የኢትዮጵያ ፖለቲካ መለያ ባህሬ #ስስታምነት ብቻ አይደለም #ቆንቋነትም።።
"የቤትህ ቅናት በላኝ።"
የኢትዮጵያ ፖለቲካ የሶሻሊዝምን ርዕዮት መከተል ከጀመረበት ጀምሮ ስስታም የሆነ ይመስለኛል። ባለፈም ቆንቋነነት። ከስስታምነት ያለፈ #ስግብግብነት። ተዳብለህ በተወሰነ ደረጃ ህሊናህ የሚልህን አድምጥ እንኳን አይፈቀደም። #ልጠቅልልህ፤ #ልሰልቅጥህ የተሰጠህ ህሊና በእኔ ቁመና ከሆነ ይሁን በስተቀር ቆልፈህ ተቀመጥ። የአንተ ህሊና በእኔ ህሊና ይመራ ነው መከራው። ይህ የሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች በሽታ ሲሆን ወታደሮች ደግሞ ደጋፊወች ናቸው። አይታወቃቸውም እንጂ ሳይለንት ዲስክርምኔሽንም ነው።
በራሱ ህሊና ሊመራ የወሰነ፤ አለኝ የሚለው የራሱ የሆነ ነገር ያለው ባይፈጠር ይሻላል። ተረባርበው ድራሹን ያጠፋታል። ይህ ስልጣን ላይ ሆነ ስልጣን ላይ አልሆነ የሁሉ ድዌ ነው። #ወረርሽኝ። አሻም ያሉ እንደ እኔ አፈንጋጮች ህሊናቸውን ያላከራዩ ወይንም ያልገበሩ በውራጅ ማንነት ፋንታዚ ያለቀዘፋ ወይንም የማይቀዝፋ በስውር እስከ ቤተሰባቸው ይመነጠራሉ። ከእስር ሳንፈታ እናልፋለንም። እስሩ ቤት ለቤት ስለሆነ ብቻችን እንዳአዝን ይሆናል እምናልፈው። በዚህ መሰል ህይወት ለመጣው ለሄደው ያላደገደጉ የእኔ መሰል መከረኞች አሉ። ትልቁ ፀጋቸው ግን በነፃነታችው ልክ መኖርን ፈቅደው ማሸነፋቸው ነው ሳይገብሩ።
የሚገርመው በአንድ ወቅት አሳዳጅ የነበረው ጠቅላይ በሌላ ጊዜ ተሳዳጅ ይሆናል በኢትዮጵያ ፖለቲካ። ቂመኝነቱን በቀለኝነቱ ሲታሰብ የአደራ እና የትውልድ ዘረፋውን ለኩት። አሁን መድረክ ላይ እምናዬው #ትዕይንት ይህ ነው። እያንዳንዱ ሰው የተሰጠውን ህሊና በነፃነት መጠቀም ሲሳነው ሌላውን ልጠቅልል ለእኔ #ሳይለንት #አስምሌሽን ነው። አንድ እስክሪብቶ ያልገዛ፤ አንድ ሜትር ልብስ ገዝቶ ያላሳደገ፤ አንድ ኪሎ ጤፍ ያልሰፈረ ነው የራሱን ህሊና ይዞ የሌላውን ልጠቅል ብሎ ሲነሳ ሲወድቅ የምታዩት። አንድ ፲አለቃ የባይወለጂ ፕሮፌሰርን ልጠቅልል ብሎ እፍ ግብ ይላል። ይህ ሥር ነቀል እርምጃ ካልተወሰደበት መቼውንም ኢትዮጵያ #መፍትሄ አታገኝም። ኢትዮጵያ የደካማ ሃሳቦች #መፍተልተያ ብቻ ሆና ትቀራለች።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሰማዕታት የታገቱ፤ የተሰወሩ፤ የተገደሉ፤ የታሠሩ ሁሉ በዚህ ስስታምነት - ስግብግብነት -:ድንብስና - ድንብርብር ፖለቲካ ሂደት ምክንያት ነው። የሰው ልጅ በተሰጠው ህሊና ልክ እንዳያስብ ስለሚታገድ ነው። ታላቁ የጥበብ ሰው ጋሼ በዓሉ ግርማ ድብዛው የጠፋው በዚህ ዕሳቤ ነው። አሁንም የሚሳደዱት፤ የሚሠወሩት፦ የሚታገተቱ ሁሉ ሃሳቡ ህሊናችሁን #የነቃውን አስረክቡን ነው። ይህ ደግሞ ሰው ሆኖ ተፈጥሮ #ቀፎዬን ልኑር ብሎ መፍቀድ በመሆኑ #ወንጀል ነው ብዬ አምናለሁ።
አቤቱ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ይህን ደፍተህ ተጠቅለል በአንድ በረት ልምራህ አይደለም እንደ እንሰሳ ልንዳህ ባይ ነው። ይህን ይሁን ያሉ የፈቀዱ መብታቸው ነው፦ በአራት ማዕዘን ጥብቆ ቤርሙዳ መጠለል ይሆናል ዕጣቸው። የሆነ ሆኖ ሁሉም በራሱ ህሊና ያስብ ዘንድ ነፃነቱ ሊያሳሳው ይገባል ባይ ነኝ። አሻም የሚሉ ሊታገቱ፤ ሊሰወሩ፤ ሊገደሉ፤ ሊታሠሩ አይገባም። የዬጊዜው የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይል የሚያስፈጽመው ይህን ነው። የሚገርመኝ ደጋፊው ነው። ለነፃነት ገፋፊው አጋፋሪ መሆኑ።
ሌላው ሁሉም የራሱ ኢንፓዬር አለው። በዛ ኢንፓዬር ያልተጠቃለለ የሚወርድበት ማት የታለፈበት፤ ያለንበትም ህይወት ነው። ይህ የተፈጥሮን ጥበብ ያለማወቅ የአስተሳሰብ ድህነት ይመስለኛል። ካልታረመም ኢትዮጵያ መዳኋ ይቀጥላል። መፍትሄው ለነፃ የሃሳብ መኖር ሁሉም እራሱን ይረም ፈቅዶ እና ወዶ እናት ካስፈልገው። በዬአካባቢው ያሉ ሹመኞችም ይታረሙ ዘንድ አለቆቻቸው ይግሯቸው። ህሊናን አከራይቶ በቀፎ መኖር ሞት በስንት ጣዕሙ።
ሰማዕታት በፖለቲካ ይሁን በሃይማኖት ሁሉም መጠቅለልን አሻም ስላሉ ነው ነፍሳቸውን የተቀሙ።
እንደ ማሳረጊያ።
በስሱ ከዚህች ላይ አንስቼ ማለፍ የምችለው የትዳር ፍርሰትም ይህ ይመስለኛል። አብሶ ግራማይንድ ሴቶች ከአቅም በታች ትዳር ከገጠማቸው፤ ወይንም የበለጠ አስተሳሰብ ያለው ከገጠመ ጭንቅላትሽን እርሽው በእኔ ተመሪ የሚለው ስውር እሰጣ ገባ ለትዳሩም ለቀጣይ ትውልድም ፍግፍግ ተመክሮ ይሆናል። በዚህ ስሌት ስንሄድ የሁለቱ የነቀ የህሊና ክፍል አቅም በስምምነት በአቻነት ቢጣመር ግን ሐሤት ሰማይ ሳይሆን፤ ገነት ሰማይ ላይ ብቻ ሳይሆን ምድርም ላይ ይሆናል።
በትዳሩ ህይወት እና ማንነት ታንፀው የሚወለዱ ልጆችም ምርቃት ይሆናሉ ለአካባቢው ማህበረሰብም አብነት ይሆናል። በቃ ተከተተ የእነሱ ትዳር የሚባልላቸው የታደሉ ጥንዶች ፀጋቸውን ማኔጅ ባደረጉበት ጥበብ ልክ ተጠቃሚ ይሆናሉ። ይህ በማህበረሰብ ግንባታ ላይ ተጽዕኖ አወንታዊ ይሆናል። አብዛኛው ይህ ቢሆን እሰቡት ስንት ግድፈት ማረም እንደሚቻል። ጥሞና አርምሞ ተደሞ የሚያስፈልገው የኛ ነገር ሁለመናችን የተጎሳቆለበትን አካባቢ በጥናት በዕውነት እና በመርህ ለመፈወስ ይረዳ ነበር። አቅሉን ቢሰጠን። ሰጥቶናል ለመጠቀም ብንፈቅድ።
ግን እንዴት አደራችሁልኝ።
"የቤትህ ቅናት በላኝ።"
መሸቢያ ጊዜ። አሜን።እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
10/06/2024
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ