ክፋ ሃሳብ #ይጋባል። ያገባልም።ክፋ ሃሳብ #ተጓዥም ነው።
ክፋ ሃሳብ #ይዛመታል። ሲንቀሳቀስ #ፈጣን ነው። እንደ እኔ ዕሳቤ ከብርሃን ፍጥነትም ይቀድማል የሚል ዕምነት ነው ያለኝ። ምንም እንኳን ጥናታዊ ሥራወችን ለመከወን ሁኔታው ባያመቸኝም።
የሆነ ሆኖ ክፋ ሃሳብ የሰውን ልጅ ትዳሩ አድርጎ አግብቶ የመኖር አቅም አለው። ከአንዱ ክፋ አሳቢ ተነስቶ ሌላውን ለማጥቃትም ሲነቃነቅም፦ ማለትም ክፋቱን #ለማጋባት ቀላል ፎርሙላ ነው ያለው ነው። ያም መቻቻልን፤ ታጋሽነትን ነጥቆ እያጣደፈ ከሚቀቅለው የክፋ ሃሳብ ውቅያኖስ ወስዶ ይዶላል።
ክፋ ሃሳብ ማስተዋል ላይ ጫና ፈጥሮ ወደ ድርጊት ተሎ የመንቀሳቀስ አቅም አለው ብዬም አምናለሁ። ለክፋ ሃሳብ #ህግ የተፈጥሮ፤ ሰው ሠራሽ #ድንጋጌወች፤ #ባህላዊና #ትውፊታዊ ተለምዶወች ግድ አይሰጠውም። ይሉኝታ አያውቅም። ለነገሩ ይሉኝታ ያላት ብቸኛዋ አገር ኢትዮጵያ ናት።
የሆነ ሆኖ ክፋ ሃሳብ ተጣዳፊ እና ሽሚያ ላይ ዘመኑን ሁሉ ስለሚሰዋ የማጥቃት አቅሙ ኃያል ነው። ክፋ ሃሳብ የሚንቀሳቀሰው #በቲምም ነው። የቲሙ አባላት መለያቸው #ተበቅለው የማይጠግቡ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፦ አዲስ አባላትን ለማፍራት ጥድፊያቸው ለጉድ ነው። ፤ #ጦርነት አነሳሹ፤ ማንኛውም ዐይነት ወንጀል፤ #ጥላቻ፦ ዘረኝነት፤ አግላይነት፤ ተጫኝነት እኮ የክፋ ሃሳብ የቲም አባላት ናቸው። ክፋ ሃሳብ ቁንጥንጥ እና ስክነት የነሳው ነው።
ምክንያቱም ማስተዋልን ተረግጦ ተልዕኮውን ስለሚያስፈጽም።
ለምሳሌ አቶ "ሀ" አቶ "ለን" ሲገድለው #ገዳዩ #ክፋ #ሃሳብ ነው። አዝማቹ ክፋ ሃሳብ ነው። አቶ #ሐመርኋ አቶ #ሰን ከመኖሪያ ቀዬው ሲፈናቅለው፦ #አፈናቃዩ ክፋ ሃሳብ ነው። ለዬትኛውም ሰዋዊ የበደል ዓይነት፤ የቅሬታ ምንጭ ገፊው አስፈፃሚው ክፋ ሃሳብ ነው። ክፋ ሃሳብ ተሽቀዳድሞ የሚቆጣጠረው #ህሊናን ነው። ፋታ ነስቶ ያቀደውን ሲያስፈጽም ቅድመ ሁኔታ የለውም። ያጣድፋል። ያሯሩጣል።
ክፋ ሃሳብ ተናዳፊም ነው።
ክፋ ሃሳብ #ገረጭራጫ ነው።
ክፋ ሃሳብ #ብስጩ ነው።
ክፋ ሃሳብ #ንዴታም ነው።
ክፋ ሃሳብ #አደብ የለሽ ነው።
ክፋ ሃሳብ ተፈጥሮውም ክንውኑም ስክነት አልቦሽ ነው።
ክፋ ሃሳብ …… ሁሉን የክፋ ሃሳብ የብቀላ ሂደቶችን ሲፈጽም እና ሲያስፈፅም ዕብኑን ነው። አቅሉም መቅኖውም በሸሸው ወቅት ነው ድርጊቱን የሚፈፅመው። እራሱን መቆጣጠር መምራት ሲያቅተው። ክፋ ሃሳብ ክፋትን አሽኮኮ አድርጎ የሚኖር ከመሆኑም በላይ፥ ክፋ ሃሳብ በሌላው ታዝሎ ሰብዕናን ብክንክን የሚያደርግ የራስም አንጡራ ጠላት ነው።
ይህን በቤተሰብ፤ በተቋማት፤ ስትመዝኑት የጠፋንበትን መሠረታዊ አመክንዮ ታገኙታላችሁ።
ክፋ ሃሳብ አመንጪወች፦ ተርጓሚወችም እኛ ብቻ አይደለንም። ጉዳዩ ግሎባል ነው። እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ ከክፋ ሃሳብ ጋር አልተወለደም። ህፃናት ሲወለዱ ቅዱስ ሆነው ነው። ነገር ግን ቅድስናቸው በተፈጠረበት ልክ እንዳይቀጥል ዓለማችን የምድርን ክፋ ሃሳብ የሚመክት ተቋም የላትም። ክፋ ሃሳብ ገኖ፤ ወንጀል ተበራክቶ፤ ጦርነት ለምልሞ፤ ጥላቻ ነግሶ የሚገኘውም ዓለማችን ጨለማን ለመመከት መብራትን እንደፈጠረች ሁሉ ክፋ ሃሳብን የሚመክት #የትምህርት #ሥርዓት አልነደፈችም።
ስለዚህም ክፋ ሃሳብ አሸናፊ ሆኖ እንሆ ይፈነጫል። ሥልጣኔን // ሥልጣኔ እንዲያጠፋው ቦንቡ፤ መትረዬሱ፤ ሮኬቱ፤ ተዋጊ አውሮፕላኑ ድሮኑ ትርሊዮን ዶላር ይፈስለታል። የዚህን 1/10 እንኳን ዓለማችን #ለፍቅር #ተፈጥሮ #አታጠፋም። አጀንዳዋም አይደለም። እቴጌ ዓለማችን የሃይማኖት ተቋማትን የሚደግፍ #የሥነ - ምግባር ሥርዓተ - ትምህርት ብትነድፍ ቢያንስ ቀጣዩ ትውልድ እፎይ ብሎ የመኖር ዕድል ያገኝ ነበር። ክፋ ሃሳብም በዬሄደበት መፈረሹን መግታትም ይቻል ነበር።
ዓለማችን ክፋ ሃሳብን ለማሸነፍ አስባ ባታውቅም እኛ ግን የክፋ ሃሳብ ተቀማጭ በውስጣችን ተደላድሎ ተቀምጦ እንዳይጋልበን፦ ክፋ ሃሳብ እንዳይራባ እንዲመክን፤ ክፋ ሃሳብ ፍሬ ሳያፈራ እንዲቀር፦ እንዳይለመልም ማድረግ እንችላለን። ምንም ወጪ አይጠይቅም። ምንም ጉልበት አይሻም።
ክፋ ሃሳብ በውስጣችን ተራብቶ እኛኑ ከማሳጣቱ በፊት እኛው እራሳችን አክ ልነለው እንችላለን። የክፋ ሃሳብ ሎሌነትን አብሶ በነፃነት ለኖረ ሕዝብ አይመጥነውም።
ነፃነት የሰጡን ቀደምት አበው እና እመውን ምስጋናችን ለመግለጽ እኛን ከክፋ ሃሳብ ጋር ማፋታት ነው። ለነገሩ ነፃነት በሰጡም ይወቀሳሉ ይነቀሳሉ።
ይህም የክፋ ሃሳብ ተገዢነት ነው። ከነፃነት በላይ የሰው ልጅን ደልዳላ እና ሙሉ የሚያደርግ ክስተት የለም። በራስ የመተማመን አቅሙ እኮ ምንጩ የነፃነት አቅም ሙሉዑነት ነው። አለን። የኛ ብቻ የምንለው እኮ ነፃነት የሰጠን ልዩ ሽልማት ነው።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
29/08/024
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ