የሃሳብ ነፃነት #ሰው #የተፈጠረበት #ዓውራ #ሚስጢር ነው። የእኔ አዲስ ፍልስፍና ነው። #መኖር የሚሰለጥነው በሃሳብ ነፃነት ነው። #የኢትዮጵያ ሳንባ ሙሉለሙሉ ንጹህ አየር ሊተነፍስ ይገባል።

 

የሃሳብ ነፃነት #ሰው #የተፈጠረበት #ዓውራ #ሚስጢር ነው። የእኔ አዲስ ፍልስፍና ነው። 
 
ህሊና ያለው ፍጡር ሲፈጠር እንዲያስብ፤ እንዲመራመር፤ እንዲፈላሰፍ ነው። እንዲያመሰግን፤ ምህረት እንዲሆንም።
 
#መኖር የሚሰለጥነው በሃሳብ ነፃነት ነው። 
 
#የኢትዮጵያ ፖለቲካ የሃሳብ ነፃነትን በአገለለ ቁጥር እየጫጫ፤ ውርጭ እየገረፈው ይኖራታል።
#አንጎልማ ዲንቢጥ ወፍም አላት እኮ። ዶሮም አለው አንጎል።
 
#ፍትህ! #ምንጊዜም #ፍትህ!ፍትህ አልባ ዓውድዓመት #ግንጥል ጌጥነት ነው። 
 
#የግንጥል ጌጥ ፈቃደኝነት #ለምን? #ስለምን?
 
#የኢትዮጵያ ሳንባ ሙሉለሙሉ ንጹህ አየር ሊተነፍስ ይገባል።
 
"አቤቱ ንጹህ ልቦና ፍጠርልኝ።" አሜን።
 
ምዕራፍ ፲፯
 
 
 
በርከት ያሉ የሚፈታትሹ ኃይለ ቃሎችን አዋህጄ ነው እርዕሱን ያጎለበትኩት። ነጠላ ከሚሆን ሰሞነ ዓውድዓመት አይደል? ዕርእሴ እንደ አባት አደሩ ጃኖም፤ ካባም፤ ካሰኜውም ካሊም ደረብ አድርጎ ቢቀርብ ከውስጥ፤ ለውስጥ የቢሆነን ዓይነት ነው ዕሳቤየ። በተፈጥሮው የእኔ ጹሁፍ ዘለግ ቢልም፤ ዕርዕሶቼ አጫጭር ናቸው። ዛሬ ግን እንደ ሐምሌ አቦ ንብርብር ድርብርብ አደረግኩት።
 
እርግጥ ነው አልፎ አልፎ ከሁለት በላይ ርዕሶችን አስተጋብሬ የማቅረብም ልማድም አለኝ። የሆነ ሆኖ ኢትዮጵያ ፈላስፊቷ ሙሉ ገፆዋ #ግርዶሽ እንዳያጥልበት የሃሳብ ነፃነት የሚበራባት አገር ትሆን ዘንድ የዘወትር ምኞቴ ነው። መናፈቅ። ሰላም ከዚህ ይፈልቃል። የልብ ሽፍትነትም ይለሞጣል። እርግጥ የከረሩ፤ እንደ ጠፍር የገረዘዙ፤ ህግን የሚጫኑ ብቻ ሳይሆን በዚያች ታላቅ አህጉርም ለሆነች አገር የማይመጥኑ የአነጋገር ዘይቤወችን ማረቅ የባለቤቱ የተናጋሪው ጉዳይ ነው። የሃሳብ ነፃነት ሃዲዱ ሥርዓት የያዘ ንግግር፤ ሥርዓት ያለው የክርክር አቅም፤ ሥርዓት ያለው የሙግት ዘይቤ እንዲኖረው ምኞቴ ነው።
 
ለዚህም ነው ፔጄ ላይ ዘለፋን ማስተናገድ እማልፈቅደው። እኔ ፌስቡክ ስጀምር የነበረው ዝንጥልጥል ያለ የአቀራረብ ሁነት ዛሬ የለም። ተመስገን ነው። ብዙ ጥረት አድርጌያለሁኝ። በእያንዳንዳችን የህይወት ቃና፤ የተሳትፎ ሂደት አክሰሱ ላላቸው ልጆቻችን ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ከእያንዳንዳችን በግል፤ ከሁላችንም በጋራ ፈቅደን ልንከውነው የሚገባ ጉዳይ ይመስለኛል። ኦኦ! ለምን ይመስለኛል አልኩኝ። ነው እንጂ። 
 
ሥርዓት ያያዘ፥ ደርዝ ያለው ንግግር - ሙግት - ክርክር እራስን ያስከብራል። የመንፈስን አቅም ያልቃል። ህግ አክባሪነት ተፈቅዶ፤ ተወዶ ሊደረግ የሚገባው ነው። የሰው ልጅ አፈጣጠር ከጽንስ ጀምሮ ሂደቱን በማስተዋል ብትከታተሉት ሥርዓትን የተከተለ ነው። የእንሰሳት፤ የዕጽዋትም የአበቃቀል፤ የአኗኗር ዘይቤ ተፈጥሯዊ ሥርዓት አላቸው። እቴጌ ጸሐይ በምስራቅ ወጥታ በምዕራብ ትገባለች። ይህ ቀየር ሥርዓተ ህግ ነው።
 
በሌላ በኩልም የውስጥ ኦርጋናችን አገልግሎትም ሥርዓትን የተከተለ ነው። እምንታመመው እኮ የውስጥ ኦርጋናችን ሥርዓቱ ሲስተጓጎል ነው። መራራ ስንብትም የሚመጣው በሥርዓተ ሂደቱ መጓጎል ነው። ይህን እንደ ማህበረሰብ፤ እንደ መንግሥታዊ አስተዳደር፤ እንደ ፖለቲካ ተቋማት፤ እንደ ግል የአኗኗር ዘዬቤ፤ እንደ ሰው የፖለቲካም ይሁን የማህበራዊ ተሳትፎ ስንወስደው ሥርዓት በተጓደለ ቁጥር ራዕይም፤ ግብም ይታመማሉ። መታመም ብቻ ሳይሆን ለሞት አደጋም ይጋለጣሉ። ሞትም አለ።
 
ይህ እንዳይሆን ሥርዓት አክባሪነት #ከአስከባሪው አብነታዊ ድርጊት ያስፈልጋል። ነፃነት ነፃ እንዲሆን በህግ፤ በደንብ፤ በድንጋጌወች ብቻ ሳይሆን #ባልተፃፋ ህግጋትም ጭምር እራስን መግዛት ያስፈልጋል። እኔ ኢትዮጵያ በተፃፈ ህግ እንደሚተዳደሩት አገሮች በተፃፈ፤ ባልተፃፈ ህግ እንደሚተዳደሩት አገሮችም ባልተፃፈ ህግ ትተዳደራለች ብየ አምናለሁ። የህግ ሊቃናት ይህን ዕይታየን ላይቀበሉት ይችላሉ። እኔ ግን ከተፃፋት ህግጋት ይልቅ የህዝብ ሙሉ ይሁንታ ያላቸው ያልተፃፋት ህግጋት ድርጊት ላይ ይውላሉ ካለ ህግ አስከባሪወች የሚል ጽኑ ዕምነት አለኝ። ይሉኝታን እሰቡት፤ ሙሽራ እና ሬሳን ቁሞ ማሳለፍን አስታውሱት ወዘተ ………
 
ወርኃ መስከረም ይህ ሁሉ ዓውድ - ዓመት በአንድም በሌላም፤ በንጽጽር ፍጹማዊ ባይሆንም ኢትዮጵውያን አክብረዋል / አክብረናል ስደተኞችም። የታሠሩ እስረኞች በካቴና በአገር ውስጥ? ቤተሰቦቻቸው፤ ልጆቻቸው፤ አድናቂወቻቸውም #ከካቴና ስሜት ሳይወጡ ሊያከብሩ እንደምን ይችላሉ? አጤ ብልጥግና ደግመህ፤ ደጋግመህ እሰብበት? የታሠሩት ዜጎችህ፤ ቤተሰቦቻቸውም ዜጎችህ ናቸው።
 
" የእንኳን አደረሳችሁ" ሁልጊዜ የጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ መልዕክት አለ? ይህ የመልካም ምኞት ዜና ካቴና ላይ ላሉ? ካቴና ላይ ለሚገኙ ዜጎች ልጆች፦ ቤተሰብ፤ ትዳር ይመለከት ይሆን? ለሞጋቾችስ? ለእኔ #ግንጥል #ጌጥ #ነው። የአጤ ብልጽግና ደጋፊወች፤ ደጋፊ ሚዲያወች፤ የመንግሥት ሚዲያወች ለእነሱ ያለው ንጹህ የነፃነት አየር ለወገኖቻቸው ሳይደርስ ሲቀር እንደ ሰው ሊያሳስባቸው ይገባል። ይህ ተዛነፍ ሁነት የበዓላቱ አውድ ትርታው ጎደሎ ይሆናል። 
 
ዓውደ ዓመት ከምህረት - ከይቅርታ - ከእርቅ እና ከሰላም ጋር ሲታረቅ የትውልድ ተስፋ ይሆናል።
*በስተቀር አንዱ እያለቀሰ? አንዱ ሲስቅ፤
**አንዱ እየጨፈረ ሌላው ኩርምት ሲል፤
*** አንዱ እንጡሩብ እየዘለለ፤ ሌላው ትንፋሽ አጥሮት፤
*** አንዱ ፈርሾ ሌላው በነፃነት እጦት በውርጭ እየተንዘፈዘፈ ከሆነ የጋራ - አገር፤ የወል - ተቆርቋሪነት፤ የዜግነት ግዴታ እና ተጠያቂነት መጠራቅቅ ውስጥ ይሆናሉ።
 
አቤቶ ብልጥግና ወደ ሥልጣን ከመጣባቸው ሚስጢራት አንዱ በኢትዮጵያ ውስጥ በነበሩ የፖለቲካ #እስረኞች ጉዳይ ነበር። ለዚህም ነው የቀድሞው ጠቅላይ ሚር አቶ ኃይለማርያም ደስአለኝ በመጨረሻው የሥልጣን ዘመናቸው፤ ሥልጣናቸውን ፈቅደው ከመልቀቃቸው በፊት ሙሉ እስረኞችን የፈቱት። የኢህአፓ እስረኞች ግን እስከ አሁን ድረስ አልተፈቱም። 
 
እንደ ሐመር አሁን ዘኢትዮጵያ የተባለው ዩቱብ የኢትዮጵያ የፖለቲካ እስረኞች በጠቅላይ ሚር አብይ ዘመን እንደተፈቱ አድርጎ ይዘግባል። ይህ የታሪክ #ግድፈት ነው። እራሱ የህወሃት መራሹ ኢህአዴግ ፈቅዶ ሥልጣኑን እንዲለቅ የሆነበት ጉልበታም አመክንዮ ይኽው ኢትዮጵያ የፖለቲካ እስረኞች የበረከቱባት አገር በመሆኗ ነበር። ልጅ ሳይረገዝ የተወለደ የሚመስል ዘጋባ አቅራቢው ዩቱብ ቻናል ግድፈቱን ለግርዛት ቢያበቃው ምኞቴ ነው። 
 
ጠቅላይ ሚር አብይ ለሥልጣን ሳይበቁ የፖለቲካ እስረኛን የማስፈታት አቅም አይኖራቸው። ለእሳቸውም ጋዳ ነበር ያን ጊዜ። ያ ሂደት በሆነ ነገር ተጨናግፎ ቢሆን ኖሮ የለውጥ ሐዋርያ በወቅቱ የተባሉት ሁሉ የካቴና፤ የባሩድ ስንቅ ይሆኑ ነበር። በጥበብ፤ በቀስታ፤ በዝምታ ውስጥ የተከወነ ክስተት ነበር። 
 
ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ በትክክል ከእስር የለቀቋቸው፤ እሳቸው ባለሙሉ ሥልጣን ጠቅላይ ሚር ሆነው በብአዴን ሙሉ ድምጽ እና በኦህዴድ ሙሉ ይሁንታ ካገኙ በኋላ፤ ዛሬ በቁልፍ ሥልጣን የተንበሸበሹት ደቡቦች የራሳቸው ተወዳዳሪ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ስለነበሩ ከሦስት በላይ ድምጽ አልሰጡም ነበር። በወርኃ መጋቢት 2010 የሥልጣን ሰላማዊ ሽግግር።
 
የሆነ ሆኖ ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ሲመጡ አቶ አንድአርጋቸው ጽጌን ከእስር እንዲለቀቁ አድርገዋል። በተጨማሪም ቤተ- መንግሥት ድረስ ፈቅደው በክብር ከጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ጋር ተነጋግረዋል። ይህም በወቅቱ ለዶር አብይ አህመድ አሊ የሚያስፈልግ የአቅም ሙሉ ቅመም ነበር። ብብልህነት የፈጸሙት ተግባር እንጂ በስሜት የከወኑት አልነበረም። ሚሊዮን የግንቦት ፯ ተስፈኛን አቅም በሙሉ በፈቃደኝነት የገበረላቸው ለዚህ ነበር። በዛው ሰሞን አንዲት የኦፔራ አርቲስት ወት ሃና ግርማ "በአንተ ላይ" ሥራዋ ሚሊዮን ተመልካች ያገኜችውን ይሁንታ ሲሰጡ በዝም ብሎ በእግር ጥሎሽ አልነበረም።
 
ከዚህ ባሻገር ለሙሉ የፖለቲካ እስረኞች ነፃነት የአቶ ኃይለማርያም ደስአለኝ ሚና ጉልህ ነበር። ምክንያታዊ ቢሆንም። ገፊ ጠንካራ ጉልበታም አቅም ቢኖርበትም። ታሪክ ግልቢያ፤ ሞቅታ፤ ምኞት፤ ፋንታዚ፤ ግልብልብ ነገር አያስፈልገውም። በሂደቱ አንቱ የተባሉ ዓራት ዓይናማ ዓለም ዓቀፍ የፖለቲካ #ቀንዲሎች በሙሉ አቅማቸው የተሳተፋበት ሂደት ነው የነበረው የህወሃት በትረ ሥልጣኑን ፈቅዶ እራሱም ተወዳዳሪ አቅርብ የተከወነው ክስተታዊ ሂደት። ይህን መሰል ወርቅማ ዕድል ይደገማል ብየ አላስብም። የዊዝደምን ዕድል ያልደከመበት መንፈስ ከእጁ ሲገባ በቅጡ የማስተዳደር ክህሎቱ የከሳ ስለሆነ። ቲም ገዱ ዛሬ የት ነው? ቲም ለማስ?
 
የሆነሆኖ የጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ መንግሥት ብዙም አልቆየም ዕድሉን ያገኜበትን ዓይን ለመጋረድ ሲቻኮል። መስከረም 05/2011 ኦነግን ከመቀበል ጋር #ከ1300 በላይ አዲስ አበቤወች ጦላይ ታሥረዋል። 5 የአዲስ አበባ ነዋሪወች በአደባባይ ተገድለዋል። ጦላይ አብዛኞቹ የታሠሩት ሲፈቱ የተወሰኑት ቢጫ ለባሾች እስከ አሁን እንደታሠሩ ናቸው። ፎቷቸውንም እለጥፋለሁኝ። አበሳቸው ምን እንደሆን እስከ አሁን ድረስ አይገባኝም። በሙሉ ሐሤት ስለተቀበሉ ስለምን ተንገላቱ? 
 
የሆነ ሆኖ ሌሎችም በተለያዬ ምክንያት አሁንም ታሥረዋል። በተለይ በአማራ ጉዳይ ጠንከር ያለ እርምጃ ነው የሚወስደው አብይዝም። ስለሆነም በዚህ በሃሳብ ነፃነት አስፈላጊነት፤ በእስረኞች ጉዳይ ተግተን ለምንሰራ ዜጎች እረፍት ፈጽሞ አላገኜነም። መኖራችን እንደ #ሻቀለ ነው። ሁልጊዜም ይጎረብጠዋል - መኖራችን። 
 
እኔ አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑን ከዲያስፖራ ጋር እንዲነጋገር ውጭ አገር ብልጽግና መላኩ ባይከፋም፤ ቀዳሚው ተግባር በፖለቲካ እስረኞች ላይ ያለው በጣም ከራር የብልጽግና አቋም ማላላት፤ ለምህረት እና ለይቅርታ ህሊናው፤ ልቦናው ክፍት ሊሆን እንዲችል በአጽህኖት መሞገት ይገባው ነበር የምክክር ኮሚሽኑ።
 
አቤቶ ብልጽግና ላቤን ጠብ አድርጌ፤ እንቅልፍ አጥቼ "እየሠራሁ ነው፤ ኢትዮጵያን ከእርምጃ ወደ ሩጫ እያሸጋገርኩ ነው" ይላል። ይህን የሚል አንድ መንግሥት እንደ እኔ #ፕሮፖጋንዲስት አያስፈልገውም፤ በሌላ በኩልም ሃሳብን እንደ ጦር ሊፈራ አይገባም ባይ ነኝ። ተግባሩ እራሱ ይረታለታልና። በቅንነት በሰዋዊነት ከልቡ ከሠራ፤ ትጋቱ እራሱን በራሱ እንዲያድን ማድረግ ይቻላልና። 
 
አሁንም ወደፊትም ምኞቴ ኢትዮጵያ በጠቅላላ ከፖለቲካ እስረኛ ነፃ እንድትሆን ነው። ክልሎች፤ ዞኖች ወረዳወች ላይ ሁሉ የፖለቲካ እስረኞች ሊኖሩ ይችላሉ። ለገዢው አቤቶ ብልጽግና የህግ የበላይነት ማስፈን፤ ቂመኝነት እና በቀላዊ እርምጃን ከራስ ለራስ አርሞ መገኜት መሰረታዊ በሳል ተግባሩ ሊሆን ይገባል ባይ ነኝ።
 
የአንድ መንግሥት ሥልጣኔ ለእኔ የሃሳብ ነፃነትን ለመተግበር #ድፍረቱ ነው መለኪያዬ። ነፃነት እኮ የፈጣሪ ስጦታ ነው። የመኖር ነፃነት ለሰው ልጅ ሲፈጠር የተሰጠው ሰማያዊ ሥጦታው፤ ሽልማቱ ነው። መንግሥት ይህን ሰማያዊ ሥጦታ በእኩልነት የማስተዳደር እንጂ ፈጣሪ በሰጠው የነፃነት ስጦታ አለቃ ሆኖ ሊገኝ ፈጽሞ አይገባም ባይ ነኝ።
 
መንግሥት የተፈጥሮ ነፃነት ተጫኝ፤ አጎሳቋይ፤ አስፈሪ መሆን ሳይሆን፥ ነፃነት በተፈጠረበት ልኩ የሚፈልገውን ፋሲሊቲውን በማሟላት አብነታዊ ተግባር ሊፈጽም ይገባል። ተግባሩ ካድሬወቹ ሳይሆኑ እኛን ከውስጣችን ሊያሳምን ይገባል። ምክንያት? በአገራችን ፖለቲካዊ ጉዳይ ፈጽሞ ፕሮፖጋንዲስት የማያስፈልገን ዜጎች አለንና።
 
በራሳችን አቅም፤ አቋም፤ አሻራ እና ጽናት መኖራችን አደራጅተን ለምንመራ፥ የብልጽግና ደራሽ እና አፍላ ካድሬወች እኛን ሊያሳምኑ ፈጽሞ አይችሉም። በምን አቅም? አብይዝም ባይመጣ ፖለቲከኛ ፈጽሞ አይሆኑም ነበር እንኳንስ ተሸላሚ ይሁን ተሿሚ። ለአብይዝም መመጣት ማጅክ ሳይሆን የሰከነ፤ የተረጋጋ፤ ደርዝ ያለው ተከታታይ ያስተዋለ በሳል የፖለቲካ ሂደት ቀመር ነው ለዚህ የተበቃው። ዕድሜ ዘመኑን ኦነግ ቢሞክር የማይሳካለት ህልሙ በኢትዮጵያኒዝም ሽፊን ከጠየቀው በላይ ተሳካለት ኦነግ።
 
በሌላ በኩል በጣም የገዘፋ ልካቸውን ያለፋ ጉዳዮችም አዳምጣለሁኝ። "ልክን ማወቅ ከልክ ያደርሳል" የጎንደሮች ብሂልን አቤቶ ብልጽግና ቢያስብበት መልካም። በጣም የተንጠራሩ ጉዳዮች ይስተወላሉ። አንዳንድ ጊዜ ኢትዮጵያ በስንት ጠቅላይ ሚር ይሆን የምትመራውም ያሰኛል። 
 
ከሰውኛው ይልቅ ኃይማኖት ካለው አቤቶ ብልጽግና እግዚአብሄር የፈቀደለትን ጊዜ በልኩ፤ ይሉኝታንም ገበር አድርጎ ቢፈጽም ጥሩ ነው። የፖለቲከኛ እሰረኞች የለለባት ኢትዮጵያ ምንጊዜም ትናፍቀኛለች። ተፎካካሪ፤ ተቃዋሚ የሆናችሁ የፖለቲካ ድርጅቶችም በዚህ ጉዳዬ ተግታችሁ ብትሠሩ ምኞቴ ነው። አክብሮታዊ አስተያዬት ነው። ኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ በሳንባዋ ልትተነፍስ ይገባታል። መተንፈስ አለባት። ጤናዋ ሊጠበቅ ይገባል። ለሰላሟ ትጉህ ልጅ ያስፈልጋታል። 
 
እርግጥ ነው የፖለቲካ እስረኞች ከእስር ሲለቀቁ ሙግታቸው አይቆምም። ይሰደዳሉ። ይሞግታሉ። ከተሰደዱ በኋላ ደግሞ ብልጽግናና ደጋፊ የሆኑ ሁሉ አይቻለሁኝ። እነ ልጅ ቴወድሮስ አስፋው ዓይነት። ይህም ዕድል አለህ አቤቶ ብልጽግና። የሃሳብ ነፃነት ሰው የተፈጠረበት ሚስጢር ነውና ዕቀባ ሊጣልበት ፈጽሞ አይገባም። ለምን ተወለድክ? ለምን ህሊና ኖረህ እንደምን ይባላል አንድ የእግዚአብሄር የአላህ ፍጡር።
 
በሌላ በኩል አቤቶ ብልጽግና የሁሉ ነገር ዕውቀት፤ ጸጋ ባለቤት አይደለም። ኢትዮጵያም የሞላላት አገር አይደለችም። ብዙ ጎደሎወች አሉ። ሃያሲያን፤ ሞጋቾች ያን የማየት አቅም አላቸው። ከውስጥ ስሌለሉ። ያ ጉድለት፤ ያ ክፍተት #ራዲዮሎጂስቶቹ ሞጋቾች ናቸው። አቤቶ ብልጽግና ቅልጥ ባለ ፌስታ፤ የሞድ ትዕይንት ላይ ስላለ የባቱን ጉድፍ አያስተውለውም። ደጅለደጅ ነው ያለው።
 
እሱ ያላየውን፤ እሱ ያላስተዋለውን፤ የሃሳብ ሞጋቾቹ፤ ተፎካካሪወቹ የሥልጣን የሚጠቁሙት ቢጠቅም እንጂ አይጎዳበትም። ስለሆነም ይህን መሰል ጠቃሚ ፍሬ ነገር እንደ ልዩ ስጦታ ነው ሊታይ የሚገባው እንጂ መሳደጃ ሊሆን አይገባም። ይህን የሚያደርጉ ብልኃን ኢትዮጵያዊ ዜጎች ሊመሰገኑ ይገባቸዋል። ይህን የሚፈጽሙ አገር ወዳድ ቅንውያን ሊከበሩ እንጂ ሊገለሉ ወይንም ሊሳደዱ አይገባም። አገር ውስጥም ያሉት መኖራቸው ካቴና ጋር እንዲሆን ሊደረግ አይገባም ነበር። 
 
እኔ እንደማስተውለው በኢትዮጵያ ፖለቲካ የህልውና ዘመን ሁሉ ግን ብልህነት አድማጭ አግኝቶ ሥራ ላይ ሲውል ያዬሁበትን ጊዜ አላስታውስም። የሰው ልጅ ፍርኃት ከተጫነው ሃሳቡን ከመግለጽ ይታቀባል። ይህ አቋም ለትውልድ አይጠቅምም። በተለይ ሳይለንት ማጆሪቲው ላይ የታመቁ ጠቃሚ ኃሳቦች አይወጡም። ስጋት ፍርኃት አገር ምድሩን ከገዛው።
 
ዕድል ሲያገኙ ግን ጠሚር አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ሲመጡ የሰማይ ታምር ነበር የታየው። ያ ውስጥነትን አቋም አንባቢ፤ ተርጓሚ እና አመሳጣሪ ጠፍቶ ነው ተስፋ ታጥቦ ጭቃ የሆነው። እኔ ከህወሃት ፈቅዶ ሽኜታ በኋላ እንደ ገና እስረኛ ፍቱልን ልማና እንገባለን፤ እንደ ገና በእርስ በርስ ጦርነት ማዕበል እንቀዝፋለን የሚል ቅንጣት ግምት አልነበረኝም። አዝናለሁኝ። ስንት ነገር ማዳን ሲቻል እንዲህ/ እና እንዲያ አቅም ብክነት ላይ ይባዝናል።
 
አቤቶ ብልጽግና የፖለቲካ እስረኞች ጉዳይ መቼ ይሆን አጀንዳህ ሊሆን የሚችለው? አዲስ ዓመት በምንም አለፈ????? ------{} ብዙ ጠብቄ ነበር። ግን ምንም። 
 
ማህበረ ቅንነት እንዴት ናችሁ። ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን። 
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassue
03/10/2025

 
የሃሳብ ነፃነት ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ!
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።