የአለምን አትኩሮት ስቦ የቆዬው የአሜሪካ የ2024 ፕሬዚዳንታዊ እና በዬደረጃው ያሉ ምርጫ አካቶ #በሰላም ተጠናቋል። ተመስገን። አሜን።
አሜሪካ ለዴሞክራሲ የምርጫ ሥርዓት መንፈስም ነው። የሚስብ ነገር አለው።
"አሁንስ ተስፋዬ ማን ነው?
እግዚአብሄር አይደለምን?
ትዕግሥቴም ከአንተ ዘንድ ነው።"
(መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ፴፰ ቁጥር፯)
የእኔ ጭንቀት ምን ይፈጠር ይሆን የሚል ነበር። እግዚአብሄር የተመሰገነ ይሁን በሰላም ተጠናቋል። እርግጥ ነው ዴሞክራቶች በሰፋ ልዩነት ተሸንፈዋል። ውድድር ለመሸነፍም // ለማሸነፍም ነውና ዴሞክራቶች መሸነፋቸውን በፀጋ ስለሚቀበሉ የምርጫው ውጤት #በሰላማዊ ሽግግር ይፈጸማል። ሪፕብሊኮች ተሸንፈው ቢሆን ግን ከባድ ችግር ይከሰት ይሆን በሚል ስጋት አድሮብኝ ነበር። እግዚአብሄር የወደደው ተፈጽሟል። የእግዚአብሄር ፈቃድ ከእኛ በላይ ለአለሙ ሰላም ይጠናቀቃል - እና።
በተረፈ ይህን መሰል ዕድል ለአገሬ ለኢትዮጵያም ይገጥማት ዘንድ እመኛለሁ። ህዝብ ካለምንም ጠበንጃ የፈለገውን፤ ያሻውን ደስ ብሎት መምረጥ የሚችልበት የዴሞክራሲ ጥበብ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ #ህልም ነው። የአሜሪካ አገር የየዘመኑ የምርጫወች ሂደት እጅግ አጓጊ እና ቀልብን የሚይዝ ነው። የዘንድሮ ምርጫ ፋክክሩ በጠሩ ፋክቶች ላይ ስለነበር መሳጭ ነበር። ስለሆነም ከውስጤ ነበር የተከታተልኩት። የሴት እጩ ፕሬዚዳንትም መኖር የበለጠ አትኩሮቴን ስቦት ነበር።
ዴሞክራቶች በእጩ ፕሬዚዳንታቸው ጎን በምክትል ፕሬዚዳንትበክብርት ወ/ ሮ ካሜላ ሃሪስ (ኮሚላ ሃሪስ) ዙሪያ ተግተዋል። ተጽዕኖ ፈጣሪወች አብዛኞቹ ከጎናቸው አሰልፈውም ነበሩ። በተደጋጋሚ ሴት የዴሞክራሲ እጩወች ለፕሬዚዳንትነት ተወዳድረው አልተሳካላቸውም። ብላቴ ሎሬት ፀጋዬ ገ/ መድህን በዚህ ጉዳይ ጠበቅ ያለ ትችት አቅርቦ ነበር። ኢትዮጵያ በቀደመው ጊዜ ለብዙ ዘመናት በሴት ነገስታት ተስተዳድራ ስለምታውቅ ነበር ባለ ቅኔው ጥያቄውን አነፃጽሮ ያቀረበው። አሜሪካኖች እስከ 2024 ይህን አላሳኩም።
የሆነ ሆኖ ዴሞክራቶች በነበራቸው የአራት ዓመት የሥልጣን ጊዜ የአሜሪካ ህዝብ ገምግሞ ድምፁን ለሪፓብሊካን ሸልሟል። ምርጫው ለተለያያ የኃላፊነት ደረጃም ስለነበረ በፍፁም የተደራጄ፦ ስልጡን በሆነ ብቁ ሁኔታ ተከናውኗል። እንዲህ ፈጥኖ ውጤቱ ይታወቃል ተብሎ አልተገመተም ነበር። #በወሳኝ #የመኖር ኢሹወች ላይ ህዝብ የራሱን ውሳኔ ካለምንም ተጽዕኖ ሰጥቷል። #ነፃነት ማለት ዕውነት መሆኑ ይህ ሂደት ምስክር ነው። #ዴሞክራሲ ማለት ይሄ ነው።
ለአንድ የፖለቲካ ማዕቀፍ በተለይ በዝምታ ውስጥ ያሉ ዜጎች #ሳይለንት ማጆሪቲው አቋም፥ አቅም እና ውሳኔያቸው ወሳኝ ጉዳይ ነው። ለእነሱ ትኩረት በመስጠት ጉዳይ ላይ ወሳኝ የፖለቲካ ድሎች ይገኛሉ፤ ወይንም ያመልጣሉ። በሌላ በኩል ሃይማኖታዊ ጉዳይ፤ ዓለም ዓቀፍ ሁነቶች፤ ጦርነት እና ኢኮኖሚ፤ የሰብዓዊ መብት እና የስደተኛ ጉዳይ ሁሉም የራሳቸው አቅም በውድድሩ ነበራቸው። በዚህ ውስጥ ሊታለፍ ወይንም ሊዘለል የማይገባው መሠረታዊ ጉዳይ ግን ፈቃደ - እግዚአብሄር ነው።
የሆነ ሆኖ ሴኔቱን ሙሉ ለሙሉ የሪፓብሊካን ስለመሆኑ አይቻለሁኝ። ተመጣጣኝ ካልሆነ ለዓለም የፖለቲካ ሥርዓት የሚከብድ ይመስለኛል። አሜሪካ ማለት #ዓለም ማለት ናት። ሁሉም አገር ሉዓላዊ ነው። ነገር ግን ሁሉንም የሚያስተሳስር ልዕለ መንፈስ ደግሞ አለ። አሜሪካ ከእግዚአብሄር በታች #ልዕለ #መንፈስም ነው። ብቻ ከዛሬ ጀምሮ አዬሩ ሁሉ መለወጥ ይጀምራል ብዬ አስባለሁኝ። ሲስተሙም ቋሚ ቢሆኑም ብዙ ነገሮች ከመሪ ሰብዕናም ሊነሱ ስለሚችሉ አዳዲስ የፖሊሲ ለውጦች ሊኖሩ ይችላሉ። ይጠበቃልም።
#ግን …… ግን
1) የተከበሩ (ፕሬዚዳንት) ዶናል ትራንፕ ሁለት ጊዜ ሴት እጩ ፕሬዚዳንትን ያሸነፋበት አቅም #ሚስጢር ምን ይሆን?
3) የአሜሪካ ሴት ፖለቲከኞች፦ የአሜሪካን ወንድ ሊቃናትን #የሚመጥን አቅም አመንጭተው #ህዝብን #ማሳመን ያልቻሉበት ሁኔታ ምንድን ይሆን?? በውነቱ ልዩ የምርምር እና #ጥናት ሊደረግበት የሚገባ ጉዳይ ይመስለኛል።
4) ዴሞክራቶች የትኛው ፋክት ፈተና ውስጥ ቢጥላቸው ይሆን እንዲህ በሰፋ ልዩነት ሊሸነፋ የቻሉት??? ይህም እንደ አንድ የትውልድ ፓርቲ ሊመረምሩት የሚገባ ይመስለኛል። ፓርቲያቸውን ማስቀጠል ከተመኙ። ለአዳጊ አገሮችም መምህርም ስለሚሆን።
4.1 ዴሞክራቶች በዚህ ያህል የሰፋ ልዩነት እንዴት ሊሸነፋ ቻሉ?
4.2 የህዝቡን መታመን ዴሞክራቶች እንደምን አጡ???
4.3 የእነሱ ውስጥ የሆኑ መተማመኛወችን ስለምን ዴሞክራቶች በሪፓብሊካን ተነጠቁ???
4.4 የወጣቶች ተሳትፎ በመዳፋቸው ነበርን ዴሞክራቶች? ካልነበረ ለምን???
4.5 የሴቶች ተሳትፎስ በምን ሁኔታ ይገኝ ነበር???
ይህም በሥርአት ሊጠና ይገባ ይመስለኛል። ዲሞክራቶች ፓርቲያቸውን አጠንክረው የትውልድ ለማድረግ እንደ ገና ፖሊሲያቸውን፤ አቅማቸውን፥ ውሳኔወቻቸውን ሊመረምሩ ይገባል ብዬ አስባለሁኝ።
#በሌላ በኩል ……
2) በሌላ በኩል አዲሱ ተመራጩ ክቡር ፕሬዚዳንት ዶናል ትራንፕ ሁለት ጊዜ ከሞት ያተረፋቸውን አምላክ፤ ሦስተኛ የመኖር እድል በሙሉ የሥልጣን አቅም ላጎናፀፋቸው አምላካቸው ለእግዚአብሄር ውለታ በምን ይመልሱ ይሆን? ከበቀል ያፀዳ - ከቅሬታ የፀዳ - በአንደበት በታረመ አኳህን ርህርህናን - ደግነትን - ፍቅርን - ሰላምን - ሰዋዊነትን - ተፈጥሯዊነትን በማክበር እግዚአብሄርን ሊያስደት የሚችል ተግባር እንዲፈፅሙ ዕድሉን እንደምን ይጠቀሙበት ይሆን??
3)የሚመሩት ህዝብ፤ አለማችንም ከስጋት የዳነ፤ ፍራቻ የሌለበት ለሁሉም እኩል አባትነትን፤ ለሁሉም እኩል ንፁህ ህሊናን በመመገብ ቀሪ ዕድሚያቸውን እንደምን ያሳልፋ ይሆን??? በዚህ አጋጣሚ የተከበሩ ፕሬዚዳንት ዶናል ትራንፕን፤ ባለቤታቸውን፤ ልጆቻቸውን እና ደጋፊወቻቸውን እንዲሁም ፓርቲያቸውን እንኳን ደስ አላቸው።
በሌላ በኩል በአጭር ጊዜ መሰናዶ ለእጩ ፕሬዚዳንትነት ውድድር ዕውቅና የተሰጣቸው የአሜሪካ የመጀመሪያዋ ምክትል ፕሬዚዳንት ክብርት ወ/ሮ ካሜላ ሃሪስ (ኮሞላ ሃሪስ) ላሳዩት ትጋት እና ብርታት፤ ጥንካሬ እና ጥረት ሁሉ ላመሰግናቸው እፈልጋለሀኝ። ዕድሉ ባይሳካም በዚህ ያህል ደረጃ በሙሉ #የራስ #መተማመን አቅም ፍልሚያውን እስከ መጨረሻው ድረስ ሳይዝሉ መከወናቸው ከበቂ በላይ ነው። ቀረ የሚሉት ነገር አልነበረም። ጥረዋል።
ክብርቷ አእምሯቸው ሳይሰናዳ ነበር በድንገት እጩ የሆኑት። እሳቸውን በመደገፍ፤ በማበረታት ከጎናቸው የቆሙት ሁሉ ሊመሰገኑ ይገባል። የሰው ልጅ ለአንድ ዓላማ እና ግብ አብሮ እንዲህ ቆሞ መትጋት መታደል ነው። ውድድር በመሸነፍ እና በማሸነፍ ትዕይንት ነው የሚወጠነው። ኪናዊ ነው። ታሪካዊም ነው። በተጨማሪም ፈቅደው እጩ ያደረጓቸው የተከበሩ ፕሬዚዳንት ጆባይደንም ሊመሰገኑ ይገባል። በሴቶች አቅም፤ ክህሎት፤ ትጋት፤ ችሎታ ላይ እምነት መጣል ከመታደል በላይ #መመረቅም ነው። ሴቶች ድንቅ ፍጥረቶች ብቻ ሳይሆኑ ጥበቦችም ናቸው እና።
#የሆነ ሆኖ …
60 ዓመት ሙሉ ሁለት ትውልድን ጨርሶ፤ ሶስተኛ ትውልድን በጭካኔ እዬመተረ የሚገኘው በበቀል ላይ የተመሠረተው የኢትዮጵያ ፖለቲካስ ከአሜሪካው ነፃ እና ዴሞክራሲያዊ፤ ሰላማዊ እና ትጉህ #ስልጡን የምርጫ ሂደት ምን ይማራል? በምርጫው ሂደት ያዬሁት እኔ ሰውኛ እና ተፈጥሮኛ ክንዋኔወችን ብቻ ነበር። ያም ስለሆነ የህዝብ ፍላጎት በትክክል ተፈጽሟል። ለአብዛኛው ድምጽ ጥቂቱ ይገዛል። በዛም ይተዳደራል። ዬዴሞክራሲ ሳይንስ ማለት ይህ ነው። ዴሞክራሲ ለእኔ ከሳይንስም በላይ ዩንቨርስም ነው። መኖርን የሚያስውብ። የነፃነት ዘውድ።
አሸናፊው ወገን ስለአሸነፈም ተሸናፊወችን #አይጫንም። ተሸናፊም አንገቱን አይደፋም። አሸናፊው ለመረጡትም፤ ላልመረጡትም ወገኖች እኩል ያገለግላል። የተከበሩ ፕሬዚዳንት ትራንፕ ሆኑ ፓርቲያቸው ሪፓብሊካን ለሁሉም የአሜሪካ ህዝብ እኩል ያገለግላሉ። ይህ ምድራዊ ገነት ነው። ምክንያቱም #ሲስተሙ በቋሚነት ስለተዘረጋ። መሠረት የያዙ ተቋማት አሉና። ህግም ገዢ ይሆናል።
ሲስተሙ ስለተዘረጋ እኮ ነው በብዙ የክስ ሁኔታ ላይ የነበሩት፤ በ2020 ምርጫም ተሸንፈው፤ ግን እንደ ገናም ለሦስተኛ ጊዜ ተወዳድረው የተከበሩ ፕሬዚዳንት ትራንፕ የተመረጡት። ህዝቡ መረጣቸው በ2016። በ2020 ከሥልጣን አወረዳቸው። ድምጽ ነፍጎ የተከበሩ ፕሬዚዳንት ጆባይደንን ህዝቡ መረጠ። አሁን ደግሞ እንደገና ተጨማሪ ዕድል ሰጥቶ በሚገርም የድምጽ ልዩነት ደግሞ ሁለተኛ መረጣቸው።
የዚህ ጥበብ ሚስጢሩ አሜሪካ #የማይናወጽ ተቋማዊ ሥርዓት ስላላት ነው። ይህ ያስቀናል። ይህ ተቋማዊ ሥርዓቷ በህግ ይመራል። ማንም ሰው ከህግ በታች እንጂ ከህግ በላይ አለመሆኑ በህግ የተረጋገጠ ነው። ስለዚህ ከእግዚአብሄር በታች ህግ + ዴሞክራሲ= ለነፃነትን #ነፃነት በእኩልነት መገቡ። ስለሆነም ተስፋ እና ምኞት ምቹ ሁኔታ ሲያገኙ እንዲህ ዕውነት ሳቀ። ድምጽ ተደሰተ። ይህ ማለት ፍፁምነት አለ ማለት አይደለም። የፖለቲካ ድርጅት የሰወች ተቋም ነው። እኛ ሰወች ደግሞ ፍፁማን አይደለንም። ፍጽምናም አይጠበቅብንም። ፍፁም አንድ እግዚአብሄር አላህ ብቻ።
በአገሬ በኢትዮጵያ ግን ሁልጊዜም ትውልዱ በዴሞክራሲ ራህብ አሳሩን ያያል። አሁን የኢትዮጵያ መንግሥት የአማራ ክልልን ብቻ ለአንድ አመት ከአምስት ወር በአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ይዞ በድሮን ሰላማዊ ዜጎች፤ ትምህርት ቤቶች፤ እንሰሳትን ሳይቀር፤ የበቀሉ አዝመራወችን፤ ገዳማትን ሳይቀር ይጨፈጨፋሉ። የአማራ ክልል ብቻ በወታደር ይገዛል። በሌላ ቦታ የሚኖረው አማራ ይገደላል፤ ይፈናቀላል። ይሳደዳል። ይታገታል። ይታፈናል።
አሁን የአማራ ህዝብ እያደረገ ያለው ተጋድሎ #የማንነት እና #የህልውና ነው። ይህ ማለት ስለምን እግዚአብሄር ሰው አድርጎ የአማራን ህዝብ ፈጠረህ ነው ትግሉ። የአማራ ህዝብ የሆኑ ታሪክ፤ ቅርስ፤ ትሩፋት፤ ሥልጣኔ፤ የተመሠረቱ ከተሞች፤ ተቋማት ሁሉ ወደ አመድነት እዬተቀዬሩ ነው። ባለ ቅኔውን ድንቁን የአማርኛ ቋንቋውን ለመስበር የተዘረጋው ሲስተም እጅግ ረቂቅ ነው።
የአማራ ህዝብን ያነቃሉ፤ ያደራጃሉ፤ ይመራሉ የተባሉ ሁሉ ለእስር እና ለስደት ተዳርገዋል። በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከሥልጣኔው ጋር እንዲጠፋ የተፈረደበት የአማራ ህዝብ ብቻ ነው። መማር አይችልም። ቅንጦት ነው ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ ህዝብም፤ ለአማራ ህዝብም ይህን የመሰለ የምርጫ ሂደት ሉክሶስ ነው። በፍርሃት፤ በስጋት፤ በሽብር፤ በለቅሶ፤ በቀውስ ውስጥ ነው የአማራ ህዝብ እዬተሰቃዬ የሚገኜው። በድህነት ለመኖር ያልተፈቀደለት የአማራ ህዝብ ነው።
ይህን የምናውቅ የወጣትነት ዘመናችን ሁሉ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ለታገልን እንደ እኔ ላለ ባተሌ የአሜሪካን የምርጫ ሂደት ሳይ በእዬሱስ ክርስቶስ ቤተ - መቅደስ የተገኜሁ ያህል ይሰማኛል። #አሜሪካ ለእኔ ለዴሞክራሲ #መንፈስ ነው። ፍጹም የሆነ ሐሤት ነው ሂደቱን ሳስተውል የሚሰማኝ። ሌላ ሥራ አልሠራም። ጸጥ ብዬ እከታተላለሁኝ።
የሰው ልጅ ነፃነት ያስፈልገዋል። ነፃነት ለሰው ልጅ መኖር #ኦክስጅን ነው። ነፃነት በዴሞክራሲ ሰልጥኖ እንዲህ ሲቀመም ደግሞ እጅግ ያረካል። ይመስጣልም።
የተከበርከው የአሜሪካ ህዝብ ሆይ! ትጋታችሁ፤ ትብብራችሁ፦ ጥረታችሁ፤ ተሳትፏችሁ ሁሉ አብነት። የተባረከው አሜሪካ ህዝቡ ነፃነቱን፤ መብቱን እንዲህ በዕውን ሲፈጽም አዬን። መታደል ነው። ይህን የሠሩ ታላላቅ የአሜሪካ ሊቃውንታትም ሊመሰገኑ፤ ሊከበሩ ይገባል። ድንቅነት። ብቁነት። መሰጠት። ሥልጣኔም። ቅንነትም ነው።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
06/11/2024
ነፃነት የሙዚቃ ኮንሰርት አይደለም።
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ