"በሰሜን ጎጃም ዞን ድሮንን ጨምሮ በተፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ ሰዎች መገደላቸውን የዓይን እማኞች ተናገሩ" bbc
https://www.bbc.com/amharic/articles/c8elz7gzg8jo
በሰሜን ጎጃም ዞን ድሮንን ጨምሮ በተፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ ሰዎች መገደላቸውን የዓይን እማኞች ተናገሩ
18 ጥቅምት 2024
በአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞን ደቡብ ሜጫ ወረዳ “የመንግሥት ኃይሎች” ከጥቅምት ወር መጀመሪያ አንስቶ ፈጸሟቸው በተባሉ ጥቃቶች ከ100 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የዓይን እማኞች እና ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።
በወረዳው ዋና ከተማ ገርጨጭ ከጥቅምት 01 እስከ ጥቅምት 04/2017 ዓ.ም. በድሮን ጥቃት እና በዘፈቀደ በተፈጸሙ ጥቃቶች ህጻናትን ጨምሮ ሽማግሌዎች እንዲሁም ወጣቶች መገደላቸውን የሟች ቤተሰቦች እና ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ስለተፈጸሙት ግድያዎች ሪፖርቶች እንደደረሱት እና መረጃ እያሰባሰበ መሆኑን ለቢቢሲ ገልጿል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የፋኖ ኃይሎች አካባቢውን ለመቆጣጠር ጥቃት መፈጸማቸውን ገልጾ፤ “53 የጽንፈኛው አባላትን” መግደሉን አስታውቋል።
አርብ ጥቅምት 01/2017 ዓ.ም. እኩለ ቀን 7፡00 አካባቢ በከተማው የሚገኘው መሀል ገነት ጤና ጣቢያ ላይ በተፈጸመ “ተደጋጋሚ” የድሮን ጥቃት የዘጠኝ ዓመት ህጻንን ጨምሮ ስምንት ሠዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በተፈጸመው ተደጋጋሚ ጥቃት ከጤና ጣቢያው ባሻገር በአቅራቢያ የነበሩ የግለሰብ መኖሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት እንደደረሰ ገልጸዋል።
“ጢዝ የምትል ድምጽ ዓይነት አላት። አሞራ መስላ ስትመጣ የምትጥለው በጣም የሚፈነዳ ነገር አላት” ሲሉ ድሮንን የገለጹ አንድ የዓይን እማኝ፤ ጥቃቱ ተከትሎ ሰባት አስከሬን አንድ ላይ መገኘቱን ተናግረዋል።
ለደኅንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የዓይን እማኝ የሆኑ አንድ የጤና ጣቢያው ባለሙያ ደግሞ በጥቃቱ የመሀል ገነት ጤና ጣቢያ መድኃኒት ቤት (ፋርማሲ) እና ገንዘብ ቤት መውደሙን ገልጸው ስምንት ሠዎች መገደላቸውን አረጋግጠዋል።
ከሟቾቹ ውስጥ አንዱ የጤና ባለሙያ (ፋርማሲስት) መሆናቸውን ለቢቢሲ የተናገሩት ባለሙያው፤ ለህክምና የመጡ እና በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች እንደተጎዱ ገልጸዋል።
ሟቾቹ ከዘጠኝ ዓመት ህጻን እስከ 70 ዓመት አዛውንት ይደርሳሉ ያሉት ነዋሪዎች፤ የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ ሰባት ሰዎች መቁሰላቸውንም ተናግረዋል።
ነዋሪዎች የድሮን ጥቃቱ ሲፈጸም በአካባቢው ለቀናት የቆየ ውጥረት እንደነበር ጠቁመው፤ በከተማዋ ግን የፋኖ ታጣቂዎች እንዳልነበሩ አመልክተዋል።
ከሰዓት በኋላ 11፡30 ገደማ የፋኖ ኃይሎች ወደ ከተማዋ መግባታቸውን ተከትሎ ግን በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተጀመረው ውጊያ “ለአምስት ሰዓታት” ያህል መዝለቁን ገልጸዋል።
ውጊያው ጋብ ካለ በኋላ ከአርብ ጥቅምት 1 ምሽት ጀምሮ ባሉት ቀናት ግን የመንግሥት ኃይሎች ቤት ለቤት እና መንገድ ላይ ፈጽመውታል በተባለ ጥቃት በርካታ ሠዎች “እንደረተሸኑ” ስማቸውን እንዲገለጽ ያልፈቀዱ ሦስት ነዋሪዎች ተናግረዋል።
“የጥይት ድምጽ እና የሰው ጩኸት ስንሰማ ሁላችንም ፈርተን ከቤታችን ሳንወጣ ቆየን” ያሉ አንድ ነዋሪ፤ የፋኖ ኃይሎች ከወጡ እና ውጊያው ከረገበ በኋላ በየቦታው ግድያዎች ስለመፈጸሙ ተናግረዋል።
“በሰዓቱ እነሱን ማግኘት ስላልቻሉ በቀል ያደረጉት ሕዝቡ ላይ ነው” ያሉ ሌላ ነዋሪ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል ብለዋል።
“መንገድ ላይ፤ ቤት ለቤት የተገኘው ሁሉ ተመቷል። . . . እያወጡ መምታት ነው። እነሱ [የመንግሥት ኃይሎች] የሚሉት መሳሪያችሁን አምጡ ነው” ያሉ አንድ ነዋሪ፤ ጥቃቱ ‘የፋኖ ታጣቂ ናችሁ’ በሚል መፈጸሙን አመልክተዋል።
የመጀመሪያ ላይ በተፈጸመው የዘፈቀደ ግድያ ሰለባዎች አካባቢው ተረጋግቷል በሚል ወደ ቤታቸው ሲመለሱ የነበሩ 15 ገደማ ሰዎች መሆናቸውን የተናገሩት ነዋሪዎች፤ የማሽላ ማሳ ውስጥ መረሸናቸውን ተናግረዋል።
“ከዚህ በኋላ በየሰፈሩ ገቡ። በየቤቱ ገብተው ግለሰቦችን ‘ስትዋጉ ቆያችሁ፤ አሁን በሉ መሳሪያችሁን አምጡ’ አሏቸው። ከዚያ መረሸኑን ቀጠሉ” ሲሉ ቢቢሲ ካናገራቸው ነዋሪዎች መካከል አንዱ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
በመንግሥት ኃይሎች ተገድለዋል ከተባሉት መካከል በ30ዎቹ መጀመሪያ የሚገኝ ዘመዳቸው እንደሚገኝበት የተናገሩ አንድ ነዋሪ፤ ከአማቱ እና አብሮት ከነበረ የ17 ዓመት ልጅ ጋር ከቤት እንዲወጣ ተደርጎ መገደሉን ተናግረዋል።
የሟች ባለቤት የአራት ወር ነፍሰ ጡር እንደሆነች የተናገሩት ነዋሪው፤ ሟች በንግድ ሥራ ላይ የተሰማራ እንደነበር ገልጸዋል።
“በብዛት ደረታቸው እና ጭንቅላታቸው ላይ ነው የተመቱት” ሲሉ አንድ አስከሬኖችን ማንሳታቸውን የተናገሩ የዓይን እማኝ ድርጊቱ “ርሸና” ስለመሆኑ ተናግረዋል።
አንድ የሃይማኖት አባት ደግሞ “እኔ ራሴ ነፍሰ ጡር አንስቼ ፍታት አድርጌ የቀበርኳት አለች፤ እስከ ልጅ ፍሬዋ አፈር የለበሰች። በጥይት ነው የተመታችው። . . . የሰባት ወር ነፍሰ ጡር ናት አሉኝ” ሲሉ በርካታ ሰዎች መገደላቸውን እንሚያውቁ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“የመረጡት [ሰው] የለም” ሲሉ የጅምላ ግድያ መፈጸሙት የተናገሩት ነዋሪዎች ከጥቅምት 01 ጀምሮ በተፈጸመ ጥቃት የተገደሉ ሠዎችን እና የጠፉ ሠዎችን ቁጥር ከ200 በላይ እንደሚሆን ያምናሉ።
ቢቢሲ ስለተፈጸመው ግድያ እና በአካባቢው ስለነበረው ሁኔታ በስፍራው ከሚገኙ ገለልተኛ ወገኖች ማረጋገጥ አልቻለም።
“ጠዋት ስንወጣ መዓት ሬሳ [አገኘን]፤ ምኑ ተቆጥሮ ይዘለቃል? እንቅበር ብለን ቄሶችን ስንልክም አናስቀብርም አሉ። . . . እኔንም የምዘክረው ጊዮርጊስ ነው የተፋኝ [ያዳነኝ]” የሚሉ ሌላ ነዋሪም የሟቾች ቁጥር በተመሳሳያ ከፍተኛ ስለመሆኑ ያነሳሉ።
“እኛ ሰፈር ማርያም ቤተ ክርስቲያን እንኳን የተቀበሩ ሰዎች ከ50 በላይ ይሆናሉ” ሲሉ የሟቾች ቁጥር ከፍተኛ ነው ያሉ ሌላ ነዋሪ፤ ከቀናት በኋላ አስከሬን በጋሪ እየተሰበሰበ ቀብር መፈጸሙን ተናግረዋል።
አስከሬን እንዳነሱ የተናገሩ ሌላ ነዋሪ፤ “ሰባት፣ ስምንት የሆኑትን በጋሪ ነው የጫናቸው” ሲሉ ቀብርም በአብዛኛው በጅምላ መፈጸሙን ገልጸዋል።
ቢቢሲ ያናገራቸው በገርጨጭ የሚገኝ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የሆኑ አባት በሳምንቱ መገባደጃ ቀናት 72 የተገደሉ ሰዎች ቀብራቸው በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት መፈጸሙን ተናግረዋል።
የ27ቱ ሰዎች ቀብር እሳቸው በሚያገለግሉበት ቤተ ክርስቲያን መፈጸሙን ያረጋገጡት የሃይማኖት አባት፤ ወደ ሌሎች ቀበሌዎች አስከሬን መወሰዱንም የተናገሩ ሲሆን፤ በዚህም የሟቾች ቁጥር ከፍ ሊል እንደሚችል አመልክተዋል።
“ሐዘንተኛው ሰው [ለቅሶ] መድረስ ስለማይችል ድንኳን አልነበረም። አሁን እያደረ ከሦስት ቀን፤ ከአራት ቀን በኋላ ነው ሰው እንደ አዲስ [ለቅሶ] እደረሰ ያለው” ሲሉ ስጋቱን ገልጸዋል።
የምስሉ መግለጫ, ገርጨጭ (መሀል ገነት) ከተማ
በአካባቢው በርካታ ሰዎች ተገድለውበታል የተባለው ክስተት በተለይ ውጊያ በተካሄደበት አርብ ምሽት “ግድያው የከፋ” እንደነበር የሚናገሩት ነዋሪዎች ለሦስት ቀናት ቀጥሎ ነበር ብለዋል።
በከተማዋ ባለው ውጥረት እና ስጋት ምክንያት ነዋሪዎች ሕይታቸውን ለመታደግ ወደ ገጠር ቀበሌዎች መሸሻቸውንም ተናግረዋል።
የመሀል ገነት ጤና ጣቢያ ባለሙያዎችም ሸሽተው ከአካባቢው መውጣታቸውን የተናገሩ አንድ ባለሙያ፤ በዓመት ከ25 ሺህ በላይ ታማሚዎችን የሚያክመው ጤና ጣቢያው መዘጋቱንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የገርጨጭን ጥቃት ጨምሮ በግጭት አውድ በንጹሃን እና በሕዝብ መገልገያዎች ላይ የደረሱ ጉዳቶችን እየመረመረ መሆኑን ለቢቢሲ ገልጿል።
ከመስከረም 19/2017 ዓ.ም. ጀምሮ መከላከያ ወደ ወረዳው መንቀሳቀሱን የሚናገሩት ነዋሪዎች ይህን ተከትሎም የፋኖ ኃይሎች ወደ ገጠራማ ቀበሌዎች ማቅናታቸውን ተናግረዋል።
መከላከያ ገርጨጭ ከተማን ከመቆጣጠሩ በፊት ከአንድ ዓመት በላይ አካባቢው በፋኖ ኃይሎች ተይዞ መቆየቱን ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ቢቢሲ በአማራ ክልል ከሚገኘው ሰሜን ጎጃም ዞን እንዲሁም ከወረዳው በርካቶች ተገድለውበታል ስለተባለው ክስተት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ለቀናት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
መከላከያ ሠራዊት ጥቅምት 02/2017 ዓ.ም. በማኅበራዊ ሚዲያ የትስስር ገጹ የፋኖ ኃይሎች አካባቢውን ለመቆጣጠር ጥቃት መፈጸማቸውን ገልጾ፤ ከ50 በላይ የሚሆኑትን “የጽንፈኛው አባላትን” መደምሰሱን አስታውቋል።
በመስከረም አጋማሽ አዲስ “ሕግ ማስከበር” ዘመቻ መጀመሩን ያሳወቁት የመከላከያ ሠራዊት ቃል አቀባይ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ “[ፋኖ] የመረጠው ነፍጥ፤ ኃይል ነው። ስለዚህ ከዚህ በኋላ በመረጠው ቋንቋ መነጋገር መቻል አለብን ማለት ነው” ብለዋል።
*ቢቢሲ ለዚህ ዘገባ አምስት የአካባቢውን ነዋሪዎች ያነጋገረ ሲሆን፣ ሁሉም ለደኅንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዲጠቀስ አልፈለጉም።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ