ዬፀጋዬ ራዲዮ ከተመሠረተ እንሆ #መስከረም 18/2023 እኤአ #ሙሉ 15 (፲፭) ዓመት ዛሬ ሞላው።
"ምንም እንኳን በለስም ባታፈራ በወይን ሐረግ ፍሬ ባይገኝ፤
የወይራ ሥራ ቢጓደል፤ እርሾችም መብልን ባይሰጡ፤ በጎች
ከበረት ቢጠፋ፤ ላሞችም በጋጥ ውስጥ ባይገኙ፤ እኔ ግን
አደርጋለሁ። ጌታ እግዚአብሄር ሃይሌ ነው።"
(ትንቢተ ዕንባቆም ምዕራፍ ፫ ከቁጥር 17 -18 )
ይህ ቃለ ወንጌል የህይወቴ ማኒፌስቶ ነው። ቤተሰቦቼ የሰብሊ መንገድ ይሉታል።
ለቅኖች ህሊና ላላቸው ወገኖቼ ብቻ እንዲያነቡት የተፃፈ ነው። ከዕውነት ጋር ለሚዘልቁት ወጀብ በመጣ ቁጥር ለማይወዛወዙት ጽኑ ዕውነቶች። ሼር አድርጉት ብዬ አላስቸግራችሁም። ታሪክ መሠረት መያዝ ስላለበት ለዛ የተፃፈ ነው።
የፀጋዬ ራዲዮን መንፈስን የሚያግዙ ሁለት ዩቱብ ቻናሎች፤ እና አንድ ብሎግም ሊንኮችን አያይዣለሁ። አመሰግናለሁ።
ልክ የዛሬ 15 ዓመት ይህ ቀን የፀጋዬ ራዲዮ ስጀምር ስደተኛ ካንፕ ውስጥ ነበርኩኝ። ቴሌቪዥን መስመር፤ የስልክ፤ የኔት ግንኙነት፤ የኮንፒተር አክሰስ በለለበት ሁኔታ በዙሪክ ክ/ አገር በአንደልፊንገን ዞን በክላይነአንደል ፊንገንባድ የስደተኛ ካንፕ ውስጥ ሆኜ የፀጋዬ ራዲዮን መሠረትኩኝ።
ከዛ በፊት በዛ ሁኔታ ላይ ሆኜ ቀድሜ ለአንድ ዓመት ጥናት ያደረግኩበትን የፀጋ ድህረ ገጽ በ2008 እኤአ በወርሃ ሰኔ 18 የፀጋዬ ድህረ ገጽን መሠረትኩኝ። በዕለቱ በወቅቱ ጠንካራ የነበረው የዛሬይቱ ድህረ ገጽ አትሞት ነበር። በታህሳስ ወር መጨረሻ የአባይ ሚዲያ መሥራች ብሩኬ በድህረ ገፁ ላይ ሊንኩን ፈቅዶለት ነበር። እኔ እና ብሩኬ ኮፐን ሀገን ለአንድ አውሮፓዊ ሰላማዊ ሰልፍ እና ውይይት እዛ ተገናኝተን ነበር።
እናም የአንዲት ባተሌ ድህረ ገጽ እንደምን ሊንኩን አልፈቀድክም ብዬ ለጠዬቅኩት የሰጠው መልስ ፈጣን ቅን አወንታዊ መልስ ነበር። የኢትዮጵያ ችግር መቀጠሉ ግን አሁንም ያሳዝነኛል። አባይ ሚዲያ እና የዛሬይቱ ሁለቱም ከፀጋዬ ድህረ ገጽ ቀደምወ የተፈጠሩ ነበሩ። ዘሐበሻ ከእኛ በጣም ዘግይቶ ነበር የተፈጠረው። የሆነ ሆኖ ሁለቱም ለሰጡት አትኩሮት ምንጊዜም አመሰግናቸዋለሁ።
የፀጋዬ ራዲዮ የፀጋዬ ድህረ ገጽን ለማገዝ የተደራጀ ነበር። አሁን የፀጋዬ ራዲዮን የከበቡሽ ልሳንወርቅ ሚዲያ እንደሚያግዘው ሁሉ። በፀጋዬ ራዲዮ እና በፀጋዬ ድህረ ገጽ መሀከል የዓላማ እና የራይ ልዩነት አልነበረም። ተወራራሽ ነበር።
የነበረው ልዩነት የፀጋዬ ድህረ ገጽ በቦርድ ነበር የሚተዳደረው። ተሳትፎውም ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ያስተናግድ ነበር። የልጆች ፕሮግራም ነበረው። ልጆችም የቦርድ አባል ነበሩበት። የሆነ ሆኖ በወል የሚሠሩ ጉዳዮች የኃይል አሰላለፍ ሲለወጥ ችግር ይገጥማቸዋል። በግል የሚሠራው ግን ሚዛኑን ጠብቆ ይጓዛል። ለዚህም ነው ብቻዬን የምሠራው የፀጋዬ ራዲዮ ለ15 ዓመት የቀጠለው። ፈተናው አንድ የፖለቲካ ድርጅት ከሚገጥመው በላይ ነው። በዬጊዜው ፈተናው እያገረሸ የራዲዮ ፕሮግራሙን ለማዘጋት የክፋነት ጥንስስ አለ። በተደጋጋሚ ክስ ተመስርቶበታል። መስተጓጎል ገጥሞታል። ወደፊትም ይገጥመዋል። እስከቻልኩ ድረስ ለማስቀጠል እሞክራለሁ።
የፀጋዬ ራዲዮ በራዲዮ ሎራ በ97.5 መካከለኛ ሞገድ በወር ሁለት ጊዜ በዕለተ ሃሙስ እኤአ ሰዓት አቆጣጠር ከ15-16 ሰዓት ለአንድ ሰዓት ያህል በአማርኛ ቋንቋ ይቀርባል። በጣም የተለዬ ሁኔታ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ ችግር ሲገጥም በጀርመንኛ መጠነኛ መለናዶ ይኖራል።
ቀደም ባለው ጊዜ በተፈጥሮ ሙዚቃ ይታጀብ ነበር። በወንዞች፤ በውቅያኖስ፤ በወፎች ዝማሬ ነበር እመሠራው። አሁን አሁን በኢትዮጵያ የመሣሪያ ሙዚቃ ቅንብርም ጭምር መሥራት ጀመሪያለሁ። የሙዚቃው ምት ተወዳጅ በመሆኑ አልፎ አልፎም በዬሦስት ወሩ ክላሲካል ሙዚቃ ብቻ ማቅረብን በዚህ ዓመት ጀምሬያላሁ።
ሌላው ቋንቋውን የማይሰሙት ሁሉ በመደበኛ ያዳምጡታል። አማርኛ ቋንቋ አውራው ይስባል፤ ይማርካል እንደ ሜድሽን ነው ይሉታል። የፀጋዬ ራዲዮ በበርካታ ጉዳዮች ላይ እዬተጋበዘ ልምዱን አካፍሏል። እዬደከመኝ ሲመጣ ነው የቀረው እንጂ ተገቢው አክብሮት፤ ተገቢው ዕውቅና ተነፍጎት አያውቅም።
የፀጋዬ ራዲዮ በስክነት፤ በተረጋጋ መንፈስ፤ በሰባዕዊ መብት በሴቶች በህፃናት በነፃነት ዙሪያ ትውልድን በሚያበረክቱ የአብሮነት ድባቦች ላይ፤ በተወዳጁ ባህላችን፤ ወጋችን፤ ልማዳችን፤ ታሪካችን፤ ሞራላችን፤ ደግነታችን ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ዙሪያ አተኩሮ ይሠራል። ሚዲያው የዜና ሚዲያ አይደለም። ዜና የሚቀርብበት እራሴ ተገኝቼ አይቼ፤ አዳምጬ የገመገምኩት ብቻ ነው የሚቀርብበት። ከዛ ውጪ የትውስት ዜና ሚዲዬዬ አስተናግዶ አያውቅም።
እምዋሰው በታሪካችን ዙሪያ፤ በትውፊታችን ዙሪያ፤ በፓን አፍሪካኒስት መሥራችነት ዙሪያ ከሸገር 102.1 የማገኛቸውን የትንፋሽ ውጣ ውረዶችን አርሜ፤ በጥንቃቄ ለራዲዮ መሰናዶ በሚመች መልኩ ጥርት ባለ ሁኔታ አሰናድቼ አቀርብበታለሁ። ከዛ በተረፈ በራሴ ግጥሞች፤ የወግ ገበታወች ዕይታወች ዙሪያ መሰናዶው ይቀርባል። በተለይ ለሚታሠሩ ወገኖቼ ሙሉ 15 ዓመት ድምጽ ሆኗል ራዲዮ ፕሮግራሙ።
መንፈሱ የጋሼ ፀጋዬ በመሆኑ በታሪኩ፤፦በለብዕናው፤ በአሻራው ዙሪያ ግድፈት፤ መጓጎል እንዳይከሰት እጅግ በጥንቃቄ ነው እምሠራው። ከዚህ ሁሉ የሥራ ዘመን አንድ ቀን ብቻ በኦፕራሲዮን ምክንያት ተደግሞ ተሠርቷል። ከዚያ ውጪ ሁልጊዜ እሸት ፕሮግራም ይቀርባል። ዕውነት ለመናገር በጥረቶቼ፤ እና በትጋቶቼ ሁሉ ተምሬያለሁኝ።
እኔ በፖለቲካ ህይወቴም ሆነ በራዲዮ ጋዜጠኝነት ህይወቴ አናጋፋ ዋርካ ሊቀ ሊቃውንታት ጋር ስለ ሠራሁኝ ያገኜሁዋቸውን ዕውቀቶች ሁሉ ምራቁን ለዋጠ ተግባር አውዬዋለሁ። በተርገበገበው ሁሉ ባለመርገብገብ፤ ከዘለለው ጋራ ባለመዛለል፤ ከጎረፈው ጋር አብሮ ባለመጉረፍ የራዲዮው ሥያሜ ከተግባሩ ጋር ስምም ይሆን ዘንድ በጠራ መሥመር ከዬትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ጋር ሳልለጠፍ፤ ምንም ዓይነት የፋይናንስ ድጋፍ ሳልጠይቅ በራሴ የጊዜ፤ የገንዘብ፤ የመንፈስ መዋጮ የእኔ በምለው ዕውነት እና መርህ ተኮር ተግባር ከውኜበታለሁ።
በጭምቷ በቅድስቷ አገረ ሲዊዘርላንድ የታላቁን የቅኔ ልዑል የብላቴ ሎሬት ፀጋዬን ሥም ከፍ ባለ ደረጃ እና ልዕልና አሻራውን ተክያለሁ። ይህንን አፍርሼ ድካሜን ከንቱ የማደርግበት ምንም አመክንዮ ስለለ እስከ መጨረሻዋ አቅሜ ድረስ የከበረ ተግባሩን አስቀጥላለሁ ብዬ አስባለሁኝ።
ሲዊዘርላንድ ውስጥ በተለያዩ ሁኔታወች የእናት አገሬ የኢትዮጵያ አሻራን አስቀምጫለሁኝ። ስድስቱ መፃህፍቶቼ በሲዊዝ የኢንተግሬሽን ቤተመፃህፍት ብሄራዊ እና አውሮፓዊ ስብሰባወች ላይ መግለጫ ተስጥቶባቸዋል። በመፃህፍት ቤቶችም ይገኛሉ መፃህፍቶቼ። በሌላ በኩል በፊደላት ቀን ኢትዮጵያ ከተመረጡት አገሮች አንዟ ነበረች። በቪንተርቱር ቤተ መፃህፍት በዲፓርትመንት ሦስት ውስጥ ከአፍሪካ አገሮች ጋር ከነበረው መዳበል የራሷ ክፍል እንዲኖር ተደርጓል።
ቀድም ባለው ጊዜ አማርኛ ቋንቋ ትረካ፤ ስድ ንባብ እናግጥም፤ ባህላዊ የሥዕል ጋለሪ ላይ በሙሉ አቅሜ ተሳትፌ እናት አገሬን ኢትዮጵያ ከእነ ግርማ ሞገሷ አስተዋውቄያለሁ። በዚህ ሁሉ መባተል ከፀጋዬ ድህረ ገጽ በስተቀር አጋዥ እረዳት አይዞሽ ባይ አልነበረኝም። የለኝምም። አጋዤ እረዳቴ አበረታቼ የቅንነት አባት መዳህኒዓለም እና ቅድስት ድንግል ማርያም ብቻ ናቸው።
ቀጣዩ ዓመት ራዕዩም ግቡም ወጥ ነው።ምንም ውራጅ ቅጥልጥ አይኖርም። እንዲያውም በመልካምነት በቅንነት በትውልድ ቡቃያ ቀጣይ መስመር በጎ እና ርህርህናው ዘለግ ያለ ተግባር እከውናለሁ። ጠቃሚ ነገሮች ሳገኝ ከሸገር እወስዳለሁኝ። ይህ የሚሆነው በህይወት ከኖርኩኝ ብቻ ነው።
ባልፍም የማልፀፀትበት ተግባር በመፈፀሜ እረፍቴ በዚህ በኖርኩበት ገዳማዊ ከተማ በቪንተርተሩ ይሆናል። ሰላማዊ እንደሚሆንም ተስፋ አደርጋለሁኝ። የሚያፎካክር፤ የሚያወዳድር ትውልድን የሚያድን የመልካምነት ሥራ ሊሆን ይገባል። ዕውነት አይዝግም። ዕውነት አያብልም። መርህም አይሮጥም። መርህ ሰክኖ ዕውነትን ለልዕልና ልቅና ያበቃል ያፀድቃልም።
ሰሞኑን አቶ ሽመልስ አብዲሳአሮጊቷን ኢትዮጵያ ቀብረናታል ብለዋል። ጋሼ ፀጋዬ መንፈሱንም ጭምር ስለመሆኑ አስተዋዮች ልብ ልትሉት ይገባል። ፍቅር አያረጅም። ፍቅር አይጠወልግም። ኢትዮጵያ ፍቅር ናት አታረጅም። አዛውንት ግን እንደ አሻተች አብባ አሸንፋ አስተምራ የምትመራ ግርማዋ የማይደፈር የአፍሪካ ጉልላት ናት። እኔ ለአቶ ሽመልስ አብዲሳ እምለው ሲያምረወት ይቅር ነው።
ኢትዮጵያ ረቂቅ ናት።
ኢትዮጵያ ሳይንስ ናት።
ኢትዮጵያፍልስፍና ናት።
ኢትዮጵያ ፋክት ናት።
ኢትዮጵያ ዩንቨርስም ናት።
ኢትዮጵያ መንፈስም ናት ቅዱስ።
ኢትዮጵያ ሚስጢርም ናት።
ኢትዮጵያ ድንጋጌም ህግም ናት።
ኢትዮጵያም ሙያም ናት። ልትጠና የሚገባት የምርምር ማዕከል። ሊማሯት የሚገባ ሳብጀክት፤ ሊያጠኗት የሚገባ የፊደል ገበታ። ኢትዮጵያ ትናት ነበረች።ዛሬ አለች። ነገ ከነገ ወዲያ ከዚያም ወዲያ ትቀጥላለች። አብባ ተሸልማ። ሚሊዮኖች የሚናፍቋት የሚሿት የሚመኟት የራሷ ያላት የውስጥነት ውስጥ ቀይ የደም ሴል።
በመጨረሻ የጋሼ ፀጋዬ ገብረመድህን ልጅ ክብርት ዶር. አደይ ፀጋዬ በሥጋ ተለይታናለች ብርቱ ጀግና በሙያዋ እንደነበረች ሰምቻለሁ። ድሮስ የዛ ቀንዲል የአብራክ ክፍያ። በወቅቱ እምችልበት ሁኔታ ላይ አልነበርኩም። ለመላ ቤተሰቡ በዚህ አጋጣሚ መጽናናትን እመኛለሁ።
የእኔ ክብሮች ደህና ዋሉልኝ። አሜን።
የእኔ ውዶች ኑሩልኝ። አሜን።
የእኔ ክብሮች ደህና አምሹኝ። አሜን።
የእኔ ክብሮች ደህና እደሩልኝ። አሜን።
"ሥራወችህ ድንቅ ናቸው።"
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
18/09/2023
"ጥበብ ቤቷን ሠራች።
ሰባት ምሰሶም አቆመች።"
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ