የአቶ ነአምን ዘለቀ ከግንቦት 7 ራስን ማግለል ዕድምታ።
እንኳን ደህና መጡልኝ። የራስነገር። „አንተ ፈጣሪያችን ግን ቸር ነህ ይቅር ባይ ነህ፤ የምትታገሥ ነህ፤ ከሀሊነትህን እያወቅን ብንበድልም ባንበድልም፤ ያንተ ወገኖች ነንና በቸርነትህ ሁሉን ትሠራለህ። ነገር ግን ያንተ ወገኖች እንደ ሆንን እናውቃለን።“ መጽሐፈ ጥበብ ፲፭ ቁጥር ከ፩ እስከ ፪ ከሥርጉተ©ሥላሴ Sergute©Selassie 20.03.2019 ከእመ ዝምታ - ሲዊዘርላንድ። · ከውስጥ ስለማዬት። የእኛ ነገር እንዲህ ነው ተሰበሰበ ሲባል መበተን፤ ተበተነ ሲባል መሰብሰብ። ተቃና ሲባል መጉበጥ፤ ጎበጠ ሲባል ደግሞ መቃናት፤ ፈሰስ ሲባል መ ለ ቀም፤ ተለቀመ ሲባል መፍሰስ እኛ እንዲህ ነን። በቀለ ሲባል መድረቅ፤ ደረቀ ሲባል ማጨብጨብ፤ ሞላ ሲባል መጉደል ጎደለ ሲባል መሙላት፤ ሞላ ሲባል መፍሰስ፤ ፈሰሰ ሲባል ክው ብሎ መድረቅ ዕጣ ፈንታችን ይኸው ነው። ሰሞኑን አንድ ዜና አዳመጥኩኝ። ሳዳምጠውም ደነገጥኩኝ። ጋደም ብዬ ስለነበር ቀና አልኩኝ እና በማስተዋል ዜናውንም ሀተታውን አዳመጥኩኝ አቅራቢው ጋዜጠኛ ሄኖክ አለማዬሁ ነበር። የሰማሁት ከዘሃበሻ ኦፊሻል ድህረ ገጽ ላይ ነበር። በምልሰት ደግሜ አዳመጥኩት። ድንጋጤዬ አብሮኝ ቆዬ። በዚህ ወቅት ይህ ይሆናል ብዬ አልገመትኩም ነበር። የእውነት። አቶ ነዓምን ዘለቀ ከግንቦት 7 ራሳቸውን ማግለላቸው ነበር ዜናው። ዜናው ከዘሃበሻ ስለገኘሁት አልተጠራጠርኩትም። ግን በጹሑፍ የሰፈረ አግኝቼ እስክመረምረው ተግ አልኩኝ። ትናንት ሚዲያዎች ላይ ጎልቶ የወጣ የውይይት አጀንዳ ይሆናል ብዬ አስቤ ነበር። አብሶ በደከሙለት ሚዲያ በኢሳት ከዜና በስተቀር እንደ አቶ ዛዲግ አብር...