የካቲት 25/2006 ሲጠዬቅ ስለ #ባለድርብ #ህሊና ብላቴ ሎሬት ጸጋዬ ገ/ መድህን።
ዛሬን በነጮቹ የካቲት 25ትን ዕለቱን ከመንበሩ ጉብ ብሎ ተደላድሎ ስናገኜው እምንጠይቀው ቁልፍ ጥያቄ አገርም- አህጉርም፤ ዜግነትም - እኛነትም፤ ዕውነትም - መኖርንም፤ ሃይማኖትን - ታሪክን፤ ትውፊትን - ትሩፋትን፤ ወግ - ባህል - ልማድን፤ ሥልጣኔን ያናገረ - ያወያዬ - #ያስጠሞነ - ያመሳጠረ፥ በእነሱ ልዩ እርካታ ከፍታም የመረመረ - #የተፈላሰመ፤ ወቅትን ከትናንት እስከ ነገ የተረጎመ - የተነበዬ ያን ታላቅ #ቁምነገር፤ የተግባር #አንቱ፤ #ዓራት #ዓይናማ ሊቀ - ሊቃውንት ባለ ድርብ ህሊና ኢትዮጵያዊ ስለምን አሳጣህን ተብሎ ነው? ዕለቱን ሳስበው እንደ አገር አውራ - ታቦት የማዬውን የሁለመናዬን ቅኝት፤ የትውልድ የቤት ሥራዬን በማሰብ - በማስላትም ነው።
መኖሬን ሳስበው መንፈሴ ያን ታላቅ ሰው እዘክረው ዘንድ በሕይወት እያለሁኝ በስደት አገሬ በኳሽ አይሏ በእምዬ ሲዊዘርላንድ ስለ ሥሙ፤ ስለተግባሩ፤ ስለ ሊቀ ሊቃውንትነቱ እናገር - እጽፍ - እመሰክር - #አውጅ ዘንድ አምላኬ ስለፈቀደልኝም በማመስገን ነው። በተለይ የጸጋዬ ድህረ ገጽ ስወጥን፤ ስጀምር ላገዙኝ ለተባበሩኝ ማህበረ ቅንነት እጅግ ከፍ ያለም ምስጋና አቀርባለሁኝ። ለምንጊዜውም አከብራቸዋለሁኝ። ቅንነታቸው ቁሞ አስተምሮኛል እና። ያ ጥንካሬዬ ጸሐዬ ሆኖ ነው የጸጋዬ ራዲዮን የጀመርኩት። ብርታቶቼ ግሉኮሶቼ ከሲዊዝ፤ ከአውስትራልያ እና ከአገረ አሜሪካ ያሉ ወገኖቼ የሰጡኝ ጥንካሬ ልዩ ነበር።
የወል ተግባር ባለመበርከቱ ድህረ ገጹን በቀደመ ትጋት መቀጠል ባልችልም #በ97.5 መካከለኛ ሞገድ በራዲዮ ሎራ የጸጋዬ ራዲዮ ከራሳችን በተፈጠሩ ያልታደሉ ከንቱወች ትብትብ ፈተና ከውጥኑ እስከዛሬ ቢኖርበትም ብቻዬን ስለምሠራው በክስ፤ በፈተና ውስጥም ሆኖ #መስከረም 18/2023 እንሆ 16 ዓመቱን አጠናቆ 17ኛ ዓመቱን ይዟል። እንኳንስ #ማብቀል የበቀለን የሚታገለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንደ እሱ ተኮርኩሜ፤ ተጨባብጬ ከትራስ እንደ አደረ ጨርቅ #ጭምትርትር ብዬ ተሳቅቄም ተግባሩን አቆም ዘንድ አሁንም ይፈትኑኛል። ያደለው ይረዳል፤ የቻለ አይዞሽ በርችልን ይላል። ያም ቢቀር የረብሻ ጋጋታ ለማን እና ለምን እንደሚረዳ ትናንትም አልገባኝ፤ ዛሬም አይገባኝ ወደፊትም እንዲገባኝ አልፈልግም።
ዬሚገርማችሁ እንደተሳሳትኩም እንዳምን የሚውተረተሩ ሰብዕናወች ገጥመውኛል። እኔ ግን አለመሳሳቴን ጠንቅቄ አውቀዋለሁኝ። እኔ ለመደቆስ ለሚሹ ባክነው ብቻ ይቀራሉ። ይህን የሚያደርገው ንጽህናዬ እና ሰፊው ገራገር ቅንነቴ፤ ለውዷ እናቴ ያለኝ የታማኝነት አምላኬ ይመክተዋል።
ክብሬን - ማክበሬ፤ ክብሬን - ማስከበሬ// ለሰማይም - ለምድርም ምቾት እንደሚሰጥ አምናለሁኝ። በብዙ መልካም/ ፈታኝም የህይወት ገጠመኞች ያለፈችው ሥርጉትሻ ስለ ጎዳናዋ ምርጫ ፕሮፖጋንዲስት ወይንም መንገድ መሪ አትሻም። ብነግራችሁ የጅብኃ መሥራቾችን በአካል አግኝቻቸዋለሁኝ በአንድ ያልታሰበ አጋጣሚ። በነፃ በቀጠናቸውም እዘዋወር ዘንድም የይለፍ ሰነድም ሰጥተውኝ ነበር። ስልካቸውን ሁሉ። ዓለም ዓቀፍ ኢቤንቶችን ከብሄራዊው ጉዳያችን ጋርም ተሳትፌያለሁኝ። ምንም ነገር ብርቄም ድንቄም አይደለም። ብዙ የተከደኑ ክስተቶች ውስጥ አልፌያለሁኝ። እና ያ ሁሉ ተመክሮዬ መንገዴን ለመምረጥ፤ ለመወሰንም ያስችለኛል። በብዙ ዕድሎች እና ገጠመኞች ያለፈች ናት ሥርጉትሻ። ዝምታዋ ጸጥታን መራጭ በመሆኗ ብቻ ነው። እና የማር ብላቴ ጸጋዬ ገ/ መድህን መንፈስ ምርጫዬ ትክክለኛ ውሳኔዬ ነበር። አሁንም ነው። ገና የጸጋዬ ትውልድ ይፈጠራል። እስከዚህ ድረስ እኔ አልማለሁኝ።
የሰው ልጅ እሱ አይሥራው፤ ሌላው በሚሠራው፤ ሌላው በሚደክምበት ላይ ስለምን ህውከት እና ትርምስ ለመፍጠር ኃይል እና ጉልበቱን እንደሚያፈስ ይገርመኛል። ስለ አገር፤ ስለ ናፍቆት፤ ስለ ትውልድ፤ #ስለድርሻ በትክክለኛው ጊዜ መላ ህሊናቸውን ሰጥተው የተጉ፤ የበረቱ ወገኖቻችነን ተግባር ብናቆላምጥ፤ ብንከበክብ፤ ብናስታውስ ትውልድን ቢጠቅም፤ የአገርን ክብር ቢያስጠብቅ፤ ስለ እናት አገር ዕውቅና አንባሳደር ቢሆን እንጂ ከማንም፤ ለማንም የሚያጎድለው አንዳች ነገር የለም። ዛሬ ሚሊዮን አማራጭ ባለበት የማህበራዊ ሚዲያ ግሎባል ዘመን እንኳን #ስስታሞች፤ ውጥንቅጦች እንሆ የብላቴውን ራዲዮ ፕሮግራም ይፈትኑታል። አልመታደል።
የብላቴ ሎሬት ጸጋዬ ገ/ መድህን ጸጋ እኮ የትምህርት ካሪክለም ሆኖ ልጆች ሊማሩት የሚገባ #ቁም ነገር ነው። ብላቴው ፈላስፋም ነብይም ነበር። የእሱን ሥራ አይደለም መተርጎም፤ አይደለም ማመሳጠር በቁሙ ለማንበብም የሚቸግር የሚስጢር ዓውድ ነው። ያን ሚስጢር ዕውቅና ሰጥቶ ትውልድ - ጠቀም የማድረግ ደግሞ የትውልድ ድርሻ ነው። እኔ በብዙ ደክሜበታለሁኝ።
በለት ተለት ቅርጥምጣሚ ፖለቲካ የትናንት የገዘፈ የተግባር ጥሪት ዛሬ እዬተደረመሰ፦ እንደ አልባሌ የሚታይበት አግባብ ከድህነታችን በላይ ሌላ የዕሳቤ የድህነት ዲሪቶ ቢከምር እንጂ፦ የሚያስገኜው ቅንጣት ፋይዳ የለም። እያለን እንደ ሌለን፤ የቀደሙት - የተጉበትን መስመር ሁሉ #በለቅ እያለበስን መጓዛችን ጎዳን እንጂ የጠቀመን የለም።
አሁንም ሆነ ወደፊትም ሊጠቅም የሚችለው የቀደመ ልፋትን፤ የቀደመ ታማራትን፤ የቀደመ ትንግርታትን በቅጡ፤ በወጉ አክብሮት ሰጥቶ ትውልድ ጠቀም ማድረግ ነው የሚበጀው። ታሪክ - ባህል - ወግ - ልማድ - ትውፊት #በቀደመ #ህዝብ የሚበጅ ስለመሆኑ አውቆ መቀበል ይገባል። ያለ የነበረ ነገር ሲኖር የየዘመኑ ባለ ድርሻወች መነሻ መሠረት ይኖራቸዋል።
ጌታ ብላቴ ሎሬት ጸጋዬ ገ/ መድህን ሆነ ቀደምት የጥበብ በረከቶቻችን ባለ ፊደል ቋንቋ #ግዕዝ እና #አማርኛ በሙሉ አቅም ማግሰስም፤ ስዋሰዋዊ ሥርዓታቸውን በጠበቀ በሚያስችል መልኩ ተፈጥረው ተደራጅተው ስለቆዩ እነሱ ተጠበቡት። እነሱ ከሸኑት። የበለጠ አሰለጠኑት። ያለ ነገር ቢጠቅም እንጂ አይጎዳም። ይህ ሁሉ ተጽዕኖ ፈጣሪ የመፈጠሩ ሚስጢር የሚያግባባ በፍጹም ሁኔታ የተደራጄ የራስ ወዝ የሆነ ባለ ፊደል ቋንቋ ስለአለን ነው። ይህን ብርቱ ማገር መፈተን እርግማን ነው። ከትምህርት ሥርዓት ማውጣትም #አረማሞነት ነው።
ይገርመኛል ከአሰበለ ነገር ጋር ግብግቡ። አማርኛ ቋንቋ የእኔ የሚለው የፊደል ገበታ ህግ እና ሥርዓት ያለው ፒላር ቋንቋ ነው። ከእሱ ጋር በአቻነት ለመቆም የደረሰበትን የሥልጣኔ እርከን መመዘን ይገባል። ውድድር ፋክክር ባለ ነገር ላይ ሊሆን ይገባል። በሌለ ነገር ፋክክሩ ደርቶ ያለን ነገር ማሳጣት የአስተሳሰብ ድህነት ነው። እንደራሴነትን ገፍቶ ትውስትን ማስቀደም #ቆባነትም ነው። ፊደል ሲኖርህ ብቻ ነው ከአማርኛ ቋንቋ ጋር መፎካከር፤ በአቻነት መቆም የሚቻለው። ትውስት የፎካከር ያለበት ከትውስት ጋር ብቻ ነው። ይህ ፋክት ነው። ልትሰርዘው፤ ልትደልዘው የማትችል የዕውነት ወርቅ።
ክብር ለቀደሙት ቱጋህን እንጂ በሚታለመው የጠላትነት ልክ ቀደምትነታችን ሙሉለሙሉ መደርመስ አይቻልም። አሻራው አነሰም አደገም በስደት አገርም አለ እና። ብላቴ ሎሬት ጸጋዬ ገ/ መድህን ጸጋውን ያላሾለከ፤ በጸጋው ልክ የተጋ፤ ፓን አፍሪካኒስት የተግባር #ስኬት ነበር። ስለሆነም ነው የፈተናው ማዬል እኔን ሊያስቆመኝ ያልቻለውም ይኽው ዕንቁ አመክንዮ ነው። ለተገፋው፤ ለተገለለው ሳይለንት ዲስክርምኔሽን እዬደረሰበት ለሚገኜው ዓለም ዓቀፍ የአማርኛ ቋንቋ ልዩ ባለውለታ ነው ጌታ ብላቴ። ማር ነው። #ጣዝማ ነው።
ስለሆነም ትርታዬ እስከአለ ድረስ ትጋቱ ይቀጥላል። ሞት ሲመጣም ተሰናድቼ ስለሆነ የምጠብቀው እንኳን ደህና መጣህ ይባላል። አይደልም ሌላው ትጋቴ ይህ ብቻ ስለሚበቃ እርፍቴ እጅግ ሰላማዊ ይሆናል። የድርሻዬን፤ የጥሪዬን፤ የፖስተኝነቴን ተልዕኮ ደልደል ባለ ወይዘሮማ ከውኛለሁ እና። ጎደለ፤ አላሳካሁትም የምለው አንዳችም ነገር በእኔ የህይወት ክብ ውስጥ የለምና።
የምችለውን በምችለው አቅሜ ልክ "በይበቃኛል" የሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስ ቃለ ምህዳን ክርክም ብዬ እራሴን ጠብቄ፤ አገሬንም ያሳደጉኝን ወላጆቼን፤ የጎንደር ከተማን ማህበረሰቤን፤ መምህራኖቼን አንገት በማያስደፋ ሁኔታ ተግቻለሁኝ። የሚጸጽተኝ አንዳችም ነገር የለም። ብዙ ጊዜ ፈተናው ሲይል በነፃ አገልግሎትም በመሰናክል ስወጠር ብቻዬን እንዳለሁ አይሰማኝም። የዛን የአገር መለያ ሥም ብላቴውን ከፍ በማድረጌ የመጣ መሆኑን ስለምረዳ በፈተናዬ አምላኬን አመሰግነዋለሁኝ። ይህን ቀኝ መንገድ ስለመራኽኝ ተመስገን እላለሁኝ። ነገረ ጸጋዬ #ሚዛኔ ነው። ዝንፍ እንዳልል፤ ሁልጊዜም አስተምኽሮውን እንዳስብ፤ በዛ ልክ እንድንቀሳቀስ ይረዳኛል።
አጽናኝነቱ መንፈሱ ከድንቅ በላይ ነው። በአንድ ተግባር ላይ፤ በአንድ ተልዕኮ ላይ አተኩሮ መሥራት እና በዛ ውስጥ መስከን መቻል መታደልም ነው። የኦሮሞ የዘር ሐርግ ሳይኖረኝ በኦሮሞ አክራሪነት፤ በተዋህዶ አክራሪነት የተከሰስኩበት የብላቴ ሎሬት ጸጋዬ ገ/ መድህን ራዲዮ በ15 ቀን አንድ ቀን፦ የቀን ቅዱስ በዕለተ ሃሙስ ከ15.00 - 16.00 ሰዓት በደጋደጓ አገረ ሲዊዘርላንድ በአማርኛ ቋንቋ አዬር ላይ ሲቀርብ ለኢትዮጵያ - ለአገሬ፤ ለአጤ አማርኛ ቋንቋም ሞገስ እና ማዕረግም ነው። ይህ በራሱ ለእኔ ጽናት ብቻ ሳይሆን የአጽናኝነት፤ የአይዞሽ ባይነት መልዕክቱ ኑሬበት - አይቸዋለሁኝ። ፈጣሪ አምላኬን አብዝቼ አመሰግንበታለሁኝ።
በኳኳቴው፤ በድውድው፤ ተፈጥሮ ብትንትኑ በሚወጣው እና ንደት በማይለዬው ቅጽበታዊው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ማህበርተኛ እንዳልሆን ያደረገኝ ጠባቄዬም የብላቴው መንፈስ ነው። በራሴ መንገድ፤ በራሴ ራዕይ በተበደለ ብቻ ዕንባን ወግኜ መገኜቴ የውስጥ ሰላሜ በውስጤ ይጰጵስ ዘንድ ረድቶኛል። የውስጤ መረጋጋት እና ፍፁም የሆነ ስክነት ለመንፈሴ መዳበር ንጥረ ነገር ሆኖለታል። ተመስገን።
መሥራት ባይቻል የሚተጉ ሰወችን እንቅፋ መፍጠር፤ ማለም ባይቻል አርቀው የሚያስቡ ሰወችን ከጉዟቸው ለማስተጓጎል መጣር፤ ታላላቆችን ማክበር ባይቻል በዚህ ዙሪያ ለሚተጉት ፈተና መደቀን እርግማን ነው። ለዛውም ዛሬ ዕልፍ አላፋ ጋዜጠኛ፤ ጸሐፊ፤ አክቲቢስት፦ ሪፖርተር፤ ዘጋቢ፤ ፕሮዲሰር፤ የጥበብ ሰው፤ ተጽዕኖ ፈጣሪ ብቻ ሳይሆን በመኖሩም ትልቅ ድርሻ ያለው አትራፊ መድረክ በተፈጠረበት ዘመን አንዲትን ያለ ትርፍ የምትባትል፤ በድካሟ እርካታ አግኝታ ሰርክ በጎደለው ክፍተት ላይ ገድማ በምትተጋ ላይ ዘመን ከዘመን መተናኮል መርገምት ነው። ዛሬም ክሱ አለ። ግን የፈተና አሸናፊ አንድዬ ነው እና እዬረታን አለን።
እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ ጥሪ ይዞ ይወለዳል፤
እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ መልዕክት ይዞ ይወለዳል፦
እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ መክሊት ይዞ ይወለዳል። እኔም ይኽኑኑ ነው እዬከወንኩ የምገኜው። ይህ ወንጀል አይደለም። ፈቃደ እግዚአብሄርን መፈጸም እንጂ። የሆነ ሆኖ የብላቴ ሎሬት ጸጋዬ አሻራ ለ18 ተከታታይ ዓመታት በጭምቷ ሲዊዘርላንድ ቀጥሏል። ትርታዬ እስካለች ድረስ ትጋቱ በአቅሜ ልክ ይቀጥላል። ሥርጉትሻ የመብት እና በግዴታዋን ጣሪያ እና ግድግዳ አሳምራ ታውቃለች። ሥርጉትሻ ከጎረፈው ጋር አብራ አትጎርፍም፤ ከዘለለው ጋርም አብራ አትዛለልም። እሷ የራሷ እንደራሴ ናት። አለቃዋ ህሊናዋ፤ ካቢኔዋ መርኽ እና ዕውነት ብቻ ናቸው። በቅንነቷ እና ርህርህናዋ ደግነት እስተዛሬ ኑራለች። ነገ ደግሞ የባለቤቱ ነው። የማያዳላ፤ የማያገል፤ የማያሳድም፤ የማይጣላ አንድ አምላክ ስላለኝ ምንጊዜም የሰማይ እና የምድር ንጉስን አማኑኤልን አመሰግነዋለሁኝ። ተመስገን።
ዛሬ ዛሬ አገር ቤትም በብላቴው ዙሪያ ወጣቶች ድንቅ ተግባር እዬከወኑ ስለሆነ ሊመሰገኑ፤ ብርታት ሊመገቡ ይገባል። ጋሼ ጸጋዬ መንፈሱ እራሱ የፊደል ገበታ ነው። የተነበያቸው ሁሉ የመኖር አናባቢ ቫወሎች ናቸው። ፈጣሪ እሱን ሰጥቶ ብቻችን ሆነን እንኳን መንፈሱ የሚያተጋን፤ የሚያረጋጋን፤ ወጀቡን እንቋቋም ዘንድ የሚመራን ፊደሎቹ ናቸው። ጥልቅ እና መኖርን ያናገሩ ያስተማሩ በጥበብ ዓውደ ምህረቱ ምንጊዜም አባታችን እንድንዘክረው ግድ ይላል።
*** አረማሞ ከእህል ዘር ተገኝቶ አፍርቶ ያፈራው ግን የጥላሸት አመድ ጸንሶ የሚገኝ የእህል ዘር በሽታ ነው።
ማህበረ ቅኖች እንዴት አደራችሁ። ፈቃዳችሁ ከሆነ ትልቅ ሰው ሥጋው ቢለይም አስተምኽሮው፤ ትጋቱ ህልው ነው እና አስበነው ብንውል በህሊናችን መልካም ነው ባይ ነው። በጸጋዬ ራዲዮ ወርኃ የካቲት የብላቴው ስለሆነ በዛ እዬተዘከረ ነው። አጤ ፌስቡክ እንዳይቀርበት ነው በምልሰትም በዛሬውም ያለውን ለመቃኜት የሞከርኩት። ኑሩልኝ። አሜን።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
25/02/2025
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ