ጨካኝነት ለመሪነት ሊያበቃ አይችልም።

 

Shared with Public

ጨካኝነት ለመሪነት ሊያበቃ አይችልም።
"የሰው ልብ መንገድን ያዘጋጃል
እግዚአብሔር ግን አካሄዱን ያቃናለታል።"
(ምሳሌ ፲፮ ቁ ፱)

አይዟችሁ የነጠፈበት፤ ማጽናናት ድርቅ የመታው፤ በቀውስ በጀት የሚተዳደር፤ በቅጥፈት ቦይ የሚፈስ፤ ቀደምትነትን የሚጠዬፍ፤ ህዝብን የሚጠላ የሚያሳድድ - የሚያሳቅቅ - የሚያቃልል- የሚያናንቅ መንፈስ ለመሪነት ለዛውም ሁለመናዋ በስጦታ ለከበረው የኢትዮጵያ መሪነት የሚታሰብ አልነበረም። ግን ተያይዘን ባበድንበት ወቅት በፈቃድ ሆ! ብለን ተቀበልን።
አሁንም ተመሳሳይ ግድፈት ተፈፅሞ አረንቋ ውስጥ ተስፋችን እንዳይዘፈቅ ብርቱ ጥንቃቄ፤ የፀሎት እና የድዋ ጥረት ይጠይቃል። ካሳለፍነው መከራ መጪው ይገዝፋል። ስለዚህም በሁሉም መስክ ህሊናን አብቅቶ ማሰናዳት ይጠይቃል። ይህ ማለት ምን ማለት ነው? ይህ ማለት እያንዳንዷ እርምጃችን ማስተዋልን ሊጠጣ ይገባዋል።
ፈቃዱ ቢኖር አቅሙ፤ ዕውነቱ ቢኖር ተመክሮው፤ ጽናቱ ቢኖር ልምዱ ሁሉም በዬዘርፋ ሊፈተሽ ይገባል። መሪነት በመፈለግ እና በመሻት ብቻ ሳይሆን ቅባዕም ይጠይቃል። ቅባዕው ከሌለ አይሆንም። እያንዳንዱ እራሱን ለመሪነት የሚያጭ ፖለቲከኛ ሁሉ እራሱን ገምግሞ በራሱ ዳኝነት እንቅፋት እንዳይሆን እራሱን መግራት ይገባዋል።
ሁሉም ኑሮ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት ቅባው ከሌለ ተያይዞ መንኮት ይሆናል። ይህ ሁሉ ግብር እዬተገበረ ነገን የተሰናዳ ማድረግ እንዲቻል ሆኖ ካልተደራጄ ደግሞ መዛገጥ ይሆናል። ከሁሉም ልዩ ጥንቃቄ የሚሻው ጉዳይ በመፈቃቀድ ላይ የሚፈጠር ሥርዓት ለማቆም መስማማት መቻል ይሆናል።
በመዘላለፍ፤ በመወራረፍ፤ በመዘነጣጠል የምናተርፈው አገርም ትውልድም አይኖርም። አክብሮ መነሳት። አክብሮ መሞገት። አክብሮ የተሻለ ሃሳብ ማፍለቅ። አክብሮ መነጋገር፤ አክብሮ አቅጣጫን መንደፍ፤ አክብሮ አቅጣጫን ማሳወቅ ያስፈልጋል። ሁልጊዜም በምንጽፋቸው፤ በምንናገራቸው አንደበቶች ሁሉ የሚሰነዘሩ ሥንኛት አክሰሱ ያላቸውን ልጆች፤ ታዳጊ ወጣቶች ታሳቢ ያደረጉ ሊሆን ይገባል። ይህን አልጀመርነውም። ግን መጀመር ያለብን በኽረ ጉዳይ ነው።
አብሶ ጭካኔን የሚያስፋፋ፤ ጥላቻን የሚያለመልሙ፤ ተስፋን የሚኮረኩድ የአነጋገር ዘዬወች ሁሉ መግራት ግድ ይላል። የመጣንበት ጉዞ ሁሉ ትውልዱን ያሰበ አልነበረም። ነገን ስናስብ ዛሬን ሳናስከፋ ሊሆን ይገባል።
ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ ለመሪነት ይመጥናሉ ብዬ አላምንም። የጎደላቸው አቅም ቢሟላም ሰውኛ ልቦና፤ ተፈጥሯዊ ህሊና፤ ርህራሄዊ ሰብዕና እንደ መኪና ዕቃ ልንገጥምላቸው አንችልም። ሳናውቃቸው ተስፋ ብንጥልባቸውም ስናዋቃቸው ተስፋችን ጥግ አጥቷል ብለን በፈቀድነው የትግል ስልት መታገል ግድ ይሆናል። እኔ ብዕር ነው ያለኝ። በብዕሬ እሞግታቸዋለሁኝ። ተጠጋግነውም ሊድኑ አይችሉም።
እኔ ከመነሻውም ጀምሮ እምታገለው ለሥር ነቀል ለውጥ ነው። ለኢትዮጵያ ፍፁም ሰዋዊ፤ ፍፁም ተፈጥሯዊ የሆነ ሥርዓት ያስፈልጋታል። የትንኝ ያህል ክብር ያጣው የሰው ዘር እልቂት ያለምንም ቅደም ሁኔታ መቆም አለበት። ለአዲስ ሩህሩህ ሥርአት፤ ለአዲስ አጽናኝ ሥርዓት ልቦናችን መክፈት ይኖርብናል። ቲሙ እራሱ ብክል ነው። ፀረ ሰው፤ ፀረ ተፈጥሮ።
እግዚአብሔር ይስጥልኝ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
19/10/2023
ዕውነት ጋራጅ የለውም።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።