የኢትዮጵያ ፖለቲካ የባህሪ መለያ ከህግ በላይነቱ ብቻ ሳይሆን በህግ አፈፃፀም ተጠያቂነትም ላይ በቀለኛ፣ ቂመኛ እና #ዱለኛ መሆኑ ነው።

 

            

 

ኢትዮጵያ ፖለቲካ የባህሪ መለያ ከህግ በላይነቱ ብቻ ሳይሆን በህግ አፈፃፀም ተጠያቂነትም ላይ በቀለኛ፣ ቂመኛ እና #ዱለኛ መሆኑ ነው።

ረጅም እርዕስ ነው። ዕርዕሶቼ አጫጭር ናቸው። አንዳንድ ጊዜ 4 ዕርስ አንድ ወጥ ጹሁፍም እጽፋለሁ። በቅድሚያ እንዴት አደርን ማህበረ ቅንነት? ምዕራፍ 13 ቀጥሏል ውስጥን በመመርመር ላይ። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሃኪም የለሽ ነውና። እኔ ሃኪሙ ነኝ እያልኩ አይደለም። ኧረ ምን በወጣኝ???

 

"አቤቱ ታድነኝ ዘንድ ፍቀድ፥

አቤቱ፦ እኔን ለመርዳት ፍጠን።"

አሜን ይደረግልን። ይሁንልንም።" አሜን።

(መዳ ምዕራፍ ፴፱ ፱፫)

#ጥቂት

በወንጌል መጀመሬ የሚከፋቸው ታዳሚወች ገጥመውኛል። እኔ እኮ የፖለቲካ ድርጅት መሪ አይደለሁም። ብሆን አላደርገውም። በሌላ በኩል ወንጌል አቅም አለው ህሊናችን የመግራት። በተጨማሪም ፀላዬ ሰናያዊ እሾሆችንም ያባርራል። ከዚህ ሌላ እኔ ሥርጉተ ሥላሴ ወይንም ሰብለ ህይወት እራሴን ተውሼው ወይንም ተወርጄው አላውቅም። በራሴ ርዕይ እና ጎዳና ቀጥ ያለ አቋም ያለኝ ነኝ። በልጅነቴ የሚያውቀኝ ሰው ዛሬም ቢገኜኝ ብትጠይቁትም እሷ ስትፈጠር እንዲህ ናት ይላችኋል። ወጣገባ ሰብዕና የለኝምና። ሞቅ ቀዝቀዝ ዳመን ፍክትም የለም። በማናቸውም እኔን በሚሻ ቦታ የራሴም የጠና ቀለም እና አርት ያለኝ ሰው ነኝ። ስለዚህ ጎርፍ ለሚያመጣቸው ዕይታወች ባርባር የሚለኝ አይደለሁም። ያማ ቢሆን እስታሁን ስንት የፖለቲካ ድርጅትን ተቀላቅያ እፈርስ እና እሰራም በነበረ።

#ሌላ

ስለፎቶው ይቅርታ ሚዲያ ላይ ስለቀረጽኩት ነው። ከቻልኩ ጉግልን የተሻለ ምስል ካለህ ብዬ እለምነዋለሁኝ። ቁምነ ገሩ ንጉሥ አይከሰስ የኢትዮጵያ ፖለቲካ መርህ ሆኖ መቀጠሉ ምን አተረፈን? ምንስ አከሰረን ፍትህ እስከ መቼ ትሳደዳለች ነው በኽረ ጉዳዬ።

#ዕፍታ

እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ #መልዕክት ይዞ ይወለዳል። እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ #ጥሪ ይዞ ይወለዳል። እያንዳዱ ልጅም #መክሊት ተስጥቶት ይወለዳል። ይህ የእኔ ዕምነት በመፃህፍቶቼ ላይም እርዕስ ሰጥቼ ጽፌዋለሁኝ። ጠበቃ እና የህግ ባለሙያ አቶ አበራ ንጉሥም ፀጋ ያላቸው፤ ጥሪም ያለባቸው፤ መልዕክት ይዘው ወደ ምድር የመጡ ስለመሆናቸው እኔ አምንበታለሁኝ። ያንንም ሳይተላለፋ ፀንተው ተማግደውበታል። ይህ በግዙፋ የትናንትን ያለፍንበትን፤ የዛሬን ያለንበትን፤ የወደፊቱን የተስፋችን ምስባክ ያሳያል። ደፋር ርምጃ ለትውልድ የሚበጅ፥ እራስን ለመሞረድም ህሊና ነው።

እኒህ ወንድማችን በተጠያቂነት እና ኃላፊነትን በአግባቡ በመወጣት እረገድ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ተፈጥሮ ፊት ለፊት ወጥተው የሞገቱ፤ #የረቱም ጀግና ናቸው። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከህግ በላይ ሆኖ መኖሩ በገላጣ ዕውቅና ያገኜበት፤ ፈተናውን ሳያልፍ የወደቀበት ሁነት ተፈጥሯል። በእኔ ዕድሜ በፖለቲካ ህይወቴ የተረዳሁት ሃቅ የፈለቀበት እርምጃ አቶ አበራ ንጉሡ የፊደል ገበታ ሆነው አሳይተውናል።

.. 2013/2014 ህወሃት ስለምን የህግ ፋክልቲ ኖረው ብዬ ስሞግት ነበር። ምክንያቱም የህግ ጥሰቱን በባለሙያ ማስመረቅ ብዛት ሊያሻሽል ስላልቻለ። የአወጣቸውን የህግ ድንጋጌወች የመፈፀም አቅሙ #ዲዳም ስለነበር።

 

#እንጂማ ለእማማ ቀርቶ ……

 

……… እንጂ እኔ ህግ የተወሰኑ ባለሙያወች ብቻ ሳይሆን የማህበረሰቡ ሙያ ሊሆን ይገባል። ልጆች የአገራቸውንና ዓለም ዓቀፍ ህግጋትን ከአንደኛ ደረጃ / ቤት ጀምረው መማር አለባቸው። ማህበረሰቡ በተደራጀባቸው አደረጃጀት ሁሉ ህግን ያውቅ ዘንድ መላ ይዘዬድ በማለት ተመድን፤ አውሮፓ ህብረትን ከዘጠኝ ዓመት በፊት ሞግቻለሁ። ባለፈውም ዓመት ከእኛ ኮሚኒቲ ባለፈ እንዲሁ ሠርቸበታለሁኝ። አሁንም በፀጋዬ ራዲዮ በጥብቅ እዬሠራሁበት ያለሁበት ጉዳይ ነው።

 

#እንዳትደነግጡ እንጂ ……

እኔ ሥርጉተ ሥላሴ ወንጀለኛ የለም ብዬ አምናለሁ። ለምን ብትሉ መብቱን ያላወቀ፤ ግዴታውን ያልተማረ ፍጡር ግድፈት ቢፈጽም የህግ ትርጓሜ ስለማያውቅ ነው የሚል ጽኑ ዕምነት አለኝ። እንደ እኔ እንደ ሥርጉትሻ ወንጀለኛ አለ ከተባለ ህግ አጥንተው በህግ አፈፃፀም ላይ ኑረው ህግ የሚተላለፋት ብቻ ወንጀለኛ ሊባሉ ይገባል ባይ ነኝ። ሙያተኛ ስለሆኑ።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ህግ አስፈፃሚ የፀጥታ ኃይሎችም ህገ ነክ ስልጠና ስላላቸው እነሱም ህግ ቢተላለፋ ወንጀለኛ ሊባሉ ይችላሉ። እርግጥ መከሰሳቸው ብቻ ሳይሆን ዳኞች ፍርድ ከሰጡበት በኋላ ከተፈረደባቸው ወንጀለኛ ሊባሉ ቅጣቲቸውንም ተቀብለው ሊከውኑት ይገባል።

ዓለማችን ብዙ በጣም ብዙ ሚስ ያደረገችው አመክንዮ አለ። ሰው ስለምን #ጨካኝ ሆነ? አንድ መሪ ከአዘኑት ጋር ማዘን ስለምን ይሳነዋል? አይዟችሁን ስለምን ይሸሻል? ማን ይከፋብኛል ብሎ? እንደምንስ ማጽናናት ባዕዱ ሊሆን ይችላል?

አንድ የአገር መሪ በሰወች ህይወት ላይ ጨክኖ በግልጽም በስውርም መወሰኑ ከዬት መጣ? ስለምንስ መጣ? ዓለማችን የርህርህናን ተፈጥሮ፤ ግዙፋን የፍቅር ተፈጥሮ ካሪክለም ነድፋ አስተምራ አታውቅም። አጀንዳዋም አይደለም። ወደፊትም አጀንዳዋ ይሆናል የሚል ተስፋዬ ልል ነው። የተጀመረ ነገር ባለመኖሩ።

#የሆነ ሆኖ የኢትዮጵያ ፖለቲ ህግ #ጣሽ ብቻ ሳይሆን ህግን #ፈሪም ነው።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ኑሮው ከህግ በላይ ነው። ህገ መንግሥቱ የተሠራው እሱን ለመቆጣጠር ሆኖ እሱ ግን ከህጉ በላይ ሆኖ ነው የኖረው። የሚገርመው በውጭ አገር ያለው ፖለቲከኛ ከሊቅ እስከ ደቂቅ የሚኖርበትን አገር ህግ ዝቅ ብሎ አክብሮ እዬኖረ ለአገሩ ህግ ግን በጅ አይልም።

አገር ውስጥም የፖለቲካ ፕሮፌሰርነት ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ህይወቱን የዕድሜ ልክ እስከ ህልፈት ያሉት ፕሮፌሰር #ዶር #መራራ #ጉዲና በዘመነ ህወሃት ሁለቱንም የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ #ጥሰዋል በወቅቱ ሞግቻቸዋለሁም። አሁን የኢትዮጵያ ቀጣይ ተስፋ አማካሪነት በምዕራብውያን ሲታጩም እስቃለሁኝ። አቶ ዳውድ ኢብሳም በቃለ ምልልሳቸው ውስጥ ከህግ በላይነት ትምክህት ጎልቶ ሳይባቸው ነበር።

በሌላ በኩል አቶ በቀለ ገርባም ታሥረው በነበረበት ጊዜ ለዳኞች አልነሳም ብለው #አምፀዋል ሁለተኛ ጊዜ የወጣውን አስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅም ከፕሮፌሰር መራራ ጉዲና ጋር በመሆን በወለጋ ጥሰዋል።

ህግ ጥሰት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ካፌያቸው ነውና። ይህም ብቻ አይደለም ስብሰባ ህግ አላው። ትማሩትማለችሁ በንግግር ጥበብ ውስጥ። የትኛውም ስብሰባ ሥርዓት አለው። ፕሮሲጀርም አለው። ባልረጋው የኦህዴድ ወደ ኦዴፓ ሽግግር ጉባኤ ላይ አቶ በቀለ ገርባ ተጋብዘው ፕሪዚዲዬሙን አድሬስ አላደረጉም። ይህም ብቻ ሳይሆን ህግ መተላለፋቸውንም በኩራት ሲናገሩ ሰምቻለሁኝ። ባህል ይሁን ትውፊት አላውቅም። ቤታቸውንስ እንዴት ይመሩት ይሆን? የረባ ሥርዓት ለኑራቸው ይኖራቸው ይሆን ብያለሁኝ።

በቀደመው ጊዜ የነበረውን ህወሃትን ያዘመነው የኢህአዴግ ህገ- መንግሥትን ሲያወግዙ፤ ሲጥሱ የነበሩ ዛሬ ደግሞ በዛው ህገ - መንግሥት ሥር ሰጥለጥ ብለው እዬተገዙ ስለመሆኑ አስተውላለሁ። ባይከፋኝም።

በእኔ እምነት ማንም ሰው ከአንድ አገር ህገ - መንግሥት በታች እንጅ በላይ አይደለም። በፍፁም። ህጉ ባይመችም፤ ባይታመንበትም ሥራ ላይ ከሆነ ማክበር መብት ብቻ ሳይሆን #የፈቃድ ግዴታ አለ። ከሁሉም በላይ ትውልድ ሥርዓት አልበኝነትን ሊጠዬፍ ይገባል። ህጉን እንጂ መሪወችን፤ ሥርዓቱን ማዬት አይገባም። ለህግ ራስን ማስገዛት ህግነትም ነው። ለዚህ ነው እኔ ኢትዮጵያ ሄግ፤ ፍልስፍና፤ ሳይንስ እና ዩንቨርስ ናት እምለውም።

"ህግ ተላላፊወችን ጠላሁ።" ልበ አምላክ ዳዊት።

#ተዚህ ላይ። ኢትዮጵያ በጣምራ ህግ መተዳደርን አስመልክቶ ፈንገጥ ያለው ምልከታዬ።

የእኔ ዕይታ ኢትዮጵያ በተፃፈ ብቻ ሳይሆን ባልተፃፈም ህግ ትተዳደራለች ብዬ አምናለሁ። ኢትዮጵያ በተፃፈ ህገ - መንግሥት እንደሚተዳደሩት አገሮች በህገ - መንግሥት፤ እንደገናም ባልተፃፈ ህግ እንደሚተዳደሩት አገሮችም ባልተፃፈ ህግ ትተዳደራለች። በብዙ ተፈፃሚ ሆኖ የሚታዬው ያልተፃፈው ህግ ሙሉ ስምምነት ያለው ብቻ ሳይሆን ተቀባይነት ሲኖረው፤ በተፃፈም ህግ መተዳደር ለኢትዮጵያ ህዝብ የማይከብደው አመክንዮ ነው። በተጨማሪም ሃይማኖታዊ ህግጋትም በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ተፈፃሚነታቸው ደልዳላ ነው።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ እና ፖለቲከኞች ላይ ግን የተፃፈውም፤ ያልተፃፈውም፤ ሃይማኖታዊ ድንጋጌወች #ድፍጠጣ ንቀት፤ የማጥቂያ መሳሪያ፤ የመበቀያ ፋስም ናቸው። የህግ ተቋማት የሚቆሙት ለህዝብ ጉዳይ ሳይሆን ሥልጣን ላይ ያለውን ሥርዓት #እንክህ እንክህ በማለት እንደ ስለት ልጅ የሚንከባከቡ ስለሆነ በኢትዮጵያ የፍትህ ቀናት የዕንባ ዋናተኞች ናቸው። ቀራንዮም ላይ ነው።

#በዘመናችን

በዘመናችን አዲስ ክስተት በአዲሱ ትውልድ አልፎ አልፎ ይከሰታል። አቶ አበራ ንጉሥ ለእኔ ክስተት ናቸው በሙያቸው። እንዴት ዓይነት ደፋር ውሳኔ ላይ እንደደረሱ ሰብዕናቸውን ፍንትው አድርጎ ያሳያል። በአሁኑ ዘመን ፖለቲካውን በቁንጮነት የሚመሩትን አካላት ከጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ጀምሮ ያሉትን በተጠያቂነት ፍርድ ቤት ለማቅረብ የሄዱበት ርቀት ለቀጣዩ ትውልድም አብነት ነው። ህግን አስከብረው እራሳቸውን ማግደዋል።

ለእኔ ስለ ህግ፤ ስለሙያቸው፤ ቃል ስለገቡለት መዳሊያቸው ሰማዕትነት በቁማቸው ተቀብለዋል። ለዛውም የዓለምን የሰላም አባት ሎሬት አብይ አህመድን (ጠሚር) በፍትህ አደባባይ በመንፈስ አቆሟቸው።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ቂመኛ እና በቀለኛ ብቻ ሳይሆን ነገን ታሳቢ የማያደርግ በቃሉ፤ ስለቃሉ ኑሮ የማያውቅ፤ ከህግ በላይም ቁጢጥ ብሎ መኖሩን በገሃድ አዬን። ይህን እንድናይ ያደረጉን አቶ አበራ ንጉሥ ሲሆኑ ኢትዮጵያ ልታመሰግናቸው ብቻ ሳይሆን ልትመርቃቸውም ይገባል።

በዚህ ሂደት ተከሳሾች ክሱን ተቀብለው / ቤት ባይወስንባቸው እራሳቸውን ዝቅ አድርገው ለህግ ተገዢነታቸውን ቢያሳዩ ለትውልዱ ሌላ ተቋም ባላስፈለገ ነበር። አሻራውም የማይገኝ ዕድል ነበር። ብርሃናዊ ተስፋ ፈንጣቂ ብቻ ሳይሆን ሐዋርያዊ ምግባር በሆነ ነበር። ይህ ዕድልን ተላልፎ ንቁውን የህግ ባለሙያ በህግ ማሰር ግን አቅመቢስነት፤ ህግ - አልቦሽነት ባለፈም #አናርኪዝም ነው።

ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ቆዳቸው ስስ መሆኑን 100 ቀናት ጉዟቸው ላይ በባህርዳሩ ህዝባዊ ጉባኤ ስለ አኖሌ ሲነሳ እንደምን ሌላ ሰው እንደሆኑ አይቻለሁኝ። በሥራ ሂደት ሁልጊዜ ተመስጋኝ - ሁልጊዜ ንፁህ - ሁልጊዜ ስኬት- ሁልጊዜ ተወዳጅ መሆን አይቻልም። አንድ ሰው ሁልጊዜ መቆም ያለበት #ዜሮ ላይ ነው።

ግምቱን መለካት ያለበት ብዙኃኑ የሰጠው ግብረ ምላሽ ላይ ሊሆን ይገባል። ምዘናው ቁልቁል ወይንስ ሽቅብ??? የሆነ ሆኖ ክሱ ፕሮሰስ ውስጥ ገብቶ ቢሆን ኖሮ የዶር አብይ መንግሥት ካድሬ ማሰለፍ አያስፈልገውም ነበር።

ታስታውሳላችሁ ባልደራስ አመራሮቹ እስር ቤት ሆነው ለምርጫ ተወዳድረው ነበር። በቅጡ ያልተጤነ ግን አዲስ ኢትዮጵያዊ አውንታዊ ክስተት ነበር። የምርጫውን ቅድመ መሰናዶ እና ክንውን የጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ደጋፊወች ጡጡ ስለሆነ ከዚህ ቀደምም በጀርመንኛ ጽፌበታለሁ። አሁንም መልክ ማስያዝ ስለሚገባ በቀጣይ ከምጽፍባቸው ጉዳዮች የተመዘገበ ነው።

#የሚዘመርለት ዬሽግግር ፍትህ እና ዕጣው በኢትዮጵያ።

የሽግግር ፍትህ በኢትዮጵያ? የሽግግር ፍትህ በገዳ ሥርዓት በምትመራ አገር? የሽግግር ፍትህ ከቅንጣቷ እስከ ግዙፋ ኢትዮጵያዊ ጉዳይ ዲሞግራፊ በሚተገብርባት አገር? የሽግግር ፍትህ ዛሬም ተበድለን ነበር በመሪ ደረጃ በሚሰበክባት ኢትዮጵያ? የሽግግር ፍትህ የተጠያቂነት ፍትህ በእኛ ይጀመር ብሎ ባልፈቀደ አካል አይታሰብም። ሃሳቡ እራሱ #የጨነገፈ ነው። መጨንገፋ ምስክሩ ሩቅ ሳንሄድ የአቶ አበራ ንጉሥ እስር በቂ ነው።

 

#እርገት ይሁን።

 

አቶ አበራ ንጉሥ አሸንፈዋል። ቅባዕቸው ደምቋል። በመከራቸው ውስጥ ፍትህን አስከብረዋል። የጠቅላይ ሚር አብይ የፍትህ፤ የፀጥታ ተቋማት ደግሞ #አዳልጧቸዋል። በግልፅ ቋንቋ ወድቀዋል። ምዕራብውያንም ሆኑ የአውሮፓ ህብረት ተስፋ ያደረጉት የሽግግር ፍትህ መጨንገፋን እስሩ ሰርቲፋይድ አድርጎታል።

 

እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

 


ሥርጉተ©ሥላሴ

Sergute©Selassie

18/05/2024

 

ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።