BBC "በሰሜን ጎጃም በድሮን ጥቃት ነፍሰ ጡር ሴቶችን ጨምሮ 50 የሚሆኑ ሰዎች መገደላቸውን የዓይን እማኞች ተናገሩ" የምስሉ መግለጫ, ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል የተባሉትን አካባቢ"

 

"በሰሜን ጎጃም በድሮን ጥቃት ነፍሰ ጡር ሴቶችን ጨምሮ 50 የሚሆኑ ሰዎች መገደላቸውን የዓይን እማኞች ተናገሩ"
የምስሉ መግለጫ, ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል የተባሉትን አካባቢ የሚያሳይ ካርታ
8 ህዳር 2024, 07:14 EAT
በአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞን ደቡብ አቸፈር ወረዳ በተፈጸመ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ህጻናትን እና ነፍሰ ጡር ሴቶችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች እና የዓይን እማኞች ለቢቢሲ ተናገሩ።
ጥቃቱ ማክሰኞ ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም. ከወረዳው ዋና ከተማ ዱርቤቴ 40 ኪሎ ሜትር ገደማ በምትርቀው አርጌ (ዝብስት) በተባለች ታዳጊ ከተማ በተከታታይ ሦስት ጊዜ መፈጸሙን እማኞች እና ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ጠዋት 1፡10 አካባቢ በከተማዋ ገበያ አካባቢ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት እና ጤና ጣቢያ ላይ ጥቃቱ እንደተፈጸመ እማኝነታቸውን ለቢቢሲ የተናገሩ የአካባቢው ነዋሪዎች፤ “ከልጅ እስከ አዋቂ ያለቀበት” ነው ብለውታል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ስለ ጥቃቱ ጥቆማ እንደደረሰው ጠቁሞ መረጃ እያሰባሰበ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግሯል።
በድሮን ጥቃቱ መረብ ኳስ ይጫወቱ የነበሩ ልጆች፣ ለሽምግል እና የተቀመጡ ሰዎች፣ ህክምና ላይ የነበሩ እናቶች፣ የጉልበት ሠራተኞች፣ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ እና እርሻ ቦታ ላይ የነበሩ ሰዎች ሰለባ እንደሆኑ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ጥቃት የደረሰባቸው ሦስቱም አካባቢዎች በቅርብ ርቀት ላይ እንደሚገኙ ነዋሪዎች የጠቆሙ ሲሆን፤ ቢቢሲ አካባቢዎቹ ከ300 ሜትር ራዲዬስ ባነሰ ርቀት እንደሚገኙ በካርታ እና በሳተላይት ምሥል አረጋግጧል።
ከጥቃቱ አንድ ቀን አስቀድሞ የድሮን ቅኝት እንደነበረ ለማመልከት “አየሯ ስትዞር ነበር” ያሉት ነዋሪዎች ጥቃቱን “ከተማዋን በሙሉ ለማጥፋት” ይመስል ነበር ብለውታል።
“ህጻናት የለ፣ ሽማግሌ የለ፣ ወጣት የለ በሙሉ መደዳውን [ተመተዋል]። ጥግ ለጥግ የነበሩ ብዙ ቤቶችም ተመተዋል” ሲሉ የጥቃቱን መጠን የገለጹ አንድ የዓይን እማኝ፤ “ንጹሃን ናቸው” ሲሉ ስለ ሟቾቹ ማንነት ተናግረዋል።
“የእግዜር ቁጣ ነው የመሰለን፤ ከሰማይ መጥቶ ነው እንደ መብረቅ የወደቀብን” ያሉ አንድ ነዋሪ ያልጠበቁት ክስተት መሆኑን መስክረዋል።
የፍንዳታ ድምጽ ሰምተው አካባቢው ላይ በፍጥነት እንደደረሱ የተናገሩ ሌላ ነዋሪ፤ በየቦታው የወዳደቀ አስከሬን ማየታቸውን ጠቁመው ሁኔታውን “ዘግናኝ” ሲሉ ገልጸውታል።
ጥቃቱ ሲፈጸም ቤተ ክርስቲያን እንደነበሩ የተናገሩ ሌላ ነዋሪ ደግሞ፤ በቅጽበቱ ራሳቸውን ለመከላከል “በያለንበት ተኛን” ብለዋል። እርሳቸው እና አብረዋቸው የነበሩ ስድስት ሰዎች “በቸርነቱ” ቢተርፉም አቅራቢያቸው የነበሩ ሰባት ሰዎች ግን እንደተገደሉ ተናግረዋል።
“ሰው መሆን ያስጠላል። ሰው በሰው ላይ እንደዚህ ዓይነት ጭካኔ ሲፈጽም አይቼ አላውቅም” ሲሉ የደረሰውን ጉዳት የሚገልጹት ነዋሪው፤ “ከባድ፤ አስከፊ ጥቃት ነው የደረሰው” ብለዋል።
ከሟቾቹ ውስጥ በትምህርት ቤቱ ጊቢ ውስጥ ኳስ ጨዋታ ላይ የነበሩት ከ13 በላይ ህጻናትን ጨምሮ ነፍሰ ጡር እናቶች የጥቃቱ አስከፊነት መገለጫ ናቸው ብለዋል።
ጤና ጣቢያው ላይ በደረሰው ጥቃት የእርግዝን ክትትል እና ምጥ ላይ የነበሩ እናቶች ሕይወት ማለፉን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ይህን ያረጋገጡት እና ጥቃቱ ሲደርስ ጤና ጣቢያው ውስጥ የነበሩ አንድ ባለሙያ፤ የእናቶች ክትትል ማዕከል ላይ የደረሰው ጉዳት ከባድ መሆኑን ጠቅሰው፤ አምስት ነፍሰ ጡር እናቶች እና ሌሎች ሁለት አስታማሚዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።
“ውስጥ የተኙ እናቶች ላይ ነው የወደቀው” ያሉት የጤና ጣቢያው ባለሙያ በጥቃቱ ሦስት ሴት የጤና ባለሙያዎች ላይም የመቁሰል ጉዳት መድረሱን አመልክተው፤ የደረሰውን ጉዳት “መሪር” ሲሉ ገልጸውታል።
ሦስት እናቶችም “በድንጋጤ” ጽንሳቸው እንደወረደባቸው ባለሙያው ተናግረዋል።
ቢቢሲ በገለልተኛነት ማረጋገጥ ያልቻላቸው በአካባቢው የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ በሰዎች ላይ የደረሱ ጉዳቶችን የሚያሳዩ ናቸው የተባሉ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች እና ፎቶዎች ባለፉት ቀናት በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ ሲጋሩ ቆይተዋል።
• በአማራ ክልል አራት ካምፖች “ለጅምላ ማሰሪያነት” መዋላቸውን አምነስቲ አስታወቀ7 ህዳር 2024
• በአማራ ክልል አዊ ዞን ከ20 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ6 ህዳር 2024
• በሰሜን ጎጃም ዞን ድሮንን ጨምሮ በተፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ ሰዎች መገደላቸውን የዓይን እማኞች ተናገሩ18 ጥቅምት 2024
የምስሉ መግለጫ, ጥቃቱ ተፈጽሞበታል የሚባለው አርጌ (ዝብስት)
ገበያው አካባቢ በተፈጸመው ጥቃት ቤታቸው ውስጥ ቁርስ እየበሉ ነበር የተባሉ አምስት የአንድ ቤተሰብ አባላትም (ነፍሰ ጡር እናት እና አባት ከሦስት ልጆቻቸው ጋር) መገደላቸውን ነዋሪዎቹ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የሟቾቹ ጎረቤት የሆኑ አንድ ነዋሪ “አንድ ላይ ነው የረገፉት” ብለዋል። የልጆቹ እድሜ ከ10 ዓመት እስከ 17 ዓመት እንደሚደርስ የገመቱት ጎረቤት፤ ነፍሰ ጡር የነበረችው እናት “እግዜር የሰጣትን ሳታራግፈው መሄዷ...” በነዋሪው ዘንድ ድርብርብ ሐዘን መፍጠሩን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በድንገተኛው ጥቃት ከባለቤታቸው እና ከልጆቻቸው ጋር መገደላቸው የተነገረው አባወራ አቶ ስመኘው በዕውቀት እንደሚባሉ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከሟቾቹ ውስጥ ሰባቱ ዘመዶቻቸው እንደሆኑ የተናገሩ አንድ ነዋሪ፤ “ከአንድ ቤት እስከ አምስት ቤተሰብ የሞተ አለ” ሲሉ እልቂቱን ገልጸዋል።
የ15 ዓመት ቅርብ ዘመዳቸው በዚህ ጥቃት እንደተገደለ የተናገሩ ሌላ ነዋሪ፤ “ሐዘኑ ያልገባበት ቤት የለም” ሲሉ ከአንድ ቤተሰብ ሁለት እና ሦስት ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።
“እልቂት ነው” ሲሉ ክስተቱን የገለጹ ሌላ ነዋሪ፤ “ይህን ያህል ስንኖር እንዲህ ዓይነት ነገር ማየት ቀርቶ ሰምተን አናውቅም። በንጹሃን ላይ እንዲህ ያለ አደጋ መድረሱ ከባድ ነው” ብለዋል።
አንድ አስከሬን ያነሱ ነዋሪም ባዩነት ነገር መረበሻቸውን ገልጸው “አሞኛል” ብለዋል።
ሌላ ነዋሪም “ያን ሁሉ ያየ እንጀራ የሚበላ እኮ የለም። እንጀራ የሚባላ ለም። ትናንትናም ዛሬም የሚበላ የለም” ሲሉ እንዲሁ መረበሻቸውን ገልጸዋል።
በጥቃቱ የተገደሉ ሰዎች ሰውነታቸው ተለያይቶ እና ፊታቸውን መለየት ተቸግረው እንደነበር የተናገሩት ነዋሪው፤ የድሮን ቅኝት በመቀጠሉ በስጋት በጅምላ ለመቅበር መገደዳቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“የእገሌ ወንድም፣ የእገሌ እህት፣ የእገሌ ልጅ፣ የእገሌ አባት እየተባለ እንጂ መልኩ አይታወቅም” ሲሉ አስከሬን ለመለየት መቸገራቸውን ገልጸው፤ በአንድ መቃብር እስከ 15 ሰዎች በጅምላ መቀበራቸውን ተናግረዋል።
“[አስከሬን] እየተለቃቀመ በጋሪ ነው የተጫነው። ተሰባስቦ ነው የተቀበረው” ያሉት ነዋሪዎች ቀብር በቅርብ ርቀት በሚገኘው እና በጥቃቱ አነስተኛ ጉዳት ደርሶበታል በተባለው ዝብስት ማሪያም ቤተ ክርስቲያን “ፍትሃት” ሳይደረግ እስከ ምሽት 12፡00 መፈጸሙንም ተናግረዋል።
አስከሬን ያነሱ አንድ ነዋሪ ጥቃቱ በደረሰበት ቀን 44 አስከሬን ማግኘታቸውን የተናገሩ ሲሆን፤ በማግስቱ ደግሞ የአራት ሰዎች አስከሬን መገኘቱን ተናግረዋል።
ሌሎች ሁለት ነዋሪዎች ደግሞ በጥቃቱ የተገደሉ “43 ሰዎችን” መቁጠራቸውን ገልጸው፤ 21 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል ብለዋል።
በድሮን ጥቃቱ 64 ሰዎች መጎዳታቸውን የተናገሩት የጤና ጣቢያው ባለሙያ፤ 43 ሰዎች መገደላቸውን አረጋግጠዋል።
21 ቁስለኞች ጤና ጣቢያው ላይ ክትትል እየተደረገላቸው እንደነበር የጠቆሙት ባለሙያው፤ “የምንችለውን አድርገናል። ግን ስምንቱን ሰዎች ማትረፍ ወደ ማንችለው ደረጃ እየደረስን ነው” ብለዋል።
ከባድ ጉዳት የደረሰባቸውን ቁስለኞች ለተሻለ ህክምና በሁለት አምቡላንስ ወደ ዱርቤቴ ቢልኩም ላሊበላ የተባለ አካባቢ ላይ “የመንግሥት ኃይሎች” ተኩስ ከፍተው እንደመለሷቸው ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የደረሱበት ያልታወቁ ሰዎች በመኖራቸው የሟቾች ቁጥር ከዚህም በላይ ከፍ ሊል እንደሚችል ነዋሪዎች ጠቁመዋል።
“በአቅራቢ የነበሩ ሰዎች ያልተገኙ አሉ። እነርሱ ሳይሞቱ አይቀሩም. . . ገና እስከ ሠልስቱ [ሦስተኛ ቀን] ድረስ የሞተ ሰው ይገኛል” ሲሉ አንድ ነዋሪ ፍለጋ እተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
“በጣም ትልቅ ጉዳት ነው” ያሉት ነዋሪው “ከሞቱት በላይ በድንጋጤ የተጎዱ ብዙ ሰዎች አሉ” ብለዋል።
ነዋሪው የፍንዳታ ድምጽ ሰምተው በድንጋጤ ሲሮጡ ብዙ ሰዎች ወድቀው እና ገደል ውስጥ ገብተው መሰበራቸውንም ተናግረዋል።
“በድንጋጤ አድራሻው የጠፋ ብዙ ሰው አለ። የተጎዱ፣ የተሰበሩ፣ በገደል ላይ ሲሄዱ ወደቁ አሉ” ብለዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች በስጋት ምክንያት ከተማውን ለቀው እየወጡ መሆኑን የተናገሩት ነዋሪዎች ከተማዋ “ወና” ሆናለች ብለዋል።
“ሰው በፍርሃት እየሸከፈ እየወጣ ነው። በጣም ከባድ ነው” ሲሉ አንድ ነዋሪ፤ ሌላ ነዋሪ ደግሞ “ሰው የሚባል የለም” ሲሉ ያለውን ሁኔታ ገልጸዋል።
“ዛሬ [ረቡዕ] ገበያ ነው። እንኳን ገበያ ሊመስል. . .የሰው ዘር የሚባል የለም” ብለዋል።
ቀደም ሲልም ጥቅምት 4/2017 ዓ.ም. በአካባቢው የአየር ጥቃት ተፈጽሞ እንደነበር የተናገሩት ነዋሪዎች፣ በዚህ ጥቃት ሁለት ሰዎች መገደላቸውን እና በርካታ ቤቶች ላይ ጉዳት መድረሱን አስታውሰዋል።
አካባቢው “በመንግሥት አስተዳደር” ስር እንደሚገኝ የተናገሩት ነዋሪዎች፣ የፋኖ ኃይሎች በአካባቢው እንደማይንቀሳቀሱ ተናግረዋል።
“ምክንያቱ ባልታወቀ ነገር ይህን ያህል ድብደባ? ሲሉ ለምን እንደተጠቁ ጥያቄ የሚያነሱ አንድ ነዋሪ፤ “እንዴት እኛ ላይ ተጣለ? ጥያቄያችን ነው። በወሬ እንደምንሰማው ፋኖ ባለበት ነው የሚጣለው” ሲሉ የፋኖ ታጣቂዎች በአካባቢያቸው እንደማይንቀሳቀሱ ተናግረዋል።
“አንዳንድ ቀን አልፎ ሲሄድ ነው እንጂ የምናየው እኛ ላይ [ፋኖ] የለም” ያሉ ሌላ ነዋሪ ደግሞ፤ “[ፋኖ] እኛ ጋር አይውልም፤ አያድርም፤ አናየውም፤ አልፎ መሄድ ብቻ ነው” ብለዋል።
“የሆነ ነገር ቢኖር እንኳ ያው ‘የእኛ ችግር ነው፤ ወይ የእኛ ሰዎች ናቸው ያስገደሉን’ ብለን መንግሥትንም የምንለው ነገር የለም ነበር። ዝም ብሎ እኛ ላይ ሲወርድብን ግን እኛ ላይ የተፈጸመ ጥቃት ነው ብለን ነው የምናምነው” ሲሉ ሌላ ነዋሪ አክለዋል።
በአካባቢው ነዋሪዎች ዝብስት በመባል በምትጠራው አነስተኛ ከተማ በተፈጸሙ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ሕዝቡ በሰቆቃ ውስጥ ነውም ብለዋል።
“ማታ ሲባባ የማያድር ህጻን የለም። ከጥቅምት 4 ጀምሮ ህጻናት ናቸው አስቸግረውን ያሉት። አብዛኛው [ልጅ] በጸበል ነው ያለው። ‘መጣብኝ፤ ጮኸብኝ’ ይላሉ” ሲሉ አንድ ነዋሪ ተናግረዋል።
የአራት ልጆች አባት የሆኑ ሌላ ነዋሪ ደግሞ “ህጻናት ጥይት በጮኸ ቁጥር፤ የሆነ ድምጽ በሰሙ ጊዜ [እየተረበሹ ነው]፤ ብዙ ህጻናት ሐኪም ቤት እና ጸበል ናቸው” ብለዋል።
“እኛ አሁን እንደ ሞቱት ብንሞት ይሻለናል ብለን ነው ያሰብነው። የመጣውን መከራ ምን እናደርገዋለን? ምርጫ የለም። ወጥቶ ወዴት ይኬዳል? ወገኖቻችን ሲያልቁ. . . በጣም ከባድ ጉዳት ነው የደረሰብን” በማለት ሌላ ነዋሪ ጥቃቱ ያደረሰው ጠባሳ ገልጸዋል።
የአካባቢው ነዋሪ ስጋት እንዳደረበትም የጠቆሙት ነዋሪዎች “አንኖርም ብሎ ሕዝቡ ወጥቶ ከከተማው እየተሰደደ ነው። ቤቱን እየዘጋ እሄደ ነው ያለው። ከዚህ በኋላ ለማን አቤት እንላለን ብሎ ሕዝቡ [እወጣ ነው]” ሲሉ ተናግረዋል።
ቢቢሲ ከዞኑ እና ከአካባቢው አስተዳዳሪዎች ተፈጸሙ ስለተባሉት ጥቃቶች እና ስለደረሰው ጉዳት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
የአማራ ክልል ከአንድ ዓመት በላይ የሆነው በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ከሚካሄደው ግጭት ጋር ተያይዞ ሰሜን ጎጃም ዞን ተደጋጋሚ የድሮን ጥቃት እና ግድያዎች እንደተፈጸመበት ከዚህ በፊት የወጡ ዘገባዎች ያመለክታሉ።
*ቢቢሲ ለዚህ ዘገባ ለደኅንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ ስድስት የዓይን እማኞችን እና ነዋሪዎችን አነጋግሯል።"

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።