በቀል፦ አመድ፤ እና ጥላቻ ለማፈስ አትሽቀዳደሙ። #እባካችሁ - ተው! #እረፋም! የጦርነት ድግስ ይቁም! የዶር ሙላቱ ተሾመ ትጋት #ለኖቤል ሽልማቱ ጥበቃ ነው። #ዘብአደርነት።

 

በቀል፦ አመድ፤ እና ጥላቻ ለማፈስ አትሽቀዳደሙ። #እባካችሁ - ተው! #እረፋም! የጦርነት ድግስ ይቁም!
የዶር ሙላቱ ተሾመ ትጋት #ለኖቤል ሽልማቱ ጥበቃ ነው። #ዘብአደርነት
 
ከሞያሌ እስከ አባይ ምንጭ፤ ከአባይ ምንጭ እስከ ሮኃ ለመስፋፋት ለአወጄ ኃይል እራስን? መታመንን? ቅንነትን ለመገበር ወረፋ መያዝ ጅልነት ወይንስ ድብነት?????
 
"የቤትህ ቅናት በላኝ።"
 
May be an image of 8 people and text that says 'thio'
May be an image of 5 people
 May be an image of 3 people, dais and text
ፖለቲካ ማለት ጥፋት መናፈቅ፤ ፖለቲካ ማለት እራስን ማንደድ፦ ፖለቲካ ማለት ትውልድን ሰርክ ለባሩድ መማገድ፤ ፖለቲካ ማለት በኋላቀርነት መቀጠልን መፍቀድ - መናፈቅ፤ ፖለቲካ ማለት ለሥልጣኔ ፀር መሆን፤ ፖለቲካ ማለት በቀውስ ውስጥ መዳከር፤ ፖለቲካ ማለት ለጥፋት መጣደፍ፤ ፖለቲካ ማለት ትውልድን ማቆራረጥ፤ ፖለቲካ ማለት ስጋትን ዲል ባለ ሆታ ማቆላመጥ፤ ፖለቲካ ማለት ህዝብን ከሰቀቀን ጋር ማፋለም አይደለም። ሊሆንም አይችልም።
 
ፖለቲካ ለህዝብ የመኖር ዋስትና ዝቅ ብሎ፦ ሎሌ ሆኖ መትጋት ማለት ነው። በቀላል አገላለጽ የህዝብን የመኖር ዘይቤ በአስተዳደር ጥበብ ማቅለል፤ ማሻሻል፤ ህዝብ መኖሩን ይወደው ዘንድ አስቻይ ሁኔታወችን በቅንነት ማመቻቸት ማለት ነው። ወደ ውስብስቡ የሳይንስ እና የፍልስፍና ተፈጥሮው ሳንዘልቅ።
 
ቀላሉን የህዝብ የማስተዳደር ተግባር ለመከወን ደግሞ ህዝብን በሰርክ ማገዶነት ማቅርብ ሳይሆን፦ መኖሩን ያለስጋት የሚከውንበት ፈሊጥ ተግቶ ማሰናዳት ነው። ይህ ሲያቅት ነው ብዙ ጊዜ የቀውስ ናፍቆት የሚመጣው። ለስሜን ህዝብ ጦርነት ከተፈጠረበት ዕለት ጀምሮ አስተናግዷል። ቢያንስ አሁን ይበቃዋል - ጦርነት። ስሜናውያን በቃን ጦርነት ብለው በህብረት ሊነሱ ይገባል። 
 
በዚህ ጦርነት ኦሮምያ፤ ደቡብ፤ ሱማሌ ሳይሆን የዶግ አመድ የሚሆኑት አፋር፤ አማራ፤ ትግራይ እና ኤርትራ ይሆናሉ። ይህ ደግሞ ቀደምትነትን #በሥልጣኔ ማስቀጠል ያልተቻለበት እንቅፋታዊ አንኳር ጉዳይ ነው። ስለሆነም በቃ ሊባል ይገባል - ደፍሮ። ጦርነት አተረፍኩ ካለ የሚያተርፈው #ጥላቻ#በቀል፤ እና #አመድ ብቻ ነው። ስለሆነም ለጥላቻ፤ ለአመድ እና ለበቀል ቅንጣት ቅዱስ መንፈስ፤ ቅንጣት ቅዱስ ጊዜ፤ ቅንጣት መዋለ ንዋይ፤ ቅንጣት አቅም ሊባክን አይገባም።
 
እምዬ ሲዊዘርላንድ ወደብ የላትም። እምዬዋ የኔቶ አባል አይደለችም። ቅድስቷ የG20፦ የG7 ወዘተ አገሮች ማህበርተኛ አይደለችም። ነገር ግን በላቀ ሥልጡን ዊዝደም ትንሽ አገር #በገነት ሆናለች። እራሱ ቆሻሻ የሚወገድበት መንገድ ምድሪቱን ፓራዲዝ እንድትሆን አድርጓታል። ጥበቡ ልቅና በልዕልና ነው።
 
እምዬዋ ኳሽ አይሏ ሲዊዝሻ ህዝቧን እምትመራው በቲም በ7 የጠሞኑ፤ የረጉ ብቁ ሊቀ - ሊቃውንታት ነው። ሥልጣኔ ማለት ይህ እንጂ ፓርክ መመረቅ አይደለም። የዓለም ሮል ሞዴሏ ሲዊዝሻ ስኖር አንድ ቀን የጥይት ድምጽ ሰምቼ አላውቅም። በሌላ በኩል ከፖሊስ ውጪ አንድ ቀን የሚሊተሪ ልብስ የለበሱ የጦር መኮንኖች፤ የከባድ መሳሪያ የጫኑ መኪኖች አይቼ አላውቅም። ለምን? ህሊና ተግባሩን በትክክል ስለ ሰው ልጅ እና ስለተፈጥሮ #በፈርኃ እግዚአብሄር ኃያልነት የሚከወንበት ባዕት ስለሆነ። ፕሮቴስታንት እና ካቶሊክ ሃይማኖቶች ተቋማታቸው ለሁሉም የሰው ዘር ሁሉ በፍቅር በአክብሮት ይረዳሉ በነጠረ እኩልነት። ኃይማኖት፤ ቀለም፤ የዞግ፤ የአህጉር የሚባል የልዩነት ጣሪያ እና ግድግዳ የለም። 
 
ለዚህም ነው ደጓ ሲዊዝሻ ከኢትዮጵያም፥ ከኤርትራም ፍትህ ያጡ ወገኖች መጠለያም ሆናለች አይደለም ለራሷ። ዓለም በሚተራመስበት ፖለቲካ ውስጥ ቅንጣት አቅም አይፈስም በሲዊዝ ፖለቲካ። ብልሆች ናቸዋ። መሪወቹ የሥም ውዳሴ፤ የቀይ ምንጣፍ ሽርጉድ ናፍቋቸው አያውቅም። በራስ የመተማመን አቅማቸው በልኩ ለልኩ ነውና። በዝምታ ውስጥ ስለ ህዝብ የመኖር ሰላም እንደ ንብ ይተጋሉ፤ ይታትራሉ በቅንነት እና በበዛ ርህርህና። ከቅንጣቷ እስከ ገዘፈው የመኖር ፈሊጥ ለድምጽ ይቀርባል፤ #የህዝብ #ውሳኔ ይሰጥበታል። ለሚወሰነው ውሳኔ ህዝብም መንግሥትም ተገዢ ይሆናል። ሲዊዝሻ እራሷም #ህግ ናትና
 
በብድር ገንዘብ የምትበጅት ኢትዮጵያ ዕድሜ ዘመኗን በጦርነት አገርን መምራት #ውርዴ ነው። ጦርነት የስኬት መንገድ አይደለም። #በቃ ጦርነት። በሰጥቶ መቀበል ዘይቤ ሥልጣንም ቢሆን ሼር አድርጎ ለኢትዮጵያ ህዝብ ሰላሙ ይጠበቅ። ኤርትራም ቢሆን ዓለም የሚመኜውን ስትራቴጅ ቦታ በተፈጥሮ ተቀዳጅታ፤ አንድ አይደለም ሁለት ወደብ ይዛ ከድህነት እርከን ከፍ አላለችም። ወጣቱ በስደት ላይ ነው የሚገኜው። በቀጣይ ጦርነት ውስጥ ቢገባ ድቀት እንጂ ትርፍ የለውም። የተሰደዱትም ወደ አገር ገብተው ሊማገዱ ይችላሉ። ይህ ደግሞ የመሪነት ስልት ዝንፈት ነው። ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አንጋፋ ፖለቲከኛም ናቸው። ሰላይም ናቸው። ግን ተመክሯቸው ለሰላም ሊሰግድ ይገባል ባይ ነኝ። አሻቅቤ መናገር ድፍረት ቢሆንም። ዕድሜ የማስተዋልን አቅል ሊያበራክት ይገባል ባይ ነኝ። 
 
የዘመነ #ትራንፒዝም ጉዞም ብልህነት ያለው የሰላም መስመር አሁን ላለው የአፍሪካ ቀንድ ፍጥጫ ምቹ አይደለም። #ትራንፒዝም ነገረ ራሺያን ያይዙበት መንገድ ለእኔ #ዊዝደም ነው። ልዩ ክስተትም ነው፦ በግልቡ ሳይሆን በጥልቀት ቢጠና። ለኖቤል ሽልማት የሚባለው ለእኔ ግርድፍ ፖለቲካ ነው። ትራንፒዝም እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሰምራ የተከተለችውን መስመር የያዘ ይመስለኛል። ይህን ዴሞክራቶች ይጠቀሙበት ዘንድ ተሽቶ ተጠቁመውም አልተጠቀሙበትም ነበር። እናም ሳያቅዱት የሆነው ሆነ።
 
ስለሆነም የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መሪወች የሁለቱ አገር ህዝብን ለመምራት ጥሞና ሊወስዱ ይገባል። በትህትና። መሪነቱ እልሁን ሰብሮ ፍጥጫውን ማርገብ ይገባል። ሁለታችሁንም በትህትና የማሳስባችሁ እስኪ ጥቂት ቀን ከፈጣሪያችሁ ጋር ምከሩ። ዕምነቱ ከኖረ። ከሌለም #ከማተር ጋርም ቢሆን ይመከር። ይህ የጋመ መከራ ተሸካሚው የስሜኑ ህዝብ እና በብድር ላይ የሚገኜው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ነው በጽኑ የሚቀቀሉት።
 
ያ --- የሙሽርነት፤ ያ --- የጫጉላ -- የሽርሽር፤ ያ - የግጥግጥ ጊዜ ብዙ የኢትዮጵያን ሆድ ዕቃ የኤርትራ መንግሥት ያይ ዘንድ ያለገደብ ተፈቅዶለት ነበር። ያ ሊደረግ የሚገባ አልነበረም። ሆድ ዕቃን እንደዛ ዘረጋግፎ የሜዳ ቄጤማ ማድረግ ብልህነት የጎደለው፦ የቅጽበታዊ ፖለቲካ ጉድ ነበር። ይደረግ ተብሎ ቢታሰብ ደግሞ ዘለቄታ ወዳጅነቱ ሊረጋገጥ ይገባ ነበር። ይህም ቢሆን አገር በዝርግ እና በዝልግልግ ሁነት ልትመራ አይገባም። ለዛውም ኢንሳን ከመሰረተ ሰብዕና። ጥንቃቄ ጎደል እርምጃ ነበር። ሳይ ያስደነግጠኝ ነበር። የአብይዝም የማግሥትነት ጉዳይነት ዕሳቤ ይህ በራሱ ይመዝነዋል። መሪነት ነብይነትንም ይጠይቃል። ቆቅ እና ጥንቁቅነትን ይጠይቃል። አገር ከደን ባለ ሁኔታ ልትመራ ይገባ ነበር። 
 
ከአንድ አገር ጋር ያለ የፖለቲካ ግንኙነት የገበጣ ጨዋታ ባለመሆኑ፤ ዓለም የሚያውቀው፤ በሰነድ ላይ የሠፈረ #ውል ሊኖር ይገባ ነበር። የኢትዮጵያ ህዝብም ሁለመናውን ያጣበት ስለነበር የማወቅ መብት ነበረው። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ግርማው ንቀት ሆኖ እንጂ። ፍርርሙ ወይንም ፍጥምጥሙ ከሁለቱ አገር መሪወች፦ ከጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ እና ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ #ልጅ በስተቀር ሌላ ሦስተኛ ሰው የሚያውቀው አይመስለኝም። ውጭ ጉዳይም ባይተዋር የነበረ ይመስለኛል። ነገረ ሥራው የምን ሞት የሆነ ነበር።
 
ለኖቤል ሽልማት ተብሎ የኢትዮ ኤርትራ እና የሰላም ሚር እንደ ተቋቋመ ነው የሚገባኝ። ጥድፊያው፤ ችኮላው፦ ቴርሞሜትር አልነበረውም። የቀጣዩ የቀውስ ቱማታ ከመከሰቱ በፊት ነበር - ሩጫው። የሆነ ሆኖ ሙሉ ስድስት ዓመት በቀውስ ለባጀ የስሜን ቀጠና አሁን ደግሞ ጦርነት ማጨት ለእኔ የፖለቲ #ወፈፌነት #ዕብደት ነው።
 
እኔ ሁልጊዜ ፕሬዚዳንት #ዘለንስኪን ስለምን የዓለም መሪወች ሌሰናቸው ሊሆኑ እንደማይችሉ አላውቅም። ፕሬዚዳንቱ እና አመራራቸው ምን አተረፈ? ብሎ ማጥናት ያስፈልጋል። ለዛውም ዩክሬን እንደ ኤርትራ እና እንደ ኢትዮጵያ በኋላቀር አገሮች ሊስት ውስጥ የምትታይ አገር አትመስለኝም። 
 
ኤርትራ ሁለት ወደብ ኖሯት፤ ኢትዮጵያም ምንም ወደብ ሳይኖራት፦ ያተረፋትን መሰረታዊ ጉዳይ በጥሞና መመርመር ይገባል። የኢትዮጵያ ፖለቲካ #ህዝብ #ቀደም አይደለም። ለዚህ ነው ህዝብ ለመብቱ ጉዳይ ሳይሆን ለግዴታው ብቻ እንዲሰለፍ ጥሪ የሚቀርብበት። ለዚህም ነው ሥልጣን ላይ የሚገኜው ሥርዓት እንደ ረገበ አልጋ የሚያረገርገው። አንድም ቀን ህዝብ ግዴታውን በሚወጣበት ጉዳይ ተወያይቶ እንዲወስን አይደረግም።
 
ያ ሁሉ ህዝብ የተማገደበት በባድመ ጦርነት፤ ያ ሁሉ ወጣት ያለቀበት የትግራይ እና የፌድራሉ ጦርነት፦ በአልጀርሱ፤ በደቡብ አፍሪካው ስምምነት፤ በአዲስ አበባ እና አስመራ ፍቅሩ ሲደራ ህዝብ ባይተዋር ነው። ውድቀቱም ምንጩ ይህ ነው። ጽናት የጎደለው ስምምነት #ንደትም ይህ ነው።
 
ወደብ፤ የባህር ኃይል ኢትዮጵያ ቢኖራት ተመራጭ ነው። የነበራትን ያሳጣት ጥበብ የገደለው የኢትዮጵያ #ዘባጣ እና #ዘረጦ ህዝብ ቀደም ያልሆነ ፖለቲካ ነው። ይህን ለማስተካከል ቅንነት፤ ግልጽነት፤ አወንታዊነት፤ ጥሞና፤ ማስተዋል፤ ፀሎት፤ እና ኢጎን አሸንፎ መገኜት ይገባል። በጦርነት የሚገኝ ትፍስት በደም የቀለመ ነው። ደም ደግሞ የውስጥ ሰላምን የሚዘርፍ ሰርክ የሚያባትት አረማሞ ደዌ ነው።
 
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶር ሙላቱ ተሾመ አስፈላጊ ሲሆን የጠሚሩ ልዩ አማካሪ ኦሮሞነታቸው አግዟቸው፦ አሁንም በቤተ- መንግሥት ጉዳይ ላይ ባለቤት ናቸው፤ እና ሰሞኑን በዓለም ዓቀፍ የዜና ዓውድ የመንግሥታቸውን ልሳን ያቀረቡበት አግባብ ለእኔ የሰጠኝ ግብረ ምላሽ የኖቤል ሽልማትን ጥበቃ ስለማሰጠት ሆኖ ነው ያገኜሁት። 
 
ኖቤል የተገኜበት መሰረታዊ አመክንዮ በሁለቱ አገሮች መሃል ጦርነት ቢነሳ ይበልዛል። ለዛ ማረሚያ - ላፒስ ቀድሞ ስላስፈለገ በብልህነት የተከወነ እንጂ፦ ለኢትዮጵያ ህዝብ በደም ጎርፍ መጥለቅለቅ ታስቦ አይደለም። ጠሚር አብይ አህመድ ተገፍተው ወደ ጦርነት ሊገቡ አስቻዩ ምክንያቱ "የኤርትራ መንግስት ቀውስ ጥማት ስለመሆኑ ለማጠያቅ" ነው ብዬ አምናለሁኝ።
 
በኢትዮጵያ አሁን ባለው ሁኔታ ሥርዓቱ እንዳይቀጥል፦ የሥልጣን ምኞተኛ የፖለቲካ ድርጅት ይህንን የሚመጥን አለ ብዬ አላምንም። ዶር አብይ አህመድ በዙሪያ ገባ አስበው በሚተረጉሙት ትብትብ የፖለቲካ አዟሪትን ሰብሮ ሊወጣ የሚችል አቅም አለ ብዬ አላስብም። እሳቸው በሚያጎርሱት አጀንዳ አቅምን ከማባከን ውጪ።
 
ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚቀርብ ጥሪ አለ ለአባ ቅንዬ አማራ። ሰሞኑን የአንድ አፍታው ልጅ አማን ልጅ የምለው እኔ ነኝ። ከዶር ዳኛቸው አሰፋ አልዘረፍኩም፤ እና ልጅ አማን "የአባቴን፤ የወንድሜን ሌጋሲ አስቀጥላለሁኝ፤ ሌላው ጥያቄዬ ይቆዬኝ ሊል አማራ ይገባል" የሚል እንደ አማራጭ አለስልሶ አቅርቦታል። ፕሮ ኤርትራ ነበር፤ አሁን "ትንሽ ስጋ በመርፌ ትወጋ" ሆኖበት ሊሆን ይችላል፤ አይፈረድበትም።
 
ሉዓላዊነት? ጁቡቲ አቅም ኖሯት፤ ኬንያ፤ ሁለቱ ሱዳኖች ድንበር ጥሰው ሉዓላዊነትን ሲዳፈሩ፤ የአማራ ህዝብ ሰርክ በድሮን ሲጨፈጨፍ ምነው ልጅ አማን ከሉዓላዊነት አሳንሶ አዬው? እዛው ላይም ጽፌየዋለሁ። ለእኔ የልጅ አማን ዕይታ ጨካኝ ሆኖ ነው ያገኜሁት።
 
የአማራ ህዝብ እኮ ነው እንዲህ ኦነግ ኢትዮጵያን በነፃ ሽጡልን ብሎ ለሚቀናጣበት ሥልጣን ያበቃው የነበር። በኦነግ ፖለቲካ ኢትዮጵያዊው ይሉንታ ፍቅፍቅ ሆኖ እንጂ። መጋቢት 18/2010 እኮ 45 ድምጽ ከግርባው ብአዴን ባያገኝ ይህን ጊዜ ማህበረ ኦህዴድ እግርብረት ላይ ይሆን ነበር። ፈጣሪ ብቻ የሚያውቀውን ዕንቁ የአማራ ልጆች የሎቢ ተግባር ትቼ ማለት ነው። 
 
እና ልጅ አማን በብዙ ነገር፤ በብዙ ምክንያት ሁልጊዜ ይጠቀም ለሚለው የማህበረ ኦነግ አመራር እስኪ አንድ ዘለላ በአማራ ጥያቄን ዕውቅና ስጡ ብሎ ያፋጥጥ። መሬት ላይ ስላለው አፓርታይዳዊ ሁነት ትናንት አዲስ ኮንፓስ ላይ ምርር ያለው የብልጽግና ደጋፊ ልጅ ኃይለየሱስ ሲገልጠው ነበር። እራሱ አቶ ኤርምያስ ለገሰ ለመመከት እስኪቸግረው ድረስ። የሰሞኑን የብልጽግና መር የኦፌኮወኦነግ ውሳኔም ልጅ ኃይሌ "አስደንጋጭ" ሲል ደጋግሞ ቁስል ባለው ውስጥነት ሲገልጠው ሰምቻለሁኝ። 
 
ሁሉ ሰው የማይገባው ሚስጢር አለ። ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ጣሊያን አድዋ ላይ ደግማ ብትገጥም፤ ሱማሌ ካራማራ ላይ ብትመጣ ምኞታቸው ነው። የባድመው ክስተትም የሚናፍቃቸው ነው። ልጅ አማን ያልተረዳው መሪው ጠሚር አብይ አህመድ አሊ ኢትዮጵያ ከተበጀቼበት ቀን አንድ ጀምሮ #በህገ ልቦና ነበርኩ ብለው ያምናሉ። መንፈስ ስለሆንኩኝ ታሪኩ ውስጥ ንጥረ ነገር ነበርኩ በማለት ነው ሁሉንም የቀደምት ትሩፋት ፍጥረተ ነገር እያማሰሉት፦ እዬበወዙት፤ ቅጥ መጠን እያሳጡት ነገር ዓለሙን ሁሉ ያሉት።
 
ይህ አይገባችሁም። ጠሚር አብይ አህመድ አሊ በኢትዮጵያ ከ3000 ዘመን በዘለቀ ታሪኳ ባልወለድም፦ በመንፈስ ነበርኩ ነው የአብይዝም ፋንታዚ። ፋሲልን ነጭ አመድ ለቅልቀው ሲወደሱ ሰንብተዋል። አድዋም የባለታሪኮች ምስል ተዘሎ የሳቸው፤ ያም አልበቃም ያን ዓለም ዓቀፍ ገድል ዜሮ ዜሮ ሲሉ ሰይመውታል። ዱላ ነው። ማራከስም ነው፦ ሥሙ እራሱ በተደሞ ቢጠና። 
 
በአንድ የሬቻ ዋዜማ አቶ ሺመልስ አብዲሳ ወደ አባቶቻችን የ3000 ሺ ዘመን ታሪካችን እያስመለስን ነው። ይህን መሰል የኦሮሞ ታሪክ በጋሜ ሚዲያ እያስተማርን ነው ብለዋል። በወቅቱ ጽፌበታለሁኝ። ቀድቸውማለሁኝ። ግርም ነው የሚለኝ። ግልብልቡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተግ አድርጎ የማህበረ ኦነግ የመስፋፋት መንፈስ ሊገታ ቀቶ ሊገባው የቻለ አይመስለኝም። 
 
እኔ የምለው ------------
 
1) ጦርነት አያስፈልግም! ለሁለቱ አገር መንግሥት እና ህዝብ። እልኃችሁን ዋጥ አድርጋችሁ - ተወያዩ።
2) የአማራ ህዝብ ተሳትፎ በኢትዮኤርትራ "ዳግም ጦርነት" በፍፁም ሊታሰብ የሚገባ ጉዳይ ባይሆን ምርጫዬ ነው። የትግራዩ ጦርነት ጊዜም አበክሬ አስገንዝቤያለሁኝ። የከሰረው ማን እንደሆን፤ ትርፋ ለማን? ስለማን? እንደሆነም መመዘን ነው። ህወሃት እኮ አልሞትባይ ተጋዳይነቱ እንጂ እርቃኑን ነው ያለው። ያ አንጋፋ የ50 ዓመት ዞጋዊ ፕሮ ሶሻሊዝም ድርጅት ዛሬ ለራሱም ለዛ አሳር ለሚከፍል በዬዘመኑ የትግራይ ህዝብም አልሆነም።
 
ለአማራ ህዝብ ሻብያ፤ ህወሃት፤ ብልጽግና፤ ኦፌኮ፤ ኦነግ፤ ወዘተ አይደለም የስትራቴጂ የታክቲክ ወዳጆች አይደሉም። ድርጅታቸው መሠረቱ የአማራ ጥላቻ ነው። ያን ሲያስወግዱ ድርጅታቸው ይፈርሳል። የእንቧይ ካብ ይሆናል። ዓላማ እና ግባቸው ይፈልሳል። የራሱን ህዝብ በድሮን ለሚጨፈጭፍ ሥርዓት ይቀጥል ዘንድ ሉዓላዊነቴ ተደፈረ ብለህ ተነስ ማለት የተከዳውን የአማራ ሕዝብ፤ ጨካኝ የሆነ ፍርደ ገምድልነት ነው። ለዚህ ጥሪ የሚሰለፍ አይኖርም ብዬ አይደለም። ይሞክረው ፦፦፦፦፦ ሞቱን ሰንቆ ትቢያውን ፦፦፦፦፦ ያተርፋል። 
 
ለአማራ ህዝብ ቅኑ የደቡብ፤ የአፋር ህዝብ ምንአልባትም የሱማሌ ህዝብ በውስጣቸው ሊያዝኑለት ይችሉ ይሆናል። በሰማይ ደግሞ እግዚአብሄር // አላህ እሱ የሰጠው ቅንነቱ ብቻ ነው ያለው። ስለሆነም ብልጽግናን ጨምሮ ማህበረ ኦነግ ይሁን ህወሃት፤ ህወሃት ይሁን ሻቢያን አምኖ የአማራ ህዝብ ተስፋዬን ላዝልቅ፦ መጠለያ ልሻት ቢል "አይጥ ለሞቷ የድመት አፍንጫ ታሸታለች" ይሆናል።
 
እኔ የማምነው በሰላማዊ መንገድ በሎቢ መትጋት ነው። አቅጣጫ የታወቀ ትግል ሲኖር። ልጅ አማን ታስታውስ እንደ ሆነ የአማራ እና የአፋር ጉዳትን የውጭ ኃይሎች እንዲዩት ዶር አብይ አይፈቅዱም ነበር። ይህ ለስልት ነበር። በሌላ በኩል በጦርነቱ---- በጦር ወንጀል፤ በዘር ማጽዳት፤ በሰባአዊ መብት ጥሰት በሦስት ዘርፍ ተከሳሹ የአማራ የጸጥታ ኃይል ብቻ ነበር። የኤርትራ መንግሥት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት፤ ህወሃት በሙሉ ኃይላቸው ተዋግተው በጦር ወንጀል ብቻ ነበር ተጠያቂነታቸው። ሚዛኑን ያልጠበቀ ውሳኔ ነበር። ይህ በአንድ ደብዳቤ ነው ቀጥ ያለው። ከግንቦት መግቢያ 2023 ጀምሮ ፀጥታ ነው የሰፈነው። አንድ ሰው አልተሰዋበትም። በሃሳብ ልቅና ብቻ ተመከተ። 
 
ሌላም ሌላም ማንሳት ይቻላል። ይህን ስልህ ጦርነት ከተጀመረ አናርኪያዊ የህዝብ ጉዳት የለም እያልኩህ አይደለም። የጎዳ የበደለ ይጠዬቅ፤ ይካስም። በተለይ የኢትዮጵያ እናቶች ነገር ውስጤ ቁስል ነው የሚለው። የጠሚር አብይ use and through method ለጊዜው ቢሰራም መካች ሲያገኝ ግን ቢና ጢናው ይወጣል።
 
ዕውነቱን ብነግርህ ልጅ አማኑ የማህበረ - ኦነግ፤ የማህበረ - ህወሃት ሊቃናት ስለ አማራ ህዝብ ማሰብም ሆነ መጨነቅም አይፈልጉም። ለዚህ ድውይ መንፈስ መማገድ ከጅልነት ያለፈም ነው። ማንንም የአማራ ህዝብ ልቡን ጥሎ ሊያምን አይገባም። ማን? ምን አድርጎለት? ማንስ በክፋ ቀኑ ቁሞለት? የመከራ ቡፌ እኮ ነው የባጀበት።
 
ሌሎችም የዜግነት ፖለቲካ አራማጆች ቢሆኑ የአማራ ህዝብ በጥርጣሬ እንዲታይ ከሚያደርጉት በስተቀር ፋይዳው ይሆናሉ ብዬ አላስብም። ዕጣ ነፍሴንም ብቀር ይህ ጽኑ አቋሜ ነው። ፕሮ ኤርትራ፤ ፕሮ ህወሃት ሚዲያወች በምን ላይ እንደሚተጉ አውቃለሁኝ። የአማራ ህዝብ ጥቅሙን የሚፃረር ተጠቃሚ መሆኑን ካልፈቀደ በስተቀር ሁሉም እግዚአብሄር በሰጠን ጊዜ እና ሜዳ ተፈትኖ ወድቋል። በወደቀ ስልት እንጓዛለን ካለ የአማራ ፖለቲካ የቁልቁለት መንገድ ለዛውም በዳጥ ይሆናል። 
 
ጦርነት የምትወደውን ሁሉ ያሳጣል። የአማራ ክልል ጦርነት - ጦርነቱን ያስጀመሩት እና የመሩት ወገኖቼ ያተረፋትን እና የከሰሩትን እራሳቸው ይመርምሩት። በ፶ ዓመት የማንተካውን ቅንነት ረፕ/ ዶር አንዱአለምን መሰል አሳጥቶናል። ድቀቱ ሆነ ውድመቱ የበቀሉ ገጀሞ ንፁኃን ገበሬወችን፥ መነኮሳትን፤ የአብነት ተማሪወችን ቤተ - መቅደሳችነን አስደፍሯል። በባዕቱ አማራ ሰላሙ ታውኳል። አሁንም ቀጥሏል። ከዚህ ላይ ደግሞ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት አማራ ሆይ! አንጋች እና ሪሞርኬ ተጎታች ሁንና ተማገድ እደግመዋለሁኝ ጭካኔ ነው። በተለይ እንደ ልጅ አማን ላለ የሚዲያ ሰብዕና።
 
ፈጽሞ ኢትዮኤርትራ ጦርነት ሊጀመር አይገባም ባይ ነኝ። በሌላ በኩል የአማራ ልጅ አሁን ያለበትን ሳይለንት ዲስክርምናሽን፤ ሳይለንት ኔግሌሽን፤ ሳይለንት አስምሌሽን በሚገባ ያጠና፦ ያስተዋለ ፖለቲካ ያስፈልገዋል። እኔ ግርባው ብአዴንም የአማራን የመረቀዘ መከራ ይታደገዋል ብዬ አላስብም። አላምንምም። አቅምም - አላባክንም።
 
በጣም ያስተዋለ፤ የጠሞነ፤ ብልህ አዲስ መንገድ በአዲስ ተፈጥሯዊ ሰብዕና እራሱን ችሎ የሚያቆመው ግን በንግግርም የታረመ ብሩህ ጎዳና ለአማራ ህዝብ ያስፈልገዋል። ሳይለንት ማጆሪቲውን በዕውነቱ ልክ ከጎኑ የማሰለፍ አቅም የአማራ ፖለቲካ ሊኖረው ይገባል። ከዬትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ቅሪት አካል ሆነ መንፈስ ውራጅ ወይንም ትውስት የሚበጅ አይመስለኝም ለአማራ ፖለቲካ። 
 
ሌላው ኤርትራ ተቃዋሚወችን እዬረዳች ነው የሚል ስሞታ በፕሮ ብልጽግና፤ ኢትዮጵያ የኤርትራ ተቃዋሚወችን እያደራጀች ነው በፕሮ ኢትዮኤርትራ ሚዲያወች ይደመጣል። ይህ አገሮች የሚያደርጉት የተለመደ - የሚጠበቅም ነው። መፍትሄው ሰውኛ እና ተፈጥሮኛ አስተዳደር በሥርዓታቸው ማስፈን መቻል ነው። ይህ ካቃታቸው የትኛውም ወገን እራሱን ይከላከላል። የሚገርመኝ ኢትዮጵያዊ ሆኖ አድሎው ለኤርትራ ሲሆን ---------ይጎረብጣል። እናት ብትጠቁርም፥ ብትከሳም ልትገፋ፤ ቸል ልትባል አይገባም። ከሁሉም በላይ ጉልላት ናት እና። እናት አገር ከግል ምቾት በላይ በማስተዋል ሊሳሳላት ይገባል ብዬ አስባለሁኝ።
 
በኤርትራ በኩል ወደ 12 የሚጠጉ ምንቅናቆች፤ አንድ የግል ታጋይ ነበሩ። በአካልም አግኝቼ አወያይቻቸው ነበር። የት ገቡ እና ነው አዲስ የሚደራጀው? ሟሙ ወይንስ ተሸበሸቡ? ጠንካሮች ነበሩ። በሌላ በኩል የሁለቱ አገር መንግሥታትን ማጣጣል፤ ትርፍ መናገር፤ መዘለፍ፦ ማቃለል በፍፁም የሚገባ አይመስለኝም። ቢያንስ ውህድ ማንነት ላላቸው ለእኛወቹ ሥነ ልቦና እንጠንቀቅ - እንደማለት።
 
እንዴት ናችሁ ውዶቼ፤ ልነካካው የማልሻውን አጀንዳ ነው ዛሬ ያነሳሁት። ምክንያቱም የሠራሁበት፤ የማውቀው ስለሆነ በተደሞ ነው ስከታተለው የቆዬሁት። አቅም በዚህ ዙሪያ ማፍሰስ ፈጽሞ አልሻም። ህወሃትንም በሚመለከት ዝምታዬም በዚህው ምክንያት ነው።
መሸቢያ ጊዜ። እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
26/02/2025
#ጦርነት #በቃን!
የአማራ ህዝብ #ለአንጋችነት ብቻ የሚፈለግበት ሁኔታ ይቁም!
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?