አማራ ክልል:- ለወራት የቀጠለው የትጥቅ ግጭት ዐውድ እና አሉታዊ የሰብአዊ መብቶች እንድምታው

አማራ ክልል:- ለወራት የቀጠለው የትጥቅ ግጭት ዐውድ እና አሉታዊ የሰብአዊ መብቶች እንድምታው

October 30, 2023 Press Release

ተፋላሚ ኃይሎች ሲቪል ሰዎችንና ንብረቶችን፣ የሕዝብ አገልግሎቶችን እና መሠረተ ልማቶችን ዒላማ ከማድረግ ሊቆጠቡ፣ መንግሥት የማኅበራዊ አገልግሎቶች እዲቀጥሉ አስቻይ ሁኔታ ሊፈጥር ይገባል



የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) በአማራ ክልል የቀጠለው የትጥቅ ግጭት ላስከተለው መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ዘላቂ እልባት ለመስጠት ሰላማዊ መፍትሔ ማፈላለግን ጨምሮ፣ በሲቪል ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመከላከል የሚያግዙ አፋጣኝ እርምጃዎች እንዲወሰዱ በተለያየ ጊዜ ባወጣቸው መግለጫዎች ማሳሰቡ ይታወሳል። ኮሚሽኑ ግጭቱ በሰብአዊ መብቶች እና በማኅበራዊ እንቅስቃሴ ላይ ያስከተለውን አሉታዊ ውጤት በቅርበት መከታተሉን ቀጥሏል፡፡ በዚህም መሠረት በተለይም የሚመለከታቸውን መንግሥታዊ ኃላፊዎችን፣ በግጭቱ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎችን፣ የዐይን ምስክሮችን፣ተጎጂዎችንና የተጎጂዎች ቤተሰቦችን በማነጋገር መረጃዎችንና ማስረጃዎችን ሲያሰባስብ ቆይቷል።

ይህ መግለጫ ይፋ እስከተደረገበት ጊዜ ድረስ በክልሉ ብዙ ወረዳዎች ውስጥ የትጥቅ ግጭት የተከሰተ ሲሆን፣ ከሐምሌ ወር 2015 .. ጀምሮ ባለው ጊዜ ውስጥ የአማራ ክልል ሁሉም ዞኖች በተለያየ ደረጃና ጊዜ የትጥቅ ግጭት ተካሂዶባቸዋል። በተጨማሪም እነዚህ አካባቢዎች ወይም ወረዳዎች በአንድ ወቅት በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች፣ በሌላ ወቅት በታጣቂው ቡድን (በተለምዶ ፋኖ በመባል የሚታወቀው) ቁጥጥር ሥር ውለዋል። የትጥቅ ግጭቱ በአንዳንድ አካባቢዎች በከባድ መሣሪያ እና አልፎ አልፎ በአየር/ድሮን ድብደባ ጭምር የታገዘ ነው።

በግጭቱ ዐውድ የአየር/ድሮን መሣሪያን ጨምሮ በከባድ መሣሪያዎች ጥቃት የተነሳ በሲቪል ሰዎች ላይ ሞት እና የአካል ጉዳት የደረሰ ሲሆን፣ ሰዎች መኖሪያ አካባቢያቸውን ጥለው ለመሸሽ ተገደዋል። ለምሳሌ በሰሜን ሸዋ ዞን፣ በረኸት ወረዳ፣ መጥተህ ብላ ከተማ ጥቅምት 5 ቀን 2016 .. በተፈጸመ የድሮን ጥቃት የአንድ ዓመት ከሰባት ወር ሕፃንን ጨምሮ በርካታ ሲቪል ሰዎች እንደተገደሉ እና የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው፤ በደብረ ማርቆስ ከተማ ጥቅምት 8 ቀን 2016 .. በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ደግሞ ቢያንስ 8 ሲቪል ሰዎች እንደተገደሉ፣ እንዲሁም በደንበጫ ከተማ ጥቅምት 3 ቀን 2016 .. በከባድ መሣሪያ ድብደባ ምክንያት ሲቪል ሰዎች ላይ የሞትና የአካል ጉዳት መድረሱን ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎችና የዐይን ምስክሮች አስረድተዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች ጥቃትን አልያም ግጭትን በመሸሽ ነዋሪዎች ሙሉ በሙሉ ከቀያቸው ተፈናቅለው በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ለማረጋገጥ ተችሏል። በምንጃር ወረዳ የአውራ ጎዳና ጎጥ ነዋሪዎች ከመስከረም 6 ቀን 2016 .. ጀምሮ ከቀያቸው ተፈናቀለው ቢያንስ 3000 የሚሆኑት አሞራ ቤቴ ቀበሌ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤትና ክፍት ሜዳ ላይ (በዛፍ ሥር) ተጠልለው የሚገኙ ሲሆን፣ ሌሎች ቁጥራቸው ያልታወቀ መተሃራና አዋሽን ጨምሮ ወደ የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለዋል። ለተፈናቃዮች የተወሰነ ድጋፍ በማኅበረሰቡና እና በአንድ ተራድዖ ድርጅት የተደረገ ቢሆንም፣ በቂ ባለመሆኑ በአሳሳቢ ሁኔታ እንደሚገኙ ለመረዳት ተችሏል። የነዋሪዎችን መፈናቀል ተከትሎ ሰብላቸው እንደወደመ፣ ንብረታቸው እንደተዘረፈ፣ የቤቶቻቸው ጣራያ እና በር እየተነቀለ እንደተወሰደ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ቤቶቻቸውን ከአጎራባች ክልል በመጡ ኃይሎች በኮንስትራክሽን መሣሪያዎች ጭምር ማፍረስ እንደተጀመረ ኢሰመኮ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎችና የመንግሥት ኃላፊዎች ያስረዳሉ።

በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የሚፈጸሙ ከሕግ ውጭ የሆኑ ግድያዎች አሳሳቢነት ኮሚሽኑ በመስከረም 4 ቀን 2016 .. ባወጣው መግለጫ ማሳወቁ የሚታወስ ነው። ሆኖም በተለይም በመንግሥት የጸጥታ ኃይል አባላት የሚፈጸሙ ከሕግ ውጪ የሆኑ ግድያዎች አሁንም መቀጠላቸውን ኢሰመኮ ተዓማኒ መረጃዎችን እየተቀበለ ይገኛል። ግጭቱ በተካሄደባቸው አካባቢዎች የመንግሥት የጸጥታ አካላት በመንገድ ላይ ወይም ቤት ለቤት ፍተሻ በማድረግ ከያዟቸው በርካታ ሲቪል ሰዎች ውስጥ ፋኖን ትደግፋላችሁ፣ ለፋኖ መረጃ ትሰጣላችሁ፣ መሣሪያ አምጡ፣ የተኩስ ድምጽ ስለተሰማበት አቅጣጫ መረጃ ስጡ በሚልና ይህንን በመሰሉ ምክንያቶች ከሕግ ውጭ የሆኑ ግድያዎች መፈጸማቸውን የሚያሳዩ ተዓማኒ መረጃዎች ለኮሚሽኑ ደርሰውታል። እንደማሳያ በባሕር ዳር ከተማ፣ ሰባታሚት አካባቢ መስከረም 29 እና 30 ቀን 2016 .. ሦስት ወንድማማቾችን ጨምሮ በርካታ ሲቪል ሰዎች፣ በሰሜን ጎጃም ዞን፣ አዴት ከተማ መስከረም 29 ቀን 2016 .. ፍልሰታ ደብረ ማሪያም የሚኖሩ 12 የአብነት ተማሪዎችን ጨምሮ ሌሎች ሲቪል ሰዎች፣ በምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ አማኑኤል ከተማ ጥቅምት 3 ቀን 2016 .. ቢያንስ 8 ሲቪል ሰዎች በቤት ለቤት ፍተሻ እንደተገደሉ ለመረዳት ተችሏል። እንዲሁም በምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ ጎንቻ ሲሶ እነሴ ወረዳ፣ ግንደወይን ከተማ ሞጣ በር ተብሎ በሚጠራ አካባቢ መስከረም 18 ቀን 2016 .. አንድ በጥይት የቆሰለን ግለሰብ እናቱና እህቱ በባጃጅ አሳፍረው ወደ ሕክምና ተቋም በመውሰድ ላይ እያሉ፣ የመንግሥት የጸጥታ አካላት ባጃጁን አስቁመው ሁሉንም ተሳፋሪዎች ካስወረዱ በኋላ የቆሰለው እኛን ሲዋጋ ነው በሚል ምክንያት የባጃጅ አሽከርካሪውን ጨምሮ አራቱን ሰዎች በጥይት እንደገደሏቸው ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች አስረድተዋል።

በባሕር ዳር፣ በፍኖተሰላም፣ በጎንደር  እና በወልድያ ከተሞች በትጥቅ ግጭቱ ቆስለው ሕክምና ሲከታተሉ የነበሩ የተወሰኑ ሲቪል ሰዎችና የታጣቂ ቡድኑ አባላት በመሆን በመንግሥት የጸጥታ አካላት የተጠረጠሩ ሰዎች ሕክምናቸው እዲቋረጥ ተደርጎ ወዳልታወቀ ስፍራ ከተወሰዱ በኋላ፣ ከፊሎቹ ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ወደ ሕክምና ተቋማቱ ሲመለሱ ቀሪዎቹ ያሉበት ሁኔታ ይህ መግለጫ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ማረጋገጥ አልተቻለም።

በሌላ በኩል በየደረጃው የሚገኙ ሲቪል የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች፣ ግድያዎችና እገታዎች በታጠቁ ኃይሎች ተፈጽመዋል። ለምሳሌ መስከረም 28 ቀን 2016 .. የአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢን ጨምሮ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ከባሕር ዳር ወደ ደብረ ታቦር ሲሄዱ አለምበር ከተማ አካባቢ በታጣቂዎች ተገድለዋል። በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ማረሚያ ቤቶችና ፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ታራሚዎችና ተጠርጣሪዎች እንዲያመልጡ ተደርጓል።

ኮሚሽኑ ባደረገው ክትትል በተለይም ከመንግሥት ተቋማት ጭምር በሚደርሱት መረጃዎች መሠረት በግጭቱ ዐውድ የሚፈጸሙ የአስገድዶ መድፈር ድርጊቶች በጣም አሳሳቢ እና በአፋጣኝ ተገቢው ምርመራ ተደረጎ እርምጃ ሊወሰድበት የሚገባው ነው። የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት በተለያዩ የጤና ተቋማት መድረስ የቻሉትን ተጎጂዎች ቁጥር ብቻ መሠረት በማድረግ፣ ከሐምሌ ወር 2016 .. ጀምሮ ይህ መግለጫ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ቢያንስ 200 የአስገድዶ መድፈር ተጎጂዎች በጤና ተቋማት ተመዝግበዋል፤ ከተጎጂዎች መካከልም የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ሴቶች እና የጤና ባለሞያ ሴቶች ጭምር ይገኙበታል።

ከትጥቅ ግጭቱ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ሲቪል ሰዎች እና የሲቪል የንግድ እና የመሠረተ ልማት ተቋማት ላይ ዝርፊያ፣ የማሳ ላይ ሰብል ውድመት ጨምሮ በሲቪል ሰዎች፣ በሕዝብ እና በመሠረተ ልማት ላይ ጉዳት ደርሷል። ሕፃናት ከትምህርት ውጪ መሆናቸው እና በአንዳንድ አካባቢዎች የትምህርት ተቋማት ለወታደራዊ አገልግሎት መዋላቸው አፋጣኝ ትኩረት የሚሻ ነው። የባለሞያዎች ማኅበራት እና የሕክምና ተቋማቱ በይፋ እንዳስታወቁት የማኅበራዊ አገልግሎትና የሕክምና ተቋማት አገልግሎት በማቋረጣቸው ምክንያት፣ ነዋሪዎችን፣ በአማራ ክልል የተጠለሉ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን እና ስደተኞችን ለተባባሰ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የሚያጋልጥ ነው። ለምሳሌ በደቡብ ጎንደር ወረታ እና እብናት የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ለወታደራዊ አገልግሎት/ካምፕ ሲውሉ የነበሩ ሲሆን፣ በሸዋ ሮቢት ከተማ የደጃዝማች ተሰማ እርገጤ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ በጀውሀ ከተማ የጀውሀ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እና በብቸና የበላይ ዘለቀ መሰናዶ ትምህርት ቤት ይህ መግለጫ ይፋ እስከተደረገበትም ወቅት ድረስ ለወታደራዊ አገልግሎት መዋላቸው ተገልጿል። የአዴት ሆስፒታል በደረሰበት ዘረፋና ጉዳት አገልግሎት መስጠት ያቆመ ሲሆን፣ የፍኖተሰላም ሆስፒታል በደረሰበት ጥቃት እንዲሁም በባሕር ዳር የሚገኘው ጥበበ ግዮን ሆስፒታል በሠራተኞች፣ ታካሚዎችና አስታማሚዎች ላይ በደረሰው ወከባ፣ ድብደባና እስራት ምክንያት አገልግሎት ተቋርጦ ከነበረባቸው የጤና ተቋማት መካከል ይገኙበታል።

በተለያየ ወቅት በአማራ ክልል አብዛኛው አካባቢዎች ተግባራዊ በተደረገው የእንቅስቃሴ ገደብ እና የሰዓት እላፊ እንዲሁም በጸጥታ መደፍረስ የተለያዩ ወረዳዎችን የሚያገናኙ የመንገድ መጓጓዣዎች በመቋረጣቸው አልያም ውስን በመሆናቸው ምክንያት፣ የንግድ እና የማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ በፈጠረው ተጽዕኖ ነዋሪዎች ለአቅርቦት እጥረት እና ለዋጋ ንረት እንዲሁም ለተያያዥ ችግሮች ተዳርገዋል። የተለያዩ አምራች አካባቢዎች ምርት ያቋረጡ ሲሆን፣ በገንዘብ ዝውውር ላይ የተጣለው ገደብን ጨምሮ በአንዳንድ ተቋማት የደመወዝ ክፍያ መቋረጥም ነዋሪዎችን ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ዳርጓል። በተጨማሪም በተለይም በሰሜን ጎንደር እና በዋግኅምራ አካባቢዎች በተደራራቢ ምክንያቶች በርካታ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ የሚሹ መሆኑ ታውቋል። በክልሉ ውስጥ በተለየ ሁኔታ ከተፈቀደላቸው ተቋማት በስተቀር ይህ መግለጫ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ የኢንተርኔት አገልግሎት የተቋረጠ ሲሆን፣ በተለይም በግጭት ላይ ባሉ አካባቢዎች የስልክ አገልግሎትም ጨምሮ ተቋርጧል። የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር / ዳንኤል በቀለኮሚሽኑ በተደጋጋሚ ባቀረበው ጥሪ እንደገለጸው ግጭቱን በዘላቂነት ለመፍታት ለሁሉም ሰላማዊ አማራጮች አሁንም ቅድሚያ መስጠትን ጨምሮ፤ ተፋላሚ ወገኖች ሲቪል ሰዎችንና ንብረቶችን፣ የሕዝብ አገልግሎቶችን እና መሠረተ ልማቶችን በማናቸውም ሁኔታ ዒላማ እንዳያደርጉ፣ በቁጥጥር ሥር የዋሉ የታጠቁ ኃይሎች አባላትና ሌሎች ተጠርጣሪዎችም ሁኔታ በሕጋዊ አግባብ ብቻ እንዲስተናገድ፤ በተለይም የአስገድዶ መድፈር ወንጀል እና ከሕግ ውጭ የተፈጸመ ግድያ በአስቸኳይ በማጣራት ተጠያቂነት እንዲረጋገጥና የማኅበራዊ አገልግሎቶች በተቻለ ፍጥነት እንዲቀጥሉ እንዲደረግአሳስበው፤ተፈናቃዮች አስፈላጊው የሰብአዊ ድጋፍ በአስቸኳይ እንዲደርሳቸው እንዲደረግ፤ ለመፈናቀል የዳረጋቸው ምክንያት እልባት አግኝቶ በዘላቂነት ወደ ቀያቸው የሚመለሱበት ሁኔታ እንዲመቻች ጥሪ እናቀርባለንብለዋል፡፡

 

 

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።