#በኖኽ #መርከቡ የአባይ ብሥራታዊ ዕጹብ ብራንድ ትልም ፍፃሜ እንኳን ደስ አለሽ ልዕልት ኢትዮጵያ! በልጆችሽ የተግባር ልዕልና #ልዩው #ብራንድሽ ለወግ በቃልሽ! !#እሰይ! ዛሬ ለእኔ ዕንቁ #ብሄራዊ ቀኔ ነው።
ዛሬ ለእኔ ዕንቁ #ብሄራዊ ቀኔ ነው።
"አድርገህልኛል እና አመሰግንሃለሁ።"



ዘለግ ያለ ጹሁፍ ነው። ለቅጽበታውያን ሳይሆን የተረጋጋ፤ የጨመተ መንፈስ ለተመረቀላቸው፤ የትውልድ ጉዳይ ህሊናቸው ለሆነ ቅኖቼ የተፃፈ ማስታወሻ ነው። አመሰግናለሁኝ ጊዚያቸውን ለእኔ ለሚሸልሙ አዱኛወቼ።
#መርኃች ሆነ መሪያችን የዕውነት ተፈጥሮ ይሆን ዘንድ እንፍቀድ። ትሁታዊ ልመናዬ።
ይህ ከደስታ በላይ ሐሤት ነው። ከምድር እስከ አርያም ፍጹም የሆነ ልዩ ቅዱስ መንፈስን የሚመግብ። የሰው ልጅ አለሁ፤ እየኖርኩ ነው ማለት የሚችለው ዕውነትን #የማይፈራ ሲሆን ብቻ ነው። ዕውነት ለቤት እና ለዱር እንሰሳት - አልተፈጠረም። ዕውነት ለጋራ ሸንተረሩ - አልተፈጠረም፤ ዕውነት ለወንዝ ፏፏቴ - አልተፈጠረም። ዕውነት ለዝናብ - አልተፈጠረም።
ዕውነት ለወጀብም - አልተፈጠረም። ዕውነትበዕውነትነት የተፈጠረው የሰው ልጅ እንዲኖርበት ነው። ዕውነት የሆነውን ዕውነት፤ ሃሰት የሆነውን ደግሞ ሃሰት ማለት ይገባል። በዘመናችን ታላቅ የተግባር ተጋሎ ለስኬት ሲበቃ የእኔ ማለት ይገባል። ሊቀ ትጉኃንን ለማመስገን ቆጥቋጣ ልንሆን አይገባም።
#ኢትዮጵያዊነት ሜዳ በቀል አይደለም! ኢትዮጵያዊነት የእዳሪ ግኝትም አይደለም። የዊዝደም እንጂ።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መሥራችነቷ፦ ኢትዮጵያ የዓለም አንድነት ከመሠረቱ ቀዳሚ አገሮች መመደቧ፤ ኢትዮጵያ የቀጥታ ቅኝ ግዛትን፤ የእጅ አዙር ቅኝ ተገዥነትን ስውር እና ግልጥ ቅዠትን ያነኮተችበት፤ እንዳይነሳ አድርጋ ቀብራ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ጠሐይ፤ የልዕልና ጉልላት፤ የልቅና ተክሊል የሆነችበት ልዑቅ ሚስጢር ኢትዮጵያን በኦርጋኒክ ተፈጥሮ አንጸው ኢትዮጵያ አድርገው የሠሯት የቀደምቶቹ ዊዝደም ነው።
ትናንት ለዓለሙ የሰላም አባት የኖቤል ሽልማት፤ ዛሬ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ለዚህ ወግ እና ማዕረግ የበቁት ኢትዮጵያ የምትባል አገር ቀደምቶቹ በልኳ አድርገው ስለፈጠሯት ነው። የኢትዮጵያ ልክነት ተፈጥሮዋ #ኦርጋኒክ መሆኗ ነው። ቅብ አይደለም።ፌክ አይደለም።
በዚህ ዕሳቤ እናቴ፤ እምየ ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ወሳኝ ሚናዋ የተመሰጠረች አገር ትሆን ዘንድ በጸሎት፤ በሱባኤ ቅድስናን መግባታለች። ግዕዝ ቋንቋ በበረከት ሸማ አጎናጽፏታል እናት ኢትዮጵያን፤ የዝማሬው ሊቀ - መኳስ ቅዱስ ያሬድ በግዕዝ፤ በዕዝል እና በአራራት ጹዑም ቃና እና ቅኔ አስጊጧታል እመቤት ኢትዮጵያን።
በሌላ በኩል የውራጅ ቀሚስ ያልሆነው፤ የትውስት ጌጥ ያልሆነው፤ የብድር ዱቄት ያልሆነው የልዕልና ብቁ ጀግና ወታደሩ የአማርኛ ቋንቋም የኢትዮጵያ የመንፈስ ሚስጢርነት የተቀመረበት ቅኔዋ ነው ለእምዬዋ። ኢትዮጵያ የእስልምና ሃይማኖትን ለሚከተሉ ልጆቿም ከፈቀደችበት ዕለት ጀምሮም የእስልምና ዕምነት ንጽህና፥ የድዋ የአርምሞ ጊዜም፤ ኢትዮጵያን ተፈሪ፤ ህብረ ብሄራዊ አገር እንድትሆን አድርጓታል።
#መቼውንም የማይሳካው ኢትዮጵያን አቅልሎ የማዬት እከክ አይሳካለትም።
በተሠራች አገር መንበር - ተረክቦ ወይንም ለመረከብ እራሱን ያጨ፥ ክብር እና ማዕረግን በሞገስ ተጎናጽፎ፤ የተሠራችበትን ሚስጢር መናቅ፤ ማጣጣል፤ ምን አላት እና በትምህርት ካሪክለም ኢትዮጵያኒዝም ይቀመር ትላላችሁ ብለው የሚያላግጡትን፤ የዘመናችን እራስ ገሊቦወች እና እሷን ፍርስራሽ ለማድረግ፤ ለመናድ የሚካሄደው ግብግቡ የውርንጫ ድካም ነው። "በማን ላይ ቆመሽ እግዜሩን ታሚያለሽ ነው።"
ኢትዮጵያ በንግሥት ማክዳ፤ ኢትዮጵያ በቅዱሳኑ አብርኃም እና አጽብኃ፤ ቅዱሱ ኢዛና፤ ኢትዮጵያ በሮኃ ዘመን፤ ከዛም በቀደመ በአክሱማውያኑ፤ በሳብውያን፤ ንግሥናውን እርግፍ አድርጎ በገደመው ቅዱስ አባት መሐንዲሱ ሐዋርያ ላሊበላ ዘመን፤ ኢትዮጵያ በአጤ ፋሲል፤ በአጤ በካፋ፤ በንግሥት ምንትዋብ ዘመን ብርና የማይችለው የቁም ነገር ህብር #ዕንቁ ውጤት ናት። ለዚህ ነው የፋንታዚ ባለሟሎች ኢትዮጵያን ለመዳፈር አልመው ግን ነኩተው የሚቀሩት።
#ኢትዮጵያን በጭልፋ አትሰቧት።
ኢትዮጵያ ጥልቅ፤ ሰፊ የቅድስና ውቅያኖስ ናትና። ብዙ ብትክ የፖለቲካ ትንተናወችን አዳምጣለሁኝ። ብዙ በቅናት ወፍፈው የሚወድቁ፤ ሊነሱ የሚድሁ የቅርብም የሩቅም የጎረቤት አገራት ምኞትንም አዳምጣለሁኝ። ኢትዮጵያ አትቻልም! ፈጽሞ አትቻልም! ኢትዮጵያ እንደ እጅ እንደ ተሠራ ዳንቴል እንደ አሻ የምትተረተር አገር አይደለችም።
ሳይንቲስቷ ኢትዮጵያ ዕምቅ ሰማያዊ ቅዱስ መንፈሳዊ ጸጋ፤ ምድራዊ የጨመቱ ሃብታት ከከርሰ ምድሯ በታችም አሏት። የኢትዮጵያ ጸጋ መንፈስ ነው። መንፈሱ ቅዱስ ነው። የነጠረ! የበቃ! የጠራ ቅዱስ መንፈስ ያላት አገር ናት - ኢትዮጵያ። ለእኔ እንዲያውም እንደ አህጉር የማይበት አመክንዮ አለኝ። ይህን ልኳን የማያውቅ ዕብን መንፈስ ሲብተከተክ አዳምጣለሁኝ። ነኩቶ - ይቀራል። እደግመዋለሁኝ። ነኩቶ ይቀራል። ሥሟን - ሲታገል - ብቃቷን - ሲያራክስ የኖረ የፖለቲካ ዕሳቤ ወድቆ ይቀራል።
ዩንቨርሷ ኢትዮጵያ ብዙ ያላት የቸርነት አገር ናት። ለዚህ ነው ኢትዮጵያ አናባቢም፤ ተነባቢም፤ ሰዋሰውም ናት ቅድስት አገር ኢትዮጵያ የምለው። የሰጠችኝን እኔ እራሴ አውቀዋለሁ እና። ለዚህ ተፈጥሮዋ ያልባለቀ አመራር ያስፈልጋታል። ስለሆነብ ገዢወቿ ልታስቡበት ይገባል። በቀደምትነቷ የሸፈተውን ልቦናችሁን ምህረት ጠይቃችሁ ከስደትም አድኑት።
#ሌላው ኢትዮጵያ ከፖለቲካ ሊቃናቷ በላይ ያለች ፍጽምት አገር ናት።
የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ከኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ዕሳቤ፤ ዛሬ ተሰርተው፤ ሦስት ወር ሳይሞላቸው ብትንትናቸው እንደሚወጡት ቤተ - ፋንታዚወች፤ ለቅመው - በሚያፈሱ፤ ያፈሰሱትን በዛው ገረጭራጫ መንፈስ ትውልድን ሲያባክኑ እና ሲባትቱ ቆይተው በመልቀም፤ ዛሬ የፈጠሩትን ድርጅት ነገ ከሚፈሱት በላይ፤ በላይ ነው የኢትዮጵያ የአፈጣጠር - ሥህን።
የኢትዮጵያ ልዕልና በተመሰጠረ ልቅናም ነው። ምርቃቷ አልፋ እና ኦሜጋ ነው። የሃይማኖት አገር እኮ ናት ቅድስቷ ኢትዮጵያ። ይህ ቢረዳን በኢትዮጵያ ምድር ላይ አይደለም የሰው የእንሰሳም #ደም አላግባብ የሚፈስባት አገር ባልሆነች ነበር። ኢትዮጵያ በሰባዕዊት መብት ጥበቃ፤ በሰባዕዊ መብት አያያዝ ተምሳሌት አገር ማድረግ ይቻል ነበር። ኢትዮጵያ የአፈጣጠር ድህነት የለባትም። እስኪ አንዱን የቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶን የዕውቀት ልክ መርምሩት። ዲካ የለውም።
ዘመን ከዘመን አላአግባብ የሚፈሰው - የሚፈራርሰው - የሚወድመው - መዋለ ሥልጡን መንፈስ፤ መዋለ - ንዋያ፤ የሚባክነው ጊዜን በአግባቡ ማኔጅ ቢደረግ ኢትዮጵያ ከሞሪሺየስ አንሳ ባልተገኘች ነበር። "አያ እንቶኔ ሰው ገዳይ፤ አያ እከሌ አገር ገዳይ" ብለን የምንተቸውን ወደ እራሳችን አቅርበን ብናየው ቢያንስ እኛ ጊዜ ገዳይነታችን ሊያስማማን እንደሚች ይሰማኛል። እምናጠፋው ጊዜ እኮ ለብልህነት አይደለም። አሁን ዛሬ ስለ እንኩቶ ነገር ይዞ መቅረብ ሰባራ ገልነት ነው። ስለ አንድ አክቲቢስት ቅል ሃሳብ ይዞ የመጣን የቤታችን ባልደረባችን ሳይ እኛ እና የኢትዮጵያ መሻት እርቀታችን ምን ያህል እንደ ሆነ አስተዋልኩት።
አጀንዳችን #የኖኽ መርከባችን የግብጽን የፖለቲካ ሊቃናትን እና የፈጠራቸውን አሰሮች በጥበብ የረታችበት የእመየ ኢትዮጵያ ትንግርታዊ ቀን ብሄራዊ ቀናችን በሆነ ነበር።
#የኢትዮጵያ ፖለቲካ ኢትዮጵያን አያውቃትም።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ መንፈስ በልኳም አልተፈጠረም። ለዚህ ነው እኔ ምዕራቡ ይሁን ምስራቁ ዓለም የፈጠረው ርዕዮትም፤ የፖለቲካ መስመርም፤ የፖለቲካ ድርጅት ለኢትዮጵያዊነት ማንነት ልኩ አይደለም ብየ እምሞግተው። ከሦስት ዓመት በላይ ሆነኝ በየዕለቱ የሚፈለፈሉ የፖለቲካ ዕሳቤን የሚወክሉ የንቅናቄ አዲስ ሥያሜወች ፔጄ ላይ እማላስጠጋው። 50/60 ዓመታት ተሞከረ። ወደቀ። በማያተርፍ ጉዞ ድግግሞሽ ሞናትነስ እና ብክነት ነው። ሁልጊዜ ፍርሻ፤ ሁልጊዜም ፍርስራሽ - መፎረሽ።
* ይህ ጥሩ ቀን።
** ይህ ብሩህ ቀን።
*** ይህ ውብ ቀን።
**** ይህ ሸበላ ቀን።
***** ይህ ድንቅ ቀን።
****** ይህ የጸዳል ቀን።
******* ይህ የፈውስ አቅጣጫ ቀን።
******** ይህ ምሩቅ ቀን።
********* ይህ የሽልማት ቀን።
********** ይህ የሰብል ቀን።
የሚኮሰኩሳቸው፤ የሚሻክራቸው ወገኖቼ እንዳሉ አውቃለሁኝ። እነኝህን ከባዕዳን የፋንታዚ ባለሙያወች ለይቼ አላያቸው። ኢትዮጵያ ስትስቅልን ሳቋ ሊፈውሰን ይገባል። ስታዝን ስናዝን ለኖርን ሰወች፤ ይህን መሰል ድንቅ፤ ብራንድ ፕሮጀክት ለፍፃሜ ሲበቃ በሂደቱ የተሳተፋትን ሁሉ ከልብና ከዕውነት የመነጨ ምስጋና ልናቀርብላቸው ይገባል።
ይህ ግድብ የሰውም ግብር የተከፈለበት ነውና ሰማዕታቱ ብርቱው፤ ሊቀ - ትጉኃኑን ኢንጂነር ስመኘው በቀለን ጨምሮ ቤተሰቦቻቸውን ባሊህ ልንላቸው ይገባል። እግዚአብሄር ይስጥልን ማለትም ይገባል። ኢትዮጵያን እንመራለን ብለው እራሳቸውን፤ በገዛ ህሊናቸው ላጩም በተጠናቀቀ ፕሮጀክት ላይ ቅዋሜያቸው ሥም የለሽ ገመና ነው።
አንድ ፕሮጀክት ከላቀው ሃሳቡ ጀምሮ፤ ቦታ- ጊዜ - አቅምን ተልሞ ማስጀመር ልቅና ነው። ልቅናውን በልዕልና ማስቀጠል ብልህነት ነው። ብልህነቱን ደረጃውን በጠበቀ አኳኋን ለፍፃሜ ማብቃት ልቅና በልዕልና ነው። ለኢትዮጵያ ህብራዊነት ብቻ ሳይሆን ለፓን አፍሪካኒዝም ይህ የኖኽ መርከብ ብራንድ ፕሮጀክት እጬጌው ነው። ካህን ነው። ሸኽ ነው። ልሳነወርቅ ርትዑም ነው። ፕሮፖጋንዲስት አያስፈልገውም። ልኩም አይደለም ካድሬያዊነት። ዕውነት ፕሮፖጋንዲስት ቀጥሮ አያውቅም። እራሱን በእራሱ ዕውን አድርጎ የማቅረቡ ሚስጢር ጠሐይነቱ፤ ብርኃናማነቱንም ፍንትው አድርጎ ይገልጠዋል።
#ውሃ።
* ሥልጣኔ ነው።
** ውሃ ምግብ ነው።
***ውሃ ጤና ነው።
**** ውሃ መኖር ነው።
***** ውሃ ጸበል ነው።
****** ውሃ እድገት ነው።
******* ውሃ ብርሃን ነው።
******** ውሃ አቅም ነው።
********** ውሃ ምርምር ነው።
*********** ውሃ የሚያነፃ ነው።
************ ውሃ የዕውቀት ዘርፍም ነው።
************ ውሃ የነጠረ የድል ብርሃን ነው።
********** ውሃ ልዩ ሥጦታ ነው።
********** ውሃ ፃድቅ ነው።
******** ውሃ ቅዱስ ቃል ካገኜ ይፈውሳል።
******* ውሃ ጎዳና ነው።
****** ውሃ ትርታ ነው።
***** ውሃ ለምለምነት ነው።
**** ውሃ አበባ ነው።
*** ውሃ አዝርት፤ ቅመማ ቅመም ነው።
** ውሃ ዕንቁ ነው።
* ውሃ ከነዳጅ በላይ ነው። ነዳጅ - አይጠጣም። በነዳጅ - መታጠብ አይቻልም። በነዳጅ ክኒን - አይዋጥም። በነዳጅ - ልብስ አይታጠብም። በነዳጅ ምግብ አይበስልም።
#የፓን አፍሪካዊነት ዳግም ብርኃን።
የዚህ ግዙፍ ኢትዮጵያዊ ብራንድ፤ ፓን አፍሪካዊ ብራንድን ህልም ለማሳካት ቀን ከሌት የባተሉ፤ ፕሮጀክቱን በየደረጃው የመሩ፤ ለፕሮጀክቱ ስኬት ቅንነትን የመገቡ፤ ያስተባበሩ - ለተግባራዊ ሂደቱ ብልህ አጋዥ ሃሳቦችን በማፍለቅ ያቀናጁ፤ ሌሊት በግርማ እና ቀን በበርሃ ቋያ እየገረፋቸው ቁሩን፤ ግርማ ሌሊቱን ታግሰው የተጉ ሊቀ - ትጉኃንን በሙሉ ከመቀመጫችን ብድግ ብለን ልናመሰግናቸው፤ ትህትናዊ አክብሮት ልንሰጣቸው ይገባል። ዛሬ ከቤቴ በጣም ብዙ ሻማ በርቷል። ቀጣዩ አዲስ ዘመን 2018 ዓ.ም፤ የብርሃን ዘመን እንዲሆንልንም በፍጹም ትሁት ልቤ ፈጣሪየን እለምናለሁኝ።
ይገርመኛል የሊቦ አውራጃ ርዕሰ መዲና ሥም "አዲስ ዘመን" መባሉ። ብሥራት የሚያውጅ፤ ተስፋን የሚያቀና ብልኃዊ ሥያሜ። በበጌምድር እና ስሜን ክፍለ አገር የሚገኝ ነው። እራሱን የቻለ አውራጃ ነበር። አሁን በደቡብ ጎንደር፤ በአማራ ክልል ይገኛል። የሊቦ ልጆች ሰብዕና እንደ ሐረሮች ዓይነት ነው። የወገራም፤ የፎገራም የደንቢያም።
ወደ ቀደመው ስመለስ የጣራ ገዳም ባለቤት አዲስ ዘመን ነው። የአርባያ ታጋዮች ያውቁታል። ኦህዴድ እዛ እንደተፈጠረ አቶ አባዱላ ገመዳ ሲገልጹ ሰምቻለሁኝ። የሆነ ሆኖ የዓለሙ ሎሬት የክቡር ሎሬት ሰአሊ አፈወርቅ ተክሌ የእናት ማስተር ፒሳቸው ከዚህ ይቀዳል ሲባል እሰማለሁኝ። ተራራውም በዛ አካባቢ ነው ያለው - ይሆነዋልም - መመረጡ።
ያው ጨዋታን ጨዋታን ስለሚያነሳው ነው አያይዤ እማቀርበው። ለነገሩ የብላቴ ሎሬት ጸጋየ ገብረመድህን እሳት ወይ አበባ መድብል መግቢያ በሩም ሊማሊሞ ነው። እቴጌ ጎንደር ትጣራለች እና። ኢትዮጵያ፤ ኢትዮጵያዊነት ትንግርቱ ሲገለጥ የጉልት ገብያ ውሎ እንዳልሆነ ልንገነዘበው ይገባል። ኢትዮጵያዊነት የዕውቀት ዘርፍ ነው። ኢትዮጵያዊነት ላወቀበት ዩንቨርስቲም ነው - ለእኔ።
#ድንቅ ብሎኛል። ሐሤትም አግኝቻለሁኝ።
ሌላው ስታገል የኖርኩት ፯ኛ ርግብ በር መጸሐፌ ላይ አጽህኖት ሰጥቼ የፃፍኩት የአመራር ተከታታይነት ሊናድ አይገባም የሚል ነበር። ቀደምቶቹ ያለሙትን "በይቻላል" መንፈስ የቀድሞው ጠቅላይ ሚር አቶ መለስ ዜናዊ ወስነው፥ ውሳኔውን ወደ ተግባር የቀየሩበት ብቃት በኢትዮጵያ የትምህርት ካሪክለም ውስጥ ሊጠቀስ የሚገባው ብልህ የሆነ የአመራር ላቂያነት ነው።
ሃሳቡን ከአጤ ኃይለሥላሴ መውሰድ ብቻ በቂ አልነበረም። ድርጊትን በበቃ የተግባር መስኖ ማጠጣት መቻላቸው ነው ቁምነገሩ። ለአቶ መለስ ዜናዊ ትልም የተግባር እርምጃቸው ነው ላቂያነት የሚያሰጣቸው። ሌላው ድንቅ ነገር የሃሳባቸውን አፈፃጸም አንከር ባለሙያ መምረጥ፤ መመደብ ሌላው የአቶ መለስ የሪኮመንዴሽን ብቃትን ያመሳጠረ አገርኛ ትሩፋት ነው።
ኢንጂነር ሰማዕቱ ስመኜው ትክክለኛው ሰው፤ በትክክለኛ ጊዜ የተመረጡ ነበሩ። ለሃሳቡ ውጥን አቶ መለስ የመረጡበት ጊዜ በግሎባሉ የወቅቱ የፖለቲካ ፍላት፤ የፖለቲካዊ አቅማቸውን ያሳየ ክህሎት ነው። ሰማዕቱ ኢንጂነር ስመኜው በቀለ ከአንዱ በርኃ ወደ ሌላው ሲመደቡ ያሳዩት ቅንነት፤ መኖራቸውን የገበሩበት ሁነት ትንግርት ነው። በፕሮጀክቱ ምርቃት ጠቅላይ ሚር አብይ ዕንባ ጋር ተዋውለዋል። ያፈሰሱት ዕንባ ስለምን መሆኑን የሚያውቁት እሳቸው ናቸው።
በሥልጣን ዘመናቸው ለሆነው የመከራ ክምር ሁሉ ደግመው ደጋግመው ፍል ዕንባ ሊያፈሱ ይገባል። እርግጥ ነው ከነገረ ብርቱካን ትዕይንት በኋላ እርማት የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ቢኖርም፤ መሪ መሆን የሚሊዮኖች አባት መሆን ነውና ታቅዶ ለተከወነው አሰቃቂ ሁነት ሁሉ ልብ እና ኩላሊት የሚመረምር አምላክ አለና ማልቀሱ የተገባ ነው ባይ ነኝ። ይህን ስሜት ማቃለልን እኔ አልፈቅደውም። አጽናኝነት በብሄራዊ መንግሥት ደረጃ መሰደዱ በእጅጉ የማዝንበት አመክንዮ። ነገስ?።? ስለ ነገ ርህርህና የውስጥነት አጀንዳ ሊሆን ይገባል።
ብዙ በርካታ ጥፋቶች፤ አሳዛኝ ትራጂዲወች አስተውለናል በዶር አብይ አህመድ የሥልጣን ዘመን። የእኛ ቅንነት፤ የእኛን መታመን አረም እንዲውጠው ስለተደረገ የበቃ የሱባኤ ጊዜ ለጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ ያስፈልጋቸዋል ለእሳቸው እና ለቲማቸው። ጎድተውናል። በማረፊያችን ጊዜ ወህታችን ቀምተውናል እና።
በሌላ በኩል አቶ ኃይለማርያም ደስአለኝ ካለምንም ሴራዊ ሁነት ተግባሩን ለማስቀጠል ትጋታቸው ንጹህ እና ልባዊ ነበር። ይህ ብራንድ የሳቸው ፃዕዳ ቅንነትም አለበት እና ሊመሰገኑ ይገባል። በዘመናቸው የኮፒራይት ጉዳይ አጀንዳቸው ሆኖ የማያውቅ መሪ ናቸው አቶ ኃይለማርያም ደስአለኝ። አቶ ኃይለማርያም ደስአለኝ እግዚአብሄር ብቻ በሚያውቀው ብልህነት፤ ሥልጣናቸውን ደፍረው እና ፈቅደው በመልቀቅ፦ ለወቅቱ የህወሃት መንበር የፈቃድ ስንብት፤ መፍትሄ በመሆናቸው ዓለም ሊሸልማቸው የሚገባ ታላቅ ሰብዕና ያላቸው ናቸው።
የኖኽ መርከቡን የአጤ አባይን ብራንድነት ተግባሩን በማስቀጠል እረገድ በኮንስትራክሽን ጀምሮ በመፈጸም ዘርፍ ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አይታሙም። እኔ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስተር በነበሩ ጊዜ፤ በዘመነ ኢህዴግ ልቤን ቧ አድርጌ እምከታተላቸው ሚኒስተር ነበሩ። ያን ጊዜ ኢህአዴግ መራሹን ህወሃትን በትጋት እሞግት ነበር። ሳይንስና ቴክኖሎጂን ግን በልዩ ሁኔታ ነበር እምከታተለው። ሳይንስ እና ቴክኖሎጂን ለትውልድ እንዲሆን አድርገው መሠረት ያስያዙት ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ናቸው። የሥራ ባህሉ ልዩ ነው።
ያን ጊዜ ዶር አብይ ቢሮክራሲውንም በርህርህና ሞድ ይከውኑ ነበር። ቃለ ምልልሳቸውን ቀድቼ ይዤዋለሁኝ። ወደ ፊት ሲመጡም ሪፈረንሴ ያ ነበር። ያን የርህርህና አመራር ማስቀጠል አለመቻላቸው ነው የችግር ቋት የሆነው በሥልጣን ዘመናቸው። ስለምን አሰደዱት???
ዶር አብይ ጠቅላይ ሚር ከሆኑ በኋላ እኔ በግሌ የጠበቅኩትን አላገኜሁም። በዚህ በአባይ ፕሮጀክት ወዘተረፈ ታቅዶም፤ በድንገቴም፤ በሌላ ኃይል ገፊነትም የተፈጸሙ ግድፈቶችን ቆየኝ ብየ፤ የአባይ ግድብን ለፍፃሜ ማብቃታቸው ድንቅ ስኬት ነው - ለእኔ። እኔ ሥርጉተ©ሥላሴ ዕውነትን ልሸሽ አልችልም።
ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ በቀደመው የመለስ ሌጋሲ አናት የነበረውን አመራር ፈጣሪ በሚያውቀው፤ ዘመን በሚገልጠው ዕውነት ገለል ካደረጉ በኋላ፤ ፕሮጀክቱን በቅርብ ተከታትለው የሚመቻቸውን የውስጣቸውን ዞጋዊ ባለሙያ መድበው ለፍፃሜ አብቅተውታል። የተጀመረ ነገር በብቃት ለስኬት ሲበቃ እግዚአብሄር ይስጥልኝ ማለት እንደ ሸክም ልንፈራው አይገባም።
ታሪኩ ሲፃፍ፤ ሲተረክ፤ ሲብራራ መሳት፤ መታለፍ የሌላቸው ክስተቶች በአግባቡ ሊሰነዱ ይገባል። ሙሉ ማህበራዊ ሚዲያ በማን መንፈስ ውስጥ እንደ ሰከና ማስተዋልም ይገባል። የህዝብ ፍቅር በጀምላ እና በችርቻሮ የገብያ ህግ አይመራም እና። በጣም ገዝፎ የማየው የሰማዕቱ ኢንጂነር ስመኜው በቀለ ሥም ነው።
#ድሉ የማን? ስለማንስ? የበቀለ አበቀለ።
በሌላ በኩል ፖለቲካ ሰው ነው። አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ የደከመበትን ተግባር በድል መቋጨት ሊመሰገን ይገባል። የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች እነሱም ከግድፈት ውጪ አይደሉም። ግድፈታቸው ገና ለሥልጣን ሳይበቁ ነው። ሲበቁማ ያው ተዚያው ነው። በኢትዮጵያ የእርስ በእርስ እልቂት ካለምንም ቅድመ ሁኔታ ሊቆም ይገባል።
ትውልድ በጦርነት እየታጨደ ነው። ገዳይነት ምላጭ መሳብ ብቻ አይደለም። ጫካ ሠራዊት እየመሩ፤ ትዕዛዝ እየሰጡ ክላሽን ኮፕ አልያዝኩም፤ የሰው ደም አላፈሰስኩም ፌካዊ ጉዞ ቧልት ነው። ብዙ በጣም ብዙ ጉዳቶች በተለይ በአማራ ክልል መነሻውም፤ መዳረሻውም የማን ትልም እንደሆነ አበጥረን፤ አንጠርጥረን እናውቀዋለን። ለዚህም ነው እኔ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ማለት አገር መሪነት ማለት አይደለም። አገር መሪ ግን ተጽዕኖ ፈጣሪ ሊሆን ይችላል በሚል በአውዲዮም፤ በጹሁፍም አምኜበት እምሠራው። ህዝብ መምራት ቁልቁለት አይደለምና።
ሌላው የጠቅላይ ሚር አብይ መንግሥት ስለ ግድቡ ቸል ባሉበት ጊዜ የቀድሞው ኢትዮ 360 ለአጀንዳውን ባለቤት ሆኖ ብዙ፤ በጣም ብዙ አዌርነስ ፈጥሮ ነበር። እነሱም ሊመሰገኑ ይገባቸዋል። የጠቅላይ ሚር አብይ መንግሥት መጨረሻ ላይ ነበር የነቃው። በዚህ ዘርፍ የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚር አቶ ገዱ አንድአርጋቸው፤ ኢንጂነር አንባሳደር ዶር ስለሺ በቀለም ትጋታቸው ቀለማም ነበር።
ይገርማል ሰማዕቱ ኢንጂነር አባታቸው አቶ በቀለ፤ የአንባሳደሩ አባት ሥምም በቀለ። *የበቀለ *አበቀለ። አንቱ የሆነ ተግባር ፈጽመዋል። በዲፕሎማሲው ዘርፍ ብርቱ ተጋድሎ አድርገው የግብጽን ህልም አምክነዋል። በዚህ ዘርፍ ሁለቱም ሊቃናት ሊመሰገኑ ይገባል።
የቀድሞዋ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴም በዲፕሎማሲው ዘርፍ የለመለመ ተመክሯቸውን በዘርፋ እንደከወኑ አስባለሁኝ። ክብርቷንም አክብሮ ማመስገን የሚገባ ይመስለኛል።
ሌላው የኢትዮጵያዊነት ሳይለንት ማጆሪት ከአባይ ግድብ ጎን መቆም፤ አረብኛ ቋንቋ የሚችሉ የኢትዮጵያ ውድ፤ ድንቅ ልጆች ያሳዩት ትጋት እኔ ጀግኖቼ ልላቸው እወዳለሁኝ።
ቁምነገር ላይ ብቻ የሚያተኩረው ጭዋው፤ ፍጹም ታጋሹ፦ ምስጋና በቅጡ አግኝቶ የማያውቀው፤ በዘመኑ ደስታ ተቅልቦ የማያውቀው ቅኑ፤ ፍቅር የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ልጆቹ እና እሱ የአባይ ግድብን ብራንድ ፕሮጀክት ፓን አፍሪካዊ የኖኽ መርከብነት ለድል አብቅቷል። ለኮፒራይት ያለውን ፋክክር አይቻለሁኝ። እሱ ተግ ቢል መልካም ነው።
2.1) ስለ ትውልድ የማግሥት ተስፋ።
2.2) ስለ ኢትዮጵያ ጽኑ ሉዓላዊነት።
እናት አገር ኢትዮጵያ፤ እምሳሳልሽ ቅድስት አገር ኢትዮጵያ፤ እምወድሽ ባለ ታምራቷ ኢትዮጵያ እንኳን ሳቅሽልኝ። እንኳን ለዚህ ፏ ፍንትው ያለ ብርሃናማ ቀን አምላኬ አማኑኤል አበቃሽ። እልልል ………… እንኳንም ደስአለሽ።
እናት ዓለም ኑሪልኝ ለምልመሽ ለዘለዓለም። ልጆችሽ በአንድም በሌላም ሙሉ ተሳትፎ ያደረጉትን በሙሉም እግዚአብሄር ይስጣችሁ ልል እወዳለሁኝ። የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል፤ የቤንሻንጉል ጉምዝ አስተዳደር እና የጸጥታ አካላት ትጋትም በአባይ ፕሮጀክት ደህንነት ጥበቃ ላይ ለፈጸሙት ተግባር ሊመሰገኑ ይገባል።
እግዚአብሄር ይስጣችሁ ይህ ፕሮጀክትን ለመተናኮል ያሰቡትን እንዳያሳኩ ጥበቃችሁ ተሳክቷል እና ልትመሰገኑ ይገባል። በሌላ በኩል ስለ አባይ የፃፋ፤ የዘመሩ፤ ያቀነቀኑ፤ በአንደበታቸው የመሰከሩ፤ የተሟገቱ አክቲቢስቶች፤ ጋዜጠኞች፤ የአባይ መብት አስከባሪ ዘብ አደሮች፤ የጥበብ ሰወች፤ ሊቃናት እና ሊሂቃን፤ የሃይማኖት አባቶች ሁሉ የምስጋና ማዕዶቱ ባለሙሉ ባለቤት ናቸው።
#የሚያስፈልገን። ለእኛ የሚያስፈልገን የጥሞና ጊዜ አትኩሮት።
1) ኢትዮጵያ፤
2)ኢትዮጵያዊነት፤ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ከእኛ የፖለቲካ ፍላጎት፤ ከእኛ የሥልጣን ጥም፤ ከእኛ የተጽዕኖ ፈጣሪነት መሻት፤ ከእኛ የ፬ ኪሎ ህልም በላይ ነው። ይህን ዕውነት መቀበል ያስፈልጋል።
እንሰበው አቶ መለስ ትልሙን ሲያበጁ ሙሉ ድጋፍ አግኝተው ቢሆን ኖሮ፤ እሳቸው ባይደርሱበትም፤ በአቶ ኃይለማርያም ደስአለኝ ዘመን ሊጠናቀቅ ይችል ነበር። ያ ዕድል ያመለጠው በተደጋገመ ግድፈታችን ነው። ግድፈት ለእኔ መሰጠትም ነው ብየ አስባለሁኝ። ሰው መሆናችን መግለጫ ነው - ግድፈት።
በተመሳሳይ ግድፈት መንጎድ ግን ጤንነት አይደለም። ለእኛም የጥሞና ጊዜ ያስፈልገናል የምለው ለዚህም ነው። ቅንነት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ መፈጠሩ እንኳን አይታወቅም። ቅንነት ያልተቀመመበት ጉዞም አይሰክንም። ዕድሉ መልሶ ለታገልነው ድርጅት ለኢህአዳግ ወጣቶች የተሰጠው ቅንነትን በሴራ ስላሰደድነው። ይህን ጊዜ የዚህ ድል ባለቤት የሚሊዮኖች ህልም የነበረው የግንቦት 7 ይሆን ነበር።
የፖለቲካ ትጉህ ሞጋቾቹን ከማሳደድ፤ ዓይናችሁ ላፈር ብሎ ከማግለል ታቅቦ ቢሆን ኖሮ አቤቱ ግንቦት 7 ይህን ድል የራሱ የማድረግ ሁለመና ነበረው። የግንቦት 7 ያህል፤ የእሱን ያህል የሊቃናት ቤተኝነት ንቅናቄ በዘመኔ አላየሁም። የእሱን ያህል ግሎባል ተቀባይነት እና ዕውቅናማ አይቼ አላውቅም። "እግዚአብሄር በአንድም በሌላም ይናገራል፤ ሰው ግን አያስተውለውም።" ሆነ እና ያን የመሰለ ፈጽሞ የማይገኝ የምርቃት ጊዜ ባከነ።
አሁንም አቤቶ ብልጽግና ሥልጣንም፤ ሹመት እና ሽልማትም፤ ዕውቅና እና የጭብጨባ ዓውድን የናቁ የኢትዮጵያ ልጆችን ምን አሉ ብሎ ማድመጥ፤ ቅንጣት አትኩሮት መስጠት ቢጠቅምህ እንጂ የሚጎዳህ ስላልሆነ ልብ ይስጥህ። አሜን። ጥሞና፤ ሱባኤ በእጅጉ ያስፈልግኃል።
አይዋ ብልጽግና ቅኑን የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባው የሚታበስበት ቅንነትን ጀምረው እስኪ። አይገድልህም ቅንነት። ፈውስ እንጂ መርዝ አይደለም - ቅንነት። አዛኝነት ከጭካኔ ይቀላል። እስኪ በሞቴ ድፈረው ንጹሁን ቅንነት።
አይዟችሁ ባይነት ቢያስከብርህ እንጂ የሚሰባበር ሸክላ አያደርግህም እና እስኪ ባሊህ በለው። የህዝብ ለህዝብ የሆነ ትህትናንም ሞካክረው እንዲሰክን ዕራይህ። የማያቅቱ ሰባዕውያን ተፈጥሮወችን ካማሳደድ መርህኽ አድርጋቸው እስቲ። ማኒፌስቶህ የቀደምትነት ጸር ነው እና ቀደህ ብትጥለውስ??? የላም እረኛ ዕይታ ነው። ከጠቀመህ አይዋ ብልጽግና።
1) ትናንት የተፈጠረው በዕድሜ በጣም ትንሹ ብልጽግናን የሚደግፋ ምን ሲባል ጃንሆይ፤ ሰማዕቱ ኢንጂነር ስመኜው፤ አቶ መለስ፤ አቶ ኃይለማርያም ይነሳሉ ባዮች ናቸው። ሃሳብ አፍላቂ፤ መሐንዲስ ጠቅላይ ሚር አብይ ብቻ ነው ባዮች ናቸው፤ ታሪክ ከቁርጭምጭሚት አይጀምርም። ታሪክ ከመሠረት ነው የሚጀምረው።
2) የተቃዋሚው ጎራ በሁለት በሦስት ጎራ ተመልክቻለሁኝ። አንዳንዱ አጤወቹ አይነሱብኝ ባይ ናቸው። ሌሎቹ የምን አቶ መለስ፤ ኢንጂነሩ ብቻ ባይ ናቸው ይላሉ፤ ሌሎቹ ጭራሽ ዶር አብይ የሚባል ሥም አንይ የሚሉ ናቸው። በጸጋ ለስኬት በቃ ይሆን? እንኳን ይህን መሰል አፍሪካዊ ፕሮጀክት የለት ተለት ኑሮም መሪ ያስፈልገዋል። ለዛውም የተደራጀ መሪ።
3) እኔን ጨምሮ በተግባሩ ለተሳተፋት ሁሉ ክብር ለሚገባው ክብር - እንስጥ፤ ሁሉም እንደ ተሳትፏቸው - ይመስገኑ፤ የአባይ ግድብ የብራንድ አንባሳደርነት መላ #የኢትዮጵያ ህዝብ ነው፤ ይህ ግድብ መጠናቀቁ ኢትዮጵያ ከፍ ያለችበት #ዕውቀትም ነው፤ ማግሥትን በተስፋ እንጠብቅ ዘንድ ዋና በራችን ነው። ዕውነትን አንሸሽ ባዮች ነን።
ዕውነት ይደፈር! በአንድም በሌላም በአባይ ብራንድ የተሳተፋ ሁሉ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ይመስገኑ፤ ይከበሩ። ከእንግዲህ ኢትዮጵያን ላቅ በሚያደርግ ፕሮጀክት መደገፋ ቢቀር እንቅፋት መሆን ይቁም እላለሁኝ እኔም በግሌ። የየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ማኒፌስቶ ከኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በላይ አይደለምና። ቀድሞ ነገር እኔ በኖርኩበት ከጋሜ እስከ ሙሉ ዕድሜየ የፖለቲካ ተሳትፎ ዘመን፤ አንድም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅት ማኒፌስቶ በኢትዮጵያ ኦርጋኒክ ተፈጥሮ ልክ የተቀረጸ አይደለም። ለዚህም ነው ስኬት እና ድል የሚሸሸው። የሚሰደደውም።
#ሐሤትን በልኩ መያዝ።
*የብልጽግና ሚዲያወች ሆይ!
**የብልጽግና ካድሬወች ሆይ!
***የብልጽግና አክቲቢስቶች ሆይ! ሐሤታችሁን በልክ አድርጉት።
ለምን?
1) ሌላ ተጨማሪ ሐሤት ቢመጣ መደርደሪያ እንዳታጡ።
2) ሐሤታችሁን የሚያደበዝዝ ሁነት ቢፈጠር፤ ተስፋ ቆራጭ ሆናችሁ ለሥነ - ልቦና ህመም እንዳትዳረጉ።
3) የበዛ ፈንጠዝያ ምርቃት አስነስቶ እርግማንን ስለሚያስችል። በልኩ ስለልኩ ይሁን ሁለመናችሁ።
መፎካከር፤ መታበይ፤ መንጠራራት፤ ትምክህት እና መታበይ ቋት አይገፋም። *ቀስታ- *ዝግታ - *ስጦታን ዕድልን በልክ መያዝ ጨዋነት ነው።። *** መጨመት የቀጣይ ብርሃን ጎዳናወች ናቸው። በዚህ ውስጥ መኖር ባይቻል እንኳን መንፈሱን አቅርቦ የእኔ ማለት ይገባል። ስለማያከስር።
ይህ የአጤ አባይ ብራንድነት በር ነው። ውሃ ያልነካው የንጽህና ውሃዊ ቅንነት - ትህትና - ሰዋዊነት - ተፈጥሯዊነት- ርህርህና፤ አክብሮት - ምስጋና፤ ንጽህና ይገባበት ዘንድ እራስን መፈታተሽ ያስፈልጋል። ሥራ ላይ ለማዋል ረቂቅ መንፈሳዊ ቅዱስ አቅሞችን ይጠይቃል። በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያዊነት የሚቀኑ የራሳችን ጋሬጣወች አሉ። ፈጣሪ አምላክ ልብ ይስጣቸው። አሜን።
በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያዊነት የሚቀኑ አገሮችም አሉ። ይህን እናውቃለን። ከዚህ ቀደም ከነበረው ተጋድሎ በላይ የፊት ለፊቱ ፈተና የአጤ አባይ ግድብ ፈተና ይከብዳል። ከባዱን መጪ ጊዜ ለማለፍ አሁንም ንጹህ ልቦና ቅንነት ያስፈልጋል።
ከዚህ ቀን በፊት ከጳጉሜ ፩ ጀምሮ እስከ ጳጉሜ ፫ ብሄራዊ የጥሞና ጊዜ ያስፈልግ ነበር። ከድልቂያው፤ ከኳኳቴው፤ ከድሎቱ መታቀብ ያስፈልግ ነበር። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ያሉ አጽዋማት ሁሉ መነሻቸው ይኽው ብሂል ነው። የልደትን የምሥራች፤ የትንሳኤን ብሥራት ለመቀበል የሱባኤ ጊዜ ይኖራል። የኢትዮጵያ ስንቅ ሱባኤ ነው። ምርቃትን፤ በረከትን ያዘልቃል - ላወቀበት።
ግዮናዊነት ሐዋርያነቱን በራሱ ጊዜ አጸደቀ። ተመስገን። አሜን።







የእኔ ውዶች ለነበረን ዘለግ ያለ ጊዜ እግዚአብሄርን አመሰግናለሁኝ። ቅኖችን የእኔወችንም እንዲሁ። ኑሩልኝ አሜን።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
09/09/2025
ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት፤ ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር።





አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ