የአቶ ነአምን ዘለቀ ከግንቦት 7 ራስን ማግለል ዕድምታ።


እንኳን ደህና መጡልኝ።
የራስነገር።
„አንተ ፈጣሪያችን ግን ቸር ነህ ይቅር ባይ ነህ፤ የምትታገሥ ነህ፤
ከሀሊነትህን እያወቅን ብንበድልም ባንበድልም፤ ያንተ ወገኖች
 ነንና በቸርነትህ ሁሉን ትሠራለህ። ነገር ግን ያንተ ወገኖች
 እንደ ሆንን እናውቃለን።“ መጽሐፈ ጥበብ ፲፭ ቁጥር ከ፩ እስከ ፪
ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
20.03.2019
ከእመ ዝምታ - ሲዊዘርላንድ።

·       ከውስጥ ስለማዬት።

የእኛ ነገር እንዲህ ነው ተሰበሰበ ሲባል መበተን፤ ተበተነ ሲባል መሰብሰብ። ተቃና ሲባል መጉበጥ፤ ጎበጠ ሲባል ደግሞ መቃናት፤ ፈሰስ ሲባል መቀም፤ ተለቀመ ሲባል መፍሰስ እኛ እንዲህ ነን።

በቀለ ሲባል መድረቅ፤ ደረቀ ሲባል ማጨብጨብ፤ ሞላ ሲባል መጉደል ጎደለ ሲባል መሙላት፤ ሞላ ሲባል መፍሰስ፤ ፈሰሰ ሲባል ክው ብሎ መድረቅ ዕጣ ፈንታችን ይኸው ነው።

ሰሞኑን አንድ ዜና አዳመጥኩኝ። ሳዳምጠውም ደነገጥኩኝ። ጋደም ብዬ ስለነበር ቀና አልኩኝ እና በማስተዋል ዜናውንም ሀተታውን አዳመጥኩኝ አቅራቢው ጋዜጠኛ ሄኖክ አለማዬሁ ነበር። የሰማሁት ከዘሃበሻ ኦፊሻል ድህረ ገጽ ላይ ነበር። በምልሰት ደግሜ አዳመጥኩት። ድንጋጤዬ አብሮኝ ቆዬ።

በዚህ ወቅት ይህ ይሆናል ብዬ አልገመትኩም ነበር። የእውነት። አቶ ነዓምን ዘለቀ ከግንቦት 7 ራሳቸውን ማግለላቸው ነበር ዜናው። ዜናው ከዘሃበሻ ስለገኘሁት አልተጠራጠርኩትም። ግን በጹሑፍ የሰፈረ አግኝቼ እስክመረምረው ተግ አልኩኝ።

ትናንት ሚዲያዎች ላይ ጎልቶ የወጣ የውይይት አጀንዳ ይሆናል ብዬ አስቤ ነበር። አብሶ በደከሙለት ሚዲያ በኢሳት ከዜና በስተቀር እንደ አቶ ዛዲግ አብርሐ ያህል እንኳን ቁብ አልተሰጠውም ወይንም ክብር አልተሰጠውም ወይንም አጀንዳ የመሆን አቅም አልነበረውም። ጉዳዩ ከግንቦት 7 ቀጣይ አዲስ ፓርቲ ምሥረታ ትልም ጋር በውል ተንታኞቹ ሊሄዱበት ይገባ ነበር። ድህረ ገፆችንም  ዛሬ ነው ያዬሁዋቸው። 

ፕሮ ግንቦት 7 ድህረ ገፆች ከዛ ዝርዝሩን አገኛለሁ ስል ጭራሹን አልዘገቡትም። ከእነሱ አገኛለሁ ብዬ ነበር ሙለውን መንፈስ ጎራ ያልኩት። ጹሑፉን በጥሞና ማንበብ ከምንም ነገር በላይ መልካም ስለሆነ። ሞትም ቢሆን ይኸው ነው የእኛ ነገር ስናገለግል ብቻ ነው ሰው ሆነን እምንታዬው፤ ያ ከቀረ አሮጌ አከፋነት ነው። በቃ መወርውር። ብቻ ለምን አልተዘገበም ብዬ ራሴን ጠይቄ ወደ ሳተናው ስዘልቅ ከዛ ሙሉውን አገኘሁት። እናም በጥሞና አነበብኩት። አንክን የለውም። ድርጅታቸውን ያከበረ ስሜት ነው ያለው። 

የሳቸውን መልቀቂያ እያነበብኩኝ ሌላ የቀደመ ጉዳይ ትዝ አለኝ።  ኮ/ ጎሹ ወልዴ መንግሥታቸውን እና ፓርቲያቸውን ሲለቁ በአሜሪካ ድምጽ ይመስለኛል ከተሳሳትኩ እታረማለሁ እጅግ አክብሮቱ ሙሉ የሆነ ቃለ ምልልስ ነበር ያደረጉት።

 ኮ/መንግሥቱ ሃይለማርያምን ትህትናው ሙሉ በሆነ አክብሮት ነበር የገለፆዋቸው። ይህ ሲመዘን እኒህ የአገር ፈርጥ የሆኑ ምርጥ ኮነሬል በዚህ በሰጡት አክብሮት ያላቸው የሙሉ ሰውነት ሰብዕና ጎልቶ ታዬኝ።

እርግጥ ነው በልጅነቴ ኮ/አሰፋ ሞሶሲ እሳቸውን ያስጠኑኝ ነበር ቀድመው አገር ውስጥ እያሉ። በዛ በወጣትነት ቀንበጥ ዕድሜዬ ከሳቸው ቃለ ምልልስ የተረዳሁት በተጨማሪነት የኢትዮጵያን ህዝብ እና አገራቸውን በሚመለከት ምን ያህል አንደሚያከብሩ አሰተዋልኩኝ። የአገር መሪ መሆን ይችላሉ የሚል እምነትም አደረበኝ። ለዚህ ነበር ጠ/ሚር አብይ አህመድን አማካሪያቸው እንዲያደርጓቸው በተከታታይ በትህትና ያሳሰብኩት፤፡፡

አሁን የአቶ ነአምን ዘለቀ የመልቀቂያ ደብዳቤም ከዚያ ጋር ተመሳሰለብኝ። እናም እጅግ አድርጌ አከበርኳቸው። ከዚህ ጋር አቶ ዘመነ ካሴም መሰሉን ነበር የፈጸመው። በቃለ ምልልሶቹ ሁሉ ለቀጣዩ አብሮነታችን ይል ነበር። ይህ ጨዋነት ነው።

በሌላ በኩል ለህሊና ማደር እና የድርጅት ዲስፕሊን ሲፋጠጡ ራስን የሚሞግቱ ጉዳዮች ይኖራሉ። መልቀቅ ከባድ ነገር ነው። አብሶ የድርጅቱ አባልም ከፍተኛ አመራር አካልም ሲኮን ደግሞ ፈተናው ከባድ ነው። እኔ እራሴ አማራ ነኝ ብዬ ለመውጣት እጅግ ፈተና ነበርብኝ። እንደዛ ሽንጤን ገትሬ እከራከርለት የነበረውን ግንቦት 7 ሞግቼ ለመውጣትም ያን ያህል ፈትኖኛል።

አስቀድሜ ግንቦት 7 ሊድን የሚችልበትን የራሴን ምልከታ በወጉ አቅርቤም ነበር። ለዛውም እኔ የድርጅቱ አባል አይደለሁም። እኔ የድርጅቱ ደጋፊ አይደለሁም። ግን አብዝቼ እሱን ጠል በሆኑ መንፈሶች ዙሪያ ገብቼ እማገድለት ነበር። እሱ ከጉዳይ ባይጥፈውም። ዘገባዎቹንም በጥሞና እሰራለት ነበር። 

ከአማራ ተጋድሎ ጋር በተያያዘ ግድፈቶች እያየሉ ሲመጡ ወጥቼ ለመሞገት ሁሉ በጥንቃቄ ነበር ሃሳቤን እማቀርበው፤ ለጠላት ጎራ ስንቅ ሃሳቤ እንዳይሆን። አንድ የአገሬ የተስፋ ማስፈጸሚያ ጥግ ለመንፈሴ አድርጌ አዬው ስለነበር በጠላት ጎራ የሚፈጥረው አታሞ ጋር  እያሰብኩ ብዙ በጣም ብዙ ታገስኩኝ። ግን ሰሚ አልነበረም።

ዛሬ በፊት ቀደምትነት ሠራዊቱን አሰልፎ አትንኩት ለሚልለት ለአብይ ሌጋሲ ቢሆን እኔ ነበርኩኝ ደፍሬ እራሱን ግንቦት 7 የሞገትኩት። መጨረሻው አማራ አላማረም ለዛሬው መተንፈሻ ግን የዛን ጊዜው የቅኖች ተጋድሎ ነበር ለራሱ ለግንቦት ግንቦት 7 መተንፈሻ የሆነው።

እንሆ ዛሬ ከማይችለው፤ ከማያዘልቀው፤ ከሰለቸውም ትብትብ መንገድ ወጥቶ ትንሽ ስልት ቀዬርኩ ለማለት የቻለው ያ  ለውጥ መንፈስ ተጋድሎ ቀጣይነት አቅም በማዋጣት የተደረገው ተጋድሎ ነበር የነፍስ ወከፍ ተጋድሎ ነው።

በሌላ በኩል በፖለቲካ ብስለት አንጻርም ሲታይ ያሰደመበት ያ በጽኑ የታገለው የአማራ የህልውና ተጋድሎ እውቅና አለመስጠት እንሆ ዛሬ በአንድ እግሩ በተንጠለጠለው መታበይ ሥር ሁሉም እንዲወድቅ አድርጎታል። ሲነግሩት የማይሰማ ድርጅት ቢኖር ግንቦት 7 ነበር። የአሁኑን አላውቅም የሚነገረውን ያዳምጥ አያዳመጥ።

 መሬት ላይ ያለው እሱ ስለሆነ ህዝብ እና እሱ፤ ሊሂቃኑ እና እሱ፤ ኢህአዴግ እና እሱ፤ ተፎካካሪ፤ ተቀናቃኝ፤ ተቃዋሚ ከሚባሉት ጋር በሞገድ ሳይሆን ፊት ለፊት ገጥ ለገጥ ስላለ ያው ይተያያሉ። ሌሎች የቀለም ሊሂቃኖች ማዶ ለማዶ ስላልሆኑ እዛው ለዛው ይፈታተሹ።

የሆነ ሆኖ ትልቅ ዓለም አቀፍ ዜና ነው የአቶ ነአምን ዘለቀ ከግንቦት 7 ራስን ማግለል። አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ለግንቦት 7 ህሊናው ናቸው። አቶ ነአምን ዘለቀ ደግሞ የጀርባ አጥንቱ ነበሩ። 

ብዙም የራሳቸው መንፈሶች ስላሉ ከሳቸው ራስ ማግለል ጋር ብዙ ንደት ይኖራል።
ብዙ የመንፈስ ሽፍትነት ይኖራል። ዲሲ፤ ፍራንከፈርት፤ ለንደን የነበሩ የግንቦት መንፈሶች ከዚህ መንፈስ ጋር በቅርበት የተሳሰሩ ናቸው በሥጋም በደምም። 

ስለዚህ አንድ ሳር እንደተመዘዘ፤ እንደ ተራ ነገር አድርጎ ማዬት አይቻልም። ትልቅ የፖለቲካም ሰው ናቸው። አይከን ናቸው። አቃሎ ማዬትም አይቻልም። የኮ/ጎሹ ወልዴ ራሳቸውን ማግለል ብዙ ዋጋ አስከፍሏል። ለዚህ ሁሉ መከራም የዳረገን ይኸው ጉዳይ ነበር። ማድመጥ አለመቻል። ግንቦት 7 እሳቸውን ማጣቱ ተጎድቷል። ልምዱም፤ ተመክሮውም እንዲህ መሆኑ ...?

ራሱ ድርጅቱን በቀጣይ አዲሱ ሥሙ ተስፋ የሚያደርጉ ነፍሶች ጥግ ያጣሉ እንዲህ የመሰለ የፖለቲካ ውሳኔ በከፍተኛው አመራር አካል ሲከሰት። በዚህ ላይ የተከፈለው መስዋዕትነት እና ድካምም ቀላል አይደለም ለድርጅቱ። ፊት ለፊት መውጣትን እንደ ጀብዱ ማዬት የማይሹ በዬመድረኩ ብዙ መዋለ መንፈስ ያፈሰሱለት እጅግ ድንቅ የነፃነት ታጋዮች ነበሩት ግንቦት 7። ኑራቸውን ሁሉ የገበሩ።

የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ መታሰርን መከራ ግንቦት 7 የተሸከመው በአቶ ነአምን ዘለቀ ላይ እንደነበር አስባለሁኝ። እሳቸው ባይኖሩ ኖሮ እውር ነበር የሚሆን ድርጅቱ። አቶ ነአምን ዘለቀ መጽናኛው ነበሩ። ደጋፊው ነበሩ። ለወቅቱም ጥቃት አውጥተዋል።  

ጋዜጠኛ አበበ ገላውም ቢሆን በዛ በጥቃት ወቅት አለሁኝ እኔ ብሎ መቀላቀሉም ሌላው ቀለማም አመክንዮ ነበር። ስላለፈ ሊረሳ አይገባም። ይህ ሁሉ ለነፃነት የተከፈለ የመንፈስ ተጋድሎ የታሪካችን ክፍለ አካል ነው በወጉ ሊያዝ፤ በወጉ ሊዘከር ይገባል። 

የእነሱ ድር እና ማግ መሆን ድርጅቱ የገጠመውን ፈተና አልፎ ዛሬ እንደሌሎቹ ለመታዬት ያበቃው ይህ መደጋገፍ ነበር። አለ መባሉ በራሱ ትርፍ ነውና። እኔ እንደማስበው አሁን ባለው ሁኔታ ገዢውን ግንባር የኢህአዴግ ግንባርን ጨምሮ ሁሉም በተመሳሳይ አቅም እና ሁኔታ ላይ ነው የሚገኙት። የሚበልጥም የሚያንስም የለም። እኔ ሳስበው እና ስገምተው። ስለዚህ ቢጠነክር ተፎካካሪ ሆኖ መውጣት ይቻለው ነበር። 

አሁን ጠንክሮ የወጣ ድርጅት አለ አብን። እሱም ቢሆን የኢትዮጵያ የሴራ ፖለቲካ ገብቶ ይበትነዋል። ለዛውም ግንቦት 7 ጥርስ የገባ ድርጅት ነው። ለዚህ የተፈጠሩ ማህንዲሶች አሉ ለመበተን፤ ለመተርትር። ልክ እንደ ሰማያዊ ፓርቲ ይተረትሩታል። ባህሉ የለንም አንዱ ሲበረታ መደገፍ፤ ማበረታት ወይንም ከሴራ እና ከሸር መታቀብ። ለዚህች ለአላዛሯ ኢትዮጵያ እንባ ሲባል ብሎ የሚያስብ የለም። 

 ማዝለቅ ሳይሆን መቅጨት ነው መደበኛ ተግባራቸው የፖለቲካ ድርጅት ሊሂቃን። የራሳችን ሲያር መሰሉ እንዲፈጽም ደግሞ ሌላ ማማሰል ከዛ የተንጠባጠበው ተጠራቅሞ ደግሞ እንደገና ማገገም፤ መልሶ ደግሞ መናድ … ከቶ ምን ያሻለናል? ከቶስ ከዬትኛው ጠበል ብንጠመቅ ይሻለን ይሆን?

የሆነ ሆኖ ድርጅቱ ራሱ ግንቦት 7 እንደ አውራ ፓርቲነቱ ለእኒህ ቅን አገልጋዩ  የእናመሰግናለን ደብዳቤ ሊሰጣቸው ይገባል። ወርጅብኙን አብረው ታገፍጠዋልና። መከራውን አብረው ታገርተዋልና። ግድፈቱንም አብረው ቤተኛ ሆነው ሸፍነውለታል እና። አብሶ በዚያ በክፉ ቀን ህሊናው ለህወሃት የበቀል ማወራራጀ ሲሆን ግንቦት 7 የእነዚህ የነፃነት አርበኞች ከጎኑ መሰለፍ ማዕረግ ሞገስ ነበርው። ዕድሜን የቀጠለ መንፈስ ነበር። 

ሰው ለሰው ልብሱ ጌጡ ማዕረጉ ነውና። ሚዲያው ኢሳትም ቢሆን የተገባውን ክብር ሰጥቶ ሊዘክራቸው ይገባል ባይ ነኝ። ትውልድ የሚማረው እንዲህ መሬት ላይ በሚሠሩ ተግባራት ብቻ ነው። መሆን መቻል። ዴሞክራሲም እንዲህ የሞገተህን መንፈስ አቅርበህ ስትሞግተው ከእሱ ለማመርም ስትፈቅድ ነው። ለነገሩ ፍሬም ላይ የግድግዳ ጌጥ ነው ዴሞክራሲ ... 

በሌላ በኩል ይህን መሰል አደብ መግዛት፤ ይህን መሰል በመቻል ውስጥ መስከን ነገ ደግሞ እኒህ ሰው በሌላ ተልዕኮ ድርጅቱን ግንቦት 7 ሊረዱ የሚችሉበት የታሪክ አጋጣሚ ሊኖር ይችላል። አሁን ሰሞኑን አቶ ታማኝ በዬነ እና አቶ አበበ ገላው ቃለ ምልልስ ሲደራረጉ አይቻለሁኝ ፓስተሩን ማለት ነው። የማድመጥ ፈቃዱ ስለሌለኝ።  

በግንቦት 7 ሚዲያ ያ ባይሆን እንኳን እስከዛሬ ላደረጉት መልካም ነገር ሁሉ ድርጅታቸው ግንቦት 7፤ የግንቦት 7 አባላት እና ደጋፊዎች ውድ ወንድማቸው ከወል ማዕዳቸው ስለተለዩ ቅያሜ ሊገባቸው አይገባም። ይልቁንም ለከፈሉት መስዋዕትንት አክብሮትም፤ አድናቆትም ሊሰጧቸው ይገባል። ያ እንደላፈው ሁሉ ይህም ያልፋልና …

አንድ የፖለቲካ ሊሂቅ በቃኝ ማለት እኮ መልካም ነገር ነው። ፖለቲካ አድካሚ ነው፤ ብዙ ማህበራዊ ህይወት ነው የሚያመሳቅለው። ሰብዕናን ሁሉ ይለውጣል። ለቆ መውጣት በእኛ የፖለቲካ ባህል ይህ የማርያም ጠላትነት ነው እንጂ ይህ እኮ ተፈጥሯዊ ነው ራስን ማግለል ሆነ ማቀብ።  

የሰው ልጅ በሁሉ ነገር አይስማም። ያማ ቢሆን ይህን መሽቶ በነጋ ቁጥር ተጋቡ በሚለው ዜና ልክ ተለያዩ የሚለውም እኩል ቤተኛ ባልሆነ ነበር። አብሮ መኖር፤ አብሮ መሥራት እንዳለ ሁሉ መለያዬትም ይኖራል።

ሌላው ቁሞ የሚጠብቅ አምክንዮ የለም። ትናንት ግንቦት 7 ፖሊሲ አልነበረውም። እንዲያውም ቢኖረው ኖሮ ቀድሞውንም ይህን ያህል አቅም ኖሮት ሊዘልቅ አይችልም ነበር። ወደፊት ግን ይኖረዋል። መሹለኪያው ስለሌለ። ፖሊሲ ሲኖረው ደግሞ የሚለዩት ይኖራሉ።

ህይወት አዟሪት ናት። ይህ የመልቀቂያ ደብዳቤም እንዲህ ነው መታዬት የሚገባው። አቅም ስለሳሳ ደስታ የሚሰጥ አይደለም። እውን ስለ ነፃነት የምናስብ ከሆነ። ደካማን ነገር የሚደግፍ ሃይል ሲነጠል የበለጠ መድከም ነው እንጂ አይጠነክርም። ግንቦት 7 ትልቅ ሰው ነው ያጣው።

የአንዱ መፈረስ፤ የአንዱ መዳከም ዙሮ ዙሮ በቀጥታም ይሆን በተዘዋዋሪ ማግስትን ይጎዳል። ስለዚህ እንዲህ መሰሉን ነገር እንደ ድል የሚቆጥሩ ሳደምጥ ይገርመኛል። መሰብሰብ እንጂ መበተን ምን ያስደስታል?  

በሌላ በኩል ግን ድርጅቱ ቁጭ ብሎ ራሱን መገምገም ያለበት ይመሰለኛል። ምክንያቱም ኢህአፓ፤ ቀስተ ዳመና፤ ቅንጅት፤ ኢትዮጵያ አርበኞች ግንባር፤ ቲፒዴኤም፤ እንደተጠጋው ነው የተናደው፤ አገራዊ ንቅናቄ፤ ሰማያዊ ሁሉም አለሰከኑም። መናድ፤ መፍረስ፤ መሰንጠቅ፤ የስንብት አደጋ ነው የሚገጥመው መንፈሱ ግንቦት 7 የፈጠረው። 

ስለዚህ ችግሩ ከማን ነው? ችግሩ ከዬት ነው? ከአዬሩ ወይንስ ከሥሪቱ? ወይንስ ከአቅም ማነስ? ወይንስ ፍላጎት እና ሁኔታ ካለመግጠም? ይህን ቁጭ ብሎ ማጥናት ይገባዋል ግንቦት 7። አዲሱ ፓርቲው ደግሞ ተመስርቶ አህዱ ሲል ያው መሰሉ ዕጣ ፈንታ እንዳይከሰት … አመሰራረቱ ላይ፤ አመራር አወቃቀሩ ላይ ማተኮር … የተገባ ነው። 

አንድን የፖለቲካ ድርጅት ወቅትን በተጠለሉ ሃሳቦች ብቻ ማንጠልጠል አያዛልቅም አገርን። በተጨማሪም ዕድልም፤ ቅባዕም፤ ስኬትም አለ … እነዚህንም ቀረብ እድርጎ መመርምር ያስፍልጋል። ፈጣሪ ያለፈገው ነገር አለ ብሎም ማሰብ ይገባል። ድካሙም፤ ልፋቱም፤ ተነሳሽነቱም እያለ ግን ስለምን ይሆን መበርከት ያልተቻለው?

እንዲሁም ዘመን የሚሰለቸው ነገር እንዳለም ማሰብ ያስፈልጋል። ምክንያቱም የሚጨንቀን በዚህ ሁሉ ማህል የትወልድ ብክነት ስላለ ነው። የትውልድ አለመበርከት ደግሞ ከታሪክም አንጻር ሲሰላ ካሳ የሚያስጠይቅ ነው። በእኛ ደግሞ አይደለም ካሳ ይቅርታ መጠዬቅም የእግዜር ደጅ ነው።

ነገ ሲታሰብ ዛሬን ለመመሰረት የትናንት ግድፈትን አጥርቶ መሆን ይኖርበታል። አሁን ተሰሞኑ መግለጫዎች ቃለ ምልልሶች፤ ንግግሮች ታሰረው የተፈቱ ይመሰል ከእስክንድር ንቅናቄ ጋር የፉክክር የሚመስል በግንቦት 7 በኩል በርከት ብለው አዳምጫለሁኝ።

ሁሎችንም አዳምጥኩኝ፤ አነበብኩኝ። ያልተያያዙ እና ያልተዋህዱ ናቸው። ግን ታቅደው የተከወኑ ናቸው። ግንቦት 7 የተጣለበት ተሰፋ ለመወጣት ሁኔታዎች አጣብቂኝ ውስጥ ሰለከተተው ይመስለኛል እንዲህ ወጥ ያለሆኑ ማህል ላይ የሚገትሩ ጉዳዮችን እንዲያስተላልፍ የተገደደው። አንዱ አቅጣጫ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ የተለዬ አቋም ይዘው አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ወጥተዋል።

ሌላው የድርጅቱ ጭንቅላት ደግሞ ማህል ላይ ነው ያለው። ችግሩ ይገባኛል። ሁሉንም ለማስደስት አይነት ይመስላል። „ሁለት አግር አለኝ ብሎ በአንድ ጊዜ ከሁለት ዛፍ መውጣት አይቻልም።“ ወይ ጠቅልሎ የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌን አቋም መያዝ ወይ ደግሞ የድርጅቱን አስኳል አቋም መያዝ። 

ሁለት ወዶ አይሆንም፤ ሁልጊዜ ይህን መንገድ በመከተል ስኬት አልተገኘም። ከአገራዊ ንቅናቄው መማር ይኖርበት ነበር ግንቦት 7። ኦነግን ላለመስከፋት ብዙ በጣም ብዙ መንፈሶችን በውዟል።

ምን ያህል የኢትዮጵያ የቀደመ ታሪክ እና ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማችን ተገፍተው እንደነበር እናውቃለን። ለዛውም ምስጋና ለሌለው። መጨረሻ ደግሞ ያ አይደረስብን የተባለ ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማ መለያ እንዲሆን ተደረገ። እኛም አብዝተን ታዘብን። 

አሁን ደግሞ በዛ ጸንቶ መሞገት ሲገባ የሚታዬውን እዬታዬ ነው … ማህል መንገድ አውላላ ሜዳ ላይ ነው የሚያስቀረው። አቋም ውሳኔ ጥሩ ነገር ነው ለአንድ ድርጅት። ለአዲስ ስልት እና ስትራቴጅ ሁለት መንገድ እከተላለሁ ብሎ ተስፋን ማማሰን የተገባ አይደለም። አንድ የቆረጠ ሌላ ማህል መንገድ ላይ ዬተከለ? ? ? እንዲህ በጥያቄ ምልክት ይዥጎርጎር …

የሆነ ሆኖ ያ የሆነው ግንቦት 7 ተስፋ ለሚያደርጉ አባልና ደጋፊዎቹ ሲባል እንጂ ድርጅቱ ግንቦት 7 እንደ ድርጅት የሚያስበው ፓለቲካዊ አቋም ምን እንደሆነ ማንም የፈለገውን ያህል ቢቆፍር አያገኛትም። የተዘጋ ነገር ነው። በብረት ሳጥን የተቆለፈበት ነው። 

ለዚህ እኮ ነው ፖሊሲ አልቦሽ ድርጅት ነኝ ብሎ ይህን ያህል መድረክ ላይ የቆዬው። ፓሊሲ ሳይኖረው የፖለቲካ ንቅናቄ ሆኖ በመኖር እረገድ እኔ በታሪክ ግንቦት 7 ብቻ ይመስለኛል። አንድ አባል እና አካል የሚሆን ነፍስም ይህን ሳያረጋግጥ መቀላቀል ከባድ ነው። በጨለማ መጓዝ ማለት ነውና። ጅሎቹም ደማቸውን ገብረውለታል። 

ይህ ዓይነት የፖለቲካ መንገድ እና ግልጽነት እና ሃላፊነት ግድፈት ሲታሰብ አፍታቶ ውስጥን ለማግኘት ከባድ ነው። እንደ አገርም ለኢትዮጵያ እንደ ህዝብም ለኢትዮጵውያን ግልጽነት የሌለው ሰብዕና መፍቻ የለሽ ነው። ድፍን ቅል ካልተከፈተ አያገለግልም፤ ዱባም ተክፍቶ በወጉ ካልተሰናዳ ለምግብ አይውልም። ጤፍ ከገለባው ካልተለዬ እህል ሆኖ ነፍስ ማትረፍ አይቻልም።

ሌላው ግን በዚህ በድፍን ጉዞ በዬዘመኑ የሚባክነው የሰው ነፍስ ደግሞ፤ የሚደቀው የተሰፋ ተፈጥሮ፤ የሚቃጠለው ጊዜ እና የሚያመልጠው ዕድል ሁሉ ታስቦ ግልጽነትን መርህ ማድረግ ከአንድ የፖለቲካ ድርጅት የሚጠበቅ ይመስለኛል። አገር እና ህዝብ እመራለሁ ከተባለ።   

የአመራር፤ የስልት ብቃት እና ቀድሞ የማዬት አቅም፤ የራስን የጥረት ውጤት ብቻ የእኔ የማለት እና በራስ ውስጥ ሰክኖ በቅሎ ጸድቆ የማስበል ጉዳይም ሌላው መሰረታዊ ነገር ነው። ከሞቀ ምጣድ የበለጠ ከደመቀ መቃጠል፤ ከቀዘቀዘ ደግሞ መብረድ ሆኖ ጥግም ተስፋም ያሳጣል።

አገር እንደ ጥንቸል በዬዘመኑ መሞከርያ መሆንም የለባትም። እንደ ዜጋም እኔ ያሳስበኛል። የግንቦት 7 መነሻ እና መደራሻ ማሳዬ የሚለው የተፈጠርኩበት እትብቴ ስለሆነ፤ የጎንደር እናቶች ሁልጊዜ የልጅ ስንቅ ማቀበላቸውን ሰከን ብለው ቢያስቡበት የሚገባ ይመስለኛል። ነገም ስንቅ አቅራቢዎች እነሱው ናቸውና።

ሌላ እኔ ያዬሁት ግጭት ነው። ሁልጊዜ አቅም ሆኖ የሚወጣ መንፈስ የወል ይሁን የግል መዳፍ ሥር ካልወደቀ ግጭት ነው። ባህሉ ነው የግንቦት 7 ነፍስ ጋር መጋጨት። ነፍስ ያለው ሆኖ አቅም ያለው ሆኖ ለግለግ ብሎ የወጣ መንፈስ ሁልጊዜ ከግንቦት 7 ጋር ግጭት ይጠብቃዋል።

አሁን ትናንት ከተፈጠረው ከአብን ጋር እራሱ ይገርመኛል። ምዕራቡ አለም ኢትዮጵያን ይመራል ብሎ ሲኮተኩተው የነበረ ድርጅት ከልጅ ልጁ ልጁ ከሚሆን እንቡጥ ጋር ገና በጥዋቱ ነው ሄዶ የተላተመው። አሁን ጉራጌ ድርጅት እንደተመሰረተ አዳምጫለሁኝ፤ ጋሞም ሰሞኑን ሰምቻለሁኝ ችግር የለባቸውም እንሱ። ያው ለቅልቅል እዬተሰናዱ ሊሆንም ይችላል።

ግንቦት 7 የሚጸዬፈውን የአማራ መንፈስ አለበት ብሎ የሚያስበውን አቅም ግን በቃ እንደ ውቃቤ ሄዶ ከበላዩ ላይ ነው የሚሰፍርበት … ይህን ደጋፊዎችም አክባሪዎችም አባሎቹም ከልባቸው ሆነው ሊመረምሩት የሚገባ አብይ ጉዳይ ይመስለኛል። የሠራዊቱ አባላት የሌላ ብሄረሰብ አባላት ሆነው ቢሆኑ ኑሮ ባለቤት ይኖራቸው ነበር። እንዲህ በጭነት መኪና ተጭነው የትሜና አይበተኑም ነበር …

ከዬትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ጋር ተፎካከሮ ተወዳድሮ ቢያሸንፍ መንግሥት ቢሆን እነዛም ዜጎቼ ናቸው ብሎ ማሰብ ካልቻለ ወደፊትም ጋዳ ነው። ባላንጣ በዬጊዜው መፍጠር አይገባም። ብሄራዊነት ሁሉን አቃፊነት ነውና።

በሌላ በኩል አማራ ግዴታ የለበትም የዬትኛውም መንፈስ ፍላጎት የመሸከም። አማራ ብቻ ለጥ ሰጥ ይበል ፈጽሞ ለዚህ ትውልድ አይሆንም። አይመጥንም። ነጥሮ ነው የሚመለሰው። 

ሃሳብን አቅርቦ ሞግቶ ተሟግቶ በማሳው ማሸነፍ እና መሸነፍ ነው። አስቀድሞ አቅም ፈርቶ መጀመር ለድልም አያበቃም። የፈለገ በፈለገው መልክ ይደራጅ። የፈለገው በፈለገው መልክ ይሰባሰብ። አቅሙ ከኖረ እኮ ጥወራ ጥመናም የሚያስኬድ ነገር አይኖርም። ስለሆነም ግንቦት 7 ራሱን ችሎ መቆምን ፊደል መቁጠር ይኖርበታል …

·       ክወና።

አዲስ መፍጠር ቀርቶ የቀደመውን ማቆዬት እንኳን ለማንችል እኛም መሰል ስለ ነገ ትውልድ ሰክኖ ማሰብ ያሰፈልጋል፤ ማህበር፤ ድርጅት፤ ተቋማትን ስንፈጠር። አቅሙ ከሌላ አለመሞኮር። እንዲህ በዬፌርማታው መናድ ... 

ገናና ሥም ድል አይሆንም፤ ገናና ሥምም ስኬት አይሆንም። ገናና ሥምም ተግባርን አያመነጭም። ድልም፤ ስኬትም ጥረት ነው። ስኬትም ካልተገኜ ሁልጊዜ በዬዘመኑ ትውልድን ከማባከን በቃኝ ማለት የተገባ ነው ልክ እንደ አቶ ነአምን ዘለቀ። ስለሆነም ለህሊና አድሮ ለተጨማሪ የትውልድ ብክነት ተጠያቂ ላለመሆን አቶ ነአምን ዘለቀ የወሰዱት እርምጃ አስተማሪ ነው። ተቋምም ነው።

ከፓርቲ ራስን ማግለል ግን የተለመደ መሆኑ ደግሞ ግምት ውስጥ ሊገባ ይገባዋል። በክፉ ዓይንም ሊታይ አይገባውም። ሊወገዝም አይገባም። ሊገለልም አይገባም። አብሮ መኖር እንዳለ ሁሉ መለያዬትም መኖሩን ሂደት ነውና በነጻ እና በጸዳ ህሊና መቀበል ይገባል። ሌላው ወሳኝ ጉዳይ ግን ክፍት ቦታ መተው ያስፈልጋል በህሊና ውስጥ። ምክንያቱም ነገ ደግሞ ዙሮ መገናኘት አይቀሬ ነውና።

እውነት የሚታዬው የሰው ልጅ በራሱ ላይ ሲደርስ ብቻ ነው። እውነት አለኝ የሚለውም  በእሱ ውስጥ ያለው እውነት ዘመድ እስኪያገኝለት ድረስ መታገስ ግድ ይለዋል። ስለዚህ እውነት ላለው እውነቱ ለሱ የህሊና ስንቁ እና ተስፋው ስለሆነ እዬባዊነትን መሰነቅ ትንፋሹ ሊያደርገው ይገባል።

ጋዜጠኛ አበበ ገላው በነአምን ዘለቀ መልቀቂያ ላይ (አበበ ገላው)
March 19, 2019
አቶ ነዓምን ዘለቀ በገዛ ፈቃዳቸው ራሳቸውን ከድርጀቱ አገለሉ
March 19, 2019
ለአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ አባላት፣ የሰራዊት አባላት፣ ደጋፊዎችና፣ በልዩ ልዩ መደረኮች ለምታውቁኝ ኢትዮጵያውያን በሙሉ
March 18, 2019

"የሠራዊቱ ሁኔታ ከፍተኛ የህሊና መረበሽ ውስጥ ከቶኛል" አቶ ነአምን ዘለቀ

ኢትዮጵያዊነት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር ነው!

የኔዎቹ ኑሩልኝ።
መሸቢያ ጊዜ።


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።