እናት ስትታሰር የትውልድ ተስፋ ይጠነዝላል።
እናት ስትታሰር የትውልድ ተስፋ ይጠነዝላል።
"የቤትህ ቅናት በላኝ።"
ጤና ይስጥልኝ ማህበረ ቅንነት። እንዴት ሰነበታችሁ? በብዙ ያልሰከኑ፤ ያልተገሩ፤ የሚወራጩ ሁነቶች ውስጥ ዝምታ የተሻለ በመሆኑ ዝምታ ቆምሶ ሰነበተ።
ከውስጤ ሊወጣ ያልቻለውን የቤተሰብ ምስል በሚመለከት ትንሽ ልጽፍበት ወደድሁኝ።
ፎቶዋን ከፌስቡኬ
https://www.facebook.com/sergute.selassie/
#እናት ናት።
#ትጉህ ፀሐፊ ናት።
#ሞጋች ናት።
#መምህርት ናት። ሚስትም ናት።
#ፖለቲከኛም ናት።
#ቁምነገርም ናት መስኪ።
#ወጣቷ ፖለቲከኛ በሳልም ናት።
መስኪ እና ብዕሯን ከ2014 ጀምሮ እኔም እሷም የደጉ ዘሃበሻ፦ የደጉ ሳተናው #አምደኛ ሆነን አውቃታለሁኝ። እኔ እንዲያውም አገር ቤት ሆና እንዲህ ትሞግታለች ብዬ አላስብም ነበር። በውነቱ ውጪ የምትኖር ነበር የሚመስለኝ። አንድ ጊዜ አመስግኜ ኢሜል ፃፍኩላት። መልስም ሰጠችኝ።
መስኪ ባለትዳር እና የልጆች እናት መሆኗን ግን በጣም ዘግይቼ ነው የተረዳሁት። ምክንያቱም እኔ ከ2019 በፊት የፌቡ ተጠቃሚ ባለመሆኔ ለብዙ መረጃወች ቅርብ አልነበርኩምና። የሆነ ሆኖ መስኪ እንዲህ #ተደፍሮ ለካቴና ልትሰጥ የሚገባ ወጣት ፖለቲከኛ አልነበረችም። ልንሳሳላት የሚገባ ልዩ ወጣት ናት እና። እንዲሁም ለገዢውም ሆነ፤ ለተፎካካሪ፤ ለተጠማኝ፤ ለተደማሪ፤ ለተቀላች፤ ለተለጣፊ፤ ወይንም ለተደማሪ ለዬትኛውም ፖለቲከኛ የምትሰጠው ጉልበታም አስተያዬት ህዝብ ጠቀም በመሆኑ ይረዳዋል፤ የአቅጣጫ አመላካች ነውና። መስኪ ለግፋፎ ጭዳ ጭድ ክምር ግርግር አልተፈጠረችም። ለምታምንበት ቁም ነገር ጽኑ እና ዕውነት አፈላላጊ ናት።
ጹሁፎቿን በትጋት አነባለሁኝ። ጹሑፎቿ የሚናፈቁ ናቸው። ሚዲያ ላይ ዕድሉን ስታገኝም ተዘጋጅታ ነው የምትቀርበው። ያቺን የመሰለች ውብ ደማቅ ብዕረኛ በመንግስት የሚተዳደሩ ሚዲያወች ግን አክብረው፤ ዕውቅና ሰጥተው ቃለ ምልልስ አድርገውላት አያውቁም። ከሁሉም ደፋሩ ጋዜጠኛ አቶ ስሜነህ ባይፈርስ አመለጠው ልለው የምችለው ዕድል ከመስኪ ጋር ቃለ ምልልስ አለማድረጉ ነው።
ምክንያቱም የእኔን ፁሁፍ በዝግጅቱ አንስቶ ፕ/ ዶር. መራራ ጉዲናን ሲሞግት ሳይ ድፍረቱ ለእኔም አስደንግጦኝ ስለነበር፤ እናቴም በጣም ደስተኛ ነበረች በእሱ ደፋር እርምጃ፦ በሥጋ እስክትለይ ድረስም ትፀልይለት ነበር ለደፋሩ ሞጋች ጋዜጠኛ አቶ ስሜነህ ባይፈርስ። ሰሞኑን ደፋር መጸሀፍ መፃፋን ሲሞገትበት አድምጫለሁኝ። በዚህ አጋጣሚ እንኳን ደስ አለህ ደፋሩ።
መስኪሻንም አቅርቦ ቢሞግት ሞጋች እና ሞጋች በሰላማዊ መስመር ሰላማዊ ትዕይንት ቢያሳዩ የትውልድ #አሻራም ነበር። እግዚአብሄር ፈቅዶ እና ወዶ መስኪ ከእስር ስትለቀቅ የዚህችን ድንቅ፤ ደፋር፤ ትጉህ ብዕረኛ መንፈስ ዕውቅና ሰጥቶ ባይ ምርጫዬ ነው። መቼም የብዕሯ መስኖ ስለ እስር ቤት ቆይታዋ አንድ መጽሐፍ ታጋራለች ብዬ አስባለሁኝ።
#ይሉኝታ #ቢሱ የአብይዝም ሥርዓተ መንግስት ለእርሱ የኢትዮጵያ ባለ ሙሉ ስልጣን ገዢነት የመስኪ ብዕርም አስተዋፆ ነበረበት። አፍሶት እንጂ፤ መስኪ የአብይዝምን ስርዓቱን ደገፈችም፦ ነቀፈች #ባለውለታነቷ ሊዘለል ባልተገባ ነበር። በፖለቲካ ዘርፍ አገር ውስጥ ሆኖ በቋሚነት ያልተመቸውን ሥርዓት በመሞገት እረገድ መስኪ መሪ ናት። እንደ እሷም አገር ተቀምጦ በብዕሩ የሞገተ ብዕረኛ አንስት አላውቅም።
መስኪን ማሰር የሴቶችን የፖለቲካ ሞጋችነት #ተስፋም ማሰር ነው። መስኪ ለሚሊዮኖች ድምጽ ናት። ትናንትም ዛሬም። ታስራም ቤተ አብይዝም የሚርድባት። መስኪ ልጆቿ የመሐፀኗ ክፋይ ብቻ ሳይሆኑ መምህርትም ስለሆነች ሺወች ናቸው። በውስጧ ያለው የመፃፍ ፀጋዋ በአንድም በሌላም ለልጆቿ የምትመግበው ማዕድም ሲቆለፍ ብዙ፤ በጣም ብዙ ያጎላል። ትውልድ አብነት ያስፈልገዋል። ልክ እንደ ኦክስጅን።
በሌላ በኩል የማህፀኗ ክፋይ የሆኑ ልጆቿም እናት አልባ ሲያድጉ የሚያስከትለው የስነልቦና ጫናም ረቂቅ ነው። ስለነገ ሲታሰብ፤ ስለ አደራ ሲታሰብ፤ ስለትውልድ ሲታሰብ እንዲህ እናት እና ልጅን በካቴና ጠርንፎ ሊሆን አይገባም። ህሊና ቢኖረው የአብይዝም አገዛዝ። እነኝህ ቀንበጦች በእናት ናፍቆት እዬተንገላቱ ትምህርቱም፤ መኖሩም ግራጫማ ነው - ለእነሱ።
በሌላ በኩል ትዳር ቅዱስ እና የማህበረሰብ መሰረት በመሆኑ ትዳሩ ሲታሰር ማህበረሰብ በካቴና እንደ ተጠረነፈ ነው ለእኔ የሚሰጠኝ ግብረ ምላሽ። የመስኪ የትዳር አጋር ጭምቱ አቶ ፍፁምም የዘወትር እንግልት፤ ልጅ ይዞ፤ እስረኛ የትዳር አጋርን እዬተመላለሱ ማጽናናት ድርብ ድርብርብ ኃላፊነትም ነው። ጥንካሬያቸው ግን ሁልጊዜም ይገርመኛል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ እናት ናት። ሴቶችም እናት ናቸው በተፈጥሯቸው። ወለዱም መከኑም እናትነት ፀጋቸው እዮራዊ ነው።
በእናትነት ውስጥ ያለው ሚስጢር ጥልቅ እና ምጡቅም ነው። እናት እንደ ሥሟ እናት ናት። ኢትዮጵያ ግን ሴቶች የሚመዘኑት፤ የሚለኩት፤ ለእናትነታቸው የሚሰጠው አክብሮት አሰጣጡ ወሳኙ በፖለቲካ አቋማቸው ነው። ይህም በመሆኑ ሞጋች ሴቶች፤ ላቅ ብለው ብቅ ያሉ ሴት ፖለቲከኞች በዬዘመኑ የጨካኝ ሥርዓቶች የጥቃቱ ሰለባ ይሆናሉ። ይህ ከስሩ ይነቀል ዘንድ ነበር እኔ የታገልኩት። ግን ጭልፊቱ ማህበረ ኦነግ ላጥ አድርጎ የግፍ ክምር አስተቃቀፈን። መንፈስ ማረፊያ አጣ። ተስፋም ጥግ ተነፈገ።
ዕውነት ለመናገር ህወሃትን ያን ያህል ስትሞግት ችግር ያልገጠማት ብዕረኛዋ መስኪ፤ በጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ዘመን ሁለት ጊዜ ታስራለች። እስርም ፍርደኝነትም የተጣመረ ግፍ ነው የተፈፀመባት። የመጀመሪያው በአራስ ቤቷ ነበር ለእስር የተዳረገችው። #ጨካኞች።
በዚህ ውስጥ የትውልድ ቀጣይ ተስፋ በተለይ የሴት ፖለቲከኞች፤ ብዕረኞች፤ የሚዲያ ባለሙያወች ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በቋሚነት በብዕር የምትሞግት ሴት ትናንትም ዛሬም አንዲት #መስኪ ናት። እሷንም አልይሽ // አልስማሽ ማለት ለእኔ #ህመምተኝነት ነው ብዬ አስባለሁኝ።
መስኪ ከአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ ጋር ያቆራኛት የአማራ ህዝብ መጎዳት እንጂ የተለዬ ቀመር የለውም። ማንም ሰው ሰውነቱን ከተቀበለ ከተጎዳ ህዝብ ጎን መቆም የተገባ እና ፍትሃዊም ነው። መስኪም ያደረገችው ይህንኑ ነው። ይህን ማድረጓ ደግሞ እንዲህ አቅሟ፦ ችሎታዋ፤ ብቃቷ በካቴና እንዲከዘን ሊያደርገው አይገባም ነበር። በምታነሳቸውን ሃሳቦች አቅም አለኝ የሚል ኃይል መሞገት ነበር ቀናው መንገድ እና ትክክለኛው ጎዳና።
ለአንድ ስኩን ሥርዓት ሞጋች ዜጎች ተፈልገው አይገኙም። ሽልማቶችም ናቸው። እራሳቸውን ማግደው እውነት ለሚሉት መርኽ ስለሚሞግቱ። ምክንያቱም ሞጋቾች አብሪ ኮከቦች ናቸው እና። የተለዬ ብሩህ ህሊና ከተሟላ ድፍረት ጋር የሚቀዳጁ ሰብዕናወች ለትውልድም #ሐዋርያ ናቸው።
ራዲዮሎጂ ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ እየኖረች በፁሁፍ በቋሚነት የምትሞግት አንዲት ሴት ብትኖር መስኪ ናት። መስኪ ፕረዘንቴሽንም ላይ ተከታትያታለሁኝ። መምህርነቷም ቢያግዛትም ጥሩ ተናጋሪነት መሰጠትም ነው። ምንም እንኳን ተናጋሪነት ክህሎቱ በስልጠና ቢዳብርም፤ የንግግር ጥበብ አዋቂነት በራሱ መክሊት ነው። በዘመነ ደርግ በትምህርት ደረጃ እንደ አንድ ዕውቀት ዘርፍ ይሰጥ ነበር።
የሆነ ሆኖ መስኪ ሩቅ የምታስብ ወጣት በመሆኗ ስለ #ኦሮሙማ የሰጠችው ዘመን ዘለቅ ትንተና አይደለም ለእኛ ለግሎባሉም ዓለም ለመነሻ የሆነ አሻራ ሊሆን የሚችል አቅም ያለው ሆኖ አግኝቸዋለሁኝ። በእሷ ልክ ኦሮሙማን በልቶ የገለጠው ሞጋች አላዳመጥኩም። ከመፃፍ፤ ከመናገር ይልቅ ማድመጥ ትልቁ ፀጋዬ ስለሆነ ግርም ብላኝ ደጋግሜ አድምጨዋለሁኝ የሰጠችውን ትንተና።
ዕውነት ለመናገር ልዕልት ኢትዮጵያ፤ ናፍቆቴ ኢትዮጵያ ከመስኪ ልታገኝ የሚገባትን የዕውቀት ክህሎት #መነፈጓ በእጅጉ ያሳዝነኛል። መስኪ ሁሉም ያላት፤ ግን ነፃነት ለፀጋዋ - ለብቃቷ - ለክሎቷ - ለችሎታዋ የተነፈጋት አብነት እናት - እህት - ሚስት - መምህርት፤ - ፀሃፊ - ብቁ ተናጋሪ - ሞጋች ናት።
የእኔ ጥያቄ ለአብይዝም ሥርዓት ብቁ፤ ንቁ፤ ደፋር፤ አቅጣጫ መሪዋ መስኪ ነፃነቷ ተስጥቷት የጀመረችው " ንቃት " ሚዲያዋ እንዲቀጥል ማድረግ መብቱ ብቻ ሳይሆን ግዴታውም ነው ብዬ አምናለሁኝ። መስኪ የፈለገችውን የፖለቲካ አቋም የመውሰድ መብቷም ሊጠበቅ ይገባል።
እንደ እኔ በመጀመሪያው ከእስር ስትወጣ #የህፃናት የበጎ አድራጎት እና የመብት ተሟጋች ተቋም ትመሰርት ዘንድ ፕሮፖዛል አቅርቤ ነበር። እኔ ጓደኝነት ስለለኝ ከቤታችን የሚገኙ ቅኖች መልእክቴን እንዲያደርሱላት ጽፌ ነበር። ይህ የልጆች በጎ አድራጎት እና መብት ተሟጋች ድርጅት ግሎባልም ስለሚሆን ተንከባካቢም፤ እረጅም ጥበቃ የሚያደርግለትም ተቋም በፍጥነት ሊያገኝ ይችላል። የመስኪ አቅም ሁለገብ ስለሆነ ዓላማውን ከግብ ለማድረስ ትችላላች የሚል እምነት ስለነበረኝ ነበር ሃሳቡን ያቀረብኩት። ከሁሉም ግን የደህንነቷ ሁኔታ ስለአሳሰበኝም ነበር። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የመስኪን ሙሉ ክህሎት ተጠቃሚ ትሆን ዘንድ አዲስ የተስፋ አቅጣጫ ነበር።
#የሆነ ሆኖ
1) መስኪ ለኢትዮጵያ ታስፈልጋለች።
2) መስኪ ለተጎዳው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ታስፈልጋለች።
3) መስኪ ለተማሪወቿም ታስፈልጋለች።
4) መስኪ ለሦስት ጉልቻዋም ታስፈልጋለች።
5) መስኪ ለትውልዱም ታስፈልጋለች።
6) መስኪ ለብዕር እና ብራናም ታስፈልጋለች።
የመስኪን የትግል መስመር እኔ መወሰን አልችልም ( ብትፈልግ የአማራን የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ፤ ብትፈልግ የዜግነቴ ፖለቲካ የመወስን መብቷ የእሷ ነው። ) ግን የመስኪ ክህሎት እና ብቃት የካቴና ስንቅና ትጥቅ መሆኑን አጥብቄ #አወግዛለሁኝ።
መስኪ እንደ አንድ ሴት አላያትም። ተጋድሏዋ ተከታታይ እና ጽኑ መሆኑን ታዝቤያለሁኝ። ሌላ መስኪ ቀናም ናት። ጠቅላይ ሚር አብይ ወደ ስልጣን ሲመጡ ብቻ ሳይሆን ሥልጣን ላይ ሆነውም ስትደግፍ ነበር። አቶ ተመስገን ጥሩነህ ወደ አማራ ክልል ሲመደቡም ጹሁፏን አንብቤዋለሁኝ። ቀና እና አወንታዊ ነበር።
ተስፋዋን ባለማግኜቷ ነው ወደ ነበረችበት የቀደመ የሞጋችነት ዓውዷ የተመለሰችው። የአብይዝም ሥርአት ያጎደለውን፤ #ያጎበጠውን፤ ያዝረከረከውን፤ ቅርምጥ አድርጎ የበላውን ቃል፤ ያስነከሰውን ዘመን፤ የዳጠውን ተስፋ ከምን ላይ እንደ ጎዳው እራሱን ማጥናት፤ እራሱን መገሰጽ፤ እራሱን መግራት ሲገባ ብዕረኛ ሞጋች እና ደፋሯን ቀንበጥ መስኪን አስሮ ሊበቀላት አይገባም። ፈጽሞ።
ለነገሩ ጭምቱን አቶ በላይ ማናዬን እና ዝምተኛዋን እህት ገነት አስማማውን ለማሰር እኮ ደፍሯል። ልጅ በላይ ማናዬ መሰደዱን ሰምቻለሁኝ። እጅግ በጥንቃቄ ነበር የሚሰራው። የተዋህዶ ጥቁር ልብስን እንኳን አለበሰም ነበር። እና፦ እናማ እንኳንስ አበጥራ፤ አንተርትራ፤ አንዘርዝራ ዕውነትን ፍለጋ የምትማስነውን ደፋር የሚዲያ ቤተኛ ማሰር ሊደንቅ አይገባም እንደ ማለት።
አሁን ተሆነ በገዢው አብይዝም ጎራ ኢትዮጵያ ጎልታ ስትሰማ አደምጣለሁኝ። ኢትዮጵያ ማለት እኮ #መስኪ ናት። መስኪ የኢትዮጵያን ዕንባ ያነበበች፤ የተረጎመች ያመሳጠረች ትጉህ ናት። የኢትዮጵያን ሃዘን፤ መከፋት፤ አንገት መድፋት ህመም ፈቅዶ እና ወደ ከመጋራት በላይ የጽድቅ ጎዳና ለእኔ የለም። የእናት አገርን ዕንባ ውስጥ ከማድረግ በላይ ምን ህሊናዊነት አለና? መስኪም ያደረገችው ይህንን ነው።
የማህበረ ኦነግ ቤተኞች የአብይዝም ሹመኞች የእናት ኢትዮጵያ መናዋን እዬተመገቡ ኢትዮጵያን እንደ ድልህ ሲደቁሷት ውለው የሚያድሩት ሚ/ ር ሆነው #ይንጎባለሉ። መስቃ ሲተረትሩ ውለውም ያድራሉ። የጠ/ሚር #አማካሪ ሆነው ይዝመነመናሉ። ከማህበረ ኦነግ ፀረ ኢትዮጵያዊነት፤ ፀረ ቀደምትነት ምን ዓይነት የምክር አገልግሎት እንደሚገኝ አላውቅም። ኢትዮጵያ ስትጠቁር አብረው የሚጠቁሩት፤ ስትከሳ አብረው የሚከሱ፤ ማቅ ስትለብስ አብረው ማቅ የሚለብሱ እንደ መስኪ አይነት ቀና እና ቅን፤ ግልጽ እና ቀጥተኛ ስጦታወች ደግሞ ይታሰራሉ፤ ቤተሰብም አብሮ ይንገላታል። አቅማቸው #ይታመቃል።
መሪነት ሚዛን ይጠይቃል። መሪነት ኮሽ ባለ ቁጥር መበርገግ አይደለም። መሪነት ቂም እና በቀልን አግብቶ መኖር አይደለም። መሪነት ቅናት እና ምቀኝነት አይደለም። መሪነት ፈሪነትም አይደለም። መሪነት በራስ መተማመን ማነስም አይደለም። መሪነት የማንነት ቀውሰኝነትም አይደለም። መሪነት ብፁዑ - ቅዱስ ነብይነት ባይሆንም መሪነት ሙሉ ሰውነት። ምራቁን የዋጠ ሰብዕና፦ አደብ እና ጥሞናን፤ አድማጭነት እና ከግድፈት መማርን ይጠይቃል።
የአብይዝም ስልጣን የተገኘው የኢትዮጵያ ፖለቲካ በገበርዲን እና በከረባት መሸለሙ ያንገፈገፈን ብዕረኞች በሰላማዊ ተጋድሎ ባደረግነው ትጋት የተገኘ ነው። ህወሃት ኮሽ ሳይል ስልጣኑን ያስረከበው ጥበብ፤ በብልህነት በታደሙ በተከታታይ ተግባራት ነው ለዚህ የኦነግ መንፈስ የተጫነው የአብይዝም ዕድል በር የከፈተው። እኔ ስታገል ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ ነበር። እነ ቲም ገዱ ዕድሉን አባከኑት ብቻ ሳይሆን ቀበሩት። ዳግም የማይገኝ ዕድል ነበር። ክስተትም ነበር።
የሆነ ሆኖ መስኪን ፍቷት። በኢትዮጵያ ከደረቅ ወንጀለኛ በስተቀር ምንም የፖለቲካ እስረኛ ሊኖር አይገባም። ሰላም የሚገኘውም ሁሉም መብት እና ግዴታውን አውቆ በነፃነት ሲንቀሳቀስ ነው። ነፃነት ሲታሰር የትውልድ ተስፋ ይታሰራል። ትውልዱን አታሳቅቁት። ትውልዱን አታስፈራሩት። ትውልዱን በስጋት አትወጥሩት። እስር ይብቃ። ሞትም ይብቃን። ሰበር ዜናም ይብቃን።
ጽኑዋ ቤተ - መስከረም እና ቤተሰቦቿ ለምታደርጉት የተቆርቋሪነት፤ የሰባዕዊነት፤ የሰዋዊነት ተፈጥሯዊ ተጋድሎ ያለኝን አክብሮት እዬገለጽኩኝ፦ ላመሰግናችሁ ወደድሁኝ። ኑሩልኝ የእኔ ጭምት ጀግኖቼ።
ቸር አስበን፦ ቸር እንሁን።
ቅን አስበን፦ ቀና እንሁን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
07/12/2024
ፍትህ ለእናት ወሮ መስከረም አበራ!
ፍትህ ለፖለቲካ እስረኞች በሙሉ!
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ