#አሜን። ዓለም የሰላም አንባ ትሆን ዘንድ የአሜሪካን ግሎባል ምርጫ እግዚአብሄር በሰላም ያስፈጽመው። አሜን።

 

#አሜን። ዓለም የሰላም አንባ ትሆን ዘንድ የአሜሪካን ግሎባል ምርጫ እግዚአብሄር በሰላም ያስፈጽመው። አሜን።
 
"አድርገህልኛል እና ለዘላለም አመሰግንኃለሁ፦
በቅዱሳንህም ዘንድ፦ መልካም ነውና ስምህን ተስፋ አደርጋለሁ "
(መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ፶፩ ቁጥር፱)
 
1) እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ መልዕክት ይዞ ይወለዳል።
2) እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ ጥሪ ይዞ ይወለዳል።
3) እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ መክሊት ወይንም ስጦታ ይዞ ይወለዳል።
የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ወ/ ሮ ካሚላ ሃሪስ ( ኮሞላ ሃሪስም) ይህን አጣምረው ተወልደዋል ብዬ አምናለሁኝ። በእኛ አገር አባባል "ልጅ እና ጢስ መውጫው አይታወቅም" እንዲሉ። 
 
ጤና ይስጥልኝ የማከብራችሁ ውድ ቤተሰቦቼ? እንዴት ሰነበታችሁልኝ? በበዛ #አርምሞ እና በሰከነ #ጥሞና ልንከታተለው የሚገባው ለእኔ ዓለም ዓቀፋ የኢትዮጵያ፤ የአፍሪካ ቀንድ፤ የመካከለኛው ምስራቅ አፍሪካ፤ የእስያ፥ የቻይና እና የታይዋን፤ የአህጉራችን የአፍሪካ፤ የእስራኤል- የጋዛ፤ የሊባኖስ - የኢራን፤ የራሽያ - የዩክሬን፤ የአውሮፓ ህብረት፤ የአፍሪካ ህብረት ጉዳይ፦ የአሜሪካዊው የ2024 የምርጫ ሂደት ጋር ህሊና ላለው የሰው ልጅ ሁሉ መንፈስን አንቅቶ ሊከታተለው የሚገባ ጉልላታዊ #ፒላር ጉዳይ ይመስለኛል።
የአሜሪካ ጠቅላላ የታች እስከ ላይ የሚካሄደው ሥልጡን፤ የተደራጀ፤ በቅጡ ኮኦርድኔት የተደረገው የምርጫ ሂደት ጉዳዩ ለእኔ #ቅንጦት አይደለም። ብዙ ግሎባል የህይወት፤ የተፈጥሮ መስኮች ላይ ተጽዕኖም አሳዳሪ ነው። 
 
ጉዳዩ #የጫጉላ የሙሽርነት ሽርሽር አይደለም። ኢትዮጵያ በዴሞክራሲ እጦት ሙሉ 50 ዓመታት እንደምን ትውልዷ እዬታጨደ እንዳለ፤ ምን ያህል የኢትዮጵያ እናቶች በዕንባ ኖረው፦ በዕንባ እንዳለፋ፥ አሁንም ማቆሜያ በሌለው ዕንባ ውስጥ የሚገኘው የአማራ ህዝብ ሰቆቃም፤ በአገሩ፤ በባዕቱ በድሮን ሰርክ እዬተጨፈጨፈ ያለበት ሁኔታ መኖሩ በስማ በለው ሳይሆን የበሞቴ ልዕልቴ #እናቴ የተቀበለችው የሙሉ ዕድሜ መከራ፤ መከራዋ እልባት ሳያገኝ በእኔ ምክንያት ተሰቃይታ መንኩሳ፤ የምናፍቀውን ምንኩስናዋን ሳልዳስሰው በናፍቆት በመራራ እንደተሰነባበትን የ5 ዓመታቱ ጥልቅ የሃዘን ጊዜዬን አውቀዋለሁኝ።
 
ስለሆነም ለኢትዮጵያ እናቶች እንባ፤ እዬባሰ በመጣው የአማራ እናቶች ሰቅጣጭ የእንባም ዘመን ተግቼ መታገሌ የተገባ ነው ብዬ አስባለሁኝ። የህይወት ውድ ስጦታ እናት ናት። እናት የህይወት የመጀመሪያዋ ትምህርት ቤትም ናት። እናት የማህበራዊ ህይወትም #የፊደል ገበታ ናት። እናት መዋለ ዕድሜዋ በዕንባ ተጥለቅልቆ ማለፍ ሃዘኑ ጎምዛዛ ነው። ይህ የሆነው በዴሞክራሲ እጦት ነው። አብሶ ለዓለም እናቶች የዴሞክራሲ ስርዓት ልጆቻቸውን ከነጣቂ ጨካኝ ፖለቲከኞች የሚታደግላቸው ፍቱን ነው ብዬ አምናለሁኝ።
ኢትዮጵያም እናት ናት። 
 
እና ስለ እሷ ሁሉንም መቀበሌ ትክክለኛ ውሳኔ ነው ብዬ አምናለሁኝ። እናትን ማጣት ምንም ሊካካስለት የሚገባ ጉዳይ ባይሆንም። እጅግ ብደክምበት - ብጎዳበትም። ጤናዬንም #ወጣትነቴን - ብገብርበትም፤ እንዲሁም ቤተሰቦቼ የፖለቲካ ትጋቴን ባይወዱልኝም - ባይደግፋኝም። እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ #ጥሪ ይዞ ይወለዳል፤ እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ #መክሊት ይዞ ይወለዳል። እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ #መልዕክት ይዞ ይወለዳል እና እኔም በጥሪዬ፤ በመልእክቴ፤ በመልእክቴ ውስጥ እንዳለሁ ይሰማኛል።
በዚህ ሂደት በከፋኝ፤ በሚከፋኝ የኢትዮጵያ ብቅ በሚሉ አንቂ፤ አደራጅ፤ ፀሐፍት፤ የሚዲያ ባለሙያ በተለይ ለሴቶች አዳላላሁኝ አንስቶች አተኩሬ ስታገል በውነቱ የአሜሪካ #ዴሞክራቶች ላደረጉልኝ ትብብር ከልብ አመሰግናለሁኝ። አሜሪካ ይሁን አውሮፓ ህብረትም መንግሥታትም፦ በተለይ የጀርመኗ የቀድሟዋ ካንስለር ድንቋ ንግሥቴ ዶር አንጌላ ሜርክል እንዲሁም #ተመድ ዋናው ቢሮ ደብዳቤ ጽፌ መንፈሱ አንገቱን ደፍቶ አያውቅም። ፈጽሞ። ሰልጥነዋል ማለት ያንሳቸዋል። ለእኔ እንደ የፖለቲካ ጽድቅነት ነው የምቆጥረው። የርህርህናቸው ጥግ ስለጨበጥኩት፤ ስለዳሰስኩት ካለምንም ፕሮቶኮል፤ ካለምንም ደንበርም።
 
" አድርገህልኛል እና ለዘላለም አመሰግንሃለሁ። "
 
ከጠቀብኩት በላይ በአገሬ በኢትዮጵያ ካሉት ገዢም ይሁን አውራ፤ በአገር ውስጥ እና በውጭ ከሚኖሩት ይሁን ሌሎችም ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ይሁን #ሚዲያወች የማላገኘው ክብር እና ሞገስ እንዲሁም እርካታም፦ መጽናናትም፦ ስኬትም የማገኘው ትልቅ ህሊና እና ሩህሩህ በሆነው የዴሞክራቲክ ፓርቲ የቀደሙትም የአሁኖችም ተወካዮች፤ የተከበሩ የቀድሟዋ ክብርቷ #ልዕልቴ ቀዳሚት እመቤት ሚሼዬል ኦባማን ጨምሮ ለወቅቱ ትክክል እና ፈጣን የሆነ ምላሽ በመሰጠት ዴሞክራሲ፤ ነፃነት፤ ግሎባላይዜሽን፦ ሰዋዊነት፦ ተፈጥሯዊነት #በዕውን አይቸበታለሁኝ። ይህ ደግሞ #መሰጠትም መሰልጠንም ነው። 
 
አነሰች፤ ጠቆረች ሳይሉ ከመከፋቴ ጎን መቆም ለእኔ እግዜር በምድር ነው። በአገሬ ፖለቲከኞች እና ሚዲያወች ያለው ግለት እና በግሎባሉ የሌላ አገር ያልተወለዱን፤ ያልተዛመዱን እጅግ ታላላቅ የተከበሩ ድንቅ ፖለቲከኞች ለሰው ልጅ የሚሰጠው ዕውቅና ለእኔ #ታምርም #ትንግርትም ነው። እኔ ውዳሴ ከንቱነቱንም፤ የሚዲያ የፎቶ ሾፑንም ፈጽሞ ማቅረብ ስለማልሻ እንጂ ከሰው ልጅ ቀደምት፤ ሃይማኖተኛ ከምንባለው ይልቅ የታላላቅ አገር ፖለቲከኞች ለሰው ልጅ ያላቸውን ክብር አይቸበታለሁኝ። 
 
ስለሆነም የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከልቤ፤ ከውስጤ ሆኜ ነው የምከታተለው። አሜሪካ የብዙ ዓለም ዓቀፍ መጠጊያ ያጡ የእኔ ቢጤወች #ሆድ ነው። ልዩ የመንፈስ ፍቅረኛም ነው። ጉሮሮም ነው። ስንት ቤተሰብ መኖሩ የሚኗኗረው በዚህ ሁሉን ቻይ በሆነው አገር አቃፊነት ነው። የተስፋ ምድር ናት። የምኞት #ማስከኛ ማህደርም። ሁሉን የሰጠው ዕውቀቱን፤ ሥልጣኔውን የማድረግ አቅምም። ለአብዛኛው የሚሆን ለጠነከረ፤ ለበረታ ለተማረ ዕድል የማይነፍግ። እቅፍ ድግፍ አድርጎ አቅም ላለው፤ ሠርቶ አደር መጠጊያ። በእኩልነት የሚያኖር አገር። ይህን ስል ምድራዊ ገነት እያልኩ አይደለም። ህይወት በአገርም በባዕትም ትግል ናት። ስለሆነም ነው የተሰደድነው። በኢትዮጵያ የህልውና እና የማንነት ትግል ሲባል ለኢትዮጵያ ፖለቲከኞች እጅግ ሊያሸማቅቅ፤ በእጅጉም ሊያሳፍር ይገባል። አይታፈርም ዴሞክራሲያዊ ምርጫ አካሄድንም በየዘመኑ ሲባል፤ ሲደሰኩር። ፋክት ተዘቅዝቆ ተሰቅሎ።
 
የሆነ ሆኖ ኢትዮጵያውያን አሜሪካ ኖርነም አልኖርነም ድምፃችን በነፃነት ካለደንበር የምናሰማባት አገር በሰላም ያሰበው ይሳካ ዘንድ ቢያንስ በፀሎት ማሰብ የተገባ ነው። ዛሬ ዓለም ግሎባላይዜሽን ላይ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፤ የማህበራዊ ሚዲያው ፋይዳ ቀላል አይደለም። አስተሳስሮናል። አገናኝቶናል። ለበጎ ሃሳብ፤ ለርህርህና፤ ለአጽናኝነት ከተጠቀምንበት እጅግ ዕድለኞች እንሆናለን። የሰው ልጅ ወደ ተፈጥሮው፤ ወደ ሰዋዊነቱ ተመልሶ ስልጣኔን በጦርነት ውድመት ስልጣኔ እናዳያጠፋው ስምምነትን ማንገሥ ይቻላል።
 
የአሜሪካ ምርጫ ምናችንም አይደለም የሚሉ አስተያዬቶችን አነባለሁኝ። በአንድም ይሁን በሌላ በዓለም ገዢ ፖለቲካ ባለ ድምጽን በድምጽ የመሻር ባለመብቱ ዬአገረ አሜሪካ በኽረ ጉዳይ በእያንዳንዱ የህይወት መስመር ንክኪ ይኖረዋል። በሌላ በኩል አሜሪካ እኮ የአንድ ሰው የድምጽ ውሳኔ ሚና፤ በቲወሪ በምናውቀው የዴሞክራሲ መንፈሱ፤ ድርጊቱ ዩንቨርስቲ እኮ ነው። በዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደት ሌላው ዩንቨርስም ነው - ለእኔ። ይህን እየሰማን ብቻ ሳይሆን እያዬን ሲፈፀም የምናይበት ልዩ ዕንቋዊ ትዕይንት። ይህም እንደ አንድ የዓለም ዜጋ #ዕድለኛነታችን #ልናደንቀው ይገባል። 
 
ዕውን ለዴሞክራሲ እምንታገል፤ ተስፋ በዴሞክራሲ እምናደርግም ከሆነ። ለእግር ኳስ እንኳን የሚሰጠው ፍቅር የአሜሪካ ብሄራዊ ምርጫ ቢበልጥ እንጂ ቢያንስ አይደለም። ለሼክስፔር ስራወችም ከምንመሰጠው በላይም ነው። የነፃነት #ቃና እና #ቅኔ የሚታይበት። እያንዳንዱ የምርጫ ትጉህ የእራሱን ውሳኔ የማሸነፍ አቅም የሚመትርበት ወይንም የሚከነዳበት። ለመንፈስም፤ ለህሊናም ምግብ ነው። የሰው ልጅ የመብቱን እና የግዴታውን ጣራ እና ግድግዳ በመዳፋ የሚከውንበት ዕድል። 
 
በቀደሙት፤ በአንጋፋወቹ፤ ለትውልድ በረከት በሆኑ ሁለቱ #የዴሞክራት እና #የሪፓብሊካኑ ውድድር ሞቅ እና ደመቅ ባሉ #ሰማያዊ ቀለማት አሸብርቀው፤ ቁጥርም አልፎለት በድምቀት ሲንቆጠቆጥ፤ ጭንቀት እና ሳቅ ሲፈራረቅ፤ ሳቅ ዕንባ ሲንሸራሸሩ፤ ልብ ሲመታ፤ ዓይን ከሰሌዳ ተተክሎ ሲያማትር፤ ስታስቲክ ሲያልፍለት፤ ጆሮ ከማይክ ጋር ተዋዶ ልብ አንጠልጣዩን ምርጫ ሲከታተል፤ ፋክቶች ከፋክቶች ጋር ሲፋለሙ እና የግሎባል ዜጋ የሆነ ማንኛውም ፍጡር በዚህ ውስጥ የስልጣኔን አሻራ አልሰማህም፤ አላይህም ማለት ምን ይሆን? ይመርመር - አይደል??? እኔስ ይመለከተኛል። ከታተላለሁም።
 
እርግጥ ነው እዛው እዬኖሩም ሲስተሙ ስለተዘረጋ ያሻው ያሸንፍ ምን ቸገረኝ የሚሉ ሊኖሩ ይችላሉ፦ እንኳንስ እኛ እማንኖርበት። ግን ከግሎባሉ የዓለም ታሪካዊው አሻራ በህይወት እያሉ እራስን መሰረዝ መኖርን መፍተን ይሆናል ብዬ አስባለሁ። ከእግዚአብሄር በታች የሰው ልጅ ስልጣኔ የሰጠውን መመረቅ ቤተኛ መሆን የተገባ ይመስለኛል። ልዩ ሽልማትም ነው - ለእኔ። ሂደቱ ሳቢ ማግኔት ነው። እጅግም አጓጊም ነው። ይመስጣል።
ይከወን ድል #ለሴት ልሂቃን!
 
በመጨረሻ የመጀመሪያዋ ሴት፤ ጃማይካዊ፤ ህንዳዊ፤ አሜሪካዊ፤ የህግ እና የፖለቲካ ሊቀ - ሊቃውንት ወ/ሮ ካሜላ ሃሪስ (ኮመላ ሃሪስ) ዕድል ይቀናቸው ዘንድ ከልቤ ከውስጤም ሳላቅማም እመኛለሁ። ዕድሉን ያገኙ ሴቶች የአገሬ የኢትዮጵያ ሴቶችን ጨምሮ በፖለቲካ ተሳትፏቸው፤ በሚዲያ ተሳትፏቸው ጦርነትን ሲያበረታቱ እጅግ የሚገርመኝ ብቻ ሳይሆን የማዝንበትም ጉዳይም ነው። ጦርነቶች አሳማኝ በሆነ አመክንዮ ሁኔታወች ቢጀመሩ እንኳን ሰላም መሪ ይሆን ዘንድ ሴቶች ሊተጉ ይገባል ብዬ አስባለሁኝ። ሴቶች ጥሪያችን ለሰላም ነው ብዬ አምናለሁኝ። 
 
የሶርያ ችግር ጊዜ የተቸገሩ ሚሊዮኖች ድምጽ እኒያ ብረት መዝጊያ የሆኑት የቀድሟዋ የጀርመን ጠሚ ዶር አንጊላ ሜርክል እናታዊ ምግባራቸውን ዓለም አይቶታል። ሶርያውያን የልጆቻቸውን ሥም ሁሉ በሳቸው ሰይመዋል። በግሪክ የኢኮኖሚ ዝበት፤ በአውሮፓ ህብረት ጥንካሬም የጀርባ አጥንት ነበር ያ የአንስት የማይበገር አቅም ልቅና እና ልዕልና። ዕድሉን ለሚጠቀምበት ብዙ በረከት አለው የሴቶች ወደፊት መምጣት። በኢትዮጵያ በተለያዬ ሁኔታ በግልም በወልም ዕድሉ ተገኝቶ ለስኬት ባንበቃም።
 
ወደ ቀደመው ጉዳያ ሳመራ ሴቶች ወደፊት በመጡ ቁጥር ማንም የማይገድበው የፈጣሪ ፀጋቸው እናታዊነት ዘውድ ስለሚደፋ አጽናኝነት እና ርህርኃዊ፤ በጎ አድራጎታዊ ጉዳዮች ባለቤት የማግኜት ዕድላቸው የሰፋ ይሆናል ብዬ አስባለሁ። ለህፃናት፤ ለታዳጊወች፤ ለወጣቶች፤ ለአዘኑ፤ ለተከፋ ሁነኛ ያገኛሉ ብዬ አስባለሁኝ። ይህ ዕድላቸውን ለማያፈሱ አንስቶች ብቻ የሚሆን ዕይታ ነው። 
 
የሰው ልጅ የእጅ ዳንቴል አይደለም። የሰው ልጅ የአንድ ቀን የእጅ ሥራ ውጤት አይደለም። የሰው ልጅ ፈጣሪ በአምሳሉ የፈጠረው ድንቅ እና ግሩም ፍጥረት ነው። ለዚህ ክቡር ፍጥረት፤ የእግዚአብሄርም የኣላህን ፈቃድ ሳይተላለፋ ለክብሩ ዘብ ሊቆም ይገባል። መንግሥታትም የሰማዩ ንጉሥ ባለ አደራወች ስለሆኑ ይህን የማስፈፀም ግዴታ ይኖርባቸዋል። ለዚህ ደግሞ መብቱ በተሰጠባት አገረ አሜሪካ የባለመብቶች ድርጊተኝነት የተገባ ይሆናል። በተለይ የአሜሪካ መሪወች የዓለም ዓቀፋ የአደራም ባለአደራወች ናቸው።
 
መልካም ዕድል ለአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ለክብርት ወሮ ካሚላ ሃሪስ፥ ( ለወሮ ኮመላ ሃሪስ) አሜሪካ አዲስ መጸሐፍ ልዩ የሴት ፖለቲከኞች ልቅና በልዕልና ካስፈለገው ምርጫው የእሱ ነው። የአሜሪካ ምርጫ ዘመኑን እዬጠበቀ፤ በትውፊቱ ልክ ይከናወን ዘንድ ዕድሉ አሁን ይመስለኛል። ይህን ዕድል የአሜሪካ ህዝብ ከሳተ የዬዘመኑ ምርጫ የማይካሄድበት ህግም ሊወጣ፤ ሊሻሻል የሚችልበት ሁኔታ ይሮራል። ዘመን ሰጥ ዕድሎችን መገመት አይቻልም። እርግጥ ሲስተሙ ተዘርግቷል። ግን??? ………
ከሁሉ በላይ ግን እግዚአብሄር አምላክ የአሜሪካን አንድነት ይጠብቅ። የ2024 የአሜሪካ ምርጫ በሳላም ይፈፀም ዘንድ ይርዳ። አሜን። 
 
የተከበራችሁ የፔጄ ታዳሚወች ደህና ሁኑልኝ። አሜን።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
 
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
04/11/2014
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።