"52 አመት በሀኪምነት አገልግያለው" - ኘ/ር ማለደ ማሩ | Prof. Malede Maru | Season 2 Epis...የተግባር #ሐዋርያው #የኔታ ፕሮፌሰር ዶር ማለደ ማሩ ሽልማቴ ናቸው።

የተግባር #ሐዋርያው #የኔታ ፕሮፌሰር ዶር ማለደ ማሩ ሽልማቴ ናቸው።
እቴጌ ጎንደርስ ሊቀ - ሊቃውንትሽን አክብረሽ #መለዮሽ የምታደርጊያቸው መቼ ይሆን???
 
ከዬት ልጀምር እንደምችል ሳላውቅ ወጠንኩት። እርእስ ለመስጠት ገና አቅሙን አላገኜሁም። እርእሱ እራሱን እስጊገልጥ ድረስ ልሰጥስጠው። እንዲህ ……
እንዴት ሰነበታችሁ ውዶቼ - ክብረቶቼ ደህና ናችሁ ወይ? ጫ ባለችው ደጓ ቪንተርቱር ከተማ በበዛ ጭመታ ላይ የሰነባበተችው እቴጌ ብዕሬ መጣች። ክረምት እና እኔ በፍልሚያ ነው። ጉንፋን ከመደበኛው በሽታ በላይ ነው። ለነገሩ አጤ ኮሮና አለምን ስንት እንዳስደገደገ እናውቃለን። ጉንፋን አይለቀኝም። ሲያሸኝ ኑሮ፤ ስንብቴም በዚህው ይሆን እንደሆን አላውቅም። 
 
"የሰው ልጅ መንገድን ያዘጋጃል፤
እግዚአብሄር ግን አካሄዱን ያቃናለታል።"
(ምሳሌ ፲፮ ቁጥር ፱)
 
#እፍታ በምልሰት - እንደ መግቢያ።
ባለፈው ሳምንት ይህን የተከበሩ #የዬኔታን ፕሮፌሰር ዶር ማለደ ማሩን ከሃኪም ዩቱብ ቻናል ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ አገኜሁት። ያዳመጥኩት በሲቃ ነበር። እኔ ፈሪ ስለሆንኩኝ ከምነገረው በስተቀር እከሌ፤ እከሊት ደህና ናቸው ወይ ብዬ ጠይቄ አላውቅም። በሥርዓትም መርዶ ተነግሮኝ አያውቅም። ትልቁ የህይወቴ ድክመት ተሎ መጽናናት አለመቻሌም ነው። እፈራለሁኝ። አይደለም ለሰው ልጅ ወፍ መንገድ ላይ ሞቶ ካገኜሁኝ አንስቼ ቀብሬ ነው የምሄደው። 
 
ሃዘን ከቤተሰብ ከኖረ እነ ታላቁ መምህር በላይ ሁሉ ውግዘት የጣሉብኝጊዜ ሁሉ ነበር። በሥጋው ለተለዬው ሳይሆን የሚታሰበው ለእኔ ነው። መገናኜቱ ላይ ቁጥብ እምሆነውም፦ መለዬትን ስለምፈራም ነው። ሃዘኔ ጥልቅ፤ ሳስተናግደውም በማምረር ነው። እንደዚህ ባልሆን በወደድኩኝ። ስለሆነም የኔታ ፕሮፌሰር ማለደ ማሩ በህይወት የመኖራቸውን ጉዳይ ጠይቄ አላውቅም። 
 
በቤተሰብም ማን በህይወት እንደ አለ፤ ማን በሥጋ እንደ ተለዬ ደፍሮ የሚነግረኝ ማንም የለም። ሞትን ያህል መራራ ስንብት እኔ የማስተናግድበት ዘይቤ እና ባህሌ እጅግ ከባድ ነው። በህይወቴም እግሮቼ ወደ ሰርግ ቤት አያቀኑም። ይልቁንም ወደ ሃዘን ቤት ያማትራሉ። በመላ የዕድሜ ዘመኔ አቅጄ ሙዚቃ ኮንሰርት ሄጄም አላውቅም። 
 
የሆነ ሆኖ በዚህ ለዓለምም፤ ለአገሬ ለኢትዮጵያም መራራ ዘመን ላይ የፕሮፌሰር ማለደ ማሩን በህይወት መኖር ስሰማ ከደስታ በላይ ሐሤት ተሰማኝ። ደስታ በእኔ ፍልስፍና ከሐሤት ያነሰ፦ ጊዜያዊ እና ምድራዊ፤ ሰው ሰራሽም ሲሆን ሐሤት ግን ሰማያዊ፤ ገሃዱ አለምን እና መንፈሳዊውን አለም የሚያገናኝ ፍጹም የሆነ የመንፈስ ተስፋን የሚመግብ ነው ብዬ አምናለሁኝ። 
 
ስለሆነም የድንቁን #የኔታ ፕሮፌሰር ዶር ማለደ ማሩን ቃለ ምልልስ ሳደምጥ ሙሉ ሐሤት አገኜሁኝ። እግዚአብሄር ደግ አምላክም ነው። የጎንደር ልጆች ወደ ሳይንስ ትምህርት የምናዘነብልበት መሠረታዊ ምክንያት የጎንደር ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ በጎንደር ከተማ መመሥረት ብቻ ሳይሆን አብዝቶ አደብ እና፤ የማድመጥ ፀጋ በተሰጣቸው በርጉው የኔታ ፕሮፌሰር ዶር ማለደ ማሩ አብነታዊ፦ አባታዊ ተግባርም፥ ሙሉዑ ሰብዕናም ጭምር ነው። ልቅና - በልዕልና። 
 
እኔ የባይወሎጂ እና የኬሚስትሪ ሰቃይ ተማሪ ነበርኩኝ። ምኞቴም ይኽው ዘርፍ ነበር። ምልክቴሜ የሊቀ ትጉሁ የዬኔታ የፕሮፌሰር ዶር ማለደ ማሩ ትጋት ነበር። ዛሬም ያልቀረለት የጦርነት ቀጠናነት፤ ወደ ትምህርት ቤት የአትሂዱ የኢህአፓ የማስጠንቀቂያ ደወል፤ የቤተሰብ በዚኽው ትግል ውስጥ መሳተፍ፤ የእኛ የልጅነት ጭንቀት፦ ፍርኃት - ርደት ተጨምሮ ህልሜ በአጭሩ ተቀጬ። ጭምቱ ደቡብ ትናንትም በስክነት ተማረ፤ ዛሬም እዬተማረ ነው፤ ነገም የእሱ መንበር መደላደያውን መስዋእትነት እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም ስሜን ይገበራል። 
 
ወጣቶች ሆይ! ትናንት እኛን አትማሩ ሲል በነበረው የኢህአፓ የጫካ ትግል ተሳታፊ፤ ዱር ቤቴ ብለው፤ ተሰደው፤ ተምረው፤ ዛሬ የትምህርት ሚር፦ ሚር የሆኑት ፕሮፌሰር ዶር ብርሃኑ ነጋ ናቸው። እኔስ? አንደኛ ክፍል የማስተምርበት ሰርትፍኬት የለኝም። የልዩነቱን ጋፕ ተመልከቱት። እኛ አትማሩ ስንባል የቀድሞው ጠሚር ኃይለማርያም ደስአለኝ ግን ተምረው አገር ይመሩ ዘንድ ዕድል አግኝተዋል። የእኛ የመማር ዕድል፤ የእኛ የደረጃ ተማሪነት፤ የእኛ ዕድሜ ግን ባክኖ ተቃጥሎ ቀረ።
 
ዛሬም ይኽው ተደግሞ አዳምጣለሁኝ። ልባሙ ደቡብ፤ መሃል አገር ግን ሳይስተጓጎል ይማራል - ይዳራል - ለወግ ለማእረግ ይበቃል። እኔ ብነግራችሁ ኬሚስትሪ 100%// ባይኦሎጂ 90 - 97 %// ነበር ማርኬ። 11/12 ክፍል 1ኛ እና ሁለተኛ ነበር የወጣሁት። ጭንቀቱ፤ ስጋቱ፤ የቤተሰብ ዱር ቤቴ ማለት ታክሎ ተጨናጎለ። እና ነገስ??? ትውልድ ሆይ! ሆይ! --- "ልብ ያለው ሸብ።"
 
የተከበሩ የኔታ ፕሮፌሰር ዶር ማለደ ማሩን እኔ በአካል አውቃቸዋለሁኝ። ተማሪ ሁኜ ፋናዬ ነበሩ። ሥራ ላይ ሆኜም አሻራዬ ነበሩ። ግንኙነታችን ተማሪ እያለሁ በርቀት፤ ሥራ ላይ ሆኜ በሥራ ምክንያት አገኛቸው ነበር - በአካል። ቆራጣ ጊዜ ያልነበራቸው ሊቀ - ትጉኃን ነበሩ። ልባምነታቸው ትዳር መሥርተው የልጆች አባት መሆናቸው ነው። 
 
ይህ የገረመኝ፤ የደነቀኝም ብቻ ሳይሆን፦ የክቡርነታቸውን አርማ ያነሳ ልጅም እንዳላቸው ስሰማ በጣም ደስ አለኝ። ትውልድን መተካት ልዩ እድልም ስለሆነ። የማስተዋል ልክም ነው።ዕድሜ በሚሰጠው ፀጋ እና በረከት እኩል ተሳታፊ ለመሆን መወሰን። 
 
የኔታ ፕሮፌሰር ዶር ማለደ ማሩ በነበራቸው የኃላፊነት መስክ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን ውስጣቸው ማድረጋቸው መታደልም ነው። ዬአመራራቸው ህብራዊነት ግሎባሊዝምን የተከተለ እንደነበር ከቃለምልልሱ ተረድቻለሁኝ። ያንጊዜም በርካታ የሻ።ጀርመን ሊቃውንት እንደ ነበሩ አውቃለሁኝ። በዚህ አጋጣሚ ሙያውን ለፈቀዱ የኢትዮጵያ ልጆች ሁሉ የጀርመን መንግሥት ላደረገው ቅን እና ቀና ተግባር ልባዊ ምስጋናዬን ላቀርብላቸው እወዳለሁኝ።
 
በውነቱ ያ ተቋም ሲመሠረት፤ ሲፈጠር፤ ሲጠነሰስ የነበረበት ሁኔታ ዜሮ ላይ ነበር። እኛ ይህን #አናውቅም። በትምህርት ካሪክለምም መግባት ያለበት ይህ ብርቱ ጥረት እና የስኬቱ ሂደት ሊሆን ይገባል። ይህ ተመክሮ ውጭ አገር ቢሆን ለእንድ ሰአት ማብራሪያ ምን ያህል እንደሚያስከፍል በሙያው ያላችሁ ታላላቆቻችን የምታውቁት ነው። ዕንቁ እኮ ነው። የነጠረ። 
 
ቢያንስ አሁን እኒህ ታላቅ የአገር ባለውለታ በህይወት እያሉ፦ ዩንቨርስቲወች ይጠቀሙበት ዘንድ ጊዜውን መሻማት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። በመማሪያ መፃህፍትም ላይ ይኽው ተመክሮ ሊቀመር ይገባል። የሚደንቅ አቅም፤ የሚመስጥ ሰብእና፤ ሐዋርያ የሆነ ፀጋ እና ተመክሮ። እኛ ይህ ሁሉችግር እንደነበረባቸው ፈጽሞ አናውቅም ነበር። ልጅ እያለሁ እሺ ይሁን። ተማሪ ነኝ። ሥራ ላይ ሳለሁ ግን በይፋ ፈተናው ሊነገርን ይገባ ነበር። ተቋሙን ማዕከላዊው መንግሥት እራሱ ፈተና ደቅኖበት እንደ ነበር ነው የተረዳሁት። በዚህም እጅግ፤ በጣም አዝኛለሁኝ። ዕውነት እንዲህ ቀን ሰጥቶት ደምቆ በማዬቴ ግን መኖሬን ለሰጠኝ አምላክ አመስግኜዋለሁኝ። የሆነውን ሁሉ ሳደምጥ፤ ጫናው እና መገፋቱ ፍንትው ብሎ ነው የታዬኝ። ጊዜ ራዲዮሎጂ ነውና። 
 
የሆነ ሆኖ ይህ ቃለ ምልልስ #ለሪሰርችም ሊያገለግል ይችላል። መፃህፍትም ሊፃፍበት ይችላል። ቀደም ብዬ እንዳነሳሁትም በሥርዓተ - ትምህርት ንድፍም ሊገባ ይገባል ባይ ነኝ። ዱር ቤቴን ያሳለጠላቸውን ጎንደር የትምህርት ሚኒስተሩ ፕሮፌሰር ዶር ብርኃኑ ነጋ አንዲት ቅንጣት አሻራ ለማሳረፍ #ዳ ባይሉ ባይም ነኝ። የአማራ ህዝብ አመድ አፋሽ ቢሆንም። 
 
በተለይ ስለ ትውልዱ ግድ ብሎን በዛ ላይ ለምንተጋ ባተሌወች ይህ ምራቁን የዋጠ የስኬት ሰብዕና የህይወት ሽልማትም ነው ብዬ አምናለሁኝ። ያን ያህል የገዘፈ ፈተናን ረትቶ ዛሬ ላለበት ደረጃ እና ብቃት ማድረስ የቅባዓ ባለፀጋነትም ነው። አሁን ባለው የኢትዮጵያ፤ አብሶ የአማራ ክልል የሃዘን ዘመን ላይ ሆኜ ይህን ቃለ ምልልስ ሳደምጥ #አጽናኝ መንፈስ ከእዮር እንደተላከልኝ ነው ያሰብኩት። ማድመጥም፤ መደመጥም ትልልፍ ላይ ስለሆኑ፤ ለገዳማዊ ህይወቴ ተስፋም አጨልኝ።
 
ግራጫማውን ሂደት በጥቂቱ አጠዬመልኝ። ቃለ ምልልሱን ያደረገው ስክን ያለ ወጣት የሃኪም ዩቱብ ቻናልንም አክብሮታዊ ምስጋናዬን ላቀርብ እወዳለሁ። እባካችሁ የማይከፈልበትን #ሳብስክራይብ አድርጉት ስልም በትህትና እጠይቃለሁ። መፃህፍ ነው የፃፈው። ምስጉን የተመሰገነ ተግባር። 
 
#ሐዋርያውን የኔታ እኔ ሳውቃቸው።
 
ልጅ እያለሁ ህልሜ የኔታ ማለደን መተካት ነበር። ሳይሳካ ቀርቶ ወደ ሥራ ስሰማራ እድገቴ ቀልጣፋ ነበር። እኔም ቀልጣፋ ነበርኩኝ። ማንም እንዲህ ሁና ትቀራለች ብሎ የሚያስብ አልነበረም። በተለይ በቀለም ትምህርት አቋርጬ ሥራ ስጀምር መምህራኖቼ አኩርፈውኝ ነበር። ታውቃላችሁ ለአንድ ትምህርት አራት ደብተር ነበረኝ። የወጣልኝ አንባቢ፤ ሃርድ ወርከር ነበርኩኝ። ይህ ደግሞ የአቨይ የአባቴ መምህር እና የቤተ መፃህፍት ባለሙያ መሆኑ ረድቶኛል። ለንባብ ደክሞኝ አያውቅም ነበር። 
 
ስራ አለምም እንዲሁ። ታሜሜ በሃኪም ትእዛዝ ቤት ስቀመጥ፦ እነኛ ለሰማይም ለምድርም የከበሩ አለቆቼ ህመሟን የሚያብሰው ሥራ መቅረቷ ነው ይሉኝም ነበር። በህይወቴ ሙሉ የሥራ ፊርማ ኖሮኝ አያውቅም። አገሬ ሥራዬ ነበር። አንድ ሰው ሲሆን ከሚከፈለው በላይ፤ በስተቀር የሚከፈለውን የሚመጥን ሥራ መሥራት እንዴት ያቅተዋል የሚል ቋሚ መርህ አለኝ። የሆነ- ሆኖ ቀንበጥ ሆኜ የአውራጃ የሴቶች ጉዳይ፤ የክፍለ አገር የሠራተኛ እና የገበሬወች ጉዳይ ኃላፊ፤ የህዝባዊ ድርጅቶች እና የሙያ ማህበራት የክፍለ አገር ጉዳይ ኃላፊ በሆንኩባቸው ጊዜያቶች በተለይ በሁለቱ ዘርፍ በእንድም በሌላም ከጎንደር የህክምና ኮሌጅ ከተቋሙ ጋር ግንኙነት ነበረኝ።
 
የሴቶች አደራጅ ሳለሁኝ በሙያው ካሉ ሴቶች ጋር ባለኝ ግንኙነት፤ የህዝባዊ ድርጅቶች እና የሙያ ማህበራትጉዳይ ሃላፊ ሳለሁም ደግሞ በጤና ባለሙያወች ማህበር፤ በኮሌጁ በነበረው የወጣቶች ማህበር ጋር በነበረው ጉዳይ አስተዳደሩ ሲያስፈልገኝ ተቋሙን አገኛለሁኝ። የሚገርማችሁ ግን አንድም ቀን ስልክ ደውዬ እርዳታ ጠይቄ አላውቅም። ወይንም አስተዳደሩን ቢሮዬ አልጠራም ነበር። እራሴው ሄጄ በአካል ተገኜቼ ነበር እርዳታ እምጠይቀው።
 
ምክንያቱም ለፕሮፌሰር ዶር ማለደ ማሩ ከነበረኝ ልዩ አክብሮት ነበር። ስለሆነም አክብሮቴን የሚያፋለስ ተግባር ፈጽሜ አላውቅም ነበር። እኔ ማን ሆኜ እሳቸውን ጠርቼ ቢሮ ላነጋግር ልቻል? በዕድሜም፤ በአካዳሚያዊ ልቅናም፤ በተመክሮም የማልደርስባቸውን አራት አይናማ ዓይነታ ዝቅ ብዬ ነበር ጥያቄዬን እማቀርበው። 
 
በሌላ በኩል ትልቁ የጤና ባለሙያወች ማህበር ሊቀመንበሩ ረ/ ፕሮፌሰሩ ነበሩ። እሳቸውም ሲያስፈልጉ እራሴ ሄጄ ነበር የማነጋግራቸው። እሳቸው እንዲያውም የእነሱን ጉባኤ መክፈቻ ንግግር ሳደርግ " #ታቸር " ነበር ያሉኝ። ያን ጊዜ ደግሞ ማህበሩ እራሱን ችሎ በጉዳይ ይመራ ነበር። እኔ ተጋብዤ ነው። 
 
የሆነ ሆኖ በወቅቱ ደብዳቤ መላክ፤ እንዲመጡ ፕሮግራም ማስያዝ ይቻል ነበር። መብቱ ነበረኝ። ግን አፈፃፀም ላይ ጥንቃቄ በእጅጉ ያስፈልግ ነበር። ወጣት ነኝ። ወጣትነት ብዙ ልትቆጣጠሩት የማትችሉት ፈተና ያቀርባል። እሱን ማሸነፍ ይጠይቃል። እውነት ለመናገር በዚህ ዘርፍ የነበረኝ ጥንቃቄ ዛሬ ላይ ሆኜ ሳስበው ብልህ ጥበብ ሆኖ አግኜቸዋለሁኝ። በዚህ ብቻ ሳይሆን ፆታዊ በሆኑ፤ ወጣትነት በሚፈቅዱ ጉዳዮችም ሥልጣናም፤ ሥራ ላይም ስሜ እሙሃይ ነበር። ዝንፍም ቅብጥም አልነበረም። እግዚአብሄር ይመስገን። አሜን። እኔ ታናሾቼን ተክቼ ናፍቆቴን ትምህርቴን መቀጠል ነበር ህልሜ። እንደ ለስታ ቅቤ ምኞቴ ቀልጦ ቀረ እንጂ።
 
#ምልሰት እንደ አበው። 
 
በግልም ፈተና ሲገጥመኝ የተከበሩ፤ ፕሮፌሰርዶር ማለደ ማሩን አወያያቸው ነበር። አልደውልም። እኔው ነው የምሄደው። በአገኜኋቸው ጊዜ ሁሉ ለሰው ልጅ ያላቸው አክብሮት የዕድሜ - የዕውቀት - የፆታ - የኑሮ ደረጃ - የተመክሮ ልዩነት ቅንጣት ገደብ አልነበረውም። ቅንነታቸው ጥልቅ ነበር። አክብሮታቸውም ምስባክ። ይህ ከክቡርነታቸው ጋር ሥራ ያገናኜን ሰወች ሁሉ ሊያስማማን የሚችል ፋክታዊ አመክንዮ ይሆናል ብዬ አምናለሁኝ። በእንድም በሌላም ሥማቸው በአልሆነ ጉዳይ ተነስቶ ሰምቼ አላውቅም።
 
ለችግር ፍጥነታቸው የምደነቅበት ጉዳይ ነበር። የማድመጥ ልዩ ክህሎታቸው እንደ አለቃዬ፤ እንደ ቀረጸኝም የተከበረው ጓድ ገ/ መድህን በርጋ ጋር መሳ ለመሳም ነው። ስነ - ምግባራቸው ሙሉዑ - የተረጋጋ - ደልዳላ - የሚመስጥ - ታጋሽነት - በዬደቂቃው የሚያስተምር ሰባአዊነት በአገኜኋቸው ቁጥር አስተውለው የነበረው ልዩ መክሊታቸው ነበር። በጣም የተወሳሰበ የጤና ችግር የገጠመውን በሽተኛ ሲዳስሱት ብቻ #ፈዋሽ መንፈስ፤ አጽናኝ ትንፋሽ ለአስታማሚወች ይናኛል። በተደሞ እከታተለው የነበረው ተማሪወቻቸውን ይዘው በሽተኛ ሲጎበኙ በአስደንጋጭ ሁኔታ ላይ ቢደርሱ እራጋታቸው ይደንቃል። የመሰጠትን የውሃ ልክ ማዬትም ይቻል ነበር። ከሞት የታደጉት ብዙ፤ በጣም ብዙ ሰው አለ። 
 
እኔ ወላጅ አባቴ አቨይ የምግብ ብክለት ደርሶበት ኦርጋኖቹ ሁሉ ተበክለው ነፍሱን ታድገውታል። ታምራት ነበር የፈፀመው ቲማቸው። ችግሩ ድንገተኛ እና አስደንጋጭ ነበር እና። አሁን በቃለ ምልልሱ ስሰማ ከአመሰራረቱ ጀምሮ ምንም የተሟላ ነገር እንዳልነበር አዳምጫለሁኝ። ግን እንዴት ቻሉ??? 
 
በሌላ በኩል የመጨረሻው ታናሽ ወንድሜ ሁለቱ ኩላሊቶቹ ደክመው ለማትረፍ የነበረው የ24 ሰዓታት ትጋትም የማይረሳኝ ዕፁብ ድንቅ ተግባር ነበር። እዛው የሠሩት የኩላሊት አጠባ፦ ችግር የማሸነፍ ጥረት እስከ አሁን ይመጣብኛል። እርግጥ ወንድሜ ከእጄ ላይ ነበር ያረፈው። የእነሱ ጥረት ግን ከድንቅ በላይ ዕፁብ ነበር። ታዳጊ ወጣት እያለሁኝ እኔንም እንዲሁ ከሞት አትርፈውኛል። ህይወቴን ታድገው ለዛሬ አድርሰውኛል። ተቋሙ ብዙ ነፍሶችን ፈውሷል። በቅንነት - በርህርህና - በትጋት። ይህ ሁሉ የስኬት ጉዞ ክንዱ፤ ክብሩ የአመራር የፊደል ገበታው የዬኔታ ፕሮፌሰር ዶር ማለደ ማሩ ነው። ህያው፥ ህልው ስኬት። እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን። 
 
#ሁልጊዜ እንደምለው እኔ እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ፦ መፃህፍቶቼ ላይ እንደፃፍኩትም...
 
1) እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ መክሊት ይዞ ይወለዳል፤
2) እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ መልእክት ይዞ ይወለዳል፤
3) እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ ጥሪ ይዞ ይወለዳል። ይህ ዕውን ሆኖ ያገኜሁባቸው ቃና ናቸው ዬኔታ --- ከእኛም ለቀደመው፤ ለእኛም፤ ለሚቀጥለውም ትውልድ። የትናንት አብሪ ዕንቁ፦ የዛሬ ብርኃናማ አልማዝ፤ የማግስት ብሩህ ኮከብ። ይህን እዮራዊ ጣምራ ዕድል ሳይተላለፋ ዕውን ያደረጉ ጀግና ናቸው ፕ/ ዶ ማለደ ማሩ። ከሳቸው ለህክምና ሄዳችሁ፤ በሥራ አጋጣሚም አግኝታችኋቸው፤ አብራችሁ በምትቆዩባት ደቂቃ ሁሉ ት/ ቤት ናቸው። ሊማር ለፈቀደ ሁሉ። 
 
የፃዲቁ የኋንስ አንደኛ ደረጃ ት/ ቤት ፍሬ አፍርቷል። ለዛውም ተንዠርክኮ ያፀደቀ ሰብላማ ፍሬ ዘር። ህያው፦ ህልው የሆነ መሰጠት። በቃለ ምልልሱ ውሽክ ያልኩበትን ጉዳይ ላንሳ ፦ ስለ እንጉቻችር ጉዳይ። የተገናኜንበት የሥራ መስክ ባለመሆኑ እንጂ እኔም የባይወለጂ ተማሪ ስለነበርኩ ብሰማ በወቅቱ ጥቆማ እሰጥ ነበር። ቀሃ እዬሱስ ክረምት ላይ የሚደላው #የፈጭፋጭት ጅረት እና፤ ጳጉሜ እምንጠመቅበት የአንገረብ ወንዝ ጋር ተያይዞ የሚገኜው ኮለል ያለው ገላእድ ተራራ ስር ያለው #የኮኮች ወንዝም እንጉቻችሪት በእኛ ዘመን በሽ ነበር። የዛሬን አላውቅም።
 
ቅኔው የኔታ ፕሮፌሰር ዶር ማለደ ማሩ አስተዳደር ላይ፤ ህክምና ላይ ምረቃ ሥነ - ሥርዓት ላይ፤ ስብሰባ ላይ ሲገኙ የነበራቸው ግርማ ሞገስ በህሊናዬ ተጥፏል። አናባቢም ነው። ሲያስተምሩ ግን ዕድል አልገጠመኝም። ተመኝቸው የቀረ ዕድል ነው። ተማሪወቻቸው ይናገሩት። እኔ ዕድል ሰጥቶኝ ውስጣቸውን ስመዝነው የማይናወጸው የተሰጣቸው ሰብዕና ግርማ ሞገሳቸው ነበር።
 
ይህ ደግሞ ባለ ቅባዕ መሆናቸውን ያመሳጥራል። ሁልጊዜም ተከብረው፤ ተመስግነው የኖሩ ታላቅ የትውልድ ምስባክ ናቸው የኔታ፦ ፕሮፌሰር ዶር ማለደ ማሩ። እሳቸውም በቃለ ምልልስ እንደ ተናገሩት ግዕዙን፤ ቅኔውን አክለውበት ቢሆን ብዬ አሰብኩኝ። እራሱ ግዕዝ ቋንቋ ከሚስጢራት ጋር ያለው ስምምነት ራሱን የቻለ ዘመን ነውና። ለዚህም ነው ጀርመኖች በርሊን ፍሪ ዩንቨርስቲ፤ ሃንቩርግ ዩንቨርስቲ፤ ሃይደልበርግ ዩንቨርስቲ ልጆቻቸውን በሙያው በዲግሪ የሚያስመርቁበት። የመጽሐፈ ፈውስ ተጠቃሚም ሆነው ጀርመን በመዳህኒት ፍልስፍና አንቱታን የተቃኙት። እኛ ደግሞ ካልጠፋ ሞተን እንገኛለን ግብ ግብ ላይ ነን። ነጣላነት።
 
#ምን ይደረግ? ጊዜን ስለመሻማት፤ ስለመቅደምም፦
 
1) የማከብራቸው፤ ፈቅጄም የማደምጣቸው ዶር ወዳጄነህ ማሕረነ አንድ ፕሮግራም ጀምረዋል " ሀ3 " የሚል አዲስ መሰናዶ አላቸው፤ ይህ ፕሮግራም ይህን የመሰለ ዕንቁ ሰብዕናን አጉልቶ የሚያሳይ መነጸር ማድረግ ቢችል፥
2) ሌሎችም በሳይንስ ዙሪያ መሰናዶ ያላቸው ሚዲያወችም ቢታትሩበት፦
3) ግሎባላይዜሽን ላይ የሚሠሩ ዩኒቨርስቲወች ዕድሉን ቢጠቀሙበት፦ ለልጆቻቸው ህሊና ምህንድስና ዕድሉን ቢጠቀሙበት፤
4) ዶንኪ ቱዩብ " ጀግና " የሚል መሰናዶ አለው። የፕሮፌሰር ዶር ማለደ ማሩ የህይወት ተመክሮ ከጀግና በላይ የሚያደርግ እንጂ ለመመጠኑ የሚያንስ ስላልሆነ ቢያስቡበት። ወድጄ እመከታተለው ዩቱብ ስለሆነ።
5) አዳዲስ ሚዲያወች አሉ እንደ መሪ፤ ማራኪ ወግ፤ ማንያዘዋል የሚባሉ ልቅም ያሉ፤ ክውን ተግባራትን የሚከውኑ። ዲስፕሊንድም የሆኑ። እነሱም የሻሞው ቅን ቤተኛ ቢሆኑ፦ እምወዳቸው ወጣቶች ናቸው። እማዳምጣቸውም። ተስፋ እማደርጋቸውም
6) ለኢትዮጵያ የራዲዮጋዜጠኝነት ህያው አብነት የሆነችው ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩም ዕዱሉ ባያመልጣት ባይ ነኝ። እስከ አሁን ተጣም እንደ ዘገያች ይሰማኛል። ፎቷቸውን ሚዲያ ላይ ማግኜት አልቻልኩኝም። አንድ ጊዜም ስለ አንጋፋው አርቲስትኪሮስ ጽፌ ፎቶ አጥቻለሁኝ። ልጅ ሰውመሆን ይስማው ኧረ ባክህ እናቱ። በዚህ ዘርፍ በርታ በል እባክህን።
7) አባይ ድህረ ገጽ በኢትዮጵያ ሊቀ ሊቃውንት ላይ ራሱን የቻለ መምሪያ ነበረው፤ ዛሬ ድህረ ገጹ አገር ገብቶ ወደ ሚዲያ ሲያድግ ለቀደመ ሃሳቡ ክፍል ይኑረው// አይኑረው ባላውቅም ዕድሉ ባያልፈው ባይ ነኝም። ውስጡ የሆነ አመክንዮ ነው እና። 
 
#ጎንደር ሚስጢሯን አታድፋ።
 
ጤና ይስጥልኝ እቴጌ ጎንደር እንዴት ባጀሽ? አሁን ከሆነ መቋዲሾ መሆንሽን አድምጫለሁኝ። ብዙ አሰቃቂ ዜናወችንም በተከታታዬ አዳምጣለሁኝ። ፆመሽ መፍቻሽ ጥቁር ልብስ መሆኑ ማህፀኔን እንደ ዱባ ይቀረድደዋል። እምዬ የእና ውብ እኛን በመፍጠርሽ ታደለሽ ወይንስ ተበደልሽ ይሆን? አንቺው ዳኚን እናታለምዬ ናፍቆቴ - ስስቴ። እኔስ እዬደከመኝ ነው። አሁን አሁን ሳስበው ሳንገናኝ መራራ ስንብቱ አይቀሬ ነው። 
 
የሆነ ሆኖ ለሊቀ ትጉኃኑ ልጅሽ ለክቡር ፕሮፌሰር ማለደ ማሩ ምን አስበሻል እምዬዋ????
 
1) ቤተ መፃህፍት - ስያሜ?
2) የጎዳና - ስያሜ?
3) ዓውደ - ጥናት?
4) መፀሐፍ?
5) ዓመታዊ - ቀን?
6) የዓውደ ጥናት፤ የፓናል ዲስከሽን? ስለ አንቺ ተፍጥሮ፤ ስለ አንቺ የደከመ ብርቱ የማህፀንሽን ፍሬ አታመሰግኝውምን?
7) ልዩ የምስጋና ቀን? እኮ ምን ተለምሽ ሆድዬ የበሞቴ የአፈር ስሆን ልዕልቴ? ምንስ -- ተሰናዳሽ? እንዲያው ትንፋሽሽ ትርትር እሚል ከሆነ ብዬ ነው ይህን ደጎስ ያለ ደርዝ ያለው ጥያቄ ያቀረብኩት? ከዛ ሁሉ ካነገሻቸው ሰብዕናወች እኮ ችግርሽን ተሸከሞ፤ ግን መፍትሄ አፍልቆ የቀረፀሽ ዓይናማሽን??? -- ያው ገዢወችሼ ጉባኤ ማካሄዳቸውን እያዳመጥን አይደል??? 
 
ጎንደርዋ እባክሽ ፍጠኚ!
ጊዜውን ተሻሚ!
ልጅሽን አክብሪ!
ሽልማትሽን ሸልሚ!
ብርኃኑን ጧፍ አብሪ!
የየኔታሽገድል እኮ -- ታቦት ያስቀርፃል።
 
በሌላ በኩልስ ልዕልት ኢትዮጵያስ? ከመላ ኢትዮጵያ ለመጡ ሸበላ፤ ቀንበጥ ልጆቹ አደራውን በፍቅር ተቀብሎ፤ ፍቅር መግብ ላሰበለ አባወራ አባት ለሆነው ልጅሽ ምን አሰብሽ? አንቺም ተጠዬቂ ንግሥት ኢትዮጵያ ። አንቺን ወዶ እና አክብሮ ስለአንቺ የሆነ ጠይም ዕንቁሽን አትርሺ! አስታውሺ! 
 
#ትዝታ ለአፍታ።
 
የማይረሳኝ፤ የሚናፍቀኝም የጎንደር የህክምና ኮሌጅ የምረቃ ሥርዓቱ ነበር። የኔታ ፕሮፌሰር ዶር ማለደ ማሩ የአገር ታቦት የሆኑት፦ በግርማ ሞገስ በክብር አለባበስ ከብረው፤ በዕለቱ መራቂ አካላት ጋር ልጆቻቸውን ከመላ ቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው ሲያስመርቁ፤ ብሄራዊው የዕውቀት መዝሙር በህብር ዝማሬ ሲቀርብ ዕለቱ በሳቅ፤ በስኬት ፈክቶ አድዮአበባ ጋር በፍቅር ሲያወጉ፦ የማይረሳኝ ልዩ ገጠመኝ ደግሞ፦ አባትም እናትም ዶክተር፤ ተመራቂውም የበህር ልጅ ዶር በዛሬ አጠራር ቤተ - ተጋሩ የሲቃ ዕንባው ዕለት ……… 
 
ሌላው ነፍስዋ ጎንደሪኒ ተመራቂወች ቤተሰብ ማረፊያ ከሌላቸው ህዝቡ ለማስተናገድ ፈቃደኛ ነበር። ከእኛ ቤት እኔ ስደት ላይ ሆኜ እንኳን ይህ በትጋት ይከወን እንደ ነበር አውቃለሁኝ። "ለትንፋሽዋ" ጎንደርዬ ይህ እንደ ልዩ ምርቃት የሚታይ ዝክረ ትጋቷ ነው። ዛሬ በመስተጓጎል ላይ በሚገኜው ጥምቀት በአልም ይህ ይትበሃል ጌጥ ነበር። ለተማሪወችም ቤተሰብ በመሆን አብነታዊ ትሩፋትም ትውፊቷም ነው ጎንደርዬ። 
 
የሆኑ ሆኑ ተቋሙ የነበረበት ችግር በጣም የከፋ እንደ ነበር ነው ያዳመጥኩት። ይህን ከቃለ ምልልሱ ነው የተረዳሁት። ተቋሙ ህዝባዊ ስብሰባ አካሂዶ ቢያወያዬን ኖሮ፦ ፕሮፌሰር ዶር ማለደ ማሩ ብቻቸውን አይሸከሙትም ነበር። እራሱ ውሎ አበሉ እና ተልእኮው እኮ አይመጣጠንም ነበር። 
 
ለዚህ ተጨማሪ በጀትን የማደራጀት አቅሙ የነበራቸው ትንታጎች ያንጊዜ ጎንደር ነበራት። እንዲያውም በእኔ ዘመን ወጣቶች በጣም ቀልጣፎች እና ስልጡን ነበር። ለኮርስ ስንላክ እንኳን በአብነት ነበር እምናጠናቅቀው።
 
እና ብቸኛው ተቋማችን ያን ሁሉ ችግር ተሸከሞ ግን ልጆቹን በፈካ ፈገግታ ለወግ ለማዕረግ ሲያበቃ ቅንጣት ችግር ያዬው አይመስልም ነበር። በወቅቱ ችግሩ ቢታወቅ የሚቻለውን ሁሉ ለማድረግ እንደ ዜጋ ትውልዳዊ ድርሻችን መወጣት በቻልን ነበር። ይህ ያመለጠ ዕድል ነበር። ህንፃውን በማስፋት እረገድ አሻራ ለማሳረፍ የድርሻችን መወጣት በቻልን ነበር።እንችልም ነበር። 
 
#እርገት ይሁን አይደል?
 
የማከብራችሁ የአገሬ ልጆች ዛሬ በማህበራዊ ሚዲያ በስፋት አድናቆትን ያተረፋት ወጣት ዶር አብይ ታደሰ በጅማ የስንት ህፃናትን የመተንፈስ ችግር እንደ አቃለሉ በተለያዬ ሚዲያወች አዳምጠናል። ይህ ሊቀ - ትጉህ ወጣትን ያፈራው ተቋም መሥራች ናቸው ክቡር የኔታ ፕሮፌሰር ዶር ማለደ ማሩ። አንዱ ፍሬ ይህን ያህል ካሰበለ፤ ተቋሙ ከተመሠረተ ጀምሮ የተከወነው ተግባር፤ ስኬት ሲሰላ ሚዛን ማውጣት አይቻልም። ነፍስን - ማሰንበት፤ ከስቃይ -- መገላገል፤ ዕድሜ -- ማርዘም፦ የእናቶች የሳቅ ቤተ ሰብ መሆን ከዚህ በላይ የሰባዕዊ መብት ተሟጋችነት የለም። 
 
በመጨረሻ የሲስተር መለሱ ተሰማ ባለቤት ዶር መልኬ እንድሪስ ከዚህ አለም በሥጋ መለያታቸውን በቃለ ምልልሱ ሰማሁኝ። ለመላ ቤተሰቡ መጽናናትን እመኛለሁኝ። ዶር መልኬ ሹፌር ነበሩ። ሹፌር እያሉ ነርስ ባለቤታቸውን ከእመት በኋላ ከመነኩሲት ጣይቱ እና ከወር ተሰማ ከተገኙት ሲስተር መሰሉ ተሰማን አገቡ። ደብረ ብርሃን ቦታ ተመርተው ቤትም ሰርተው ነበር። መልካም ቤተሰብም ነበሩ። በጥረታቸው በሹፌርነት ያገለገሉትን ተቋም ተምረው በዶክተርነትም አገለገሉ። ይህ የነበረውን ቀና እና ቅን አስተዳደር ያሳዬ የዘመን ራዲዮሎጂም ነው። 
 
ይህ አብነታዊ ጉዞ ደርዝ ያለው ቋሚ አሻራዊ ተግባር ይፈፀምበት ዘንድ ነው የጹሁፌ አላማ። የታሪኬ ክፍለ አካልም ስለሆነ በምልሰት ባድማዬን እዬቃኜሁኝ በሲቃ ነው የኮለምኩት። በህይወት ኖሬ ለዚህ ላበቃኝ አምላኬሜ ክብር ምስጋና ይሁን። አሜን።
እጅግ ለሚናፍቁኝ፤ በበዛ ክብር ለማከብራቸው ለዬኔታ ፕሮፌሰር ዶር ማለደ ማሩ እና ቤተሰቦቻቸው፤ ለሙያ ልጆቻቸው ሁሉ ያንጊዜ አብረው ለታተሩት ለእነ ዶር ማስረሻ ለጠቅላላ ቲሙም የማይነጥፍ ትሁታዊ አክብሮቴ ይድረሳችሁ ልል እወዳለሁኝ።
 
 
በዛ ዘመን የጎንደር የህክምና ኮሌጅ ለሠራተኞቹ ሙሉ የመኪና ሠርቢስ ይሰጥ ነበር። የገዘፈው የአስተዳደሩ ልቅና በልዕልና ቁም ነገርንበቃለ ምልልሱ ከሰማሁት ቢሮክራሲያዊ ትብትብ ችግር አንፃር ሳስሰበው የማይቻለውን ያስቻለው ፀጋ የኔታ ፕሮፌሰር ዶር ማለደ ማሩ እንደ አባቶቻችን የዊዝደም ባለፀጋ እንደነበሩ፤ ማንበብ ችያለሁኝ። መተርጎሙን እና ማመሳጠሩን ለእድምታ ባለሙያወች የቤት ሥራ ልሰጥ እሻለሁኝ።
 
አባ ቅንዬ ርጉው፥ ደልዳላው፤ ታጋሹ፤ ሞጋቹም የኔታ ፕሮፌሰር ዶር ማለደ ማሩ እግዚአብሄር ይስጥልኝን ያልኩት ስጽፈው ቆሜ ነው። የማቱሳላን ዕድሜ እመኛለሁኝ። የሺወች የዕውቀት አቨው ምስባክ ነወት እና ሰብለወትን ጨምረው ያዩ ዘንድ ዘንካታ ምኞቴን እገልፃለሁኝ። ለእኔ በግል ለችግሬ ደራሽነት፤ ለኃላፊነቴ ስኬት የማይጠገበው ቅንነት፤ ደግነት፤ ርህርህና ምንጊዜም ቁሞ ያስተምረኛል። ይኑሩልን አባት፤ ወንድም፤ የኔታ። አሜን።
 
……… /// #ልዩ ማስታወሻ የተከበሩ ዶር ፍሰሃ ጎንደር ከተማ የግል ክሊኒክ የነበራቸውም የተቋሙ ፍሬ ናቸው እና ሃኪም ዩቱብ ቢቀጥልበት።
 
"አድርገኽልኛልና ለዘላለም አመሰግንሃለሁ፥
በቅዱሳንህም ዘንድ መልካም ነውና
ስምህን ተስፋ አደርጋለሁ።"
(ልብ አምላክ ዳዊት መዝሙር ምዕራፍ ፶፩ ቁጥር ፰ - ፱ )
 
"52 አመት በሀኪምነት አገልግያለው" - ኘ/ር ማለደ ማሩ | Prof. Malede Maru | Season 2 Episode 10 | Podcast | Hakim
ከ3000 በላይ ቀዶ ህክምናዎች? የብዙ ህፃናት አባት ዶ/ር አብይ ታደሰ ከጂማ!#Drabiytadessejimma#gizachewashagrie#health#child
«ጀግናው ዶክተር… የልጆቹን ስቃይ ሳይ እያለቀስኩ የምሰራበት ወቅት አለ ለኔ ትልቁ ክፍያዬ ድነው ሳይ ነው ዶ/ር አብይ ታደሰ ||» Seifu on EBS
«በ32 አመቴ ከ4ሺ በላይ ቀዶ ጥገናዎችን አድርጊያለሁ!» ⁠ዶ/ር አብይ ታደሰ | Dr Abiy Tadesse|⁠ |Ethiopia| @DawitDreams
 
የማከብራችሁ የሥርጉትሻ ገጽ ቤተኞች አብረን ቆዬን። ትህትናችሁ ሁልጊዜም ቆሞ ያስተምረኛል። ኑሩልኝ የኔ ውዶች። አሜን።
 
ቸር አስበን፦ ቸር እንሁን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
ሸበላ ሰንበት። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
16/11/2024
{ ኮሽ አይሏ ሲዊዘርላንድ - ዙሪክ ደጓ ቪንተርቱር ከተማ። )
 
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ዕውነት ጋራጅ አያስፈልገውም።
የመፍትሄ የኔታወች ይከበሩ!

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።