#የኩርፊያ #ፖሊሲ እና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ።

 

#የኩርፊያ #ፖሊሲ እና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ።
 
"ለተከፋ ማጭድ አታውሰው።" 
 
"ከፍትፍቱ ፊቱ።"
"እንዳያማም ጥራው እንዳይበላም ግፋው።" የጤና ባለሙያወች ከጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ጋር የነበራቸው መቅድመ ግንኙነት እነኝህ ይተባህሎች ይገልጡልኛል። 
 
"ጥበብን ከወደድሃት ትዕዛዙን ጠብቅ
እግዚአብሄር ጥበብን ይሰጥሃል።"
(መጽሐፍ ሲራክ ምዕራፍ ፩ ቁጥር ፳፭)
 

 
ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ከማህበረ ቅንነት የጤና ባለሙያወች ጋር የሚያደርጉትን ውይይት በጥንቃቄ ስጠብቀው ነበር። ሕይወት፤ እስትንፋስ፤ ነፍስ፤ ሩህ፤ ሥጋ፤ ሰው፤ መኖር፤ ተስፋ ከእግዚአብሄር በታች ከሙያው ጋር በእጅጉ የተዋህዱ ስለሆነ በብርቱ ጥንቃቄ እና ማስተዋል ከጤና ጋር የተያያዙ ክስተቶች ሊያዙ ይገባል ባይም ነኝ።
 
በኢትዮጵያ የጤና ባለሙያወች ታሪክ ውስጥ "#እራበን፤ ባለቤቴን #በሽሮ አረስኩ፤" ወዘተ የሚሉ የሁላችንም የህሊና ጓዳ የፈተኑ ክስተታዊ ሁነቶችን መከታተል የተገባ ስለነበር ተከታትየዋለሁኝ። በዚህ ዙሪያ በሌላ መድረክ "እኔም የደሞዝ ጥያቄ አለኝ" የጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ሳስታውሳት #ውሽክ የምታደርግ ተረባዊ አገላለጽም ስትገርመኝ ሰነባብታለች።
 
እሳቸውም፤ ባለቤታቸው ቀዳሚ እመቤቱትም፤ እንዲሁም የካቢኔ አባሎቻቸውም #የሞድ ዲዛይነር ሲሳይ ሆነው እንደባጁ ልባቸው ያውቀዋል። ቤተመንግሥታቸው ፕሮቶኮሉ የአመጋገብ ሥርዓቱ ቡፌ ነው። የሰርክ ቡፌ። በሌላ በኩል ክብራቸው ተጠብቆ፤ በፈለጉት ጊዜ ለአጫጭር አገራዊ ጉዞ ኤሊኮፍተር፤ ረጅም ጉዞውን በአውሮፕላን ዓለምን እያዳረሱ የሚገኙት ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ፤ የኖቤል ተሸላሚ፥ እኔም የደሞዝ ጭማሪ ጥያቄ አለኝ፤ ወይንም ደሞዜ አይበቃኝም የተዋጣለት አክተርነት ነው። 
 
ሠርክ ቡፌ፤ ሰርክ በቅንጡ ሆቴል፤ ሰርክ በግብረ ሰላም ቅብጥ እና ቅልጥ የሚሉ ጠቅላይ ሚር እራሳቸውን በልፋት፤ በትጋት፤ በብርታት ተምረው ግን የዕለት ኑሮን ለመሸፈን #አቃተን ካሉ የህክምና ባለሙያወች ጋር ማለካካት የተገባ አይደለም። ማለካካት፤ ማፎካከር፤ መፎካከር ከሚችል ጋር ነው። ቤተ - መንግሥትና ኮንድሚኒየምን (የቀበሌ ቤት) ለፋክክር ማቅረብ እራስን ያስገምታል። ለእዮቤል ቤተ - መንግሥትም እራሳቸውን እያሰቡ ስለመሆኑ ዜናወችን አደምጣለሁኝ።
 
ለአንዲት በኢኮኖሚ ከአደጉት ጋር ስትነፃጸር ዝቅ ብላ በምትገኝ አገር ያለው ቤተ መንግሥት ይበቃ ነበር። ልዩ ድሎት እና ምቾት ከመሻት፤ ዕውነት ከሆነም (መረጃው እርግጠኛ ስለማያደርገኝ) ያ ሁሉ ሃብት ከሚፈስበትም። አዲስ ቤተ - መንግሥት፦ ቅንጡ፤ ዝንጥ ያለ፤ ቅብጥ ቅልጥ የሚያደርግ ለኢትዮጵያ ቀዳሚ ጥያቄ አይደለም። ምቾት ለናፈቀው መሪ ግን በኽረ ጉዳይ ነው ይባላል።
 
ይህም ሆኖ ስናምጥ ሰነባብተን ከጤና ባለሙያወች ጋር ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ተገናኝተዋል። ስጠብቀው የሰነበትኩት ጉባኤ ግን በሩ #ተከርችሞ ነው ታደሙብኝ ያለው። እኔ መጀመሪያ ገጽን ነው እማየው። የፈለገ የገዘፈ ጉዳይ ኑሮኝ የጨፈገገው ገጽ ከገጠመኝ ጉዳየን ውስጡን ሳልገልጥ ከድኜው እመለሳለሁኝ።
 
ጥበበኞቻችን አባቶቻችን እና እናቶቻችን "ከፍትፍቱ ፊቱ" ሲሉ የተቃኙትም ለዚህም ነው። እየተራባችሁ ራህባችሁን ለወላጆቻችሁ ከመግለጽ በራህብ #ሙታችሁ ማየት ይናፍቀኛል የሚል የአገር መሪ ሰውኛም፤ ተፈጥሮኛም አይደለም። ኩርፊያው ምንጩ ያ ስለሆነ። ሁልጊዜ መንግሥቴ እና ፖሊሲየ ፍጹም፦ ዝንፍ የማይል ነው ብሎ ማሰብ #ድብ ያለ መታበይም ነው። 
 
በኢኮኖሚዋ ኋላቀር በሆነች አገር ቅንጡ የከተማ፤ የኮሪደር፤ የሆቴል ግንባታ እየተደረገ የመጨረሻው የዕውቀት ዘርፍ "#ራበኝ" ሲል መደመጥ ለዛውም በአክብሮት ሊሆን በተገባ። የመጀመሪያው ህዝባዊ ስብሰባም ለዚህ ሰባዕዊ ማህበረሰብ ሊሆን በተገባ ነበር። ስብሰባወቹ ለእኔ #የብልጽግና የምረጡኝ ቅድመ ቅስቀሳ እንደሆኑ ነው እማምንበት። 
 
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድም ጉዳዩን አትኩሮት ሰጥቶ ሊከታተለው ይገባል። በመንግሥት በጀት ብልጽግና ብቻ የተቋም መንፈስ ግንባታውን ሲያጧጡፈው አቤቱ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ጨከን ብሎ መርኽንም እራሱንም ቢያስከብር ይከበር ነበር። ሌሎች ቢያደርጉት አለንጋውን መዥለጥ አድርጎ እንደሚነሳው ሁሉ።
 
የሆነ ሆኖ በጉጉት የጠበቅኩት የጤና ባለሙያወች እና የጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ሃዲዱ በዚህ መሰል #አላያችሁም፤ ግን #ተናገሩ ጥንዙል የዛለ፤ የሚያዝልም ድባብ እንደምን ለወደፊት ጤናማ ሐዲድ ሊያዘረጋ እንደሚችል አላውቅም። የእኔ የማድመጥ ፍላጎቴ ነው የተዘጋው። የሚር መሥርያ ቤቱ ሹመኞች የሚሰጡት መልስም አሳዛኝ ነው። ዕውነት የተገፋበት። መርኽ አድራሻ ያጣበት።
 
እነኝህ ተምረው፤ ደክመው፤ ጥረው ግረው ከመጨረሻው የዕውቀት ደረጃ የደረሱ የሊቃውንታንት ቁንጮወች በኢትዮጵያዊ ትህትና መሪያችን ጠሚር አብይ አህመድ እንኳን ደህና መጡልን ብለው ከመቀመጫቸው ተነስተው ሲቀበሏቸው ይህን ያህል ፍቅራዊ አክብሮትን አልይህ ብሎ መግፋት አለመታደል ነው። ጤናማም አይደለም።
 
ለነገሩ ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ በሰማያዊ ንጹህ ዕድላቸው መጠቀም ያልቻሉ፤ ፍቅርን አክብሮ ለማስተዳደር ያልፈቀዱ በመሆናቸው ያ ሁሉ ሚሊዮን ህዝብ የሰጠውን ልባዊ ንጹህ ፍቅር ፈቅደው #ደፍተውታል። ስለሆነም ዛሬ ባሳዩት የማግለል፤ ከውስጤ የላችሁም፤ ላያችሁ አልፈቅድም ዓይነት እርምጃቸው አልደነቅም። አላዝንምም። ግን ኢትዮጵያ እና ሚስጢሯ ለሁላችን እንደከበዱን ተረድቸበታላሁኝ።
#ኩርፊያ ለመሪ??? ለዓለም የሰላሙ ሎሬት አባት? ሰላም እራሱ ለስደት ያመለክታል። "ካለ ቤቱ ዶሮ ባጓቱ።"
 
ኩርፊያ ለፓን አፍሪክስቷ ኢትዮጵያ? ኩርፊያ ፖሊስ ይሁነኝ ማለት፤ ምን የሚሉት መንገድ ይሆን? የአብይዝም መንግሥት እና የጤናው ሴክተር ትጉኃን ድልድይ እንዴት በዚህ መስመር ጤናማ ሆኑ ሊዘረጋ ይችላል? ከፋን ያለ ቤተሰብ ምን ሆነህ ከፋህ? ቀረብ ብየ እየደባበስኩ ላደምጥህ እሻለሁ ማለት እንዴት ያቅታል? ከተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ገዢው ብልጽግና ትሁታዊ አክብሮትን #በብልጫ ሥራ ላይ ለማዋል ስለምን ይጨንቀዋል? ዥንጉርጉር።
 
ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድን መሪየ ለሚሉ ሁሉ ይህ ግብረ መልስ ምን አሉታዊ የዜና በረከት ያቀርብላቸዋል? የነገ የኢትዮጵያ መሪወች ከዚህ እጅግ ደካማ አያያዝ ምን ሊማሩበት ይችላሉ? አንድ የአገር መሪ ለሚመራው ህዝብ #ንጉሱ አይደለም። #ሎሌው ነው። ሎሌነት ደግሞ እንዲህ እና እንዲያ ተሁኖ አይሆንም። ቤት ጠርቶ፤ በር ዘግቶ፤ ቁልፍ ሰብራችሁ፤ ሥርዓት ጥሳችሁ ግቡ እና አዳምጡ? ለማን ይጠቅማል? "የሚያድግ ጥጃ ከገመዱ" ይላሉ አበው እና እመው። ከመግቢያው ነው ትልሙ ያነከሰው። "ሆድ ለባሰው ማጭድ አታውሰው።"
 
7 ዓመታት ሙሉ ኩርፊያ???? መጥኔ አንች ፈላስፊት ኢትዮጵያ? ነገሽ በእጅጉ ያሳስበኛል። በተደገሰው ቅድመ የፍርኃት ደርዘን የጭንቀት ቋት፤ እጁን አውጥቶ የመረጠን ወገን በዚህ ዓይነት #ጥዩፍ አተያይ ለዘመን ለራሱ ዕዳ ነው። የውሸት ሳቅም እንዲስቁ አልሻም ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ። ከውሸቱ ይሄኛው ተጠርታችኋል፤ ላያችሁ ግን አልፈቅድም የሚሻል ይመስለኛል። ግን ለምን ይመስለኛል አልኩኝ። ነው እንጂ።
 
የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያወች ሐኪሞች ብዙም በፖለቲካ የመሳተፍ ፍላጎት የላቸውም። ለተግባራቸው ትጋት ሎጅስቲክ ባልተሟላባት አገር፤ አብዛኛው ህዝቧ ለመጠለያ፤ ለከፈን እና ለለት ጉርስ ያልበቃ፤ ሲታመም መታከሚውም፤ መመርመሪያውም፤ መዳህኒት መግዣውም የማይቻል በሆነበት ዘመን ሃኪም መሆን ፈታኝ የሆነ ጉዳይ ነው።
 
 በዛ ላይ ያልተቋረጠ ጦርነት እና ቀውሱ ሲታከል የቁስለኛው መበራከትም ሌላ የፈተና ዶፍ ነው ለዘርፋ። ስለሆነም እኔን እንደሚገባኝ የኢትዮጵያ ሃኪሞች የሚያሳስባቸው የበሽተኞቻቸው ፈውስ እንጂ #የሥልጣን ውድድር አይደለም። አይተንም አናውቅ። በታሪክ አምስት አይሞሉም ከዘርፋ በቁልፍ ፖለቲካዊ ዕሳቤ የተሳተፋ። ከሁሉ በላይ እነኝህ ዓራት ዓይናማ ሊቀ - ትጉኃን በዘመነ ኮፒድ የከፈሉት ሰማዕትነት ለምን ይረሳል? 
 
እርግጥ ነው የብልጽግና ተቃዋሚ መንፈሶች በተሻለ ሃሳብ፤ በበለጠ ተቋም እራሳቸውን አደራጅቶ ለፍሬ ከመብቃት #ኳሽ ባለ ቁጥር ተስፈኝነት የተለመደ ነው። ሁልጊዜ አሽኮኮነት ይናፈቃል። ቢመኙትም ግን እራሳቸው ባልደከሙበት ማሳ የሚታፈስ ሰብል እንደሌለ ጊዜ የኔታ ነውና ቢማሩበት ምርጫየ ነው። እነሱ መንፈሱን #ሰፍ ባሉለት ቁጥርም ዕውነተኛው የሃኪሞች ጥያቄ መልስ ያጣል። ለዚህም ነበር አስቀድሜ እኔ የፃፍኩበት። ምክንያቱም የሚሊዮኖች የጤና ጉዳይ በባለሙያወች መዳፍ ነው ያለው። ስለሆነም በማናቸውም ሁኔታ ፖለቲከኞች ይሁኑ ሚዲያወች በማስተዋል እራስን መግራት ይጠበቅባቸዋል ባይም ነኝ። ለህዝባቸው ሊያስቡ ይገባል።
 
የአማራ ሰላማዊ የበቃን ንቅናቄ ድርጁ ነበር። እጅግም ጉልበታም ነበር። ሁሉ ጎመጀበት። በእጃቸው ላይ ያለውን ዕድል የበተኑ ፖለቲከኞች ገቡበት። ተው እያልኩኝ። የተከፈለው መስዋዕትነት እና ስኬቱን በማስተዋል መመርመር ነው። የአብይዝም ሥርዓት አልተመቸኝም የሚል የፖለቲካ ኢሊት #ከሞፈር #ዘመት የኮፒራይት ሽሚያ ወጥቶ አቅም ፈጥሮ፤ በአቅሙ ልክ ምኞቱን ቢያሰክን በትህትና ላሳስብ እሻለሁኝ።
 
ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ሰው ናቸው። አንድ ግለሰብ። ስለሆነም በአመራራቸው፤ በፖሊሲያቸው፤ በቲም መሪነታቸው የተለየ ቅድስና የላቸውም። ወዘተረፈ ስህተት፤ ድክመት፤ የአፍ እላፊ አለ። ስለሆነም በሚመሩት ህዝብ እና በሳቸው ማህል ክፍተት አለ። ክፍተቱን እጅግ እራስን ዝቅ ባደረገ ትህትና፤ ህዝብ ተከብሮ፤ ልጆቹ የሚያነሷቸው ጥያቄወች በሚገባ አትኩሮት ተሰጥቷቸው፤ ባልታቀደ ውሽልሽል ሁነት ሳይሆን፤ በታቀደ የመፍትሄ ቅደም ተከተል ወደ ተጨባጭ የተግባር መስክ ሊገባ ይገባል። የፈንግጠው፤ የኩርፊያ፤ የአሸናፊ እና ተሸናፊ፤ የፍረጃ ድሪቶወችን አጥርቶ በተቀራረበ፤ ከልብ ባደመጠ፤ በአዲስ የፖሊሲ አቅም በታገዘ ሁነት የዓይነት ለውጥ ለማምጣት፤ አቅምን መጥኖ መንቀሳቀስ ይገባል።
 
በሌላ በኩል የቁልፍ መሪወች ጉዳይም ወሳኝ ነው። ሚኒስተሩን በዞግ የኮታ መደላድል ሳይሆን ጠረናቸውም፤ ተግባራቸውም አንቱ በሆኑ ለአሰተዳደር፤ ለሰብዓዊነት ቅርብ የሆኑ ሊቃናት ሊመራ ይገባዋል ባይም ነኝ ጤና ሚኒስትር። 
 
#ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ሆይ!
 
ኩርፊያ የአገር መሪ ፖሊሲ ሊሆን አይገባም። የገበጣ፤ የዳማ፤ የልጆች የእንድርች እንድርቺ፤ ወይንም የግጥግጥ ወይንም የጫጉላ ሽርሽር አይደለም የአፍሪካ ቀንዲል አገር የኢትዮጵያ መሪነት። ኢትዮጵያን ያህል አንከር አገርን ለመምራት መታደል ልዩ ሰማያዊ ስጦታ ነው። ይህን ስጦታ እንደ አልባሌ አይቶ በማጣጣል ወይንም በመገላመጥ ቀጣይ ዕድል ደግሞ ላይገኝ ይችላል። 
 
የቀጣዩ ምርጫ ቀን ሁሉም ህዝብ ከቤቱ ቁጭ ቢል፦ ምን ሊያደርጉት ይችላሉ? 120 ሚሊዮን ሠራዊት አለወትን አስገድዶ ለድምጽ ህዝብ የሚያወጣ። ተገዶም፤ ተገፍትሮም እንደዛም ቢወጣ ምርጫ ካርዱን እየቀደደ የቁርጥራጭ ባስኬት ቢያደርገው መራጩ ህዝብ ምን ሊባል ይችላል? የከፋው፥ መከራው ያንገፈገፈው ህዝብ ልቡ ሙሉለሙሉ የሸፈተ እንደሆን ማጣፊያው ያጥረወታል። ለዛ ከተበቃ። ምርጫ ለማካሄድ የኢትዮጵያ የሰላም ዋስትና እርግጠኛ ካደረገ። 
 
እባከወትን እስኪ #ደግመው ይዩት አገባበወትን። ይህ ለዓለሙ የሰላም አባት ለሎሬት ይመጥናል???? ይጨንቃል። በዕውነት ይጨንቃል። "እንዳያማ ጥራው፤ እንዳይበላም ግፋው" በትክክል የተተረጎመበት ነው። ኢትዮጵያ እኮ ለእርስወም ለጤና ባለሙያወችም እኩል እናት አገር ናት። የዜግነት #ሲሶ፤ የዜግነት #እርቦ የለውም። ለዚህ ዕድል ላበቃወት አምላክስ ምን ውለታ ይከፍሉለታል? የተነሱበትን ያውቁታልና። ምርቃት እንጥፍጣፊ የለውም። ምርቃት በላይኛው ከተነሳ ሙሉው ነው የሚነሳው። 
 
መሪነት ጥበብ ነው። የሚሰጠውም ከላይ ነው። ጥበቡም ቅብዓውም። ጥበብ ደግሞ ለሰማዩም ለምድሩም ህግ ተገዢነት ነው። የመሪነት መፍቻው ጥበባዊ ብልህነት ነውና።
 
ማህበረ ቅንነት እንደምን አደራችሁ፤ ዋላችሁ? አረፈዳችሁ? ቢገርመኝ ነው ይህን ጉዳይ ባሊህ ያልኩት። አክሰሱ ላላቸው ልጆች ማናቸውም ተግባር በጥንቃቄ ሊከወን ይገባል።
 
በመጨረሻ ሰማዕትነት የተቀበሉ የጤና ባለሙያወች አሉ። ኃላፊነቱን መንግሥተወት ሊወስድ ይገባል። ልጅ፤ ትዳር፤ ወላጅ አላቸው እና። ፈውስ ሊታሠር ስለማይገባ ይቅርታ ተጠይቀው የታሰሩ የጤና ባለሙያወች ሁሉም ሊፈቱ ይገባል። ከጤና ጠባቂ መድህን ጋር እልሁም፤ ኩርፊያውም፤ በደሉም ሊቆም ይገባል። 
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከመላው ኢትዮጵያ ከተውጣጡ የጤና ባለሙያዎች ጋር ያካሄዱት ውይይት
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
24/06/2025
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ትዕግሥት ሲያልቅ፤ ፍቅር ይሰደዳል።
ፍቅርም ሲያልቅም፤ ትዕግሥት ይሰደዳል።
0:07 / 0:08

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?