
 
ተስፋዬ አምላኬ ነው። አምላኬ ተስፋዬን ይባርከዋል። ይቀድሰዋልም። ጦርነትን በጭራሽ አልፈልግም። የጦርነት ህልመኛ በፍፁም አይደለሁም። ትውልድ በጡንቸኛ እንዲከተከት አልሻም። ብዕሬ እና ብራናዬ የሠራውን፤ የሚሠራውን በልኩ በፀጋው እና በጥሪው ልክ የተፈጥሮ፤ የሰማያዊ ህግጋትን ተከትሎ ይከውናል። ይህ ማለት ትዕቢተኛው ማህበረ ኦነግ የሚፈፅመውን አፈና ለመከላከል ዞር ማለቱ የተገባ መሆኑን ግን አምንበታለሁ። ነገን ለማዬት ስልታዊነት። 
 
በእጅ ያለ ዕንቁ አለ። ህዝቤን ለማገዶ፤ ቅርሴን ለባሩድ የማያቀብል። የ12993 ተማሪወች የፈተና ዕገዳ ይጠዘጥዘኛል፤ የማዳበሪያ እገዳ በይሁንታ አልቀበለውም። በልኩ ካለ ባሩድ ጢስ እና ካለ ቀረርቶ እዬተሠራበት ነው። ምኞቴ ከእንግዲህ ብዙ ማህፀን እና አብራክ እንዳይጨስ፤ እንዳይነድ፤ እንዳይማገድም ነው። በተለይ እስር ቤት ያሉ ወገኖቼ አንድ ሱናሜ ቢነሳ በእጅ ስላሉ እነሱ ምን ይሆኑብኛል ብዬ አስባለሁ። ይህንንም አሳውቄያለሁኝ። 
 
እናንተማ ዛሬ ተፈጥሮ ነገ ምራቅ ለሚሆን ፋንታዚ ለካቴና ከበቁትም ያለ እርህራሄ የእኛም መንፈስ አለበት ስትሉ ድርብ አንጀታችሁን አስተውያለሁ። በሃሰት ፈጥሮ ለተከሰሰ መንፈስ የእናንተንፈንታዚ ክብር ለማቀዳጀት ወስዳችሁ ስትማግዟቸው ቅጭጭ አላላችሁም። ቢሆን እንኳን ፖለቲካ እንዲህ በዝልኝ መረማመጃ ሊሆን አይገባም ነበር። 
 
የሚገርመኝ ትንፋሽ ሲገኝ ደግሞ በኮፒ ራይቱ ትርምስምሱ ነው። 
 
ውቦቼ እንዴት አደራችሁ? እንደምን ዋላችሁ? አይዞን። እርጋታ። ስክነት። ማድመጥ ይሁን መሪያችን።
ቸር ሁኑልኝ።
 
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
14/06/2023
 
ዕውነት ለራሱ አይሰንፍም።
ትዕግሥት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል።
ፍቅርም ሲያልቅ ትዕግሥት ይሰደዳል።

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።