እስኪ፨

 

 

ስኪ

"በእግዚአብሄር ሕግ ጸንተህ ብትኖር

ለዘላዓለም፦ በተድላ በደስታ በኖርክ ነበር።"
(መጽሐፈ ባሮክ ምዕራፍ ፫ ቁጥር ፲፪)
 May be an image of 6 peopleMay be an image of 1 person and textMay be an image of 2 people and textMay be an image of 2 people
(አብይ እንኳን አገር ወረዳ መምራት አይችልም። ወሮ ፈትለወርቅ)
እንፈትሸው። ዶር አብይን " ማን ፈጠረው? ማንን ይመስላል? ማን ዕድሉን ፈጠረለት? ማን ኮትኩቶ አሳደገው? ተጠያቂው አሳዳጊው ወይንስ ታዳጊው? ትንሽ በስሱ ልፈትሸው። የተለሞጠ ስለሆነብኝ። 
 
ህወሃት ፈቅዶ ስልጣኑን ከለቀቀ በኋላ ጽፌበት አላውቅም። አብዝቼ እሞግተው የነበረ የዞግ የፖለቲካ ድርጅት ነበር። ይህን እኔን የሚውቁ ሁሉ ጠንቅቀው ያውቃሉ። ወዲያው ሥልጣኑን ሲለቅ በወጀብ ያላጉት የነበሩትን ሁሉ ሞግቻለሁ። ስለምን? ፈቅዶ እና ወዶ መንበረ ሥልጣንን በሰላማዊ መንገድ መልቀቅ ሥልጣኔ መሆኑን አምኜ ስለተቀበልኩት። ህወሃት ሥልጣን የለቀቀበት መሠረታዊ ምክንያትም ሚዲያ ላይ እንደሚነገረው አለመሆኑን ጠንቅቄ አውቅም ስለነበር።
 
ህወሃትን ከልጅነቴ ጀምሮ ነበር እማውቀው። ያ የካቲትን ተንተርሶ የጎንደር ገበሬን አዝመራ ለመዝረፍ ባለዓዋጁ፤ በዘመቻው የሲዊዲን ተራድዖ ድርጅት በገጠር የሠራቸውን፤ የአውራጃ እና የወረዳ ከተሞችን እዬዘረፈ፤ ፈንጅ እዬቀበረ ወገኖቹን ይጨርስ የነበረ ድርጅት በለስ ቀንቶት 27 ዓመት ፀጥ ለጥ አድርጎ መግዛቱን ሳስተውል ይገርመኝ ነበር በእጅጉ። በፌድራሉ እና በህወሃት ጦርነት በአፋር እና በአማራ ክልል እራሱ በዘመኑ ያለማውን የደከመበትን ሲያነድ፤ ሲያወድም፤ ሲዘርፍ አልደነቅም ነበር። ለምን? ተፈጥሮውን ስለማውቅ። 
 
አመጣጡን በህይወት ስለምረዳ። ስለሆነም በሁለቱ ጦርነት ጉዳቱን የግራ ቀኙን ከመዘገብ ውጪ ጦርነቱ ሲጀመር፤ ሲዋገድ፤ ሲጠናቀቅም በቁጥብነት ነበር እምከታተለው። ሰላም ወረደ ሲባልም ዕድሜውን ሙሉ በባሩድ ጢስ ልጆቹን ያሳደገው የስሜን ሰው ትልቅ እፎይታ ስለነበር ዘግቤዋለሁኝ።
 
#በጣም የሚገርመኝ።
 
1) ህወሃት ዕድሜ የማያስተምረው መሆኑ ነው። አሁንም እንደገና በራያ ከ10ሺህ በላይ ወገኖቹን ሲያፈናቅል፤ ሲዘርፍ፤ ሲያስጨንቅ ሐሴቱ መሆኑ ይገርመኛል።
 
2) ለትግራይ ህዝብ፤ ለዓለም ዓቀፋ ማህበረሰብ ወልቃይት ጠገዴ፤ ጠለምት፤ ማይጠምሪ፤ አዲረመጥን አስመልሳለሁ የሚለው ቧልቱ ነው። ከጦርነቱ በፊት በጉልበቱ ወሮ የያዛቸው ቀዬወች በእጁ እያሉ ስለምን መዋጋት አስፈለገው? ጦርነቱ ማን አስነሳው የሚለው እኔ የራሴ ግምገማ ስላለኝ ወደዛ መግባት አልሻም። ነገር ግን የጦርነቱ ፍሬ ነገር ወደ ማዕከላዊ መንግስት የመምጣት ፍላጎት ነበር። ይህ ዕውነት ተደፍጥጦ ለወልቃይት ለራያ ሲባል የሚባለው ኩሸት ነው። እነሱም ያውቁታል እኛም እናውቀዋለን።
 
3) በጦርነቱ ጊዜ የሰማሁት 1.5 የትግራይ ህዝብ በዕለት እርዳታ ላይ እንደነበር ስሰማ ደንግጫለሁኝ። ቢያንስ ለለት ጉሮሮ፤ ለለት ከፈን፤ ለለት መጠለያ የትግራይን ህዝብ ህወሃት እንዴት አላበቃም? የእነሱን ልጆች የወርቅ እና የዘመናይ ኑሮ እናስተውል ስለነበር። የህወሃት መሪወች ዲታነስ? ለዛ ነበር ያን ሁሉ ዓመት ልጁን ግብር የሰጠው የትግራይ ህዝብ?
 
4) ቂም፤ በቀል፤ ምህረት አልባነትን መቼ ይሆን ህወሃት የሚማረው? አስተውሎት አግኝቶ ለፀፀት፤ ለንሰሃ የሚበቃው። ምድር የማትችለው ገመና ያለበት ድርጅት ነው ህወሃት። የዚህ ሁሉ ቀውስ ፈልፋይ እና አድራጊ ፈጣሪም እሱ ነው። ኢትዮጵያን በማሳጣት፤ በማስጣትም ሁሉ ያዬው የታዘበው ሃቅ ነው። በስሜን ዕዝ ይሁን በማይካድራ፤ በአፋር ትቤት፤ በኮንቦልቻ የፈፀመው ግፍ ከሰው ባይደርስ የላይኛው ፈጣሪ ይመረምረዋል።
 
5) እስከ መቼስ ስሜን በጦርነት ነጎድጓድ ይታመስ? በጮሆት ይናጥ? 
 
6) መቼ ነው ህወሃት ከፋንታዚው የሚገላገለው። ከእንግዲህ መቼም ጠቅልሎ መግዛት አይታሰብም። ምን አለ በዬጊዜው የትግራይ ህዝብ በጥርጣሬ እንዲታይ መከራ ከማምረቱ ቢታቀብ። ሙሉ ስድስት ዓመት ይህ ህዝብ ፍዳውን አዬኮ።
 
#ህወሃት እና ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ።
 
እኔ ጠሚ አብይ አህመድን አንቱ እያሉ፤ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚር ሆነው ነበር መከታተል የጀመርኩት። በፍቅር ተፈጥሮ ላይ ኢትዮጵያ ላይ ምን እዬተሰራ እንደሆን ሳጠና ዶር ምህረት ደበበን አገኜሁ ከዚያ "አቶ" አብይ አህመድን። ንግግራቸው፤ ራዕያቸው ይመስጥ ነበር። ለእኔ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የማውቃቸው አቶ አብይ ሙተዋል ባይ ነኝ።
የሆነ ሆኖ ህወሃት አይደለም ወይ አቶ አብይን የኢንሳ ዲያሪክተር ያደረገው? አቶ አብይ የኢንሳ ዲያሪክተር መሆናቸውን የሰማሁት ጠሚር ከሆኑ በኋላ ነበር።
 
የሆነ ሆኖ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚር ህወሃት አይደለም ወይ ያደረጋቸው?
የኦሮምያ ክልል የቤቶች ልማት ቢሮስ ያደረጋቸው ህወሃት አይደለም ወይ?
ዛሬ ነው ለህወሃት ጠሚር አብ ይ አህመድ ወረዳ መምራት አለመቻላቸው ለህወሃት፤ የህወሃት ቀደምት ተገዳላይ የሆኑት ወሮ ፈትለወርቅ የሚነግሩን? የት ነበሩ እስከዛሬ? በጠሚር አብይ አህመድ የሚር ቦታም ተስጥቷቸው የካቢኔ አባል፤ አካል ነበሩ። እና ያን ጊዜስ ስለምን ሹመቱን ተቀበሉ?
 
#መሪነት በስሱ።
 
አለመታደል። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ያልታደለ ነው። የመሪነትን ሥነ ምግባር፤ ክህሎት፤ የማስተዋል እና የማስተዳደር አቅም የማያውቁ ሰብዕናወች በአጋጣሚ ስጦታ ቁብ እያሉ ህዝባችን ሰቆቃ ስንቁ እንሆ ሆነ። ጠሚር አብይን ሌኮ፤ ዳይሪክተር፤ ሚር፤ በዓዋሳው የኢህአዴግ ጉባኤ በሙሉ ድምጽ የኢህአዴግ ሊቀመንበር እና ጠሚር ያደረገ ተቋም ዛሬ ተነስቶ ወረዳ መምራት የማይችል ሊል ፈፅሞ አይችልም። ማላገጥም ነው።
 
እኛ ጠሚር አብይን፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ጠሚር አብይን፤ የአፍሪካ እና የዓለም ህዝብ እና መንግሥታት ጠሚር አብይ አህመድን የት እናውቃቸዋለን። በዞግ ፖለቲካ ኮትኩቶ አሳድጎ ከራዲዮ ኦፕሬተርነት እስከ የዓለሙ የሰላም የሎሬት አባት ያደረገው ህወሃት ነው። ተጠያቂው ጠያቂ ሆኖ ሲቀርብ ያስገርማል። 
 
ሌላው ህወሃት ስለ ሰብ ጨንቆት አያውቅም። በጭካኔ ተኮትኩቶ ስለአደገ የእሱ ተፈጣሪወች ጭካኔ ነው መርኃቸው። ሌላው ቀርቶ ጠቅሚር አብይ አህመድ አሊ ከመጡባት ዕለት ከመጋቢት 24/2010 ጀምሮ በመጀመሪያ ገዲዮ፤ በቡራዩ፤ በአማራ፤ በወላይታ፤ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ላይ የሰነዘረውን ማጥቃት አንድም ቀን አውግዞ ተቆጥቶ አያውቅም። 
 
የደንቢ ደሎ የዩንቨርስቲ ተማሪወች ሲሰወሩ ኃላፊነት እና ተጠያቂነት ቢሰማው፤ እርህርህና ቢኖረው፤ እንደ ሰው ቢያስብ አጀንዳው ሆኖ ባርመጠመጠው ነበር። ህወሃት ብቻ ሳይሆን የየክልሉ አስተዳደር ይህን የመሰለ ግፍ ሲፈፀም በአንድ ድምጽ ሊያወግዙት፤ ሊጠዬፋትም ይገባ ነበር። ግን ሰውነት ተኗል። ለዚህም ይመስላል በእያንዳንዱ የሚደርሰው መከራ ወላዊ የቁጭት የሃዘን ስሜት ሊፈጠር ያልቻለው። ለተከፋ፤ ላዘኑ፤ አይዟችሁ መሪነትን፤ ማጽናናት የመሪነት ልቅና ያሳይ ነበር።
 
ህወሃት ህልመኛ ነው። ግን ሰው ሳይሆኑ ማለም መብት ቢሆንም፤ ህልምን ማግኜት ግን አይቻልም። ይህ ለህወሃት ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የክልል አስተዳደሮች የሚመለከት ይሆናል።
 
ንጽህት ትግራይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የደረሰው በደል እና መከራንም ውስጤ አላለችውም። ተዋህዶ ለ33 ዓመት የተመራው በማን ነው? ይህ ከቁጥር የማይገባ ማስተዋል ያልመገበ ጉልላታዊ ጉዳይ ነው። ከጦርነቱ በፊት ለተዋህዶ ዕንባ ትግራይ ድምጽ አልነበረችም። ለምን??? 
 
ህም። 27 ዓመት ህወሃት ኢትዮጵያን ሲመራ የደከመበትን ዕዳው ሳይመለስ በአማራ ክልል እና አፋር ክልል የዶግ አመድ አድርጎታል። ይህ መሪነት ነውን ወሮ ፈትለወርቅ? ይህን ያደረገ ድርጅት ምን ይባል? ሥም ያውጡለት እንጂ ለራስ ሲቆርሱ ካልሆነበወት? ስለ ሌላ የመሪ ብቃት አስተያዬት ለመስጠት የራስን የአመራር አቅም በቅጡ መመርመር ያስፈልጋል?
ማህበረ ህወሃት ሆይ! መሪነቱን ብትችሉበት ኖሮ የ100 ዓመት ህልማችሁ ባልጨነገፈ ነበር። በዬትኛውም ዘመን ህወሃት እራሱን ችሎ ኢትዮጵያን የመምራት አቅም አርግዞ ሊገላገል አይችልም። አወዳደቃችሁን ያከፈቻሁት የመሪነት በራ ስላለባችሁ ነው።
 
ዓለምን ህወሃት ያታለለበት ገመና ነው። ፌድራሊዝም በኢትዮጵያ ያለው አማራ ክልል ብቻ ነው። ሌላ ቦታ ፌድራሊዝም የህልም እንጀራ ነው። በትግራይ በራሱ ፌድራሊዝም ሀሁ አልተቆጠረም። የትኛው ዞግ ነው በትግራይ ክልል የራሱ የወረዳ፤ የዞን አስተዳደር ያለው????
ማፊ። 
 
ወሮ ፈትለወርቅ በዓላማቸው ፀንተው ድሎትን ክላ ማለታቸውን ባከብርላቸውም የአመራር ብቃት ግን አላቸው ብዬ አላስብም። የዚህ ሁሉ ውድቀት እነሱን ጨምሮ ብልህ መሪ በአውራው የዞግ ድርጅት በህወሃት አለመኖሩን መቀበል ግድ ይሆንባቸዋል። የጠሚር አብይ ጥንካሬም ድክመትም ልኩ በፈጣሪያቸው በህወሃት ዕውሃ ልክ ይመዘናልና።
 
ከሁሉ በላይ ሰውን ለመምራት ሰው ሆኖ መገኜት። ከዕድሜ ልክ ግድፈት አንድ ቀን እራስን አርሞ ወደ ተስተካከለ መስመር መግባትን። እና ለበደሉ ሁሉ ይቅርታ ጠይቆ ንስኃ መግባትን። ጥሞና መውሰድን። ሁልጊዜ ለእኔ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ተሰውልኝንም ማስቲገስ ይገባል። በተለይ ሌላውን ለመተችት ከራስ መጀመር ይገባል።
 
ህወሃት የሚተማመንበት የውጭ ዲፕሎማሲው ነው። እኔ እምመክረው ሁሉም እንዳኖሩት አለመገኜቱን ቢውቅ ህወሃት መልካም ይመስለኛል። በልኩ ለልኩ መሆንን። ኦቨር ኮንፊደንስን ማስታገስን ይጠይቃል። እያዳመጣችሁ ነው አይደል የእስራኤል፤ የአሜሪካ ቤተኝነትን? ተማሩበት። 
 
#ውሸት ማቅናት ቀላል ነው። ዕውነት ሆኖ መገኜት ዳገት ነው። 
 
ሰሞኑን በአንድ ቃለምልልስም ዶር አብይን ከብልጽግና የመለየት ስልት አዋጭ እንደሆነ ሲጠቀስ ሰምቻለሁ። ብልጽግና ህሊናው ያለው ከጠሚር አብይ ዘንድ ብቻ ነው። እሳቸው ከተነጠሉ ከባህር የወጣ አሳ ይሆናል። ጠሚር መለስ ዜናዊን ያጣው ህወሃት ምን ላይ እንዳለ በማስተዋል መዳኜት ይገባል። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች ሲደራጁ በአንድ ሰው ካንፓኒነት ሞኖፖሊ ነው። ፈጣሪውን ሲያጣ ይሞታል። ሊወዛወዝ ይችላል። ግን ደመነፍሱን። ለምን? አዲስ ሃሳብ አፍላቂ ስለሚፈራ፤ ስለሚነቀል ተተኪ አልቦሽ ሆነው ስለሚፈጠሩ።
የኔወቹ እንዴት ናችሁ?
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
22/04/2024
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።