#ብክነት ካለ #ስኬት፦ ግን #በማገዶነት። የኢህአፓ እስረኞች ፎቶውን ብሎጌ ላይ አይፈቀድም። ግን ፌስቡኬ ላይ አለ።
"የቤትህ ቅናት በላኝ። "
የመዋለ ዕድሜ የኢህአፓ አባላት በአገራቸው ግዞተኛ ናቸው። ማፍቀር፤ መዳር - መኳል፤ መውለድ - መሳም፤ ዘር መተካት፦ ዓይንን በአይን የማዬት ሃሴት ተፈጥሯዊ ሂደቱም እስረኛ ነው። የቤተሰብ፦ የማህበራዊ ኑሮም፥ ጤናማ ግንኙነት ድፍርስ ወይ ያጎረፈ፦ ያጎፈረም ነው። በፖለቲካ የሚሳተፍ ትጉህ ሁልጊዜም ይገለላል ጥቃትም ይፈፀምበታል። ከዚህ አስፈሪ ሂደት ነገ ትውልዱ ምን ይማርበታል???
እነኝህ ምንዱባን በዘመነ ደርግ የኢህአፓ ታጋይ አፍለኛ ወጣት የነበሩ ይመስለኛል። #ሴት እህታችንም አለችበት። በዛ ዘመን ሴቶች ደፍረው ወደ ትግል መግባታቸው በራሱ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ #ጌጥ እንጅ እንደ ዕዳ ባልታዬም ነበር። ህሊና ቢኖር። አሳረኞቹ በዘመነ ህወሃት ታሠሩ፤ በዘመነ አብይዝም እስሩ ቀጠለ። ግዞተኛ በባዕት።
እኔ የታገልኩት የፖለቲካ እስረኛ #የክት እና #የዘወትር እስረኛ ዘመን የሰጠው ገዢ እንዲኖረው አልነበረም። የሚገርመው በዘመነ ህወሃት ከነበረው በናረ ሁኔታ በዘመነ አብይ የፖለቲካ እስረኛ ኢትዮጵያ ውስጥ አለ ከምል ተጥለቅልቋል ብል ይሻላል። ለዛውም በበቀል የተቁላላ፤ በቅሬታ ክምችት የተቀመመ። የሚገርመው የዚህኛው የጭካኔው ስታይሊንግ ከነበሩት ገዢወች የተለዬ፤ ያልተለመደ መሆኑ ነው።
በዚህ ዘመን የሚያስደነግጡ የአረማዊ ክንወኖች ያለፋታ ህሊናችን እንዲሸከም መገደዱ ስለ ሰብ ይመለከተኛል የሚል ሁሉ አብሮ መንፈሱም፤ ጤናውም እንዲደቅ ተደርጓል። በምንኖርበት የስደት አገርም ትናንትም ያሳድዱናል፤ ዛሬም ያሳድዱናል። ለምን? ያው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉዞው በማሳደድ የተመሰረተ ስለሆነ።
አቅም ያለው ፖለቲካ እና ፖለቲካ ሃሳቡን አቅንቶ የሃሳብ ፍትጊ ማድረግ ይገባ በነበረ። ግን የአቅም ወኔ ከዬት? እንዴትስ? ይህ የሚሆነው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅት አመሰራረት በማንነት ቀውስ ላይ የተገነባ ስለሆነ ይመስለኛል። ዕድሉም ንጥቂያ እና ዘረፋ የረበበት ነው።
የሆነ ሆኖ የኢህአፓ አንዱ አካል አገር ውስጥ #ህጋዊ የፖለቲካ ድርጅት ነው። ይሁን እንጂ አገር ውስጥ ያለው ኢህአፓ ስለ እነዚህ የተረሱ፤ ጭራሽም የማይታወሱ እስረኞቹ ምን እንደሚል አላውቅም። ሄዶስ እስር ቤት በአካል ተገኝቶ ይጠይቃቸው ይሆን? አጀንዳውስ ናቸውን?
ለኢህአፓ የትግል ጓዳዊነት ብርቱ ቃልኪዳን ነው ሲባል እሰማ ነበር። ኢህአፓ ይህን በጎ ባህሉን አስቀጥሏል ወይንስ አቋርጧል ወይ? ከሆነስ ዕድል የሸፈተባቸው በህይወት እያሉ ለካቴና የውርስ ቅብብል የተፈፀመባቸውን እነኝህን የግፍ #እስረኞች ጉዳይ እንደምን ይዞታል? ቤተሰቦቻቸውስ በምን ሁኔታ ይገኙ ይሆን? ሁሉም ከእናትም ከአባትም የተፈጠረ ነውና።
በሌላ በኩል እነኝህን የኢህአፓ መንፈሶች በእስራታቸው እንዲቀጥሉ ያደረገው ለአብይዝም አገዛዝ ደግሞ - አንድ በኽረ ጥያቄ አለኝ። ዱር ቤቴ ብለው የፖለቲካ የፊደል ገበታቸው ኢህአፓ የነበሩትን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን የትምህርት ሚኒስተር ሚኒስተር አድርጎ በመሾም፤ የካቢኔውም አባል አድርጎ እያሰራቸው ይገኛል።
እርግጥ ነው ፕሮፌሰር ዶር ብርሃኑ ነጋ ኢህአፓን ከተው በኋላ ሌላ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ቢሰሩም (ቅንጅት፤ አርበኞች ግንቦት 7፥ አገራዊ ንቅናቄም)፤ የራሳቸውን ቀስተዳመናን እና ግንቦት 7 #መስራች ቢሆኑም መነሻቸው ግን ኢህአፓ ነው። ለምን ተሾሙ እያልኩ አይደለም። ኧረ ምን በወጣኝ።
ዕድላቸውን ሳያፈሱ በመጠቀማቸውም ላይ ምንም ብዬ አላውቅም። እንዲያውም በሰሞኑ በቃለ - ምልልሳቸው ስረዳ የቀደመው ትግላቸውን የኮንፒተር፤ የአሁኑን የመንግሥታዊ ኃላፊነት እና ተጠያቂነትን የማግስትን ቁምነገርነት ያመሳጠረ እንደሆን ሲገልፁ አዳምጫለሁኝ።
ጉዳዩን እዚህ ላይ ያነሳሁት ህሊናዬን የሚሞግተኝ ቁልፍ አመክንዮ ስላለም ነው። ለአንዱ የኢህአፓ አካል ህጋዊ ዕውቅና የሰጠ አገዛዝ፤ ሌላውን ቀደምት አባል ከሾመ፤ የኢህፓ እስረኞችን ለከእስር ለመፍታት ለምን አቃተው???
የኢህአፓ እስረኞች ዘመናቸውን ላልተሳካ የፍትህ፤ የነፃነት፤ የዲሞክራሲ ጥያቄ ወጣትነታቸውን ሁሉ በትግል፤ ጎልማሳነታቸውን በካቴና፦ ምን አልባትም የአዛውንትነት ተስፋቸውም በካቴና መቀጠሉ፦ አሳዛኙ የትውልድ ጠቀራዊ ታሪክ ስለሆነ የኢትዮጵያ አገዛዝ የልጅ እና የእንጀራ ልጅ፤ የቤት እና የእዳሬ ልጅ የዘበጠ ሚዛኑ ትውልድን እንደምን ሊያስተምር ይችላል ነው ጉዳዬ? እነኝህ ባተሌወች፤ ብክነታቸው ለስኬት ባይበቃም ቀጣይ ማገዶነታቸው ለምን ነው ወሳኙ ጉዳዬ።
ቀድሞ ነገር ስሙ ብቻ ያለው የዕንባ ጠባቂ ተቋም፤ የኢትዮጵያ የሰባዕዊ መብት ኮሚሽን፤ ኢሰመጉም፤ ሌሎችም በዘርፋ የሚተጉ ሁሉ ስለ እነዚህ በቁማቸው እዬተቀጡ ላሉ ነፍሶች ምን ይላሉ?
ሁልጊዜ አስባቸዋለሁኝ። በአገራቸው፤ በባእታቸው፤ በመሬታቸው የሙሉ ዕድሜ ግዞተኞች ዬከፈሉት መስዋእትነት፤ በመክፈል ላይ ያሉት መስዋዕትነት እንዴት ትውልዱ ሊመዝነው እንደሚችለውም አላውቀውም። ሊመሰገኑ ቀርቶ ተወቃሽም ሊሆኑ ይችላሉ። ይህን ማድመጥ የማይፈልግም ይኖራል። በሌላ በኩል ግን ከእነሱ ጋር ለትግል ጫካ የወጡ የተሳካላቸውም ይኖሩ ይሆናል።
ግን የተሳካላቸው ወደ አገር ጎራ ሲሉ ይጠይቋቸው ይሆን??? የተሰውት አጽምስ በህይወት እያሉ ግን ግዞት ላይ የሚገኙት ጓዶቻቸውን እንደምን በአፀደ ነፍስ ያስቧቸው ይሆን???
እነኝህ እስረኞች ዕድሜያቸው ተዘርፏል። ቢያንስ #ሚኒስተርነት ቀርቶባቸው፦ ሹመቱ ቀርቶባቸው፤ በምርጫም መፎካከሩ ቀርቶባቸው፤ በሚዲያም ለመሞገት በሃሳብ ዕድሉን ባያገኙም፤ መኖራቸው አንፃራዊ የነፃነት ፈቃድ ሊሰጠው አለመቻሉ በኢትዮጵያ ፖለቲካ የወጣትነት ህይወት እንዴት #አስፈሪ እንደሆነ ማገናዘቢያ ይመስለኛል።
ለመሆኑ የኢትዮጵያ መንግስት በትምህርት ካሪክለሙ ላይ #የፖለቲካ #ሳይንስን ማስገባቱ ትርፋ ምን ይሆን? የፖለቲካ ታጋይነት እንዲህ መቀጣጫ ከሆነ? እንዲህ ማስፈራሪያ ከሆነ? በገፍ ወደ እስር የሚዳረጉት ወጣት እና ጎልማሳ የአማራ ፖለቲከኞችም የአብይዝም የመጀመሪያ ረድፍ ተጠቂነታቸው ለኢትዮጵያ ፖለቲካ የኪሳራ ሞተርም ይመስለኛል። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባህልሆደ ሰፊነት ሆነ አሳታፊነት #ዝግ ነው። #ድንብልብልም።
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ተሳትፎ የፍርሃት፤ የራድ፤ የጭንቅ እና የስጋት፦ እስከ ቤተሰብ የመሳደድም #ተጋባዥነት ነው። የፖለቲካ ተሳትፎ በኢትዮጵያ ወጣትነቱ ሆነ ጉልምስናው፤ ጉልምስናው ሆነ አዛውንትነቱ #በትሬኮላታ ሽቦ የታጠረ ነው። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ስለ ሰው፤ ስለ ተፈጥሮ አመራር አስተዳደር ስልጡን ማድረግ ሳይንስ ሳይሆን የበቀል፤ የሴራ ማወራረጃ #ፋስም ሆኖ ነው የኖረው። ዛሬም እንዲሁ። ከዋናው አውራው ድርጅት ገጀሞ በላይ፤ የደጋፊው ዘመቻ ምጣት ነው።
ለዚህም ነው እኔ የፖለቲካ ድርጅት እና ኢትዮጵያ አልተመጣጠኑም። የፖለቲካ ድርጅት ባህል ለኢትዮጵያ ተፈጥሮ ግጥሙ አይደለም። የፖለቲካ ድርጅት አደረጃጀት፤ መርህና አፈፃፀሙ ማህፀን እና አብራክን ቄራ የሚያደርግም ነው። ስለሆነም ኢትዮጵያ ከፖለቲካ ድርጅት ውጪ በራሷ በኢትዮጵንያኒዝም ፍልስፍና ሰዋዊነት፤ ተፈጥሯዊነት የሰፈነበት ቲም ቢመራት የሚል ጽኑ እምነት ያለኝ።
በፖለቲካ ድርጅት ህይወትን አሰልጥኖ፤ በፍቅር ተፎካክሮ፤ አንተ ትብስ፤ አንቺ ትብስ ተባብሎ፤ በርጉው ቤተሰባዊ ይትባህላችን መኖርን ማስጠበብ ፈጽሞ አላወቅንበትም። ሁሉም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅት አድማጭ አይደለም። ቅን አይደለም። አወንታዊ አይደለም። የሚበልጠውን የሚፈቅድም አይደለም። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅት የአፈጣጠር ሩሁ ከፖለቲካል ሳይንስ ዊዝደም ሥርዓቱም አልገዛነም፤ ሊገዛንም አልፈቀድንም። ሁልጊዜ የሰው ልጅ ማገዶ??? ለምን? ስንቱን #አጣን?
#ስኬት ከመታለሙ በፊት #ስክነት ይታቀድ። #ስክነት ከመታለሙ በፊትም #ጥሞና ይታቀድ። የእኛ ኢትዮጵንያኒዝም ከፍልስፍናም፤ ከሳይንስም በላይ ዩንቨርስ ነው። ቅንጣቷ የኢትዮጵያ ዕፅ በትርጉም እና በሚስጢር የከበረ ነው። ኢትዮጵያኒዝም በሚስጥራት ሥህን የከበረ ማንነት ነው። #ግኖች ግን ራሳችን አፍሰን፤ እራሳችን ነቅለን በውራጅ ርዮት መዳከሩን ተግ ብሎ ማሰብ ይገባ ይመስለኛል።
የሆነ ሆኖ አሁንም በአዲሱ የምርጫ ዘመን ነጣላም፤ ድርብም አዳዲስ የፖለቲካ ድርጅቶች ምስረታ፦ ህብረት ማዬታችን አይቀሬ ነው። ወጣቶች ሆይ! እሰቡበት። እነኝህን የዘመን እስረኞች እሰቧቸው። ተማሩባቸውም። አስተዋሽ አልቦሽ ናቸው። በእኔ የወጣትነት ዘመን ዝና፤ ውዳሴ፤ ጭብጨባ አናውቀውም። የምናውቀው ለተሰለፍንበት መስክ በትጋት ሌት ተቀን መባተል ብቻ።
እኔ የራሴን መርኽ ልግለጥላችሁ። አንድ ሰው ሲሆን ከሚከፈለው በላይ መስራት፤ ያን ባይችል የሚመጥን ስራ መስራት ግዴታው ነው ብዬ አምናለሁኝ። በአገርም፤ በስደትም ስራ አገሬ ነው። መስራት አእምሮን ጤነኛ ያደርጋል። አቅም አቅምን ያድሳልና።
ግን እንዴት ናችሁ ውድ ቤተሰቦቼ?
ቸር አስበን፦ ቸር እንሁን።
ቅን አስበን፦ ቀና እንሁን።
ኑሩልኝ። አሜን።
ደህና ሁኑልኝም። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
29/11/2024
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ