ፋኖ ባክግራውንዱ "ሽፍትነት" አይደለም። ፋኖ አፈጣጠሩ ሲፈረካከስ ውሎ የሚያድረው የውራጅ ፖለቲካ ርዕዮት አልፈጠረውም።
ፋኖ ባክግራውንዱ "ሽፍትነት" አይደለም።
ፋኖ አፈጣጠሩ ሲፈረካከስ ውሎ የሚያድረው የውራጅ ፖለቲካ ርዕዮት አልፈጠረውም።
ሰማዕቱ የተከበሩ ጄኒራል ሰኃረ መንፈሳቸው ምን ይታዘብ ይሆን????
በኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት፤ አሠራር፤ አቅም፤ አመራር እጅግ ጠንቃቃ እና ቁጥብ ነኝ። ዛሬ በዚህ ዕርስ ዙሪያ ስጽፍ የዜግነት #ተጋርቶዬ እራሱ እያሰቃዬኝ ነው። በአንድ ላይ ኢትዮጵያዊ መባል ምን ያህል ፈተና መሆኑን ያዬሁበት አጋጣሚ ነበር።
"አቤቱ ለአንደበቴ ጠባቂ አኑርለት።"
የማከብራችሁ የአገሬ ልጆች ዘለግ ያለ ሙግት ነው።
የማህበረ ኦነግ ፖለቲካ - ልቅነቱ ብቻ አይደለም የሚያስገርመኝ። ይልቁንም የቁንጮ መሪወቹ የህግ ጥሰት #ህጋዊነት እንጂ። ብልሽቱን እኮ አስተካክሎ ማቅረብ ለካስ ይህም መሰጠትን ይጠይቃል። ሳይመረኝም፤ ሳያንገፈግፈኝም የኢትዮጵያ ኢታማጆር ሹሙ ጄኒራል ብርኃኑ ጁላ ከሉዓላዊ ሚዲያ ጋር የነበራቸውን ቆይታ ሁለቱንም አዳመጥኩት። መጥኔ ለአንቺ ኢትዮጵያ አልኩኝ።
እነ ክቡር ጄኒራል ፈንታ በላይ እና ፍፁም ድንቅ እና ብቁ ጓዶቻቸው የነበሩባት አገር እንዲህ እና እንዲያ ስትንገላታ፦ ወጀብ ሲንጣት ማዘን የሚለው ቃል አይገልፀውም። አቅምስ አቅልስ የት ይሸመት??? ለምን ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ በዬጊዜው የሚበውዙት የካቢኒያቸው፤ እንዲሁም "የብልጽግናቸውም" #ኮሚሳርያት አድርገው ደርበው አይሾሟቸውም የኢትዮጵያን ኢታማጆር ሹሙን። የኢትዮጵያ አዬር መንገድን እና የኢትዮጵያ አዬር ኃይልን እንዳጣመሩት።
ሥርዓት ለኦነግ ፖለቲካ አጀንዳው አይደለምና። ወይንም ላም ጣም በሌላቸው የዶር ለገሰ ቱሉን #የኮሚኒኬሽን ቦታን አይሰጧቸው??? አንደበቴ፤ ልሳኔ ስለሆኑላቸው። ለነገሩ ጄኒራል ብርኃኑ ጁላ በሥማቸውም፤ በእናታቸው ዞጋዊ ማንነትም ፍንትው ያለ ጥያቄ እንዳላቸው በአደባባይ አውጀውላቸዋል። ንዝረቱን አጅሬ ቀብ ነው የሚያደርጓት ዶር አብይ።
ውዶቼ በፍፁም ሁኔታ ሙግትም ትንተናም መስጠት የማልፈልገው ዘርፍ ቢኖር #መከላከያ እና #ኢኮኖሚን ነው። በብዙ ሺህ ከሚቆጠሩ ጽሁፎቼ ውስጥ ቢበዛ ሦስት መጣጥፍ ጽፌ ይሆናል። ከዛ ውጭ ዘው ብዬበት እማላውቅ ርዕሰ ጉዳይ ነው። ተሰደንም፤ ለረጅም ጊዜ በዝምታ መቆዬትም ለማህበረ ኦነግ ትምህርት ሊሆን አልቻለም። እኔ እኮ ከፋኖ ጋር ጦርነት ከጀመሩ በኋላ በጥሞና ውስጥ ነኝ። ምን አለ ዝምታዬ ቢከበር።
#ሆነ።
እኔ ፋኖን እመራለሁ ብለህ እንዳትሞክረው ብዬ ለአቶ እስክንድር ነጋ ገና ከእስር ቤት እንደወጣ ከፃፍኩ በኋላ በጦርነቱ የተከሰተውን ጉዳቱን ከመዘገብ ውጪ ጠቅልዬ ነው የወጣሁት ማለት ይቻላል። ምክንያቴ አመክንዮዊ ነውና። ስደግፍ እንቅስቃሴውን እንደ ራዲዮሎጂ ነው እምከታተለው።
አቅሙን ስኬቱን፤ እርጋታውን እለካለሁ። ዝም ብዬ አቅም አላፈስም። በማይሆን ሁኔታ ሞራል እንዳልነካ ስልም ዝምታን እመርጣለሁኝ። በብዙ ዘርፍም፦ ዘርም ባላቸው አመክንዮወች ፋኖ እና አቶ እስክንድር ነጋ፤ የአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ ተዋህደው ለስኬት ይበቃሉ የሚል ቅንጣት እምነት አልነበረኝም። ወደፊትም። ጥሪ፤ ፀጋ፤ መክሊት፦ ቅባዓ፦ እርጋታ፤ ጥሞና፤ አቅም፤ አቅል፤ የሚባሉ የማይዘለሉ አመክንዮወች አሉና።
ይልቅ ተመስጌን ነው ጄኒራል ብርኃኑ ጁላ ቀልባቸው አቶ እስክንድር ነጋን አሰኝቷቸዋል። ተመስገን ነው በማህበረ ኦነግ የትምክህት ቁንጮ ምስክርነት ማግኜት ልዩ ሽልማትም ነው። እኛ በጋዜጠኝነቱ ሳለ፤ ባልደራስንም እስቲ ይሞካክረው በማለት ለ15 ዓመታት ያህል በፍፁም ታማኝነት እና ትጋት ከአላንዲት ቆራጥ አመሰግናለሁ የመሰከርንለትን ሰብዕና አጽንተውለታል። ይህ ተመስገን ነው። ግን ጥረታችሁ ቢሳካ ጠሚር አብይ አህመድ አሊ ከአቶ እስክንድር ነጋ ጋር ቁጭ ብለው ሊወያዩ ይችሉለወት ይሆን? ፈጽሞ አይመስለኝም።
የአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ፤ የአዲስ አበባ ጉዳይ፤ የፋኖ ጉዳይ ታክሎ ድቅቅ ያለው እኮ በአቶ እስክንድር ነጋ እና በጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ፋክክር ነው። በዝርዝር ማቅረብ አቅቶን አይደለም። ዝምታ ቢያርም ብለን እንጂ። ከአቶ ጃዋር ጋርም ነበረ ፋክክሩ። የደንቢዶሎ ዩንቨርስቲ ልጆች እገታ የቄሮ ክስ በተመድ ያመጣው ጦስ እንደሆን ነው እኔ እማምነው።
ከ1000 በላይ በአንድ ጀንበር የአማራ ጭፍጨፋም በወለጋ በድጋሚ በመሰል ከተመድ ጋር በነበረ የስልክ ቆይታ እልህ የተፈፀመ ነው ብዬ እማምነው። ዜናው ሳይደርቅ ክትትሉ ክው ብሎ ይደርቃል። ተጠቂወችም በባዶ ሜዳ ጥግ አልባ ይቀራሉ። ተወጥኖ በማይጠናቀቅ፤ እጅግ ዲስፕሊን በሚጠይቁ የሎቢ ተግባራት የመወድስ ሽሚያ ብዙ በጣም ብዙ ኪሳራ አድርሷል።
የሆነ ሆኖ በፖለቲካው ዓውድ ዶር አብይ አቶ እስክንድር ነጋን የማዬት፦ የመታገስ አቅም አላቸው ብዬ አላምንም። በሎሌላ በኩል ታስሮ ከተፈታ ጀምሮ ስለ እሱ መፃፍም መናገርም ፈጽሞ አልፈልግም። #ስለማያደምጥ። #ስለበቃኝም። የአማራ ሕዝብ መስዋዕትነት የገዘፈው፦ ማገዶነቱን ማለቂያ ያጣው የሚመራ ጠንቃቃ ጥበብ ርቆ ነው። መሪነት #ምኞት አይደልምና።
እሱ የረገጣት ጥምቀት ተደግማ ሳቀችን??? ስንት የተደከመበት መስመር ለመያዝ ጥንቃቄ የተሞላበት ተግባር ሁሉ ነው እክል የገጠመው። ጉዞው አትራፊ አይደለም። ቅብዓም ጊዜም ያልፈቀደው ነገር ሊሆን ይችላል። አቅም የእጅ ሥራ ውጤት ነው። "ሁሉ ተፈቅዶልኛል፤ ሁሉ ግን አይጠቅም።" ብዙ ትጋቶችም የሳይለንት ማጆሪቲው ቤተኛ ሆነዋል።
የሆነ ሆኖ የኢትዮጵያ ሠራዊት ኢታማጆር ሹም ሽፍታ፤ ወንበዴ ካሉት ምልዓተ አምሃራ አዳኑት አቶ እስክንድር ነጋን። እንኳንም እኔ ፋኖ ነኝ ከምንል ሚሊዮኖች ከሽፍቶች፤ ከወንበዴወች፤ ከዘራፊወች መደብ አውጥተው ፃድቅ ሐዋርያ አድርጉት። እንኳንም አቶ እስክንድር ነጋ የአማራ ገበሬ ልጅ አልሆነ። ይህም አጽናኝም ፈዋሽም ሂደት ከሆነ። እኛ እኛነታችን እናውቃልን። የመብታችን እና የግዴታችን ጣሬያና ግድግዳም እንዲሁ።
የተከበሩ ኢታማጆር ጄኒራል ብርኃኑ ጁላ ሆይ!
#ፋኖነት ክስተት ነው።
1) የፋኖ የመነሻ መሠረት ሽፍትነት ውንብድና አይደለም። ፋኖነት የመሰጠት መክሊት ነው። ፋኖነት ዛሬ ጄኒራል ብርኃኑ ጁላ ተንቀባረው በሚሾሙበት፦ በሚሸለሙባት አገር ሉዓላዊነቷን አስጠብቆ፤ ዳር ደንበሯን አስከብሮ፤ ደሙን ካለማህያ ገብሮ፤ አጥንቱን ካለሜዳላይ ከስክሶ ያቆያት ባለውለታ ክስተት ነው ፋኖነት።
ፋኖነት አርቲፊሻል ሳይሆን ተፈጥሯዊ ዘብአደር ነው። የአማራ ህዝብ ሌላውን #ለመውረር፤ ሌላውን #ለመጫን፤ ሌላውን #ለመሰልቀጥ፦ ዜጋን እዬደፈጠጡ በኃይል #ለመስፋፋት ሳይሆን ራሱን፦ በባህሉ፤ በትውፊቱ፤ በታሪኩ ልክ አደራጅቶ እና መርቶ የኖረ ሕዝብ ነው። የአማራ ህዝብ ለዛሬ ሳይሆን ለነገ መኖር ተግቶ የሚሠራ ባተሌ ህዝብ ነው። የአማራ ህዝብ የተደራጀ ብቻ ሳይሆን መኖር ያምርበት ዘንድ አኗኗሪ ጥበባትን ፈጥሮ እና ከሽኖ መኖርን ያዝመነመነ ስልጡን ህዝብ ነው።
በአማራ ህዝብ ዘንድ #እገታ ባህል አይደለም። እኔ ሳድግ ሰምቼው አላውቅም። በአማራ ህዝብ ዘንድ ስርቆት፤ ዘረፋ #ሃራም ነው። #እርግማንም ነው። የአማራ ህዝብ በረት ገልባጭ እና ተፈጥሮን አሳዳጅ ህዝብ አይደለም። እኔ ተውልጄ ባደግኩበት፤ የጠቅላይ ሚኒስተረወት ባለቤት ባልደረባወትም የሰራዊቱ አባል ስለሆኑ ቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው፤ ብርኃነ - ዘኢትዮጵያ እቴጌ ጣይቱ ብጡል በተፈጠሩበት በዕት፤ ያቺ የድንቆች ንግሥት ምንትዋብ በተቀባችባት ምድር ሰው "ታግቶ" የሚለውን ቃል ሰምተን አላደግንም። ሴት ልጅን አስገድዶ መድፈርም ታስቦ አያውቅም። ጎንደሬ እና ክብሩ ደሙ እና ፕሎላዛው ነው። ክብራችን ክብረታችን ነው። ለማተባችን አዳሪ፦ የግንባር ሥጋወችም ነን።
ያደግንበት ቀዬ ከገጠር እስከ ከተማ በሥርዓተ -- ቤተ መንግሥት ወግ እና ባህል ነው። ይህ የበጌምድር ስሜን ብቻ ሳይሆን የአማራ ህዝብ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ አገርንም ያስቀጠለ ትውፊት ነው። ማህበረ ኦነግ ሥልጣን ከያዘ ነው ሰው ተገድሎ ተዘቅዝቆ ሲሰቀል ያዬነው፤ ተገድሎ ሲቃጠል የሰማነው። ሥርዓተ - አልበኝነት አገር ሲመራ የተመለከትነው።
መንግሥት ያደራጀው ማፍያ እንደአለ እኮ ዓለም ዓቀፍ ሚዲያወች ዘግበውታል። ቅኝቱም ተቃኙም የማህበረ ኦነግ ነው። እሱኑ ነው እያስፋፋችሁት ያለ። ጎንደር በታሪኳ አይታው የማታውቀው የውንብድና ረመጥ ውስጥ ናት። በስድስት ዓመት ስምንት ከንቲባ ቀይራችኋል። አቅሏን ሰወራችሁት።
ፋኖ በኢትዮጵያ ካመፁትም ይለያል ብለው ያቀረቡት መረጃ የኦነግ ታጣቂ ክንፍ ስንት ባንክ ዘረፈ? ህወሃት ጫካ እያለ ለቀባሪው አረዱት ይሆንበወታል። በህይወት ያለን ስላለን። የካቲት ወር እኮ ህወሃት ለዘረፋ የሚሠማራበት ወር ነው። ያልዘራውን፦ ያላጨደውን በቁሙ ነበር የሚዘርፈው። ሆስፒታሎች፦ ትምህርት ቤቶች ይዘረፋ ነበር።
እኔ በዓይኔ በብሌኑ ያዬሁትን ነው እምመሠክረው። ያ ቡድን ነው መንግሥት ሆኖ ለዓመታት የገዛው። እነሱም አይክዱትም። በሌላ በኩል ከእናንተው ጋር በነበረው ጦርነት በአማራ ክልል እና በአፋር ያደረሰውን ጥፋት አዲሱ ትውልድ ስላዬው ዕብለት ነው የሆኑት። እኔ ህወሃት ሥልጣኑን ፈቅዶ ከለቀቀ በኋላ የመፃፍ ፍላጎት የለኝም። እርምጃው ሊከበር ስለሚገባ። አሁንም እርስወ ፃድቅ አድርገው ስለሚያሽሞነሙኑት ነው።
#ህም።
ለኦነግ አቀባበል 1300 የአዲስ አበባን ልጆች ስታስሩ "የጎንደር ሽፍታወች የወሎ ደረቅ ወንጀለኞችን" ነው ያሰርነው ብለዋል። የደገሙት ያንን ነው። በውስጠወት የተቀመጠ የቂም እንክብል ያለ ይመስለኛል። የአማራ ገበሬ ልጅ ሁሉ ሽፍታ፤ ወንበዴ፤ ዘራፊ እያሉ ሲያራክሱ የውስጠወትን ገመና ግን ማጋለጥ አልፈለጉም።
ይህን ያህል የአማራ ጥላቻ ካለበወት ስለምን ፈቅደው ስልጣነወትን አይለቁም። እንዲህ እያንገሸገሸወት ከሚመሩ። ከሚመሩት ሠራዊትም የአማራ ገበሬ፤ የአማራ የገበሬ ልጅ፦ የአማራ ገበሬ ቤተ ዘመድ ይኖራል እና። ደግሞ አለመማርንም እንደ ዘራፊነት መለኪያ አይተውታል? ዘረፋ መደብ አለውን? በሙስና የሚጨማለቀው ቢሮክራሲስ???
የሆነ ሆኖ በሥረወት የሚገኙትን የአማራ የገበሬ ልጆች እነሱን #በጀርባወት ይሆን የሚመሩት????? እኔ በፌድራሉ እና በትግራይ ክልል ጦርነት የአማራ መኮንኖች ተነጠልው በህወሃት ተጨፈጨፋ ሲባል እማልቀበለው። ብቻውን ህወሃት ፈፅሞታል ብዬ አላምንም። ከ15 ቀን በፊት መረጃው እንዲደርስ ተደርጎ ነበርም ስለሚባል። የማህበረ ኦነግ የውስጥ ጢስም ስለሚታወቅም።
ለነገሩ እኔ የጦርነቱም ደጋፊ አልነበርኩም። ቅንጣት አቅም አላዋጣሁም። ያን ስታጠናቁ ፕላን ቢ ለአማራ እንደሚሆንም ጽፌ ነበር። እሞግትም ነበር። ጉዳቱን ከመዘገብ ውጪ በጦሩነቱ ላይ ሚና እንዲኖረኝ ፈቃደኛ አልነበርኩም። በጦርነት አሸናፊ የለም። አሸናፊ ከኖረም በቀል እና አመድ ብቻ።
የሆነ ሆኖ ሽምቅ ውጊያን ማሸነፍ አይቻልም። ንቀቱንም አቁም። ከህወኃት የታደጋችሁ #ቅራቅር ላይ ህወሃትን በጀግንነት የመከተው የአማራ #ፋኖ በጎንደር ነበር። ያ የተበተነ ሠራዊትን አልብሶ፤ አብልቶ፤ ጠግኖ፤ አስታሞ ለወግ ያበቃችሁ የአማራ ህዝብ እና የአማራ ፋኖ፤ የአማራ ልዩ ኃይል፤ የአማራ ሚሊሻ ነው።
መንገዱን ቢከፍት አጤ አማራዬ ዛሬ ኢትዮጵያ ሌላ ምዕራፍ ላይ በሆነች ነበር። ለውጪ ግቢ ነፍሳችሁ #ኦክስጅናችሁ በአማራ ሙሉ ህዝብ ካለተጨማሪ ባጀት በርደኑን በዘመነ ኮረና ተሸከላችሁ። ምሩኝ ብሎም እጁን አውጥቶ መረጣችሁ። የአማራ ህዝብ እጁ አማድ አፋሽ ነው። ልብ ቢሰጠው መልካም ነው።
2) የአማራ ፋኖ #በሳልባጅ የፖለቲካ ርዕዮት አልተፈጠረም። እናንተ እምትመሩት በሳልባጅ ፖለቲካ ነው። ከሶሻሊዝም በተቀዳ ርዕዮት። የብልጽግና አባላችሁ ከሻገተው ኢህአዴግ በውርስ የወሰዳችሁት አባል እና አካላት ነው። ማጣፊያው ያጠረውም ለዚህም ነው። የጨነገፈ ብዬ በወቅቱ ጽፌበታለሁ።
አንድም የፖለቲካ አደረጃጀት ሳይከተል ከአንዱ የጭነት መኪና ወደ ሌላ ሪሞርኬ ሽግሽግ ነው የተደረገው። የአመራራችሁ የአናርኪዝም ምንጩ ይኽ ነው። የሚፍረከረከው፤ የሚናደውም በዚህ ምክንያት ነው። ሠራዊቱንም ለመምራት የአቅም ውስንነቱ ምንጩ የፖለቲካ ድርጅታችሁ ራሱን ያልቻለ፤ ያልጠና ስለሆነ ነው። ዲስፕሊን የለውም የሚያይዝ ማስትሽ።
በመላ ኢትዮጵያ የሚታዬው አናርኪዝም የብልጽግና የመደረጃጀት መርኽ ጣሽ በመሆኑ የመጣ ነው። ዓውራው ፓርቲ እሱ ነውና። አቅም ካለ እሱን አስተካክሉ። ለአዛዥ ትዕዛዝ አይሰጥምና ትሁታዊ ዕይታ ነው ያጋራሁት።
#ግንስ???
መቼ ይሆን ይህ ያመረቀዘ፤ ደም የሚተፋ የአማራ ጥላቻ በማህበረ ኦነግ ኢሊቶች የሚደርቀው? ስሌላው ሲናገሩ እና ስለ አማራ ህዝብ፤ የአማራ ኢሊት ሲነሳ ውስጥ እንዲህ መወራጨት ለሠራዊት የቁንጮ መሪነት እንደምን ይዘለቅ ይሆን? ዘመነ - ምጣት። የአካለወትን ንቅናቄ ሁሉ እከታተል ነበር።
የሆነ ሆኖ ዛሬ ተመሥርተው ነገ በሚፈርሱ፤ ዛሬ ተሰብስበው ነገ በሚበቱን ብትክትክ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅት ባህል #የአቅም መዋጮ የአማራ ፋኖ አልተፈጠረም። እስኪ ባጀት፤ አልባሳት፤ ስንቅ እና ትጥቅ ለአማራ ፋኖ የበጀት ይንገሩን? እርግጥ ነው ዶር አብይ ገብ የሆኑ በዲያስፖራ የሚገኙ የአውሮፕላን ትኬትም፤ ሆቴልም የሚከፈልላቸው ፋኖን የሚመሩ ኢሊቶች እንዳሉ አውቃለሁ። የሚያምታቱ፤ የሚያደፈርሱም፤ መስዋዕትነቱን ያገዘፋትም።
ትርምሱን የሚፈጥሩት በተለይ ጎንደርን ቁሚ ተቀመጪ የሚሉ ጎንደርን ሞቃዲሾ ያደረጉ ለልደተ ክርስቶስ እንኳን ክብር የሌላቸው ደባሎች እንዳሉ እረዳለሁኝ፤ የራሷ የጎንደር እትብቶች ናቸው እያቃጠሏት የሚገኙት። የጭንቅ ባድማ ያደረጓት።
የግርባው ብአዴን ሚሊሻወችም አሉ እነኝህ በእውነተኛው ፋኖ ተፈጥሮ ላይ የጉሮሮ አጥንት ሆነው ያልተገባ ነገር በመከወን የፋኖን ታሪክ ጥላሸት ለማድረግ ይታትራሉ። የኢትዮጵያ ፖለቲካ የሴራ ነውና። እንደምን አድርገው የዛሬ 4 ዓመት ተባብራችሁ ያገታችኋቸውን ቀንበጦች ጉዳይ ስትታመሱበት ባጅታችሁ አምጥተው ከጎንደሬ ጋር እንዳጋቡት እራስወትን ይለኩበት። ነውርም ስለሆነ። ለመሆኑ "ቸጎቢራ" ጃል ጫላ አሸናፊ ጎንደሬው እናትዋን፤ ትንፋሽዋ ጎንደርን ያውቃት ይሆን? ምነው አፈሯን ጉንብስ ብሎ በተሳለማት???
የአማራ ፋኖ አማራ ሲፈጠር የተፈጠረ አልፋ እና ኦሜጋ ነው። የማንም ልጥፍ ቁሮ አይደለም። እኔ የገበሬ አደራጅ ነበርኩኝ። እራሱን ገበሬው የሆነበት ባህላዊ አምዱ ነው ፋኖነት። የአማራ ፋኖ ለአማራ ህዝብ ቀይ የደም ሴሉ ነው። የአማራ ፋኖ ለአማራ ህዝብ እናቱ ነው። የአማራ ፋኖ #አናቱም ነው። ለአማራ ህዝብ የአማራ ፋኖ አናባቢው ነው።
ግን በመንግሥት በጀት የማይተዳደረው ተፈጥሯዊው ፋኖን ነው እኔ እማመሳጥርለወት። ውስጡን አውቀዋለሁና። ፋኖ በበጀት መተዳደር ከጀመረ የፋኖነት ጠረኑ ይበወዛል። የፖለቲከኞች ሞፈር ዘመት ጉዞም ይህ ነው። አቅሙን፤ መማገዱን ለእሱ ክብርና ሽልማቱን እነሱ ሊወስዱ ነው ትልሙ። የገራገሩ አምላክ ያውቃል። ሙትልኝ። ከድል መልስ ወደሞፈርህ ሲሉ አዳምጫለሁ። ነውረኝነት።
//// ፋኖን በፖለቲካ ድርጅት እንመራለን ማለት ምን ማለት ስለመሆኑ ቆራጣ ጊዜም ባይኖረወት ፖለቲካው ስለማያዳርስ ይህው ጊዜ ሲያገኙ ያዳምጡት። የፋኖ ተፈጥሮ ለፖለቲካ የአደረጃጀት መርህ እጅግ ከባድ ነው።
ኢትዮጵያ በማታውቀው ሶሻሊዝም ምን ያህል ከድህነት ጋር ተቃቅፋ እንደዘለቀች ያላችሁበት ነው። ለዛውም ለራሱ ነፍስ መቀጣጠል ጭንቅ ውስጥ የሚገኘው #አብን? ለዛውም ራሱን ማስቀጠል ያልቻለው ግንቦት 7 ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ፦ ግን ለመደመራችሁ ዋልታና ማገሩ እኮ ግንቦትሻ ነው? አቅሙ ጓጉሎ፤ ተስተጓጉሎ አልችልም ብሎ በጦር ኃይል የሚመራው ብአዴን??? ለዛውም ስደት ላይ የሚገኘው፤ በትውስት የጦር አመራር የሚተዳደረው፤ እራሱም አስቸኳይ ጊዜ ዓውጅ ውስጥ የሚገኘው ግርባው ብአዴን ፋኖን ሊፈጥር? ፋኖ እኮ የዘመናት ቋሚ አምድ ነው።
በውጭጭ #በሳልባጅ ርዕዮት ፋኖ ሊፈጠር? ግን ባልደራስን ስለምን ዘለሉት? ምክክር አለን? ፋኖ አደራጅም ፈጣሪም አያስፈልገውም። እንደ ተፈጠረ የተፈጠረ አብሮ አደጉ ነው ፋኖነት ለገራገሩ የአማራ ገበሬ።
3) ፋኖ #ኦርጋኒክ ነው። ስለ ፋኖ አንድነት ብዙ ሲነሳ አዳምጣለሁኝ። እንደ ድክመትም ይታያል። የፋኖ ተፈጥሮ መሬት ላይ ከህዝብ እቅፍ እና መንፈስ ርቆ ህልው መሆን አይችልም። ሚስጢሩ ይህ ነው። ለዚህ ምክንያቴን በአውዲዮ ስለሰራሁ ሊንኩን አስቀምጣለሁኝ። እንደ ፈቀደው የአደረጃጀት ደረጃ ዕውቅና ሰጥቶ ለመፍትሄ ማሰናዳት ነው። መሬት ላይ ሃሳቡም ህልሙም ወጥ ነው። ማማከሉ ግን ተፈጥሮው አይፈቅድም። ቢሞከርም ይሰባበራል። ይበተናልም።
በነገራችን ላይ እኔም መሪ የለለኝ የአማራ ፋኖ ነኝ። በራሴ ወጪ፤ በራሴ ጊዜ በነፃ ሰላማዊ ሁኜ እምተጋ። ግን በሃሳብ ሙግት የማምን። በሰላማዊ ትግል ተስፋ የማደርግ ፋኖ ነኝ ብዕሬም፤ ሚዲያወቼም በዚህ ላይ እንተጋለን። ዛሬ ማህበራዊ መሠረቱ የተናደው ሁሉ ፋኖ ሳይሆን ሥርጉትሻ ፋኖ ነበረች። በድርጊት ዱር ቤቴ ብላ። ለዛውም ለዘመኑ ብቸኛዋ አንስት ፋኒት። ዛሬም ፋኒት ነኝ።
4) የተከበሩ ጄኒራል ብርኃኑ ጁላ በአማራ ፖለቲከኞች፤ በአማራ ተቋማት መሪወች ላይ ያን ያህል ውርጅብኝ ሲያወርዱ ምነው ውስጠወትን ዘለሏቸው? አንድም ቦታ ዶር ለማ መገርሳ፤ አቶ ዳውድ ኢብሳ፤ አቶ ሌንጮ ለታ፤ አቶ ሌንጮ ባቲ፤ ዶር ዲማ ነግዖ፤ ፕ/ ዶር መራራ ጉዲና፤ አቶ ጃዋር መሃመድ አልተነሱም? ከ10 ያላነሱ የኦነግ የዞግ ድርጅቶች እንዳሉ እሰማ ነበር? ትንፋሻቸው ካለ? ኦፌክ፤ ኦነግ ወዘተ በምንም ሁኔታ አልተነሱም። ለምን????
መሪነት እኔ እማውቀው ቆፍጣናው የሠራዊት መሪነት እንዲህ አይደለም። አይሆኑ አደረጉት። እኔ ኮሚሳሮችን፤ የኮር አዛዦችን፤ የሆለታ ገነት አስተዳዳሪወችን በአካል አውቃቸዋለሁኝ።
ግርማ ሞገሳቸው፤ ድምፃቸው፤ ላሂያቸው፤ ቁጥብነታቸው፤ የኢትዮጵያዊነት ልዕልናቸው፦ ዲስፕሊናቸው፤ አድማጭነታቸው፤ አስተውሎታቸው፤ ትህትናቸው፦ ሐዋርያነታቸው ልዩ ፍፁም ልዩ ነበር። በሥራ በቢሮ፤ በመስክም፤ በስብሰባም ህይወታቸው በራሱ መምህር ነበር። ተፈጥሯቸው ዲፕሎማትም ነበር። እንዲያውም ስለ ኮነሬል ጎሹ አስተዳደግ፤ ሰብዕና፤ ብቃት ሁሉ በመደበኛ ያስጠኑኝ ነበር። የቶጎ እና የጁቡቲ ጉዳይ ሲነሳ ሰውነቴ ነበር የተንዘፈዘፈው። ሁሉ ቢቻልም ሁሉ ግን አይዘረገፍም።
ከቀደምቶች ቅብዓ #እንጥፍጣፊ ማግኘት አልቻልኩም። ቀደምቶች አድሎም፤ ማግለልም፤ መታበይም፤ በማያገባቸው ቦታ ገብተው ትርፍ ተናጋሪነት አላይባቸውም ነበር። ወጣቶችን እንደምን ታግሰው ያደምጡን እንደነበር ማህተሜ ነው።
5) የአማራ ህዝብ ኢትዮጵያን በሚመለከት ፀፀት የለበትም። ግማዷን ሁሉ ተሸክሞ የኖረ። ፍፁም - ትሁት። ፍፁም - ቅን። ፍፁም - አዛኝ። ፍፁም ለችግር ጊዜ ደራሽ። ፍፁም አክባሪ ( ተፈጥሮን፤ ሰውን፤ የሰማይ እና የምድርን ህግጋት እና ድንጋጌወችን)። ፍፁም የሆነ ፈርኃ እግዚአብሄር እና ፈርኃ አላህ ያለበት፤ ፍፁም - ለጋስ። ፍፁም የሆነ ይሉኝታ ያለው። ሰው ወዳጅ። ተፈጥሮን ወዳጅ። በከፋ ጊዜ ፈጥኖ ደራሽ። በህብራዊነት ውህድነት መታመን ያለው። ወደ ገበሬው ሲገባ የዚህ እጥፍ ድርብ ነው። ፋኖ በግልፁ ቋንቋ የገበሬ የደህንነት አስጠባቂም ጠባቂም ኃይል ነው።
6) ዘመን የሚለካው በመሪወች ነው። ዘመኑ የማህበረ ኦነግ የገዳ ሥርዓት አና ያለበት ነው። ህይወቱን ውጭ የምንገኝ እኛ አንኖረውም። ህዝቡ እዬኖረው ነው። እሱ ይመዝነው። ኦነጋዊነት እና ኢትዮጵያ በትርፍ ወይንስ በኪሳራ? ህዝብ ራዲዮሎጂ ነውና ይለካው። ነቁጧ መስታውት አላት። ለዛውም የጨዋና የደግ ህዝብ።
እኔም ያደግኩበት በዕቴም፤ ቤተሰቦቼ የተገኙበት ዞግ አማራነት ሲዘርፍ፦ ሲወነብድ፤ ሲያግት፤ ሲቀጥፍ፤ ሲወር፤ ሲስፋፋ፦ ህግን ተዳፍሮ ሲተላለፍ፤ አስገድዶ ሲደፍር አላዬሁም። አልኖርበትም። በክርስትና፤ በአይሁድ እና በእስልምና ኃይማኖትም እነኝህ ጎደሎ ሥነ - ምግባሮች #ሃራም ናቸው።
በህግ አምላክን ተምሮ በሥርዓተ - መንግሥት ሞራል፤ ልቅና እና ልዕልና ተኮትኩቶ ላደገ የአማራ ህዝብ፤ የአማራ ገበሬ #መስቃው፤ መገፋቱ፤ ስድቡ እና ውረፋው ሊቆም ይገባል። ይህ የሆነበት መሰረታዊ ምክንያት የማንነት ቀውስ ነው። አገር የሚበጀው፤ ባህል የሚፈጠረው፤ ታሪክ የሚሠራው በቀደመ ህዝብ እና በባለ ቅብዓ መሪ ነው።
መሪነት ለዛውም የአንድን ሉዓላዊት አገረ መንግሥት የጦር መሪ ይህን ያህል የሥርዓት ጥሰት መጥኔ ለአንቺ ለኢትዮጵያ። ይህ ሥልጣን እንደምን እንደተገኜ ሚስጢሩን ባላውቀው በሆነ። እኔ ግን በሁለመናው ውስጥ በቂ ዕውቀትም፦ የሚታይ የሚጨበጥ የስልት እና የጥበብ መረጃ በእጄ ስላለ የመታበዩ ጣሪያ ይህን ያህል ሲንጠራራ፤ ሲወጣጠር ፈጣሪ ሆይ! ይህን እያዬህ ዝም ለምን ትላለህ ማለቴ አልቀረም።
7) #የሥም ልሙጥ ፖለቲካ እና የታደገበት ቀዬ ባይታወርነትን መመገብ እንዳለበት ያስገነዘበው የጄኒራል ብርሃኑ ጁላ ዝርግ ፖለቲካ ማንነት የአስተሶሳሰብ ዝበት ያለበት ነው። በ2010 ፕ/ ዶር መራራ ጉዲና ለማ "#ፊቱ ኦሮሞ ይመስላል" ብለው ነበር። በጣም ነበር የደነገጥኩት። በተደጋጋሚም በአካል አግኝቻቸው ስለማውቅ ያ ዲስፕሊናቸው ሲመንን መደንገጥ ትንሹ ነበር። ጠያቂው ዶር አብይስ ቢላቸው ሸጋ ነበር። በወቅቱ ጽፌበታለሁኝ።
የአሜሪካ ኢታማጆር ሹም በውስጠ ታዋቂ የዓለምም ሲሆኑ፤ የኢትዮጵያም የአፍሪካ ነበር። ኢታማጆር ሹሙ ጄኒራል ብራኃኑ ጁላ አይደለም ፓን አፍሪካኒስት ለኢትዮጵያም #ሃቅ እያንገዳገዳቸው ነው። አዬ አንቺ አገር ኢትዮጵያ??? አሸናፊ ጎንደሬ አማራነቱን ነገሩን። አማራ ሆኖ በኦሮምያ ክልል ከተወለደ የምንም ዓይነት የፖለቲካ ውክልና ሊኖረው አይገባም ነው ጉዳዩ።
በዚህ ላይ የገዳቸው ሞጋሳዊ ሂደትም አፈር አስግጠውታል - ጄኒራሉ። አወያይ እና ጸሐፊዋ ቤቲ ታፈሰስ ከዬት ይመዱባት ይሆን? አስቱሻም አለች ሚዲያ ላይ??? ልሙጡ የጄኒራል ብርኃኑ ጁላ የሥያሜ ገደላገደል ፖለቲካ።
በሌላ በኩል ከኦሮሞ የሥም አወጣጥ ውጪ ሥም ያለህ #ወጥ ኦሮሞ ሁሉ ኦሮሞ አይደለህም ነው። ይህ ብቻ አይደለም ውህድ ማንነት ያላችሁም የኦሮሞን የደም መሥፈርት አታሟሉም ነው። ይህ ንፁህ ዲስክርምኔሽን ነው። ፋሺዝምም ነው። ለዛውም ግርር ያለ። ይህ #ሰዋዊነትን መቀማት ነው። ይህ ፈጣሪን አሻቅቦ #መዝለፍ ነው። በዚህ በውህድ ማንነት ዙሪያም ሰሞኑን የሰራሁት አውዲዮ አለ እለጥፋለሁኝ።
ውህድ ማንነታችን አስተምኽሯችን፤ ዶግማችን ሊሆን ይገባል። Zusammengesetzte Identität. Farbe. Schönheit. Menschheit.
ሚሊዮን የዓለም ህዝብ በድርብ ዜግነት ይኖራል። የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ለስምንት ዓመታት የዓለም ቁንጮ ነበሩ። የአባታቸው መፈጠሪያ ኬኒያ ነው። በጄኒራል ብርኃኑ ጁላ ፍልስፍና ዓለም ፈርሳ ትሠራ የተስፈነጠረ ገመና ነው የተገለፀው።
የሰይጣን ጆሮ ይደፈን እና የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ቢደፈር ኃላፊነቱን እንደምን ሊወጡ ይይችሉ ይሆን? ለነገሩ ለስሜን ሱዳንም፤ ለደቡብ ሱዳንም የመሬት በረከት በዚህ ስሌት ይሆን? ይህ ዝንቅ የዘረኝነት አዲስ ዶክተሪን ይዘው መጥተዋል ኢታማጆር ሹሙ። {}።
ለመሆኑ አለቃቸው፤ የዓለሙ ሎሬት፤ የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስተር #አብይ #አህመድ #አሊ።
ሥማቸው አገራዊ፤ የአባታቸው የአያታቸው ሥም #አረባዊ ነው። ይህን መስጥረው ነው አብረዋቸው እዬሠሩ የሚገኙት። ለዛውም ማህበራዊ መሠረታቸው የበሻሻ ቀዬ ነው። አቤት በል ጅማ???? ፈተና ላይ ተቀምጠኃል። ሊፈራ የሚገባውስ ይሄ???
የሳቸው የኢታማጆር ሹሙ የራሳቸው ሥምም #ብርኃኑ ነው። ይህ ሥም ኢትዮጵያዊ ሥም እንጂ የኦሮሞን ቋንቋ መሰረት ያደረገ አይደለም። እንዲህ ሥማቸውን ከተጠዬፋት ስለምን አይቀይሩትም? የኦህዴድ ጽኑ ባለውለታ ዶር ወርቅነህ ገበዬሁስ እንዴት ይሁኑ??? እስከ አሁን በማተቡ ፀና ሆነው ቀጥለዋል።
መቼም የኦሮሞ ህዝብ በኢሊቶቹ አሳሩን እያዬ ነው። የማይመዙት የመርዝ አይነት የለም። እግዚኦ ነው።
ይህ እኮ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የሰው ልጅ ሥያሜ ዲስክርምኔሽን አይፈፀምበት አስብሎ ግሎባል ንቅናቄ የሚያመጣ ነው። በሌላ በኩል የዓለም ዜጎች ከቀያቸው ከራቁ ለኃላፊነት መብቃት የለባቸውም ነው። የፖለቲካ ውክልናም አይገባቸውም ነው።
ፌድራሊዝምም በአናትህ ተተከል አይነት። ዱዳም፤ ጎግም ውሳኔ። እንዴት ያለ ጠማማ እና ጎባጣ ሃሳብ ነው? የሚታሰበው በህሊና ወይንስ በቁርጭምጭሚት ያሰኛል????
ሦስት አራት አፍ ያለው ሰይፍ፤ መርዝ የሚረጭ ፀረ - ሰው፤ ፀረ - ተፈጥሮ፤ ፀረ - ዕውቀት፤ ፀረ - መኖር፤ ፀረ - አብሮነት፤ ፀረ - ሂደት የሆነ ርጉም ሃሳብ ነው። አይደለም ለኢትዮጵያ ለተራ የቡና ደንብኝነትም ቃር የሚሆን። ኮምዳዳ እና ጎምዛዛ። ወደፊት ከመጡ ጀምሮ በጎንደር ላይ ጥርስ የነከሱበት ምክንያት ለእኔ ግልጽ ነው። ህልም ዕልም ስለሆነ። አቶ ጃዋርም ወደ ትግል የገባበት መሠረታዊ ምክንያት ከጎንደር ጋር አያይዞ ሲገልጥ ሰምቸዋለሁኝ። ትንፋሽዋ ጎንደሪና ምቀኛ አታሳጣኝ ይባልልሽ ይሆን???
#እርገት ይሁን።
የአማራ ህዝብን እና ልጆቹን #መናቅ አይገባም። ማቃለል - አይገባም። የዓለም ኃያላን መንግሥታት ሆኑ ህብረቶች ቢሰሙ ይታዘባሉ። አበጥረው አንጠርጥረው ያውቁናል። ያ አቅማችን መሪ ሆኖ እንዲወጣ ባይፈቅዱትም። ብልህነታችን፤ ዊዝደማችን ያለው የማሳመን አቅም ይረዱታል።
ለብዙ አመክንዮ የወርቅ ድልድዮች ነን። ለዬዘመኑ #ቅመሞች ነን። ቅመምነታችን በበዛ ልግሥናም - ቅንነትም ነው። ያ ነው በነፃ የሚሰጥ ሁለመና እያስቀጠቀጠን የሚገኘው። ይህን በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁኝ። ብዙ ደክመናል። ድካማችን በተራ #ሽፍትነት እና #በውንብድና ሲወራረድ ፈጣሪ ይዳኜው ማለት ግድ ነው።
በአግባቡ ሃሳብን አቅርቦ መሞገትም ይገባል። እኔ የቂም እና የበቀል ደንበኛ ስላልሆንኩኝ። የሆኖ ሆኖ የእመ አማራዬ ቅንነት፦ የአበው የአማራዬ ቅንነት ይቀጥል። የተፈጠርንበት ነውና።
ህዝብን በተለያዬ ቀውስ ወጥሮ አማራጭህ እኔ ነኝ ለማለትም ነው ይህ ሁሉ የጭካኔ፤ የክህደት፤ የዘለፋ ማዕት እዬዘነበ ያለው። ያ የእርግጫ ምርጫ መጥቶ እስኪያልፍ የሚታዩ መርዷዊ ትዕይንቶች ይኖራሉ። ተጀምሯልም። ሁሉን ቢናገሩት ……
ግን ግ ን ስዮሜ ምኑ ይሆን ፍንሽንሽ ያስደረገህ? ምኑ???? በኢታማጆሩ ቃለምልልስ ፍንክንክ??? የትኛው አመክንዮ? ለነገሩ ሰሞኑን መረጃ ከአንተ እራቅ ስላለች ሊሆን ይችላል። ለክብር ተሸላሚወች ሹክ አልተባለም የረፋዷ የፕሬዚዳንት ሹም ሽር፤ ዲሞሽን እና ስንብት። ለተሿሚውም ስብሰባቸው በሰበር ተስተጓጉሎ መሆኑን አዳመጥን።
መዝረክረኩም መዝለግለጉም ተለምዷል። "የብልጥግና" እና የካድሬወቹ መተማመን ጋር #መራራቅ ዳዴ እያለ ይሆን??? ማሟያ ሆነችሁሳ? የክትና የዘወትር መረጃ #እረድፍ ተበጀለት መሰል። በፊት ከህወሃት ጋር ዛሬ ከፋኖ ጋር ያው ሰጥስጡት ቤተ - መንግሥቱ ግን ተውት ዓይነት ተብላችኋል።
ውዶቼ ህይወት ነው። ነፍስ ይህን ያህል ማት ሲወርድባት ዝምታ አይገባም። ለዚህ ሥርዓት ተብሎ ዛሬም መገበር???
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
10/10/2024
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ትዕግሥት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ