ዘለግ ያለ ሙግት ከዶር ገዱ አንዳርጋቸው ጋር። ዕውን ዶር ገዱ አንዳርጋቸው ጠሚር አብይ አህመድን ጠቅላይ ሚር ከመሆናቸው በፊት #አያውቋቸውም ነበርን? ኮሚኩ ድራማ። ተያያዥ ጉዳዮችንም አነሳለሁኝ። የእሳቸውን ጉዳይም በዝምታ ነበር ስታደም የባጀሁት። ዛሬ ግን ይደባበስ። በእኔ ቤት እንክህ እንክህ አይታሰብም እና።
ዕውን ዶር ገዱ አንዳርጋቸው ጠሚር አብይ አህመድን ጠቅላይ ሚር ከመሆናቸው በፊት #አያውቋቸውም ነበርን? ኮሚኩ ድራማ።
ተያያዥ ጉዳዮችንም አነሳለሁኝ። የእሳቸውን ጉዳይም በዝምታ ነበር ስታደም የባጀሁት። ዛሬ ግን ይደባበስ። በእኔ ቤት እንክህ እንክህ አይታሰብም እና።
"አቤቱ አድነኝ፤ ደግ ሰውአልቋልና፥
ከሰው ልጆችም መተማመን ጎድሏልና።"
Anchor Media '' ትልቁ ጥፋታችን ስልጣኑን ለአብይ አህመድ መስጠታችን ነው።''
ዶ/ር ገዱ አንዳርጋቸው
እንዴት ዋላችሁ አመሻችሁም ማህበረ ቅንነት። ደህና ናችሁ ወይ????
ጋዜጠኛ መሳይ መኮነን በቀደመው ጊዜ የአማራ ክልልን በቁንጮነት ይመሩ ከነበሩት፤ "በሱሴ" ኦሮማራ ዘመን ቲም መሪነት፤ ቀን ቀና ሲልም የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ የነበሩት፤ ቀን ደፋ ሲልም የጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ የደህንነት አማካሪ የነበሩት፤ ቀን ሲያነክስም ከሁሉም የሥልጣን ኃላፊነቶች ጋር ፍች የፈፀሙት ዶር ገዱ አንዳርጋቸው ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ክፍል ፩ አዳመጥኩት። ክፍል ሁለት መጠበቅ አላስፈለገኝም። ሳዳምጣቸው ነውና የባጀሁት። አዲስ ነገር የለውም።
ጋዜጠኛ መሳይ መኮነን አቅም ባለው ሁኔታ አልሞገታቸውም። ምክንያት እሱ #ተስፋ ለሚያደርግበት አዲስ የለውጥ ዋዜማ አጓጓዥ በመንግሥት ሥርዓት ውስጥ ጠቀም ያለ ልምድ ያላቸውን፤ በውጭ የዲፕሎማቱ መድረክም ከሁሉም የተሻለ አጋጣሚ ተፈጥሮላቸው ከነበሩ ፖለቲከኛ የሚገኘውን ተመክሮ ሥራ ላይ ለማዋል ታስቦ ይመስላል ውይይቱ #የቤተ - #ዘመድ ዓይነት ይመስል ነበር - ለእኔ።
ዶር ገዱ አንዳርጋቸው በውይይታቸው ሁሉ ዝንፍ ሳይሉ #ከደን ማደረግ የሚሹትን ነገረ ኦህዴድ እዬከዳደኑ የኦሮማራ #ጥበቃ መልሳቸውን ረጋ ብለው ሰጥተዋል። ነገረ ማህበረ ኦነግ ጉዳይ ንክች እንዲል አይሹም፤ ህውሃትሻም #ሽው ያላቸው ይመስላል። እኛ የምናውቀውን ነው የነገሩን። ሌላ የነገሩን ነገር የለም። ለእኔ አዲስ መረጃ የምለው የለኝም። ይህ እንግዲህ የኢህአዴግ ቤተ - ሚስጢር ዲስፕሊን ሊሆን ይችላል። በውይይቱ አወንታዊ ትዝታ እንዳለባቸው ተረድቻለሁኝ - ከኢህዴግም ጋር።
#በአደባባይ የሰማነው የዶር ገዱ አንዳርጋቸው ጥንካሬ።
1) በዛ ቋያ ወቅት የአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ ፋና የነበሩትን ኮነሬል ደመቀ ዘውዱን ወደ ማዕከላዊ እስር ቤት እንዳይሄዱ ማስደረጋቸው፦ ለህወሃት አሳልፈው አለመስጠታቸው ለወቅቱ ትልቅ አስተዋፆ ነበረው። አመክንዮ የሚዳኜው እንደ ወቅቱ ነውና። ትግሉም ሊጨነግፍ ይችል ነበር። በሂደቱም ተጨማሪ ሰማዕታት ሊኖሩ ግድ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ እንደዛ ባህርዳር ላይ በስናይፐር ያለቁ ንጹኃን ወገኖቻችን ይህን መሰል የቆረጠ ወገናዊነት ቢያሳዩ ኖሮ በመሪነታቸው ዘመን መስዋዕትነቱ ይቀንስ ነበር። ሰማዕቱን አቤንም አናጣም ነበር።
2) ነገረ አባይን በሚመለከት አደጋ ላይ መሆኑን ኢትዮ 360 አበክሮ ይገልጽ ነበር። ባለሙያ እዬጋበዘ ያወያይ ነበር። ያን ጊዜ የዶር ገዱ አንዳርጋቸው መንግሥት አባይዝም ፈጽሞ አጀንዳው አልነበረም። ጉዳዩ ከረር ሲል ግን በውጭ ጉዳይ ሚር በነበሩበት ወቅት የእሳቸው እና የአንባሳደር ዶር ስለሺ ሚና ጉልህ እንደነበር አዳምጫለሁኝ። አሳክተዋልም።
3) ከሥልጣናቸውም ተነስተው፤ አሁን እንዳጫወቱን የጡረታ መብታቸው ማዕቀብ ከተጣለበት በኋላ በከፍተኛ ቁጥጥር ላይ ሆነው በፓርላማ ያቀረቡት #ጉልበታም ሃሳብ ማምሻ ላይ ቢሆንም፦ ይህንን የማያደርጉም ስለአሉ ለታሪክ ስንብታቸው መልክ እንዲኖረው ያደረገው ይመስለኛል። ይህም ሆኖ መውጣት ተፈቅዶላቸው ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ መደረጉ ደግሞ ሌላው ላቅ ያለው ዕድል ነው። ህይወታቸው መትረፋም እንደገና የመፈጠር ያህል ነው። ቲም ዶር አንባቸው ይህን ዕድል አላገኜም።
የሆነ ሆኖ ሦስቱ በህረ ጉዳይ ለእኔ ትርጉም ይሰጠኛል።
በኦሮማራ ጥምረት ለፖለቲካ ሥልጣን የበቃው ማህበረ - ኦነግ እና ማህበረ ደህዴን እንጂ የአማራ የፖለቲካ ሊቃናት አፈር እና ካቴና፤ መሰደድ እና መነቀል ነው የደረሰባቸው። ይልቁንም ደቡብ አብዛኛውን የፌድራሉን #ቁልፍ ቦታ ይዟል። ውጭ ጉዳይ፤ ደህንነት፤ ኢኮኖሚ፤ አፈጉባኤ፤ ክህሎት ……… ወዘተ ካቢኔ ላይ ደቡብ ጎልበት ብሎ ይታያል። ኢዜማ ሲጨመር የበለጠ ይጎላል። የትምህርት ሚር ቦታ፤ የጤናው ቦታ በዘመነ ኢህአዴግ የብአዴን የነበረ ነው። ሥልጣኑን ሚዛን ለማስጠበቅ ከኦሮሞ አይወሰድም። ከአማራ ድርሻ ነው ቦጨቅ ቦጨቅ የሚደረገው። እነ ዶር ገዱ ለሥልጣን አልታገልንም ብለው በአደባባይ ስላወጁ ሊሆን ይችላል። ድርጅታቸው የኢቤንት ነበር። ካባ በቦንዳ የሚያከፋፍል።
ሥልጣነ መንግሥቱን የተረከበው ኦህዴድ ሁሉንም ኃላፊነት ሊወስድ ሲገባ፤ የኦሮማራ ግዴታ ሙሉ ለሙሉ ተሸካሚ ግርባው ብአዴን ነበር። መሸከም አይሰለቸው። ሌላ ቦታ ተቃዋሚ፤ ተፎካካሪ አይታሰብም መድረክ ለማግኘት። ለዛ በገፍ ለገባ የተቃዋሚ ፖለቲከኛ አቀባበል እና መስተንግዶ ቲም ገዱ ነበር። በዛን ጊዜ ጭምቱ ዶር ለማ መገርሳ ግን #ነጠላ የነበረውን ኦህዴድ በሦስት ድርብ አቅም አባዝተው በሚገባ አደላድለው አደረጁት። መደበኛ ተግባራቸውን እንጂ እንግዳ ተቀባይ እና ግብረ ሰላም አዘጋጅ አልነበሩም።
የሚገርመው ዶር ገዱ አንዳርጋቸው ለመመረቂያቸው በፃፋትም፤ በተለያዬ ጊዜ በሚያደርጉት ቃለ- ምልልስም የአማራ ህዝብ እኩል ፖለቲካ ሥልጣን ላይ #እንደተወከለ አድርገው ይገልፃሉ። ይህ ፈጽሞ ሊገባኝ የማይችለው የአመክንዮ #ፍልሰት ወይንም ስደት ነው። ያደለው በጥናት የተመሠረተ ስታስቲክስ ሠርቶ ተጨባጩን በፋክት ማቅረብ ይችላል። ያም ቢቀር የተዛባ መረጃ መስጣት የታሪክ ጆሮ ደግፍ መፍጠር ነው። ሌላው ቀርቶ እሳቸው ይመሩት በነበረው ውጭ ጉዳይ ሚር ሁለቱም ዲኤታወች ከኦህዴድ ናቸው። መምሪያወችም በመሰሉ ሁኔታ እንደተዋቀሩ ሰፊ ስሞታወች ይደመጣሉ።
አንድ የሚር መ/ቤት ለሌላ ዞግ ከተሰጠ ምክትሎች ኦህዴድ ይሆናሉ። በዶላር ከሚከፈልበት ቦታም በብሄራዊ፤ ከአህጉራዊ ድርጅቶችም፤ በዓለም ዓቀፋ መድረክም ዳጎስ ያለ ዶላር ዝቀሽ ከሆነ ኦህዴወኦነግ ይመደቡበታል። ጠብ የምትል ቅንጥብጣቢ የአማራ ልጅ አይደርሰውም። ሞቱ እና መከራው ግን ያው ቡፌውን ከፋች የአማራ ልጅ ነው። የሚገርመው ለነገ የኢትዮጵያ ተንሳኤም አማራ ማገዶነትህን ቀጥል ነው የዶር ገዱ ጎዳና። እቅፍ ድግፍ የሚደረጉትም ይህን ያሳካልናል ነው። ቀደም ባለው ጊዜ ዶር ገዱ አንዳርጋቸው በግንቦት 7 ይታሙ ነበር።
የሆነ ሆኖ እዞችም፤ ቁንጮ የጸጥታው ዘርፍ ሙሉ ለሙሉ ኦህዴዶች ናቸው። የሚገርመው የአቶ ገዱ አሁንም ለኦሮማራ ያላቸው ስፍስፍ የሚል አንጀት እና የሚያደርጉለት ጥበቅ የሚገርም ነው። የአማራ ህዝብ፤ የነፃነት ተጋድሏችን በመና ያወራረደ፤ የመከራ ዘመንን በእጥፍ ድርብ ያቀናበረ ጉድ ነው #ኦሮማራ። አይመልሰው ፈጣሪ አምላኬ። አሜን። ይህ ሰላቢ። እንዴት እንደተጫወተብን። የእኛ ድካም እማ የትቢያ ያህል ነው። ግፍም ነው። በቃ በጣት የሚቆጠሩት ሲጠራሩ፥ ሲሰባሰቡ፤ ሲበተኑ እንደገና ፈሰው ሲለቀሙ መሽቶ ይነጋል።
በኦሮማራ ጥምረታዊ ጉዞ በዛ ሂደት የተጠቀመ ተጠቅሞ ሊሆን ይችላል። እሳቸው በዓለም ዓቀፋ ዲፕሎማሲያዊ መንገድ ዕውቅና ጥላ ከለላ ብቻ ሳይሆን፤ ዶር ለማ መገርሳ የተሻለ ዕድል እና ትምህርት፤ ኢንጂነር ታከለ ኡማ እና ሌሎችም የላቀ የትምህርት ዕድል አግኝተው ዶር ሆነዋል። እነ ዶር አንባቸው መኮነን እና ቲማቸው፤ እነ ኢንጂነር ስመኜው ደግሞ አፈር ላይ አርጅተዋል። አማራ ናቸዋ። ሚሊዮን እናቶች የአሳር #ቡፌ አስተናግደዋል። ሌሎቹ ደግሞ እንደ ወጡ ቀርተዋል።
አሁን "ስሜታዊ" ነበር ይሉናል። እሳቸው እኮ የደረጁ ፖለቲከኛ ናቸው። የፈላውን ስሜት ማስከን፤ ጥላቻውን ተዋግቶ መልክ ማስያዝ የእሳቸው የልቅና ልክ ሊመክተው ይገባ የነበረ አመክንዮ ነው። ይህ ዝርክርክነት እና ዝልግልግነት ነው የስንት ሁለገብ ድቀት መሠረት የሆነው።
#በነገረ አማራ ጉዳይ ውስጣቸው ስለመነካቱ ………
1) የአቶ ጃዋር መሃመድ ከበባ እና ጦሱ፦
2) የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ህልፈት እና ዲል ያለው የመከራ ትዕይንት ……
3) የአማራ ታጣቂ ትጥቅ መፍታት እና የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጁ ………
#በቃ ይህ ብቻ ነበር ግፋ??????! እስቲ የማስታውሰውን የመከራ ማሳ ልዘክር ……… እሳቸው ሥልጣን ላይ፤ ግጥግጥ ላይ ሳሉ ብቻ የሆነውን፤ ጦርነቱን የግራ ቀኙን አላነሳም። ጉዳቱንም።
1) በሱማሌ የተፈናቀሉ ወገኖቻችን ፈቃዳቸው ሳይጠዬቅ 1/2 ሚሊዮን በአዲስ አበባ እና በዙሪያው እንዲኖሩ መደረጉ ዕውነቱን ቁልጭ አድርገው ዶር ለማ መገርሳ ተናገሩ። አዲስ አበባን በዲሞግራፊ ማመጣጠን እንዳስፈለገ። ያ ጉዳይ ሁለተኛው የዓለም ጦርነትን ያስነሳ፤ ብዙ እልቂትን ያስተናገደ ስለመሆኑ ለድርጅው የፖለቲካ ታጋይ ዶር ገዱ አንዳርጋቸው ስለምን ባዕዳ ሆነ???? ወይንስ ያምኑበት ነበርን አሉታዊ ዴሞግራፊውን???? የአዲስ አበባ ህዝብ እኮ አሳሩን ነው ያዬ። እልል ብሎ በደገፈ።
2) አጣዬ ስንት ጊዜ ነደደ? አጣዬ የኢትዮጵያ አካል አይደለምን????? የህፃናት ተስፋ የዶግ አመድ ሲሆን አባት ናቸው እና ከውስጣቸው እንደምን አልገባም? ህፃናት እኮ ወላጅ እንዲሆኑ የተገደዱበት አጋጣሚ ብዙ ነው። ብዙ ህፃናትም ወላጅ አልባ ሆነዋል። ሞቱም በሚተከል ችግኝ ጥላ ከተገኜ በቂ ነው ያዳመጥነው የመረጧቸው ጠሚር አብይ አህመድ ገመና ነበር። ይህን ችሎ አብሮ መሥራት እንዴት ቀለላቸው??? ሞቱ ላይበቃ መስቃው እና ቅላፄው????
3) አዲስ አበባ ከንቲባነት ቃል የተገባው ለብአዴን እንደነበር ሰምቻለሁኝ። እርግጠኝነቱን ተመካካሪው ያውቃሉ። 50+ አማራ ሆኖ ለ32 ዓመታት አንድም የአማራ ልጅ የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆኖ አያውቅም። በቀደመውም፦ አሁን ባለውም ፖለቲካዊ ተሳትፎ ይህን እንደምን ያጣጥሙታል ዶክተሩ???
በዘመነ ኦሮማራ ህግ ወጥቶ ኢንጂነር ታከለ ኡማ፤ እሳቸው ሲነሱም ወ/ሮ አዳነች አበቤ ሲመደቡ ዶር ገዱ እና ቲማቸው የት ነበሩ? ፍትኃዊ ነበር ሂደቱ??? በለገጣፎ ለገዳዲ፤ በሰንበታ፤ በቡራዩ የተፈፀመውስ ስቃይ እና የዘመን ቁስለት ማን ያክመው? 5 የአዲስ አበባ ልጆች አደባባይ ላይ ሲረሸኑ፤ 1300 ጦላይ ሲታሠሩ ተመቻቸው ወይ ዶር ገዱ????? እስከ አሁንም ከእስር ያልተለቀቁ አሉ። ከጉለሌ ወደ ባህርዳር እንዲመለሱ ስለተደረጉ ወገኖቻችን ዶር ገዱ ውስጣቸው የተሰማው ነገር አልነበርንም ማለት ይሆን???
5) ነገረ ብልጽግና በውራጅ አባል፤ ደንብ፤ ፕሮግራም፤ ጉባኤ እና ማዕከላዊ ኮሚቴ ሳይኖረው ዕውቅናውን የምርጫ ቦርድ ሲሰጠው አንድ በድርጅት ውስጥ ዕድሜ ዘመኑን ለዘለቀ የፖለቲካ ሊቅ መርህ ይጠይቀኛል ብሎ እንዴት አያስብም??? የአመሰራረቱ ግድፈት እኮ ነው እሳቸውን ከፖለቲካ ሚና ውጭ ያደረጋቸው።
በቃ እሳቸው ስልጣናቸው እስካልተነካ ድረስ የሚጎረባብጥ ነገር አይኖርም ማለት ይሆን?
6) እነኛ የደንቢደሎ ዕንቡጥ የአማራ ልጆች እገዳ ለዶር ገዱ የሠርግ የሙሽርነት የጫጉላ ሽርሽር ነበርን? ያመለጠችው ያቺ ገራገር ወ/ት አስምራ ሹምዬስ የት ገባች ብሎ መጠዬቅ እንደምን አይችልም አንድ የአማራ ህዝብ መሪ ሃዘኑ ቀርቶ ማለት ነው። መጀመሪያ በሃረምያ 3000 ከዚያ በደንቢደሎ 45 ሺህ የዩንቨርስቲ ተማሪወች በማንነታቸው ከትምህርት ገበታ ውጭ ሲሆኑ፤ በአማራ ክልል ሁሉም የኢትዮጵያ ልጅ ተረጋግቶ ተምሮ መመረቅ ሲችል፥ ተስፋ ላጡት የአማራ ወጣቶች ማን ዋቢ ይሁናቸው? ቢያንስ የአማራ ክልል ተማሪወች በክልላቸው እንዲማሩ ማድረግ አይቻልም ነበርን? ሌላው ቀርቶ በአማራ ክልል ላሉ ዩንቨርስቲወች ለቦርድ አባልነትም በሞፈር ዘመት ነው የምናዬው። ሌላው ክልል አይደፈርም። ልውስውስ ልፍስፍስ ያለ ጉድ።
7) መተከል የሰርክ ብርንዶው የአማራ ልጅን ማሰቃዬት ነበር። ያስ ለአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ህሊና በምን ተስተናገደ????
8) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ በዓላት በመጡ ቁጥር የሚሞተው፤ የሚታገተው፤ የሚታሰረው የመስቀሉ አማኝ እንግልት እና ሰማዕትነት የዜጋቸው ጉዳይ አጀንዳቸው ሊሆን እንደምን አልቻለም - ለዶር ገዱ አንዳርጋቸው???
ውሃ በቀጠነ ቁጥር የአማራ ልጅ ከገብያ እንደተገዛ ከረጢት በገፍ ሲታሠር ትክክል ነበርን? በዬጊዜው ለእስር የታዳረጉትን ፎቶም ከእጄ ያለውን ለጥፌያለሁኝ። አድካሚወች።
9) የባህርዳር የመሪወች በዬጊዜው ሲቀዬሩ፤ የአመራር ተከታታይነት ሲጠፋ - ሲደረመስ፤ ህዝቡ እረኛ አልባ ሲሆንስ ይደላ ነበርን የለውጡን ቲም መሪ በመሆን ለተንቀሳቀሰ የፖለቲካ ሊሂቅ? የቤንሻጉል ጉምዝ መሪ እኮ በዘመነ ህወሃት የነበሩት ነው የዘለቁት፤ ኦሮምያ እና ሱማሌ አንድ ጊዜ ብቻ ነው ለዛውም ለጠሚሩ ፕሮጀክት ስኬት የተቀዬሩት።
አማራ ህዝብ ላይ ግን አቅመ ቢስ ናችሁ ተብሎ ሰርክ የጓሮ ጎመን መሆን ይደላ ነበርን???? አይቆጠቁጥም፤ ጥቃት አይሰማም? የአማራ ሊሂቅ ከሌሎች አንሶ የሰርክ መዘባበቻ???? ማህፀንን እንደ ዱባ ይቀረድዳል ከህሊናው ጋር ላለ የአማራ ልጅ ሁሉ። ንቀቱ ፋስም አለበት። በ7 ዓመት አንድ የሚመጥን ማጣት????? አቅም ያለው መሪ አላሳካችሁም ነው እኮ ዱላው። ለመሆኑ ማን ነበር የመስተዳድሩ መሪ ዶር አብይ ወይንስ ዶር ገዱ??????? ውሏቸውም አዳራቸውም እኮ አማራ ክልል ነበር የዶር አብይ አህመድ አሊ። ከሊሂቃኑ መሰዋት በኋላ ነበር እግራቸው የተሰበሰበው።
10) የአማራ ክልል ከንቲባወች በተለይ #ባህርዳር እና ጎንደር ሰክነው እንዲሰሩ አለመፈቀዱ ይህንንም እንደ አልባሌ ይታይ ይሆን???? ለምን ተብሎ መጠዬቅ እንደምን አልተቻለም????
11) በህወሃት እና በፌድራሉ ጦርነትን በሚመለከት የተጎዱት ሦስቱ ክልሎች ሆነው የዲፕሎማሲው ማህበረሰብ አፋር እና አማራ ክልል በአካል ተገኝተው ጉዳቱን እንዳይረዱ የተደረገበት ምክንያት የአዘቦት ጉዳይ ሆኖ ይሆን????
12) አዲስ አበባ የአማራ ልጅ አትገባም ተብሎ በዬፌርማታው እገዳው ለምን አልቆረቆራቸውም የአማራው ክልል ርዕሰ ሊቀ - ሊቃውንት ??? ያስምጣል - ያሰምጣልም። የተጓዦች መጉላላት፤ መንከራተት ይህ የጫጉላ ሽርሽር ነበርን??
13) የሰኔ 15ቱ ጉዳይ እሳቸው ወደ አውሮፓ፤ አቶ ደመቀ መኮነን ወደ ዲስ በረራ ነበራቸው። ይህን አልጠዬቀም ልጅ መሳይ ለምን? እንዴት ብሎ? መርማሪ ጋዜጠኛ ስላልሆነ ሊሆን ይችላል። የሆነ ሆኖ መልሱ ተንከራፎ ነው የቀረበው። እንደ አልባሌ ጉዳይ።
ሌላው ቀርቶ የዶር አንባቸው መኮነን ወላጅ እናት፤ የአቶ ምግባሩ ወላጅ እናት እና አባት በተከታታይ ሦስት ቀናት ነበር በሥጋ የተለዩት ይህ የእግዜሩ ወይንስ አጋጣሚ የፈጠረው ሱናሜ???? ከውስጥ ለውስጥ ሆኖ የጉዳቱን ስሜቱን የመጋራት አቅም በሰውኛ አግባብ ጓድነቱ ቀርቶ አላገኜሁትም። የአቶ ጌታቸው ተስፋዬ ጉዳይስ የህመም ወይንስ? ይህም ዘመንን የሚጠዬቅ አመክንዮ ነው። በወቅቱ የክልሉ መሪው ዶር ገዱ አንዳርጋቸው ነበሩና።
//#ምልክት ……… //
ሌላው በዚህ አጀንዳ ዙሪያ ቀንጨብ አድርገው ያነሱትን ነጥብ ላጎልብትለወት። የውጩ ማህበረሰብ ዕውቅና የሰጠው ነፍጠኛው ወደ ሥልጣን ለመመለስ መፈንቅል ሊያደርግ ተንቀሳቅሶ ከሸፈ ነው የነበረው። የመንግስታችሁ ሚዲያ ያስተጋባውን አለመለሙት። ይህን ሚዛን ማስጠበቅ ያስፈልግ ነበር የፎቶ ውዳሴ ከንቱ ለማይሹ፤ አጃቢ ለማይፈልጉ ባተሌወች። ምን ሆነ??/
13.1 ከ15/2011 ዓም አስደንጋጭ ክስተት የጊዜ ክበብ ውስጥ በአንድ ቅዳሜ ዶር አብይ አህመድ ጭምቱ አለቃቸውን ዶር ለማ መገርሳን ይዘው እስራኤል ተገኙ። ያስታውሳሉን? እጅ መንሻ ይዘው ነበር የተገኙት።15ሺህ ኤርትራውያን ስደተኞች በተመለከተ። ከውስጥ መጎዝጎዝ ለአብይዝም ፕሮጀክቱ ነውና። ተልዕኮውን ካሳካ በኋላ ………
13.2 በድንገት የአውሮፓ ህብረት ጉልላት ዶር ኡርዙላ በዚህው የጊዜ ማዕቀፍ ውስጥ ኢትዮጵያ ተጋበዙ። ተጋበዙ የምለው እነሱ የአመት የቀጠሮ ትልም ስላላቸው ነው። ኢትዮጵያ ሲገኙ የነበረው አቀባበል በኢትዮጵያ መሪ ሹፌርነት የተስተናገደ ነበር።
13.3 በዚህው የጊዜ ማዕቀፍ ባልተራራቀ ሁኔታ የተመድ ዓመታዊ ጉባኤ ነበር። የቀድሞው ምክትል ጠሚር አቶ ደመቀ መኮነን ሳይሆን የዲፕሎማቲ ቁንጮ፤ የተመድ ቤተኛ፤ አንስት የፖለቲካ ሊቀ ሊቃውንትን ላኩ። አንባሳደር ወሮ ሳህለወርቅ ዘውዴን። ንግግሩ በሙሉ የሰብዕና ግንባታ ነበር። የኖቤል እጮኛ ናቸዋ ዶር አብይ አህመድ። ይህ ተራ ግጥምጥሞሽ አይደለም። አልነበረምም። የተደራጄ ተግባር፤ ሚዛናዊ የሆነ የዕንባ አጋርነትን የሚከውኑ የሳይለንት ማጆሪት ቤተኞች አሉ። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሳይለንት ማጆሪቲው የተናቀ ግን ጠንካራ አቅም ያለው ሰውኛ እና ተፈጥሮኛ ለዛ ያለው ሥጦታ ነው። ግን የጨመተ። ግርግር ውቂ ደብልቂ ግጥሙ ያልሆነ።
የሆነ ሆኖ ዶር አብይ የዲፕሎማሲውን አቅም በስልት መዳፋቸው ውስጥ በፍጥነት ያስገባሉ። ያልቻሉት የህወሃትን ሱናሜ ነበር። እሱም ጦርነቱ ከቆመ በኋላ ያጋደለውን ሚዛን ያስጠበቀው እንደ አልባሌ የምታዩት ሳይለንት ማጆሪቲው ነበር። በማንኛውም ሁኔታ ሳይታሰብ፤ ሳይታቀድ ጠቃሚ የሆነ አቅም ካልታሰበ ቦታ ፈልቆ ሲታይ ያ የጭምቶች ተግባር ነው።
#ልከልለወት …… በስሱ የአማራ የጸጥታ አስከባሪ በሦስት ወንጀል ተከሰሰ።
የኤርትራ መንግሥት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት፤ ህወሃት በሙሉ አቅማቸው ተዋጉ። የተከሰሱት ግን በአንድ ወንጀል ብቻ ነበር። ለምን? ባለቤት የለውማ አባ ቅንዬ አማራ። በጦርነት ወቅት ገኖ የሚወጣው ጥላቻ እና በቀል ነው። በግራ ቀኙ ወገን ህዝባችን ተጎድቷል። ያ ያንገበግበኛል።
ስለሚፈጠሩ አሰቃቂ፤ አግላይ እንሰሳዊ ወንጀሎች ጥበቃ ማድረግ ወንጀለኝነት ነው። ግን የወንጀለኝነት ተጠያቂነት የክት እና የዘወትር ሊኖር አይገባም፦ ነበር ሙግቱ። እናም ተሳካ። ከግንቦት መግቢያ 2023 እአአ ጀምሮ መልክ ያዘ። አላዩም ጥድፊያ ላይ የአማራን ጉዳት ለማድመጥ የነበረውን ጉዳይ። ይህ የቅርብ ጊዜ እኮ ነው። አስረጂወች ብቻ ሳይሆን ከክብር ማማ ላይ ቁብ ብለው እንክብካቤ በእንክብካቤ የነበሩት ሌሎች ናቸው። ዕውነት አጃቢ የላትም እና።
በመንግሥት መዋቅር ያ ሁሉ ባለሙያ ተይዞ የማይሳካው በፈጣሪ ጥበብ ግን ይሳካል። ዲፕሎማቶች የአማራ ክልል እና የአፋር ክልልንም ጉዳት እንዲመለከቱ አይደረግም ነበር። ለዚህ ነበር የመረጃ ክፍተቱ የተፈጠረው። ይህን እንደ አንድ የውጭ ጉዳይ ሚር ይሁን እንደ አንድ የደህንነት አማካሪ መሞገት ይገባ ነበር። መሃያ አልቦሽ መንፈስ ነው እናንተን ተክቶ በያዘመኑ የባተለው።
ከዕለታት በአንዱ ቀን የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የተከበሩ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ኢትዮጵያ እንደሚሄዱ ተደመጠ። ወቅቱ የኮፐን ሃገኑ ታላቁ ትሩፋት የሆነው የካቲት 29 በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የሚከበርበት ነበር። ለአውሮፓ አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ በ2008 በረዷማ ቀንም ታዳሚ ለመሆን ሂጄ አይቸዋለሁኝ።
ወደ ቀደመው ምልሰት ሳደርግ ለእኔ የአንዲት ጋዜጠኛ፤ አንዲት ብሎገር አንስቶች ታስረውብኛል። ወጣት ጸሐፍያን አምሳዬ ብሎገሮችም ታስረዋል። ወጣትነታቸው ያሳሳኛል። ትጋታቸው ሐሴት ይመግበኛል። ስለሆነም ለየካቲት 29 ስጦታዬ የተስፋወቼ መታሰር ነበር እና ያነን ላኩኝ። ያን ጊዜ በህወሃት መራሹ ኢህአዴግ ዶር ገዱ አንዳርጋቸው የአማራ ክልል ቁልፍ ሰው ነበሩ።
እና ምን ሆነ ነው ጥያቄው? የታሳሪ ቤተሰቦች ስንቅ ለማቀበል ሲሄዱ በድንገት የምስራች ጠበቃቸው። ታናሽ እህቶቼ እና ታናሽ ወንድሞቼ ከእስር ተለቀቁ። ለእኔ የዞግ ጉዳይ አይደለም። ለእኔ የሥጋ መቀራረብ ጉዳይ አይደለም። ለእኔ የዕውነት እና የርህርህና ጥያቄ ነው። በዛን ወቅት ደማቁ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ምን አለ መሰለወት ፕሮፌሰር ዶር ብርኃኑ ኤርትራ በመግባታቸው ህወሃት ተደናግጦ ፈታ የሚል ትንታኔ ሰጠ። ለግንቦት 7 ቀልፍ መሪው አቶ አንዳርጋቸው ወይንስ ጋዜጠኞች ብሎገሮች ማን ይቀርበው ነበር???
የትኛውም የፖለቲካ ድርጅት፤ የትኛውም ተጽዕኖ ፈጣሪ የታገልኩለትም ሆነ የሞገትኩለት፤ የተማገድኩለት ይሁን የባተልኩለት አያውቀኝም። እኔም ከማናቸውም ጋር ግንኙነት የለኝም። አያስፈልገኝም። ስቀው ማዬት ነው የሚናፍቀኝ ያን አያለሁኝ። በማምንበት ጉዳይ በፈጣሪዬ እርዳታ እተጋለሁኝ። አሳካለሁኝ። ግሎባላይዜሽኑ ምን ዓይነት ዲግሪ አላት፤ እነማን ወገኖቿ ናቸው አይደለም ጉዳያቸው። ካለ ፕሮቶኮል አስከልካይ ሙግቴን ይዤ መቅረብ ብቻ ነው የሚጠበቅብኝ። "ሙያ በልብ" ቅኔው የጎንደር ህዝብ ያሳደገኝ ማህበረሰብ የዊዝደም ጎዳናዬ ነው።
የተከበሩ ዶር ገዱ አንዳርጋቸው ድርጅት መሰረትን ብላችኋል። እንኳን ደስ አላችሁ። ታማኝነት ላይ ምን ዕሳቤ ድርጅታችሁ አለው??? የሥያሜውን ብልቅልቅነት ተወት አድርጉት። የሆነ ሆኖ ዝምተኛው ማህበረሰብ የአቅማችሁ ልክ እንደምን ከውስጡ አሳምኖ ከጎኑ ያሰልፋል ይሆናል ወሳኝ ጥያቄ ነው። መመሥረት አይደለም ጉዳዩ፦ ዕውነት ሆኖ ቁም ነገሩ ተደራሽ ሲሆን ነው። ከምትጠዬፋት የብልጥግና የፖለቲካ መስመር በብዙ መስፈርት ተሽላችሁ መገኜታችሁን ማሳዬት ነው።
#ያደክማል ………
ሌላው ውሽክ ያደረገኝ አመክንዮ ስለ አማራ ክልል ተሳትፎ የዲፕሎማሲ ዕውቅና የተገኜው በሊሂቃኑ መሰዋት ነው ያሉት ነው። ከዛ በፊት እንደምን የለውጥ ኃይል የተባለው ቲምን በሚመለከት ወሳኞቹ የግሎባል ፖለቲካ አዛዦች ዕውቀን ሳይኖረው ነበርን ህወሃት ስልጣኑን ፈቅዶ እንዲለቅ የተደረገው? ኧረ በፈጣሪ ትንሽ ከምድጃ ፈቅ ያለ ነገር አምጡ። ያ ከሆነ ለምን አሁን ድርጅት አቋቋሙ? የዲፕሎማቲኩ ማህበረሰብ ሚና ከሌለው??? ለዛውም በስደት አገር??? ብቻ የሚቻል ከሆነ --- እንደማለት።
የኦሮማራ ከህወሃት ጋር የሥልጣን ርክክብ የሂደቱ ሞተር ዲፕሎማሲው አቅም ስለመሆኑ ማገናዘብ መሳን እንዴት ሊሆን ቻለ ለአንድ ባለ ተመክሮ መሪ???? የዶር ገዱ አንዳርጋቸው የዕድሜ ዘመናቸው ተመክሮ ይህን ፋክት እንደምን ሊመረምረው አልተቻለውም??? በግልብ ሁኔታ ነበር የሥልጣን ርክክቡ የተፈጸመውን??
ለማንኛውም ከዓመት በኋላ አልነበረም ቲም ገዱ የታወቀው። ይህ ሳይረጋገጥ ኢትዮጵያን ያህል አንከር አገር በዝም ብሎ ሂደት ለመንገደኛ ይሁንታ አይሰጥም። ነገም እንዲሁ ነው። ሁነኛ የሚመሰከርለት አቅም በእርግጠኝነት መኖሩ ሲረጋገጥ ብቻ ነው ይለፍ የሚሰጠው። አሁንም እማደምጠው ብቻ ያለው ይወገድ ነው። ካቢኔው እንዲነካ አይፈለግም። በዛው በቅሬት አካል ያው መልፈስፈስ??? ብቻ ጠቅላዩ ይልቀቅ ነው ዘመቻው።
ትችላላችሁ፤ ታሳካላችሁ፤ የገበርዲን እና የሱፍ ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን የሴት የፖለቲካ ሊሂቃን ተሳትፎ ተመጣጥኖ ከቀደመው የኢትዮጵያ እናቶች ዕንባ እና መከራ የተሻለ ይሆናል ነበር ሃሳቡ። ብልጡ ዶር አብይ ለይስሙላ 50% ካቢኔያቸውን በሴት ሚር፤ ፕሬዚዳንት ሴት አድርገው ዓለምን ያስጨፈሩት አመክንዮ መነሻ ስለነበረው ነበር። በዝም ብሎ በመደዴ የተገኜ ዕድል አልነበረም። ቲም ገዱ አፈርድሜ አስጋጠው እንጂ። የደከመው የሚስጢሩን አስኳል - ያውቀዋል። በዓላማ እና ግባችሁ ውስጥ ጭራሽ አልነበራችሁም ማለት ይቻላል።
ቢያንስ በሌሎች ክልሎች የአማራ ህዝብ የፖለቲካ ውክልና እንዲኖር ማስደረግ እንደምን አልተቻም??? በዛ የጫጉላ ጊዜ ሽርሽር ድምፃችሁን ሙሉለሙሉ ከመስጠታችሁ በፊት። ፌድራሊዝሙን ሥያሜ በተግባር የተሸከመው እኮ አማራ ክልል ነው። በአማራ ህዝብ የፖለቲካ ውክልና የዳማ ጨዋታ። አገው፤ አርጎባ፤ ኦሮሞ፤ ቅማንት በልዩ ዞን፤ በልዩ ወረዳ ልዩ የፖለቲካ ውክልና አላቸው። ዶር ለገሰ ቱሉ በአማራ ውክልና የገቡ ናቸው። እስኪ በዘመናችሁ ኦሮምያ ላይ አይደለም ለዚህን ያህል የፖለቲካ ዕውቅና በክልሉ ደረጃ ላይ አንድ ይጠቀስልን? በሃይማኖት ስብጥርም እንዲሁ።
ለነገሩ ከሚሴ ላይ እኮ አማርኛ ቋንቋን ግዞት የላካችሁ ጉደኞች እኮ ናችሁ። ቢያንስ በአማራ ክልል የአማራ ህዝብ ሙሉ የፖለቲካ ውክልና እንኳን እንዲያገኝ ማድረግ አልቻላችሁም። ሁሉም ክልል ከተስማማ መልካም ነው፤ ካልተስማማ ግን ቁርጥ ያለ እርምጃ መውሰድ ይጠበቅ ነበር። አሁን ከመቆዘም። በታሪክ የማይደገም ዕድል ተገኜ። ደፍታችሁ --- ቀበራችሁት። አሁን ከዜሮ????
#ጠቅላይ ሚሩ አላውቃቸውም ነበር። ኮሚኩ ትዕይንት የዶር ገዱ አንዳርጋቸው ውሃ ያልነክው ጉዳይ።
1) …… ዶር ገዱ አንዳርጋቸው መስተዳድሩን እዬመሩ ዶር አብይ የሳይንስ እና የቴክኖሎጂ ሚር ነበሩ። "ከእርምጃ ወደ ሩጫ" የሚል ብሄራዊ ሞቶ ፈጥረው ሙሁራንን ሰብስበው ሲያወያዩ ነበር። ቢያንስ ይህን አያውቁም? ወይንስ ዶር ገዱ አንዳርጋቸው ወደ #ማርስ መጥቀው ነበር???
2) ወደ እስራኤል ከተጓዘው የኢህዴግ ልዑክ ጋር ዶር አብይ አህመድ ነበሩ። እናም ቃለምልልስ አድርገው ነበር። ያ የሚዲያ ቃለምልልስ ኢትዮጵያን ውስጥ ያደረገ ነበር። እሱንስ አላዳመጡትንም????
3) ዶር አብይ አህመድ አሊ በዲሞሽን ከሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስተርነት ወደ ኦሮምያ የከተማ ቢሮ ሲዛወሩ ጎንደር ከተማ ላይ ስብሰባ ነበር። የልምድ ልውውጥ ይመስለኛል። ነፍሳቸውን ይማረው እና ዶር አንባቸው መኮነን ተገኝተው ነበር። ያን ጊዜ ዶር ገዱ አንዳርጋቸው የአማራ ክልል ቁልፍ መሪ ነበሩ። ይህንንስ አልሰሙም? አላዩም? ወይንስ እንደ እኛ ስደት ላይ ነበሩን????
4) #ኢንሳን ከመሠረቱት ውስጥ አንዱ ዶር አብይ አህመድ እንደሆኑ ከመሼ ሁላችንም ሰምተናል። ይህንስ ዶር ገዱ አንዳርጋቸው አያውቁም ነበርን? መሪያወቻቸው አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ደመቀ መኮነን ያውቃሉ። በጭልፋ መረጃው አልነበራቸውምን?
በዚህ ጉዳይ ላይ ኢሳትም መረጃው እንደነበረው በኋላ ላይ ሰምተናል። ስለሆነም ስለ ጠቅላይ ሚር አብዬ ማንነት ዱብ ዕዳ ለኢሳት ጋዜጠኞች ሆነ ሊባል አይችልም። የኢህአዴግ ሥ/አ/ አካላት ለነበሩት ለዶር ገዱ ሊሆን አይችልም። ሌላው ቀርቶ በዚህ ጉዳይ አቶ ጃዋር መሃመድ እና አቶ ኦባንግ ሜቶም መረጃው እንደነበራቸው አቶ ኤርምያስ ለገሰ ሲገልጥ ሰምቻለሁኝ።
እኔ እንዲያውም ጋዜጠኛ አበበ ገላው ኢትዮጵያ ስለነበር፤ አቶ ጃዋር መሐመድ (ሐጂ) እስር ላይ ስለነበረ፤ አቶ ኦባንግም ሜቶ ኢትዮጵያ ስላለ አደጋውን ጽፌ ነበር። ለእኛ እርግጥ ነው የጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ የኢንሳ መሥራችነት አዲስ ነበር። ምንአልባትም መረጃው ታውቆ ቢሆን ከብዙ የተስፋ መስተጓጎል ይዳን ነበር። አቅምን በገፍ ከመመገብ ማመጣጠን ይቻል ነበር። መረጃው አዲስ ነበር ለእኔ።
5) ዶር አብይ አህመድ በኢህአዴግ ፓርላማ ተመራጭ ነበሩ። ዶር ገዱ አንዳርጋቸው ለዚህ ሃቅም ባይታዋር ነበሩን????
በብሄራዊ ጉዳይ የሹመት፤ የሽልማት ጉዳይም እንደ አንድ የክልል መሪ የኢትዮጵያ ሚኒስተር የሆኑ ሊቃናትን የማወቅ አቅም አለመኖር እንዴት ሊፈጠር ቻለ???? አልገባኝም።
6) ጠሚር አብይ አህመድ ኦኮ መኖሪያቸው አማራ ክልል ነበር። ውሃ በቀጠነ ባህርዳር ይመላለሱ የነበሩት ዶር ገዱ አንዳርጋቸው የአማራ ክልል መሪ በነበሩበት ጊዜ ነበር። የአማራ ሊቃናት ማህበር ነገር ተመስርቶ ግን #አገልጋይ እንዲሆን የተደረገውም በሳቸው ዘመን ነበር።
የሚደንቀኝ የአሁኑ የዶር ገዱ አንዳርጋቸው ለአማራ ህዝብ ዘርፈ ብዙ መከራ ተቆርቋሪነታቸው ዝልቅ እና ልሁቅ መሆኑን ማዘከራቸው ነው። የአማራ ሊቃናት ለአማራ እናት ዕንባ በትርፍነት፤ በደባልነት ካልሆነ የውስጣቸው አጀንዳ ነው ብዬ አላምንም። አሁንም የአማራ እናት ተስፋ ማገዶነቱ ይቀጥል ግን ለአዲሱ ኃይል ድል ሲቀናው ኢትዮጵያን ለማዳን ደግሞ ርክክብ እናስፈጽም ነው ዕድምታው። በአንድ ጉዳይ አንድ ሰው የሚታመነ ካልሆነ በሌላውም ሊታመን አይችልም።
በጠቅላላ በኦሮማራ ጥምረታዊ ጉዞ የአማራ ህዝብ ለከፈለው ስፍር ቁጥር የሌለው መማገድ ቅንጣት ትርፍ አልተገኜበት። 30 ቀናት ወህ ብለን ይሆናል። አንድ ፋሲካን። በስተቀር የማቅ ነዶ። ነገረ ወልቃይት እና ራዕያ ቢሆኑ በለስ ቀንቷቸው የጦርነቱ በረከት ነው ትንፋሽ ያሰጣቸው። ለዛውም ባጀት አልባ በርሃብ ተቀጡ ነው ፍርዱ። ደራ እና መተከልማ ቀራንዮ።
#የአማራ ወጣቶች ሳይለንት ዲስክርምኔሽን ነበረባቸው።
በኦሮማራ ጥምረት ወቅት የቄሮ ወጣቶች በሙሉ ነፃነት ይንቀሳቀሱ ዘንድ ይለፍ ነበራቸው። በኋላም በአመዛኙ ኑሯቸውን መምራት ወደሚችሉበት ሁኔታ ሽግግር ተደርጎላቸዋል። የአማራ ወጣቶች ግን ያ ቀርቶባቸው ለምን አማራነትን አጠበቃችሁ ተብለው ሰርክ ከወጣቶች ጋር ቲም ገዱ፦ ደዲያቆን ዳንኤል ክብረት ጋር በባህርዳር፤ በዬከተሞች እዬሰበሰቡ ያስጨንቋቸው ነበር። እንዲያውም እንደ 13ኛው መቶ ክ/ ዘመን እሰቡ ሁሉ እዬተባለ ስውር ጫና ይደረግባቸው ነበር። እናም እኔ እዬተከታተልኩ እሞግታቸው ነበር። ፕ
ፔጄ ላይም ይገኛል።
የማከብራችሁ የአገሬ ልጆች ……
የነበሩ ሳተና ወጣቶች እንደምን እሳሳላቸው እንደነበር ልነግራችሁ አልችልም። ከወርቅ በላይ ዕንቁ ነበሩ። ሐዋርያ ነበሩ። አሁን ባለው ተጋድሎ ምን ያህሉ በህይወት እንዳሉ አላውቅም። በትክክል የተገኜውን ዕድል ሚዛኑን በጠበቀ መልክ አስፈፃሚ አካል ተገኝቶ ቢሆን ኖሮ የማህበረ ኦነግ አቅም እንዲህ ጎልብቶ በኢትዮጵያ ጉዳይ ብቻውን አድራጊ ፈጣሪ ባልሆነ ነበር።
ዶር ገዱ አንዳርጋቸው ይህ ሃቅ ያቅራቸዋል። ይሸሹታል ፋክቱን። እሳቸው የብአዴን አመራር ከሚሆኑ የኦህዴድ ቢሆኑ በተሻላቸው ነበር። ሁልጊዜ ውስጥን ቁስል የሚያደርግ አቋም ነው ያላቸው። ይህን የተዛባ ትርክት ለዲፕሎማሲው ማህበረሰብ እንዲያስጡ ነው አሁን መሰረትን በሚሉት ተቋም አማካሪ የሆኑት።
የለጠፍኩት ፎቶ ዶር ገዱ አንዳርጋቸው ሥልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ የሆነውን ብቻ ነው። እሳቸው ከሥልጣን ከለቀቁ በኋላ ለተፈጠረው ነገር ተጠያቂ አይደሉም። ለአንድ የአማራ ልጅ ለዛውም ቲም መሪ ለሆነ ሰብዕና በጣት በሚቆጠሩ ሁለት ፍሬ ጉዳዮች ብቻ ውስጤን ነካኝ ውስጥን ያቆስላል። እኔ ቆስያለሁኝ።
የአማራ ህዝብ ባሊህ ባይ እረኛ አልነበረውም። አሁንም የለውም። ሃግ ባይ የሚፈራ ቆፍጣና አካል ቢኖር ይህ ሁሉ መደፈር የአማራ ህዝብ አይደርስበትም ነበር። ጠቅላይ ሚር አብይን በሙሉ ድምጽ ያመጣው ቲም ገዱ ነው። ማገር ዋልታው የነበረውም ቲም ገዱ ነበር። ይህን ፋክት መሸሸት እራስን በሸምቀቆ አንቆ እንደመግደል እቆጥረዋለሁኝ። የሆነውን ሁሉ ጭምቱ ዶር ለማ መገርሳም፤ ጎልጉሉ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ሳይሸማቀቁ ነው የሚናገሩት። ተኝቶ በለኝ ያለ ቢጠሩት አይሰማም ሆነ እንጂ።
ኃላፊነትን መቀበል ኃላፊነትን ለመወጣት እንጂ ለመተላለፍ ሊሆን አይገባም። በግልም በጋራም ለሆነው ሁሉ ተጠያቂነትን ዘመን ይመልሰውም የሚባለው ፈሊጥም አይገባኝም። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ጠያቂም ተጠያቂም ታይቶ አይታወቅም። ለጫወታ ማሟያ ክልሆነ። ንሳኃውን አቅርቦ መፈፀም ይገባል ባይ ነኝ። ሁልጊዜ አሻግሮ ወርውሮ አሻግራችሁ አማትሩ ከማለት።
እኔ ሥርጉተ ሥላሴ የዶር ገዱ አንዳርጋቸው የትግል ተሳትፎ የመነጨው ሥልጣናቸው ስለተነካ ብቻ ነው ብዬ ነው በጽኑ እማምነው። እኛ እኮ እምነታችን ሚዛን ያስጠብቃሉ ነበር። እሳቸው "ሚዛኑ የተጠበቀ ነው። ምንም ዝንፈት የለበትም። ሥልጣኑ ላይ አቅም ያላቸው አማራወች አሉ። በአንድ ድርጅት አልተዋጥነም" ነው የሚሉት። ይህ ከሆነ የአማራ ገዳዩ እራሱ የአማራ ሊቃናት ነው ማለት ይሆናል።
#ክወና።
ለትግል ተሳትፎ ዶር ገዱ አንዳርጋቸው የማንም ፈቃድ አያስፈልጋቸውም። መብታቸው ነው። ተመክሯቸው ይረባኛል ያለ ማንኛውም አካልም አብሮ የመሥራት መብቱ የተጠበቀ ነው። በአማራ እናት ማህጸን ቄራነት፥ የ120 ሚሊዮን ግማድን ይሸከም አማራ ግን ጨካኝነት ነው። የዶር ገዱ አንዳርጋቸው ጉዞም ከዚህ ውጪ አንዲት ስንዝር ፈቅ ሊል እንደማይችል ልብ ልክ ነው። ለዚህ መንፈስ አቅም ማዋጣት፤ አቅም መመገብ ተጨማሪ ጭካኔ ለአማራ እናት ማከል ይሆናል።
የከፋው እራሱን ገብሮ ለድል ይብቃ። ዘመን ከዘመን የአማራ እናት ማህፀን ይታጨድ ግን አረማዊነት ነው። ይኮሰኩሳልም። በዚህ ዕሳቤ የሚቀጥሉ መንገዱን ጨርቅ ያድርግላቸው። ይቅናቸውም። ድምጽ አልባው ሳይለንት ማጆሪቲው ተሳትፎ ማዕቀብ በተጣለበት ልክ የድሉ ጊዜም ይራዘማል።
የአንድ ሰው አቅም ብዙ ነው። ችግሩ አቅሙን ለመመገብ ታማኝነትን ይጠይቃል። ተማላውን ታማኝነት አይደለም። ፍፁም ታማኝነት። መሬት ላይ 7 ሙሉ ዓመት የፈሰሰው የአማራ ልጅ ደም የአቤል ነውና ይጮኃል። ለዚህ ማህበር ለመሆን የማንፈቅድ ባተሌወች ደግሞ እንኖራለን። ከዘለለው ጋር እማንዛለል። ከአጎረፈው ጋር እማንጎርፍ። መስዋዕትነታችን እዬተደፋ በአዲስ ገበርዲን የላውንደሬ ሠራተኛነት በነፃ አገልግሎት አቅምን ማባከን የተገባ አይደለም። የሚችሉም ይኖራሉ፥ አሁንም ይቅናቸው። ለዶር ገዱ አንድአርጋቸው አዲስ ኃላፊነትም መልካም ዕድል እመኛለሁኝ። መልካም የትግል ዘመን።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
06/03/2025
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ