የኔታዋ የቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት የምህላ ተደሞ ጎንደር በአርምሞ! ከጥቅምት 01 ቀን እስከ ህዳር 10... ይህ ፀጋ ነው አሁን አናርኪዝም የሚባል ባላንጣ እንደ #ዳንቴል በእጅ ተሠርቶ ከፈጣሪዋ ጋር ጎንደርን እዬነጠላት የሚገኜው።

ይህ ፀጋ ነው አሁን አናርኪዝም የሚባል ባላንጣ እንደ #ዳንቴል በእጅ ተሠርቶ ከፈጣሪዋ ጋር ጎንደርን እዬነጠላት የሚገኜው። ጎንደር እንደ እኛ እንደ እያንዳንዳችን የሚቀናባት #በዕት ናት። ማይክ የያዘ ሁሉ ሲያብጠለጥላት ውሎ ያድራል። ከዛች በዕት የተገኙ ልጆቿም ቀና ባሉ ቁጥር ቅጥቀጣው፤ እገታው የላይኛው ያውቀዋል። እነሱም ችግሩ እራሱ አኃቲ ልቦና ፈጥሮላቸው አይተዛዘኑም።
 
ልጆቿም የሌላ #ጌጥ ናቸው እንጂ ስለ እትብቴ የተቀበረባት ብለው አስበው አያውቁም። የራሷ ልጆች እየገፏት እሷ ግን አክብሮት #ነፍጋቸው አታውቅም። የጎንደር #ሳቋ #የሚኮሰኩሳቸው በርካታ ናቸው። ሳያውቋት ሂደው ሳያዮዋት ግን ማቱን ሲያዝንቡባት ውለው ያድራሉ። አንድ ፔና ያልገዛ አንጋች ካልሆንክ ብሎ ልጆቿን ቁሚ ተቀመጪ ሲላት ውሎ ያድራል።ይህ ሁሉ ተከማችቶ እንሆ ጎንደር የሥርዓት አልበኞች መፈንጫ #ትንሿ #መቋድሾ ሁና አረፈችው። እንደ ተመኙት አደረጉት።
 
ይገርሙኛል የክፋ ሃሳብ ድውያን የማይገናኜውን አምጥተው አገናኝተው ጎንደርን ሲዘለዝሉ፤ ሲያዘላዝሉ እንደምን ችለው ቤተሰቦቻቸውን እንደሚመሩ ሁሉ ይገርመኛል። ጎንደር ወደምድር ብትሰምጥ ወይ ብትተን ይመኛሉ። ለዚህ ብቻ የተፈጠሩ እስኪመስለኝ ድረስ። ዝም እምለው ክፋ ሃሳብ ትርፋ ክፋት መሆኑን ጠንቅቄ ስለማውቅ አንድዬ አንተ ሁናት ብዬ ዝም እላለሁኝ። ለሞቱ ጊዜ ግን ትፈለጋለች። ወጣት ናሆሰናይ የተገበረው በዚህ ካልኩሌሽን ነበር። የጎንደር መናጥ ታልሞ። ማን አተረፈ??? ምን ተረፈ???
 
በመጨረሻው የጎንደር ጥምቀት በአንድ ቀን 28 ጊዜ በረራ እንደ ነበር አድምጫለሁ። በአውቶብስ የመጓዝ አጋጣሚው ቢኖርም ያኑ ያህል ይሆን ነበር። ግን ዋስትና የለም በአውቶብስ መጓዝ። ፈልጌ እማዳምጠው የተጋሩ ተዋህዶወችን ነበር። አዳኞች ስለሆኑ። የእነሱ መንፈስ ቅድስናው ስለሚያጽናናኝም። 
 
የሆነ ሆኖ በአመት አንድ ቀን ለሚገኝ የጎንደር ፍካት ቁርጥማት የሚሆንባቸው የክፋ ሃሳብ ተሸካሚወች ግን አይተኙም። እንዳሰቡትም አነኩረው አነኩርው ተሳካላቸው። ይህን የሰከነ ህዝብ ፁሞ ፆሙን እንዲፈታ እንኳን አለፈቀዱለትም። ትናንትም ዛሬም ይህን ቢዲዮ እያዬሁኝ እንደገና ለመመለስ የሚፈጀውን ጊዜ አሰላሁኝ። ይቻል አይቻል አላውቅም። በአዘቦቱ ቀን ነው ሥጋ ቤቶች ተዘግተው ይህን የመሰል ህዝባዊ ድንቅ ዕፁብ ድንቅ አርምሞ የሚካሄደው። 
 
#ከተማ ላይ #ውጊያ???? ያውም ጎንደር ላይ??? እንደ ሻሸመኔ፤ እንደ አጣዬ?? ደሴ በፀጥታዋ ውስጥ ናት። ለምን? ዋርካው ምሬ ከአባቶቹ #ጥበብ ጋር በመሆኑ። የእኔ አማኑኤል ይጠብቅልኝ። አሜን። አንድ #ከተማ የራሱ #ማንነት አለው። አንድን ጥንታዊ ከተማ 6/7/8/9/10 ትውልድ ቢተካካ ፈፅሞ ሊመልሰው አይችልም ጥንታዊ ከተማ እራሱን ካጣ። 
 
አይደለም ከተማው #መንፈሱን መመለስ አይቻልም። በዚህ ቢዲዮ ያለውን መንፈስ ደግሞ አምጦ ለመውለድ አይቻልም። እችላለሁ ቢባልም ብዙ አቅም ለዛውም የሰከነ አቅም እና ልዩ ክህሎት ይጠይቃል። ያን ሁሉ ከጎንደር እስከ አዲስ አበባ መታመስ ያቁላሉት ነፍሶች ዛሬ እስከ ቤተሰቦቻቸው #ስደት ላይ ናቸው። ይቅናቸው። 
 
አማራጭ የሌለው ህዝብ ግን በዕንባ እና በስጋት እንሆ #ተቀቀለ#ረመጡ ኑሮህ ይሁን ተባለ። ጉዳዩ ሲወጠን ጉዞው #አናርኪ ስለነበር ተው ብዬ ፃፍኩኝ። ሰሚ አላገኜም። ከዛ በኋላ ቅንጣት አቅም አላዋጣሁም። በዝምታ ውስጥ ጠንክሬ የምሠራባቸውንም ተግባሬን ተግ አድርጌ ሁኔታውን ተከታተልኩኝ። ጥምቀት ቢመጣ ሦስት ዓመት። እኔ ብቻ አይደለሁም ሌሎችም እንዲሁ። 
 
የህወሃት ስንብት በበዛ #በጩኽት አልነበረም። በላቀ ልባም ጥበብ እንጂ። ለዚህም ነበር ሰላማዊ ሽግግር የነበረው። የማይቻለው የተቻለው በላቅ ጥበብ - በስልት እና በጥሞና ስለተከወነ ነበር። ለሚዲያ ፍጆታ ባልዋለ #ልባም ጥበብ። ህወሃት መንበሩን ከለቀቀ በኋላም ዱላቸው ለህወሃት ያላባራ ነፍሶች ሳይ ይገርመኝ ነበር። ፈቅዶ ሥልጣን ከመልቀቅ በላይ ምን ያድርግላቸው ህወሃት?
 
የኢትዮጵያ ፖለቲካ በእጁ ባለው ዕድል እና ድል ከመጠቀም የሌለውን ሲያልም የህዝብ እልቂት እና ጉስቁልናን እንደ መደበኛ ተግባር ሲከውን ይታያል። ያልታደለ።
የሆነ ሆኖ ጎንደርን በጥርስ ለያዛችሁ የክፋ ሃሳብ ተጠቂወች አሁንስ ይህ ሐሴታችሁን ይመልስላችሁ ይሆን??? 
 
አማራነት እና አማራዊ ተጋድሎ ብርቱ ማስተዋል ይጠይቃል። እንኳንስ አማራነት ኢትዮጵያዊነት ሃሳብን በመከታተፍ ትውልድ አያድንም። ባህርዳርም ሐይቅም የጎንደር ነበር ሲባል እሰማለሁ። ይህ ማለት ውህድነቱ ተመስጥሮ አለ ማለት ነው። ጣና እና አባይ ሲገናኙ እንደምን ሆነው ለዘመናት አብረው ተጓዙ???? ጥበብ ቢኖር ሰውነት እኮ ከፈጣሪ ጋር እኩል መስሎ መፈጠር በቂ በሆነ ነበር። #ብንታደል
 
አንድ የፖለቲካ ድርጅት ማኒፌስቶ አለው። ማኒፌስቶው #ደንበሩ ነው። ያን ጥሶ ሲሄድ አንድም ሰው ሊከተለው አይገባም ነበር። #ሊጠዬፈው ይገባ ነበር። እራሱን አፍርሶ እንደምን ሌላውን ሊመራ ይችላል???? በዛ ስገረም ባጅቼ ……
 
አሁንም ሰሞኑን ጠሚ አብይ አህመድ ተመሳሳይ ግድፈት ፈጽመዋል። አናርኪ + አናርኪ= አናርኪዝም። በምን አግባብ ለብሄራዊ ሆነ ለውጭ ጉዞ ከንቲባ አዳነች አበቤን ይዘው እንደሚጓጓዙ አይገባኝም። የራውንዳ ጉዞ ላይ ነበሩ። የአባይ ግድብ እና የጎርጎራ ፕሮጀክትም ላይ ነበሩ። 
 
አሁን ደግሞ ጭራሽ የጎንደር ከተማ የበላይ #ከንቲባ ተደርገው መሾማቸውን አዳመጥኩ። የሥራ ደንበራቸው አዲስ አበባ ነው። ህግ ጥሶ ህግ ማስከበር አይቻልም። ፈጽሞ።
ውድቀትን ማፈስ ነው። ለነገሩ የአዲስ አበባው ከንቲባ እሳቸው ናቸው ዶር አብይ አህመድ። እራሳቸውን እንዳይመድቡ #ልጥፍ አስፈለጋቸው። ለጎንደር ከኮሪደር ልማት ይልቅ #ሳቋን ይመልሱላት። እልህ ከማን ጋር እንደተጋቡ አውቃለሁ። ቢያንስ እሳቸው የአገር መሪ ስለሆኑ ተሽለው ይገኙ። በሙሉ ድምጽ ለመረጠ ህዝብ #ቀለሃ ማቃም ፍትኃዊ አይደለም እና።
 
በሌላ በኩል በአገር ውስጥም በውጭም የጎንደሩን ፋኖ እንመራለን የምትሉም በአደብ ጥሞና ወስዳችሁ እራሳችሁን መርምሩ። ከጠሚር አብይ አህመድ የተሻላችሁ መሆናችሁን እንደ ዋርካው ምሬ ሆናችሁ አሳዩ። ከጨረሰለት ዋርካው ምሬ አያያዙ ይመስጠኛል። ለህዝቡ ያስባል። ካልተገደደ በስተቀር በግብታዊነት የሚፈጽመው አንዳችም ነገር የለም።
አናርኪዝም ማፍረስ ተግባሩ ነው። 
 
በህግ አልባነት ደግሞ ተጎጂዊ ሙሉ ማህበረሰቡ ነው። እንደ ገና ወደ ህጋዊ የአኗኗር ዘዬቤ ለመመለስ በዬትኛው የዊዝደም አቅም ለድል እንደሚበቃ አላውቅም። ለዚህ ነበር ማኒፌስቶ የስኳር መጠቅለያ መጋዚን አይደለም ብዬ አስቀድሜ የዛሬ ሦስት ዓመት በወርኃ አስተርዬ የፃፍኩት። 
 
ለነገሩ ጠሚ አብይ ከመጡ የጎንደር ከንቲባ ምደባ የጓሮ ጎመን ማለት ነው። ወደ 8 ከንቲባ ቀይረዋል። ነገም ይቀይራሉ። ከአዲስ አበባም ወስደው የሾሙት ነበር። አንገዋለው አባክነው ያስቀሩት ልዩ አቅምም ነበር። የሚመሩትን ህዝብ እና አገር እንደ ጥንቸል መሞከሪያ ጣቢያ ማድረግ ለምድር ወንጀል፤ ለሰማዩም ኃጢያት ነው።
 
ጎንደርዬን ብቻ ሳይሆን በዕንባ ውስጥ ያሉትን ምንዱባን ሁሉ እግዚአብሄር ያጽናቸው። እኛም እረፍታችን ሰላማዊ ይሆን ዘንድ አማኑኤል ይርዳን። አሜን። እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
03/09/2024
ከአናርኪዝ ትርፍ የለም።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።