ድርድር የሰላም መቅኖ ነው። #የበኽሩ ድርድር የእውቀት ዘርፍ ነው። ብልሆች በፀሎት // በድዋ ከከወኑት እዮራዊ በረከትም ነው። ለተጨነቁም ፈጥኖ ደራሽ።
#የበኽሩ ድርድር የእውቀት ዘርፍ ነው። ብልሆች በፀሎት // በድዋ ከከወኑት እዮራዊ በረከትም ነው። ለተጨነቁም ፈጥኖ ደራሽ።
"የሰው ልብ መንገድን ያዘጋጃል፤
እግዚአብሄር ግን አካሄዱን ያቃናለታል።"
(ምሳሌ ፲፮ ቁጥር ፱)
ከማገዶወች ውስጥ የተወሰኑትን አቅርቤያለሁኝ። ስማቸው እና ተግባራቸው አደባባይ ስለወጣ እንጂ ከ10 - 20 ሺ የሚጠጉ የአማራ ልጆች በአፋር በረሃ እንደታሰሩ አድምጠናል። እነኛ ምንዱባን ምን እንደ ገጠማቸው በተጨባጭ እምናውቀው ነገር የለም። የትኞቹ በህይወት ይኑሩ፦ የትኞቹ አካላቸው ጋር ይኑሩ፤ የትኞቹ በጤናቸው ላይ እክል ይግጠም እምናውቀው የለም። መሬት ላይ አማራን የሚወክል ተቋም የለም እና። በሌላ በኩል በሌሎች ክልሎችም ከፋኖ ጋር በተያያዘ የታሰሩ የአማራ ሊቃናት ሊኖሩ ይችሉ ይሆናል። በአማራ ክልልም የአማራ ልጆች ማሰቃያ #ማጎሪያ የአገር ውስጥ #ስደተኛ ካንፕ መሰራቱን ቢቢሲ የአማርኛው መረጃውን አጋርቶናል።
በኢኮኖሚ የተሻሉት ከተሞችን በማንደድ አብሮ በማደህዬት ፕሮጀክት ዛሬ እንኳን ለሌላ ለራስም አልሆን ብሎ የሰው እጅ ተመልካች የሆኑ ከስድስት አመት በፊት ግን የፕሮጀክት ባለቤት የነበሩ የአማራ ልጆች በርካቶች ናቸው። ጫካ የገቡትም የፋኖ ታጋዮች ቢሆኑ ቤተሰብ ይኖራቸዋል። ትዳር ልጅም እንዲሁ። ሁሉም #እናት አለው።
ህዝባችን ሙሉ ስድስት አመት #ቀራኒዮ ላይ ነው። ይህ ግነት አይደለም። በህወሃት እና በአብይዝም መሃል በተከፈተው ጦርነት የተጎዳው የአማራ እና የአፋር ክልል ነው። እርግጥ ትግራይም ለሰባት ወራት የጦርነቱ አውራ ቀጠና ነበር። አብዛኛው የጦርነቱ ለረጅም ጊዜ ዶፍ የወረደው፤ ተቋማት ሳይቀሩ የተቀጡት ታቅዶ የተከወነው የማሳቃቅ ተግባር አማራ ክልል ነው። ገና ጉዳዩ ባጉም ባጉም ሲል አበክሬ ተናግሬም ነበር። ሰሚ የለም። ጦርነትን በጦርነት ቀጠና ላደግን ሰብእናወች እናውቀዋለን እና።
እኔ በአዬሁት፤ በመረመርኩት ልክ በዬትኛውም መስፈርት ይሁን የማህበረ ኦነግ መንፈስን የሰነቀው አብይዝም ለአማራ ህዝብ #መጣበት እንጂ #አልመጣለትም። የማስተዋል ግድፈት፤ በወቅቱ ተስፋ የሚጠጋበት ምንም አይነት እራፊ ነገር ባለመኖሩ ማህበረ ሱሴ ተደገፋ። ጥቂት ብልሆች ግን አወገዙ። ያሉት አልቀረም የባሰ ማእት ዘነበ። ማቆሚያ የለሹ የማሳደድ ዘመቻ እንዲታገስ በተለያዬ ጊዜ የአማራ ህዝብ ሰላማዊ ትግሉን አደባባይ እዬወጣ አስገንዝቧል። ይህም በቂ መረጃ በድምጽም፤ በትእይንትም አለ። የአማራ መላ ህዝብ የጣና እና የላሊበላን ጉዳይ በኽረ አጀንዳው አድርጎ በትህትና በጥዋቱ ነበር ያሳሰበው።
ሌላው ቀርቶ ባህርዳር ከተማ በተደረጉት ህዝባዊ ሰልፎች የመንገድ ውበት የሆኑ #እሳሮች ሳይቀሩ ብርቱ ጥንቃቄ ይደረግባቸው ነበር። የአማራ ህዝብ አብዝቶ በሰጠው #ትእግስት አክብሮ ፍቅሩን በአደባባይ ገልፆ የተቀበለው የማህበረ ኦነግን መንፈስ ያዘለው አብይዝምወለማኢዝም ግን በጥዋቱ ነበር የበቀል ሦስት አፍ ያለውን ሰይፋን የመዘዘው። የመጀመሪያ ኢላማው የአባይ ግድብን ህሊና ኮፒ ራይት ለመንጠቅ የኢንጂነር ስመኜው በቀለ መሰዋት እና ቀብሩ ህዝባዊ ተሳትፎ እንዳይኖረው በግዞት እንዲሆን የተደረገበት ነበር። እኔ ተስፋዬ መቃብር መውረዱን ያረጋገጥኩበት ተርኒግ ፖይንቴ ያ ነበር። ከዛች ቅጽበት በኋላ አቅሜን አላባከንኩኝም። ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ በ100 ቀን ትጋታቸውም ሞጋች ጹሁፍ አጋርቼ ነበር። በኋላ የኢንጂነሩ ሰማእትነት ብዙ የጎሹ ክስተቶችን አጠራልኝ።
ከዛ በተከታታይ ምጣት ዘነበ። ማት ወረደ። አለመተማመኑ ሰፋ። ጥርጣሬም - ነገሰ። አሁን ያለው የፋኖ ንቅናቄ #ትእግስት እም ብሎ አምጦ የወለደው የተጋድሎ ክስተት ነው። እንዴት ተጀመረ? ማን ጀመረው? ለምን ተጀመረ? የፁሁፌ አላማ አይደለም። እኔ እማውቀው ሲሞላ ይፈሳል፤ ሲከር ይበጠሳል ያመጣው ክስተት እንደሆን መቀበል የሚገባ ይመስለኛል። መድረሻ፤ መጠጊያ ያጣ፤ የተገፋ ህዝብ ቋፍ ላይ ነበር። ወያኔ ፈጠረው፤ የደቡብ አፍሪካ ስምምነት አመጣው የሚሉ አሉ። እኔ በዚህ አልስማም። መከፋት በዝምታ ውስጥ ቢሰክንም ቀን ሲከፍትለት መገንፈሉ አይቀሬ ነው።
ግፍ በረከተ። ዘለፋ ተናኜ። ማቃለል አንቱ ሆነ። #መስቃ ነገሰ። አፍ እላፊ አና አለ። ሃግ የሚልም አልነበረም። ከታሪክ ሙሁሩ ከጋዜጠኛ ታዲዮስ ታንቱ፤ የት እንደ አለ ባላውቅም ዛሬ ከአቶ ኦባንግ ሜቶ፤ ከአቶ ዳንኤል ሺበሺ በስተቀር ደፍሮ ወጥቶ አማራን አትጉዱ ያለ፤ አማራን አትግደሉ፤ አማራን አታሳዱ ያለ በቃሉ የፀና አልተገኜም። ዛሬ ጎሽቷል። ዛሬ #አጎፍሯል። ይህን አጥርቶ፦ ከርክሞም ነገን አፍክቶ እንዲያመጣ የሚጠበቀውም ይህ ማገዶ ህዝብ ነው።
ለዛውም ተሰውተህ የምትተርፍ ካለህ ወደ ቀይህ ትመለሳለህ። አንተን እኛ ያሰማራነህ ለአንጋችነት ብቻ ነው። የፖለቲካ #ስልጣኑ ለአንተ የተፈጠረ አይደለምም አለበት። ግፋ በዬአቅጣጫው ነው የአመድ አፋሹ ነገር አማራ። ዝምታዬም እንዲህ አይነት ገረጭራጫ እሳቤወችን፤ ግፍ ያዘሉ መልእክቶችን ታግሶ ማሳለፍ የተገባም ስለሆነ። ትግሉን ግን ይጎዳል። ትጉኃን ነገን ለማን ታጬ? ስለምን እደክማለሁ ሊሉ አስችሏል። ስለተሰው ፋኖ ቤተሰብ የተጀመረ ፕሮጀክትም ነበር። ያም እክል ገጥሞታል። ለአንድ ለተሰዋ ቤተሰብ በአመት በነፍስ ወከፍ 600.00 USA$ ተሰልቶ መጀመሩን አውቅ ነበር። የተቀደሰ ፕሮጀክትም ነበር።
የፋኖን ንቅናቄ የፖለቲካ ድርጅቶች የባለቤትነት ጉዳይ ጋር ግን የሚሰዋው አማራ፥ ስኬቱ ብስራቱ ለማን??? ሁልጊዜ ጅልነት አልቦሽነት ስለሆነም። የአማራ ልጅ ባለቤት የሆነ የፖለቲካ #ባለስልጣን ቢኖረው እኮ ይህን ያህል መረማመጃ ባልሆነ ነበር። "በሞኝ ክንድ ዘንዶ" አይሆንም ነበር። ማህበራዊ መሰረቱን ያጣ፤ በጅማሬው መጨንገፍ የገጠመውም፤ ትንሽ መጠለያ ቢጤ ያለውም የሚተመው ወደ ዚህ የነፃ አቅም ቅርምት ላይ ነው። ይህ በማህበሩ ተጋሩ፤ በማህበረ ኦነግ ግን ትውር የሚል የለም። አይሞከርም። ባለ ጉዳዩ እራሱ ባለቤቱ ብቻ እና ብቻ ነው።
የሆነ ሆኖ እያንዳንዱ የኢትዮጵያ መንደር የሚታወቀው በአማራ መገደል ሆነ። ጭራሽ በባዕቱ #አግብቶት የኖረውን መሳሪያ ፍታ??? ከድፍረት በላይ ንቀትም ነው። ከዚህም በላቀ ውርዴትን ማጨትም ነበር። እደጃፋ ሄዶ ባሩድ መቀለብም የተገባ አልነበረም። የግፍም የጡርም አይነት አለው። በቀሉ እጅግ ይጎመዝዛልም።
በቅንነት የደገፈ። ያበረታታ። የመረጠ። ችግር ሲገጥም ስንቅም ትጥቅም አንጋች ሆኖ መኖሩን ለገበረ ህዝብ እራፊ ሰላም መንሳት የተገባ አልነበረም። የአማራ ህዝብን መከፋት #ብሶቱን ፕሮጀክት ያደረጉ ነፍሶች ሊኖሩ ቢችሉም፦ ለአማራ ህዝብ የመኖር እለታዊ ሁነት ግን ዋስትና ማጣት፦ ለራሱ ነፍስ መቀጠል መትጋቱ ተፈጥሯዊ ነው። ትግሉን እንዳልጎዳ በማለትም ለረጅም ጊዜ በተደሞ ቆይቼ በዚህም በዚያም ዘለፋ ሲበረክት አንድ አውድዮ ስለፋኖ ባህላዊ መንፈስ ሰራሁኝ። የገበሬ አደራጅም ስለነበርኩኝ ፋኖነት ምን ማለት እንደሆን አውቀዋለሁኝ። በአንድ ወቅትም በወጣትነት ሞክሬዋለሁኝ። ፋኖነት ንፁህ ትጋት ነው። ለነፃነት በቅንነት መትጋት።
አድማጭ ነኝ። የፖለቲካ ህይወቴን የተከበረው ጓድ ገ/ መድህን በረጋ ሲቀርፀው ፊደሉ አድማጭነት ነበርና። በፋኖ ንቅናቄ ሰፊ ጊዜዬ የታደመው በአድማጭነት ነው። ጉዳቱ በመረጃ ተደግፎ ሲወጣ፤ የውጭ ሚዲያወች ዕውቅና የሰጡበት መስክ ሲኖር መረጃውን አጋራለሁኝ። በአንድም በሌላም ሳዳምጥ የፋኖ ንቅናቄ" #ዲሴንትራላይዝድ ተደርጎ በምክክር እንደ አስጀመሩት፤ ድርድርም ቁምነገር እንዳልሆነ" አሁን ከመሼ አዳመጥኩኝ።
በመቅድሙ ደግሞ በሌላ በኩል በአንድ ቀን በበርካታ ከተሞች በአንድ አመራር ትርጉም ያለው ተግባር እንደ ተከወነም የመጀመሪያው "ግንባር " እማልወደው ቃል ነው፤ "ግንባር" ለአማራ ህዝብ የምጽዓቱ ቀን የታወጀበት ስለነበር በ60ወቹ ዘመናት አልወደውም። ትርጉሙም፤ አፈፃፀሙም ለወቅቱ የአማራው "ግንባር" ባይገባኝም በዝምታ ተከታትዬው ነበር።
ትግሉ አማራ ከፋኖን በባለቤትነት ለማግለል ስለመሆኑ ቢገባኝም ዝም ነው ያልኩት። በ2013 ዓም የምርጫ ዘመንም #አማራ የሚል ድርጅት አዲስ አበባ ላይ እንዳይወዳደር መደረጉ ስለማውቅ ብቻ ሳይሆን በወቅቱ በትጋት ብታገልበትም፤ ብዙ የደከምኩበት የአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ የባለቤትነት ወዘተረፈነትን ታግሶ ማየቱ፤ ማድመጡ ይገባል የሚለው ውሳኔዬ ዛሬ ላይ ሳያው #ልከኛ ውሳኔ ነበር።
ዛሬም የማነሳው ለእነኛ ለሚታወቁትም ለማይታወቁትም እስረኛ ቤተሰቦቻችን #የድርድር በሩ በተዘጋ ቁጥር ነገን ቋጥረን ስላላይዝነው እጅግ ያሳስበኛል። እረፍትም ይነሳኛል። ድርድር እምታጣው ነገር ብቻ ሳይሆን እምታተርፍበትም ነገር ይኖራል። በአሉታዊ ክስተት ውስጥም፤ በድክመት ውስጥም መማርም፤ ማትረፍም ይቻላል። በምህረት፤ በይቅርታም እዮራዊ በረከት አለበት። እግዚአብሄር በፈቃዱ ውስጥ ማስገዛት ከተቻለ።
እርግጥ ነው ማመን አለመቻል የተገባ ነው ብዬ አስባለሁኝ። አብይዝም አፈጣጠሩም፤ አካሄዱም #አሳቻ ስለሆነ።
የአማራ ተጽእኖ ፈጣሪወች ቀጣይ ህይወት ላይ የአብይዝም ሁነት በአለም አቀፍ ውል ካልተያዘ አሳቻ ነው። እራሱ ቤተሰብም ቢሆን አስተማማኝ አይደለም። ህክምና ሂዶ የተመለሰ፤ ተኝቶ የሚነሳ አላዬነምና። ብዙ በጣም ብዙ የማናውቃቸው የምንጠራ ተግባራት በበቀል ተከውነዋል። ግን "እንቅልፍ ተፈርቶ ሳይተኛ" እንደሚባለው …… ሊሆን አይገባም። በአብይዝም እጅ የሚገኙ፤ የታገቱ፤ የተሰወሩ፤ የታሰሩ ወገኖቻችን ህይወትን ማትረፍ #ብልህነትም ነው። "ድርድር" "እርባና ቢስ፤ ቁምነገር የሌለው" አይደለም። ድርድር ሰውን፤ መኖርን፤ ህልውና፤ መንፈስን የሚታደግ ቅዱስ ክንውን ነው። ሊፈራም፤ ሊሸሽም አይገባም።
ድርድር ብልሆች በፀሎት በድዋ ከያዙት ለስኬት የሚያበቃ ነው። ድርድር የእውቀት ዘርፍ ነው። ድርድር የምህረት፤ የእርቅ ድልድይም ነው። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማልዱን የምንለው ቅዱሳንን፤ ሰማእታትን፤ ነብያትን እኮ እርቅ፤ ምህረት፤ ይፍታህ ሽተን ነው። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የቃልኪዳን ህሊና ናት።
በዬትኛውም የኑሮ መስክም ድርድር ውል፤ ስምምነት እኮ መኖርን የሚቀባ ነው። ጋብቻ የትውልድ መሠረት ነው። የውል የድርድር ውጤት ነው። ቀለበት ምንድን ነው? ተክሊልስ???? ድርድር ቃሉ እራሱ ቃለ ወንጌል ነው - ለእኔ። አጤ ድርድር ሊፈራ፤ ሊጣጥል፤ ሊሸሽ አይገባም። ፈጣሪን // አላህን አስቀድሞ፤ አመክንዮዊ የመደራደሪያ ነጥቦችን በማስተዋል አዘጋጅቶ፤ ትርፍ እና ኪሳራውን መዝኖ፤ ኪሳራንም መዝኖ - ኪሳራንም ለመቀበል አቅዶ እና ወስኖ፤ እማኞችን በሚገባ አጥንቶ ፍላጎቱን ሰይሞ - ለእኔ አገረ ሲዊዲን ለአማራ ህዝብ ችግር የቀረበ ህሊና እንዳለው አስባለሁኝ፤ ሊሆን የሚገባውን ደርዝ ባለው ሁኔታ ከርክሞ እና አዘጋጅቶ፤ በርን ሳይዘጉ ወደ መላ መቅረብ የማስተዋል፤ የብልህነት ልኬታ እንጅ ቂልነትም መሸነፍም አይደለም።
መሬት ላይ፤ ቋያ ላይ የሚገኘው ህዝባችን፤ በአብይዝም እጅ ውስጥ የሚገኙ ሺ እስረኞች፤ የታገቱ፤ የተሰወሩ፤ በክልሉ እና ከክልሉ ውጭ የሚኖሩ ወገኖቻችን የደረሰባቸውን፤ የሚደርስባቸውን ሰቆቃ፤ ጭንቀት፤ ስቃይ፤ ስጋት ሁሉንም በተደሞ መርምሮ የሚያዋጣውን መስመር ዘግቶ ሳይሆን ህሊናን ከፍቶ ማሰብ፤ ማንሰላሰል፤ መመካከር ይጠይቃል።
ከ30 -50 ሚሊዮን የሚገመትን ህዝብ ህይወት ለመወሰን " ድርድር " "ከቁብ አይቆጠረም፦ እርባና ቢስ ነው" የሚያዋጣ መንገድ አይመስለኝም። ለእኔ ድርድር ህይወትን የሚያሰክን፤ ማስተዋልን የሚያጎናጽፍ ሁለገብ ኢሹ ነው። ድርድር በማህበራዊ ኑሮ፤ በፖለቲካ ዘርፍ፤ በሃይማኖታዊ አመክንዮም፦ በኢኮኖሚያዊ ግንኙነት፤ በምህንድስና ህይወትም አወንታዊ፤ ጤናማ፤ ችግር ፈች፤ ለችግር ደራሽ፤ የስኬት መሳሪያ፤ የሰላም ድልድይም #ካፒቴን ነው።
ስለሆነም መሬት ላይ ስደት፤ ምቾት ሳያምራቸው ቁሩንም፤ ሃሩሩንም፤ ግርማ ሌሊቱንም፤ ቸነፈሩንም፤ ባሩዱንም፤ አውሎውንም፤ ድሮኑንም፤ መቃለሉንም፤ ዛቻውንም፤ መጣጣሉንም፤ ርሃብ - ጥማቱንም፤ መገፋቱንም ችላችሁ ሌት እና ቀን የምትባትሉ የፋኖ ትጉኃን ሁሉ በአደብ፤ በጥሞና፤ በአርምሞ ሁናችሁ ስለድርድር ደግማችሁ ደጋግማችሁ ልታስቡበት ይገባል ባይ ነኝ። ሳታቋርጡ እሰቡበት። ምከሩበት ፀልዩበት። ድዋም ያዙበት።
ድርድርን በሚመለከት ገዢው #አብይዝም በስማበለው፤ ለጭዋታ ማሟያ የሚደርገውን ልግጫም ሊያቆም ይገባል። በስሚስሚ፦ ለእግረ መንገድ ማሟያ ከሚናገረው በስተቀር ዕውቅና ያለው ኦፊሻል #አዋጅ ሲያውጅ አልሰማሁም። ሰላም ፈላጊነት በእልህ አይደለም። በዛቻም ሰላም አይመጣም። ያከበረን ህዝብ አክብሮ ዝቅ ብሎ በትህትና መፈፀም ይገባል። መንግሥት የህዝብ አለቃ አይደለም። የህዝብ አለቃ አምላኩ አላሁ ብቻ ነው። የመንግስት አለቃ ህዝብ ነው።
የአማራን ህዝብ ሁለገብ ክህሎት፤ ተመክሮ፤ ጥረት እና ስኬት አቃሎ ማዬት አይገባም። ስለማንኛውም የነገረ አማራ ጉዳይ የማዬው ሁሉ በንቀት እና በበቀል የታጨቀ ነው። ለዚህ ሁሉ ክብር ያበቃ የአማራ ሙሉ ድምጽ ነው። ለውጩው ይሁንታም የአማራ ልጆች የእጅ ስራ ነው። አማራን በዚህ ልክ መቅጣት ማስፈለጉ ምንጩ የማንነት ቀውስ ይመስለኛል። እንጂማ የአከበረን፤ የከበከበን ህዝብ በዚህ ልክ እንዴት ይናቃል? እንደምንስ በበቀል መሽቶ እስኪነጋ ይጠቃል?
ንቀቱን የሚያካክስ አቅም ግን ፋኖ እንዳለው በውስጠ ታዋቂነት የተያዘ ነው። ለዚህም ነው የሰሞኑ የደራን አሰቃቂ ጭካኔ ከፋኖ ጋር በማጋባት ያን ያህል ብሄራዊ ንቅናቄ እዬተደረገበት የሚገኘው።
የሆነ ሆኖ ፋኖ ለአንደበቱ ወጥነት ብቻ ሳይሆን በቃል አጠቃቀም ብርቱ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል። የትኛውም በውጭም በአገር ውስጥም የሚደረጉ ንግግሮች መስዋእትነቱ ጋር የሚመጥኑ ዲስፕሊን ቢሆኑ ምኞቴ ነው። በእጅጉ ለድርድር የሚረዳው ቁም ነገር የአንደበት ጥንቁቁነት ነው። ጉዳይን ብቻ ማስቀደም ይገባል። ትርፍ ነገር ምን ይጠቅማል???
በሌላ በኩል ከጥር 2025 ጀምሮ ብዙ የፖለቲካ ክስተቶች በአለም ደረጃ ይቀየራሉ። የአለም መሪ ሃይል አሜሪካ፤ አራጊ ፈጣሪ አሜሪካ በአዲስ ምዕራፍ አዲስ ሽግግር ያደርጋሉ። በዚህ የሽግግር ጊዜ #በውስጥ ፖለቲካ አትኩሮት ይኖራል። የእስራኤል እና የጋዛ፤ የራሽያ እና ዩክሬንወኔቶ ፍጥጫም ሰከንዶች የሚያስተዳድሩት ይሆናል።
በዚህ ውስጥ አፍሪካ፤ የአፍሪካ ቀንድ፤ ኢትዮጵያ፤ አማራ ለተከበሩ ፕሬዚዳንት ዶናል ትራንፕ ካቢኔት አጀንዳነቱ ምን ያህል ሊሆን ይችላል? የመጪው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ፖሊሲ ሰላም - ተኮር፤ ድርድር - ተኮር፤ ኢኮኖሚን በአትራፊ ፕሮጀክት ላይ ማሰማራት መርሁ ያደረገ ይመስለኛል። ድርድር፤ ስምምነት ቁምነገርም መሪ የሚሆኑበት፤ ሰላም ለሰው ልጆ የመኖር ትንፋሽ እንዲሆን፤ የኢኮኖሚ ብክነት ለጦርነት የማዋል ጉዳይ በቅጡ የሚያዝበት ይመስለኛል - አያያዙ።
ስለዚህ ትንታጉ ፋኖ ትጋቱን በስኬት ለመቋጨት ወደ እማ እና አባ ዊዝደም ማምራት ያለበት ይመስለኛል። አንድ ቀንን፤ አንድን ሰዓት፤ አንድን ሰከንድ ማትረፍ ብልህነት፤ የማስተዋል ልኬታ እንጅ ቂልነት አይደለም።
በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ድርድር ለፍላጎት ቅርብ ነው። ጥያቄወቹ ተጨባጭ ሁኔታወችን ያጠኑ፤ ለተግባራዊነቱ እክልን መመከት የሚችሉ አቅም ያላቸው፤ በቀላል ቋንቋ፥ ቁልጭ ብለው የሚታዩ፦ ያልንተንዛዙ በአጫጭር አረፍተ ነገሮች የተኮለሙ፤ ሞናትነስ ያልሆኑ፤ በእያንዳንዱ የአማራ ህዝብ ህሊና ሰሌዳ ሊጠኑ፤ ሊያዙ የሚችሉ ያላበጡ ወይ ያልተንኳሰሱ፤ ያልተንጠራሩ ወይንም ያልተነፈሱ ሳይሆኑ የአማራ ህዝብን የሥርአተ መንግስት ጥበብ የተላበሱ ብልህ፤ ልብ የሚገዙ፤ መንፈስን እንደማግኔት የሚስቡ፤ የሚያቀራርቡ ለቅንነት የቀረቡ ከማንኛውም ትርፍ ነገር የታቀቡ፤ እንዲሆኑ በጥንቃቄ ሊነደፋ ይገባል። ተደጋግመው ሊታሹ፤ ሊታረመሙም ይገባል። ምንም አይነት የፊደላት ግድፈት ሊኖርባቸው አይገባም።
ከዛ በፊት ግን ምንም እንኳን ጦርነት ላይ ብትሆኑም ጥሞናን ማስቀደም፤ የፈጣሪ ፈቃድን መጠዬቅ ያስፈልግ ይመስለኛል።ተወደደም ተጠላም ብቻችን ልናሳካ የምንችለው ጉዳይ ቋት አይገፋም። በዘመነ ግሎባላይዜሽን እኛም አለንበት። ዘመኑ ማጥናት፤ ለዘመኑ የሚመጥን የፍላጎት አቅጣጫ መንደፍ በእጅጉ ያስፈልጋል።
በሌላ በኩል እኔ በመደበኛ የፖለቲካ ድርጅት ሰራተኛነት ሰርቻለሁኝ። ኮርሶች፤ ሰሚናሮች፤ ፓናል ዲስከሽኖችን፤ ጉባኤወችን የተለያዩ ተሳትፌያለሁ። ብሄራዊም ከዚህም የዘለለ። በጣምም አንባቢ ነበርኩኝ። በማውቀው ልክ ከቅንጣቱ እስከ ገዘፈው የተቋማት ምስረታ "ዲሴንትራላይዝድ" ሆኖ የሚወጠን ነገር አላውቅም።
ቢወጠንም የአናርኪዝም ሰርግ እና መልስ ይሆናል። ትውልድም፤ አገርም፤ ትውፊትም፤ አደራም ሁሉም የአናርኪዚም ወረራ ባለድርሻ ይሆናሉ። በነበርም ጨንግፈው ይጠናቀቃሉ።
ለዬትኛውም ሁኔታ "ዲሴንትራይዜሽን" ሃሳቡ እራሱ አፍራሽ ነው። ፋኖ እኮ በጥንት - ጥንት ዘመን እራሱን ለግዳጅ ሲያሰማራ በጎበዝ አለቃ ነው። የቅርቡን የሀምሌ 5ቱን የአማራ ህዝባውዊ አብዮት እኮ ፋኖ ሲደርስለት አርበኛ ፋኖ ጎቤ የጎበዝ አለቃ ነበር። ይህ ያዬነው የተመለከትነው ሃቅ ነበር። አይደል???
ዕውነቱ ፋክቱ በባህላችን ይሁንታ የሰመረ የሰከነ ትውፊት ነው። እኛ በኋላው ተፈጥረን ተፈጥሮውን በርዘን እንነሳ ተብሎ መታሰቡ ግርም ብሎኛል። እኛ ያበጀነው አይደለም ፋኖነት። የእኛ የፈጠራ የእጅ ስራ ውጤት አይደለም ፋኖነት። የእኛውማ ሙሉ 60 ዓመት ኢትዮጵያን የደም መሬት አድርጎ አፍሶ ሲለቅም፤ ለቅሞ ሲያፈስ ዘመን በዬዘመኑ በምርኩዝ።
ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት የአማራ ፋኖን አቅም ለመጠቀም ሲያማትር ሙሉ ህጉን ተቀብሎ ሊሆን ይገባል። ህጉ ፋኖ በጎበዝ አለቃ ሴንትራላይዝድ ሆኖ መሬት ላይ የሚፈጠር የአማራ ህዝብ የአደጋ ጊዜ ተጠሪ ነው ፋኖ። የቀይ የደም ሴል፤ አናትም እናቱ ነው ለአማራ ህዝብ ፋኖ። ፋኖ - ያወቀ- የተደራጄ - መሪ ያለው። ዓላማ እና ግብ ያለው። በራሱ በጀት የሚተዳደር የፈቃድ ሙያ ነው ፋኖነት።
የሱዳንን ደንበር የትኛው የኢትዮጵያ ሠራዊት ነው አስከብሮ ዘመን ከዘመን ያቆዬው? በጀት ተመድቦለት ነበርን? ስማቸው የጀግኖቹ ይታወቃልን??? ይህ ተግባር የትውፊቱ አካል ነው ይቀጥላል። የማንንም ፈቃድ አይጠይቅም። ፋቲክም ስንቅም ትጥቅም ጠይቆ አያውቅም የአገሬ ገራገር ገበሬ በፋኖነቱ። ድረስ ሲባልም ሞፈሩን ሰቅሎ፤ ትዳሩን በትኖ ፈጥኖ ይደርሳል ያ ሊቀ ትጉሃን አራሽ ገበሬ።
ወደ ውስጥ ማዬት። መስከን። መርጋት ያስፈልጋል። ይህ ግሎባል ንቅናቄ በስኬት እንዲጠናቀቅ ባህሉን ተቀብለው አብረው እዬተጉ የሚገኙ ሙሁራን ስኬቱን በጥበብ ሊቋጩት ይገባል። በበሳል ስኩን ፍላጎቶች የተገነባ የድርድር አመክንዮ ማሰናዳት ቀዳሚው ተግባር ሊሆን ይገባል። ፋኖ መንፈሱ አንድ ነው። መነሻው የቀደመው ይተባኃል ነው እና። ለዚህ ደግሞ የተደራጄ አቅም መሆን በጉዳዩ ላይ በቀጥታ የሚሳተፋ ወገኖች ጉዳይ ይመስለኛል።
ስለ ሎቢ ሲነሳ እሰማለሁኝ። ድምፃቸውን አጥፍተው የሚተጉ ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን በወዘተረፈ የባለቤትነት ግብግብ ውስጥ ግን አቅም ማዋጣት? ሌላም እንደ አለፋት ጊዚያት ቀጣዩ ዘመንም ቀላል አይሆንም። ይህም ብቻ አይደለም ድካም ሲደፋ እንጂ ሲበረክት ስላልታዬ የዚህም ስጋት ያለባቸው ወገኖች ይኖራሉ። አንድ ሰው አፋጦ ጠይቆኛል። ፋኖ የማን ነው ብሎ?
#ክወና።
በአጭር የሰማሁት አብይዝም አማራ ክልልን ለቆ ሊወጣ ይችላል የሚል ነው። አሳቸነትን ማቀድ አይቻልም። የአማራን ማእከል ሊያዞር ይችላል። በጀት ሊያግድ ይችላል። የደረቅ ወንጀለኞችን ከእስር ሊለቅ ይችላል። ማፍያም አደራጅቶ ሊያሰማራ ይችላል። መዳህኒት ሊቆም ይችላል። መጓጓዣ የየብስ፤ የባህር የአዬርም ሊቋረጥ ይችላል። የፈንጅ የቦንብ ቀበራም ሊኖር ይችላል። አሳቻነት አሳቻ ነውና።
ይህን ኃላፊነት ለመወጣት አሁን ያለው የፋኖ አቅም ይችላል ወይ?
የትኛው አገር መንግሥትስ እርዳታ በአስተማማኝ ፋኖ አለው?
የመንግስት ተቋማት ሰራተኞች እንዴት ሊያስተዳድር ታስቧል?
ግንባር ውጊያ እና ማስተዳደር ኃላፊነትን ወስዶ መንግሥትነት?
ደግማችሁ 100 ጊዜ መትሩት። ሌሊትም ተኝታችሁ እሰቡት። በአንድ ማዕከል ሁሉን የአማራ ክልል አማክሎ መምራት የሚችል የሊቃናት እውቀት ሊኖር ይችላል። ግን ሂደት ጊዜ ይጠይቃል። እኔ ይህንን ውሳኔ በጥልቀት ብታስቡበት ምርጫዬ ነው። አቅማችሁን እምታውቁ እናንተው ናችሁ እና።
ሰሞኑን ፕ/ ዶር ብርሃኑ ነጋ ከሉአላዊ ሚዲያ ጋር በነበራቸው ቆይታ የድሮ ትግላቸውን የኮንፒተር ሲሉት አድምጫለሁ። ቀጥለውም መንግስት መሆን ቃናውን አብራርተዋል። ይህ የአቋም ለውጥ ኃላፊነት ላይ ሆነው ስላዩት በውሳኔው ውስጥ ቤተኛ መሆናቸው እና ተጠያቂነትን ያብራሩበት አመክንዮ ነው። ይህ ነጥብ በራሱ በምልሰት ብክነታችን እና ስኬቱን መመዘን የሚያስችል ይመስለኛል። ወደፊትም በረጋ እና በሰከነ ሁኔታ በእጅ የገባን ገጠመኝ በቅጡ ለማስተዳደር የሚቻልበት ሁነትን ያመለክታል። አላስፈላጊ የወል ድካም አድራሻውን አውቆ ይነሳ የሚል እድምታም ያለው ይመስለኛል።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ደህና ዋሉልኝ።
ደህናም አምሹልኝ። ኑሩልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
23/11/2024
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ድርድር የሰላም መቅኖ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ