"ኢትዮጵያውያን በሊባኖስ፡ በእስራኤል የአየር ጥቃት ስር በምትገኘው ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሁኔታ" ፈጣሪ ይጠብቃቸው። አሜን።

 https://www.bbc.com/amharic/articles/cx257vzkxxyo

 

ኢትዮጵያውያን በሊባኖስ፡ በእስራኤል የአየር ጥቃት ስር በምትገኘው ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሁኔታ 

 

"እስራኤል ተደጋጋሚ ጥቃት እየፈፀመችባት ባለችው ሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስጋት ላይ መሆናቸውን ለቢቢሲ ገለፁ።

ቢቢሲ ካነጋገራቸው በቤይሩት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዷ የሆነችው ትዝታ ነዋሪነቷ በደቡባዊ ሊባኖስ ቢሆንም የእስራኤል ጥቃት ግን እርሷ ከምትኖርበት ራቅ ያሉ አካባቢዎች ላይ እየደረሰ መሆኑን ተናግራለች።

የአየር ድብደባ ሲደርስ እርሷ በምትኖርበት አካባቢ እንደሚሰማ፣ ከአየር ድብደባው የተነሳ ቤቶች እንደሚነቃነቁም ትናገራለች።

“በባሕር ዳርቻው አካባቢ የሚኖሩ፣ ለምሳሌ ሱራ አካባቢ፣ መውጫ አጥተው ልጆቻቸውን ይዘው ባሕር ዳርቻው አካባቢ ያደሩ ሰዎች [ኢትዮጵያውያን] አሉ” ስትል ከጥቃቱ ለመሸሽ በወጡ ሰዎች መንገዶች መዘጋጋታቸውን ተናግራለች።

የእስራኤል አየር ኃይል ከፍተኛ ጥቃት እየፈጸመባቸው ካሉ የሊባኖስ ግዛቶች ለመውጣት መኪኖቻቸውን እና ያገኙትን መጓጓዣ እየተጠቀሙ በመጣደፍ ላይ ሲሆኑ፣ ዋና ዋና ጎዳናዎች በተሽከርካሪዎች ተጨናንቀዋል።

ከዚህ ቀደም 20 ደቂቃ ይፈጅ የነበረው መንገድ አሁን ከስምንት እስከ 16 ሰዓት ይወስዳል ስትልም መንገዶች ከጥቃቱ በሚሸሹ ሰዎች መጨናነቁን ትናገራለች።

በሊባኖስ የኢትዮጵያውያን በጎ አድራጎት ድርጅት የሆነው ‘እኛ ለእኛ በስደት’ ምክትል ዳይሬክተር እና በቤሩይት ነዋሪ የሆነችው እኑ በበኩሏ በእስራኤል የሚፈጸመው “ጥቃት እየከፋ” መምጣቱን ትናገራለች።

ወትሮም በአስቸጋሪ ሁኔታ በሊባኖስ ውስጥ በቤት ውስጥ ሥራ ላይ ተሳማርተው ለሚገኙት ኢትዮጵያውያን እንዲህ ያለው ቀውስ ችግራቸውን የበለጠ ያባብሰዋል።

በእስራኤል የእየተፈጸመው ያለው የአየር ድብደባ እየተጠናከረ ቢመጣም ለኢትዮጵያውያኑ ግን እየተደረገላቸው ያለ ድጋፍ አለመኖሩን እኑ ጨምራ ተናግራለች።

ትዝታ በበኩሏ በጥቃቱ የተነሳ በአገሪቱ አለመረጋጋት በመፈጠሩ ወጥታ ለመሥራት አለመቻሏን እና ቤት ውስጥ ተቀምጣ “የሚሆነውን እየተጠባበቅኩ ነው” ብላለች።

አብዛኛዎቹ ሊባኖሳውያን ከሚፈጸመው የአየር ጥቃት ለመሸሽ ረጅም ሰዓት ተጉዘው ከደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል ራቅ ወዳሉ እና የእስራኤል ጥቃት ወደማይደርስባቸው አካባቢዎች በመሄድ ላይ ናቸው።

ትዝታ ግን በማታውቀው አገር ወደየት መሄድ እናዳለባት እርግጠኛ አይደለችም። “ከቤቴ ወጥቼ 16 ሰዓት ሙሉ መንገድ ላይ ምን እንደሚደርስብኝ በምን አውቃለሁ? እዚሁ ሆኜ ፈጣሪ የሚያመጣውን መጠበቅ ይሻለኛል” በማለት በቀጣይ ቀናት የሚፈጠረውን በተስፋ እየጠበቀች ነው።

የሊባኖስ መንግሥት 50 ሕጻናትን ጨምሮ ከ550 በላይ ሰዎች በእስራኤል የአየር ጥቃት መሞታቸውን አስታውቋል።

በርካቶች ከደቡባዊ ሊባኖስ ቤተሰቦቻቸውን በመኪኖቻቸው አጭቀው አንጻራዊ ሰላም አለ ወደሚሉባአው ቦታዎች እየተሰደዱ መሆኑን የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን እየዘገቡ ነው።

በአገሪቱ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ለተፈናቀሉ ዜጎች በመጠለያነት እያገለገሉ ነው።

በሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ በቤሩት የምትገኘውን እኑ ስታስረዳ “ሁኔታው በጣም አስፈሪ ነው” ትላለች።

የእስራኤል የአየር ጥቃት ከድንበር አካባቢ ወደ መሃል ቤይሩት እየመጣ ነው የምትለው እኑ፣ ስላለው ሁኔታ ቶሎ ቶሎ መረጃ እንደሚደርሳቸው ትናገራለች።

በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እስራኤል የሂዝቦላህ ዒላማዎች በምትላችው ላይ ጥቃት መክፈቷን ተከትሎ “ከፍተኛ ችግር ውስጥ” መሆናቸውን እኑ ጨምራ ለቢቢሲ ተናግራለች።

መንግሥት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶቾ ጥቃቱ ከሚፈጸምበት ስፍራ ለሚፈናቀሉ ሰዎች የተለያዩ አካባቢዎች መጠለያዎችን ማዘጋጀታቸውን የሚናገሩት ሁለቱ ኢትዮጵያውያን፣ እነርሱም ለኢትዮጵያውያኑ ይህንን መረጃ ባላቸው መንገድ ሁሉ እያደረሱ እንደሆነ ይናገራሉ።

የእኛ ለእኛ በስደት ምክትል ዳይሬክተር የሆነችው እኑ “ትናንት [ሰኞ] ለምሳሌ ዳህዬ ከሚባል አካባቢ ወደ እኛ የመጡ [ኢትዮጵያውያን] አሉ። እዚያ አካባቢ ይመታል ተብለናል እና መሄጃ የለኝም፤ ከዚያ አካባቢ ነው የመጣሁት ብላ እኛ ጋር አንድ ኢትዮጵያዊት መጥታ” እንደነበር እና ከኢትዮጵያ ቆንስላ ጋር መነጋገሯን ገልጻለች።

ምንም እንኳ በቤይሩት የሚገኘው የኢትዯጵያ ቆንስላ የጥንቃቄ መልዕክት በይፋዊ የማኅበራዊ ሚድያ ገጹ ላይ ቢያጋራም “ያገኘነው ምላሽ ግን አስደሳች አይደለም” ትላለች።

“እኛ ማድረግ የምንችለው መረጃ ማሠራጨት እንጂ ሰዎችን ተቀብሎ ማስጠለል አንችልም፤ ምክንያቱም የቱ አካባቢ ደኅንነቱ የተጠበቀ እንደሆነ አናውቅም” በማለት ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን አመልክታለች።

ቢቢሲ በሊባኖስ ቤይሩት የሚገኘውን የኢትዮጵያን ቆንስላ ጽ/ቤት ወክለው እየሠሩ እንደሆነ የገለጹትን ባለሥልጣን ስለ ጉዳዩ ቢጠይቅም፣ አዲስ አበባ የሚገኘውን “የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን አነጋግሩ” በማለት መረጃ መስጠት ኃላፊነታቸው እንዳልሆነ ተናግረዋል።

በቤይሩት ሊባኖስ የሚገኘው ቆንስላው በሊባኖስ እና አካባቢው ያለው የፀጥታ ስጋት እና ውጥረት “ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ” መምጣቱን በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ ባጋራው የጥንቃቄ መልዕክት ላይ ገልጿል።

በደቡባዊ ሊባኖስ እና ቤይሩት የሚደርሱ ጥቃቶች ተጠናክረው መቀጠላቸውን በመግለጽ የጥንቃቄ መልዕክቶችን ለኢትዮጵያውያን አስተላልፏል።

ከእነዚህ መልዕክቶች መካከልም የጥቃት ዒላማ ይሆናሉ ተብለው ከሚታሰቡ ቦታዎች ራስን ማራቅ እና በሊባኖስ መንግሥት የሚሰጡ መመሪያዎችን መተግበር እና ማክበር የሚሉ ይገኙባቸዋል።

በእስራኤል ጥቃት ኢትዮጵያውያን ላይ ጉዳት ወይንም ሞት ስለመድረሱ የተጠየቀችው እኑ፣ እስካሁን ባለው መረጃ መሠረት፣ የሞቱ ሰዎች ፎቶ በተለያዩ አካላት በማኅበራዊ ሚድያ ስለሚጋራ፣ በኢትዮጵያዊ ላይ ስለደረሰ ምንም ዓይነት ጉዳትም ሆነ ሞት አለማየታቸውን ተናግራለች።

“ሊባኖሳውያን፣ ሶሪያውያን ናቸው በአብዛኛው መሞታቸው እየተዘገበ ያለው። ጉዳት የደረሰባቸው ኢትዮጵያውያን አሉ ወይ ለሚለው እስካሁን የምናውቀው ነገር የለም።”

የቤይሩት አውራ ጎዳናዎች በመኪኖች ከደቡብ ሊባኖስ ወደ ዋና ከተማዋ በሚሸሹ ሰዎች “በጣም ተጨናንቀዋል” የምትለው እኑ፣ ከቤይሩት ወጣ ብሎ ደኅንነታቸው የተጠበቀ ነው ተብለው የሚታሰቡ አካባቢዎች የቤት ኪራይ በጣም መወደዱን ገልጻለች።

በቤይሩት ትምህርት ቤቶች እና መሥሪያ ቤቶች ዝግ መሆናቸውን የሚገልጹት እኑ እና ትዝታ በውስጥ ለውስጥ መንገዶች የሚደረግ እንቅስቃሴም የተቀዛቀዘ መሆኑን ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ትዝታ አክላም በትምህርት ቤቶች ከተጠለሉት መካከል ኢትዮጵያውያን ሊገኙበት እንደሚችሉ ገልጻ፤ “አይኦኤም [የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት] ያነሳት ልጅ እንዳለች ሰምቻለሁ። ጠጋ ብዬ አላየሁም እንጂ ሌሎችም ይኖራሉ” ስትል ተናግራለች።

በተደጋጋሚ የመገናኛ ብዙኃንን የሚከታተሉ እና በፍርሃት ውስጥ ያሉ ሰዎች እንደሚታዩ የምትናገረው እኑ በአጠቃላይ “ድባቡ ያስፈራል” ብላለች።

ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን በአብዛኛው በቤት ውስጥ ሥራ ላይ ተሰማርተው በሊባኖስ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ ባለፉት ዓመታት አገሪቱ ባጋጠማት የምጣኔ ሀብት እና ፖለቲካዊ ቀውስ ምክንያት ለተለያዩ ችግሮች ሲጋለጡ ቆይተዋል።

በጋዛ ውስጥ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ባለፈው አንድ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ የሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ ከደቡባዊ ሊባኖስ በመሆን ከእስራኤል ጋር ድንበር ዘለል የሮኬት ጥቃቶችን ሲፈጽም እስራኤል ደግሞ በአውሮፕላን እና በከባድ መሳሪያ ምላሽ ስትሰጥ ቆይታለች።

ካለፈው ሳምንት ማብቂያ ወዲህ ደግሞ በሁለቱም ወገኖች በኩል የሚፈጸመው ጥቃት ከመጠናከሩ ባሻገር እስራኤል ከባድ የአየር ድብደባዎችን የሄዝቦላህ ይዞታዎች ናቸው ባለቻቸው የሊባኖስ ግዛት ውስጥ እየፈጸመች ነው።"


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።