#የስብሰባ ባለሪከርዱ የአቤቱ ህወሃት የእግር #ጥፍር ጉዞ፤ ጫፍ - ለጫፍ! አፋፍ - ላፋፍ።

 

#የስብሰባ ባለሪከርዱ የአቤቱ ህወሃት የእግር #ጥፍር ጉዞ፤ ጫፍ - ለጫፍ! አፋፍ - ላፋፍ።
 
"ህግ ተላላፊወችን ጠላሁኝ።"
 
 May be an image of 1 person
 
መሸነፍን መቀበል ማሸነፍም ነው።
በመሸነፍ ውስጥ የማሸነፍ ብልህነትም አለ።
እልህ ጥበብ አይደለም።
እልህ ስልትም መሆን አይችልም።
እልህ ስትራቴጅ እና ታክቲክ ሊሆንም አይችልም።
እልህ ልቅናም አይደለም።
እልህ ልዕልናም አይደለም።
እልህ ዊዝደምም አይደለም።
እልህ ለዬትኛውም ፖለቲካ ድርጅት ዓላማ የግብ መዳረሻ ምርኩዝ መሆንም አይችልም።
እልህ ገረጭራጫ ግራጫማ፦ ኮቴ የለሽ #የሲቃ ወኔ ነው።
 
ህወሃትን በሚመለከት መንበረ ሥልጣኑን ፈቅዶ ከለቀቀ በኋላ ሞግቼው አላውቅም። ከዚህ በላይ ከህወሃት እምጠብቀው ቁልፍ አመክንዮ አልነበረኝምና። በዚህ አቅሙ እና ብቃቱም አመሰግነዋለሁኝ። ለምንጊዜም። የተቀበለውን መልሶ ፍልስልስ ቢያደርገውም ቅሉ። ትርፍና ኪሳራውን የመመዘኛ ዳታ ባልሠራም በወቅቱ ሊገጥም ይችል ከነበረ ውስብስብ ችግር የመፍትሄ አካልነቱን ህወሃት በድርጊት አስከብሯል ብዬ አምናለሁኝ። መደበኛ የፕሮፖጋንዳ ተግባራቸው ህወሃት ብቻ ለነበሩ የአዲሱ አመራር የአብይዝም ደጋፊወች እራሱ አዝንላቸው ነበር። ስለሚያባክኑት ጊዜ። 
 
በሌላ በኩል እላፊ በሄዱ ንግግሮች እና ፋክክሮችን ተከትሎ ለመጣው ፍጥጫ፦ በጦርነቱ ዋዜማም ጦርነቱ #ሊያዋጣ እንደማይችል አበክሬ በተከታታይ ሞግቻለሁኝ። ጦርነቱንም ፊት ለፊት ወጥቼ አውግዣለሁኝ። ጉዳቱን ብቻ የዓለም ዓቀፍ ሚዲያ ተቋማት የሚሰጡትን መረጃ ተመርኩዤ በሃዘን ውስጥ ሆኜ ስዘግብ ነበር። 
 
በሌላ በኩል ህወሃት ትንፋሽ አግኝቶ ከጫካ ወደ መቀሌ ከተመለሰ በኋላ፤ በበቀል ሰምጦ፦ በሥልጣን ዘመኑ በብድርም ይሁን በእርዳታም ባገኜው መዋለ ንዋይ፦ በራሱ አመራር የገነባቸውን ተቋማት፤ ያሳደጋቸውን ወጣቶች በአፋር እና በአማራ ክልል ሲያወድም ውስጤ ያዘነበት ክስተት ነበር። ድካሙን በራሱ አፈርድሜ አስጋጠው። የደፂዝም የአመራር ልክ በዚህም መመዘን ይቻላል። አንድ ልባም ጠፍቶ??? ከዚህ ውጪ በጠቅላላ ህወሃትን በሚመለከት ከማድመጥ በዝምታ በመታደም ነው የባጀሁት - ሙሉ ፯ ዓመታት። 
 
ዛሬ ትንሽ ስለ ህወሃት መሪ ስለ ዶር ደብረጽዮን ገብረሚኬኤል አመራር እና የጠቅላይ ሚኒስተርነት መሻታቸውን ወይንም ትግራይን አገር አድርገው የአፍሪካ መሪወች ቤተኛ ለመሆን ህልማቸውን በሚመለከት ቅኝት ቢጤ አሰኜኝ። ግን የፖለቲካ ድርጅት መርህ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት እና ህገ - መንግሥት ለደጺዝም ምን እና ምን ናቸው? መሪነትን መናፈቅ መርህን #ተጠቅጥቆ ይቻል ይሆን???
 
በጦርነቱ ዋዜማ የትግራይ እናቶች ተንበርክከው ሲማጸኑ በወቅቱ ጽፌያለሁኝ። ሰሞኑንም የትግራይ ወጣቶች እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በሥሟ እዬጠሩ ተማጸኑ። ካዬሁት ዕለት ጀምሮ ከውስጤ ሊወጡ አልቻሉም እነኛ ትሁታን ወጣቶች። ጭንቅ ላይ መሆናቸውን ነገረ ሥራቸው አስገንዝቦኛል። ለትግራይ ክልል እና ለተጋሩ የህወሃት መፈጠር እርግማን ይሁን ምርቃት ተጠቃሚው፤ ባለቤቱ ብይን ይስጥበት። 
 
የህወሃቱ ቁንጮ መሪ ዶር.. ደብረጽዮን ገብረሚኬኤል እንደ አባቶቻችን እና እናቶቻችን #ዊዝደሙን ሰጥቷቸው ቢሆን ኖሮ፦ የኢትዮጵያ ጠቅላይ አዛዥ ህወሃት በነበረበት ዘመን እራሱንም ኢትዮጵያንም የመታደግ አቅም ይኖራቸው ነበር። ቁንጮ ነበሩና። ጎልተው የሚታዩ። ከአራቱ አውራ የኢህዴግ ተጠሪወች አንዱ ዶር ደብረጽዮን ገብረሚኬኤል ነበሩ። መሪውም ህወሃት ነበር። 
 
ግን የመሪነት #አቅም በፍጹም አልነበረም። ስልትም፦ ጥበብም #ፍግፍግ ስለነበረ መጋቢት 18ቱ 2010 ዓ.ም በእኩለ ሌሊት ላይ ለእጩ የኢህአዴግ መሪነት ተወዳድረው #ሁለት ድምጽ ብቻ ነበር ያገኙት። ይህ ለቀጣይ የመሪነት አቅም መራራ ስንብትን በፈቃደኝነት የሚጠይቅ እንቅጩ ጭብጥ ነበር። "ልክን ማወቅ ከልክ ያደርሳል" ይላሉ ባለ ቅኔወቹ ጎንደሬወቹ። ድምጽ አለማግኜት አቅም የለህም ብቻ አይደለም፤ በሰብዕናህ ላይም መታመናችን አንሸልምም ነው። 
 
… ከተስፋ ምናኔ በኋላ፦ ኢህዴግ እንደ ባህሉ አዋሳ ላይ ጉባኤውን አካሄዶ ከአንድ ድምጽ በሰተቀር የኢህአዴግ ቁንጮ ዶር አብይ አህመድን የሚያደርግ ውሳኔ ተወሰነ። አውቶማቲካሊ ይህ ውሳኔ ለጠቅላይ ሚር ቦታ ፈረመ። ዶር. ደብረጽዮን ገብረሚኬኤል ፍጥረተ ነገራቸው በፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ነው። ምንም እንኳን አጀማመራቸው ሚዲያ ላይ ቢሆንም፤ ዘመናቸው በዞግ የፖለቲካ ድርጅት የአደረጃጀት መርሆን ወተት ጠብተው ያደጉ ናቸው።
 
ህወሃት ዞጋዊ የሶሻሊስት ርዕዮትን ቃና መርሆ አድርጎ የተቀበለ ስለነበረ፥ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን በማክበር፤ በማስከበር እረገድ ፈቅዶ እና ወዶ የሚፈጽመው ነበር። የድርጅቱ ዲስፕሊን ዶግማዊ መሠረቱ #ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ነው። ስለዚህ ይህን መርሆ የመፈጸምም፤ የማስፈጸምም ኃላፊነት ቀዳሚው፤ አብነት ሊሆኑ የሚገባቸው ዶር ደብረጽዮን ገብረሚኬኤል ሊሆኑ ይገባ ነበር። ግድም ነው። ከውሳኔ በፊት ሃሳብን ማቅረብ ሲቻል፤ ከውሳኔ በኋላ ግን የብዙኃኑን ድምጽ እንደ ራስ ውሳኔ አድርጎ መቀበል ግዴታ ነው። መርኽም ነው። በምንም ሁኔታ በድምጽ ብልጫ ላለፈ ሚስተር A ይሁን ሚስተር B ሚስተር C ፈቅዶ የመገዛት ግድ ነው በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የአደረጃጀት መርኽ። 
 
በአንድ የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ የመምረጥ፤ የመመረጥ መብት ይኖራል። ለተመረጠው አካል አመራር የመገዛት ደግሞ #ግዴታ ይኖራል። ይህ ነፍሳቸውን ከሶሻሊስቱ ርዕዮት ላቆራኙ ህወሃት መራሽ መዋቅሮች ሁሉ የሚሰራ ግዴታ ነው። ከዚህ ከተፈነገጠ #አናርኪዝም ነው።
የሶብዬት ህብረቱ የቦልሼቢክ እና የሜንሼቢክ ጉዳይ የሰከነውም በመርህ ማስጠበቅ እና መተላለፍ በተከሰተ ሁነት ነበር። ስለዚህ ለእኔ ዶር ደብረጽዮን ገብረማርያም የ7 ዓመቱ የትግል ቆይታ አልታያቸው ካለሆነ በስተቀረ #በአናርኪዝም አልጋ ላይ ነው የሚገኙት ባይ ነኝ። የሳቸው ምርጫ ይህ በመሆኑ፤ መርህ አስጠባቂ አካል በአንጋፋው የዞግ የፖለቲካ ድርጅት በህወሃት አለመኖር ምክንያት ድርጅቱም ትግራይ ውስጥ የሚኖር ነዋሪም የመከራው ሰለባ ሆኗል። አንድን ድርጅት ቀጥ አድርጎ የትውልድ ማድረግ የሚችለው መርሃዊነት ነው። ይህ ፋክት ነው። በሌላ በኩል ህወሃት እራሱ ባደራጀው ምርጫ ቦርድ አልመራም ብሎ ምርጫ አድርጎም ነበር። መሪው ዶር ደብረጽዮን ነበሩ። ይህም አናርኪዝም ነው። ለራስ ህግ አለመገዛት። 
 
አሁንም እኔ እማዬው ህወሃት ባልተሳተፈበት ብሄራዊ ምርጫ በበርካት ስጋት ታጅቦ፤ በፍርሃት ተወጥሮእና በብዙ የቀውስ ትዕይንቶች ገፊ ምክንያት ቢሆንም ብልጽግና ነኝ ያለው ድርጅት #አሸናፊ ነው። ይህ ቁጭ ብለን ያዬነው ሃቅ ነው። በጀት በቀጥታ ከዚህ ድርጅት አመራር ከሚያገኜው ማዕከላዊ መንግሥት የሚሰጥ ከሆነ የግድ ኢትዮጵያ አንድ ጠቅላይ ሚር ብቻ እንዳላት አምኖ መቀበል፤ በዛ ሥር ፍላጎትን አማክሎ መጓዝ ግድ ይሆናል። በደጺዝም የተመሰጠረው ትግራይ አልመረጠችም ነው። ይህ ይገባኛል። ሌላው ለመረጠውም መገዛት ግድ ነው። ባጀቱ ካስፈለገ። አገልግሎቱ ከተፈለገ። ይህ ፕሮፓግንዲስት አያስፈልገውም። መርህን መቀበል ነው። መራራም አይደለም። ሥርዓታዊ ሂደት እንጂ።
 
በዛ ሰሞን በ2011 ዓም በቅድስት ጽዮን ንግሥ በዓላት፤ በተለያዩ ኢቬንቶች ዶር ደብረጽዮን ገብረሚኬኤል ያሳዩት የነበረ አክሽን እራሳቸውን እንደ አንድ አገር መሪ አድርገው እንደነበር ያስተዋልኩት ጉዳይ ነበር። የመሻት እና የሚሽቱት ጭብጥ አራባ እና ቆቦነት ስበቃው የተቃርኖ እንዝርቱ ያጠነጠነው በዚህ ዙሪያ ነበር። የችግሩ አስኳልም ይህ ነው። ኢህዴግ በጉባኤው ያጸደቀው አመራርን አልቀበልም - ትቀበላለህ በዚህ መሃል ህዝብ በመራር ሃዘን ደቀቀ። ኢትዮጵያም የዕንባ ባዕት ሆነች። ብዙ ቤተሰብ ተበተነ። ብዙ ወጣቶች መሬት ውስጥ አረጁ። ብዙ አበባወች አካላቸውን አጡ። ብዙ ያላቸው ከመኖር በታች ሆኑ። 
 
ባሳለፍናቸው 7ዓመታት በዚህ ወሳኝ ማህለቃዊ ሂደት ዶር ደብረጽዮን እኔ በግሌ አላዬኋቸውም። ለህዝብ ሃዘን ቅርብ መሆን እኮ ተመሳሳይ ግድፈት ላለመፈጸም መጠንቀቅ ነው። መሪነት እኮ ጠንቃቃነት ነው። 
 
በሌላ በኩል ህገ መንግሥት የህጎች ሁሉ የበላይ ከመሆኑም በላይ ማንኛውያ ህግ ሆነ የአፈፃፀም ድንጋጌወች የሚቀዱት ከዚህ ህገ መንግሥት ነው። ህገ መንግሥቱ ደግሞ በህወሃት #ራዕይና ግብ የቀለመ ነው። ለዚህ ህገ መንግሥት አፈፃፀም ፒላር ሊሆኑ የሚገባቸው ዶር ደብረጽዮን ገ/ሚኬኤል ሊሆኑ በተገባ ነበር። በዚህ ዘርፍም ትውፊቱን ለማስቀጠል አቅመ ቢስ ሆነው ነው ያገኜኋቸው። የመሪነት የማስተዋል ጥሞናዊ ቃና አላዬሁባቸውም።
 
ረግረግ -- አፋፍ -- በእግር ጥፍር #ተንቆራጦ መጓዝ ስለምን ምርጫቸው ሊሆን እንደቻለ አላውቅም። ሁሉም ይቅር የትግራይ እናት ከጭንቀት መቼ ትገላገል? አጽናኝ ዘመኗን እንዴት ላዋልድ ብሎ መጨነቅ መጠበብ ሲገባ ዛሬም እልህ። ለመሆኑ ህወሃት በምን መብቱ ይሆን የዲፕሎማሲ ማህበረሰቡን በአድራሻ በደብዳቤ መግለጫወቹን የሚያሳውቀው??? ይህ ለአንድ ክልል እንደምን ይፈቀዳል? ይህ በራሱ አናርኪዝም ነው። ሁልጊዜ ህዝብ ጠቀም ያልሆነ ትወና ሰርክ???
 
የደፂዝም ቀመራቸው በመርህ ጥሰት የተጓዘ ስለሆነ መቼውንም ቢሆን አሸናፊ ሆኖ የመውጣት አቅም የለውም። መቼውንም። የኢትዮጵያ ፖለቲካ በረከት የሚያጣውም፤ የሚያጸድቁት ማኒፌስቶ እና አመራሩ የአለመተዋወቅ ችግር ነው። አብዛኞቹ ማኒፌስቷቸውን እንደ ቡና እና ሱካር መጠቅለያ መጋዚን በማድረግ ነው ጫጭተው ወይንም ተነው የሚቀሩት። ይህን ግድፈት ዘመን በቆጠረ ዞጋዊ ድርጅት ማዬት መቼም የሚገርም ጉዳይ ነው። 
 
#የደቡብ አፍሪካ ብሥራት።
 
ደቡብ አፍሪካ ላይ የተካሄደው " የፌድራሉ" (ፌድራሊዝም ያለው አማራ ክልል ብቻ ስለሆነ ነው ጥቅስ ውስጥ ያስገባሁት፤ ቧልት ስለሆነ)እና የህወሃት የእርቀ ሰላም ውይይት ለህወሃት ሆነ ጦርነት አያስፈልግም ለምንል እኔን መሰል ዜጎች ታላቅ ብስራት ነበር። ወዲያው ነው የዘገብኩት። አንድ ሰዓት ምን ያህል መርግ እንደ ሆነ በጦርነት ቀጠና ጭንቁን ኑሬበት አይቸዋለሁና። ህወሃት ኢትዮጵያን ሲቆጣጠር የነበረውን ምጥ ወጣት እያለሁ ቀምሸዋለሁኝ ወላፈኑን። ለዚህ ነው ጦርነትን አክ እንትፍ አድርጌ በህሊናዬ ያሰናበትኩት። ይህን ስል አጥቂ ማዕድ ላይ ሲመጣ፥ መከላከል የተገባ መሆኑን አምንበታለሁኝ። እራስን ማዳን ነውና። 
 
የሆነ ሆኖ በዛ ወቅት ህወሃት ብቻ ሳይሆን ዛሬ ያሉት የህወሃት አመራሮችም የመትረፋቸው ሚስጢር የደቡብ አፍሪካ ብሥራት ነው። ጦርነቱን ገፍቶበት ቢሆን የአብይዝም መንግሥትም ሌላ ቅርቃር ውስጥ ይገባ ነበር። ያሸንፋል ግን??? 
 
ስለሆነም ድሉ ለአብይዝም አገዛዝ ለራሱም ለህወሃትም የቀውስ ዓውድማ ይሆን ነበር ነገረ ዓለሙ። ስለዚህም የደቡብ አፍሪካን ዲክላሬሽን ህወሃትን የሚደግፈው በጉጉት የሚጠብቀው፤ ህወሃትን የሚቃወመው መቀሌና በዙሪያው ያለው ነዋሪም ብሥራቴ የእኔ ሊለው ይገባል። የብልጽግና ደጋፊውም።
 
ለእኔ በጣም ብልህ እርምጃ ነበር። ምን ተሰናድቶ እንደሚጠብቅ የሚታወቅ ነገር አልነበረም። በዛ ላይ ዓለም ዓቀፋ ማህበረሰብ የዛሬን አያድርገውና በአብይዝም ሥርዓት ላይ አዲስ ሦስት አፍ የተሳለ ሰይፍም ይዞ ብቅ እንደሚል ሳይታለም የተፈታ ነበር። የተመድ የጸጥታ አካል ስንት ጊዜ ተሰበሰበ??? ትወና እና ህወሃት ነጭ እና ቀይ የደም ሴሎች ናቸው። በርግጥ በደረሰ የህዝብ ጉዳት፤ በሚቃጣውም ክስተት፤ በማይሆነውም ጉዳይ ድርጁ ተግባር ህወሃት አሰናድቶ ይጠብቅ ነበር። ከሁሉ ያ መከረኛ ህዝብ የተደጋጋሚ የመከራ #መሞከሪያ ጣቢያ ይደረግ ነበር። 
 
ተጠቃሚወች አብይዝምም፤ ህወሃቲዝምም ናቸው። አብይዝም በህወሃት ጉዳይ የልቡ ስለደረሰ በበዛ የዘለቀ አደብ ውስጥ ሆኖ ነው የማዬው። በሰሞኑ የፓርላማ ውይይት እንኳን በዛን ያህል ትህትና ጉዳይን ሲያስተናግዱ ጠ/ሚር አብይ አህመድ አሊን አስተውዬ አላውቅምም። "ትብብር ካገኜን ተፈናቃዮችን ለመመለስ ፈቃደኞች ነን" ነበር ያሉት። ይህ ትህትና ለአማራ ህዝብ አይታሰብም። ይህ #ዝቅታ ለአማራ ህዝብ መከራ አይታለም። እሳቸውም ሆኑ አንደበታቸው ዶር ለገሰ ቱሉ ስለ አማራ ሲያነሱ ብስጭታቸው፤ ግልምጫቸው፤ ቁጣቸው መስፈርት የለውም። የፖለቲካ ኢሊት ብቻ ሳይሆን፦ በሥር ያለው ህዝብም ሊከበር የሚገባው በእኩልነት ሊሆን ይገባል። በዚህ ዘርፍ የአስተሳሰብ ግድፈቱ የሁሉም ነው። የአማራ ህዝብ ደመ መራራ ነው። 
 
#አሁናዊ ሁኔታ።
 
የዓለም፤ የአህጉሩ፤ የአፍሪካ ቀንድ፤ የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች የኃይል አሰላለፍ ዴሞክራቶች መሪ ከነበሩበት ጊዜ ለዬት ያለ ነው። ትራንፒዝም የራሱን መንገድ ይዞ ጉዞ ጀምሯል። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ጎረቤት አገር የሱዳን ጉዳይም አዲስ ቅርጽ እየያዘ ነው። እንዲሁም ኢትዮጵያ የነካካቸው የሱማሌ ላንድ፦ የአሜሪካ እና የሱማሌ ሁነት በሌላ ፎርማት ላይ ያሉ ይመስላል። እንዲሁም የእስራኤል፤ የጋዛ እና የሊባኖስ፤ የአውሮፓ (ራሺያ እና ዩክሬን ጦርነት እና የሰላም ቅምሻ ሂደት) እና የትራንፒዝም ሁነት፤ ዱብ ዕዳው የቱርክ ፖለቲካ የሰሞናቱ ጉዳይ በጥንቃቄ መራመድን ይጠይቅ ይመስለኛል። 
 
ህወሃት በውሃ ብቻ የበሰለ ሙጌራ ዳቦ ያለ ይመስለዋል። በምዕራብውያን ላይ ሙሉ ተስፋውን የጣለው ህወሃት ሁልጊዜ ሠርግ ያለ ይመስለዋል - መሰለኝ። አይደለም ዛሬ ከግንቦት መግቢያ 2023 ጀምሮ በሚተማመንበት የዴሞክራቶች ሙሉ ድጋፍ በነበረበት ደረጃ አልነበረም። ማስተዋል ለሰጣቸው ሰብዕናወች 3/4ኛው ተስፋው አስቀድሞ ተቀዶ ነበር ለህወሃት። 
 
በትራንፒዝም ያለው ሁነትም አስተማማኝ የሚያደርግ ዋስትና አለ ብሎ ማሰብ የተገባ አይመስለኝም። በርካታ ተለዋዋጭ ውሳኔወችን ስለማስተውል። ትራንፒዝም ሰላም ይቅደምልኝ፦ የፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊው መርሁ ይመስላል። ወጪ መቀነስ። በሌላ በኩል እርግጡን ባላውቅም ህወሃት ከምሰማው በኤርትራ መንግሥትና በሱዳን መንግሥትም መተማመኑን እንዳለው አስተውላለሁኝ። ሱዳኖች እና የፖለቲካ አቋማቸው፤ የኤርትራ መንግሥት እና ፖለቲካዊ አቋም ህወሃት የኖረበት ስለሆነ ምንም አልልም።
 
እኔ ለህወሃት አስተማማኙ ጉዳይ ሊሆን ይገባል በምለው #መርህ ቢሆን ይሻለዋል። በህግ ለመገዛት መፍቀድን። ምኞትን በአለ ተጨባጭ ሁኔታ ላይ መመሥረትን፤ ቢያንስ እራሱ አርቅቆ ላጸደቀው ህገ - መንግሥት ለመገዛት መፍቀድ አዋጪ መስመር ይመስለኛል። 
 
ህወሃት በጀቱን የት ያገኛል?
ህወሃት በሚመራት ትግራይ ምን ያህሉ ህዝብ በዕለት እርዳታ ውስጥ ይሆን?
ህወሃት መውጪያ መግቢያ ደንበር አለው ወይ?
ህወሃት እራሱን ችሎ ይቆም ዘንድ ምን የኢኮኖሚ አስተማማኝ መሠረት አለው?
ህወሃት በጦርነቱ ምን አተረፈ?
ህወሃት ቀጣይ ጦርነት ቢያደርግ ምን ያሳካል?
ለህወሃት ከኢትዮጵያ ተነጥሎ መኖር የሚስገኜው ፋይዳ ምንድን ነው?
ህወሃት አለኝ የሚለው የመንፈስ ጥሪት ጭብጡ ምንድን ነው?
ህወሃት ነገስ መርህን ሆነ ህግን አክብሮ ለመጓዝ ምን ያህል ቁርጠኛ ነው?
ህወሃት ውህድ ማንነት ላላቸው ተጋሩ ጉዳይ ምን ያስባል?
የህወሃት የጥሞና ጊዜው መቼ ይመጣ ይሆን?
 
ህወሃት የወሎ እና የበጌምድር እና ስሜን ቀደምት ግዛቶች በነበሩት ወልቃይት፤ ጠገዴ፤ አድአርቃይ፤ ማይጠምሪ፤ ጠለምት እና ራዕያ በእጁ በመዳፋ እያሉ እኮ ነው ጦርነት የጀመረው። ይህ ፋክት ነው። አሁን ለትግራይ ህዝብ እነሱን ላስመልስልህ ነው የሚለው አመክንዮ ሚዛን የሳተ ነው።
 
በእጁ እያሉ እነኝህ ባዕቶች ለምን ጦርነት ጀመረ???? ስለዚህም የህወሃት የጦርነት ወይንም የህውከት ቀጣይነት እነኝህ በዕቶች ፈጽሞ ሊሆኑ አይችሉም። የህወሃት የመዳረሻ ፍላጎት የቀደመውን በኢትዮጵያ ላይ የበላይነት ማስመለስ ነው። የአፍሪካ አንከርነትም ምኞት ነው። ያ ደግሞ ይቻላል የሚል ግምት የለኝም። የትውልድ ጋፕ አለ። በተጨማሪም እራሱን በዲስፕሊን አርቆ፦ ግድፈቶችን አርሞ ቀጣይ ህልውናውን ለማስጠበቅ የፖለቲካ አቅሙም የለውም። ያለው እልህ ብቻ ነው። እልህ ጥበብ አይደለም። እልህ ግራጫማ የሲቃ ወኔ ነው።
 
?
 
ትግራይ በኢትዮጵያ ፓርላማ ውስጥ የለችም። --- ይህ አይጎረብጥምን???
ትግራይ ፌድሬሽን ምክር ቤት ውስጥ የለችም። - ይህ አያምም???
ትግራይ በካቢኔ ውስጥም ከዚህ ግባ የሚባል ወሳኝ ቦታ የላትም። - ይህ አይሰማንም???
ትግራይ በዕድሜያቸው ለፖለቲካ የደረሱ ወጣቶቿ በኢትዮጵያ ፖለቲካ እነሱም፤ ከእነሱም የሚገኜው በረከት ተስተጓጉሏል። - ይህ አይቆረቁርምም እንደ ድንጋይ መቀመጫ???
 
 
ጄ/ (ብጄ) ምግበይ ሃይለን በሚመለከት የተለያዩ መረጃወች ሲወጡ ተመልክቻለሁኝ። ዕውነት ሆነም ዕውነት አልሆነም እሳቸው የመሩት ጦር ነበር #በጭና የሰው ልጅ ቤት መቃብር እንዲሆን - የተደረገው። ተፈናቃዮች ወደ ቤታቸው መመለስ አልተቻላቸውም፤ ቤታቸው፤ ጓሯቸው የሰው ልጅ ቀብር ስለተፈፀመበት ብቻ ሳይሆን፦ ቀዬው ከእንሰሳት ውጪ ለሰው ልጅ ጠረኑ እጅግ አሰቃቂ እንደነበር ዘጋቢወች ሲዘግቡት ነበር። የዘመናችን ሰቅጣጭ ገመና። የተጋሩ ልጆችም በብዛት እንደተገበሩ አዳምጫለሁኝ። ሁሉም እናት አለው። እንደ ትውልድ ይህ ሊሰማን ይገባል።
 
አብሶ ፋኖ የአማራ የማንት እና የህልውና ተጋድሎ ከሊቀ - ትጉኃን ከተረከበ ዘንዳ በማስተዋል ሊራመድ ይገባል። ኃላፊነት እና ተጠያቂነት አለበት። የተጋድሎው ማዕከልነኝ ካለ ዘንዳ። መስዋዕትነቱም እጅግ የገዘፈ ነው። የደረሰው በደል ከልብ ይቅርታ ቢባል እንኳን ያን የተደራጄ የበቀልን ክምር ሊክሰው አይችልም። እንኳንስ ይቅርታ ያልተጠዬቀበትን። አጤ ፋኖ በሚወስዳቸው እርምጃወች እና ውሳኔወች ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል። ዝም ብለን ማዬታችን በእጃችን ምንም ነገር የለም ማለት አይደለም። 
 
ለደረሰው የግፍ በደል ፍትህ መስጠት አቅሙም ወርዱም ባይኖረንም፦ ግፍን እና የትውልድን መከራ የጋራ ማድረግ ግን ይገባል። ጨካኞች ምንጊዜም የቀልባችን ገዢወች ሊሆኑ አይገባም።
 
#መቋጫ ለእኔ።
 
ህወሃት አባላትም፦ አካላትም ደጋፊ ህዝብም አሉት። ህልውናው እንዲቀጥል የሚፈልጉ። መብትም ነው። በሌላ በኩል በአንድም በሌላም የህወሃት ናፋቂወች የኢህዴግ አድናቂወችም እንደ አሉ አሁን አሁን አስተውላለሁኝ። በተጨማሪም እጅግ ሙሉ ጊዜዬን ሰጥቼ ለታገልኩለት ለአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎን ሳስብ፤ ለህወሃት የማያባራ ፍላጎት ያላቸው፤ ተጋድሎውን ተገን አድርገው በስውር የህወሃትን የጸሐይ ቀን የሚጠብቁ፤ ህወሃት የሚፈጽመው ሁሉ ሽፋን የሚሰጡ ሳያስጠጡ ህወሃትን የሚደግፋ አያለሁኝ። እታዘባለሁኝ።
እርግጥ ነው የተሻለ ተጠብቆ ታይቶ በማይታወቅ የሰቀቀን ረግረግ ውስጥ መንፈሳችን እንደባጄ አውቃለሁኝ። ይህም ቢሆን የተሻለን ሳስብ ጭካኔን /// በጭካኔ አጣፍቼ ጭካኔን ልናፍቅ ፈጽሞ አልችልም። ሳላውቅ ብዙ አቅም ያፈሰስኩላቸው ሰብናወች አፍቅሮተ - ህወሃት ቀበቷቸው መሆኑን ዛሬ ዛሬ አስተውላለሁኝ። 
 
በእኔ ህይወት አንድን ነገር እምቀበለውም፤ እማምነውም አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ሳንክ ካገኜሁ - አልመለስበትም። አብሶ መታመን ከከፋው። ህወሃትን መኖሬን ያጎሳቆለ፤ ትምህርቴን ተረጋግቼ ተምሬ ቤተ - ዕውቀት እንዳልሆን ሰላሜን ያወከ ድርጅት ስለሆነ፦ ለአንዲት ደቂቃ ደግፌው አላውቅም። ለረጅም ጊዜ በጥሞና ቆዬሁ። ከዛ ጭካኔው ሲከረፋ - ሞገትኩት። አሁን አልሞግተውም። ግን በተአምር አቤቶ ህወሃት አይናፍቀኝም። አረመኔነት ምኑ ይናፍቀኝ? ሲኦልነቱ ምኑ ትውስታ ያሳድርብኝ? ጉድጓድነቱ? ቀራኒወነቱ ከሥልጣን ወርዶ በተከፈተው ጦርነት ምን ያህል ግፍ እና ጥሰት እንደፈጸመ አዬሁ እኮ??? ከሚታገለው ተሽሎ መገኜት ሲገባው የሥልጣን ዘመኑ የሠራውን ሁሉ እኮ ነው ያወደመው??? ይህ ሽው ሊለኝ? አይታሰብም። 
 
ነገር ግን ማንም ዜጋ ግሎባሉን ጨምሮ ህወሃትን መቀበል አይደለም አምላኬ ብሎ ታቦት ቢቀርጽለት የባለመብቱ - መብት ነው። እኔ ግን ቁስል እዬቀረፍኩኝ በቀልን አላበረታታም። ቂምን እያቆላመጥኩኝ ሰርክ አልጨቃጨቅም። ግን ህወሃት በኢትዮጵያ መንበረ - ሥልጣን ቁልፋን ቦታ ደግሞ ይቆናጠጥ ዘንድ ቅንጣት አቅም አላፈስም።
 
ዶር ደብረጽዮን ገብረሚኬኤል አቅም የላቸውም፦ ኢትዮጵያን ለመምራት የሚል ጽኑ አቋም እና እምነት አለኝ። ስብሰባ ትርታው የሆነው ባለሪከርዱ ህወሃት ማዕከላዊ መንግሥትን ይመራ ዘንድ አይናፍቀኝም። ፈጽሞ! ይህ ሁኔታ የሚፈጠር ከሆነ ትርታዬ እስካለች ድረስ መቀነቴን ከቁም ሳጥኔ መዥለጥ አድርጌ፦ የብዕር ሙግቴ ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ፦ በሰከነ መንገድ እቀጥላለሁኝ። ይህን ስል ከጀማሪ የፖለቲካ ድርጅት አንጋፋው የዞግ ድርጅት በልምድም በተመክሮም እንደሚበልጥ አውቃለሁኝ። መብለጡ ለስኬት፦ ለሰውኛ፤ ለተፈጥሮኛ፤ ለአጽናኝነት፤ ለአይዟችሁ ባይነት፦ ካላበቃው ዕድሜው ቁጥር ብቻ ይሆናል። ካልኩሌሽኑ ትናንትም የገደፈ ነበር፤ ዛሬም ዕብን ነው። የቅንነት ድርቅ የመታው ድርጅት ነው ህወሃት። 
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
 
ምዕራፍ ፲፭ በዚህው ይጠናቀቃል። የእኔ ውዶች ለማድመጥ፤ ለጥሞና ጊዜ ያስፈልገኛል። ደህና ሰንብቱልኝ። አሜን። ቸር ያገናኜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
01/94/2025
 
ትዕግሥት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል።
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?