የአትሌት ሲሳይ ለማ #አብነትነት ትውልዱ፤ የፖለቲካ ድርጅት መሪወች ምን ይማሩበታል?

 

የአትሌት ሲሳይ ለማ #አብነትነት ትውልዱ፤ የፖለቲካ ድርጅት መሪወች ምን ይማሩበታል?
 
"የቤትህ ቅናት በላኝ።"
 May be an image of 1 person and textMay be an image of 4 people and textMay be an image of 4 people and text
 
ግን እንዴት ሰነበታችሁልኝ ማህበረ ቅንነት? ደህና ናችሁን? ሰሞኑን ተጠፋፋን።
የዘንድሮን ኦሎንፒክ ብዙም አልተከታተልኩትም። ምክንያቴ ውዝግቡ አውሎማ ስለነበር ብቻ ሳይሆን መክፈቻው ላይ የነበረው ሁነትም ብዙ በትጋት እንድከታተለው አልገፋፋኝም። የሆነ ሆኖ የሴቶቼ 10 ሺን፤ የወንዶች ማራቶን እና የሴቶች ማራቶን ተከታትያለሁኝ።
 
በውድድር ማሸነፍ እና መሸነፍ እኩል ዕውቅና ሊሰጣቸው ይገባል ብዬ አምናለሁ። ድካሙ #እኩል ስለሆነ። በልፋት፤ በጥረት የሚገኝ መሸነፍም ቢመጣ ከባለ መዳሊያው ጋር እኩል ዕውቅና ሊሰጠው ይገባል ባይ ነኝ። አሰልጣኞችም ቲሙም እንደሚያስገኙት ውጤት ሊመዘኑ ይገባል ባይም ነኝ። 
 
አራቱ ኮከብ አትሌቶች መዳሊያ ያስገኙት በዛ ውዝግብ ላይ ሆነው ነው። ይገርማል። እንደምን ተረጋግተው ለድል እንደበቁ ሚራክል ነው - ለእኔ። የውስጥ ሰላም ከሌለ የጎረስከውን እህል እንኳን በቅጡ አጣጥሞ መዋጥ ያቅታል። በአፍህ ውስጥ ከርታታ ስደተኛ ይሆናል። ይተናነቅኃልም። አትሌቶች ተሰናድተው ሄደው ግን የውድድር ዕድል ተነፍጓቸው ሲመለሱ፤ የተፈቀደላቸውም አሰልጣኛቸውም ግዳጃቸውን ሳያጠናቅቁ #ተመላሽ ሲሆን፤ በቀጥታም ይሁን በተጠባባቂነት የተመረጡትም ተመላሽ ሲሆኑ በራሱ በቀሪ ተወዳዳሪወች ላይ ሊያመጣ የሚችለው #ተጽዕኖ ከባድ ነው። ተስፋቸው ይኮማተራል። 
 
አትሌቲክ ብቻ ሳይሆን ስፖርት የአንድ አገር #የውጭ #ጉዳይ ሚር ማለት ነው። ኢኮኖሚካሊም የሚክስ፤ ለተሳታፊወች የመኖር ዕድላቸውን ቧ አድርጎ የሚከፍት፦ ታሪክን በዓለም አደባባይ የሚያበጅ ልዩ አርት ነው እስፖርት። #በተረጋጋ አገር፤ ሥርዓት በተቋቋመለት አገር አትሌቲክስ አመክንዮዊ ዕውቅናም በበቂ አትኩሮትም ያገኛል። በኢትዮጵያ የአገር ውስጥ ጦርነቱ ብቻ ሳይሆን ተስፋን የሚነጥቁ ወጣ - ገባ አመራሮች ከውጭ በስተቀር ትርፈ ቢስ ይሆናሉ። እገታው፤ የሃዘን ቁልሉ፤ ሞቱ፤ ስደቱ እስሩ ሲታሰብ ህሊና ላላቸው አትሌቶች ጭንቅ ነው።
 
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የዛሬ ሦስት ዓመት የአነሳሁት ሊስተካከል ይገባል ያልኩት እራሱን ደገመ የማለት ያህል በውስጥ ባዘነ ስሜት መከፋታቸውን ገልጠውታል። መሪወችም ተመሪውም ሽሽት ላይ ከሆነ ማን ኃላፊ እና ተጠያቂ ይሁን???? ማን ጠያቂ? ማን ተጠያቂ ስል ክብርቷንም መንግሥታቸውንም ልጠይቅ እገደዳለሁኝ።
 
ክትትል የሚፈልጉ ጉዳዮች ዘመን እዬቆጠሩ ሳይሆን በመደበኛ ሊከወን የሚገባ ጉዳይ ይመስለኛል። በብሄራዊ ጉዳይ የአዘቦት ተግባር አይደለም። ገመና እኮ ነው እንደ ቄጤማ የተነሰነሰው በዓለም አደባባይ። እንደፓርኩ፤ እንደ ሌግዠሪ ሆቴሎች አትኩሮት ቢሰጠው ኖሮ ከደረጃ በታች ባልወጣ ነበር። ይህ የአትሌቶቹ ተግባር ብቻ ሳይሆን የመንግሥታዊው መዋቅር መሸብሸቡ ያመጣው መከራ ነው። ቢያንሥ ኢትዮጵያ የምትነግሥበት አትሌቲክስ እንደምን ትኩረት ይነፈገዋል??? ለዘባጣ አመራርን ወጌሻ መሆን እንደምን ይሳናል?።?
 
አገሬ በሚባል ቲቢ የጨመተች አትሌት ፍረወይኒ ኃይሌ የሰጠችውን አዳምጫለሁ፤ የአትሌት ጽጌ አሰልጣኝም ከእኛ ቲቢ ጋር ያደረገውን ቆይታ አዳመጥኩኝ። በአጠቃላይ ሳዬው #ዝርክርክ እና #ዝልግልግ የሆኑ ሁኔታወችን ነው የታዘብኩት። በመከፋት ውስጥ የሚመጣ ተስፋ ቆራጭነት አደጋው የሥነ - ልቦና ይሆን እና ለዘለቄታው ከተስፋ ውጪ ሊያደርግ ይገባል። #ማንም#ምንም ከአገር በላይ የለም። ቡቃያን የሚያሰናክል አረም ካለ ማስወገድ ግድ ይላል። አትሌቶቹ ጥሩ ሲያመጡ #ደረት የሚነፋውን ያህል፤ ሲደክሙም ችግሩን መርምሮ እልባት መስጠት ይገባል። ቀነ ቀጠሮም የሚያስፈልግ አይመስለኝም።
 
የገረመኝ ኢትዮጵያ በውስን አትሌቲክ ብቻ ለውድድር መቅረቧ ነው። እኔ ተማሪ እያለሁ አለሎ እና ጦር ውርዋሮ፤ ዝላይ፤ ባስኬት እና መረብ ኳስ፤ ሳይክል ነበሩ። #ገና ጨዋታም ታስቦ የማያውቅ የባህል ስፖርት ዘርፍ ነው።፦እነኝህ እንዴት ትኩረት አጡ??? ሌላም #ዒላማ በአትሌቲክስ አንድ የውድድር ዘርፍ ነው። ከሩጫ ጋር ተዋህዶ ሲቀርብ አያለሁኝ። በዚህ ዙሪያስ  ምን አይታሰብበትም።
 
 ሰፋ አድርጎ ውድድር ማድረግ ያኑ ያህል ሰፊ የማሸነፍ ዕድል ይኖራል፤ ዓለም ዓቀፍ ዕውቅናውም ያኑ ያህል ይመጣል።ሌላው መሠረታዊ ነገር ኢትዮጵያ ላይ በዞግ የተሸነሸነ መንፈስን ከአገር ውጪ ሲኮን በግሎባል ላይ እንደምን #ብሄራዊ ስሜት መፍጠር ይቻላል? ይህም ትልቁ መሰናክል ነው። ድሉ እራሱ በዞግ መንፈስ ተሸንሽኖ ነበር #የተሰጣው። ብሄራዊነት ከዲስኩር ያለፈ ተግባር አልቦሽ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ላይ ፈተና ውስጥ ነው። በዚህ ምክንያት #ኦሮምያ ክልል ልጆቹን ይዞ የተለዬ ሴሪሞኒ ፈጽሟል። በፍፁም #አልገባኝም#እንዲገባኝም አልፈቅድም።
#የሆነ ሆኖ።
 
የወንዶች እና የሴቶችን ማራቶን የተከታተልኩት #በሲዊዝ ሚዲያ ነበር። ከአትሌት አበበ ብቂላ ጀምሮ ያለውን ታሪክ በሚገባ የዳሰሰ ዘገባ ነበር ያቀረቡት። በወንዶች ማራቶን በአትሌት ቀነኒሳ ሰፊ ዕድል አጭቶ ነበር ሚዲያው። ለአትሌት ሻ/ ኃይሌም የሰጡት ክብር ድንቅ ነበር። ሲዊዝሻ ጭምት ስለሆነች ያ ምስክርነት ሲገርመኝ ውሎ አደረ።
 
ቅዳሜ በነበረው የወንዶች ማራቶን አትሌት ታምራት ቶላ በጀመረው የፍጥነት ልክ ነበር የጨረሰው። የነበረው ከምድብ አንድ ጉሩፖች ጋር ነበር። ፈጽሞ አልደከመም። ኮንፊደንሱ ይደንቅ ነበር። በተረጋጋ መንፈስ ነበር ለድል የበቃው።
 
በሴቶች ማራቶን ጥቂት ኪሎሜትር እስኪቀር ድረስ ሁለት አናብስት #ኢትዮጵያውያ አንስቶች ነበር ሲመሩ የነበሩት። እነሱም የተረጋጉ ብቻ ሳይሆን ይረዳዱም ነበር። ቅንነት በድንቅነት። በኋላ ላይ ጉሩፕ ሁለት የነበረችው አትሌትሲፋን ሃሰን ወደ ግሩፕ አንድ ተቀላቀለች። ይገርማል አጨራረስ ላይ በሰከንድ ልዩነት ነበር አትሌት ትዕግስት በአትሌት ሲፋን ሃሰን ተቀድማ የብር ሜዳሊያ አሸናፊ የሆነችው። ሁኔታውን የምታውቀው እሷ ስለሆነች ይህ ቢሆን፤ ያ ቢሆን ልል አልችልም። ግን ዕንቁ ዕድል #በመገፋት አጣች። አገፋፋም ስልታዊ ነበር። 
 
አትሌት ሲፋን ሃሰን በሴቶች 5000/10000 የነሃስ ሜዳሊያ በማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ለተወከለችበት አገር ለሆላንድ አስገኝታለች። የሆላንድ ደረጃ እንግሊዞችን የቀደመውም በእሷ የወርቅ ግኝት ነው። ለእሷም ለራሷም ታሪኳንም ጽፋለች። #መጋፋቷ ግን የተገባ አይመስለኝም። ይቅርታ ልትጠይቅበትም ይገባ ነበር። ሌላው ግን በዓለም የስፖርት መስክ እንዲህ ዓይነት ታክቲክ የሚጠቀሙ መጨረሻ ላይ ድንገተኛ ችግር ሊገጥማቸው ይችላል። ያላቀዱት። የአትሌት ሲፈን ሃሰን አቅም ግን የሚገርም ነው። 
 
አትሌት ትዕግስት እንደ ሥሟ ታግሳ ሁሉንም ነገር #በዝምታ #አንግሳወለች። ይህም ጨዋነት ነው። አሳዳጊሽን ይባርክ ያሰኛል።
 
#አሁን ወደ ተነሳሁበት አውራ አመክንዮ።
 
በዜና እንደሰማነው አትሌት ታምራት ቶላ #ተጠባባቂ ነበር። መደበኛ ሯጩ አትሌት ሲሳይ ለማ ነበር። ውስጡን አዳምጦ ዕድሉን ለተጠባባቂው አትሌት ታምራት ቱላ መስጠቱ #ታምር ነው። ታምሩንለታምራት የፈጣሪ ሥራ። ገድልም ነው። አትሌት ታምራት ቶላም የተሰጠውን ዕድል #ሳያባክን እግዚአብሄርም ረድቶት አሸናፊ ሆነ።
 
 በሁለቱ መሃከል ያለው የኃላፊነት እና የተጠያቂነት ውህድ ጥበብ ለትውልድ ብቻ ሳይሆን ዘመኑን በቅንነት ያነበበ፤ ያናገረ፤ የተረጎመ እና ያመሳጠረ ጭብጥ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። የአደራ ቅብብሉ ቃልኪዳኑን በወርቅ ሞሻሸረው። እንድጽፍም ያነሳሳኝ ይህ የአትሌት ሲሳይ ለማ የመወሰን አቅም ልቅና እና ንፁህ የሆነ ቅንነቱ እንዲሁም ርህርህናው ስለ እናት አገሩ ያለውን የተቆርቋሪነት ልክ አይቸበታለሁ።
 
ኢትዮጵያ የሚናፍቃት ከዲስኩር፤ ከፎቶ ሾፕ፤ ከከንቱ ውዳሴ፤ ከአጓጉል ፋክክር የተፈወስ ይህን መሰል ቅንነት ነው። ይህን መሰል ግለኝነትን ወደ መቃብር የላከ ጀግንነት ነው። የከበረ ሰብዕና አገርንም ትውልድንም ያስከብራል። ታሪክን በፋክት፤ በመርኽ፦ በዕውነት መፃፍ ማለትም ይኽን መሰል ራስን ለሚወዱት ራዕይ እና ግብ መገበር ነው። ተምሳሌቱ ቅኔ ነው። አዳኝም ነው ዕዝነ ህሊናው ላልተኮመታተረ ሰብዕና።
 
ው "ብልጥግና" ጨምሮ ተቀላች፤ ተጠማኝ፤ ተዋህጂ፤ ተፎካካሪ፤ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት መሪወች፤ የንቅናቄ አዝማቾች ይህን ከመሰለ ቅን አትሌት ምን ሊማሩ ይገባል? ዘመኑ ዛሬም ብቻ ሳይሆን ነገም የሚጠይቀው አቅም፤ ችሎታ፤ ክህሎት፤ ልምድ እና ተመክሮ ያላቸው ይቅደሙኝ የማለትን ጥልቅ ብልህነት፤ መጠነ ሰፊ ጥበብ ቢጋሩት ጥሩ ይመስለኛል። ለእኔ ክስተት ነው። ለመዳን - ለመፈወስ - ለመጽናት እና ለመዝለቅ ቅንነት እንዲመራ መፍቀድ ምድራዊ ፃድቅነት፤ ሙያዊ ሐዋርያዊነት ነው ለእኔ።
 
“ክቡር ፕሬዚዳንታችን እርሶን ካላስከፋዎት …ሽልማቴን መመለስ እፈልጋለሁ” - አሰልጣኝ ገመዶ ደደፎ
«እንኳን ብቻ በደህና ሀገራችሁ ገባችሁ- ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ «
"ደራርቱ ቱሉ ዋሽታኛለች" አትሌት ፍሬወይኒ ሀይሉ | ሀገሬ ስፖርት | ሀገሬ ቴቪ»
"ስልክ ወረወረብኝ!"ፓሪስን እንደረገጠ የተባረረው የፅጌ ዱጉማ አሰልጣኝ የደረሰበት ግፍ ተናገረ ! «|Paris 2024 Olympics | Tsige Duguma
 
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
14/08/2024
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።