ስለትውልድ፤ ለትውልድ፤ የትውልድ የሚሆን ሰብዕና የአጽናኝነት ዋዜማ ለእማማ #ስለመናፈቅ።
ስለትውልድ፤ ለትውልድ፤ የትውልድ የሚሆን ሰብዕና የአጽናኝነት ዋዜማ ለእማማ #ስለመናፈቅ።
"አቤቱ እንደ ቸርነትህ ብዛት ማረኝ ይቅር በለኝ፦" አሜን።
በወርኃ መስከረም ዓዲስ ዓመት፤ ዓዲስ ዘመን አዲስ ተስፋ ይጠበቃል። ከበዓላቱ ጋር የፈጣሪ ጥሪ ቢኖር ቢከብድም ይቻላል እንደምንም። በአደጋ፤ በጦርነት ሲሆን ግን እራስን ይመረምራል። እራስን ይፈታትሻል። በየዘመኑ ስለትውልድ፤ የትውልድ፤ ለትውልድ የሚሆኑ ተግባራት ቢከወኑም፤ ስንቃቸው አመድ፤ ለቅሶ #ራሮት ከሆነ ድካሙ፤ ብድሩ፤ ወለዱ ለምን እና ለማን ያሰኛል።
በቤተክርስትያን ግንባታ ላይ እያሉ እንደወጡ የቀሩት፤ በጦርነት ምክንያት በጤና ክሊንክ ላይ የተሰው ንጹኃን፤ " ሴቶች ሱሪ አትለብሱም" ተብለው የተፈጠረ ግጭት እና ጉዳት፤ በሰማይም በምድርም በአገረ ኢትዮጵያ ሆነ በዓለም ደረጃ የሚወርደው የቀልሃ መርዝ እና ማግስት ሲታሰቡ ተስፋን በተፈጠረበት ምርቃት ልክ #ተስፋነት ለመጠበቅ ይከብዳል።
የሰው ልጅ የተፈጥሮ አደጋን ለመቋቋም፥ የአየር ብክለት ላይ ተግቶ ሊሠራ ይገባው ነበር። ሚሳኤል፤ ቦንብ፤ ሮኬት ወዘተ ከማምረት ይልቅ። በሌላ በኩል እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ደሃ አገራት በረጅም ጊዜ ብድር ይሁን፤ በዕዳ፤ በእርዳታም ቢሆን የተሰሩ የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን እሱ እራሱ ጥበቃ ማድረግ የማይችል ከሆነ፤ እንዲሁም ለአገልግሎት ተጠቀማዊም የደህንነት ዋስትና መስጠት ካልቻለ የአገር መሪነቱ ድርሻ፤ ደረጃን ይፈትነዋል #እርሱ #በእራሱ።
በህክምና ተቋማት፤ በትምህርት ቤቶች፤ በሃይማኖት ተቋማት ላይ የሚደርሱ የድሮን ይሁን የከባድ መሳሪያ ጥቃቶች #እራስን #በራስ የማጥፋት ተግባር ነው - ለእኔ። ጉባላፍቶ ወረዳ ላይ የደረሰወን ጥቃት መልሶ ለመጠገን፤ ሠራተኞች በሙሉ አቅማቸው ተረጋግተው ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ በቀጣይ ለማድረግ ተጨማሪ ጊዜ፤ ተጨማሪ ወጪ ይጠይቃል። የወደሙ፤ የተቃጠሉት የሚጠገኑበት ስንት አዲስ ፕሮጀክቶች ሊያስከፍቱ ይችሉ ነበር? በሌላ በኩል እንደ መንግሥት ዒላማ የሚደረጉ ቦታወች የሲቢሊያን መገልገያ ከሆኑ አስቀድሞ #መረጃ በመስጠት ሲቢሊያንን ማዳን ይቻል ነበር። የሚሊተሪው ህግ እና ደንብ ይፍቀድ አይፍቀድ ባላውቅም።
እውነት ለመናገር ለኢትዮጵያ የተፈጥሮ አደጋ አያምጣ እንጂ እሱ ብቻ ቢበቃት ጥሩ ነበር። እንዲህ ዕድሜ ዘመኗን በጦርነት ወላፈን በሰማይ እና በምድር ከምትቀቀል።
ከትናንት ዛሬ እየከፋ፤ ከዛሬም ነገ #እየከበደ የሚሄደው መሰረታዊ ምክንያት #ሰውኛ እና #ተፈጥሮኛ ሰብዕና ሽሽት ላይ ስለተሆነ ይመስለኛል፤ እንጂ ኢትዮጵያ እኮ ሥልጣን ለሚሹ ሁሉ ትበቃለች።
እንዲህ አዲስ ዓመት እንኳን #ወህታ የለለበት አገር ኢትዮጵያ ከምትሆን። ተቃዋሚወች ፋኖወች እና የጫካው ኦነጎች #ሳይናናቁ ቁጭ ብሎ ተነጋግሮ ስለትውልድ፤ ለትውልድ፤ የትውልድ የሚሆን፤ ዘላቂ እና መምህርም የሚሆን፤ የሰላም እና #የእርቅ መስመር ዘርግቶ #በምህረት ዓውደ ምህረት ከሰቀቀን፤ ከስጋት፤ ከፍርሃት የወጣ ማህበረሰብ መፍጠር ይቻላል።
ይህን ማድረግ ቢቻል ሙሉ አቅምን #በሙሉ #የራስ መተማመን መንፈስ በቅጡ #ማስተዳደር በተቻለ ነበር። #የማይከብደው ነገር በኢትዮጵያ ፖለቲከኞች #ከብዶ ነው ይህን ያህል አሳር እና ፍዳ ህዝባችን እያዬ የሚገኜው።
ነገም ዳመና ነው። የሚያፋፍም እንጂ የሚያበርድ፤ የሚረባብሽ እንጂ የሚያረጋጋ መንፈስ አላይም። ግራ ቀኙ የብልጽግና ይሁን የዱር ቤቴ ድምፆች ሚዲያወች #ከቆስቋሽነት፤ #ከአፋፊሚነት፤ እልህ ከማጋባት ወጥተው ወደ #የሚቀራርብ የንግግር ሥርዓት #ግራቀኙ ተፋላሚወች እንዲመጡ የማድረግ ተግባር በኽረ አጀንዳቸው ሊሆን ይገባል ብየ አስባለሁኝ።
ፋክክሩ፤ እሽቅድምድሙ ለዘላቂ #ሰላም ቢሆን የሚናፍቀኝ ጉዳይ ነው። ለምን? ከስጋት የተላቀቀ ትውልድ በራስ የመተማመን አቅሙ ሙሉዑ ስለሚሆን። በሙሉዑ የራስ መተማመን የተቀረጸ፤ የተገነባ ትውልድ ደግሞ ኃላፊነት የሚሰማው ትውልድ መሆን ስለሚችል።
ለትውልድ መሥራት ማለት ለእኔ የተግባሩ ማሳ #አዕምሮ ላይ ሊሆን ይገባል ብየ አስባለሁ። የአዕምሮ ትኩረት እክል እንዳይገጥመው ደግሞ ትውልድን ከስጋት፤ ከሽብር፤ ከቀውሳዊ ሁነቶች መታደግ ሲቻል ብቻ ይመስለኛል። ውስጥ #ጥቁር ከለበሰ ውስጥ #ይሸፍታል።
ሽፍትነቱ በራስ የመተማመን አቅሙን ይጠዘጥዘዋል። ህመሙ የተስፋ ጎደሎነትን ይሰጣል። የእኔ ትውልድ የእኔ ኃላፊነት ነው። ስለሆነም የጠየቀውን መስዋዕትነት ከፍየ ትውልዱን ለአደራ አበቃዋለሁኝ ግብ ሊሆን ይገባል። መስዋዕትነቱ የህዝብ አገልጋይነትን ዝቅ ብሎ መውሰድ። የህዝብን ጥያቄ ማድመጥ። ሞትን፤ እሮሮን፤ ዋይታን መቀነስ ይገባል።
የየትኛውም ችግር ፈውስ #ከሰባዕዊነት በገፍ ይገኛል። ፈውሱ ይህ ከተገኜ የወል ስኬት መዳፍ ላይ ሊሆን ይችላል። ምርቃት ስለሚበረክት። የትውልድ በሞራል፤ በሥርዓቴ #እነፃ የህሊና ሙሉ መሰናዶ ይጠይቃል።
በመጨረሻ በድሮን፤ በባሩድ፤ በድንገተኛ አደጋም ለተሰው ወገኖቼ ቤተሰቦቻችን፤ መጽናናትን እመኛለሁኝ። አሜን። ዛሬም ነገም ግን ያሳስቡኛል። መፍትሄ እየራቀ ስለማስተውል።
እንዴት ናችሁ ቤተ ቅንነት? የጹሁፌ መነሻ ከቢቢሲ አማርኛው ክፍል ያገኜሁት ነው።
«በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ጉባላፍቶ ወረዳ ቅዳሜ መስከረም 17/2018 ዓ.ም. ጤና ጣቢያ ላይ በተፈፀመ የድሮን ጥቃት ነፍሰ ጡር እናትን ጨምሮ የአራት "ሰላማዊ ሰዎች" ሕይወት ሲያልፍ 10 በላይ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን የዓይን እማኞች እና የሕክምና ምንጮች ለቢቢሲ ተናገሩ።» ዘገባው የBBC የአማርኛው ክፍል የሠራው ነው። ምስል የጉግልን ነው የተጠቀምኩኝ።
• «በሰሜን ወሎ ጤና ጣቢያ ላይ በተፈፀመ የድሮን ጥቃት አራት ሰላማዊ ሰዎች ሲገደሉ 10 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን የዓይን እማኞች ተናገሩ»
• «በምንጃር ሸንኮራ የቤተ ክርስቲያን ግንባታ መሸጋገሪያ ተደርምሶ ቢያንስ የ36 ሰዎች ሕይወት አለፈ»
• «በወንዶ ገነት 'ሴቶች ሱሪ መልበስ የለባቸውም' በሚል ፆታዊ ትንኮሳ ከመድረሱ ጋር በተያያዘ ስድስት ሰዎች መታሰራቸው ተገለጸ»
• «እንደ ተዋጊ ጀቶች፣ታንኮች እና የጦር መርከቦች ያሉ ከባድ የጦር መሣሪያዎች እና የአየር ንብረት ስጋት»
• ዘገባው የBBC የአማርኛው ክፍል የሠራው ነው።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
02/10/2025
በቃ! ጦርነት።
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ